ዋለልኝ አየለ
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2006 ዓ.ም ስለዓድዋ በተደረገ ውይይት ላይ የሰማሁት ነው።የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅራቢው አንድ ገጠመኝ ተናገሩ።ነገሩ የሆነው ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነው።ሰዎች በአንድ የወንዝ ዳርቻ ላይ ቁጭ ብለው ይዝናናሉ።ወንዙ ብዙም የመዋኛ ወንዝ አልነበረም።
በድንገት ግን ከዚህ ወንዝ ውስጥ አንድ ጥቁር ሲዋኝ ታየ።ሰዎችም ‹‹ምን አይነት ሰው ነው!›› በሚል ተገረሙ።ከመካከላቸው አንደኛው ‹‹ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት›› አለ።‹‹በምን አወቅክ?›› እያሉ ተከራከሩት።‹‹እንዲህ አይነት ድፍረት የእነርሱ ነው›› አለ።ከክርክር በኋላ የዚያን ሰው ማንነት ማወቅ ፈለጉ።ጠየቁትም።አዎ! ያ ደፋር ኢትዮጵያዊ ነበር!
በየትኛዋ የአፍሪካ አገር እንደሆነ ባላስታውስም ሌላም የሰማሁት የአንድ ኢትዮጵያዊ ታሪክ አለ።አንድ ጥቁርና ነጭ ይጣላሉ።ጥቁሩ ነጩን ደበደበው።ይህን የተመለከተ አንድ ጥቁር ለነጩ አግዞ ‹‹እንዴት ነጭ ትደበድባለህ›› ብሎ የራሱን ወገን ጥቁሩን ደበደበ።ይህን የተመለከተ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ‹‹እንዴት ለነጩ ትወግናለህ!›› ብሎ ጥቁሩን ደበደበው።
እዚህ ላይ እንግዲህ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ታሪክ መጥቀስ የግድ ይለናል።በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር መስፍን በልጅነታቸውና በወጣትነታቸው ሞገደኛ እንደነበሩ ቃለ መጠይቅ በተደረጉባቸው መገናኛ ብዙኃን በራሳቸው አንደበት ተናግረዋል።ይህኛው ገጠመኛቸው ግን ከላይ የጠቀስናቸውን አጋጣሚዎች ያረጋግጥልናል።በራሳቸው አንደበት እንዲህ ብለዋል፡፡
‹‹…ኬንያ ናይሮቢ አንዲት መዝናኛ ቤት ተገኝቼ እየተዝናናሁ ነው። ቤቱ እንደ ፓርቲ ቤት ያለ ነው። ባንዱ ጥግ መጠጤን ይዤ፣ የዳንሱ ወለል ላይ ጥንድ ጥንድ ሆነው የሚደንሱ ወጣቶችን አያለሁ። በዚህ መሃል የባሕር ኃይል የደንብ ልብስ የለበሱ እንግሊዛዊያን ነጮች ገቡ። አንዱ እንግሊዛዊ ቀጥታ ወደ ዳንስ ወለሉ ሄደና ከወዳጁ ጋር እየደነሰ ያለውን ኬንያዊ በካልቾ መታው።
ኬንያዊው ተርበድብዶ የሴት ወዳጁን ጥሎ ገሸሽ አለ። እንግሊዛዊውም ከዛች ኬንያዊት ጋር መደነስ ጀመረ። በእንግሊዛዊው ድርጊት በጣም ተናደድኩ። ከመቀመጫዬ ተስፈንጥሬ ተነሳሁና ወደ ዳንስ ወለሉ አመራሁ።
እኔም እንግሊዛዊውን በካልቾ ጠልዤ ኬንያዊቷን ተቀበልኩ። ጥቂት ካስደነስኳትም በኋላ ለተቀማው ኬንያዊ አስረከብኩ። ይህን ፈፅሜ ወደ መቀመጫዬ ሳመራ እንግሊዛዊው የጠየቀኝ አንድ ጥያቄ ነበር ‹ኢትዮጵያዊ ነህ? የሚል››
ያ እንግሊዛዊ ምንም ግርግር መፍጠር አልፈለገም ማለት ነው።በቃ ሰውየው ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ሲያረጋግጥ አርፎ ተቀመጠ ማለት ነው።የኢትዮጵያን ታሪክ ያውቃል ማለት ነው።
የኩባ ፕሬዚዳንት የነበሩትን የፊደል ካስትሮን ንግግር እንጨምርና ወደ ዋናው የዓድዋ ጉዳይ እንገባለን።በአንድ ወቅት አንዲት ጣሊያናዊት ጋዜጠኛ የኩባውን መሪ ፊደል ካስትሮ ቃለ መጠይቅ አደረገች።በቃለ መጠይቁም የኢትዮጵያና ሶማሊያን ጦርነት አነሳች።
ጣሊያናዊቷ ጋዜጠኛ፡- በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገው ጦርነት ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር አጋር ሆና ተሰልፋ ነበር?
ፊደል ካስትሮ፡- አዎ! እንደማንኛውም ወዳጅና ወንድም ሀገር በተወሰነ መልኩ አግዘናቸዋል።
ጣሊያናዊቷ ጋዜጠኛ፡- በተወሰነ መልኩ ሳይሆን ለድሉ መገኘት የኩባ ወታደሮች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሆኖ ሳለ፣ ኢትዮጵያዊያን ጦርነቱን ያሸነፍነው በእኛ ጀግንነት ነው ይላሉ፤ እውነት እርስዎም በኢትዮጵያዊያን ጀግንነት የመጣ ድል ነው ብለው ያምናሉ?
ፊደል ካስትሮ፡- ጀግንነት ለኢትዮጵያውያን ብርቅ አይደለም! ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለውን ምስክርነት እኔ ልሰጥሽ ከምችለው በላይ ለምን የሚሰጡሽን ሰዎች አትጠይቂያቸውም?
ጣሊያናዊቷ ጋዜጠኛ፡- እነማን ናቸው እነሱ?
ፊደል ካስትሮ፡- አያቶችሽን ጠይቂያቸው!
የኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክ እንዲህ ነው።ጣሊያናዊቷ ጋዜጠኛም እንዲህ አጥብቃ የጠየቀች የአያቶቿን ታሪክ ስለምታውቅ ኢትዮጵያን ያጣጣለች መስሏት ነበር።የጀግናን ልክ የሚያውቅ ልኳን ነገራት እንጂ!
ዛሬ ዓድዋ ነው።ፊደል ካስትሮ ‹‹አያቶችሽን ጠይቂያቸው›› ያላት የዓድዋን ታሪክ ነው።የዓድዋ ታሪክ እነሆ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ታሪክ ሆነ።‹‹ለካ እንዲህ ነፃ መውጣት ይቻላል›› ያሉ የአፍሪካ አገራት የነፃነት ትግል ጀመሩ።በኢትዮጵያ አርዓያነት ነፃ ወጡ።ይህ የዓድዋ ታሪክ ኢትዮጵያውያን በየሄዱበት ደረታቸውን ነፍተው እንዲናገሩ አደረጋቸው።የጀግንነት ድርጊት ሲፈጸም ‹‹ይሄማ ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት›› ተባለ።
ዓድዋ ባይሆን ምን ይፈጠር ነበር?
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር መምህር የሆኑት መምህር ሀሳቡ ተስፋ የመጀመሪያውን የአሜሪካ ህገ መንግስት ይጠቅሳሉ።ይህ ህገ መንግስት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1787 ተጽፎ፣ በ1788 ጸድቆ በ1789 ሥራ ላይ የዋለ ነው።
መምህር ሀሳቡ እንደሚሉት፤ ይህ የአሜሪካ ህገ መንግስት ጥቁሮችን እንኳን ከነጮች እኩል እንደ ሰው አያይም ነበር።ይህ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግስት ጥቁሮች ከነጮች ጋር ያላቸው ድርሻ 60 በመቶ ነው ይላል።
የቀረውን 40 በመቶ ሰው አይደሉም ማለት ነው።ከነጮች እኩል ለመሆን የ40 በመቶ የሰውነት ደረጃ ይቀራቸዋል እያለ ነው።የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግስት ይህን ሲል ከታች ያሉት ህጎችና ደንቦች ደግሞ ጥቁሮችን ‹‹ቺምፓንዚ›› እያሉ ከዝንጀሮ ጋር ያመሳስሉ ነበር።
በዓድዋ ድል ግን ታሪክ ተቀየረ።መምህር ሀሳቡ እንደሚሉት ‹‹ዓድዋ የአፍሪካ ሳይሆን የዓለም የጥቁር ህዝቦች የድል አርማ ነው›› ።ዓድዋ ባይኖር ኖሮ ይህ የአሜሪካ ህገ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ጥቁር ህዝቦችን የሚያሳንሱ አስተሳሰቦች ረጅም ታሪክ ምእራፍ ይጓዙ እንደነበር ለማሰብ አይከብድም።
ለዚህም ምስክር የሚሆነው አፍሪካውያንን ለመቀራመት በ1884 በርሊን ላይ ያደረጉት የክፍፍል ውይይት ነበር።ይህን ያደረጉት ከአሜሪካው ህገ መንግስት ከተረቀቀ ከመቶ ዓመት በኋላ ነው።በመቶ ዓመት ውስጥ እንኳን አስተሳሰባቸው አልተቀየረም ነበር ማለት ነው።የድርሻቸውን ሲከፋፈሉ አፍሪካውያን በራሳቸው ብቁ አይደሉም ብለው ያምኑ ነበር።
ከ12 ዓመት በኋላ ግን ታሪክ ተቀየረ።በ1896 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) ዓለምን ያስደመመ ክስተት ተከሰተ።አፍሪካን ሊቀራመት ሲዶልት የነበረው የነጭ ስብስብ ጉድ ተሰራ።በዓድዋ ድል ሆነ!
ይህ የዓድዋ ድል ባይገኝ ኖሮ ‹‹ምን ይከሰት ነበር?›› ብለን ከጠየቅን መልሱ ቀላል ነው።በርሊን ላይ ባስቀመጡት ክፍፍል መሰረት ኢትዮጵያ ቅኝ ተገዢ ሆና ትቀር ነበር።ዛሬ እንዲህ በራሳችን ቋንቋ አንናገርም ነበር፡ ፡በነጻነት መንፈስ አንገታችንን አቅንተን አንሄድም ነበር ።
ከዓድዋ በኋላ ምን ተፈጠረ?
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ፋንታሁን አየለ እንደሚሉት፤ በዘመኑ እንደ መላዕክት ይታዩ የነበሩ አውሮፓውያን ነጮችን ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ ዶግ አመድ አደረገቻቸው።‹‹ለካ ጥቁር ነጭን ያሸንፋል እንዴ!›› ማለት ተጀመረ።ይህ የዓድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን አቀጣጠለ።በዚህም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሁሉ ኮሩበት።ነፃ መውጣት እንደሚቻል ከኢትዮጵያ ተማሩ።ብዙ የአፍሪካ አገራትም በብዙ መራራ ትግል ከነጭ አገዛዝ ነፃ ወጡ።
እንደ ዶክተር ፋንታሁን ገለጻ፤ ብዙ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት መነሻ አድርገው ተጠቀሙ።ስምንት የአፍሪካ አገራት ሌላ ምንም አይነት ቀለም ሳይጨምሩ አረንጓዴ፣ ብጫ እና ቀዩን ቀለም የራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ አድርገዋል።
ለምሳሌ የጋና፣ ካሜሮን፣ ጊኒ ቢሳዋ፣ ጊኒ፣ ኮንጎ፣ ቤኒን፣ ቦሊቪያ፣ ማሊ… የመሳሰሉት አገራት አቀማመጡና የሚጠቀሙት አርማ ቢለያይም ሁሉም አረንጓዴ፣ ብጫ እና ቀይ ቀለማትን ነው የተጠቀሙት።በተለይም የጊኒ እና የማሊ አቀማመጡ ይለያይ እንጂ በድንገት ሲታይ የቀድሞውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ነው የሚመስል።
ዶክተር ፋንታሁን እንደሚሉት፤ ከዓድዋ በኋላ የተፈጠረው ሌላው ነገር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታላቅ አገር እንድትሆን ማድረጉ ነው።የአፍሪካ ሕብረትን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንንን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን ተደርጓል።ይህም የአገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማት መቀመጫ እንዲትሆን አድርጓል።ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዲካሄድባት አድርጓል።በእነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ስም በዓለም ይጠራል።
‹‹የዓድዋ ድል ‹ታሪክ አበቃ› የተባለለት ነው›› ያሉት መምህር ሀሳቡ፤ ታሪክ አበቃ የተባለበት ምክንያት ለዘመናት የነጭ የበላይነትና የጥቁር የተበታችነት ታሪክ ያበቃበት መሆኑን ያብራራሉ።በህገ መንግስታቸው ነጮች መቶ በመቶ ሰው ሲሆኑ ጥቁር ደግሞ ሰው የሆነው ገና 60 በመቶ ነበር።ያ ታሪክ አብቅቶ በእነዚህ አገራት ጥቁሮች የአገር መሪ እስከመሆን ደርሰዋል።ይህንን ነው እነ ጆርጅ በርክሌይ ‹‹ታሪክ አበቃ›› ብለው የገለጹት።
በወቅቱ የሶሻሊስት አገሮች ‹‹ቪቫ ምኒልክ! ቪቫ ጣይቱ!›› እያሉ አድናቆታቸውን ሲገልጹ ነጮች ግን ሽንፈታቸውን ለመሸፈን አደናጋሪ ነገሮችን ሲጠቀሙ ነበር።በዓድዋው ጦርነት ጊዜ የዘመተውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ‹‹አንድ ነጭ በፈረስ ላይ ሆኖ ሲወጋን ነበር፤ እሱ ነው ያሸነፈን›› ብለዋል።
ይህን ያሉት ጥቁር ነው ያሸነፈን ላለማለት ነው።‹‹ያ ትርክት ግን አሁን ላይ አልሰራላቸውም›› ያሉት መምህሩ፤ አውሮፓውያን ከመለኮታዊ እሳቤ ወደ ሳይንሳዊ እሳቤ መሄድ ሲጀምሩ ጥቁሮች ማሸነፋቸውን አመኑ።የኢትዮጵያ ማሸነፍ የመላው ጥቁሮች ድል እንደመሆኑ ሁሉ የጣሊያን መሸነፍም የመላው ነጮች ሽንፈት ሆነ።
የዓድዋን ድል የዋጋውን ያህል ተጠቅመንበታል?
‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ ከጠጠር ይቀላል›› ሆኖብን እንጂ የዓድዋ ድል ትልቅ ዋጋ ያለው ነው።የሌላ አገር ታሪክ ቢሆን ይሄኔ እንዴት ባደነቅነው ነበር? ከፈረንጆች ወስደን እኮ ‹‹የጅል ቀን፣ የእብደት ቀን›› የሚል ሳይቀር እያከበርን ነው አይደል?
‹‹ቅኝ ብንገዛ ኖሮ ያልፈልን ነበር›› የሚል አስተሳሰብ መኖሩን የገለጹት መምህር ሀሳቡ፤ ቅኝ የተገዙ አገሮች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ መመርመር ያስፈልጋል ይላሉ።በራሳቸው ቋንቋ አይጠቀሙም፣ የራሳቸው የዘመን አቆጣጠር የላቸውም።ያልተበረዘ ቱባ ባህል የላቸውም።የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ የመገልገያ ዕቃዎቻ እና ሌሎች የዕደ ጥበብ ሥራዎቻቸው የኢትዮጵያን ያህል ብዝሃነትና አገር በቀላዊነት የላቸውም።እንዲያውም የተሻሉ የሆኑትም ከነፃነት በኋላ ወደራሳቸው ማንነትና አገር በቀላዊነት በመመለሳቸው ነው፡፡
የመምህር ሀሳቡን ሀሳብ የሚያጠነክርልን አንድ እውነት አለ።ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በአፍሪካ አገራት ላይ የሚሰሩትን ዘጋቢ ፊልም ልብ ብለን እንይ።የኢትዮጵያን ያህል አገር በቀላዊነት የለውም።የዕደ ጥበብ ሥራዎቻቸው፣ ቋንቋዎቻቸው፣ የሙዚቃና የፊልም ሥራዎቻቸው እንኳን የቅኝ ገዥዎቻቸውን ፈለግ የተከተለ ነው።ያ ማለት አንድ የአውሮፓ አገር ሊጎበኛቸው ቢመጣ የራሱን አገር ባህል ነው የሚያየው ማለት ነው።ይሄ ማለት አልጎበኘም ማለት ነው።በሌላ በኩል የዓድዋ ድል ከባርነት፣ ከታዛዥነት፣ ከአሽከርነት ነፃ አውጥቷል።
የዋጋውን ያህል አልተጠቀምንበትም ነው የሚሉት መምህር ሀሳቡም፤ ዶክተር ፋንታሁንም።ማክበር የተጀመረው እንኳን በቅርቡ ነው።የዋጋውን ያህል ብንጠቀምበት ኢትዮጵያን ሃያል አገር የሚያደርግ ነው።ይህም በዓይነ ቁራኛ ለሚከታተሏት አገራት ማንነቷን ያሳያል።ዓለም አቀፍ ተቀባይነቷን ከፍ ያደርገዋል።ዓድዋን የዋጋውን ያህል እንጠቀምበት የሁለቱም ምሁራን ምክረ ሀሳብ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013