
የ30 ዓመቱ ግለሰብ እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 በአሜሪካዋ ኢዳሆ ኮሌጅ ከተማ አራት አብረውት የሚኖሩ ተማሪዎችን መግደሉን አመነ። ግለሰቡ ጥፋቱን ያመነው የሞት ቅጣትን ለማስቀረት ከአቃቤ ሕግ ጋር የገባውን ስምምነት ተከትሎ ነው። ብርያን ኮህበርገር የተባለው የቀድሞ የሦስተኛ ዲግሪ የወንጀል ምርመራ ተማሪ መላ አሜሪካንን ያስደነገጠውን ጥቃት ተከትሎ የፍርድ ሂደቱ ለነሐሴ ተይዞ ነበር።
ረቡዕ ዕለት በተካሄደው ችሎትም ዳኛ ስቲቭ ሂፕለር ግለሰቡ ከአቃቤ ሕግ ጋር የደረሰበትን ስምምነት ዝርዝር አንብበዋል። በዚህ የሞት ቅጣት በሚቀርበት ስምምነት ግለሰቡ ይግባኝ የመጠየቅ ወይም ቅጣቱ እንዲቀልለት መብት እንደማይኖረው ተጠቅሷል።
ካይል ጎንካልቭስ፣ ኤታን ቻፒን፣ ዣን ክርኖድል እና ማዲሰን ሞግን የተገደሉት ከሦስት ዓመታት በፊት በሞስኮ ከተማ ከዩኒቨርሲቲ ካምፓስ ውጭ በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ነው። ሌሎች በቤቱ ውስጥ የነበሩት ቢታኒይ ፈንክ እና ዲይላን ሞርትንስን ከጥቃቱ መትረፍ ችለዋል ተብሏል፡፡
የግድያው ሰለባዎች ስም ሲጠራ በፍርድ ቤቱ የነበሩ ሰዎች ስሜታዊ ሆነው የነበረ ሲሆን ግለሰቡ ግን ግድያውን መፈፀሙን ባመነበት ወቅት እንኳን ምን ዓይነት ስሜት አልታየበትም።
ረቡዕ ዕለት በተካሄደው ችሎት ዳኛው ግለሰቡን “ጥፋተኛ መሆንህን ያመንከው ጥፋተኛ ስለሆንክ ነው?” ሲሉ የጠየቁት ሲሆን ግለሰቡም ይህንን አረጋግጧል። ኮህበርገር ቀደም ብሎ ለተፈፀመው ጥቃት ጥፋተኛ አለመሆኑን ገልጾ ነበር።
ከዚያም ዳኛው በኮህበርገር ላይ የቀረበውን ዝርዝር ክሶች አንብበዋል። አንደኛው ክስ የአስር ዓመት እስር ሊያስቀጣ የሚችል ሲሆን አራቱ ክሶች ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ የግድያ ወንጀል ሲሆኑ በእድሜ ልክ እስራት ያስቀጣሉ። ኮህበርገር ለቀረቡበት ሁሉም ክሶች ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።
ዳኛው ፍርድ ለመስጠት ለአውሮፓውያኑ ሐምሌ 23 ቀጠሮ የሰጡ ሲሆን የእድሜ ልክ እስራት ይተላለፍበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
ተከሳሹ ከአቃቤ ሕግ ጋር በገባው “ጥፋተኝነቱን በማመን ቅጣቱን የማቅለል ስምምነት” ምክንያት በችሎት ወቅት ሊመለሱ የሚችሉ ግለሰቡ ለምን ጥቃቱን እንደፈጸመ የመሰሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ሊመለሱ አልቻሉም። በችሎቱ ወቅት አቃቤ ሕግ ቢል ቶምፕሶን ኮህበርገር ጥቃቱን ለመፈፀም አቅዶ እንደነበር እና ግድያውን ከመፈፀሙ ከስምንት ወር በፊት ስለት መግዛቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የስለቱ ሰገባ የተገኘ ቢሆንም ስለቱ ግን አልተገኘም። አቃቤ ሕጉ ወሲባዊ ጥቃትን የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንዳልተገኙ ገልጸዋል።
በዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ተማሪ የሆነው ኮህበርርገር ክስ የተመሠረተበት ከሁለት ዓመት በፊት ጥር ወር ላይ ነበር። ከጥቃቱ ሰላባዎች ጋር ግላዊ ግንኙነት እንዳለውም አይታመንም። ተከሳሹ ፔንሲልቫኒያ በሚገኘው የቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ሥር የዋለው የወንጀል መርማሪዎች ግድያው በተፈፀመበት ሥፍራ ባገኙትና ከቆዳ በተሠራው የስለቱ ሰገባ ላይ የዘረ መል ናሙና ካገኙ በኋላ ነበር።
የፍርድ ቤት ሰነዶች እንዳስረዱት ፖሊስ የኮህበርገርን ቤት በፈተሹበት ወቅት ቢላ፣ ጥይት፣ ጥቁር ጓንት፣ ጥቁር ባርኔጣ እና ጥቁር የፊት መሸፈኛ ጭንብል አግኝተዋል።
የተከሳሹ ተከላካይ ጠበቆች የዘረ መል ምርመራ ውጤቱ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ከማንሳት በተጨማሪ ችሎቱን ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ችለው ነበር። በተጨማሪም ግለሰቡ የኦቲዝም ተጠቂ ነው በሚል የሞት ቅጣት የብይኑ አካል እንዳይሆን ቢከራከሩም ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ ነበር።
እንደ የሞት ቅጣትን የሚመለከት መረጃዎች ማዕከል ከሆነ ኢዳሆ የሞት ቅጣትን ከሚፈቅዱ 27 የአሜሪካ ግዛቶች መካከል አንዷ ናት፤ ሆኖም ከአውሮፓውያኑ 2012 ወዲህ እንዲህ ዓይነት ቅጣት ተፈፅሞ አያውቅም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም