ራስወርቅ ሙሉጌታ
ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የሕዝቦቿ አንድነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የገባበት የጨለማ ዘመን ሆኖ ቆይቷል።
በእነዚህ ዓመታት ሀገሪቱን በዘር በማጋጨት ሲገዛ የነበረው የህወሓት ቡድን የስልጣን አድሜዬን ያራዝምልኛል የሀገሪቱንም ሀብት ለመመዝበር በር ይከፍትልኛል ብሎ ባልተጻፈ ሕግ ሲተገብረውና ሲሰብከው የነበረው የከፋፍለህ ግዛ አካሄድ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም በርካታ መስዋዕትነቶችን እያስከፈለ ቆይቷል።
ይህ ቡድን የዘራው የመበታተን ዘር ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በእርስ እንዲቃቃሩ አንዱ አንዱን በጠላትነት እንዲያይ በግለሰብም ደረጃ አለመተማመን እንዲስፋፋ በማድረግ የቁርሾ የቂም አስተሳሰቦችና ተግባራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲፈጸሙና ከፍተኛ ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኖ ኖሯል።
ምንም እንኳን በሀገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ዛሬ ነገሮች መስተካከል ቢጀምሩም ለሃያ ሰባት ዓመት የህወሓት ቡድን ባስቀመጡት የዘረኝነት እሾህ የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል፤ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመትም ተከስቶ ከግለሰብ እስከ ድርጅት ብሎም እስከ መንግሥት በርካታ ኪሳራዎች ሊደርሱ በቅቷል።
ሲፈጸሙ በነበሩት ሕዝብን የማበጣበጥ ተግባራትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ሀብት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል፤ በርካታ ህጻናት ያለ አሳዳጊ በርካታ አዛውንቶች ያለ ጧሪ እንዲቀሩ ምክንያት ሆነዋል።
በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ወደሀገር ውስጥ የገቡ የግለሰብና የመንግስት ንብረቶች፤ ፋብሪካዎች ወድመዋል በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ሥራ አልባ በመሆናቸው ራሳቸውም ቤተሰቦቻቸውም ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመዳረግ በቅተዋል።
እነዚህ ሁላ በከፋፍለህ ግዛ መርህ ሲከሰቱ የነበሩ ችግሮች አክተመው ኢትዮጵያ የመላው ኢትዮጵያውያን ስትሆን ማየት የሚፈልጉ ዜጎች በተለያየ መንገድ ሲታገሉ ቆይተዋል። በዚሀም ከዓመታት በፊት ለውጥ ተከስቶ ተበታትና ትጠፋለች የተባለችው ኢትዮጵያ በውስጥ ጠላቶቿ እንደተደገሰላት ሳይሆን ቀርቶ አንደነቷን እንደጠበቀች የከፋፋዮቿን መጨረሻ ለማየት በቅታለች።
የተከሰተውን ለውጥ ምንም እንኳን የዘመናት የሕዝብ ብሶትና እንግልት የወለደው ቢሆንም፤ ለውጡን በመምራት አቅጣጫ ሲያሲዙ የነበሩት አካላት ይህ የመበታታን የመለያያት አካሄድ እንደማያዋጣ በመገንዘብ በአንድነት በመደመር ጉዞ ኢትዮጵያን የማሸጋገር እንቅስቃሴ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ያለፉት አመታት እንደ ሀገር ለሚሰሩ ስራዎች አጭር ቢሆኑም የተመዘገቡት ውጤቶች ግን ሀገሪቷን ከመበታተን የታደጉና አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ በተስፋ የሞሉ ናቸው።
የዚህ ውጤት ምስጢሩ ደግሞ ከሁሉም በፊት ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማስቀደም ውሳኔ ነበር። በዚህ ረገድ ከለውጡ ቀዳሚ መሪዎች መካከልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በ2012 ዓ.ም ባሳተሙት «መደመር» በተሰኘው መጽሐፋቸው ያስቀመጡትን ሀሳብና የኖረው ሀገራዊ አንድነት መቀጠል ለኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፈንታ ያለውን ፋይዳ የምሁራን አስተያየት በመጨመር እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
በመደመር መጽሐፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመደመር ብያኔ በሚል የአንድነቱ ጉዞ እንዴት እንደሚቀጥል የሚከተለውን ሃሳብ አስፍረው ይጀምራሉ «መደመር የማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችን ጨምሮ ሁሉንም ግላዊና ማህበረሰባዊ የህይወት ዘይቤን የሚነካ እሳቤ ነው።
አላባዎቹም ሀገራችን ኢትዮጵያ ልትሄድበትና ልትደርስበት የሚገቡ መንገዶችና መዳረሻዎች ናቸው። ለእሳቤው መዳበር ገፊ ምክንያቱ በሀገራችን ባለፉት አራት ዓመታት የተቀጣጠለው ሀገራዊ ለውጥ ፍንትው አድርጎ ያሳየን ዘላቂና አፋጣኝ መፍትሄ የሚፈልጉ ሀገራዊ ተግዳሮቶች ናቸው።
በመሆኑም የመደመር እሳቤ የሀገራችንን ተጨባጭ ችግሮችና ህሊናዊ ሁኔታዎች መሰረት ያደረገ ነው። የእሳቤው ምንጭ ሀገራዊ ተጨባጭና አውዳዊ ሁኔታዎች በመሆናቸው ለመደመር የሚሰጠው ትርጓሜም ከዚሁ አውዳዊና ተጨባጭ ሁኔታ የሚመነጭ ነው።
ዓለም አቀፍ እውቀቶች የመደመርን ሀሳብ ለማዳበር አጋዥ ሚና አበርክተዋል። ሆኖም ግን የእነዚህ ዓለም አቀፍ እውቀቶች ፋይዳ መለኪያውና ማንጠሪያው ተጨባጭ ውስጣዊ ሀገራዊ ሁኔታ ነው።»
በየዘመኑ የነበሩና ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የነበሩ መንግሥታት የየራሳቸው ደካማም በጎም ጎኖች፤ እንዲሁም ውጤታማና ውጤታማ ያልሆኑ ስራዎች እንዳሏቸው ይታወቃል። ይሄ አይነት የአስተዳደር ዘመንና የመንግሥታት መገለጫ ደግሞ የትኛውንም ሀገራት በሚያስተዳድሩ ገዢዎች የግዛት ዘመን የሚከሰት እውነታ ነው። ይሄ አንደተጠበቀ ሆኖ እንኳን በሀገር ደረጃ በቡድን ለሚንቀሳቀሱም የህብረት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያም አሁን እንደ ሀገር ያሉባትን ችግርች ለመቅረፍ ብሎም ሕዝቦቿ ከሚመኙት የእድገት፤ የሰላምና የብልጽግና ማማ ለመድረስ ያሉት ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው በኢትዮጵያዊ አንድነት ውስጥ መጓዙ ተመራጭ መንገድ ነው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የማበር፤ የመደመር ጉዞ አማራጭ መሆኑን ከላይ በጠቀስነው የጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ መጽሐፍ እንደሚከተለው ቀርቧል።
« የመደመር ዋነኛ ዓላማ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበቻቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎች ጠብቆ ማስፋት የተሰሩ ስህተቶችን ማረም፤ እንዲሁም የመጻኢውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት ነው። በመሆኑም መደመር ከችግር ትንተና አንጻር ሀገር በቀል ነው። ከመፍትሔ ፍለጋ አንጻር ደግሞ ከሀገር ውስጥም ከውጪም ትምህርት በመውሰድ የተቀመረ ነው። »
ጨምረውም መተባበር ካለው ፋይዳ በተጨማሪ እንለያይ ብንል እንኳን የመጣንበትም የምንሄድበትም መንገድ አዋጭ እንደማይሆን፤ ከዚሁ በተጓዳኝ ደግሞ የዜጎችን ሁለንተናዊ ጥቅም ማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን እንደሚከተለው አስፍረዋል «…. ከመደመር እሴቶች መካከል አንዱ ʽሀገራዊ አንድነት ነውʼ ሀገራዊ አንድነት ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተጋመደ ፤ የተሰናሰለ እና የተዋሀደ መሆኑን አመላካች ነው።
የሀገራችን ብሔሮች እጣ ፈንታ በጋራ ለማደግ የተሰራ ብቻ እንጂ ተለያይተን ወይንም ተነጣጥለን ሉዓላዊ ሀገር ሆነን፤ የነጠላ ህልውናችንን አስጠብቀን በሰላም መቆየት አንችልም ። ሀገራዊ አንድነታችን የምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ማስጠበቅ ጉዳይ ጨምር ነው። ሌላኛው የመደመር እሴት ʽየዜጎች ክብርʼ ነው። የዜጎች ክብር ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም ይሁን በውጪ ሀገር ክብራቸው ተጠብቆና ሀገራቸውን መከታ አድርገው እንዲኖሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የመስራት ፍላጎት ነው ….. ። » ሲሉ አስቀምጠውታል።
በሌላ በኩል ማንኛውንም ዓላማ ለማሳካት የሚደረግ ጉዞ ሁሌም አስቸጋሪ ሁኔታዎችና እንቅፋት እንደሚገጥመው ይታወቃል። በኢትዮጵያም የተጀመረው የብዙኃን መኖሪያ የሆነች አንዲት ሉዓላዊነት ሀገር የመገንባት ጉዞ ግቡን እንዳይመታ በርካታ ሳንካዎች ከፊቱ ተጋርጠውበታል።
ከዚህም ውስጥ ዋነኛውና ቀዳሚው ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ሀገሪቱን በመከፋፈል በዝርፊያና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የግዛት ዘመኑን ለማራዘም ሲሰራ የነበረው ቡድን ያስቀመጠው የመለያያት ጉዞን የማራገብና በተለያየ መንገድ የመተግበር እሳቤ ነው። ምንም እንኳን ይህ ቡድን ሲያስበውና ሲያራምደው የነበረውን ሀገር የመበታተንና ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት ሴራ ከግብ ለማድረስ አቅሙንም ህልውናውንም ያጣ ቢሆንም የዘራውን የሾህ ሰብል ፍሬ እንዳያፈራ ማድረግ ካልተቻለ ግን ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ ዳግም ጋሬጣ መሆኑ አይቀርም ።
በዚህ ረገድ የመደመር የለውጥ ጉዞ ጋሬጣዎች ሊሆኑ የሚችሉትን ነገሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ገጽታ ሰፋ ባለ መልኩ ያቀረቧቸው ሲሆን ጠቅለል ተደርገው እንደሚከተለው ተገልጸዋል ። ….…. የመጀመሪያው ጋሬጣ የአስተሳሰብ ሳንካዎችን የሚያካተት ሲሆን « የመደመር የአስተሳሰብ ሳንካዎች አጠቃላይ የአስተሳሰብ ችግሮቻችንን የሚመለከቱ ናቸው ። ተደማሪነታችንም እነዚህ የአስተሳሰብ ችግሮች በቀረፍንበት መጠን የሚወሰን ይሆናል ።
መደመር ማለትም የእነዚህን የአስተሳሰብ ችግሮች ተሻግሮ የአስተሳሰብ ልዕልና ማምጣት ማለት ነው ። በማለት ቀጥሎ እርሳቸው የተዘረዘሩትን ቀዳሚ የአስተሳሰብ ችግሮች ዘርዝረው አስቀምጠዋቸዋል ። …… ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ …. ግዜ ታካኪነት….. አቅላይነት…. ሙያን መናቅ…. ሞገደኝነት፤ ፌዘኝነት እና አድር ባይነት» ናቸው።
በሁለተኛ መደብ የተቀመጡት የለውጥ ጉዞ ጋሬጣዎች ደግሞ የግብር ሳንካዎች የመደመር ቀይ መስመሮች ናቸው። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅሁፍ …. ምንም እንኳን መደመር በአጠቃላይ የልኬት ፍልስፍና የሚታይ ቢሆንም የግብር ሳንካዎቹን ማለፍ የታችኛው ወለል መስፈርት ነው ።
ይህም ማለት የጉዞውን ኃይል የሚገቱና የሚገዘግዙ ድርጊቶችን የተጓዦችን ልብ የሚያዝሉና ስግብግብነትን የሚያስፋፉ ተግባሮችን ለግለሰቦችና ለጥቂቶች ጥቅም ሲባል የብዙሃኑንና የሀገርን ህልውና የሚገዳደሩ ልማቶችንና ጥፋቶችን በፍጥነትና በማያዳግም ሁኔታ ማስወገድን ታሳቢ ያደርጋል ። በተለይም በላሸቀ ሞራል የሚደረጉ ዝርፊያዎችንና የተደራጁ ሌብነቶችን የሚታገስበት ጎን የለውም።
…. እንዲሁም በስንፍናና በዳተኝነት ያለብቃት ከሚደረጉ ድፍረቶች የሚከሰቱትን ውጤት አልባና ዝርክርክ አሰራሮችንና ብክነቶችን አይቶ እንዳላየ የማያሳልፍበትና የይለፍ ፈቃድ የሚከለክልበት ግልጽ የሆነ ቀይ መስመር ያሰምራል። መደመር ሁለት ነገሮችን የሚጸየፍ ፍልስፍና ነው ።
በእነዚህ ነገሮች ውስጥ የተዘፈቀ ሰው ለመደመር ራሱን ከእነዚህ ነገሮች የግድ ማጽዳት ይኖርበታል፤ ከህሊና ቢስነትና ከልግመኝነት … በማለት ተንትነው አስቀምጠዋቸዋል። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ያሳለፈቸውን በመለያያት ስጋት የተወጠሩ ሶሰት አስተ ዓመታት በመሻር ብሩህ ተስፋ የሚታይበት ነገን ለማየት ከግለሰብ እስከ መንግሥት የአንድነትን የመደመርን እሳቤ መከተል ቀዳሚው ምርጫ መሆኑን ያመላክተናል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሑፍ ሀሳብ በተመሳሳይ «ይሄ ለሩብ ምእተ ዓመት ሲዘራ የነበረን እሾክ በአንድ ወቅት ዘመቻ ማስወገድ አይቻልም። ነገር ግን ችግሩ ግዙፍ መሆኑን ከተረዳንና በዛው ልክ እኛም እንደ ሕዝብ በህብረት ትልቅ ስራ ሰርተን ትልቅ ሆነን ከተገኘን ይህን ቀን ማለፍና በአንድነታችን በመጽናት የምንመኛትን ታላቋን ኢትዮጵያ ማየት እንችላለን።» በማለት አስተያየታቸውን የሰጡን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዋቅጋሪ ነጋሪ ናቸው።
ዶክተር ዋቅጋሪ እንደሚሉት ከመነሻው ስንመለከት በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ በተለያዩ አካላት በርካታ ትግሎች ሲደረጉ የነበረ ሲሆን አብዛኛዎቹ በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነው በሀገሪቱ የነበረውን ችግር ኢትዮጵያዊነታቸውን ሳይክዱ ለመፍታት የሚሞክሩ ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ግን ህወሓት ትግል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያዊ አልነበረም ኢትዮጵያዊነትንም ሆነ ኢትዮጵያን አይፈልጋትም ነበር።
ይልቁንም በግልባጭ ህወሓቶች የመገንጠል ሀሳብ በመያዝና በማቀንቀን ኢትዮጵያን የመበታተን አጀንዳ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ናቸው። ይህንን ዓላማቸውን ለማሳካት ደግሞ ከየቦታው ለዚህ ዓላማ ተከታይ የሆኗቸውንና ግባችንን ያሳኩልናል ብለው ያሰቧቸውን እያባበሉም እያስፈራሩም አብረዋቸው የዚሁ የጥፋት ተልእኳቸው አጋዥ እንዲሆኑ አድርገዋቸው ቆይተዋል።
ነገር ግን በሀገሪቱ ጎራ ለይተው በተሰለፉ የተለያዩ አካላት ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በደርግ መንግስት መውደቅ ሲጠናቀቅ እነሱ ወደስልጣን እንዲመጡ በር ስለከፈተላቸው የተደበቀ ቡድናዊና ግላዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ኢትዮጵያ የሚለውን እንደ ሽፋን መጠቀም ጀመሩበት።
በወቅቱ በሀገሪቱ ሌላ ጠንካራ ኃይል ባለመኖሩ እነሱ ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀምና ከውጪ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚፈልጉ አካላት የሚያገኙትን ድጋፍ ጨምረው ሀገር መምራት ጀመሩ እንጂ ከመሰረቱ ኢትዮጵያን የመምራት እቅዱም ፤ ዝግጅቱም ፍላጎቱም አልነበራቸውም ።
በዚህ ሁኔታ የሥልጣን መንበሩን ከተቆጣጠሩ በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያን ይዘው እየዘረፉም እየሰረቁም ለመቀጠል ተመራጭ ሆኖ ያገኙት መንገድ ገና በትጥቅ ትግል ወቅት ሲያካሂዱት የነበረውን ሕዝብን እርስ በእርስ በማጋጨት በማቃቃርና በማጣላት በዚህም አንድነቱን በማሳጣትና በማዳከም ሥልጣናቸውን ማቆየት ነበር።
በዚህም አካሄድ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ብሄር ብሄረሰቦች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ ለማድረግ የአንዱ መኖር ለሌላኛው ስጋት እንደሆነ አድርገው ሲሰብኩ፤ ከስብከትም አልፈው በተግባር «ይሄ የዘመናት ጠላትህ ነው፤ ይሄ አጥፊህ ነው፤ በዚህ ዘመን እነ እከሌ እንዲህ አድርገውሀል» በማለት የሀሰት ትርክቶችንም እየጨመሩ ሲናክሱት ሲያጋጩት ኖረዋል።
የህወሓት ቡድን መሪዎች በሥልጣን በነበሩባቸው ጊዜያት በሙሉ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ማንነት አጉልተው ከማውጣት ይልቅ በይፋ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በመካድማንነትን በብሔር በዘርና በጎሳ ተክተውት ቆይተዋል። ይህ አስተሳሰብ ሥር እየሰደደ መጥቶም ዜጎች ኢትዮጵያዊ ነን ከማለት ይቅር አገው ነኝ፤ ሺናሻ፤ አኙዋክ ነኝ፤ ሀደሬ ነኝ… እያሉ እንዲጠሩ ይህንንም አምነው እንዲቀበሉ በማድረግ ማንነትንም አስተሳሰብንም እንዲጠብ አድርገውት ቆይተዋል።
እነዚህ አካሄዶች በፕሮፖጋንዳ በስብከትና በታሪክ ማንሻፈፍ ብቻ የተሰሩ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ የሚይዘው መታወቂያ ላይ ሳይቀር ዜግነቱን ከኢትዮጵያዊነት ወደ ብሔረተኝነት በማውረድ እኩይ የመከፋፈል ሕዝቡ ላይ ስራቸውን ሲሰሩበት ኖረዋል።
በዚህም ጥቂት የማይባል የማህበረሰብ ክፍል ተደጋግሞ በተዘራበት የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመመራትና በመጠለፍ ግማሹም በተለያዩ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ኢትዮጵያዊነት የእኔ ማንነት አይደለም እስከሚልበት ደረጃ እንዲደርስ ገፍተውት ነበር። እነዚህ አካላት ከዚህ በተጨማሪም የራሳቸውን እኩይ ሀሳብ በሕዝቡ ዘንድ ለማስረፅ ከመጣር በተጨማሪ በየወቅቱ የአንድነት ሀሳብ ይዘው የሚነሱትን ግለሰቦችም ይሁን በተለያየ ዓላማና ስያሜ የተሰባሰቡ ቡድኖችን የማሸማቀቅ የመበታተንና አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙትም የማስወገድ ሥራ ሲሰሩም ነበር።
እነዚሁ አካላት ኢትዮጵያዊነትንም በከፍተኛ ደረጃ ለመበርዝም በቅተው የነበር ሲሆን ከፍራቻ በሚመነጭ ስሜት የገዛ አገራቸውን ዜጋ ወዳጅ ጠላት ብለው ከግለሰብ እስከ ድርጅት በየጎራው መድበው ሲያደርጉት የነበረውም እንቅስቃሴ ሌላው የዛ ዘመን የኢትዮጵያ አንድነትም እድገትም እንቅፋት ሁነት ነበር። ይህን አመለካከታቸውን ምንም እንኳን ተቀባይ ባያገኙም ዛሬም እመቃብር አፋፍ ሆነው እየሰበኩትም እያራመዱትም ይገኛሉ ።
እነዚህ አካላት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እናስከብራለን ብለው ሲያወሩ የነበረ ቢሆንም በዲሞክራሲ ረገድም ሥልጣን ከያዙ ጀምረው ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የሕዝቡን መብት ሲነፍጉ የቆዩ ናቸው። በተለይ ከዘጠና ሰባት ምርጫ በኋላ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከደርግም ዘመን በባሰ መልኩ ሕዝቡ በጫና በአፈናና በጉልበት በእነዚህ ኃይሎች ሲገዛ መቆየቱና ለተለያዩ እንግልቶች መዳረጉ የአደባባይ ምስጢር ነው።
የዚህ ሁሉ ግፍ የዚህ ሁሉ የማናለብኝነትና የጥፋት ጉዞ የህወሓት ቡድን መሪዎችን ዛሬ ለተዳረጉበት የከፋ ችግር አብቅቷቸዋል። በኢትዮጵያ የተከሰተውም ለውጥ ሊመጣ የቻለው እነሱ በሕዝቡ ዘንድ ሲሰሩት የነበረው አሻጥር ያደረሰው ጥፋትና ውድመት በሕዝብ ላይ ያደረሰው ሰቆቃ የወለደው እንጂ ሌላ አይደለም።
በሌላ በኩል በተመሳሳይ ዛሬም በአንዳንድ አካባቢዎች ተማረ በሚባለው ኃይልና በአንዳንድ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንደ ችግር መነሻነት የሚሰበከው የስህተት መንገድ ነው። የሚሉት ዶክተር ዋቅጋሪ እነዚህ አካላት ሊረዱት የሚገባው ሀቅ ያለፉ ነገሮችን እያነሱ መጮሁ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ በማስገኘት በኩል ፋይዳ የሌለው ሲሆን ለጊዜያዊ ስሜትና ጥቅም ለማሳካት ካልሆነ በቀር በዚህ ዓይነት አካሄድ ሕዝብን ማስደሰትም አይቻልም ይላሉ።
ዶክተር ዋቅጋሪ ጨምረው እንዳብራሩት ህወሓቶች ያለፉ ነገሮችን የተዛቡ ትርክቶችን ሲያቀርቡ የኖሩት ለሕዝብ የሚበጅ ሆኖ ሳይሆን የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት ይጠቅመናል ብለው ስለሚያስቡ ነበር። ይህ እሳቤ ግን መጨረሻው ምን ሊያስከትል እንደሚችል እኛ ኢትዮጵያውያን በዘመናችን በአይናችን ለማየት በቅተናል።
ከላይ የተነሱት ሀሳቦች እንደተጠበቁ ሆነው የተለያየ ቋንቋ መናገራችን የተለያያ ማንነት መያዛችን ያለውን ጥቅም ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል የሚሉት ዶክተር ዋቅጋሪ ። የተለያየ ቋንቋ መናገር የተለያየ ባህል፤ ማንነት መኖር ማለት የተለያየን ነን አንድ አይደለንም ማለት አይደለም ። አንድ መሆን ማለት አንድ ዓይነት ማለትም አይደለም የተለያየ ሀሳብ የተለያየ ማንነት እንደያዝን በኢትዮጵያዊነታችን ግን አንድነት ሊኖረን ይገባል ። በሌላ በኩል ለሁሉም ቋንቋዎች ለሁሉም ባህሎች ክብር መስጠት መንከባከብና ማሳደግ ከመንግስትም ከእያንዳንዱ ግለሰብም ይጠበቃል ።
እንኳን በቋንቋ ደረጃ ይቅርና በአንድ ቋንቋ ስር ያለ ዘዪ ለመጥፋት ከተጋለጠ እያጣን ያለነው የኢትዮጵያን አንድ ክፍል አንድ አካል መሆኑን መገንዘብ አለብን በመሆኑም በመንግሥት በኩል ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ከሕዝቡም በተገኘው አጋጣሚ ይህንን ማድረግ የሚጠበቅ ይሆናል ሲሉ አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ እንደ ታሪክ ያለፉ ነገሮች መታየት ያለባቸው በዘመኑ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት በዛ ዘመን ሊኖር የሚችለውን አስተሳሰብ፤ እውቀት፤ የትምህርት ደረጃ፤ የሥልጣኔ ደረጃና የነበረውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የሀገራት እድገት እንዲሁም ሊሎች ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት እንጂ ዛሬ ላይ ሆኖ በዛሬ አዕምሮና ነባራዊ ሁኔታ መሆን የለበትም ።
ያለፉ ነገሮችን እያነሱ ማውገዙም መውቀሱም በተመሳሳይ ለሕዝቡ ጠብ የሚያደርገው ፋይዳ የለውም። ይልቁንስ ካሳለፍነው ታሪካችን ለእድገት ለአንድነትና ለህብረት የሚጠቅሙንን ነገሮች ነቅሰን እያወጣን ማስፋፋት ማዳበር ይገባል ።
ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በርካታ ሊጠቅሙን የሚችሉ የታሪክ አካላችን የነበሩ ሁኔታዎችን እየጣልን እየገፋንና ይሄ ያንተ፤ ይሄ የኔ፤ እያልን እየተገፋፋን በመምጣታችን በርካታ ያጣናቸው ነገሮች አሉ እንጂ ያተረፍነው ነገር የለም።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁላችን ልናውቀው የሚገባው ዋናው ሀቅ በሀገር ማስተዳደር ሂደት ውስጥ ትናንት የተሰሩ ስህተቶች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ነገም ይኖራሉ። እነዚህን ነገሮች የምናነሳውና የምናስታውሰው ግን ደግመን ላለመሳሳት መማሪያ ማድረግ መሆን አለበት እንጂ የማይመለሱ ነገሮችን እያነሳን በማማረር ቁርሾ የምንፈጥርባቸው ቂም የምንቋጥርባቸው የምንተቻችባቸውና የምንገዳደልባቸው ሊሆኑ አይገባም ።
ይህን ካላደረግን እየሰራን ያለነው የትናንትን ስህተቶችን ዛሬ ለመድገም ይሆናል ። ችግሮችንም ለመፍታት መኬድ ያለበት የትናንት ምክንያቶችን የትናንት ሁነቶችን በማንሳት ለዛሬ ምክንያት በማድረግ ሳይሆን ዛሬ ላይ ያለውን ነባራዊ ችግር መነሻ በማድረግ ችግሩን ለመፍታትም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ያለፉትን ለመማሪያነት ብቻ በመጠቀም ሊሆን ይገባል ።
ያለፈ ታሪካችን እንደሚያስተምረን በኢትዮጵያ ውስጣዊም ሆነው ውጪያዊ የተለያዩ ችግሮች ተፈጥረው አልፈዋል። በሌላ በኩል በርካታ ያልተመለሱ ነገር ግን ሊመለሱ የሚገባቸው የሕዝብ ጥያቄዎች አሁንም ድረስ አሉ ነገር ግን አንዳቸውም በመበታተንና በመለያየት ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉ አይደሉም ።
የመጣንበት መንገድና የነበረን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም ቢሆን ለመለያየት እድል የሚሰጥ፤ የሚፈቅድ አይደለም ። የሚሉት ዶክተር ዋቅጋሪ አንድነትና ህብረት ለአሁኗ ኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑን እንደሚከተለው ያብራራሉ ። በአንድነት ውስጥ እድገት ብልጽግና ይገኛል ኃይል ይዳብራል።
እንደ ኢትዮጵያዊ በሀገር ውስጥ ያሉ ጥቂት ልዩነቶችን እያነሱ መነታረኩ መተናነቁ በትልልቅ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት ይዘው ለሚመጡ የውጪ አካላት በር ከመክፈት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም ። እንኳን ተለያይተን በህብረትም ለመቅረፍ የሚያስቸግሩን በርካታ ችግሮች አሉብን በመሆኑም እንቅስቃሴያችን በሙሉ እነዚህን ከግምት ያስገባ መሆን ይጠበቅበታል ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የትምህርት ፋይዳውም እየተገለባበጠ የመጣበት ሁኔታ አለ የሚሉት ዶክተር ዋቅጋሪ አንዳንድ የተማሩ ሰዎች ቢኖሩም በአንድ ወገን ጭንቅላታቸው በማይሆን ነገር በመሞላቱ የሚሰሩትን እኩይ ስራ እያየን ነው ። ነገር ግን ያልተማሩ ሆነው ለሀገር የሚበጅ ለሕዝብ ሰላም የሚያሰፍን በርካታ ነገሮችን ሲያደርጉ እያየን እንገኛለን።
በግለሰብ ደረጃም አንዳንድ ወላጆች እቤታቸው የመለያያት የመራራቅ ነገር እየሰበኩ ውጪ ለሕዝብ ሌላ የሚያስመስሉም ይህ አካሄድ ለማመንም ስለማይበጅ ከዚህ መታቀብ ይኖርባቸዋል ።
በትምህርት ቤትም አንድነትን የሚያስፋፉ ነገሮችን በመስጠት እንኳን በሀገር ውስጥ ይቅርና ሰፋ አድርጎ እንደ አፍሪካ ብሎም እንደ ዓለምም ስለወንድማማችነት የሚያስብ ትውልድ ለመፍጠር አመለካከት ላይ መሰራት አለበት ።
ዛሬ በአንዳንድ ቦታዎች በጥቂቶች እየተፈጠሩ ብልጭ ድርግም የሚሉ ግጭቶችም ህወሓት ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ያጠመዳቸው የዘረኝነትና የመበታተን እቅድ ውጤቶች ናቸው። በመሆኑም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ሁለት ነገሮችን በአንክሮ ሊመለከቱ ይገባል።
የመጀመሪያው በተቻለ መጠን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ሆነው ቢሆን ያሏቸውን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መጣር ያለባቸው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ከጥፋት መስመር ወጥተው መሆን አለበት ።
በሁለተኛ ደረጃ ምንም አይነት ጥያቄ ቢኖርም ኢትዮጵያዊነታቸውን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ስላስገቡ የሚያገኙት ምላሽ ስለማይኖር ለእነሱም የራሳቸው ሀገር መሆኗን በመገንዘብ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ሆነው መታገልም መጠየቅም መልመድ አለባቸው።
እንዲህ አይነቱ አካሄድ ለትውልድ የሚተላለፍ ጠቃሚ ታሪክ ለማስቀመጥም የሚረዳ ይሆናል ። በአጠቃላይ እንደ መንግሥትም እንደ ሕዝብም እንደ ግለሰብም ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር መታቀብ ይጠበቃል ።
ይሄ እንዳለ ሆኖ መንግሥት ህወሓትን ወደ መስመር ለማምጣት ብዙ ቢጥርም አሻፈረኝ በማለታቸውና ሀገርን ወደሚያፈርስ ተግባር በመሸጋገራቸው መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ሀገርን የመታደግ የሕዝብን አንድነትና ሰላም የማስጠበቅ ሕግ የማስከበር በመሆኑ ተገቢና ሊቀጥል የሚገባው ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የገጠሟት ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሚገጥሟት ፈተናዎችም እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። በመሆኑም ለማንኛውም የውጪም ሆነ የውስጥ ሀገር አፍራሽና ሕዝብን የመበታትን ሴራ ባለመንበርከክ ይልቁንም የሚገጥሙ ችግሮችን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ሕዝብን ለማስተባበርና የሀገርን አንድነት ለማጠናከር መጠቀም ከመንግሥትም ከሕዝብም ይጠበቃል ።
በኢትዮጵያ አንድነትን ሊያደፈርሱ የሚችሉ የውጪ ጣልቃ ገብነቶች ትናንት ነበሩ ዛሬም አሉ ነገም ይቀጥላሉ እነዚህ ጣልቃ ገብነቶች ሊቆሙ የሚችሉት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በልጽጋና አድጋ የሁሉም ዜጎቿ ሁለንተናዊ መብት የሚጠበቅባት በአቅሟም የሁሉም ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝባት ስትሆን ብቻ ነው ።
ይህንንም ለማድረግ ከመንግሥት በኩል በሰከነ አዕምሮ እየተከታተሉ ችግሮችን በወቅቱ መፍታት ይጠበቃል አሁን የተዘጋጀው የሀገሪቱ የውጪ ፖሊሲ እንደ ከዚህ በፊቱ አንዱን ወዳጅ አንዱን ጠላት ብሎ የሚፈርጅ አካሄድ የሌለው በመሆኑ ተስፋ የሚጣልበት ነው።
በፖሊሲው እኛ እንደ ሀገር የምንወዳጀው የኢትዮጵያን ልማት ሰላም ሊደገፍ ሊያሳካ ከሚችል ከማንኛውም ጋር እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል። ነገር ገን ሁሉም ሀገራት ይጠቅሙናል ብለን የተነሳን ቢሆንም አንዳንድ የማያስማሙን ነገሮች ሲኖሩ በዛ ጉዳይ ላይ ብቻ በመደራደር በመወያያት እየፈታን የምንሄድበትንም አቅጣጫ አስቀምጧል።
በዚህ ረገድ የአባይ ጉዳይ የተያዘበት አካሄድ ይሄንን የሚያሳይና ይበል የሚያሰኝም ነው። በተጨማሪ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኃይል አቅርቦት በዲፕሎማሲና በሕዝብ ለሕዝብ የጀመርናቸው ግንኙነቶችም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
ሁሉም ግንኙነት መጀመርም መካሄድም ያለበት በጠንካራ ዲፕሎማሲ ላይ በመመርኮዝ ብቻ መሆን አለበት በጦርነት ልናገኘው የምንችለው ነገር ቢኖር እንኳን አክሳሪም ከመሆኑ ባሻገር ዘለቄታዊነትም አይኖረውም ። በመሆኑም አለመግባባቶችን የሀሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ አካሄድ በውይይት በንግግር የመፍታት ልምድ ለሀገር ውስጥ ጉዳዮችም ለውጪ ግንኙነት የሚጠቅምም የሚመረጥም ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ዛሬም ያኮረፉ ሰዎችና ቡድኖች እንዳሉ ይታወቃል። በተመሳሳይ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትም ታፍነው ስለነበር እንጂ በሕዝብ ዘንድ በርካታ ጥያቄዎች በርካታ ኩርፊያዎችም ነበሩ። ትግራይ ክልል ውስጥም ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች እንዳሉ ይታወቃል ።
ዋናው ነገር ለውጥ በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ የማይቀር ሂደት መሆኑን በመገንዘብ የለውጡ ተሳታፊ በመሆን በዛው ውስጥ ለጥያቄም ምላሽ ለማግኘት ዓላማንም ለማሳካት በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ መቻሉ ነው። በዚህ በኩል ማህበራዊ ሚዲያው አንድ የመከፋፈያ የችግር መፍጠሪያና ማባባሻ መንገድ እየሆነ ነው ።
ቴክኖሎጂውን መከልከል ወይንም መገደብ አስፈላጊ ባይሆንም መንግስት በተለያዩ ግዜያት ያወጣቸውን ሕጎች በመተገበር መቆጣጠር ይጠበቅበታል ። በተጨማሪ ሕዝቡም እንደ ሕዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በኃላፊነት ሊጠቀሙባቸው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ዶክተር ዋቅጋሪ በቅርቡ የሚካሄዱ ወቅታዊ ኩነቶችንም አስመልክተው እንደተናገሩት እስከዛሬ ህወሓቶች አድዋን የሚያክል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ብሎም በዓለም ላሉ ጥቁር ሕዝቦች የድል ብስራት የሆነ ትልቅ የድል በዓልን ሳይቀር ለመከፋፋል ለመበታተን ሲጠቀሙበት ኖረዋል።
በመሆኑም ከዚህ የተንሻፈፈ አመለካከት በመውጣት እንዲህ አይነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ብሎም ለመላው ጥቁር ሕዝብ ምሳሌ የሚሆን በዓልን ስናከብር በአንድነት የነገዋን ኢትዮጵያን እያሰብን ሊሆን ይገባል ።
በተጨማሪ በቅርቡ የሚካሄደው ምርጫም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያ ውድድር እንዲሆን ለማድረግ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የበኩላችንን መስራት አለብን ።
ነገር ግን ፍጹማዊ የሆነ አካሄድም ውጤትም መጠበቅ የለብንም በተቻለ መጠን በሰላም እንዲጠናቀቅና ማጭበርበር እንዳይኖር ማድረግ የተሳሳቱ ነገሮችም ካሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲታረሙ ማድረግ ይጠበቃል ። በዚህ ረገድ ከምንም በላይ ሚዲያዎች ትልቅ ኃላፊነትም አደራም አለባቸው ሲሉ ዶክተር ዋቅጋሪ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013