(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
ቅድመ ነገር፤
“ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች” በሚል ርዕስ የውጭዎቹና የሀገር ውስጥ ደብዳቤዎች በተናጥል የተካተቱባቸው ሁለት ዳጎስ ያሉ የመጻሕፍት ጥራዞች ለንባብ የበቁት በ2003 ዓ.ም ነበር። አሳታሚው ደግሞ አስቴር ነጋ የተባለ ድርጅት ነው።
እነዚህ ሁለት መጻሕፍት መሠረታዊው ይዘታቸውና የጥራት ደረጃቸው ተጠብቆ እንዲታተም ከፍተኛውን የአርታኢነት ኃላፊነት የተወጣው ይህ ጸሐፊ ነው። የጳውሎስ ኞኞ ቤተሰቦችና የቤተሰቡ የቅርብ ሰው በሆኑ አንድ አባት ተነሳሽነት ለአንባቢያን እንዲደርሱ የተደረጉት እነዚህ ሁለት ታሪካዊ መጻሕፍት የሚሸፍኑት ከ1887 – 1901 ዓ.ም አፄ ምኒልክ ከተጻጻፏቸው እጅግ በርካታ ደብዳቤዎች መካከል የተወሰኑት ብቻ ተመርጠው ነው።
ይህ ጸሐፊ እንደ አርታኢነቱ “ዜና መዋዕል ዘምኒልክ” በሚል ርዕስ አጭር የማስታወሻ መንደርደሪያ በመቅድሙ ክፍል ለማካተት ሞክሯል። እጅግ ጠቃሚ ሃሳቦች ከተካተቱበት የመቅደሙ ክፍል ጥቂቱን ብቻ ማስታወሱ ለዚህ ወቅት ትርጉሙ ቀላል እንዳልሆነ ስላመነበት አንዳንድ ሃሳቦችን እንደሚከተለው ለማስታወስ ይሞክራል። የዓድዋ ጦርነት በኢትዮጵ ያዊያን ጀግኖች አሸነፊነት የተጠናቀቀው ከመቶ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት ልክ በዛሬው ዕለት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር።
ይህ የድል በዓል ከሌሎች ዓመታት ይልቅ በተለየ ሁኔታ ከሀገራችን ጫፍ እስከ ጫፍ በድምቀት እየተከበረ ያለው በዚህ በያዝነው ዓመት መሆኑ እውቅና ሊሰጠው ይገባል። ይህ ታላቅ ክብረ በዓል በቀደምት ዓመታት “አይቅርብን” በሚል “የአወቅሁሽ ናቅሁሽ” ዓይነት ስሜት ሲከበር ስለመኖሩ በብዙ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል። ዓድዋን ያህል ታላቅና ገናና “ዓለም አቀፍ በዓል” ለምንና በምን ምክንያት በራሳችን ጓዳ ውስጥ ብቻ፤ “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” በሚል የለበጣ ዝክር ሲታወስ እንደኖረ ዝርዝር ምክንያቱን መተንተኑን ለጊዜው በቤት ሥራነት በማስተላለፍ ወደ ተነሳንበት ዋና ሃሳብ ማቅናቱ የተሻለ ይሆናል።
የድል ማግሥት ርህራሄ፤
የዓድዋ ጦርነት በተጠናቀቀ ልክ በወሩ መጋቢት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለነምሳ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዊልያም፣ ለሮም ሊቃነ ጳጳስ ሊዮን 13ኛ፣ ለፖርቹጋል ንጉሥ ቀዳማዊ ቄርሎስ፣ ለቤልጅግ ንጉሥ ዳግማዊ ሊዎፖልድ፣ ለፈረንሳይ መንግሥት ፕሬዚዳንት ፊልክስ ፎርና ለሌሎች በርካታ የዓለም መንግሥታት፣ መሪዎችና ወዳጆቻቸው ከመቀሌ ሠፈራቸው ከጻፉት ደብዳቤ ውስጥ ከፊሉ እንደሚከተለው ይነበባል።
“…የኢጣሊያ ገንዘብ በላያችን ላይ የለብን። ለአገራችንም ድንበራቸው የራቀ ነው። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ነፃነትዋንና ራስዋን የቻለች መንግሥት የሆነውን በተንኮል ሊወስዱ እንዴት ይቻላቸዋል። …የእግዚአብሔር ኃያል በኔ አድሮ ድል አደረኳቸው። እኔም ወደዚያው ተከትዬ ብሔድ መቀሌ እርድ ገብተው አገኘሁ። ጦርነት ከሆነ ከትልቁ ጋራ እዋጋለሁ፤ እናንተ ክርስቲያኖች በውሃ ጥም አትለቁ ብዬ እስከ መሣሪያቸው ከእርድ አስወጥቼ ለጄኔራል ባራቴዬሪ ሰደድኩለት።…ጥንት ከአሕዛብና ከአረመኔ አገራችንን ጠብቋት የሚኖር እግዚአብሔር ከኛ በማይለይ ኃይል ድል አደረግኋቸው።
ጀግና ሰው ትሁት ነው። ጀግና በድሉ ግዝፈትና በምርኮው ብዛት እየፎከረ እብሪተኛና ትምክህተኛ ተሸናፊ ጠላቱን ከሰብዓዊነት ውጭ እያንገላታና እያሰቃየ “ጉሮ ወሸባዬ!”ን አይዘምርም። በማረከው ጠላቱ ጭንቅላት ላይ ቆሞም ኢሰብዓዊ ትርዒት አይከውንበትም። እንዲህ የሚያደርጉት ጨካኝና አረመኔ ፈሪ ወራሪዎች ብቻ ናቸው“ ።
የአፄ ምኒልክ የርህራሄ ጥግ እስከ ምን ድረስ የሰፋ እንደነበር ብዙ ተጠቃሽ አብነቶችን መዘርዘር ቢቻልም ለፈረንሳዩ ወዳጃቸው ለሙሴ ሸፍኔ ይህንንው ጉዳይ አስመልክተው በአንደኛው ደብዳቤያቸው ላይ ያሳፈሩትን ሃሳብ ብቻ እንደሚከተለው ማስታወስ ይቻላል።
“…ትግሬ ዘምቼ ካላጌ ጦርነት በኋላ፣ ኢጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያን ደምም በከንቱ አይፍሰስ፣ እርቅ ይሻላል ብላቸው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ። እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደርግኋቸው ብዬ ደስ አይለኝም። ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን።“ጀግንነት ይህ ነው። ምኒልክ ተግባራቸው ጮኾ የሚመሰክርላቸው እውነተኛ ርህሩህ ጀግና ናቸው ።
አሁንም ወደ መቀሌው ፍልሚያ ተመልሰን ሌላ የታሪክ ምስክር እናስታውስ። የምስክርነቱ የዓይን እማኝ የምኒልክ ጸሐፌ ትዕዛዝ የነበሩት ገብረ ሥላሴ ናቸው። እኒህ የታሪክ ምስክር “ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተለውን አስደናቂና ብዙ የውጭ የታሪክ ተመራማሪዎች ለማመን እስከመጠራጠር የደረሱበትን አንድ የጀግና ተግባር እንደሚከተለው በግልጽነት አስፍረዋል።
“… ከዚህ በኋላ በጅሮንድ ባልቻ መቀሌ ከእርዱ ውስጥ ገብቶ የኢትዮጵያን ባንዲራ ተከለበት። ኢጣሊያኖችም ከመቀሌ ከእርዱ ውስጥ ዕቃቸውን አንስተው ወጥተው ከሠፈር ዳር ከሜዳ ሰፈሩ። ነገር ግን ከእርዱ ውስጥ ከብታቸው በውሃ ጥምና በመድፍ በመትረየስ አልቆባቸው ዕቃቸውን የሚያነሱበት ከብት አጥተው ነበርና አፄ ምኒልክን ለመኑ። አፄ ምኒልክም በቸርነትዎ (የጥንት የታሪክ ጸሐፊዎች ነገሥታቱን እርስዎ እያሉ መጥቀሳቸውን ያስታውሷል) ከእንደርታ ነጋዴና ከባላገሩ 500 ግመልና በቅሎ በየዋጋቸው እየገዙ ጭነው እንዲሄዱ አዘዙላቸው። ለማጆር ጋሊያኖም ማለፊያ መርገፍ ኮርቻ የተጫነች በቅሎ ሰጡት።”
“ ይህንን ሁሉ መልካም ሥራ ለጠላቶቻቸው ሲሰሩ ባየ ጊዜ ያፄ ምኒልክ ሠራዊት ደስ አላለውም። እንዲህ ያለ መልክም ሥራ ለመልካም ሰው ውለታ ለሚያውቅ ሕዝብ ተደርጎ ቢሆን ከእንደዚህ ያለ ከከበረ ብልህ ንጉሥ ጋራ ብንዋጋ አይቀናንም ሲል እርቅና ፍቅር አድርጎ ይመለስ ነበር እያለ ተናደደ” (ገጽ 249)።
ጀግኖች አብዝተው ጦርነትን ይፈራሉ። የፍርሃታቸው መነሻ ለፍልሚያው በመስጋት ወይንም እንሸነፋለን ብለው ስለሚገምቱ አይደለም። ጀግኖች የድል በለስ እንደሚቀናቸው እርግጠኛ ቢሆኑም ጦርነትን የሚፈሩት የውጤቱን መራራነትና የአስከፊነቱን ጥግ ቀድመው ስለሚረዱት ብቻ ነው። የጀግኖች ፉከራ “ከእኔ በላይ ላሳር” በሚል እብሪት የተቃኘ አይደለም። ጀግንነት በፍርሃት ላይ ሰልጥኖ ድልን መቀዳጀት ብቻ ሳይሆን በጥልቅ ትህትናና ሰብዓዊነት የተንበረከከን ጠላት አቧራ አራግፎ በተገቢው ሰብዓዊ ክብር ተንከባክቦ ትምህርት መስጠትንም ያጠቃልላል። ዳግማዊ ምኒልክ ለወራሪው ተሸናፊ የኢጣሊያ ሠራዊት ያደረጉትም ይህንኑ ነው።
ዛሬን በትናንት እይታ፤
ስለ ዓድዋ ድል ሰሞኑን ብዙ ሲዘከርና ሲዘመር ከርሟል። “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ …” እንዲሉ ሆኖብን ባለፉት ረጂም ዘመናት በታሪካችን ጉዳይ እኛ ባለቤቶቹ ብዙ ጊዜ ዓይን አፋር አንዳንዴም ዓይን አውጣ በመሆን ወይ ድሉን አቅልለን አለያም ለድሉ ተቀዳሚ ተጠቃሾች ተገቢውን ክብር በመንፈግ በራሳችን ታሪክ ላይ በደል ስንፈጽም ብንኖርም እንደማያዋጣ በመገንዘብ ሀገራዊ ቀልባችንን ወደማሰባሰብ እየተቃረብን ይመስላል። በጽሑፎቼ ደጋግሜ ለማስታወስ እንደሞከርኩት “ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን መጫር ሳይሆን ፍሙን ማጋገሉ” ይበልጥ አዋጭ ይሆናል።
ዓድዋ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ብቻም ሳይሆን ለመላው የጥቁር ሕዝቦች በሙሉ ትርጉሙ የላቀ ስለመሆኑ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። የምንደጋግማቸውን “የስሙልን አዋጆች” በታሪክ ማረጋገጫነት ለዓለም ማኅበረሰብ በስፋት ለማስተዋወቅ ምን ያህል ዳተኛ እንደሆንን ግን ራሳችንን ብንወቅስ አይከፋም።
የታላላቅ ታሪክ ባለቤቶች ነን እያልን ለልጆቻችን የታሪክ መማሪያ መጻሕፍት እንኳን የመንፈጋችንን “ኃጢያት” ደግመን ደጋግመን እያወሳን ንስሃ ልንገባበት ይገባል። “የዓድዋን ድል ምን ያህል አክብረን ኖርን” ብቻም ሳይሆን ለወደፊቱስ ምን መደረግ አለበት በሚሉ ሀገራዊ ጉዳዮቻችንም ላይ በግልጽነት ልንወያይ ጊዜው የቀረበ ይመስላል።
በታሪኩ የሚያፍር ትውልድ በማንነቱ ላይ ጭቃ እንደመቀባት ይቆጠራል። ብዙ ዓለም አቀፍ ምሁራን ስለ ዓድዋ ድል በሚገባ የሚያውቁትን ያህል የእኛዎቹ “ቀለም ቆጠር ተመራማሪዎች ” ምን ያህል ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብለን ብንጠይቅ ስለሚያቋስለን በድርበቡ ጠቅሶ ማለፉ ብቻ ይበጅ ይመሰለኛል።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአንድ ወቅት በሊቢያ ሲርት በአንድ ዓለም አቀፍ የታሪክ ጉባኤ ላይ በተገኘበት አጋጣሚ ብዙዎቹ ባዕዳን የጥናት ወረቀት አቅራቢዎች ስለ ዓድዋ ድል አግዝፈው እየተናገሩ በአንፃሩም ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በምሬትና በትችት፣ አልፎም ተርፎ አሳፋሪ ገለፃዎችን ሁሉ እየተጠቀሙ ሲራቀቁና ሲመጻደቁ ማየት ምን ያህል አሸማቃቂና ለስሜት ህመም ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማዘጋጃ ቤታችን የቆመበትን እምብርት ታሪካዊ ቦታ አጎራብቶ “የዓድዋን ማዕከል” እየገነባ መሆኑን በአክብሮት ማበረታታቱ አግባብ ይሆናል።
በአቅራቢያው የሚገኘውን ታሪካዊውን የቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል (1860-1917፤ ሁለተኛው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ የንግድና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጠቅላይ ሚኒስት የነበሩ) መኖሪያ ቤት ለጣይቱ የትምህርትና የባህል ማዕከል መገልገያ እንዲሆን መስጠቱም የሚያስመሰግነው ነው።
ከዚህ በተረፈ ግን የዓድዋው ታሪካዊ ድል ወደፊት እጅግ ደምቆና ፈክቶ ክብሩን እንደጠበቀ ለትውልድ እንዲተላለፍ የትምህርት ሥርዓቱን በሚመራው አካልና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ብዙ ሥራ የሚጠበቅ ይሆናል። ይህ ግዙፍ ታሪክ መታወስ የሚገባው የየካቲት ወር በተቃረበ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ዓመቱን በሙሉ በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተዘከረ አርአያነቱ ሊታወስ ይገባል።
በዚህ ጸሐፊ የልጅነት ዕድሜ ከማዘጋጃ ቤቱ ግርጌ ግዙፉ ፎቅ በቆመበት ቦታ ላይ “ሲኒማ ዓድዋ” በሚል ስያሜ የሚጠራ ሲኒማ ቤት እንደነበር ያስታውሳል። ያ የበርካታ የዘመኑ ወጣቶች መዝናኛ የነበረው ሲኒማ ቤት ለምንና በማን ትዕዛዝ ፈርሶ ታሪኩ አቧራ እንዲለብስ እንደተደረገ ሊጠና ይገባል። በግንባታ ላይ ያለው የዓድዋ ማዕከል ሲጠናቀቅም ይሄው ሲኒማ ቤት ስሙና ተግባሩ ዳግም ደምቆ ቢታደስ ፋይዳው ከፍ ያለ ሊሆን ስለሚችል ከወዲሁ ቢታሰብበት አይከፋም።
ዛሬ ሀገራችንን በውጥር ቀስፈው የያዙ ችግሮቻችን መበርከታቸው ብቻም ሳይሆን መልካቸውም ዝንጉርጉር ነው። የዓድዋ የድል ብርሃን በፈነጠቀበት በትግራይ ክልላችን ውስጥ የተፈፀመውና እየተፈፀመ ያለው ሀገራዊ ፈተናችን በቀላሉ ተራምደን እንደምንሻገረው የበጋ ወንዝ የቀለለ አይደለም። ከሕግ ማስከበሩ ግዳጅ በኋላ ሕዝቡ ተረጋግቶ ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ ፈጥኖ እንዳይመለስ ብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ወጀቦችና አውሎ ነፋሶች እያወኩን እንዳሉ ነጋ ጠባ የምናስተውለው ነው።
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የፈፀሙትን ፈለግ በመከተል ከሰሞኑ ድንበር ጥሶ የገባውን የሱዳን የጦር ኃይልም መንግሥት ትእግስትና ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ተላብሶ ወራሪው ሠራዊት የደፈረውን አካባቢ በሰላም ለቆ እንዲወጣ ዕድል መስጠቱ እንደ ሽንፈት እየተቆጠረ ከዚያኛውም ወገን ሆነ ከወዲህኛው የእኛ ጎራ “እንካ ሰላንትያው” በስፋት እያወዛገበ እንዳለ እየሰማንም እያስተዋልንም ነው።
ይህ ሀገራዊ ፈተናችን በርግጥም በጥበብና በጥንቃቄ መያዙ በጀ እንጂ ዘገር ነቅንቀንና ነጋሪት ጎስመን ሆ! ብለን ብንነሳ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳን እኛና “የካርቱሞቹ ደርቡሾች” ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም። ትእግስት የፍርሃት መሸፈኛ ማስክ እንዳይደለ እስኪገባቸው ድረስ መታገሱ አግባብ ቢሆንም የሆደ ሰፊነታችን ምስጢር የማይገባቸው ከሆነ ከቀዳሚ ታሪኮቻችን መካከል አንዱ ሊፈፀም ግድ መሆኑ በአጽንኦት ሊነገራቸው ይገባል።
ታሪኩ የተፈፀመው በየካቲት ወር 1881 ዓ.ም ነበር። በመተማ በኩል ድንበር ጥሶ የገባው የሱዳኖቹ የደርቡሽ ጦር ይመራ የነበረው ዘኬም በሚባል ሰው ነበር። ይህ የወረራ ዜና የደረሳቸው አፄ ዮሐንስ ለእብሪተኛው ወራሪ መሪ እንዲህ ሲሉ መልዕክኛ ላኩበት። “…መጣሁብህ ተዘጋጅተህ ቆየኝ። እንደ ሌባ በድንገት መጣብኝ እንዳትል። …መምጣቴም ድፍረትህን ለመበቀል ነው።” እርግጥ ነው ለማስታወስ የተሞከረው የአፄ ዮሐንስን የጀግንነት መልስ እንጂ የጦርነቱ ውጤት በምን ዓይነት የከፋ መስዋዕትነት እንደተጠናቀቀ ታሪካችን ጠፍቶን አይደለም።
ዓድዋ የጀግንነታችን መገለጫ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ የኩራት ታሪካችንን ደግፈው ከያዙት ዋና ምሰሶዎች መካከልም አንዱ ነው። ክብር ለዓድዋ ሰማዕታት ጀግኖች! ክብር ዘላለማዊ የድል ሸማ አጎናጽፈውን ላለፉት ቀደምት መሪዎቻችንና ጀግኖች ወላጆቻችን! ክብር በተለያዩ ዘመናት ሀገራቸውን ከወራሪ ለመታደግ የደምና የአካል መስዋዕትነት ለከፈሉት ባለውለታዎች! ክብር ታሪካችን እንዳይደበዝዝ የአቅማቸውን ያህል ቅርሶችንና የታሪክ ምስክር ጽሑፎችን ትተውልን ላለፉ ምሁራን! ክብር! ክብር! ክብር በየዘመናቱ እንደ ወርቅ በእሳት እየተፈተነች ለምታሸንፈው ኢትየጵያችን! ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013