የሂውጂን ዳይመንድ ሊግ የ10ሺ ሜትር ፍልሚያ

የአትሌቲክሱ ዓለም ነገ ሙሉ ትኩረቱ ወደ አሜሪካ ኦሪገን ግዛት ሂውጂን ዳይመንድ ሊግ ይሆናል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከአርባ ሀገራት የተውጣጡ ከ300 በላይ ክዋክብት አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች በሀይዋርድ ፊልድ በሚካሄደው የሂውጂን ዳይመንድ ሊግ መፋለማቸው ነው።

50 ዓመቱን ነገ በሚያከብረው በዚህ ውድድር በርካታ የዓለምና የኦሊምፒክ ሻምፒዮኖች እንዲሁም የክብረወሰን ባለቤቶች በተለያዩ ውድድሮች የሚያደርጉት ትንቅንቅ በጉጉት ይጠበቃል። ከዓለም አትሌቲክስ የውድድር መርሐ ግብሮች እየጠፋ የሚገኘው የ10ሺ ሜትር ፉክክር ነገ ሂውጂን ላይ በወንዶች የምሥራቅ አፍሪካ የርቀቱን ፈርጦች ያገናኛል። ውድድሩ ለኬንያውያን ለ2025 የቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና እንደመምረጫ የሚያገለግል ነው። ኢትዮጵያውያንም በዚህ ፉክክር በርቀቱ የተሻለ ፈጣን ሰዓት አስመዝግበው ሀገራቸውን በዓለም ሻምፒዮና መወከል እንዲችሉ የሚያደርግ በመሆኑ ተጠባቂ አድርጎታል። ዩጋንዳውያን አትሌቶችም ቀላል ተፎካካሪ እንደማይሆኑ ተገምቷል።

በ10ሺ ሜትሩ ፍጥጫ የተሻለ ሰዓትና ውጤት ያላቸው ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ12 ኬንያውያን አትሌቶች ጋር ለቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና ሚኒማ ለማሟላት ብርቱ ትንቅንቅ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በፓሪስ ኦሊምፒክ በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ወጣቱ ኮከብ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ትልቅ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶታል። 26:31:13 የበሪሁ የርቀቱ ምርጥ ሰዓት ሲሆን፣ ነገ በሂውጂን ከሚፎካከሩት አትሌቶችም ቀዳሚ ያደርገዋል።

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የርቀቱ አሸናፊ አትሌት ሠለሞን ባረጋ በ26:34:93 ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት የያዘ አትሌት ሲሆን ከሀገሩ ልጅ በሪሁ ጋር የሚያደርገው ፉክክር ከወዲሁ ትኩረት ስቧል። በዘንድሮው የኢትዮጵያውያን ዓመት ከወራት በፊት በስፔን ሲቪያ የመጀመሪያውን የማራቶን ውድድር አድርጎ 2:05:15 በሆነ ሰዓት ያሸነፈው አትሌት ሠለሞን ባረጋ ወደ መም ውድድሮች ትኩረቱን በመመለስ የተሻለ ሠዓት ለማስመዝገብ ሲዘጋጅ ሰንብቷል።

የአትሌት ሠለሞን ባረጋ አሠልጣኝ ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሸቦ “ሠለሞን ለወራቶች ወደትራክ ተመልሶ ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፤ ወደ አሜሪካም የሚጓዘው ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ሠዓትም ማምጣትን አቅዶ ነው፤ በጣም ጥሩ የሚባል አቋም ላይም ነው” በማለት ለሐትሪክ ስፖርት ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በረጅም ርቀት የመም ውድድሮች ተስፋ ሰጪ ብቃት እያሳየ የሚገኘው ሌላኛው ወጣት ኢትዮጵያዊ አትሌት ቢኒያም መሐሪ 26:37:93 ሰዓት ያለው ሲሆን በዓለም ሻምፒዮና ሀገሩን ለመወከል ነገ ሂውጂን ላይ ብርቱ ተፎካካሪ ይሆናል።

ታደሠ ወርቁ በ26:45:91፣ ሐጎስ ገብረሕይወት በ26:48:95 ከባድ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት መዝገቡ ስሜ ለተሻለ ሰዓትና ለአሸናፊነት ከሚፎካከሩ ኮከቦች መካከል ተጠቃሽ ሆኗል። ስድስቱ ኢትዮጵያውያን ኮከቦች ከኬንያውያኖቹ ቤንሠን ኪፕላጋት፣ ኒኮላስ ኪፕኮሪር እና ከሮኪቶ ኪፕኩሩይ ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ከዳይመንድሊግ አሸናፊነት ባሻገር የዓለም ሻምፒዮና ትኬት የሚቆርጡበት በመሆኑ ከወዲሁ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You