ከገብረክርስቶስ
ከትውስታዬ ጓዳ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
መሬት ይቅለላቸውና አያቴ ከዓመታት በፊት ያጫወቱን የቀደምት ኢትዮጵያውያን የገድል ሰበዝ ትዝ ይለኛል።ከሃያ ዓመታት በፊት በማላስታውሰው አንድ ቀን ረፋድ ላይ ከእድሜ ጠገቧ የአባታችን እናት ከወይዘሮ የሺወቄት ከድር አልዩ ጋር እንጫወታለን።የአያታችን የሁልጊዜም የጨዋታና የንግግር ማጠንጠኛና የማሰሪያ ውሉ የቀደሙት ኢትዮጵያውያን የአርበኝነት ገድል ነበር።
ያን ቀን የዓድዋ ነገር ተነሳና ስለ ድሉ ብዙ የአፍ ነገርና ታሪክ አጫወቱን።ካጫወቱን ታሪክ ሁሉ ታዲያ አንዱ በሕጻንነት አዕምሮዬ ተቀርጾ ቀረ።እስከዛሬም ድረስ የዓድዋ በዓል በመጣ ቁጥር ከሕሊናዬ ጓዳ ብቅ እያለ ያስገርመኛል።
የዓድዋ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በብሔርና በሃይማኖት ሳይለያዩ የንጉሣቸውን የክተት ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰሜን ተመሙ። በወቅቱ አራቱም ማዕዝናተ-ኢትዮጵያ በየጦር አዝማቾቻቸው እየተመሩ ቀደምት እናት አባቶቻችን ደማቅ ታሪክን ጽፈዋል።
የአያታችን እትብት የተቀበረበት አገር ወረኢሉ አካባቢ ነው (ወሎ ውስጥ ማለት ነው)።ወረኢሉ ማለት ደግሞ ንጉሡ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ የክተት አዋጁን ካስነገሩ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ተሰባስቦ እንዲጠብቃቸው ከተቃጠሩባቸው ታሪካዊ ሥፍራዎች ውስጥ አንዱ ነው።
በዚሁ መነሻ ታዲያ አያታችን በዓድዋ ጊዜ ባይወለዱም ከእናት አባቶቻቸው የሰሙትን እውነተኛ ታሪክ ነበር ለእኛም የነገሩን። ታሪኩ እንዲህ ነው – ንጉሡና መኳንንቱ ወረኢሉ ከዚያም ደሴ ደርሰው ሠራዊቱን ሸክፈው ወደ ዓድዋ አቀኑ።ይሁንና ብዙም ሳይቆይ የንጉሡ የክተት ጥሪ ዘግይቶ የደረሰው የሩቅ አገር ኢትዮጵያዊ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ዘግይቶ ከክተቱ ስፍራ የከተመው ሕዝብ በርካታ ነበር፡፡
በተለያየ ጊዜ የሚመጣው ዘማች የንጉሡንና የሠራዊቱን ወደ ጦርነቱ ማቅናት እየሰማ እሱም እየገሰገሰ ወደ ትግራይ ይጓዛል።ደግሞ ሌላው ዘግይቶ ሲደርስ እሱም እንዲሁ እንደቀደመው ወደ ሰሜን ያቀናል። እንዲህ እንዲህ እያለ ከብዙ ሳምንታትና ከወራት በኋላም ሳይቀር የአገሩን ጥቃት ለመወጣት በክተቱ ስፍራ የሚደርሰው ሕዝብ ማለቂያ አልነበረውም።
በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ ከዓድዋው ድል በፊት የተገኙት የአምባላጌውና የመቀሌው ድሎች በወሬ ነጋሪዎች መሃል አገር ሲደርሱ በጦርነቱ ባለመሳተፉና የጠላትን አንገት ባለመቁረጡ እየተበሳጬ የደረሰበትን ውጊያ ለመሳተፍ በወኔ የሚጓዘው ኢትዮጵያዊ ቁጥር አልነበረውም።
በመጨረሻም ከብዙ ቀናት በኋላ ወረኢሉን እየረገጠ በእነ አያቴ መንደር ወደ ሰሜን የሚጓዘው ዓርበኛ ሁሉ የዓድዋን ድል ሰምቶ ኖሮ የሚያሰማው ቁጭት ልብ ይነካ ነበር ይባላል። ከእነዚያ አልፎ ሂያጅ ዓርበኞች እንዲያ ቁጭት የገባቸው ደግሞ በትክክለኛው ወቅት የደረሱት ሌሎቹ እድለኞች ንጉሣቸውን ተከትለው በሾተልና በጎራዴያቸው ዓድዋ ላይ በደም የደመቀ ታሪክ ሲጽፉ እነርሱ የዚህ ድል ተካፋይ ባለመሆናቸው ነበር።
የሆነው ሆኖ ዓድዋ ላይ የተጻፈው ያ ታላቅ ገድል በጦርነቱ ላይ በቀጥታ በተሳተፉት ጀግኖች ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በነበሩት መላ ኢትዮጵያውያን በመሆኑ እነዚያ ዓርበኞችም የታሪኩ ተካፋዮች ነበሩ።
ኋላ ላይ የኢጣሊያ መንግሥት የዓድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል ከአርባ ዓመት በኋላ ጦር ሰብቆ ባህር ተሻግሮ ኢትዮጵያን ሲረግጥ የዓድዋን አኩሪ ታሪክ ሲሰሙ ያደጉት አያታችን ከባላቸው ጋር ሆነው ወደ ጎጃም በማቅናት ከእነ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ጋር ዘምተዋል።
ከአምስት ዓመታት የዓርበኝነት ቆይታ በኋላም በድሉ ማግስት በመልስ ጉዞ ላይ ወንድ ልጅ ወልደው ባንድ እጃቸው ጠብመንጃ፤ በአንድ እጃቸው ደግሞ የእኔን አባት አቅፈው ወረኢሉ ደርሰዋል።ዛሬ ላይ ታዲያ ዓድዋንና አያታችን የነገሩንን ይህንን አስደማሚ ታሪክ ባስታወስኩ ቁጥር አሁን ያለነው ትውልድ ሁኔታ ድቅን ይልብኛል።
እርግጥ ነው ባለንበት ዘመን እንደያኔው መላውን ሕዝብ ጦር የሚያስከትት ጠላት እንደሌለብን ይሰማኛል። ይሁንና በብሔር ተቧድነን፤ ብሔራዊ ማንነታችን ኩራታችን መሆን ሲገባው እንደ አለት ገዝፎብን ታላቁን ጥላችንን ኢትዮጵያነትን አኮስሶብናል።
ከዓድዋ ድል ማግስት ጀምሮ ዓድዋ ባገዘፈው የልዕልና ከፍታ ልክ ኢትዮጵያ በሁሉ መስክ የምትበለጽግባቸው መልካም አጋጣሚዎች ሁሉ ላይ መለሱ ከሽፈዋል። በተቃራኒው የርስ በርስ ጦርነትና የረሃብ ተምሳሌት ተደርገናል። በመቻቻል ቦታ መነቃቀፍ፤ በአንድነት ምትክ በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ መከፋፈልን አንግሰናል፡፡
የእሳት ልጅ አመድ እንደሚባለው እንዳንሆን የዛሬዎቹ እኛ ትላንት በልዩነት ውስጥ በተሰናሰለው አንድነት የተጻፈልንን ደማቅ ታሪክ እያጎላን በዘመናችን ለተተኪዎች የሚተርፍ የድል እርሾ ትተን ማለፍ ይኖርብናል። ይህንን ለማድረግ እንዲቻለን ደግሞ እንደ ዓድዋ ያሉትን የአንድነትና የኩራታችንን ችቦዎች ከፍ አድርገን ማብራት ይገባናል።ለዚህ ነው ስለ ዓድዋ ብዙ ልንዘምር የሚገባን።
የዓድዋን የድል መድብል በወፍ በረርየታላቋ ሮም የፍርስራሿ አስኳል ኢጣሊያ እንደምንም ተንገዳግዳ እ.ኤ.አ በ1861 ዓ.ም. አገር ሆና ከመቆሟ እንደዘመኑ ሃያላን ቅኝ አገር አማራት። አምሯትም አልቀረ ሰሜን ምሥራቅ አፍሪካን ዕጣዋ አድርጋ ቀይ ባህርን ተሻግራ ዘለቀች።ተንኮል የጠነሰሰችበትን የውጫሌ ውልን ተገን አድርጋ የሦስት ሺህ ዓመታት የመንግሥትና የሕግ ታሪክ ያላትን ነፃ ምድር – ኢትዮጵያን ወረረች።
የመረብን ወንዝ ተሻግራ ዓድዋና መቀሌን እጅ አድርጋ ወደ መሃል አገር ለመግባት የሚያስችላትን ጉዞ ሽንጠ ረዣዥሞቹን የአምባላጌ ተራራማ ኮረብታዎችን በመያዝ አሳካች።
ግና ምን ጠቀማት፤ በእነ ራስ መኮንን፣ በእነ ፊታውራሪ ገበየሁና በሌሎቹም የሚመራው ጦር ከያኔው የትግራይ ገዥ የዓፄ ዮሐንስ ልጅ ራስ መንገሻ ጋር በመሆን የኢጣሊያ ጦርን ድባቅ በመምታት ወደ መቀሌ መለሱት።
ኋላም መቀሌ ላይ የኢጣሊያ ወራሪ ለሁለት ወራት ተከቦ ውሃ ጥም ጉሮሮውን ሲያደርቀው፤ ፍርሃት ልቡን አርዶት ሽንቱ በቦላሌው ሲንቆረቆር በዓፄ ምኒልክ ደግነት የወንድ በር ተከፍቶለት ከነትጥቅና ስንቁ ሸሽቶ ዓድዋ አካባቢ ከመሸገው ወገኑ ጋር ተደባለቀ።
የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ – በወዲያኛው ጥግ የዘመኑን መድፍና መሰል ከባድ መሣሪያ ከነፍጥ ጋር ታጥቆ፤ ምሽግ ሠርቶ በዘመናዊ የጦር ጀነራሎች የሚመራ ባዕድ ወራሪና ቅጥረኛ ሠራዊት ተሰልፏል።
ወዲህ ማዶ ደግሞ ምድሬን በጠላት አላስደፍርም ብሎ ጦር ሰብቆ ጋሻ ነቅንቆ፤ ማተቡን አጥብቆ፤ “ኢትዮጵያን አትንኩ” የሚለውን የነብዩን (ሰ.ዓ.ወ.) ቃል በልቡ ሰንቆ በባዶ እግሩ የተሰለፈ ኢትዮጵያዊ አለ። “ነፃነት አጥቼ ከምሰለጥን፤ ነፃነቴን ይዤ ኋላቀር ልሁን” የተሰኘችው የዘመኑ ዕውቅና ድንቅ የዓርበኞች ዜማ አባታችን ሁልጊዜ ሲያንጎራጉራት እነዚያን የነፃነት ዓርበኞች ያስታውሰኛል።
በዚያ የቁርጥ ቀን ከብረት የጠነከረ የኢትዮጵያ አንድነት ታይቷል። ብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊ የአገሩን ደፋሪ ጥሎ ወድቋል። ሦስት እጅ የሚሆነው የኢጣሊያ ወራሪ ጦር ሞተ፣ ተማረከ።የኢትዮጵያ የአይደፈሬነት የድል ችቦ ዓድዋ ላይ ተለኮሰ።
በዓድዋ የደመቀው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በጦርነቱ ማግስት ኢጣልያ ውስጥ አርድ አንቀጥቅጥ የወጣቶች ቁጣ ገነፈለ፤ የሕዝብ አመጽ ተቀሰቀሰ።የአመጹ ጎርፍም ቁንጮ የአገሪቱን ሹማምንት ከሥልጣናቸው ጠራርጎ ወሰዳቸው ።
ብዙም ሳይቆይ ኢጣልያ የሽንፈት ካባዋን ደፍታ አዲስ አበባ ላይ የሰላም ስምነትን ፈረመች።ኢትዮጵያንም ከእንግዲህ ወዲያ እንደነፃና እኩል አገር ልትቀበልና የወረራ ዓይኗን ዳግም ላታማትርባት ቃል አሰረች።
የዓድዋ ድል በአገር ቤት ጠንካራ የሕብረ-ብሔራዊ አንድነትና የአብሮነት መንፈስን አጠናክሯል።ኢትዮጵያ የማህፀኗ ፍሬዎች በሆኑት ብሔር ብሔረሰቦቿ ታፍራና ተከብራ የያኔውን የባህር ማዶ የዘመናዊ ሥልጣኔ ትሩፋት መቋደስ ጀመረች።
የዓድዋ ድል በባርነት ሰንሰለት እና በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ላሉ ጭቁን ሕዝቦች በተለይም ጥቁሮች የነፃነት ትግልን ያስተጋባ የድል ብስራት ደውል ሆኗቸዋል። ኢትዮጵያም የጥቁሮች የነፃነት ቀንዲል ሆናለች። ኢትዮጵያ የሚለው ስም የክብር፣ የሕብረት፣ የአንድነት፣ የነፃነትና የሉዓላዊነት ተምሳሌት ሆኗል።
የዓድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት ነው። ለአህጉረ-አፍሪካም የሕዳሴዋ መነጽር ሆኗታል። ዓድዋ ለጥቁርነት በራስ የመተማመንና የጥንካሬ እርሾ ነበር።ዓለም አቀፍ የጥቁርነት ሕብረት ለመፍጠርም የመሰባሰቢያ ጥላ ሆኗል።
በዓለም የፖለቲካ መድረኮች ጥቁሮች ጎልተው መውጣትና አንገታቸውን ቀና አድርገው ድምጻቸውን ማሰማት የጀመሩት ከዓድዋ ድል ማግስት ነበር። በተለይም በአሜሪካና በእንግሊዝ የጥቁሮች ሕብረታዊ ስብሰባዎች መጀመርና የዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አፍሪካ እሳቤ ማቆጥቆጥ የዓድዋ የድል ትሩፋት ናቸው። እድሜ ጠገቡ የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ መሰረቱን በኢትዮጵያኒዝም እሳቤ ላይ ነው ያቆመው።
የኋላ ዘመኖቹ የእነ ማርክስ ጋርቬይ የነፃነት የአስተምህሯው አስኳል፤ የእነ ክዋሜ ንክሩማህ እና የጆሞ ኬንያታ የወጣትነት የትግል ፋና ኢትዮጵያኒዝም ነበር። የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአብራኩ ክፋይ የሆነው የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረትም የምስረታው ጥንስስ ኢትዮጵያኒዝም የወለደው ፓን አፍሪካኒዝም ነበር።
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ ዓላማም የጥቁሮች የነፃነት ምልክት ሆኖ በመወሰዱ አፍሪካውያን ከነፃነታቸው ማግስት ብሔራዊ ምልክታቸው አድርገውታል። የዓድዋ የድል ትሩፋት በዚህ አያበቃም – ከደቡብ አፍሪካ ጀምሮ በመላው አህጉሪቱ በኢትዮጵያ ስም በርካታ የጥቁሮች ራስ-ገዝ አብያተ-ክርስቲያናት ተመስርተዋል፡፡
ዛሬስ እኛ?
ዓድዋ ከትላንት ታሪክም በላይ ነው።ገድሉ እንደጅረት በጊዜ ወንዝ መፍሰሱን የማያቋርጥ፤ ችቦው በትውልዶች ቅብብሎሽ እስከዘለዓለም የሚዘከር የኩራት ማህተም ነው።
ዓድዋ የግለሰቦች አልያም የጥቂት ስመ-ጥር መሪዎች ድል ብቻ አይደለም።እርግጥ ነው ጃንሆይንና እቴጌን ጨምሮ የያኔዎቹ መሪዎች ለድሉ ቁልፍ ሚና ነበራቸው።ከሁሉም በላይ ደግሞ ዓድዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድል ነው።
የዓድዋ ድል የተገኘው በሕብረ-ብሔራዊነት በተሰናሰለ የአንድነት ክንድ ነው።ዛሬም በተባበረ ክንድ ድል ልናደርጋቸው የሚገቡ ያልተፈቱ ቋጠሮዎች አሉብን።የጋራ ቤታችን ለሆነችው ለዚህች ድንቅ አገርና ለሕዝብ ፍቅር ቅድሚያ መስጠት ይገባል።ቤት ከፈረሰ ዞሮ መግቢያ የለም፤ ክብርም አይኖርም።
በዘርና በሃይማኖት ተቧድኖ ከመናቆር፤ በፖለቲካ ልዩነታቶች ተራርቆ ከመቆራቆስ ይልቅ ለብሔራዊ ጥቅም ዘብ መቆም ይገባል።የአገርና የእምነት መሪዎች እንዲሁም ሀሳብ አፍላቂዎች ሁሉ የአገር ሕልውናና የሕዝቦች አንድነት ሊያሳስባቸው ያስፈልጋል።
ዛሬ ያለን ትውልዶች ልክ እንደቀደሙቱ እናልፋለን። የሠራነው አሻጋሪም ሆነ አደናጋሪ ታሪክ ግን ሕያው ሆኖ ይቀጥላል። ከተራዘመ የእርስ በርስ ጦርነትና ከአስከፊ ረሃብ ማግስት የነበሩት የያኔዎቹ የዓድዋ ዘመን ኢትዮጵያውያን ለልዩነታቸው ቅድሚያ ሰጥተው ቢሆን ኖሮ ዛሬያችን ከዛሬው የተለየ መሆኑ እርግጥ ነው።
ኢጣሊያ ከ40 ዓመት በኋላ ለበቀል በተመለሰችበት ወቅት ከታጠቀችው መድፍ፣ ታንክ፣ አውሮፕላንና የኬሚካል መሣሪያም በላይ ኢትዮጵያን በዘርና በሃይማኖት የመከፋፈል እኩይ ዓላማንም ሰንቃ ነበር።
በጦር አውሮፕላን ታዘንብ ከነበረው ቦንብና የኬሚካል መርዝ ጋር ለትግሬው “አማራና ኦሮሞ ወረሩህ”፤ ለአማራው “ኦሮሞ ሊውጥህ ነው”፤ ለኦሮሞው “ሰሜኖቹ እያሴሩብህ ነው” የሚሉ የዘረኝነት መልዕክቶቿን በሕዝቡ ዘንድ አሰራጭታለች።
ባሳለፍነው የቅርብ ጊዜ ታሪካችንም እፉኝቱ ትህነግ ተመሳሳይ የዘረኝነት ፋሺዝም በኢትዮጵያ ላይ ፈጽሟል። በዚህ ሁሉ መካከል ወርቃማ እድሎች ከሽፈዋል።የሺህ ዘመናት የንግሥና ሥርወ-መንግሥትን የገረሰሰው የ1960ዎቹ አብዮት የያኔው የኢትዮጵያ ዕድል ነበር። ግና ያለፍሬ ጨነገፏል።የ1983ቱም አጋጣሚ ከነችግሮቹ የአገራችንን የጉዞ ትልም ያበሰረ ቢሆንም ቅሉ ከመክሸፍ አልዳነም፡፡
የ1997ቱ ደግሞ የቅርብ ጊዜ ትውስታችንን ያጭራል።ምርጫ 97 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የዴሞክራሲና የፍትሃዊ ሥርዓት ቋጠሮ የተወጠነበት ነበር።ይሁንና እንደቀደሙቱ ወርቃማ ዕድሎች መጨንገፍ ሆኗል ፍጻሜው።
አሁን ሌላ ዕድል መጥቷል። ይህ ዕድል ከቀደሙቱ በተለይም ከ1983ቱ እና 1997ቱ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ አንፀባራቂ አጋጣሚ ነው። የሕዝብ ብሶት የወለደውን ለውጥ አስቀድሞ ምርጫ 2013 በእጃችን ይገኛል።
ቀዳሚዎቹ ዕድሎች ትህነግ ይሉት የሸፍጥና የዘረኝነት ደራሲ ራሱ ጽፎ ራሱ የተወናቸው ነበሩ። የአሁኑ አጋጣሚ ግን በዋናነት ሴረኛውን ወያኔን ወደ ገሃነም የከተተ በመሆኑ ከሁሉም በጣሙን ይለያል። የተሻለ የተስፋ ነፀብራቅም ይታይበታል።እናም አሁን የተገኘው ዕድል እንዳይጨነግፍና ተስፋውም እውን እንዲሆን በልዩነታችን ያጌጥንበትን አንድነት ማጠንከር የግድ ነው።
የብሔርና የሃይማኖት ልዩነት ውበት ነው።ተደጋግሞ እንደሚገለፀው አንድ ዓይነት አበባ ካለበት መስክ ይልቅ ሕብረ-ቀለም ያላቸው ልዩ ልዩ አበቦች ያሉበት መስክ ጌጠኛ ነው።ኢትዮጵያም እንዲሁ በሕብረ-ብሔራዊነት ያጌጠች አገር ናት፡፡
በልዩ ልዩ ምክንያት የተቆራቆዝንባቸውን አሉታዊ የታሪክ ሰበዞች እየመዘዝን እንዲሁም የተቃርኗችንን ስንጥሮች እየነቀስን በንትርክ ልዩነታችንን ከምናሰፋ ይልቅ እንደ ዓድዋ ባሉት የጋራ ድሎቻችንና የከፍታ ኩራቶቻችን ዙሪያ መሰባሰብ አለብን።
ኢትዮጵያ ባልተረጋጋ ቀጠና ውስጥ ያለች ግን ደግሞ የተረጋጋ ሰላም ግንብታ የማደረግ መልካም ዕድልም ያላት ድንቅ አገር ነች። ከሁሉም በላይ የታታሪና ኩሩ ሕዝብ አገር ናት። እናም ሕዝቡም ሆነ መሪዎቿ እንደያኔዎቹ የዓድዋ ታሪክ ሠሪዎች አዲስ የድል እርሾ ለተተኪዎች ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል።
በደህና እሰንብት!
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013