
በልጅነቱ ያስተናገደው አብሮ የመኖር የመረዳዳት ባህል በልቡ ትልቅ ቦታ ነበረው። በመሆኑም በአንድ ወቅት የገና በዓልን ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ለማክበር የበዓል ማድመቂዎችን ለማሟላት መማከር ጀመሩ። ለሻሎም ግን በዓሉ ከፌሽታ ይልቅ በአካባቢው ከሚመለከታቸው በመንገድ ላይ የሚያድሩ ህጻናት በእምነት ተቋማት በር ላይ ምጽዋት ጠብቀው ከሚቀመጡ ጋር በህብረት ማሳለፍ ፍላጎቱ ነበር።
በጊዜው ከክፍል ጓደኞቹ በእድሜ ትንሹ ቢሆንም በሃሳቡ ተስማምተው ከየቤታቸው ያሰባሰቡትን የምግብ ግብዓቶች ተባብረው በመሥራት ነዳያንን በማብላት ሲያሳልፉ ይህ አጋጣሚ ለትንሹ ልጅ በሕይወቱ እጅግ የተደሰተበት ጊዜ ነበር።
ሻሎም አርአያ የዛሬው የወጣቶች እንግዳችን ሲሆን ህልሙን እውን ለማድረግ በሄደባቸው ርቀቶች የወጣቶችን የፈጠራ አቅም እውቅና መስጠት እና ማበረታት ያለው ትልቅ ቦታ እንዲሁም የእርሱን ጉዞ አጋርቶናል።
ሻሎም ትውልድና እድገቱ አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፤ ወደትምህርት ቤት ሲሄድ ሁልጊዜ የሚያያቸው ነዳያን ልቡን ይነኩት ነበር። የሕይወት ዓላማውም ለብዙዎች መድረስ የሚችል የርዳታ ድርጅት መክፈት እንደሆነ አወቀ። ሻሎም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲገባ 17 ዓመቱ ነበር። በዩኒቨርሲቲው ወደሶስተኛ ዓመት ሲሸጋገርም ይህንን ህልሙን እውን ለማድረግ ተጨማሪ ትምህርት መማር ቀጠለ።
ትምህርቱንም ሲያጠናቅቅ ከፍተኛ ውጤት የነበረው በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ መመህር ሆኖ የመቀጠል እድልን አግኝቷል። በዚህ ውስጥም የምንጊዜም ህልሙ አይዞን የርዳታ ድርጅትን እውን አድርጎ ብዙዎችን ማገዝ ነው።
በየጊዜው በትምህርት ራስን ማሻሻል እና ማሳደግ ሻሎም በእጅጉ የሚያምንበት ሲሆን፤ ባገኘው የውጭ የትምህርት እድል መሠረት በውጭ ሀገር ሁለተኛ ዲግሪውን መማር ቻለ። ‹‹በውጭ ሀገር ቆይታው የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ ወደ 17 የሚጠጉ ዓለምአቀፍ ሰርተፍኬቶች፣ ሁለት ዓለምአቀፍ ዲፕሎማዎች በሚማርበት ሀገር ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመሄድ ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሟል። ታዲያ ሻሎም ለትምህርት ወደ ሌላ ሀገር ከመጓዙ በፊት ለ10 ዓመት ያክል ለማስተማር ለራሱ ቃል ገብቶ የነበረ ሲሆን፤ ሲመለስም ቃሉን ባለመርሳት በተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኮሌጆች በመዟዟር ለ10 ዓመት ያክል በመምህርነት አገልግሏል።
ሻሎም የመምህርነት ሙያው ህልሙ የሆነውን አይዞን ፋንውዴሽን ለመመሥረት ትልቅ እድል ፈጥሮለታል። የተባበሩት መንግሥታት የልማት እቅዶች የሚያተኩርባቸው የትምህርት፣ ጤና ንጹህ የውሃ መጠጥ እና የወጣቶችን ማብቃት ፋውንዴሽኑ ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ነጥቦች በማጥናት የአይዞን ፋውንዴሽን የረጅም ዓመት እቅድ አብሮ አዘጋጀ።
‹‹ከማስተማሩ ጎን ለጎን የአይዞን ፋውንዴሽንን ለመመስረት ሃሳብ ነበረኝ ነገር ግን ሕጋዊ ለማድረግ ያለው ሒደት ረጅም በመሆኑ ቀስ በቀስ ለማድረግ ወሰንኩኝ።›› በዚህ ሒደት ውስጥም እንደ ልጆቹ ለሚያያቸው ተማሪዎቹ ህልሙን በማጋራት አይዞን የመጀመሪያ አባላቱን አገኘ። አይዞን የሚለው ቃል የተመረጠበት ምክንያትም ተስፋን የሚሰጥ ነው ሲል ይገልጸዋል። አይዞን በሲቪል ማህበረሰብ እውቅናና ሕጋዊነትን አግኝቶ በመመዝገብ ሥራ ከጀመረ ሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል።
በአሁኑ ሰዓትም ከ500 በላይ የሚሆኑ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ የሚገኙ በጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች ይገኙበታል። የበጎ ፍቃደኛ ክፍሉ የጥናትና ምርምር ቡድን፣ የኢንጅነሪንግ ቡድን፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የፈጠራና ኪነጥበብ፣ የስልጠናና ጥናት ቡድን፣ የቴክኖሎጂ ቡድን እንዲሁም የሕግ ጉዳይ ቡድን በውስጡ ይገኛሉ።
ፋውንዴሽኑ ከተመሠረተ በኋላ ከሚያተኩርባቸው ማህበራዊ ዘርፎች የመጀመሪያው ትምህርት ነው። የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ያለባቸውን ችግር በማጥናት የትምህርት ቤት ቁሳቁሶችን ከማሟላት ጀምሮ በጥሩ ሁኔታ ላይ የማይገኙ ትምህርት ቤቶችን በተሻለ መልኩ መልሶ ገንብቶ ለህጻናት ተማሪዎች ምቹ አድርጎ ያስረክባል። ሌላኛው በአይዞን ፋውንዴሽን ትኩረት የተሰጠው ፕሮጀክት የንጹህ የውሃ መጠጥ አቅርቦትና ንጽህና ነው። ይህም ትምህርት ቤቶችን መገንባት ብቻ ሳይሆን ምቹ የመማርያ ሥፍራዎችን ለሴት ተማሪዎች መፍጠር ላይ ያለመ ነው።
በዚህም በእያንዳንዱ ሥራዎች ላይ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በሚያደርገው እንቅስቃሴ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያን አብሮ ያቀርባል። ሌላኛው ፕሮጀክት ወጣቶችን እና ሴቶችን ማብቃት ነው። ትምህርት ቤቶችን በመሥራት ሒደት የመጀመሪያው ስፍራ በጉራጌ ዞን የተመለከቱት ነበር። ትምህርት ቤቱ ሰፊ የመማሪያ ስፍራ ይኑረው እንጂ ተማሪዎች የሚማሩበት ክፍል ግን ለመማር በፍጹም ያልተመቸ ነበር።
ታዲያ የአይዞን የኢንጂነሪንግ ክፍል ቦታውን በመጠቀም የትምህርት ቤቱ ዲዛይን ምን ሊመስል ይገባል የሚለውን በንድፈ ሃሳብ ካስቀመጠ በኋላ ከመማሪያ ባለፈ የተማሪዎች ቤተ-መጽሀፍት፣ ቤተ-ሙከራ ማረፊያ፣ መጫወቻ የያዘ እንዲሆን በእቅዱ ውስጥ አስቀምጦታል። ቀጣዩ ትምህርቤቶችን አቅም በፈቀደ መልኩ ለመሥራት ወደ አፋር አሉልአባድ የሚባል ቦታ ላይ ተማሪዎች በድንኳን ውስጥ ሆነው የሚማሩበትን ቦታ አገኘ።
‹ወደ ትምህርትቤቱ ለመምጣት በረሃ አቋርጠው ነው የሚመጡት፤ ከመጡ በኋላ ደግሞ የአንደኛ ክፍል ሁለተኛ ክፍል በአንድ ላይ በድንኳኑ ውስጥ ተማሪዎች ጀርባ ተሰጣጥተው ነበር የሚማሩት። ይሄ በጣም አሳዛኝ ነው።›› ይህንን ችግር ከተመለከተ በኋላ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሰባሰብ ትምህርትቤቱን መሥራት ላይ ሻሎም አብሮ እንደ ግንበኛ ተሳትፎበታል።
አይዞን ፋውንዴሽን ትምህርትቤቱን በሚሠራበት ወቅት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እና ባለሙያዎችን ከራሱ አሟልቶ የሚወስድ በመሆኑ በአንድ ክልል ከአንድ በላይ ትምህርት ቤት የመሥራት እቅድ አለው። ቀጣዩ ፕሮጀክት በጦርነት የተጎዱ ሶስት ክልሎች ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ‹‹ከጦርነት ወደ ትምህርት ቤት›› ኢኒሼቲቭ ነው ።
ከዚህም በተጨማሪ በአይዞን ፋውንዴሽን ውስጥ ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ ‹‹ትችላለች›› የተሰኘ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁ ሴት ተማሪዎች በሥራው ዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ስልጠናዎች ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ይሰጣል። በዚህም በርካታ ወጣቶችን በማሰልጠን ከተለያዩ ምሳሌ መሆን የሚችሉ የረጅም ዓመት የሥራ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ልምድ እንዲወስዱ የሚያደርግ መድረክ ጭምር መሆኑን ሻሎም ይናገራል።
ስኬት በአይዞን ፋውንዴሽንም ሆነ በሻሎም እይታ በቁጥር ብቻ አይለካም፤ ይልቁንም በተለያዩ ስልጠናዎች ተጠቃሚዎች ሆነው ሕይወታቸውን የቀየሩ እናቶች፣ ወጣቶች፣ አካልጉዳተኞች የስኬት የለውጥ ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።
ታዲያ እንደዚህ ያሉ የልማት ሥራዎች፣ መልሶ የመጠገን እንቅስቃሴዎች፣ ወጣቶች እይታቸውን እንዲያሰፉ የሚደርጉ የስልጠና እድሎች ከፍተኛ የወጣት ቁጥር ለሚገኝባት እንደ ኢትዮጵያ ላለች ሀገር አስፈላጊ መሆኑን ሻሎም ጠቁሟል።
‹‹ወጣቶች ልዩ የፈጠራ አቅም የሥራ ፈጠራ ፍላጎት ፖሊሲን ወደሚጨበጥ ሒደትና ለውጥ መቀየር፤ አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር የተዘጋጁ ናቸው። ነገር ግን ይላል ሻሎም እነዚህ ወጣቶች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ቀይረው ለውጥ ማምጣት እንዲችሉ ለማድረግ የመነሻ ካፒታል ችግር አለባቸው። በተጨማሪም በሥራቸው እውቅና ማግኘት፣ ሃሳባቸውን የሚመዝኑ መድረኮች፣ ሀገር አቀፍ እንዲሁም ዓለምአቀፍ መድረኮች ላይ የመገኘት እድላቸው እምብዛም ነው።
ሀገር አቀፍም ሆነ ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር በጥምረት መሥራት አስፈላጊነት የሚነሳው እዚህ ጋር ስለመሆኑ የሚገልጸው ሻሎም የወጣቶችን ሥራ ፈጠራ የሚያበረታቱ እና ራሳቸውን የሚገልጹበት መድረኮችን በማዘጋጀት አወዳድረው እና መዝነው ሃሳባቸውን ወደተግባር ቀይረው ወደሥራ የሚገቡበትን የገንዘብ ድጋፍ ማመቻቸት የሚያስችል ዓለምአቀፍ እውቅና ያለው የውድድር መድረክ መለመድ ይኖርባቸዋል።
በሀገራችንም ሥራ ፈጣሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማስቻል ያለሙ ውድድሮች መኖራቸውን ገልጾ እንደ ዛይድ ለዘላቂነት ሽልማት የሥራ ፈጠራ ውድድር ከሽልማትም በላይ የሆነ እድልን እንደሚፈጥር ሻሎም ገልጿል። እ.አ.አ በ2008 የተመሠረተው ይህ ዛይድ ለዘላቂነት ሽልማት በዓለምአቀፍ ደረጃ ላሉ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች በማወዳደር ፈጠራን እውቅና በመስጠት የገንዘብ ሽልማት በማዘጋጀት ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ወደፊት በማምጣት ለውጥ ፈጣሪ እንዲሆኑ ያስችላል።
መቀመጫውን በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ያደረገው ይህ ተቋም ላለፉት 17 ዓመታት በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ወጣቶችን በማወዳደር እና በየደረጃው የገንዘብ ሽልማት ያበረክታል። የምግብ ደህንነትን በማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ውሃ፣ ጤና እና ትምህርት የሚያወዳድርባቸው ዘርፎች ሲሆኑ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማትን ከማቅረብ ተግባራዊነታቸው እንዲረጋገጥ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጭምር ሻሎም ገልጿል።
ይህ የዛይድ ሽልማት ውድድር ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እና ፋብሪካዎች ትልቅ እድል የሚፈጥር ሲሆን ከዚህ ቀደም ከናይጄሪያ፣ ህንድ፣ ባንግላዲሽ፣ ታንዛንያ፣ ጋና እና ሌሎች ሀገራት ላይ የሚገኙ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆነው ነገር ግን የሥራ ሃሳብ ያላቸው በቴክኖሎጂ በየአር ንብረት ለውጥና ሌሎች ዘርፎች አካባቢያቸውን የሚቀይር ሃሳብ የነበራቸውን ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ አስችሏል።
17 ዓመት እድሜ ያስቆጠረው ይህ ድርጅት በአሁኑ ሰዓት አዲስ ውድድር ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህ ውድድር ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሚሳተፉበት እንዲሆን በአይዞን ፋውዴሽን መስራች ወጣት ሻሎም በኩል የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል።
‹‹ውድድሩ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለሚገኙ ወጣቶች በሙሉ የቀረበ ነው። ከዚህ ቀደምም በአፍሪካ ሀገራት የተሳተፉ አሸናፊዎች ነበሩት። ተደራሽነት፣ ዘላቂነት ላይ መሥራት የሚሹ ወጣቶች ሊሳተፉበት የሚገባ ሲሆን ሃሳብ፣ ዓላማ፣ ጥረት እና ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል እና ህብረተሰቡ ውስጥ ቢተገበር መፍትሄ የሚሰጥ ሊሆን ይገባል።››
ለዚህም እንደ ወጣት እና ለብዙዎች ተጽዕኖ መፍጠር የቻለ ፋውንዴሽን መስራች ሻሎም አባባል ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሃሳብ እጥረት የለባቸውም፣ እውቅና፣ ድጋፍ እና ዓለምአቀፋዊ የሆነ ትስስርን ይሻሉ ይላል።
በሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም