
በሲዳማ ማኅበረሰብ አለባበስ እና አጋጌጥ ከዕድሜ፤ ከጾታ እና ከማኅበራዊ ኃላፊነት አንጻርና ደረጃ ጋር በእጅጉ ይሰናሰላል። ተወላጆቹ በተለይም ስለዚሁ ባሕል የቀደመ እና ጥልቅ እውቀት ያላቸው የዕድሜ ባለፀጋዎች እንደሚናገሩት፣ይሄው አለባበስና አጋጌጥ በራሱ ጌጡን ስላደረገው እና ልበሱን ስለለበሰው ሰው የሚያንፀባርቁት የተለየ ባሕሪ አላቸው።
የለበሰችውን እና ያጌጠችበትን ወይም የለበሰውን እና ያጌጠበትን በማየት ብቻ የለባሽዋን እና ያጊያጭዋን ወይም የለባሹን እና ያጊያጭዋን ዕድሜ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ደረጃ ማወቅ ይቻላል። በሲዳማ ማኅበረሰብ አለባበስ እና አጋጌጥ የሀብት እና የተደላደለ አኗኗር ምቾት ወይም ድሎት ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድም ይገልፃሉ።
በሴቶች እና በወንዶች መካከል ጎላ ያሉ አለባበስ እና የአጋጌጥ ልዩነቶች ስለመኖራቸው የሚጠቅሱት የእድሜ ባለፀጋዋ ሀሪቱ ዋቃዮ፣ ከዚህ የዕድሜ እና ደረጃ ባሻገር በተጨማሪ ሌላ ዓይነት የአለባበስና አጋጌጥ ስርዓት ያለ ስለመሆኑም ያስረዳሉ። ይሄውም የጀግንነት ተግባር የፈፀሙ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለያየ ኃላፊነት እና ማዕረግ ያላቸው ግለሰቦች የሚዋቡት የአለባበስና አጋጌያጥ ሁኔታ ነው ይላሉ። እነዚህ ግለሰቦች በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለየ ኃላፊነት ያላቸው ስለመሆናቸውም ያነሳሉ።
የሴቶች አለባበስ
የእድሜ ባለፀጋዋ ሀሪቱ እንደሚናገሩት፣ የሴቶች አለባበስ እና አጋጌጥ ፈርጀ ብዙ ነው። አለባበሳቸውን ለአብነት ወስደን ብናይ በአዋቂ፤ በሕፃናት እና በልጃገረዶች እየተባለ የሚሄድ የራሱ ሥርዓት ያለው ነው። ለምሳሌ፦ የሴት ሕፃናት አለባበስን ብናይ ሴት ሕፃናት ከበግ ቆዳ ተለፍቶ የሚዘጋጅ የበግ ለምድ ይለብሳሉ። ወጣት ልጃገረድ ሴቶች ደግሞ ከውስጥ በብሔረሰቡ አጠራርና በሲዳምኛ ቋንቋ›› ጎሎ›› የሚባል ልብስ እንዲለብሱ ይደረጋሉ። ከላይ ደግሞ ከጥጃ ቆዳ ተለፍቶ የሚዘጋጅ አላባሽም ይደርባሉ።
የልጃገረዶቹ ልብስ ከጥጥ የሚሠራ ሲሆን፣ ከላይ እስከታች ወጥ ሆኖ የሚሰፋ ነው። እንደልብ ለመራመድ እንዲያስችልም ዳርና ዳሩ ክፍት ይተዋል። ወጣት ልጃገረዶች የሚለብሱት ቆዳ የተለያዩ ቀለማት ባላቸው አዝራሮች (ቁልፎች) ጨሌዎችና ፈትሎች ያሸበረቁም ናቸው።
የሲዳማ ልጃገረድ ከጋብቻ በፊት ቀኝ ጆሮዋን አትበሳም። ነገር ግን ከጋብቻ በፊት ግራ ጆሮዋን ተበስታ የተለያዩ ጌጣጌጦች ማድረግ ይፈቀድላታል። በተጨማሪም አንዲት ልጃገረድ ስትዳር ››ዱዳ›› የሚባል ከቆዳ የሚሰራ ልብስ ትለብሳለች። ባለቤቷም የሴቶች የክት ልብስ የሆነውን ከበሬ ቆዳ የሚሰራ ልስላሴ ያለው ልብስ ወይም በባሕሉ ››ወዳሬ›› እየተባለ የሚጠራውን ልብስ ይገዛላታል። ልጃገረዲቱ ልብሱን ከሁለት ታጥፈዋለች። አጥፋም ከቆዳ በሚሰራ መቀነት በማሰር እጥፋቱን ወደ ታች ለቅቃ ትለብሰዋለች።
የኑሮ ደረጃቸው የተሻሉ የሀብታም ልጅ የምትባለው ልጃገረድ አለባበስ ደግሞ ከዚህ ይለያል። ከእናቷ በስጦታ የሚሰጣትን ››ወዳሬ›› ታጥቃና በልዩ ልዩ ጌጣጌጦች የተሸቆጠቆጠ ለምድ ትደርብበታለች። የሙሽርነት ጊዜዋን ጨርሳ ስትወጣም የክት ልብሷን ››ወዳሬ›› ለብሳ እና በተለየ ሁኔታ ያጌጡ እና በባሕሉ ››ቆሎ›› እና ››ቆንጦሎ›› የተሰኘ ልብስ ደርባ በአደባባይ እንድትታይ ትሆናለች።
የአዋቂ ሴቶች ባሕላዊ አለባበስ
በማኅበረሰቡ አዋቂ ሴቶች የሚለብሱት ልብስ ይለያል። ልብሱም ››ጎርፋ ቱባ ዱዳ›› ይሰኛል። በተጨማሪም ቦኬ፤ወዳሬ የተሰኙ የክት ልብሶች አሏቸው። ››ቱባ እና ዱዳ›› የሚባሉት በአዘቦት ቀናት እንዲሁም በሥራ ቀናት የሚለበሱ አልባሳት ናቸው። ››ጎርፋ›› ከተሰኘው አልባሳት በቀርም ሁሉም አልባሳት ከወገብ በታች በመታጠቅ የሚለበሱ ሲሆኑ፣ ››ጎርፉ›› የተሰኘው ልብስ በተለያዩ ጨሌዎች ያጌጠ እና ሴቶች ወደ አደባባይ ሲወጡ ከላይ የሚደርቡት እጅግ ለዓይን ሳቢ እና ማራኪ የሆነ የክብር ካባ ነው።
በብሔረሰቡ በአብዛኛው እንደተለመደው ሴቶች በተለያዩ ጌጣጌጦች ያሸበረቀ ››ቆሎ›› እና ››ቆንጥሎ›› የሚለብሱበት ሁኔታ አለ። ይሄም ከፊት እና ከኋላ በማጣፋት የሚለበስ ሲሆን የሲዳማ ሴቶች የድሎት ምልክት የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። በዚህ አይነቱ አለባበስ የምትታወቅ ሴትም ››ለማ ላሞ ለንደቲ›› ተብላ ትወደሳለች። ትርጉሙ ‘ቅምጥልና ባለሁለት ለምድ ናት‘ እንደማለት እንደሆነም ሀሪቱ ያስረዳሉ።
በብሔረሰቡ በትልቅነቷ እና ሴቶችን በማስተባበር ሚናዋ እውቅና ያላት ሴት ደግሞ ››ጋርቾ›› የተሰኘ ባሕላዊ ሥነ ሥርዓቶችን ለማስፈጸም ወደ አደባባይ ስትወጣ ››ወዳሬ›› ትለብሳለች። በልዩ ልዩ ጌጣጌጦችም ታሸበርቃለች። ካባም ትደርባለች። በፀጉሯም ላይ አበባ ትሰካለች። በተጨማሪም የስልጣኗ ተምሳሌት የሆነችውን በትርም ትይዛለች። ይህችን ሴት ተከትለው የሚወጡ ሴቶችም በበኩላቸው ‹‹ዱዳ ወይም ቱባ›› ይለብሳሉ። ከላይ ደግሞ ‹‹ቦኬ›› የተባለውን መለስተኛ ካባ የሚደርቡበት ሁኔታ አለ።
የሴቶች አጋጊያጥና የፀጉር አሰራር ደረጃዎች
በማኅበረሰቡ ዘንድ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ሴት ሕፃናት የሚሰሩት የፀጉር ስሪት ከአዋቂዎች ይለያል። ሕፃናት ፀጉራቸው ዙሪያው ተላጭቶ ማህል ላይ ቁንጮ ያሳድጋሉ። የተለያየ መልክ ያላቸው እና ለዓይን ማራኪና ሳቢ የሆኑ ዛጎሎች፤ጨሌዎች እና ዶቃዎች ይደረግላቸዋልም። አንዳንዴም ቁንጮው ተፈትቶ ቅቤ እየተቀባ እርስ በርሱ እንዲያያዝ በማድረግ ጉድሮ ወደ የሚባል የፀጉር አሰራር ዓይነት ይቀየራል።
ጉድሮ የተደረገላቸው ሕፃናት እየተሯሯጡ በሚጫወቱበት ወቅት ጉድሮው ወዲያ እና ወዲህ እየተወዛወዘ ለሕፃናቱ ልዩ ውበት ያጎናጽፋቸዋል። በጉድሮ የፀጉር አሠራር የተዋቡ ሕፃናት ያላቸው እናቶቻቸውም የልጄ ጉድሮ መዓዛው አወደኝ ወይም ጠራኝ በማለት በዜማ መልክ ልጆቻቸውን ያሞካሻሉ።
በብሔረሰቡ ለጋብቻ ያልደረሱ ልጃገረዶች ከፊት ያለውን ፀጉራቸውን እየተላጩ ቀሪውን ወደ ኋላ የሚሠሩበት ባሕል አላቸው። የእነዚህ ልጃገረዶች ፀጉር ዙሪያውም በክር ይሰፋል። ይሄም የፀጉር አሠራር በማኅበረሰቡ ዘንድ ‹‹ጎዳያ›› በመባል ይታወቃል። ጎዳያ በማኅበረሰቡ ባሕል እና ወግ ሥርዓት ዘንድ አንዲት ልጃገረድ ለጋብቻ የደረሰች ወይም የታጨች መሆኗን ከሚገልፁ ምልክቶች መካከል አንዱም ነው።
ጉዳያዋን ቅቤ ተቀብታ ስታበጥረው የንጋት ጤዛ ያረፈባት ትመስላለች። እንዲህ ተውባ በመንገድ ስትሄድም ጓደኞቿ በፋሮ ዘፈን፦ ‘የእገሊት ጎዳያ የማለዳ ጤዛ ይመስላል” በማለት ውበቷን እየገለፁ በዜማ ያሞካሽዋታል። ወጣት ልጃገረዶች ከፀጉር አሠራሩ በተጨማሪ በእግር እና በእጅ ጣቶቻቸው ላይ ከመዳብ የሚሠሩ ቀለበቶች በማድረግ የሚያጌጡበት ሁኔታ አለ። በግንባራቸው ዙሪያም በልዩ ልዩ ቀለማት ያሸበረቁ ጨሌዎች እና አዝራሮች ወይም ቁልፎች ያስራሉ። እንዲሁም በተለያዩ መጠን እና ቅርጽ የተደረደሩ ጨሌዎችን፤ ዶቃዎችን በአንገታቸው በማጥለቅ ይዋቡባቸዋል።
ልጃገረዶቹ ፊታቸው የበለጠ ደምቆ እና ተውቦ እንዲታይም ጉንጫቸው ላይ ጭረት መነቀስ ነው። አንዳንዶቹ ጭረት ሳይሆን ‹‹ቁራ›› በእግራቸው ባት ላይ የሚነቀሱበትም የአጊያጌጥ ባሕል አላቸው።
በሲዳማ ፍቼ ዘመን መወለወጫ በዓል ወቅትም እጃቸውን እና እግራቸውን እንሶስላ በመሞቅ ይበልጥ ደምቀው እና ተውበው ለመታየት የሚጥሩበት ሁኔታ አለ። ወደ አገባች ሴት አጋጌጥና አለባበስ ባሕል ስናልፍ በብሔረሰቡ ቋንቋ አጠራር ‹‹ድኮያ›› የሚባል አሠራር ትሠራለች። የፀጉር አሠራሩ ከማሕል እኩል በመከፈል ወደፊት እና ወደ ኋላ ይታሸማል። ዳር እና ዳሩም በወፍራም ክር ይቀመቀማል። ከዛም በጃንጥላ ቅርጽ ይጎነጎናል። በቅርብ ያገባች ሴት ከሆነች ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በሲዳማ ዘመን መለወጫ ፍቼ ጨንበለላ በዓል ማግሥት በአማቷ ታጅባ በሲዳማ ቋንቋ አጠራር ‹‹ጉድማሌ›› በአማርኛ ደግሞ አደባባይ ወደሚባለው ትወጣለች።
ሴቲቱ በዚህ ጊዜ የምትሠራው እና ተውባ እና ደምቃ የምትታይበት ባሕላዊ የፀጉር አሠራር ደግሞ ‹‹ሹራ›› ይሰኛል። በተጨማሪም ወጣት ሴቶች ‹‹ሾዶለሳ፤ ታይ ሺሻ፤ ጎንቢሳ እንዲሁም ማኖ›› የሚባሉ ባሕላዊ የፀጉር አሠራር አይነቶችን በመሠራት ተውበውና አምረው ደምቀው ይታያሉ። የወለደች ሴት በፊናዋ በባሕሉ አራስ ቤት እለችም ሆነ ከአራስ ቤት ስትወጣ ‹‹ቦንኮዬ›› የተባለ የፀጉር አሠራር በመሥራት ትዋባለች።
ጠና ያሉ የሲዳማ ተወላጅ ሴቶች በበኩላቸው በባኅላቸው መሰረት ‹‹ሾዶሎ እና ናኖ›› የተሰኘ የፀጉር አሠራር የሚሠሩበት ሁኔታ አለ። ሴቶቹ ዕድሚያቸው እየገፋ ሲመጣ እና ልጆቻቸው ለጋብቻ በሚደርሱበት ወቅትም ‘ቡፍ” የሚሰኝ እና በወፋፍራሙ ተገምዶ ወደ ታች የሚሠራ የፀጉር አሠራር አዘወትረው ይጠቀማሉ። ልጆችን አድርሰው የዳሩ ሴቶች በፊናቸው በባኅላቸው የፀጉር አሠራር መሰረት ፀጉራቸውን አሳጥረው በመቆረጥ ጎፈሬ በማድረግ ያበጥራሉ። በብሔረሰቡ ባሕል እነዚህም ሴቶች ‹‹ኩዶኖ›› በመሰኘት ይታወቁና ይጠራሉ።
ልጅ አድርሰው የዳሩ ሴቶች ግን በባሕሉ ፀጉራቸውን መቆረጣቸውም ሆነ መሠራታቸው በባሕሉ እንደነውር ተደርጎ ይቆጠር። እዚህ ጋር የሲዳማ ሴቶች በባኅላቸው መሰረት አንባር፤ጨሌ፤ዶቃ፤ዛጎል የዝሆን ጥርስ፣ ቀከለበት እና ሌሎች ቁሶች ለማጋጌጫነት ይጠቀማሉ። እነዚህም በብሔረሰቡ ቋንቋ ”ኢራ‘ በሚሰኝ የወል (የጋራ) መጠሪያ ስም ይታወቃሉ።
የሴቶች የአጊያጌጥ ሁኔታ ከማኅበራዊ ደረጃቸው እና ከባላቸው ማኅበራዊ ደረጃ ጋር በእጅጉ ይቆራኛል። ወጣት ሴቶች በፊናቸው ከጨሌ፤ ከዶቃ እና ከመዳብ የተሠሩ አንባሮች እና ቀለበቶች በማድረግ ያጌጣሉ። ትልልቅ ሴቶች በፊናቸው ባኮ እና ጉሜ የሚባሉ ከመዳብ እና ነሐስ የሚሠሩ አንባሮችን በክንዳቸው ላይ ያደርጋሉ።
የጀግና ሚስት የሆነች ሴት ደግሞ በብሔረሰቡ ቋንቋ እና በባሕሉ ‘ላካና ሳዮ” የተሰኙ ሰፊ እና ከባድ የሆኑ አንባሮችን በክንዳቸው ላይ የሚያጠልቁበት ሁኔታ አለ። በአጠቃላይ የሲዳማ ልጃገረዶችም ሆኑ ሴቶች በሙሉ በእግሮቻቸው እና በእጆቻቸው ጣቶች ላይ ከመዳብ እና ከብር የሚሠሩ ቀለበቶችን በማድረግ የሚያጌጡና የሚዋቡበት ባሕል ያላቸው ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
በተጨማሪም የሲዳማ ሴቶች የራሳቸው መዋቢያ ዕቃዎች አላቸው። እነዚህም ከእንጨት ተጠርበው የሚሠሩ ትራሶች ወይም በብሔረሰቡ ቋንቋ አጠራር ‘ባኮ‘ የሚሰኙት ይጠቀሳሉ። እንዲሁም ከእንጨት የሚሠሩ ማበጠሪያዎችም አሏቸው። በሲዳማ ባሕል እነዚህ ቁሳቁሶች ሁሉም የሲዳማ ሴቶች እንዲኖራቸው ግድ ይላል።
የሲዳማ ወንዶች አለባበስና አጋጌጥ
በሲዳማ ባሕላዊ አለባበስ ሥርዓት መሰረት ወንድ ሕፃናት እንደ ሴት ሕፃናት ሁሉ ከበግ ቆዳ ተለፍቶ የሚዘጋጅ ለምድ ይለብሳሉ። ከወደ አናታቸውም ቁንጮ በማስቀረት ሌላውን የቀረ ፀጉራቸውን ክፍል በሙሉ ይላጫሉ። በጉድሮው ላይም ዶቃ እና ዛጎል በማሰር የሚዋቡበት ባሕላዊ ሂደት አለ። በተጨማሪም ወንድ ሕፃናት ድክ ድክ ማለት ሲጀምሩ በሲዳምኛ ቋንቋ ‘ሜክሲ” የተሰኘ ቀጭን ጠፍር በወገባቸው ላይ ይታሰርላቸዋል።
ወደ ወጣትነት የእድሜ ክፍል የገቡ ወንዶች በበኩላቸው በብሄረሰቡ ቋንቋ ”ሀፌር” የተሰኘ ከጥጥ የሚሠራ ባሕላዊ ልብስ ያገለምዳሉ። ከላይም በብሔረሰቡ ቋንቋ ‹‹ጋሶ›› የተሰኘ ከጥጥ የሚሠራ አነስተኛ ጋቢ ይደርባሉ። በሲዳማ ባሕል ወጣት ወንዶች ለጥርሳቸው ጤንነትና ውበት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ። በመሆኑም ከብት ሲጠብቁም ሆነ ሲጓዙ ጥርሳቸውን እየፋቁ ነው። መፋቂያ ከአፋቸው አይለያቸውም።
ከዚህ በተጨማሪም ወጣት ወንዶች ክርናቸው እና ክንዳቸውን በብሔረሰቡ ቋንቋ ”እስቲ ‘ የተሰኘውን በመተኮስ ተውበው እና አምረው ደምቀው ለመታየር ጥረት ያደርጋሉ። እንዲሁም ፀጉራቸውን ቅቤ በመቀባት ጎፈሬ ያበጥራሉ። ይሄን የሚያደርጉት በተለይም ጭፈራ በሚሄዱበት ጊዜ ነው። በተጨማሪም ወደ ክብረ በዓላት እና ገበያ ቦታዎች በሚሄዱበት ወቅት ይሄንኑ ያደርጉታል። የሲዳማ ወጣት ወንዶች ለአደንም ሆነ ከብት ለማገድ ሲወጡ በሲዳምኛ ቋንቋ ‘ካኮ” የምትባል አነስተኛ ጦር ከእጃቸው አትለይም። ጦሯን ሰርክ እነዚህን ተግባራት በሚፈጽሙበት ጊዜ ይዟታል።
የሲዳማ አዋቂ ወንዶች በባሕላቸው ከጥጥ በተሠራ የተለያዩ ቀለማት ባላቸው ክሮች የተሠራ እና በብሔረሰቡ ቋንቋ ”ጎፋ‘ የተሰኘ ጌጥ ያጠልቃሉ። ከጥጥ የተሠራ መታጠቂያም ይታጠቃሉ። ከላይም ቡልኮ ይደርባሉ። እነዚህ የሲዳማ ወንዶች በእርሻ ሥራ ላይ በሚሆኑበት ወቅትም ‘ኮንኮሎ” እና ”ላንዲ‘ የተሰኙ ከበግ እና ከጥጃ ቆዳ የተሠሩ አልባሳት ከወገብ በላይ ጀርባቸው ላይ ጣል ያደርጋሉ። ወንዶቹ በባሕላቸው በራሳቸው ጓሮ የእርሻ ሥራ በሚያከናውኑበት ወቅትም ከቆዳ የሚሠሩ የተለያዩ አልባሳትን ያገለድማሉ። መልካም ሳምንት!
በሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም