በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ከአገር የመውጣታቸው ሚስጢር የተለያየ ቢሆንም ሁሉም ግን በልባቸው ስለ አገራቸው ያላቸው ክብርና ናፍቆት ከፍተኛ ነው። ይህን አገርን የመውደድ ፍቅር የሚወጡት ለአገራቸው በሚያደርጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ጭምር ነው። በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማህበራዊ መስኩ በመሳተፍ አገራቸውን እያገለገሉ ያሉት ጥቂት አይደሉም። የአገር ዲፕሎማት ሆኖ በመቆም፣ በህጋዊ መንገድ ገንዘብ ወደ አገር ቤት በመላክ፣ በኢንቨስትመንት ዘርፉ በመሰማራት ለአገራቸው አለኝታ መሆናቸውን ደጋግመው አስመስክረዋል። አሁንም ተጠናክሮ እየቀጠለ ያለው ይሄው ነው።
ዲያስፖራው በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት አገሩን ከምን ጊዜውም በላይ ያሰበበት ወቅት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ከረጅም ዓመታት የባእድ አገር ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው የገቡ ሰዎች ቁጥር መብዛት አንዱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት አገር ከውስጥና ከውጭ በተወጠረችበት ጊዜ በገንዘብ፣ በሃሳብ፣ በእውቀት እንዲሁም የሚኖሩባቸውን አገራት ባለሥልጣናት የአገራችንን እውነት እንዲረዱ በማድረግ (በዲፕሎማሲ)፣ በአገራችን ላይ ጫና ሲደረግም አደባባይ ወጥተው በመቃወም በኩል የተወጡት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
የክፉ ቀን ወዳጅ ደግሞ በማንኛውም መልኩ በተለይም ችግር ሲያልፍ ማመስገን ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነውና በችግራችን ወቅት ከጎናችን የነበሩ፣ እናት አገራቸውን አስቀድመው አደባባይ የዋሉ፣ ሌሎችን ያስተባበሩ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ያሏቸውን እድሎች ተጠቅመው በጦርነቱ ምክንያት ችግር ውስጥ የገባውን ወገናቸውን አለሁልህ በማለት ላይ ታች ያሉ ሊመሰገኑ እነሆ ቀኑ ደረሰ።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት አብረውት ከፍ ዝቅ ሲሉ የነበሩ ለአገራቸው ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉትን የዲያስፖራ አባላትን ዛሬ የሚያመሰግኑበት ቀን ነው። “ኢትዮጵያ” ታመሰግናችኋለች ፤ ስራችሁም እውቅና ይገባዋል በማለት ተዘጋጅቷል። በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ ወንደሰን ግርማ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ እስከ አሁን ዲያስፖራው አገሩን ለመገንባት ያበረከተው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ወንደሰን፦ ሁሉም አገራት እንደሚያደርጉት ዲያስፖራው አንድ የእድገት አማራጭ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። በዚህም የእኛ ዲያስፖራዎች እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ እጅግ በጣም በርካታ ነው። በተለይም ያላቸውን እውቀት፣ ክህሎት፣ ቴክኖሎጂ እንዲሁም የገንዘብ አቅም በማቀናጀትና ወደአገር ቤት እንዲሸጋገር በማስቻል ነው። በሌላ በኩልም ዲያስፖራው በንግድ፣ በቱሪዝም ዘርፎች ላይ በመሰማራት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው።
የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ቤት ይልካሉ፤ በተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎን ያደርጋሉ፤ አገራዊ ጥሪዎችን በመቀበልና ፕሮጀክቶች ከፍጻሜያቸው እንዲደርሱ ድጋፋቸውን እያበረከቱም ነው። በኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ዲያስፖራውን ለመሳተፍ የሁለተኛው አስር ዓመት የዲያስፖራ ፖሊሲ ሰነድ ወጥቷል። በዚህ አማካይነት የተለያዩ ስራዎች እየተተገበሩ ከመሆኑም በላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ የዲያስፖራው ጉዳይ ከፍ ያለ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራበት ቆይቷል። ባለፉት አራት ዓመታት ደግሞ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶታል። በተለይም የለውጡ መንግሥት ወደ አመራር ከመጣ በኋላ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ፣ አውሮፓ ፣መካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ላይ ከሚገኙ ዲያስፖራዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። ይህ ውይይት “ ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ“ የሚል ነበር ፤ በዚህም ዲያስፖራው ከአገሩ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ለአገር ቤት የሚያስፈልጉትን ድጋፎች እንዲያደርግ በፊት የነበሩት ልዩነቶች እንዲወገዱ አስችሏል ማለት ይቻላል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ብዙ ለውጦች መጥተዋል።
በሌላ በኩልም አሁን አገራችን እየተከተለች ያለው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በመሆኑ ሚስዮኖቻችን ለዲያስፖራው እንደቤታቸው ሆነው በማገልገል ለሚፈልጓቸው ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎዎች የሚገናኙባቸው ቦታዎች ሆነዋል። ይህ ደግሞ ግንኙነቱ የተጠናከረ እንዲሆን እያደረገውም ይገኛል።
በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ዲያስፖራው የአገሩን ገጽታ በመገንባት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት (ፐብሊክ ዲፕሎማሲው) ላይ ተሳትፎ በማድረግ ዲጅታል ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘ የተውጣው ሚና ዲያስፖራው ከአገሩ ጋር ያለውን ቁርኝት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው።
በሰሜኑ ኢትዮጵያ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ አገራችን ላይ ሲፈጠሩ የነበሩ የውጭ ጫናዎችን በመመከት በኩል ያሳዩት ተሳትፎ ቀላል አልነበረም። በዓለም አቀፍ ደረጃም ከ 40 በላይ በሚሆኑ ትልልቅ ከተሞች ከ 70 ያላነሱ ሰላማዊ ሰልፎችን በማድረግ ለአገራቸው ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት ይችላሉ ብለው ድርድሩንም ከተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ወደ አፍሪካ ህብረት በማምጣት ተግባራዊ እንዲሆን አስችለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የአቋም መግለጫዎችን በማዘጋጀት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ሊያሳድሩ ያሉትን እንዲያውቁት በማስቻል የማሳመንና የመቀስቀስ (የሎቢና አድቮከሲ) ስራዎችን በመስራት የሎቢ ድርጅቶችን በመቅጠር የኢትዮጵያ እውነትን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳው ያልተገባው ጫና ደግሞ እንዲለዝብ ዲያስፖራው እጅግ በጣም በርካታ እንቅስቃሴዎችን ነው ያደረገው። ይህም ዲያስፖራው ከአገሩ ጋር ያለው ትስስር ጠንካራ እንዲሆን ለአገሩ ሊያስገኛቸው የሚችላቸውን እሴቶች ምን ያህል ሰፊ እንደሆኑም ያመላከቱ ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ ዲያስፖራው በኢንቨስትመንት እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ፤ በተለይ በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ወደ አገር በመላክ ኢኮኖሚውን በመደገፍ ያለው ሚና እንዴት ይገለጻል?
አቶ ወንደሰን፦ ዲያስፖራው ካከናወነው የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ (ፐብሊክ ዲፕሎማሲ) ባልተናነሰ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብን አሰባስበው ወደ አገር ቤት በመላክ አጋርነቱን አሳይቷል። ባለፉት አራት ዓመታት ከ ሶስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፎች ተደርገዋል። ለምሳሌ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፣ በጦርነቱ ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍና መልሶ ማቋቋሚያ በማድረግ አጋርነታቸውን ያሳዩ ሲሆን ፤ እዚህ ላይ በተለይም ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በዓይነትና በገንዘብ የመጣው ድጋፍ ተጠቃሽ ነው።
ሌላው ባለፉት አራት ዓመታት በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ወደ አገር በመላክ በኩልም ከ 15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ አገር ቤት ተልኳል። ይህ ገንዘብ ለብዙዎች የስራ እድል ለመፍጠር ምክንያት ሆኗል። በጠቅላላው ዲያስፖራው ያደረጋቸው ድጋፎች ሰፊ ከመሆናቸው አንጻር የተገለጹት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።
በየዓመቱ እቅድ አቅደን ከምንለከው አንዱና ግንባር ቀደሙ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር የሚላክን ዶላር ፍሰትን ማሳደግ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ሁለት አይነት ስራዎችን እናከናውናለን። አንዱ በአገር ቤት ፍሰቱን ለማሳደግ የሚያስችሉ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎቶች እንዲሁም ተመጣጣኝ ክፍያዎችን የሚጠይቁ ሥርዓቶች እንዲዘረጉ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር መስራት ሲሆን ሁለተኛው ሚሲዮኖቻችን ዲያስፖራው ዶላርን ወደአገር ቤት እንዲልክ የሚያበረታቱ ስራዎችን እንዲሰሩ ማስቻል ነው። በሁለቱ በኩል ጠንካራ ስራ እየሰራን ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሶስት ሚሊዮን የማያንስ ዲያስፖራ ያለን አገር ነን። ይህ አቅም ደግሞ ቀላል አይደለም። ባለፉት አራት ዓመታትም ከ 15 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ተልኳል። ይህንን በዓመት ስናሰላው ወደ 4 ሚሊዮን ዶላር ይጠጋል። ይህ ግን ከእኛ የሕዝብ ቁጥር ጋር ተቀራራቢ በሆኑት የአፍሪካ አገራት ከሚያገኙት አንድ አምስተኛ ነው። ስለዚህ በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ ይጠበቅበታል። ለማሳደግ ደግሞ ከሚሲዮኖቻችንና በአገር ውስጥ ካሉ ተቋማት ጋር መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ዲያስፖራው በዚህን ያህል መጠን ለአገሩ ድጋፉን አጋርነቱን ያረጋግጥ እንጂ አንዳንድ ጊዜ የድጋፍ ሁኔታው ሞቅ እና ቀዝቀዝ የሚልበት ምክንያት ምንድን ነው? ይህስ እንዳይሆን እንደ አገር ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
አቶ ወንደሰን፡- እንግዲህ ዲያስፖራዎቹን የምናያቸው ከአገራቸው ውጪ እንደሚኖር ኢትዮጵያውያን ነው። እናም በአገር ቤት በሚፈጠሩ ነገሮች ላይ እንደ ግለሰብ የተለያዩ አመለካከቶች ሊኖሯቸው ይችላሉ። በዚህም በሚፈጠሩ ነገሮች ደስ ሊሰኙም፤ ሊከፋም ይችላሉ ማለት ነው። ይህ ሁኔታ በስሜት ደረጃ የምንወስደው ነው። ነገር ግን ከአገራቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት እኛ እንደምናምነውም ሆነ የሌሎች አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሁኔታዎችን ተሻጋሪ መሆን እንዳለበት ነው። በየወቅቱ ከሚፈጠሩ ነገሮች ጋር የተያያዘ ሳይሆን ቋሚና ዘላቂ ተሳትፎ ነው የሚያስፈልገው። እስከ አሁን ያለው ተሳትፎ የአገርን ወቅታዊ ችግር ከመፍታት አንጻር የተሰራ ነው። ነገር ግን አገር ሊያድግ የሚችለው መደበኛ በሆነ የዲያስፖራ ተሳትፎ ብቻ ነው። በመሆኑ እውቀትና ቴክኖሎጂን በመደበኛነት በማሸጋገር በአገር ቤት ያሉ ተቋማትን አቅም በመገንባት ስራዎች በተቀላጠፈ ሁኔታ የሚሰሩበትን መንገድ በማመላከት በቱሪዝም ፣ በኢንቨስትመንት ላይ በመሳተፍና ሌሎችም እንዲሳተፉ በማስተዋወቅ መገለጽ አለበት። በመሆኑም እነዚህ ነገሮች እንዲሳኩ የማይዋዥቅ በአገር ቤት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተ ተሳትፎ ያስፈልጋል። እኛም እንደ ተቋም የምናምነው ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮውም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የዲያስፖራው ግንኙነቱ እንዳይዋዥቅ፣ በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ስሜት እንዳይሆን በተለይም በእናንተ በኩል የሚሰራው ስራስ ምን መልክ አለው?
አቶ ወንደሰን፦ ዲያስፖራው ከአገር ቤት ጋር ያለው ግንኙነት ዘላቂ አገራዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያደርጉ በርካታ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል። ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ለዛሬ የተዘጋጀው የዲያስፖራው የእውቅና መድረክም አንዱ ዓላማው ተሳትፏቸውን ወደመደበኛ ሁኔታ ማስገባት ነው።
ቅድም እንዳልነው ወቅታዊ አገራዊ ጥሪዎችን፣ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ከዲያስፖራው ሀብት ማሰባሰብ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ መስራት ከዚህ በፊት ሄደንበታል። ከዚህ በኋላ የሚኖረን ነገር ተሳትፏቸውን መደበኛ የማድረግና ዲያስፖራው በሚኖርበትና አገርና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር፣ ወዳጅነታችን እንዲጎለብት ባሉበት አገር ያሉ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንዲጎበኙ አምባሳደር ሆኖ የመስራት ጥሪ ነው እየቀረበ ያለው። እነዚህን ስራዎች እውን ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ ስትራቴጂክ ሰነዶች ደግሞ ተዘጋጅተዋል።
አዲስ ዘመን ፦ አገር ችግር ላይ በወደቀችበት ወቅት ዲያስፖራው ዲፕሎማት በመሆን የተጫወተውን ሚና እንዴት መግለጽ ይቻላል?
አቶ ወንደሰን፦ ያለፉት ሁለት ዓመታት በአገራችን ላይ ምን ያህል አላስፈላጊ ጫናዎች ሲሰነዘሩ እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ነው። እነዛ ጫናዎችን ለማስወገድ ደግሞ ዲያስፖራው ያደረጋቸው ጥረቶች በጣም ሰፋፊ ነበሩ፤ በ40 ትልልቅ ዓለም አቀፍ ከተሞች ከ 70 በላይ ሰልፎች ናቸው የተደረጉት። በሌላ በኩል ደግሞ በቲውተር ዲፕሎማሲ ዘርፍ የተሰራው ስራም በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። የትልልቅ ተቋማት አመራሮችን የአገራት ተመራጮችን በተለያየ መልኩ በማግኘት ያልተገባውን ጫና አቁመው ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታተ እንዲችሉና የኢትዮጵያ መንግሥትም የተጣለበትን መንግሥታዊ ሃላፊነት እንዲወጣ በማስቻሉ በኩል ከፍ ያለ ጥረትን ሲያደርጉም ነበር።
በዚህም የተፈለገውን ያህል ጫና ሳይፈጠር ኢትዮጵያም የራሷን ችግር በራሷ እንድትፈታ በማድረጉ በኩል ዲያስፖራው የተውጣው ሚና በጣም ትልቅ ነው። በነገራችን ላይ በተለይም በአሜሪካና በአውሮፓ ዜግነት አግኝተው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከጫና ነጻ ለማውጣት የሚኖሩበትን አገር ባለሥልጣናት በማስገደድ በኩል የተወጡት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለምሳሌ በአሜሪካን ምክር ቤት ቀርበው የነበሩት ሁለት ትልልቅ ህጎች ጸድቀው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ አይከብድም፤ ነገር ግን ዲያስፖራው ባሳደረው ጫና እነዚህ ሕጎች ተፈጻሚ ሳይሆኑ ለመቅረት ችለዋል።
በመሆኑም ዲያስፖራው ያከናወናቸው ስራዎች የኢትዮጵያን ህልውና ከመታደግ አንጻር እንዲሁም አሁን ለምንገኝበት የራሳችንን ችግር በራሳችን ለመፍታት ለቻልንበት አውድ አብቅቶናል ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ አንዳንድ የዲያስፖራ አባላት በተለይም በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉት አገሩን ለመደገፍ ቁርጠኝነት ያለውን ዲያስፖራ በመበረዝና የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨት ጫና ለማሳደር ሲሞክሩ ይስተዋላል። የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ለእነሱም ጭምር በማብራራት በኩል እየተሰራ ያለው ስራ ምን መልክ አለው?
አቶ ወንደሰን፦ ዋናው ነገር የዲያስፖራ ተሳትፎ ስራችን አግላይ አይደለም። ማለትም የነቃፊና ደጋፊ አካሄድን አንከተልም። ሁሉም የራሱ አቋም ሊኖረው ይችላል ፤ እንደውም ይህንን በማበረታታት ነው የምንጀምረው። ነገር ግን ተቃውሟችንም ሆነ ድጋፋችን ከአገር መሰረታዊ ጥቅም ጋር የተስማማ መሆን አለበት።፡ የምንደግፈው ነገር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከብራል ወይ? የምንቃወመውም ነገር ልክ እንደዛው ማለት ያስፈልጋል። በመሆኑም ዲያስፖራው ድጋፉም ሆነ ተቃውሞው ከአገሩ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የተቃኘ መሆን አለበት የሚለውን ነው የምናምነው። ይህንን ሃሳብ ለማስረጽም በርካታ ስራዎች ይሰራሉ።
ለምሳሌ የዲያስፖራ አገልግሎት በአገር ውስጥ ነው ያለው። ዲያስፖራው ደግሞ በተለያዩ የዓለም አገራት ነው የሚኖረው። በመሆኑም በዋነኝነት የምንሰራው ከኢትዮጵያ ሚሲዮኖች እንዲሁም የዲያስፖራ መሪዎች ጋር ነው። ከእነሱ ጋር በመሆን የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያያት እንዲሁም ሌሎች የቅርርብ ስራዎችን በመስራትና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ዲያስፖራው የጠራ መረጃ እንዲኖረው ይሰራል። ሌላው በቀጥታ ከዲያስፖራው ጋር ለመገናኘት ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ስራ ይሰራል። በዚህም እንደ “ዋት ሳፕ” (whatsApp) ና መሰል ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በየደቂቃውና በየሰዓቱ በመገናኘት የመረጃ ልውውጥ እናደርጋለን። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ተፈጠረ ለተፈጠረው ነገርስ የዲያስፖራው ሚና ምን ሊሆን ይገባል? በሚለው ላይ እንወያያለን። ነገር ግን ልዩነቶች ያሉና የሚጠበቁ ተፈጥሯዊም ናቸው። ዋናው ነገር ግን በንግግር እና በውይይት ለችግሮቻችን መፍትሔ መፈለግ ነው።
ሁልጊዜም ትልቁን አገራዊ ስዕል ማየት ለሁላችን በተለይም ለመጪው ትውልድ የሚጠቅመው የትኛው ነው? በልዩነቶቻችን ላይ ማተኮር ነው ወይንስ በጋራ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ተሰባስበን መስራት በሚለው ላይ እንወያያለን። ሁልጊዜም የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጉን ነገሮችን ይዘን መሄድ እንዳለብን እንግባባለን።
አዲስ ዘመን፦ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ጦርነት በርካታ ውድመት ተከስቷል። እነዚህን ሁኔታዎች ወደቀድሞ ገጽታቸው ለመመለስ (በመልሶ ግንባታ) የዲያስፖራው ሚና ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
አቶ ወንደሰን፦ ይህ ትክክል ነው፤ ከሰላም ስምምነቱ ጋር በተያያዘ አንድ እየተሰራ ያለ ስራ ቢኖር የወደሙ ተቋማትን መልሶ ማቋቋም ነው። ከግንባታና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ደግሞ በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል። በዓይነት የተሰበሰበው ደግሞ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይገመታል። በመሆኑም ዲያስፖራው አሁንም ድጋፉን እንደቀጠለ ነው። ነገር ግን እቅዳችን ከሰላም ስምምነቱ ቀጥሎ ወደመደበኛ የዲያስፖራ የተሳትፎ ስራዎች መግባት ስለሆነ እዛ ውስጥ የሚያጋጥመን ደግሞ መልሶ ማቋቋም ነው።
በመሆኑም አሁን በመልሶ ማቋቋም ስራው ላይ ከገንዘብ ባሻገር የተለያዩ የሥነ ልቦና ህክምናዎችና ሌሎች ድጋፎች ስለሚያስፈልጉ ዲያስፖራው እውቀቱንና ክህሎቱን ወደአገር ቤት አሻግሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወደቀደመ ማንነታቸው እንዲመለሱ በማድረግና በማቋቋም ማገዝ ይጠበቅበታል። ይህም የሚሆነው ባለበት አገር ገንዘብ እየሰበሰበ የተሰበሰበው ገንበዘብ ደግሞ ለመልሶ ማቋቋሙ መሰረታዊ የሆኑ ተቋማትን እንዲገነቡ በማስቻል በተለይም ከጤናና ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀትና የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ስራ ተገብቷል።
በመግባቢያ ሰነዱ መሰረትም ዲያስፖራው የወደሙ የትምህርትም ሆነ የጤና መሰረተ ልማቶችን መልሶ በተለይም በተሻለ ሁኔታ ገንብቶ በቁሳቁስ አሟልቶ ለማስረከብ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአገር ባለውለታ ለሆኑ የዲያስፖራ አባላት የእውቅና ፕሮግራም ያለው ጠቀሜታ፤ እንዲሁም ለዚህ የምስጋና ፕሮግራም የተመረጡ ሰዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ምን ነበር?
አቶ ወንደሰን፦ ከላይ የዘረዘርናቸው ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ ያደረጉ ዲያስፖራዎች ናቸው። እውቅናውን የሚያገኙት የዲያስፖራ አባላት በተለይም በእውቀትና ክህሎት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በገጽታ ግንባታ፣ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በሀብት አሰባሰብ ላይ የተሳተፉ ናቸው። እነዚህ በጣም በርካታ ቢሆኑም አሁን ላይ የእውቅና ዝግጅቱ የተደረገው ከ40 ለሚበልጡ የዲያስፖራ አባላት ነው። እነዚህ ሰዎችን ከላይ በተዘረዘሩት ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎን በማድረግ በማስተባበር ላበረከቱት አስተዋጽዖ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋላች ስራችሁ እውቅና ይገባዋል ለማለት ነው።
በሌላ በኩልም ዛሬ እነዚህን አካላት እውቅና መስጠታችን ሌላውን ማበረታታትና ማነሳሳት ስለሆነ በተለይም አሁን ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የእሳት ማጥፋት ስራን ትተን ወደመደበኛ የዲያስፖራ ተሳትፎ ለመግባት የምናደርገውን ጉዞ ለማጠናከር እንደ ድልድይም የሚያገለግለን ነው።
አሁን የመጡብንን ጫናዎች ተረባርበን በማሸነፍ አንዱን ምዕራፍ ዘግተናል ከዚህ በኋላ ወደመደበኛ የዲያስፖራ ተሳትፎ ስራችን መግባት አለብን ሌሎች አገራትም ቢሆን የተቀየሩት በዚህ መንገድ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። በመሆኑም ዲያስፖራው በቋሚነት ክህሎትና እውቀትን ወደ አገር ቤት በማሸጋገር በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ዘርፍ ላይ በስፋት በመሳተፍ ራሳቸውም ኢንቨስት በማድረግ ሌሎችም መጥተው በኢንቨስትመንቱ ላይ እንዲሰማሩ በመቀስቀስና አገራቸውን በማስተዋወቅ የአገራቸውን ገጽታ በመገንባት በሚኖሩበት አገርና በአገራቸው መካከል እንደ ድልድይ ሆነው በማገልገል የአገራት ግንኙነት እንዲጠናከር ሚናቸውን እንዲወጡ ምቹ መደላደልን የሚፈጥር ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ወንደሰን፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም