ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ የሥራ ዘመን ሰባተኛ መደበኛ ስብሰባውን ግንቦት ዘጠኝ ቀን 2014 ዓ.ም ሲያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
በወቅቱ በርካታ የምክር ቤት አባላት የዲፕሎማሲ ስራዎችን የሚያጠናክር እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፤ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለው ግንኙነት ምን ደረጃ ላይ ነው፤ የውጭ ጫናዎችን ለመከላከል ዲያስፖራውን ባሳተፈ መልኩ ምን እየተሰራ ነው ፤ የተቋሙ ለውጥና የዲፕሎማቶች ምደባ ምን ያክል ፍትሃዊ ነው፤ የሳዑዲ ተመላሾችን በተመለከተ ምን አይነት የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ ነው፤ በሰብዓዊ ድጋፍ ረገድ ዕርዳታ በሰፊው ማቅረብ ያልተቻለው ለምንድነው የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን አንስተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።
እኛም የምክር ቤቱን ውሎ መሰረት በማድረግ ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ ጥቂቱን በማንሳት የተሰጠውን ምላሽ ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰው የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በምን ደረጃ ላይ ነው፤ ጫናዎችስ ለመከላከል የተወሰዱ ዕርምጃዎች ምንድን ናቸው?
አንዳንድ አገራት በልዩ ልዩ ፍላጎቶች አገራችንን በዳይና ተጋፊ አድርጎ በመሳል ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለመነጠል ከፍተኛ ጫና አድርገውብናል። ይህንንም ጫና በኢትዮጵያ ህዝብ ፅናትና ጥረት፣ በውጭ በሚኖሩ የዲያስፖራ አባላት፣ በቁርጥ ቀን ወዳጆችና በዲፕሎማሲያችን ጥረት ተቋቁመን የከፋ ችግር ሳይደርስና መስመራችንን ሳንለቅ ቀጥለናል።
ለዚህም በቅድሚያ መላው ሕዝባችንንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ። በማህበራዊ ሁሉ የጋራ ርብርብ በኋላ ጫናዎቹ በተወሰነ ደረጃ የመለዘብ ምልክት ቢያሳዩም አሁንም ግን በተለያየ መልኩ ቀጥለዋል።
እርግጥ ነው! ባለንበት ዘመን የዓለም ስርዓት ተገማች ባለመሆኑ እንዲሁም በተለያዩ ፍላጎቶች እና የአሰላለፍ ለውጦች ምክንያት የዲፕሎማሲ ስራን በእጅጉ ፈተና የበዛበት ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው።
ስለዚህ ውስጣዊ አንድነታችንን የማጥበቅና የመጠበቅ እንዲሁም ሰላምን ከማረጋገጥ ሂደት ጎን ለጎን በማስገንዘብና በማለዘብ ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነትን አጠናከሮ መቀጠል ይጠይቃል።
በሌላ መልኩ ወደ ቀጣናውም ቀረብ ብለን ስንመለከት በጂኦፖለቲካል ፍላጎትና በልዩ ልዩ ውስጣዊና ቀጠናዊ ሁኔታዎች ዲፕሎማሲያችን የበለጠ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ቀድሞ መንቀሳቀስ የሚፈልግበት ዘመን ላይ እንገኛለን።
ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጋር ከተደረጉ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችና ጉብኝቶች በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተካሄደው የ35ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን ከጎረቤት አገራት በተጨማሪ ከተለያዩ አገራት መሪዎችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በመገናኘት በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክከር ተደርጓል። አገራችን ከሁሉም የአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችና ትብብሮችን የሚያጠናከሩ ሥራዎችን በአፍሪካዊነት ስሜት ተጠናከረው እንዲቀጥሉ እየተደረገ ይገኛል።
በአፍሪካ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያለንን ጉልህ ተሳትፎ ከማስቀጠል አንፃር የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል አገራት በአንዳንድ አገራት ጫና ምክንያት አገራችንን የም/ቤቱ አጀንዳ ለማድረግ ጥረት ባደረጉበት ወቅት የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር ከማንም ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆና ለመፍታት እንድትችል አፍሪካውያን ጠንካራ አቋማቸውን አሳይተዋል።
በሚኒስትሮች ደረጃ የተካሄዱትና እና በኢትዮጵያ የተመሩት የህብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባዎች ለአገራችን አቋሞች የድጋፍ መሠረት ሆነዋል።
በተመሳሳይ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር፣ ተደማጭነታችንን ለማሳደግ እና ተደራሽነታችንን ለማስፋት ካለፉት ዓመታት በጎ ልምዶችና ዘመኑ የሚጠይቀውን የዲፕሎማሲ ተልዕኮ መነሻ ያደረገ ተቋማዊ የለውጥ ስርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።
ጥያቄ ፡- ሰብዓዊ ጉዳይን እንደፖለቲካ መሳሪያ አድርገው ከሚደረጉ ጫናዎች ምን ደረጃ ላይ ናቸው?
አቶ ደመቀ ፡- በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ጥቅሞቻችንን ለማሳደግ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ሕብረት እና አባላቱ ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም (ከአሜሪካና ከአውሮፓ) ጋር በፖለቲካ፣ በልማት ትብብር፣ በጸጥታና ደህንነት እንዲሁም ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ የጠበቀ ወዳጅነት የነበራት አገር መሆኗ የሚታወቅ ነው።
ይሁን እንጂ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት፣ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች እየጣሰ እንደሆነ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት እየፈጠረ እና ሌሎች ተመሳሳይ ክሶችን በመደርደር የተቀናጀ ዘመቻ በማካሄድ የሰብዓዊ መብትን ጉዳይ እንደ ፖለቲካ መሣሪያ በመጠቀም ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል።
አንዳንድ የምዕራባውያን የሚዲያ ተቋሞች አዲስ አበባ ከበባ ውስጥ መሆኗንና በሕዝብ ድምጽ የተመረጠ መንግሥት ያበቃለት በማስመሰል ጭምር ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ጦርነት አድርገዋል።
ይህንን ተከትሎም ጥቂት የማይባሉ የምዕራብ አገሮችና ተቋማት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት ዜጎቻቸውና በኤምባሲዎቻቸው /በተቋማቱ/ ውስጥ ሲሠሩ የቆዩ ዲፕሎማቶችና ቤተሰቦቻቸው አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ ሲያሳስቡ፣ ሲያስተባብሩና ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል። የተወሰኑት ደግሞ የተለያዩ ማዕቀቦች በመንግሥት ላይ እንዲጣሉ ጭምር በመወትወት ትልቅ ተጽዕኖ ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል።
አንዳንድ የምዕራብ አገራት በአገራችን ላይ የሚያሳድሩትን የዲፕሎማሲ ጫና ለመቀነስና ግንኙነቱ እንዲሻሻል ለማድረግ በአዲስ መልከ ግንኙነቱን መልሶ የማሻሻል ስትራቴጂ በመንደፍና ወደ ዕቅድ በመቀየር ከበርካታ አገራት ጋር በየደረጃው ግንኙነቱ ተጠናከሮ ቀጥሏል። አንዳንድ አዎንታዊ ውጤቶችም መታየት ጀምረዋል።
መንግስት በቅርቡ የወሰዳቸውን በርካታ እርምጃዎች ዕውቅና የመስጠትም አዝማሚያ ከማስተዋሉ ባሻገር ከመንግስት ጋር ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡ ሆኖም ግን አሁንም የተለያዩ ጫናዎች ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ ነው።
ጥያቄ፡- በአሜሪካ ሴኔት አባላት የሚዘጋጁ አፋኝ ህጎች እንዳይጸድቁ ከማድረግ አኳያ የተደረገው ጥረት ምን ያክል አጥጋቢ ነው?
አቶ ደመቀ፡- በአሜሪካ ሴኔት እና ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነት ኮሚቴዎች የቀረቡት HR6600 S.3199 ቢሎች አገራችንን የሚጎዱ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ ለማድረግ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ዝርዝር የድርጊት መርሀ-ግብር የተዘጋጀ ሲሆን በረቂቅ ህጎቹ የተካተቱት አንቀጾች አደገኛነት እንዲሁም በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ የሚያስረዳ ጽሑፍ (Aid Memoir) ተዘጋጅቶ ለሴናተሮችና እና ለሌሎችም የኮንግረስ አባላት እንዲሰራጭ ተደርጓል።
በተከበሩ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተፈረመ ደብዳቤም ጭምር ለአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ለተከበሩ ናንሲ ፔሎሲ እንዲደርስም ተደርጓል።
በአሜሪካ ሕግ አውጭ አካላት የተረቀቁት ሕጎች የሚኖራቸውን አሉታዊ ውጤት ለማስረዳት እና የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ለመሻሻል በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የአሜሪካ መንግስት አካላት ጋር የሚነጋገር አንድ የልዑካን ቡድን ወደ አሜሪካ ተልኮ ነበር።
ልዑኩ የሴኔት እና የተወካዮች ምክር ቤት አባላት አገራችንን በሚመለከት ያላቸውን አቋም በማጤን እና ተደራሽ በመሆን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ የሴኔት እና የተወካዮች ምክር ቤት አባላትንና ሰራተኞች አነጋግሯል። የተዘጋጁት ረቂቅ ሕጎች አደገኛነትና የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በማሻከር ረገድ የሚኖራቸውን አሉታዊ ሚና በተመለከተ የማስገንዘብ ስራ በስፋት ተከናውኗል። የዲያስፖራ አባላት ጥረትም ተጠናከሮ ቀጥሏል።
ጥያቄ፡- የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ አዲስ ጥናት አደርጋለሁ ብሏል፤ ጉዳዩን ለማለዘብ ጥናቱ ቢደረግ ምንድነው ችግሩ?
አቶ ደመቀ፡- ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ ተፈፀሙ የተባሉት ጥሰቶች የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በጋራ እንዲያጣሩ ተደርጓል። ያቀረቧቸውን ምከረ ሃሳቦች ለማስፈፀምም የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑ ይታወቃል።
የማጣራት ሥራው የሚሸፍነው እስከ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ያሉት በመሆኑ ከዚህ ቀን በኋላ በአማራና በአፋር ክልሎች የተፈፀሙ ጥሰቶችም በጋራ እንዲጣሩ ሃሳብም አቅርበናል።
ይህ በእንዲህ እያለ በአውሮፓ ኅብረት አስተባባሪነት በቀረበ ረቂቅ ውሳኔ የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት የኤክስፐርቶች ኮሚሽን አቋቁሟል።
ይህ ውሳኔ በተመድና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተደረገውን የጋራ ማጣራት እንደገና ለመድገም የሚሠራ፣ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይሉ በጋራ በተደረገው ማጣራት መሠረት የቀረቡትን ምክረ ሃሳቦችን ለመፈፀም የሚያደርገውን ስራ የሚያወሳስብ ነው። በመሆኑም ተቀባይነት እንደሌለው አበከረን አስገንዝበናል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲጣሩ የምትደገፍ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል የምትፈልግ መሆኑን ገልጸናል። የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ኮሚሽን የኢትዮጵያ የሰላማዊ መብት ኮሚሽንና የተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት በጋራ ያደረጉት ማጣራት የሚደግም መሆኑ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
የዚህ የጋራ ማጣራት ውጤት የሆኑት ምክረ-ሃሳቦች መንግስት ለማስፈጸም የወሰዳቸውን እርምጃዎች የሚያስተጓጉል መሆኑን በመግለጽ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ለተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በደብዳቤ ገልፀናል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ከአጋር አገሮችም ጋር ለመወያየት ፍላጎታችንን አሳውቀናል።
ጥያቄ፡- መንግስት መሰረታዊ በሆነ መንገድ ለትግራይ ህዝብም ሆነ አሸባሪው ሕወሓት ላፈናቀላቸው የአፋርና የአማራ ወገኖቻችን ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳያደርስ ዋነኛ ማነቆ የሆነው ምንድነው?
አቶ ደመቀ፡- ወደትግራይ ዕርዳታ ይላካል ነገር ግን የገባው ተሽከርካሪ እንዳይወጣ እየተደረገ፣ ለማድረስም የደህንነት ችግሮች እየተነሱ ከአቅም በላይ የሆኑ ጥያቄዎች ሲያስተጓጉሉን ቆይተዋል። ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንኳን ትግራይ ላሉ ተጎጂ ቤተሰቦች ዕርዳታ የማድረስ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለብን እናውቃለን።
በቅድሚያ በመንግሥት በኩል የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረገው ለሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታዎችንን ለማመቻቸት ነው፤ ይህ በተደረገ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ግን አሸባሪው ሕወሓት ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ወረራ አካሂዷል።
ወረራው በተካሄደበት ሁኔታ፣ በየትኛውም መልክ ዕርዳታ ለማስገባት ከአቅም በላይ ነው፤ በአየር መሰረታዊ የሚባሉ የመድኃኒትና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን ግን ለማድረስ ሞክረናል።
በኋላም ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ የዕርዳታ አቅርቦት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ ቢገቡም እዛው ነው የቀሩት። ይህ ደግሞ የሰብዓዊ ዕርዳታውን ለማሰናከል ነው። ተሽከርካሪዎቹ መኪኖቹ ከመቅረታቸው በላይ ለወታደራዊ እንቅስቃሴ ውለዋል።
ወደ ትግራይ የሚሄደውን ዕርዳታ ያህል ወደ አፋርም መሄድ እንዳለበት እናምናለን። ወራሪው የሕወሓት ኃይል ከአፋር ከወረዳ ማዕከላትና ከተወሰኑ ወረዳዎች ወጥቷል እንጂ ዛሬም ድረስ በዚህ ወራሪ ሃይል ቁጥጥር ውስጥ ያሉ ቀበሌዎች ስለመኖራቸው ከአካባቢው መረጃ አለን።
በተመሳሳይ አማራ ክልል ረጅም ጊዜ በወራሪው ቁጥጥር ስር ውሎ ስለነበር ዕርዳታውን ለማድረስ አልተቻለም ነበር። ወደአማራ ክልል ዕርዳታውን ለማስገባት ዕድሉ ቢገኝም ግን ስርጭቱን የሚያካሂዱ ተቋማት ቀድመው በትግራይ ክልል የዘረጉትን ስርዓት አይነት የተመቻቸ ስርዓት አልዘረጉም ነበር።
በአንድ በኩል በድርቅ ምክንያት የተጎዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች አሉን፣ በሌላ በኩል ጦርነቱ በተካሄደበት ቦታ ያሉ የምግብ ዋስትና ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች አሉ። ሙሉ ለሙሉ ተፈናቅለው የመጡ እንዲሁም በየቤቱ የሚገኙ ጦርነቱ ተጋላጭ ያደረጋቸው ሰዎች አሉ። ስለዚህ ያለንን ሀብት ለዚህ ትኩረት በማድረግ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋርም በመሆን እርዳታውን የማፋጠን ስራ ነው የምንሰራው ብለዋል።
ጥያቄ፡- በተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ውስጥ ያለን ተሳትፎ ለማጠልሸት የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ ይህ እንዴት ይታያል?
እንደሚታወቀው አገራችን በተመድ የሰላም ማስከበር ታሪከ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጋለች። ምንም እንኳን በአንድ አጋጣሚ ወደአገር ቤት በሚመለሱ የሰላም አስከባሪ ኃይላችን ጋር በተያያዘ ከተመድ መርህ ባፈነገጠ መልኩ ጫና ለመፍጠር የተሞከረ ቢሆንም ከድርጅቱ ጋር በመነጋገር ለማስተካከል ተችሏል።
ሌላውና ትልቁ ችግር ግን በተለይ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ ተጠርጣሪ አድርጎ የማየት ችግር ነው። በቀጣይም በሚኖሩ የሰላም አስከባሪ ተግባሮች ላይ ወታደሮቻችን ሲመደቡ የሰብዓዊ መብት ምዘና እናካሂዳለን የሚለው ጉዳይ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተናል።
ይህ አይነቱ ሃሳብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጣረስ በመሆኑ በየትኛውም መንገድ ተግባራዊ የሚሆን ሃሳብ አይደለም። ከዚህ ባለፈ ግን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ
ኃይሎች እያበረከቱ ያሉትን አኩሪ ተግባር በማስፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለንን የኢትዮጵያ ወታደሮች ዝና አስጠብቀን የምንቀጥል ይሆናል።
ጥያቄ፡- ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከርና በድንበር አካባቢ ያለውን የሰላምና ደህንነት ችግር ከማስወገድ ባለፈ የእርስ በእርስ ንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ምን ተሰራ?
አቶ ደመቀ፡- የዲፕሎማሲያችን ዋነኛ ትኩረት የጎረቤት አገራትን ማዕከል ያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስርን በማጎልበት ረገድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከጎረቤት አገሮች ጋር በመሠረተ ልማት፣ ግጭትን በማስወገድ፣ በሁለትዮሽ ግንኙነት እና በኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ ፈርጀ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል።
አገራችን ከጎረቤት አገሮች ጋር የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ሕዝቦች፣ ድንበሮች እና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶችን የምትጋራ በመሆኑ ሕልውናዋ፣ ሠላምና ልማቷ ከነዚህ ጎረቤት አገሮች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።
ከኤርትራ ጋር አሁን ያለው ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ ነው። ኤርትራ በቁርጥ ቀን ከአገራችን ጋር የቆመች በመሆኑ በፀጥታ ጉዳዮች ትብብር ለማድረግ የሚያስችል መሠረት ጥለናል። ከኤርትራ ጋር የጋራ ጥቅምን መሰረት በማድረግ በትብብር እየተሰራ ነው።
የፖለቲካ ግንኙነቱን ወደ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር ለማሸጋገር የድንበር አካባቢ ንግድንና የሰዎችን ዝውውር የሚያሳልጡ መሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ የወደብ አጠቃቀም፣ የንግድ ልውውጥ፣ የጉምሩክ፣ የኢሚግሬሽን እና የመሳሰሉ የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የትብብር ማዕቀፎች ለማበጀት ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን።
ከጅቡቲ ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ዘርፈ ብዙ ግንኙነትና ትስስር ያለን መሆኑ የሚታወቅ ነው። ጅቡቲ ካለፉት ሃያ አመታት ወዲህ ለአገራችን የወጪና ገቢ ምርት ዋና መግቢያና መውጫ በራችን ናት። በዚህም ምክንያት የሁለቱ አገሮች መደጋገፍ ከማንኛውም ጊዜ የበለጠ ጎልቶ ይታያል።
ከወደብ አገልግሎት በተጨማሪ ኢትዮጵያና ጅቡቲ በመንገድ፣ በባቡር ትራንስፖርት፣ በውሃና ኤሌክትሪከ አገልግሎት የተሳሰሩ ናቸው። የሁለቱ አገር ሕዝቦች በዘር፣ በቋንቋና በባህል የተሳሰሩ በመሆናቸው ለግንኙነቱ መጠናከር የራሱን ሚና ይጫወታል። ከጅቡቲ ጋር ያለን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከርና አጋርነታችን ለማጎልበት የበለጠ የማጠናከሪያ ሥራ መሥራት ይገባል።
ከኬንያ ጋር የቆየ መልካምና ታሪካዊ ግንኙነት ያለን ሲሆን፤ የሁለቱን አገሮች የድንበር አካባቢ ጸጥታ፣ የመሰረተ-ልማት ትስስር እንዲሁም የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ ስምምነቶች እና የትብብር መድረኮች አሉን። በተመረጡ የትኩረት መስኮች ላይ መስራት የሚያስችል ልዩ የትብብር ስምምነት ተፈርሟል።
የገቢና ወጪ ንግድ ልውውጡን በአንድ የጋራ ቁጥጥር ማዕከል ለማስተናገድ የሚያሰችል አሠራር በጋራ ተዘርግቶ ስራ ጀምሯል። ለአገራችን ወጪና ገቢ ምርቶች በአማራጭነት ያገለግላሉ ተብሎ የሚታሰበው የኬንያው ላሙ ወደብ ፕሮጀክትም ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ የመሰረተ-ልማት አካል ነው። በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱን አገሮች ማህበረሰቦች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የድንበር ንግድ ረቂቅ ስምምነት ተዘጋጅቶ ለውሳኔ ቀርቧል።
ጥያቄ፡- ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ጋር ያለው ግንኙነትስ በምን ደረጃ ላይ ነው?
አቶ ደመቀ፡- ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በመልከዓ-ምድር አቀማመጥ ሳቢያ በጋራ ድንበራቸው አካባቢ በሚኖሩ ሕዝቦቻቸው መካከል ጥልቅ የሆኑ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ግንኙነቶች እንዲሁም በሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች የተቆራኙ ትስስሮች አሏቸው።
ሁለቱን አገራት በመሰረተ-ልማት የሚያስተሳስሩ በተለይም በመንገድ፣ በባቡር ሃዲድ፣ በኃይል አቅርቦት ለመተባበር የሚያስችሉ በርካታ ስምምነቶች ተፈራርመዋል።
የደቡብ ሱዳን ሕዝብ እና መንግስት ለአገራችን ሰላምና ሉዓላዊነት መከበር ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያለው ነው። በኢትዮጵያ በኩልም ወዳጅ ለሆነው የደቡብ ሱዳን መንግስት እና ሕዝብ ሰላምና እድገት ድጋፋን በማጠናከር በትብብር መንፈስ እየተሰራ ይገኛል።
የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር በስምምነቱ መሠረት እንዲቀጥል አገራችን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኑ፣ በድንበር አካባቢ የሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የፌደራልና የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ከደቡብ ሱዳን አመራሮች ጋር በጋራ ችግሩን ለመፍታት እየሰሩ ሲሆን ግንኙነቱን በሁሉም መስከ አጠናከሮ መቀጠል ይጠይቃል።
በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት በጥሩ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን ግንኙነቱም ትብብርንና መደጋገፍን መሠረት ያደረገ ነው። በአገራችንና በሶማሊያ መካከል የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ለማቋቋም፣ የመከላከያ ትብብር፣ የመረጃ ልውወጥ ትብብር እና የሶማሊያን ፖሊስ ኃይል አቅም ግንባታ ትብብር የመግባቢያ ሰነዶች ተፈርመዋል።
አገራችን ከሶማሊያ ፌደራል መንግስትና ከከልሎቹ ጋር በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በሰላምና ጸጥታ፣ አሸባሪነትን በመዋጋት፣ በጋራ ድንበር ቁጥጥር፣ በንግድና በመሳሰሉት በትብብር እየሠራን ነው።ለሶማሊያ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ የበለጠ መጠናከር ይኖርበታል።
ጥያቄ፡- ጎረቤታችን ሱዳን አሁንም ድንበር በወረራ ከመያዟ ባለፈ ለአሸባሪው ሕወሓት ሳምሪ ቡድን ስልጠና እየሰጠች ነው፤ ሱዳንን ከድርጊቷ እንድትታቀብ ምን ጥረት ተደርጓል?
አቶ ደመቀ፡- ከሱዳን ጋር አገራችን ከምትጋራው ረዘም ያለ ድንበር በተጨማሪ የሁለቱ አገር ህዝቦች ተወራራሽ ባህልና ቋንቋ ያላቸው መሆኑና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩም የጠበቀ በመሆኑ ለግንኙነቱ ጠንካራ መሆን አስተዋጽኦ አድርጎ ቆይቷል።
መንግስታችንም በሱዳን የተረጋጋ ሰላምና ዕድገት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን ህዝቡም ጠንካራ ድጋፍ አድርጓል። በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጠረውን ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሱዳን ድንበራችንን ከመውረሯ በተጨማሪ የአሸባሪ ቡድን መነሻ በመሆን ችግር መፈጠሩ የነበረውን መልካም ግንኙነት አሻክሮታል።
ሳምሪ የተባለውን ገዳይ ቡድን በማሰልጠን ጭምር ከለላ እየሰጠች በተደጋጋሚ ጊዜ አስወግታናለች። ይህ አይነቱ ህገወጥ ተግባር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው።
በሌላ በኩል የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሱዳን በወረራ የያዘችው የኢትዮጵያን ምድር ለቃ መሄዷ አይቀሬ ነው። ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታቱ የተሻለ አማራጭ በመሆኑ እና ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት ያለ በመሆኑ መንግስታችን ሰላማዊ መፍትሔዎች ላይ በማተኮር እየሠራ ነው።
ጥያቄ፡- አንዳንድ የዩጋንዳ ባለስልጣናት ሕወሓትን እንደሚደግፉ በግልጽ ሲናገሩ ተደምጧል፤ ይህን ጉዳይ እንዴት እየተከታተሉት ነው?
አቶ ደመቀ፡- የኢትዮጵያ መንግስት ዩጋንዳ በሕወሓት ጉዳይ ላይ ያላትን አቋም ለማወቅ አዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠርቶ አነጋግሯል። በዩጋንዳ ካምፓላ የሚገኙትም አምባሳደራችን ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ዩጋንዳን ጠይቀዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሄደው የወታደራዊ ኦፊሰሮች ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ ከዩጋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ውይይት ተደርጓል።
አንዳንድ ዩጋንዳ ባለስልጣናት የሚሉት ምንድነው፣ ይሄን የሚናገሩ በራሳቸው የሚኖሩ እና ራሳቸው የሚጠየቁበት ነው፤ እኛ እንደአገር ይሄን አንደግፍም ይላሉ።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት አንድ የዩጋንዳ ከፍተኛ ባለስልጣን በአንድ አገር ጉዳይ ላይ አቋም ከወሰደ፣ የመንግስት አቋም አድርገን ነው የምንወስደው። በመሆኑም ዩጋንዳ ግልጽ አቋሟን እንድታሳውቀን እንፈልጋለን።
ጉዳዩ በቀላሉ የሚያይ እና የሚተው አይደለም። በመሆኑም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዝርዝር ተገምግሟል። ስለዚህ የትኛውም አገር ለአሸባሪው ቡድን ድጋፍ እንዳለው ካሳወቀ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የሚጣረስ ጉዳይ በመሆኑ አስፈላጊው ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት እንምናለን።
ጥያቄ፡- ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ኢጋድ የተሻለ ሆኖ እንዲወጣ ምን አይነት ጥረት ያስፈልጋል?
አቶ ደመቀ፡- ኢጋድ በቀጠናው ከሚታዩ የተለያዩ ችግሮች አንፃር የሚጠበቅበትን ሚና አሟልቶ ለመጫወት የበለጠ መጠናከር ይኖርበታል። ከጎረቤት አገሮች ጋር ካለን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪ አገራችን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚነሱ ግጭቶች እንዲፈቱ የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች።
ኢጋድን በተመለከተ፣ ኢጋድ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ዓላማዎችን አንግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ትኩረቱን በኢኮኖሚ ትብብርና አካባቢያዊ ትስስር፣ በጤናና ማህበራዊ ልማት፣ በግብርናና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ አድርጓል።
ይሁንና ኢጋድ የዕድሜውንና የልምዱን ያክል እየሰራ አይደለም። ልክ እንደሌሎች ቀጣናዊ ድርጅቶች የተደራጀና አካሄድና ውጤታማነት ያስፈልገዋል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም የበኩሏን ለመወጣት ዝግጁ ናት።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ያለውን የሰላም ሂደቶችና ለማረጋጋት የሚደረጉ ጥረቶችን ከአጋሮች ጋር በመሆን ስትከታተልና ስትደግፍ የቆየች ሲሆን ወደፊትም ግጭቶች ወይም አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች።
በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የአገራችን መልካም ገጽታ ግንባታ ከማሳደግ አንፃር ምንም እንኳን አንዳንድ ተቋማት (ቡድኖች) በጎ ገጽታችንን ለማጠልሸት ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩብን ነው።
በመሆኑም አዳዲስ የሚዲያ ቲንክታንከ፣ አድሾኬሲ ግሩፕና የምርምር ተቋማት እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችና ምሁራን በመለየትና የአገርን መልካም ገፅታ የሚያንፀባርቁ ዘገባዎች እንዲያወጡ ተከታታይ መረጃዎችን በመስጠት በጎ ገጽታ የሚያንፀባርቁ ዘገባዎች፣ ሪፖርቶችና ምስክርነቶች እንዲያወጡ ጥረት እየተደረገ ነው።
ለተለያዩ ሚዲያዎች መረጃ በመስጠት አዎንታዊ ዘገባዎች እንዲወጡ ለማድረግ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች በአገር ውስጥና በውጭ ሚዲያዎች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በፐብሊክ እንዲሁም በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮሩ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን በቀጣይም ተጠናከሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ጥያቄ፡- ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን ለማጠናከር የውጭ ጉዳይ ያደረገው ተቋማዊ ለውጥ ምን ያክል ተቋሙን ውጤታማ ያደርገዋል?
አቶ ደመቀ፡- በአገራዊ ለውጡ ማዕቀፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋማዊ የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያ የሚያስፈልግባቸው ጉዳዮችን በመለየት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚከናወነው ማሻሻያ ጋር በተናበበ ሁኔታ የመስሪያ ቤቱ የአደረጃጀት ማሻሻያ ሥራ ተከናውኗል።
አደረጃጀቱ የመስሪያ ቤቱን የመፈጸም አቅም ማጎልበት፣ ውጤታማነትን ማሳደግ፣ ብክነትን መቀነስ፣ ተጠያቂነትን ማስፈን እና ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር የሚሉ ዒላማዎች ይዞ በዋናው መስሪያ ቤትና በሚሲዮኖች የመዋቅር ማስተካከያ ተደርጓል።
የማሻሻያው ሥራ ዋና ዓላማ ሥራና ሠራተኛን ማገናኘት፣ የሰው ኃይል ልማትን ማሣደግ፣ ከውጭ ጉዳይ ተልዕኮ አንፃር ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር፣ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ዲፕሎማቶችን ማብቃትና ማፍራት እንዲሁም ለዲፕሎማሲ ሥራ ተፈላጊው ከህሎትና ብቃት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።
በዚህ አግባብ ሁሉንም የውጭ ግንኙነት ሠራተኞች ወደ ዋናው ተቋም በመጥራት ወቅቱን የሚመጥን ሥልጠና ከመሰጠቱም በላይ የዲፕሎማቶቻችንን ብቃት እና ዝግጁነት ለማረጋገጥ ምዘና ተደርጓል። ምዘናው የክህሎትና የሙያ ደረጃን በመለየት በሥልጠና ማጠናከር የሚያስችል ዓላማን አንግቦ የተከናወነ ነው።
የምዘናው ሂደት የተከናወነው በቅድሚያ የሥራ ኃላፊዎችና የዲፕሎማቶች ምዘና ለማካሄድ አስፈላጊ የሆኑትን ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በመቀመር የምዘና መሥፈርቶች እና መመሪያዎች እንዲዘጋጁ በማድረግ ነው።
በምዘናው ክፍተት የታየባቸውን ሠራተኞች ተጨማሪ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙም በማድረግ በአዲሱ መዋቅር መሠረትና በተዘጋጁ የድልድልና የምደባ መመሪያዎች አማካኝነት በዋና መ/ቤትና በሚሲዮኖች የመልሶ ምደባና ድልድል ተከናውኗል። ይህ ተግባር ቀጣይነት ባለው መልኩ በየጊዜው ዲፕሎማቱ በተመደበበት ቦታ ብቁ መሆኑን በማረጋገጥና ክፍተቱን በመለየት እያሟላና አቅሙን እየገነባ እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችል ነው።
ጥያቄ፡- የዲፕሎማቶች ምደባ ምን ያክል በፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ ነው?
አቶ ደመቀ፡– አሁን ላይ አንድ አምባሳደር ሲመደብ ብቃቱና ሊወጣ የሚችለው ኃላፊነት ተለክቶ ነው። በእርግጥ ብዙ ሰው ሞቃዲሾና አንዳንድ ጎረቤት አገራት ከሚሆን ይልቅ ወደ ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ መመደብ ይፈልጋል። ነገር ግን ሁሉንም አንድ ቦታ ማስቀመጥ አይቻልም።
ውጤታማ ይሆናል ተብሎ በተመዘነበት ቦታ ነው የሚመደበው፤ በዚህ አግባብ ጄኔራሎችም ሳይቀር በአምባሳደርነት ተመድበዋል። ይህም በሄዱበት አገር ከሙያቸው ጋር ተያይዞም በጸጥታና ደህንነት ጉዳይ ከሌላው የተሻለ ስራ እንደሚሰሩ ስለሚታመን ነው።
በሌላ በኩል አንድ አምባሳደር አሜሪካ አሊያም ሌላ አገር ሲመደብ ከፍተኛ አመራሩ ብቻ ሳይሆን ዝርዝር ጉዳዮችን የሚመለከቱ ቡድኖች ጭምር ውጤታማነቱን ፈትሸውት ነው።
በዚህ አግባብ አንድ ዲፕሎማት አራት አመት ቆይቶ መልሶ ወደዋናው መስሪያ ቤት እንደሚመለስና ከዚያ በኋላ ታይቶ ወደሌሎች አገራት እንደሚመደብ ግልጽ አሰራር ተቀምጧል። ተመልሶ ከመጡ በኋላስ ማን ቅድሚያ ይመደባል ማን እዚሁ መቆየት አለበት የሚለው በፍትሃዊነት እንዲሰራበት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።
ጥያቄ፡- በሳዑዲ አራቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎች በተመለከተ የተጀመሩ የማጓጓዝ ስራዎች ቢኖሩም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት አሁንም እዚያው በችግር ላይ በመሆናቸው ዜጎችን ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ምን ደረጃ ላይ ነው?
አቶ ደመቀ፡- በሳዑዲ አረቢያ በችግር ላይ የነበሩ ዜጎቻችንን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መንግስት በወሰነው መሠረት በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሯል። በዚህም መሠረት ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር በመተባበር በችግር ውስጥ የነበሩ 41 ሺህ 256 ዜጎቻችንን በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ወደ አገር ቤት መመለስ ተችሏል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በቅርቡም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ያሉ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገር ቤት ለመመለስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚመራና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን እና ክልሎችን ያካተተ ብሔራዊ ኮሚቴ ተደራጅቶ ዜጎችን ወደ አገር ቤት የመመለስ ስራ በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን እስካለፈው ሳምንት ድረስ ከ23 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ አገራቸው መመለስ ተችሏል። ይህም ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ በየዕለቱ እየተከናወነ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ዜጎችን የመመለሱ ሥራ እንደቀጠለ ሆኖ ዘላቂ መፍትሄው ግን ከአገር ቤት በደላላ አማካኝነት በህገ ወጥ መንገድ የሚሄዱት ዜጎችን የማስተማርና የመቆጣጠር ስራ፣ ዜጎች ወደ ውጭ አገር መሄድ ሲፈልጉ ግልፅ በሆነ መንገድ የስራ ስምምነት ካላቸው አገራት ብቻ እንዲሆንና ከመሄዳቸውም አስቀድሞ አስፈላጊውን ከህሎት ይዘው እንዲሄዱ ማድረግ የሚያስፈልግ ሲሆን በሚሄዱባቸው አገራትም መብቶቻቸው እንዲጠበቁ የማድረግ ስራውን አጠናከሮ መቀጠል ያስፈልጋል።
ዜጎች ከተመለሱ በኋላም ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው መልሶ የማቋቋምና የስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ የማድረጉ ስራ በእጅጉ የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ባለፈ በየመን፣ በታንዛንያና በቤሩት በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ዜጎችን ደግሞ በማስፈታት ወደአገራቸው እንዲገቡ ተደርጓል።
ጥያቄ፡- ከመደበኛው የዲፕሎማሲ ስራ ባለፈ በዲጂታል ዲፕሎማሲው ሰፊ እንቅስቃሴ ብዙ ይጠበቃል፤ ከዚህ አኳያ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ደመቀ፡- የዲጂታል ዲፕሎማሲ ሥራዎችን ከማጠናከር አኳያ መስሪያ ቤታችን ከተለምዷዊው የዲፕሎማሲ አሰራር በተጨማሪ ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ አፈራሽ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀምና ቡድን በማደራጀት እየሰራን ነው።
በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዲያስፖራዎች የተባበረ ድምጽ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል። በተለይ በበቃ ወይም በNo more እንቅስቃሴ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዲያስፖራዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ።
ሕዝብ ለሕዝብ ያለን ቁርኝት ጠንካራ በመሆኑ በሁለቱ አገሮች ያሉትን ህዝቦችና እና በውጭ የሚገኙ የዲያስፖራ አባላት ተባብረውና ተደጋግፈው እንዲሠሩ የበለጠ መስራት ይገባል።
የዲፕሎማሲ ሥራ የሁሉንም ዜጎች አቅም በመጠቀም በሁሉም ቦታ ተደማጭ ሆኖ ለመዝለቅ በዘመኑ ቴክኖሎጂ ዕውነትን የሚጋፉ፣ አገርን የሚያጠለሹ እና ኢትዮጵያን ነጥሎ ለማቆም የሚደረጉ ጥረቶችን በመመከት አገራችን ከብሯና ጥቅሟ ተከብሮ እንዲዘልቅ የሁላችንም ጥረትና ርብርብ ይጠይቃል።
በአሁኑ ወቅት በአንፃራዊነት ካለፈው ዓመት በተሻለ የመደመጥና በሮች መከፈት የጀመሩበት፤ እጅግ በተዛባ ሁኔታ የአሸባሪው ቡድን ተገፊና ተበዳይ ተደርጎ ሲሳል የነበረው አጥፊነቱና ባህሪው እየታወቀ እና በገሃድ እየተጋለጠ የመጣበት ሁኔታ በግልፅ እየታየ ነው።
በዚህ ረገድ ደጋፊዎቻችንን በተሟላ መረጃ የተጠናከረ ድጋፋቸው እንዲቀጥል ማድረግ፣ በመረጃ ክፍተት በመደናገር የተሳሳተ አቋም የሚይዙትን በማስገንዘብ፣ ሆን ብለው የተለያየ ጥቅምና ትስስር ይዘው በኢትዮጵያ ላይ የሚዘምቱትን አካላት ደግሞ ተፅዕኗቸውን እየመከቱ ቢቻል ወደ እውነታው እንዲሻገሩ የማድረግ ሥራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ጠያቂ፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን::
አቶ ደመቀ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2014