ጌትነት ተስፋማርያም
ሆ ብየ እመጣለሁ ሆብየ በድል
ድሮም ያባቴ ነው ጠላትን መግደል
ብሎ የተነሳው የኢትዮጵያ ሰራዊት በዓድዋ ወራሪውን ፋሺስት በማሳፈር ታላቅ ገድል አከናውኗል። ይህ ገድል ታዲያ በሀገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፤ ሰራዊቱ ወደ ተለያዩ ሀገራት በማቅናት የሌሎችንም ሰላም እና ነጻነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
የኢትዮጵያ ጦር ለሰላም ማስከበር ስራ ባህር አቋርጦ ድንበር ተሻግሮ ለዓለም ሰላም የተዋደቀ ሰራዊት ነው። ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባልነቷ ድርጅቱ በሚያደርግላት ጥሪ ዓለም አቀፍ ሠላም የማስከበር ተልዕኮ በመሳተፍ የተደነቀ ተግባሮችን አከናውናለች፡፡
ዛሬም ይህንኑ ግዳጅ በመወጣት ላይ ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ግዳጅ በመጀመሪያ መሳተፍ የጀመረችው እና የሀገር ክብርና ዝናን የተከለው በኮሪያ ጦርነት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አንስቶ ከክቡር ዘበኛ ከጦር ሰራዊቱ የተውጣጡ 6ሺህ 37 ሰራዊት በማዘጋጀት በተለያዩ ዙሮች በተመድ የጋራ ደህንነት ሰላም መርህ መሰረት ወደ ደቡብ ኮሪያ በመላክ ምላሿን ሰጥታለች። የኢትዮጵያ ሠራዊት ቀደም ባለ ታሪኩ ይህን የመሰለ ዓለም አቀፍ ግዳጅ ተሰጥቶት ተሰማርቶም ባያውቅም በድል እንደሚመለስ ግን ህዝብ አምኖበታል።
ከ1943 ዓ.ም እስከ 1945 ዓ.ም በኮርያ የዘመተው ቃኘው ሻለቃ በአዲስ አበባ ሽኝት ሲደረግለት የተሰጠውን ‹‹በክብር ያስረከብናችሁን የኢትዮጵያ ባንዲራ በክብር እንድትመልሱ›› የሚል የአደራ ቃል በማክበር የሀገር ባንዲራ ከፍ ብሎ በዓለም መድረክ እንዲውለበለብ ማድረጉን ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል።
ከጅቡቲ በመርከብ ለ21 ቀናት ተጉዘው ደቡብ ኮሪያ ፑዛን ወደብ ከደረሰ በኋላ ለስድስት ሳምንታት የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችን የወሰደው ቃኘው ሻለቃ ሰላም አስከባሪ ጦር ከስልጠናው በኋላ ወደ ግዳጅ ነበር ያመራው።
በወቅቱ ኢትዮጵያን እና አሜሪካን ጨምሮ 21 ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባልነት በኮሪያ ምድር ሰላም አስከባሪ ጦር አሰልፈው ነበር። ቃኘው ሻለቃም የተየሰጠውን ግዳጅ በሚገባ በመፈጸም የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካንም ስም በማስጠራት ትልቅ ጀብዱ ፈጽሟል።
በወቅቱ የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ማርኮ ክላርክ ለኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው ስለጀግንነታቸው መስክረዋል። የቃኘው ሻለቃ አባላትም በፈፀሙት ግዳጅ የኢትዮጵያ ሰራዊት የደቡብ ኮሪያን ፕሬዝዳንታዊ ጦር ክፍል ከፍተኛ ሜዳይና ሪቫን ተሸልሟል።
በአጠቃላይ እስከ አምስት ዙር ከዘመቱት 6ሺህ 37 የኢትዮጵያ ወታደሮች ውስጥ 121 በውጊያ ላይ ሲሰዉ 536ቱ ደግሞ ቆስለዋል። ለሰማዕታቱም የመታሰቢያ ሃውልት ቆሞላቸዋል።
በአጠቃላይ አንድም ምርኮ እና የጠፋ ወታደር ያላስመዘገበች ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ሆና ግዳጇን አጠናቃለች። የኢትዮጵያውያን ጀግና የሰራዊት አባላትም ስም በኮሪያ ምድርና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ከዳር እስከ ዳር የናኘ ዝና እና ክብር አገኝተዋል።
ከኮሪያ ቀጥሎ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር የተሳተፈችው በኮንጎ ዘመቻ ነው። በኮንጎ ካታንጋ በተሰኘው በተፈጥሮ ማዕድን በበለጸገ ስፍራ ላይ በተነሳ የይገባኛል ግጭት ሀገሪቷን ለከፋ አደጋ አጋለጣት። በቤልጂየም የሚደገፈው ቾምቤ በተሰኘው የሚመራው ቡድን እና በፓትሪስ ሉሙምባ የሚመራው የሀገሪቷ መንግስት መካከል ግጭት ተፈጠረ።
በወቅቱ ተመድ ከ30 ሀገራት የተውጣጡ 19ሺህ 828 ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ሲያሰማራ ኢትዮጵያም ፈጣን ምላሽ በመስጠት ከ 1952 ዓ.ም አንስቶ እስከ 1955 ዓ.ም ድረስ በብርጋዴር ጄኔራል ኢያሱ መንገሻ የሚመሩ አራት ጠቅል ብርጌዶችን ልካለች።
ይህም ብቻ አይደለም ከሁሉም ሀገራት የተውጣጣውን ሰላም አስከባሪ ጦር በዋና አዛዥነት የሚመሩት ኢትዮጵያዊው ጄኔራል ከበደ ገብሬ ነበሩ። የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጠቅል ብርጌዶችም በኮንጎ ካታንጋ፣ ስታንሌይቬልና ኦርየንታል በተሰኙ ግዛቶች የኮንጎን ህዝብ ከአደጋ በመከላከል ዓለም አቀፋዊ ተልዕኳቸውን በብቃት ፈጽመዋል። ይህ ጀብዱ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የጋራ ደህንነትና ሰላም ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ይዞ እስካሁንም ሲታወስ ይኖራል።
ከኮንጎ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ሰራዊት የዘመተው ወደሩዋንዳ ነው። ከ1986 ዓ.ም እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ በሩዋንዳ ሁቱ እና ቱትሲ ጎሳዎች መካከል የተነሳውን የእርስ በእርስ ግጭት እና የዘር ጭፍጨፋ ሲፈፀም በሀገሪቷ ሰላም አስከባሪ መስፈር እንዳለበት ተመድ ወሰነ።
በወቅቱ በዋነኛነት ለአካባቢው የሰላም ማስከበር ኃላፊነት የታጨው የኢትዮጵያ ሰራዊት ነበር። ሊበርድ ያልቻለ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተስፋፋበት እንዲሁም የበቀል እርምጃ በጎሳዎች መካከል ሊፈጸም ይችላል ተብሎ በሚሰጋበት ወቅት በመሆኑ ኃላፊነቱ ቀደም ካሉት የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከባድ ነበር።
ይሁንና በጊዜው ጥርጣሬ ውስጥ የወደቀውን የተመድ የጋራ ደህንነት ሰላም መርህ ለማዳን እና ተልዕኮውን ለመፈጸም የኢትዮጵያ ጦር ግጭት ወዳናወዛት ሩዋንዳ መዝመቱን የመከላከያ ሰራዊት ሰላም ማስከበር ማዕከል መረጃዎች ያሳያሉ። በሩዋንዳም ሰራዊቱ ለየትኛውም ወገን እና ጎሳ ሳያዳላ ሰላም ለማስከበር በመጣሩ ለውጦች መታየት ጀመሩ።
ወደ ጎረቤት ሀገራቶች ሲሰደዱ የነበሩ ሩዋንዳውያንም ወደሀገራቸው መመለስ ጀመሩ። አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ የኢትዮጵያ ጦር እውነተኛ ሰላም አስከባሪ መሆኑን በማስመስከር ስደተኞችንም ጭምር በማቋቋም ስራ ተጠመደ። ታጣቂዎችንም ጦር በማስፈታት ዘላቂ ሰላም በሀገሪቷ እንዲሰፍን ሰፊ ስራ አከናወነ።
ፋብሪካዎች እና ኢንዱስትሪዎች ሰላሙን ተከትለው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ የዓለም ህዝብም ለኢትዮጵያ ጦር ይበልጥ አድናቆቱን መግለጽ ጀመረ። በዚህም ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን የኢትዮጵያን አቋም በማንፀባረቅ ታላቅ ታሪክን ጽፏል።
በመቀጠልም በብሩንዲ ከ1996 ዓ.ም እስከ 2001 ዓ.ም በሰላም ማስከበር የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከተመድ በተለየ በአፍሪካ ህብረት ስር ነበር ወደቦታው የተጓዘው። ተመድ በአፋጣኝ የሰላም አስከባሪ ኃይል ባለማስፈሩ ኃላፊነቱ ለአፍሪካ ህብረት ተሰጠ። የአፍሪካ ሚሽን በብሩንዲ በሚል ስያሜ በህብረቱ ስር ሲመሰረት ኢትዮጵያ ዋኛዋ የሰላም አስከባሪ በመሆን ጦሯን ወደ ስፍራው ላከች።
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በብሩንዲ ቆይታው ከአፍሪካ ህብረት የሰላም ተልዕኮ የሚሰጡትን ግዳጆች ከመፈፀም ባለፈ ሕዝባዊ ባህሪውና ሰብአዊነቱ የሚያስገድዱትን ተግባራት ፈፅሞ ከብሩንዲ ሕዝብና መንግስት ክብርና ፍቅርን ተጎናጽፏል። በተመሳሳይ በላይቤሪያም በተሰጠው የሰላም ማስከበር ግዳጅ ሰራዊቱ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ሀገሪቷ እንድትረጋጋ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
መሰረተ ልማት ባሌለባቸው አካባቢዎች እንኳን እየተጓዘ ትጥቅ በማስፈታት እና ሰዎች ሰላማዊ ትግልን ምርጫቸው እንዲያደርጉ በማስተማር ባደረገው ጥረት ለተልዕኮው ከተመድ የሜዳሊያ እና የሪቫን ሽልማት ተበርክቶለታል።
እንደ መከላከያ ሰራዊት ሰላም ማስከበር ማዕከል ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በዳርፉር የተከሰተውን ግጭት ለማብረድ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ተመርጧል። ሰራዊቱ ከተመረጡ የሌሎች ሀገራት ሰላም አስከባሪዎች መካከል ልምድ ያለው እና በስነምግባሩ የተመሰገነ ነበር። በዳርፉር ያለውን አስቸጋሪ የአየር ንብረት ተቋቁሞ አይበገሬነቱን አሳይቷል።
በዘመናዊ የጦር ታንኮች እና ሄሊኮፕተሮች ጭምር በመታገዝ የሰላም ማስከበር ስራ ከማከናወኑም በላይ የእራሱን መገልገያ መሳሪያዎች በውስጥ አቅም በመጠገን ጭምር ቴክኒካዊ ብቃቱንም በግልጽ ያሳየ ሰላም አስከባሪ ጦር መሆኑን አሳይቷል። ሱዳን ከዳርፉር በተጨማሪ በደቡብ እና በሰሜን ሱዳን መካከል የይገባኛል ጥያቄ በተነሳባት አብዬ ግዛትም የኢትዮጵያ ጦር አሁንም ለሰላም ማስከበር ስራው ዘብ መቆሙ አልቀረም።
የተመድ ኃላፊዎች ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ሰራዊቶች ወደግዛቷ እንዲያመሩ ሃሳብ ቢያቀርብም የደቡብ ሱዳን እና ሱዳን መሪዎች ግን ሃሳቡን ባለመቀበል ተመራጭ የሆነውን የኢትዮጵያ ሰራዊት ብቻ ወደግዛቷ እንዲገባ ጥያቄ ማቅረባቸው የወቅቱ መነጋገሪያ ነበር። ተመራጭ ሆኖ የገባው ፤ ጀግንነትን እና ከእራስ በላይ የሌሎችን ህይወት ታድጎ ሰላም ማስከበርን የሚያውቅበት የኢትዮጵያ ሰራዊት ልክ እንደ ጥንቱ ሁሉ በአብዬ ግዛትም ስኬትን አስመዝግቧል።
የቦታው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ልዩ የሚያደርገው በአማካይ አንድ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደር ሁለት ነጥብ ሶስት ስኩዌር ኪሎ ሜትር በመሸፈኑ በወቅቱ ከሁሉም ዓለማት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ጋር ሲነጻጸር በትልቅነቱ ተጠቃሽ ሆኗል።
በቦታውም አርአያ የሚሆን የማረጋጋት ስራ በመፈጸም ዳግም ታሪክ የማይረሳው ተግባር ፈጽሟል። ሰራዊቱ በተመሳሳይ በአይቮሪኮስት፣ ቻድ እና ማሊ የጦር አባላቱንና የቢሮ (ስታፍ) ሰራተኞቹን በማሰማራት በተለያዩ ዘርፎች የሰላም ማስከበር ስራ ላይ ተሰማርቷል፤ እየተሰማራም ይገኛል።
በሶማሊያም ከተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) ሴክተር በሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሀገሪቷ ሰላም እንዲመጣ ጥረት በማድረግ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ጦር በየጊዜው ከሚደርሱ የአልሸባብ ሽብር ቡድን ጥቃቶች ጋር በመጋፈጥ የሀገሪቷን ብሎም የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛል።
የጎረቤት ሀገራት ሰላም የኢትዮጵያም ሰላም ነው በሚል መርህ የሚሰማራው የሰላም አስከባሪ ጦር በየሄደበት ሀገር ሁሉ ከህዝቡ አመኔታን እና ድጋፍን እያገኘ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ታሪክ በመፃፍ ላይ ይገኛል።
እንደ መከላከያ ሰራዊት ሰላም ማስከበር ማዕከል መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ እስካሁን በታሪኳ ከ140ሺህ500 በላይ የሰራዊቱ አባላትን በተለያዩ ሀገራት ለሰላም ማስከበር ስራ አዝምታለች። በአሁኑ ወቅት ብቻ ከ10ሺህ 550በላይ የሰራዊቱ አባላት በአብዬ፣ በዳርፉር፣ በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ ግዳጃቸውን በመፈፀም ላይ ናቸው።
በሰላም ማስከበር ግዳጃቸው ወቅት ከፊሉ በሞተራይዝድ ሻለቃ ጦር የተደራጁ ሲሆን ከፊሉ ደግሞ በመድፈኛ አሊያም በኮማንዶ ጦር ተመድበው ይሰራሉ። በታንከኛነት፣ በውሃ ቁፋሮ፣ በሁለገብ ጥገና አገልግሎት እና በቴክኒሻንነት እንዲሁም በቀላል መሃንዲስ ስራዎች የተሰማሩ የሰላም አስከባሪ አባላትንም ኢትዮጵያ አሰማርታለች።
በሄሊኮፕተር ጥገና እና በህክምና አገልግሎትም ሴቶችም ጭምር ከፍተኛ አገልገሎት በመስጠት ላይ ናቸው። በሴቶች የሰላም ማስከበር ተሳትፎ ረገድ ኢትዮጵያ ተጠቃሽ የዓለም ሀገር ስትሆን፣ ከሶስት ዓመታት በፊት ከ800 በላይ ሴት ሰላም አስከባሪዎችን በማሰማራት ከዓለም ቀዳሚውን ድርሻ ይዛ ነበር።
አሁንም ቢሆን ሴት ሰላም አስከባሪዎች ፈታኝ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ተመድበው በተለያዩ መስኮች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን የሰላም ማስከበር ማዕከል መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሴት የሰላም አስከባሪ ሠራዊትንም ጭምር በመላክ የምታደርገው ተሳትፎ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆን የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት ምስክርነቱን በተደጋጋሚ ሰጥቷል።
ኢትዮጵያ አሁንም ለሠላም ማስከበር ተልዕኮ ተመራጭ ሀገር ሆና የመቀጠሏ ምክንያት ከእራሷ አልፎ ለሌሎችም የሚተርፍ በዲሲፕሊን የታነጸ ሰራዊት እና አመራር በመያዟ ነው። የአድዋ ድል ጀግኖች አባቶቻችን ገድል በሰራዊቱ የሰላም ማስከበር ስራዎች እየተደገመ ይገኛል። ይህን ታላቅ ታሪክ እና ገድል ለማጠልሸት የሚፈልጉ ኃይሎች ግን አንዳንድ ጊዜ የሰራዊቱን ስም ለማጉደፍ ጥረት ማድረጋቸው እልቀረም።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገራት ነጻነት ብሎም ለዓለም ሠላምና መረጋጋት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ዛሬም በየሀገራቱ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን በዓለም መገናኛ ብዙሃንም ጭምር ምስክርነት ሲሰጥበት ይኖራል።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013