‹‹የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ›› የሚለው የአሸባሪ ሕወሓት ሰነድ በወርሃ ነሃሴ 2014 ዓ.ም ሾልኮ መውጣቱ ይታወሳል። በጽሁፉም ከአጋሮቹ ጋር የሚከተለውን ስትራቴጂ አስመልክቶ የሚተነትን ሲሆን፤ በየደረጃው ለሚገኝ አመራር ግብዓት እንዲሆን የቀረበ ስለመሆኑም መረጃው ያሳያል።
በዚህ ሰነድ እንዴት ኢትዮጵያን መቀመቅ እንከታለን ሲልም ሕወሓት ሴራ ለመሸረብ ሞክሯል። የሁኔታ ትንተና፤ መልካም ዕድሎችን ማስፋትና ፈተናን መቀነስ በሚለው ርዕሱ ስር ‹‹የልዩነት ነጥቦችን በማሕበራዊ ሚዲያ በማጉላት አሃዳዊው የዐቢይ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት እንዳይኖረው መሸርሸር ያስፈልጋል ሲል ያትታል።
በሌላ በኩል፤ ይሄ ጠባብ እና ተስፋፊ ሃይል በፍጹም የትግራይ አጋር ሊሆን እንደማይችል መረዳት ያስፈልጋል። ይሁንና ይህንን እውነታ በግልጽ ባለማሳየት በተመረጡና የጋራ ስራ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጥቂት አጀንዳዎች በጥንቃቄ ሊቀረጹ ይገባል። በግልጽም ይሁን በስውር በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መብዛታቸው የአማራ ክልል መንግሥትን የሚፈትን እንቅስቃሴ ይሆናል፤ ይህም ለትግራይ ካለው ፈተና ይልቅ መልካም እድል ይዞ የሚመጣ አጋጣሚ በመሆኑ ሚዛን የሚደፋ ነው። ስለሆነም ይህ ግንኙነት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያዝ ይገባል›› ሲል ይመክራል።
በአጠቃለይ በሰነዱ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ መስተጋብሮችን በማናጋት የሥልጣን ጥማችን እንወጣለን ይላል የአሸባሪው ሕወሓት ሰነድ። በተለይም አማራን በማጥላላት ሥነልቦናውን ሊጎዳ ይችላል ብሎ ባሰበው መልኩ ይገልጻል፤ በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሕወሓትን አፈጣጠርና ታሪካዊ ሥሪቱን በማጣቀስ ከታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን ከሕወሓት ሾልኮ በወጣው ሰነድ በተደጋጋሚ የአማራ ሕዝብን እንደ ጠላት ይፈርጃል። ለመሆኑ አማራን በተለየ ሁኔታ ለማየት ያስገደደው ታሪካዊ ሁኔታ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ ?
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- እንግዲህ ይህን በሁለት ክፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው በሕዝብ ደረጃ የትግራይ እና የአማራ ሕዝብ በታሪክ ጥላቻ ነበረው ወይ ብለን ማየት አለብን። በታሪክ ስንመለከት እነዚህ ሁለት ሕዝቦች በጣም ጠንካራ የሆነ ሃይማኖታዊ፣ ማሕበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያላቸው ናቸው ። ሌላው ቀርቶ ተራው ሕዝብ ወይም ዜጋውን ተትን ባለአባቶችን ስንመለከት እርስ በእርስ ሲጋቡ የኖሩ ናቸው። ከግዛት ባለፈ ወዳጅነት ነበራቸው። ስለዚህ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ምንም የተለየ ጥላቻ የለም።
አሁን ከሕወሓት ሾልኮ በወጣው ሰነድ አማራ ላይ የሚንጸባረቀው ጥላቻ የመጣው ከምንድን ነው ስንል የራሱ ታሪክና አካሄድ አለው። ይሄ የሕወሓት ቡድን እንደ ቡድን ሲደራጅ ያመጣው ነው። የብሄር ፖለቲካ ሲነሳ ማጠንጠኛዎች አሉት። ለሥልጣን ለመብቃት አንድ ነገር መፈልግ አለበት። ወይንም ደግሞ የጦስ ዶሮ የሚሆን አካል ይፈልጋል። ስለዚህ ሕወሓትን ያቋቋመው ቡድን ጠላት ብሎ የተነሳው አማራን ነው ። ለራሱ ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ብሄር አማራ ጠላትህ ነው ብሎ ነው የተነሳ።
ሁለት ደረጃ ነበረው የመጀመሪው የአማራ ገዥ መደብ ነው የሚል አቀነቀነ። ከዚህም አለፍ ሲልና ትግል እያቀነቀነ ሲሄድ ለሌላኛም ጠንቀኛ ብሎ ለማሳየት አማራን መፈረጅ ጀመረ። ምንጩ ከሕዝብ ግንኙነት ሳይሆን ከፖለቲካ አደረጃጀቱ የመነጨ ነው። ይህ ነው በመላ ኢትዮጵያ 1983 ዓ.ም ጀምሮ በየሚዲያ እና ሕዝብ የተቀነቀነው። ይህ ሆን ተብሎ ታስቦ የተሰራበት ነው።
ሰሞኑን ሾልኮ የወጣው ሰነድም ያንን የማስቀጠል ነው። ሌላው ደግሞ ከአስተዳደራዊ ወሰን ጋር ጠላት ብሎ የሚመለከተውም የአማራን ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያዊ አቋም በመያዝና ኢትዮጵያን በማቀንቀኑ የትኛው ወገን ነው በሚለው ላይ ሲያነጣጥሩ አሁንም ዓላማቸው አማራን ሕዝብ የማዳከም ስልቶች ተንጸባርዋል።
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪ ሕወሓት ቡድን መግለጫዎች በብዛት አማራን በማስፈራራት ፤ ጥላቻን በመግለጽ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ሰሞኑን እንደሚሰማው፤ የአማራ ሕዝብ ወዳጃችን ነው የምናወራርደው ሂሳብ የምንነቅለው ሰንኮፍም የለም ሲሉ ይደመጣሉ። ይህን የሚያደርጉት ለምን ይመስሎታል ?
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- እንግዲህ እነዚህን መግለጫዎች ልብ ብሎ መመልከት ይገባል። ፕሮፓጋንዳ በሁሉም ቦታ እና ፖለቲካ ዘንድ አለ። የሕወሓት ፕሮፓጋንዳ እኩይ ፕሮፓጋንዳ ነው። ይህ አንዱን በሌላው ላይ ለማስነሳት የሚጠቀምበት ስልት ነው። እውነተኛ ፕሮፓጋንዳ ግን አንድን በጎ ነገር ይዞ ሕዝብ እንዲያውቀውና እንዲቀበለው ማድረግ ነው።
ስለዚህ የሕወሓት መግለጫዎች እኩይ ነገሮችን ይዞ የተነሳ ነው። በዚህ ውስጥ ወጥ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ማካሄድ አይቻልም። በዚህ የእኩይ ፕሮፓጋንዳቸው ውስጥ አማራን ጠላት አድርጎ ፈርጇል። ሌላ ጊዜ ወዳጅ አድርገው ይሄዳሉ። ለመሆኑ እየጨፈጨፉት የነበረው አማራ ሕዝብን አልነበረም። ሌላ ቦታ ሲያስጨፈጭፉ የነበረውም ይህን ሕዝብ አይደለም። ስለዚህ ጉራማይሌ ብቻ ሳይሆን እኩይ ሲሆኑ የሚታይ ባህሪ ነው። ሕወሓቶች ከተፈጥሮ ባህሪያቸው የተነሳ ይህን የሚያደርጉ ናቸው። የሕወሓት ሰዎችም በባህሪቸው በጣም ውሸት ያበዛሉ። ለዚህም ሲሉ አንድ ጊዜ ጠላት ብለው የፈረጁትን ሌላ ጊዜ ወዳጅ አድርገው ይገልጹል። አሁን የጀመሩት አማራ ሕዝብን በቃላት መሸንገል ነው።
የሕወሓት ሰዎች መግለጫዎች እንድ ሕዝብ አማራን ጠላት ብሎ ከፍረጃ ካልወጣ እና ሕወሓት አማራ ላይ ያለውን አቋም ካልቀየረ መግለጫዎች ለውጥ አያመጡም።
አዲስ ዘመን፡ በሰነዱ ከተገለጹት ውስጥ በአማራ መካከል ያለውን ልዩነት ማስፋትና ክልልነት ጥያቄዎች ጋር የሚነሱትን በማንሳት ግጭት ማቀጣጠል የሚለውን እሳቤ እንዴት አዩት?
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ጦርነት የሚያነሳ አካል አንድ ትልቅ ሥራዬ ብሎ የሚሰራው ነገር አለ። ይህም ዲሞብላይዜሽን ነው። ይህ ማለት ሕዝብና መንግሥት አንድ እንዳይሆን ማድረግ ነው። በሁለቱ አቅም እንዳይፈጥር ክፍፍል እንዲኖር ይሰራሉ። አንደኛው ሕዝብና መንግሥትን መነጣጠልና ማቃቃር አጀንዳ መፍጠር ላይ ይተጋሉ። ሁለተኛው ደግሞ ሕዝብም እርስ በእርሱ መጠራጠርና መከፋፈል እንዲፈጠር ይፈልጋሉ። እነዚህ ስሜቶች እንዲኖሩና አንድነት እንዳይኖር ማድረግ ነው። በአሁኑ ወቅትም ጦርነት ለመጀመር ያነሳሳቸው ይህን የተሳሳተ የፖለቲካ ትንተናና ስሌት በመያዝ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታም በአማራ ክልል ፋኖዎች ስለታሰሩ፤ በመንግሥትና በፋኖዎች ብሎም በሕዝብ መካከል ክፍተት ስላለ ሕዝብን ለማነሳሳት አይቻለውም። ስለዚህ አቅማችንን አጠናክረን ብናጠቃ የሚመክተን አካል የለም በሚል ስሌት ነው። ስለዚህ እየተሰራ ያለውና አሸባሪው ህወሓት እየተጠቀመ ያለው ይህን ስሌት ነው። በአንድ በኩል በፕሮፓጋንዳ ፋኖን የመኮነን ሥራ ይሰራል። በሌላ በኩል ደግሞ የክፍተት ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም ይፈልጋል። ይህን በግልጽ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ያለ ቡድን ነው።
ሁለተኛው ደግሞ አካባቢያዊ አስተዳደሮች ላይ ሕዝብ እምነት እንዲያጣ ማድረግን ዓላማ አድርገው እየሰሩ ነው። ለምሳሌ የአማራ ክልልን የልዩነት ነጥቦችን ወስዶ የማዳከም ሥራ ነው እየሰሩት ያሉት። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝባዊ ተቀባይነት እንዲያጣ ማድረግ ነው። በዚህም መንግሥት ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ እንዲሆንና ይህን አጠናክረው እንደሚሰሩ የታወቀ ጉዳይ ነው።
የፖለቲካ ነበልባል የሚያስነሱ ጉዳዮችን ለራሳቸው ጥቅም ለመቀየር ይጥራሉ። ለምሳሌ በደቡብ አካባቢ ያለውን ጉዳይ በተለይም ከክልል አደረጃጀት ጋር ያለውን ሁኔታ ለማገዝ የቆሙ መስለው ነገሮችን ማባባስ ይፈልጋሉ። በዚህም እንቅስቃሴያቸው ወትሮም እኛ እንሻል ነበር ለማለት የሚሰሩት ነው። ወቅታዊ የፖለቲካ ንፋስ የሚያመጣቸውን ነገሮች በደንብ ነዳጅ በመስጠት መንግሥትን በተለያየ ነገሮች መወጠር፣ አቅሙን ማዳከም፣ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ እንዲወርድ የማድረግ ስልትና ስትራቴጂ ነው። ዋነኛ ሥራው ወይንም ድምር ውጤቱ የመንግሥትን ተቀባይነት ማሳጣት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሕወሓት የሴራ ሰነድ ውስጥ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነትን ማባባስና የኢኮኖሚ አሻጥር ማባባስና አርሶ አደር ምርት እንዳይሰበሰብ ማድግ የሚል አለው። ይህን ከቡድኑ የቀድሞ ባህሪ ጋር እንዴት ያዩታል?
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- እንደሚታወቀው ክረምት ማለት በተለይም ደግሞ ከሰኔ ጀምሮ እስከ ታህሳስ ያለው ለአብዛኛው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ወሳኝ ወቅት ነው። ይህ በብዛት የስራና የምርት ወቅት ነው። የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህልውና በዚህ ወቅት ላይ የተመሰረተ ነው። አርሶ አደሩ የሚለፋበት ጊዜ ነው። ስለዚህ ጦርነቶችንና ግጭቶችን መቀስቀሱ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። ዝምብሎ አመቸኝ ብሎ አይደለም የተነሳው። ሌላው ሕዝቡን በመንግሥት ላይ ማስነሳት የሚቻልበት ትልቁ ነገር የኢኮኖሚ ዋስትናውን ዜሮ ማድረግ ነው።
ስለዚህ አሸባሪ ሕወሓት በአማራ ክልል ላይ ያለው ስትራቴጂ የእርሻ ስራ በወቅቱ እንዳይሰራ ማስተጓጎልና እርሻውን በሙሉ ማደናቀፍ ነው። አርሶ አደሩን ከሥራ ውጭ ማድረግ ነው። በተለያየ መንገድ ተፈናቃይ ማድረግ ነው። ይህ ሥራ በጣም አደገኛ ነው። ከርሃብና ችጋር በላይ የሰው ልጅ የሚፈራው ነገር የለም። ስለዚህ ይህን እንደ ፖለቲካ ስልት መጠቀም ይፈልጋሉ። ህወሓትም ይህን እያረገ ነገሮችን ማናጋት ይፈልጋል። እንደፖለቲካ ስልት መጠቀም ይፈልጋል፤ በእቅድም የሚሰራው ነው። ርሃብ ሲኖር ሰዎች በመንግሥት ላይ ያምፃሉ። በዚህ ጊዜ ግለሰብና መንግሥትን ማናጋት ይፈልጋሉ። ይህን እንደ አዲስ ስትራቴጂ እየተጠቀሙበት ነው። ይህን ባለፈው ዓመትም አድርገው አሳይተዋል። ባለፈው ዓመት በወረራም አረጋግጠዋል። ሌላው ቀርቶ ኢኮኖሚ ዋስትና የሆኑ እንስሳትን ጭምር ገድለዋል። እንስሳት ፖለቲካውን አያውቁም። ይህ ዋነኛ ዓላማው ኢኮኖሚውን ማናጋትና መሰረቱን ማዛባት ነው። ስለዚህ ድንገት የተካሄዱ ሳይሆን በደንብ ተጠንተው የተካሄዱ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ውይይት እፈልጋለሁ ቢልም፤ አፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ አፍሪካዊ ተቋማትን ያጣጥላል። ይህን ለምንድ ማድረግ ፈለገ?
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ሕወሓት ከመጀመሪያው ሲነሳ በአፍሪካ ደረጃ የነፃነት ቡድን አይደለም። እዚህ ግባ የሚባል ቡድንም አይደለም። ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ የዓርነት እንቅስቃሴዎችና ጦርነቶችን አካሂደዋል። የሕወሓት ከዚህ አኳያ ሲታይ ምንም ስያሜ ለመስጠት የሚያስቸግር ነው። ስለዚህ ለመሰል ቡድን በርካታ አፍሪካ ሀገራት የዲፕሎማሲም ሆነ የፖለቲካ ድጋፍ አይሰጡም ነበር።
ለሕወሓት ቡድን ዓላማ እና አካሄድ ግልጽ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩት ጥቂት አገራት ሲሆኑ እነዚህም ግብጽ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ናቸው። ሶማሊያ በትጥቅም በምንም ሳይሆን ፓስፖርት በመስጠትና በመሳሰሉት ያግዙ ነበር። ይህን ሲያደርጉ የነበረውም በወቅቱ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ካላቸው ቁርሾ እና የውሃ ፖለቲካም ጋር በተያያዘ ነው። ከዚህ በተረፈ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለሕወሓት ፖለቲካ ባይተዋር ናቸው፤ ምንም አይፈልጉም።
ከእነዚህ ይልቅ ሕወሓት ገና ጡጦ መጥባት ሲጀምር ጀምሮ ‹አይዞን አለን› ሲሉ የነበሩት ምዕራባውያን ናቸው። ይህም የሆነው እነዚህ የሕወሓት ደጋፊዎች የነበሩትም ምዕራባውያን የራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ስለነበራቸው ነው ። ወደ ሥልጣን ለመምጣት ዋዜማው ላይ ሆኖም፤ ሥልጣን ላይ ከመጣ በኋላ እና ከሥልጣን ማግስትም ሕወሓት ያደረገው የአፍሪካ ፖለቲካ ጉዳዩ አይደለም። ከአፍሪካውያን ጋር አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አይሰራም። ይልቁንስ በፖለቲካም በኢኮኖሚም ትልቅ ድጋፍ አድርጎና ይበጀኛል ብሎ የወሰደው አውሮፓውያንንና አሜሪካን ያሉ የምዕራባውያንን ሃይል ነው። በእርግጥ አሁንም እየደገፉት ያሉት እነርሱ ናቸው። ይሁንና ኢትዮጵያ ያካሄደችውን አፍሪካ ወንድሞቻችን በጣም በደስታ የተቀበሉት ጉዳይ ነው።
ስለዚህ አሸባሪው ሕወሓት አፍሪካ ሕብረትን በአደራዳሪነት ያለመቀበሉ ምክንያት፤ አፍሪካውያን ችግራቸውን የሚመለከቱት ከሃቅ አኳያ በመሆኑ ነው። ከግብጽ እና ሱዳን በስተቀር አንድ የአፍሪካ ሀገራትን ብንወስድ የአፍሪካ ችግር ይፈታ የሚሉት እውነታውን ይዘው ነው። ሁኔታዎችን የሚያዩት ደግሞ እንደ አፍሪካ ሕብረት ሀገርነቷ ነው። ሌላው ደግሞ ከኢትዮጵያ የሚያጋጫቸው ነገር የለም። ምዕራባውያን ግን ብዙ ጥቅሞችና የፖለቲካ ፍላጎቶችን ያራምዳሉ። ይህን በደንብ ሸክፎ እና ታዛዥ ነኝ ብሎ ራሱን ያዘጋጀው ሕወሓት ነው።
ሕወሓት ብሄራዊ ጥቅም የሚባል ነገርን አያስብም። ሕወሓት ከፖለቲካ ጥቅሙ ውጭ፤ ብሄራዊ ጥቅምን ከግምት ውስጥ አስገብቶ አያውቅም። ብሄራዊ ጥቅምን የማያስቀድም ደግሞ እንኳን ለሀገር ለራሱ ህልውና መቀጠሉም አጠራጣሪ ነው። ይህ ቡድን ለማነው የሚቆመው፤ እንዴት ነው ሀገርን ሊወክል የሚችለው፣ እንዴት ነው ሕዝብን የሚጠቅመው? ስለዚህ ሕወሓት የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ አያነሳም። የምዕራባውያን ጉዳይ ለማስፈጸም ምንም አያቅማማም። እነርሱ ደግሞ ይህንን በጣም ይፈልጉታል። ሕወሓት ያላግጣል። አፍሪካ ትልቅ አቅም አለው። ምዕራባውያንን ድረሱልኝ፤ ይህን ሆንኩ ብሎ ማለቃቀስ፤ የረድዔት ድርጅቶችን የሚጣሩበት ምክንያት ሥር መሰረታቸውና ባህሪያቸው ይህ ስለሆነ ነው። ለዚህም ሲባል ይፈልጉታል።
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪ ቡድን ከሚያሳያው ባህሪ በመነሳት ለትግራይ ሕዝብ መብት፣ ነፃነት፣ ጥቅም፤ እኩልነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ማበብ የቆመ ነው ማለት ይቻላል?
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ሕወሓት አይደለም ለትግራይ ሕዝብ ለራሱ ውስን ቡድን በአግባቡ የሚቆም አይደለም። የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ እንደፈለጉ የሚያሾሩት፤ የሚያደርጉትና የፖለቲካ ፍላጎታቸውን የሚያራምዱበት ነው።
ለትግራይ ሕዝብ ቢቆም ኖሮ፤ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው ኢትዮጵያዊነትና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ መኖርን ነው። ተጋብቷል፤ ተዋልዷል። የኢኮኖሚ ትስስር አለው፤ የሚጋራው ማሕበራዊ ሥነ-ልቦና አለው። በጣም ሰፊ ነው። በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ ንብረት አፍርቶ፤ ትዳር መስርቶ ሥራ እየሰራ የሚኖር ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ትግራይ እንዲህ ነው እያሉ ሌላ ፖለቲካ ማንሳት ለትግራይ ሕዝብ መቆም አይደለም።
በመጀመሪያ የፖለቲካ ነፃነት የተነፈገው የትግራይ ሕዝብ ነው። በመጀመሪያ የመደራጀት ነፃነትና መብት የተነፈገው የትግራይ ሕዝብ ነው። ትግራይ ውስጥ የእውነት ነፃነት እንዲመጣ፣ ዴሞክራሲ እንዲያድግ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን አለፍ ብሎም ትግራይ ውስጥ ሕዝቡ ነፃነት ይኑረው ካልን ለምን የሕዝብ ጥያቄ ማፈን አስፈለገ?
ነፃ በሆነ መድረክ ላይ የፖለቲካ መድረክ እንዲፈጠር ለምን አያደርግም? ትልቁ የሕወሓት ችግር ለትግራይ ሕዝብ ከእርሱ ውጭ ወይንም የእርሱን አጀንዳ የሚያቀነቅን አምሳያ የሆነ የፖለቲካ ኃይል ካልሆነ በስተቀር ሌላ እንዲበቅል አይፈቅድም።
ይህን ወትሮም ሲሰራ ነበር። ከ2010 ዓ.ም በፊትም ሆነ ከዚያን በኋላ ይህን ሲሠራ ነበር። ስለዚህ ለትግራይ ሕዝብ ቆመ የሚባለው ነገር፤ ራሱ የትግራይ ሕዝብ ያውቀዋል። ለትግራይ ሕዝብ ቆሜያለሁ ቢልም ‹‹ሆድ ሲውቅ ዶሮ ማታ›› የሚሉት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪ ቡድን በዚህ ደረጃ የትግራይ ሕዝብን የሚጨቁን ከሆነ ሕዝቡ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- የትግራይ ሕዝብ ማድረግ ያለበት ለሕወሓት ማርከሻውና ፍቱን መድሃኒቱ ራሱ ነው። በእርግጥ በሃይል ተገዶ የተያዘ ሕዝብ ነው ይታወቃል። የሕወሓት አደረጃጀት ቀላል የሚባል አልነበረም። የትግራይ ሕዝብ በግድ አጥሮ ነው የያዘው። ሆኖም መሆን ያለበት በትግራይ ክልል የሚኖርም ሆነ ከሀገር ውጭና በሌሎች ቦታዎች የሚኖር የትግራይ ተወላጅ ይህንን መኮነንና ሕወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ እና ከትግራይ የፖለቲካ መድረክ እንዲገለል ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለበት። እንዲሁም ከሀገር ውጭ የሚኖረው የትግራይ ተወላጅ ይህን ማወቅ አለበት፤ በጥቂት የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መፈታት የለበትም። እዚህ ላይ ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- የረድኤት ድርጅቶች፣ ምዕራባውያንና ሌሎችም አሸባሪ ሕወሓት አማራ እና አፋር ክልሎችን የሚፈጽውን ወረረራና ግፍ ብሎም ሕፃናትን ለጦርነት ሲማግድ በዝምታ ያልፋሉ። ይሁንና በመንግሥት የመከላከል እርምጃ ሽንፈት ሲከናነብ ሁሉም በአንድ ላይ ይረባረባሉ፤ መግለጫ ያወጣሉ፤ ያግዛሉ። ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገ?
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ይህን ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ያውቃሉ። ሕወሓት ለሕዝብ የመጣን እርዳታ ለጦርነት ሲያውል ይህ የመጀመሪው አይደለም። ወትሮም ገና እየታገልኩ ነው ሲልም 1977 ዓ.ም ያደረገው ነው። በረድዔት ሥም ደግሞ ሲዘርፍ ነበር። በ1977 ዓ.ም ሆነ አሁንም እያደረገው ነው። እርዳታው ለትግራይ ሕዝብ ደርሷል ወይ ለሚለው፤ በማያጠራጥር ሁኔታ አከፋፋዩ ሕወሓት ነው፤ ሰጪና ነሺውም ሕወሓት ነው። ስለዚህ ለደጋፊውና ለሚዋጋላት ይሰጣል። በአጭሩ ሕወሓት መፈክር አውጥቷል። ይህም ‹‹ለመብላት መዋጋት›› የሚል ነው። ወጣቱንና ሕፃናቱን የሚያሰልፈው በዚህ መልኩ ነው።
ምዕራባውያንን ለምን አልኮነኑትም ለሚለው፤ ዓላማቸውን ያውቁታል። በአንድ በኩል እየሰሩ ያሉትም ይህ እንዲሆን ነው። የሰው ልጅ መራብ፣ ሰብዓዊነትና የሰው ልጅ መጎሳቆል ሙሉ ለሙሉ አስገድዷቸው ነው የሚል እምነት የለኝም። ስለዚህ ይህንን ምዕራባውያን ያውቁታል። ሁለተኛው የሕወሓትን አጥፊነት ሳያውቁት ቀርተው አይደለም። አማራ እና አፋር ክልል ሲወረር ጉዳያቸው አይደለም። ይህ ለምን ሆነ ስንል የፖለቲካ ዓላማቸው ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያ ጠንክራ እንዳትወጣ ይፈልጋሉ። ነገ ከነገ ወዲ ጎልታ ከወጣች ለአፍሪካም ዓርዓያነቷን ብሎም በአካባቢዋ ብሄራዊ ጥቅሟን እነደምታስከብርና በምስራቅ አፍሪካ የሚኖራት ሚና እንዲኮስስ ብሎም ከሌሎች ጋር ተባብራ ሰርታ ከፍ እንዳትልና ሁነኛ ኢትዮጵያን ስለማይፈልጉ ነው። ስለዚህ የምዕራባውያን ዝምታው ምንድን ነው ቢባል ነገሩን እያወቁ ዓይን እንደመጨፈን፤ ጆሮ እንደመድፈንና አፍን ከመዝጋት የሚመጣ ነው። ይህ አሁን ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም በነበሩት የታየ ነው። ሀገር ሲሆን ለምሳሌ ሕወሓት ሀገርን በሚያስተዳድርበት ወቅት ከኤርትራ ጋር ጦርነት ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ ጉዳይ ሲነሳ ያደሉት የነበረው ወደ የት ነው? ሕወሓት ሥልጣን ላይ በነበረ ጊዜ እና ኢትዮጵያ ሲል ከኤርትራ ጋር እኩል ማዕቀብ ይጥሉ ነበር። አሁን ግን ብቻውን ሲሆንና የእነርሱን ዓላማ ሲያስፈጽም ደግሞ ዝም ይባላል። የሕወሓት ጭፍጨፋ አይነሳም። ይህን እያወቁ ማውገዝ አልፈልጉም። ይሁንና የኢትዮጵያ ኃይል ሲጠናከር ምንም ማድረግ አይፈልጉም።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍላችን ሥም እናመስግናለን።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን መስከረም 2 / 2015 ዓ.ም