የሴትነቴ ኮቴዎች

የሴትነቴ ኮቴዎች አይረሱኝም.. ብቻዬን የረገጥኩት የምድር ርቃን የለም። በሃሳቤ ውስጥ፣ በምኞቴ ውስጥ እናቴ አብራኝ አለች። ብቻዬን የረገጥኩት በመሰለኝ የነፍሴ ምድር ውስጥ እንኳን በማላውቀው መንገድ እናቴን ከዳናዬ ጎን አገኛታለሁ። ብቻዬን የኖርኩት በመሰለኝ የአፍላነት መንገዴ ላይ እንኳን እንዳላፍር ተጠንቅቃ ከጎን ስትሳብ እናቴን አገኛታለሁ። ብቻዬን የኖርኩት በመሰለኝ የሴትነቴ ድብቅ እኔነት ውስጥ እንኳን በየት እንደገባች ሳላውቀው እናቴን ጎኔ ቆማ አገኛታለሁ።

ብቻዬን የሄድኩበት..ብቻዬን የተራመድኩበት የብቻ ጎዳና የለኝም። አንዳንድ ጊዜ ለማንም የማይነገር የብቻ ሴትነት ያለ ይመስለኛል። አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ጣልቃ የማይገቡበት የራስ ብቻ ሚስጢር አለ እላለሁ..በዛ ሁሉ ውስጥ እናቴ አለች። በእኔ ውስጥ እሷን፣ በእሷ ውስጥ እኔን ስላ በአንድ ሴትነት ውስጥ ሁለት አርጋ ነው ያኖረችኝ። ይቺ ሴት ታማ ሆስፒታል ገባች።

እናቴን ድንገተኛ ክፍል ሲያስገቧት ድጋሚ የማላገኛት ነበር የመሰለኝ። ከእሷ የባሰ ታምሜ ተዝለፈለፍኩ..መዝለፍለፌን ማንም አላየልኝም። ዶክተሩ የሆነ ነገር ጽፎ በአስቸኳይ ይሄ መድሃኒት ይገዛላት ብሎ ሲናገር የማዘዣ ወረቀቱን ከእጁ ላይ የተቀበልኩት እኔ ነበኩ። የእናቴ መኖር ከእኔ የተሻለ የሚጠቅመው ስለሌለ ነበር ወረቀቱን ተቻኩዬ የተቀበልኩት። የእናቴን ሕይወት ለመታደግ ከኔ ፈጥኖ መድሃኒቱን ገዝቶ የሚመጣ ያለ ስላልመሰለኝ ነበር ተስገብግቤ የማዘዣ ወረቀቱን የነጠኩት።

መድሃኒቱን ፍለጋ ብዙ ቦታ ዞርኩኝ..ከገባሁባቸው አራት መድሃኒት መሸጫ ፋርማሲዎች በአንዱ ውስጥ የተባለውን መድሃኒት አገኘሁት። መች ሳቅሽ ላለኝ ዛሬ ስል ይሄን ቀን አስታውሰዋለው። እናቴ የሌለችበት ሕይወት የሌለኝ ሴት ነኝ። ጠዋት ከእንቅልፌ የምነቃው በእሷ ተቀስቅሼ ነው። ሕይወቴን የምትኖርልኝ እሷ ናት። በራሴ ያደረኩት አንዳች ነገር የለኝም። በራሴ አስቤ የወሰንኩት፣ ያለ እርሷ ብቻዬን ሞክሬ የቻልኩት አንዳች ነገር የለኝም።

‹እማ ነገ ሁለት ሰአት እንድትቀሰቅሽኝ፣ እማ ነገ ፕሮግራም አለብኝ የትኛውን ልብሴን ልልበስ? እማ ጸጉሬን ቀለም ልቀባ አስቤአለሁ ምን ትይኛለሽ? እንዲህ ነን..እየጠየኳት እየመለሰች..እያስቸገርኳት እየተቸገረች የምንኖር። እማ ያ ልጅ እኮ እወደሻለው አለኝ! ‹እማ ከመምህራችን አንዱ የፍቅር ጥያቄ አቀረበልኝ..ምናምን።

ሰብሳቢዬ ናት..ዝርክርክ ብዬ የምጸዳው በእሷ ነው። ተመሰቃቅዬ የምስተካከለው በእሷ ነው። ዝርክርክ ማንነቴ..ምስቅልቅል ሴትነቴ ወግ ያየው በእሷ ነው። እኔ ምኗ እንደሆንኩ አላውቅም ሳስቸግራት እንጂ አንድም ቀን ስቸገርላት ራሴን አላገኘሁትም። የዚህች ሴት በሕይወት መኖር ዋጋው በምን ይለካል?

ሆስፒታል ደረስኩ..ሆስፒታል ስደርስ የማውቀው የአክስቴ ድምጽ የተሰማኝ መሰለኝ። እናቴ ወደተኛችበት ድንገተኛ ክፍል ስጣደፍ የለቅሶ ድምጽ ሰማሁ። እዛ ጋ መኖር አቆምኩ። በምን ሃይል እንደተራመድኩ አላውቅም እግሮቼ እየተሳቡ ከእናቴ ክፍል አደረሱኝ…የገዛሁት መድሃኒት ከሌላ እጄ ላይ አምልጦኝ ወደቀ።

በሕይወቴ ተመኝቼ ያጣሁት ነገር በዚህ ቀን ለዛውም በእናቴ ሞት መጀመሩ መቼም የማልቋቋመው ኀዘን ሆኖ ታየኝ። ክፉ ነገሬ በእናቴ ህመም ጀምሮ በሞቷ መጠናቀቁ ዓለምን፣ እግዜርን እንድጠላቸው አደረገኝ። እንዴት እንደማስብ አላውቅም ግን አስባለው.. ከእናቴ ሞት በኋላ የሚኖር ሴትነት፣ የሚያስብ አእምሮ የሚኖረኝ አይመስለኝም ነበር። በቆምኩበት ዓይኖቼን ወደ እናቴ ክፍል ወረወርኩ እናቴ በተኛችበት አልጋ ላይ በነጭ አቡጀዴ የተሸፈነ አንድ በድን ተመለከትኩ..ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ያየሁት የእናቴ ሴትነት ያ ነው።

ወደፊት መራመድ አልቻልኩም..ወደ ኋላ ሳፈገፍግ ይታየኛል። ወዴት እንደምሄድ አላውቅም። የሆስፒታሉን ጊቢ ለቅቄ ከአስፓልቱ ስገናኝ ግን ትዝ ይለኛል። እናቴ የሌለችበት ብቻዬን የረገጥኩት የሴትነት ዳናዬ ጀመረ..

ሞት እናቴን ወስዶ የጀገነ መሰለኝ። ሞት እኔን ከእናቴ፣ እናቴንም ከእኔ አቆራርጦ አሁን ገና ጥሩ የሠራሁ ያለ መሰለኝ። ግን እንዴት አምኜ ልቀበል? በእናቴ ከመጣብኝ በእግዜር ላይ እንኳን መፈንቅለ መንግሥት የማደርግ ሴት ነኝ። በእናቴ ከመጡብኝ ዓለምን በአንድ ሰከንድ ውስጥ ከማጥፋት የማልመለስ ሴት እንደሆንኩ አውቃለው። ግን ምንም አላመጣሁም። ውሸታም ነበርኩ ማለት ነው? በእናቴ ሞት ምንም እንዳልተፈጠረ መሆኔ አስመሳይ እንደሆንኩ እንዳስብ አደረገኝ። እናቴ ወደሌለችበት..ትዝታዋ ናፍቆቷ ወደማይደርስበት የሆነ የምድር ጥግ ገብቶ መስመጥ አምሮኛል። ግን ያ ቦታ የት ነው?

ብዙ አይነት ሞቶች መጡብኝ..እናቴን እንድከተላት ብዙ ሃሳቦች ተፈጠሩብኝ። ብን ብለሽ የሚበር መኪና ውስጥ ግቢ፣ ራሽን ሰቅለሽ ግደይ፣ መጨረሻው ከማይታይ ገደል ላይ ራሽን ወርውሪ፣ ከረጅም ፎቅ ላይ ራሽን ፈጥፍጪ የሚሉ እልፍ የሞት ስሜቶች አእምሮዬን ወረሩት። ለምን መሞት እንዳልቻልኩ አላውቅም? ግን ሞቼ እናቴን ከምረሳት ኖሬ በሞቷ እየናፈቅኳት ብኖር የተሻለ ስለመሰለኝ ነው እላለሁ።

እንዴት እንደተራመድኩ አላውቅም ብቻ የሆነ ሀገር፣ የሆነ ቦታ ላይ ቆሜ ሳለቅስ ያየችኝ አንድ ሴት ‹ምን ሆነሽ ነው የምታለቅሽው? ስትል ጠየቀችኝ። መልስ አልሰጠኋትም። ‹ንገሪኝ ምን ሆነሽ ነው? ስትል ደግማ ጠየቀችኝ። ሁሉንም ነገርኳት አዲስ አበባ ይዛኝ መጣች። ከእናቴ ርቄ በሴትነቴ ጎዳና ላይ አስር አመት አስቆጠርኩ። የሳደገኝ የዲማው ጊዮርጊስ ምስክሬ ነው በነዚያ አስር ዓመታት ውስጥ ሳላለቅስና ሳልንገዳገድ በጽናት የኖርኩት ሴትነት አልነበረኝም። እናቴን ለመርሳት የሄድኩበት መንገድ እናቴን እንድናፍቅ አድርጎ መከራ ሲያበላኝ ነበር።

ከአስር ዓመት በኋላ የሆነ ሃሳብ ወደ አእምሮዬ መጣ። ወደ ትውልድ መንደሬ መመለስ እንዳለብኝ የሆነ ሃይል ሹክ አለኝ..እናቴ የሌለችበት ሰፈር ላለመሄድ ከራሴ ጋር ብዙ ብሟገትም የውስጤ ሃሳብ ግን ሊለቀኝ አልቻለም። ለምን እንደምመለስ እርግጠኛ ሳልሆን በሚጎተጉተኝ ስሜት ተመርቼ ወደትውልድ መንደሬ አቀናሁ። ወዴት እንደምሄድ ግራ ገብቶኝ ነበር። ቀዬው የአስር ዓአመት እድፍ ተለጉዶበት ከማውቀው ሌላ ሆኖ ነበር። የትም አልሄድኩም..ወደዛች እኔና እናቴ ወደተመላለስንባት የጉልት ገበያ አቀናሁ። እናቴ እንጨትና ከሰል፣ ሽሮና በርበሬ የምትሸጥባትን ትንሽዬ የመንደራችንን ጉልት ማየት አምሮኛል። በዛ ሳልፍ የሚዋሃደኝ አንድ ስሜት እንዳለ አውቃለሁ..እዛ ቦታ አለማልቀስ አልችልም። ጠዋትና ማታ ከእናቴ ጋር እዛ ቦታ ነበርን።

ጉስቁልቁል ብዬ ሄድኩ..ግን ግን..ህልም የሚመስል ነገር አስተዋልኩ። የማየው ነገር ከሆነ መንፈስ ጋር ተዋህዶ አንድ ነፍሴን እያስጨነቃት ከመሆን ውጪ ምንም እንደማይሆን ባለሙሉ ተስፋ ነበርኩ። በማየው ነገር ተደነባብሬ ወደ ፊት ተራመድኩ። እናቴን የምትመስል አንድ ሴት ከዛሬ አስር ዓመት በፊት የማውቀውን አዳፋ ነጠላዋን ለብሳ በዛ ቦታ አየሁ። ከራሴ ጋር አስር ሆኜ እሟገት ነበር። በነፍሴ ውስጥ የማላውቃት ሌላ ነፍስ ተፈጠረች። እያበድኩ መሰለኝ..

ፊቷን አየሁት..እናቴ ናት..እንዴት ሊሆን ይችላል? ስል ራሴን እጠይቃለሁ።

ምን እንደማስብ፣ ምን እንደምል ጠፋኝ? ራሴ የፈጠርኩት የናፍቆት ድራማ መሰለኝ..ግን ደግሞ አይደለም። ባለሁበት ሳልንቀሳቀስ ቆየሁ..እናቴ መሆኗን የሚያረጋግጡ ብዙ ነገሮችን አስተዋልኩ። እናቴን እንዳጣሁበት እንደዛ ቀን የደስታ መጀመሪያዬ ከዛ ቦታ በዛ ቀን ጀመረ።ጓዟን ሸክፋ ወደ ቤቷ ስትሄድ ከኋላ ተከተልኳት። የማውቀወን የድሮ መንገዳችንን ትታ በሌላ አቅጣጫ ሄደች..በዚህ ጊዜ በቃ እሷ አይደለችም ስል አሰብኩ።

ከብዙ መራመድ በኋላ የእናቴን ደሳሳ ማረፊያ አየሁት። እናቴ በአንድ መንገድ ዳር በላስቲክ በተሠራ ደሳሳ ቤት ውስጥ ነበር የምትኖረው። እናቴን ሳቅፋት..ስስማት ዳግም እየተወለድኩ ነበር።

ከሻሿ ያመለጡ ነጫጭ ሽበቶች ግንባሯንና ጆሮ ግንዷን ወሮታል።ቆሜ ባስተዋልኳት ሁለት ሰአታት ውስጥ እናቴ አንድም አልሸጠችም ነበር። እንባዬ መጣ..ስለእናቴ ድህነት ነፍሴ መረቀዘች።

በበትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You