ማህሌት አብዱል
ዛሬ አንደአገር የመቆማችን ሚሥጥር የቀደሙት አባቶቻችን የደም ዋጋ የከፈሉበት ታላቅ ቀን ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሣንሆን በጭቆና ቀንበር ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦች ለነፃነታቸው እንዲነሱ እንደአብሪ ጥይት ብርሃን የፈነጠቀላቸው ታላቅ በዓል የሚከበርበት እለት ነው። ለዚህ ድል ያበቁንና ኢትዮጵያን የምንዘክርበትና የምናወሣበት ብሎም ለቀጣይ ዕድገታችን መሠረት ለመጣል ተሥፋ የምንሠንቅበት ድል ነው።
ይህንን ታላቅ በዓል ምክንያት አድርገን ባሠናደናው ልዩ መሠናዶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአርኪዮሎጂና በቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና በኢትዮጵያና ፈረንሣይ የቅርስ አድን ፕሮጀክት የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶክተር መንግሥቱ ጎበዜን እንግዳ አድርገናቸዋል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዓድዋ ድል የጦርነት ታሪክ ብቻ ነው ብለው የሚያነሱ ሰዎች አሉ፤ ለእርስዎ የዓድዋ ድል ምን ምን እንደሆነ ያንሱልንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ዶክተር መንግሥቱ፡– ብዙ ሰዎች የሚያስቡት የአገራችን ታሪክ የጦርነት ታሪክ እንደሆነ ነው።ግን አይደለም።በእርግጥ አገራችን ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ የታሪክ ዘመንዋ በርካታ ጦርነቶችን አስተናግዳለች።
ሆኖም አብዛኛዎቹ ጦርነቶች የአገርን ዳር ድንበር ከውጭ ወራሪዎች ለመጠበቅ የተደረጉ ናቸው።ከተሥፋፊዎች፣ ከቅኝ ገዢዎች ነፃ ለማድረግ የተደረጉ የመከላከል ጦርነቶች ስለሆኑ የኢትዮጵያ ጦርነት የመስዋዕዋትነት ጦርነት ነው።
ስለዚህ ለእኔ ዓድዋ አገር ለመጠበቅ የተከፈለ የመስዋትነት ቅርስ ነው ብዬ ነው የምወስደው።እንደሚታወቀው በድሮ ጊዜ በርካታ ጦርነቶች ከቱርክ ጋር፣ ከግብፅ ጋር፣ ከጣሊያን ጋር፣ ከደርቡሾች ጋር ፣ ከሶማሊያ ጋር ዳር ድንበር ለማስከበር በርካታ ትግሎች ተደርገዋል።እንግዲህ ከእነዚህ መካከል አንዱና ዋነኛው ሲሆን አባቶቻችንና እናቶቻችን የደም ግብር ከፍለው ያቆዩልን ድል ነው።
ስለዚህ ትልቅ የመስዋትነት ድል ነው።የመስዋዕትነት ቅርሣችን ነው።ቅርሥነቱም በዚህ ደረጃ የሚገለፅ ነው።በዓድዋ ጦርነት በርካታ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በአራቱም አቅጣጫ ተሣትፈዋል።ብዙ ጊዜ አንደሚባለው ከ100 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ሲሣተፉ ዘጠኝ ሺህ የሚደርሱት መሰዋታቸው ይታወቃል።በመሆኑም ለእኔም ሆነ ለብዙሃኑ ትልቅ የታሪክ አሻራ ያረፈበት ድል ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንዳሉት መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት መንፈስ ሆነው በሕብረት ያሸነፉበት ድል ነው።ከዚህ ድል በስተጀርባ ምን ሚሥጥር አለ ብለው ያምናሉ?
ዶክተር መንግሥቱ፡- እውነት ነው፤ ወትሮም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ከውጭ ወራሪዎች ጋር በነበራቸው የትጥቅ ጦርነቶች ተሸንፈው አያውቁም።ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉ።ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያውያን አንድነትና ውህደት ነው።በአንድ ልብ አስበው በመሣተፋቸው ነው ድሉ ሊገኝ የቻለው ባይ ነኝ።በተለይ ግን የዓድዋን ድል ስናነሣ ኢትዮጵያውያን የድሉ ባለቤት ስለመሆናቸው በርካታ አስተያየቶች ይሰጣሉ።በኢትዮጵያውያን ሠራዊት በኩል ድል እንዲቀናጅ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል በዋናነት የነበረው ጥልቅ የአገር ሥሜት ነው።
ከራስ በላይ አገርን የማስቀደም ጉዳይ፣ ጦርነቱ ለአገርም ለሃይማኖትም ጭምር የሚደረግ መስዋዕትነት መሆኑንም ለዚህ ደግሞ የአፄ ምኒሊክ የላቀ የጦርነት ሥልትና አመራር መሆኑ ይታወቃል።ለዚህም ደግሞ በወቅቱ የነበረው የሠራዊት ጠንካራ ሞራልና የሥነልቦና ዝግጅት ሕዝቡን የመንቀሣቀስና የመምራት ብቃት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በጣሊያን በኩል ደግሞ ኢትዮጵያውያን የነበራቸው ግንዛቤና ካርታ የተሣሣተ መሆኑ፤ በተለይም የመንገድ መሣሣት፣ በሁሉም መልክ የተሻልን ነን ብለው በማሠባቸው፣ ለኢትዮጵያውያን የሰጡት አነስተኛ ግምት ለሽንፈታቸው እንደመንስዔ ሊወሰድ ይቻላል።
ኢትዮጵያውያን ለሠንበትና ለሃይማኖታቸው የተለየ ክብር እንደሚሰጡ ያውቁ ስለነበርና ጦርነቱ ደግሞ የተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል በሚከበርበት እለት በመሆኑ እናሸንፋቸዋለን የሚል የተሣሣተ ምልከታ የነበራቸው መሆኑም አስተዋፅኦ አበርክቷል ባይ ነኝ።ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያውያን የነበራቸው ትልቅ ሞራል የአገር ፍቅር ሥሜትና አንድነት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዓድዋ ድል ዳር ድንበርን ከማስከበር ባለፈ ምን አበርክቶልናል ማለት ይቻላል?
ዶክተር መንግሥቱ፡- በእውነት የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በታሪኳ ካደረገቻቸው ጦርነቶች ሁሉ የተለየ ነው።እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ በርካታ ጦርነቶች ተደርገዋል፣ ግን የዓድዋ ጦርነት ለየት የሚያደርጉት ባህሪያት አሉት።አንደኛውና ዋነኛው ነገር ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም አቅጣጫ የተሣተፉበት የጦርነት ድል መሆኑ ነው።
በዚህ የዓድዋ ጦርነት የዘር፣ የብሄር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት ልዩነት ሣይኖር በድፍን ኢትዮጵያውያን የተገኘ መስዋዕትነት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።ስለዚህ የትኛውም ኢትዮጵያዊ በዚህ ጦርነት ውስጥ ያልተሣተፈ የለም።እናም የጋራ ጦርነት፣ እኛ የእኛ ብለን የምናስበው የአንድነታችን መገለጫ መሆኑ ነው።
ሌላው የዓድዋ ድል በጣም የተለየ የሚያደርገው ነገር ይህ ጦርነት በሁለት አህጉራት መካከል የተደረገ መሆኑም ጭምር ነው።ይህም ማለት በአፍሪካ የምትገኘው የኢትዮጵያና በአውሮፓ የምትገኘው የኢጣሊያ ጦርነት ነው።ስለዚህ ሁለት አህጉራትን ያሣተፈ ትልቅ ክብደት ያለው ጦርነት ነው።
በዚህ ላይ በዚያን ዘመን ጣሊያኖች ከፍተኛ የሆነና የተደራጀኛ የሠለጠነ የሰው ሃይል እንዲሁም በአግባቡ የተደራጀ ትጥቅ ነበራቸው።በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያውያን አልነበራቸውም።ስለዚህ በጣም ኋላቀር የሆነ መሣሪያ የያዘው ሃይል የተደራጀውን ሃይል ማሸነፍ መቻሉ ትልቅ ሚሥጥር ነው፡፡
ያ ዘመን በዓለም ውስጥ የቀኝ ግዛት የተሥፋፋበት ዘመን ነበር። አውሮፓውያን በተለይ ከበርሊን ኮንፈረንስ በኋላ አፍሪካን የተቀራመቱበት ዘመን ነው የነበረው። በዚያን ጊዜ የነበረው እሣቤ ነጭ የበላይ፣ ከፈጣሪ ቀጥሎ የሚታይ፣ ሌላው ደግሞ እንደ አገልጋይ በሚቆጠርበት ዘመን መሆኑና ነጮች በጥቁሮች መሸነፋቸው ልዩና የመጀመሪያ ያደርገዋል።
ስለዚህ የጥቁርን ማንነት ያስከበረ፣ የማይታሠበውን ይሆናል ተብሎ የማይገመተውን እንዲሆን ያደረገ ድል መሆኑ ለየት ያደርገዋል።ሌላው የዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያውያንን ነፃነት ከማረጋገጥ አልፎ ዓለማቀፋዊ እንቅስቃሴም የፈጠረ ነው።በርካታ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች በዚህ ምክንያት ተፈጥረዋል።ስለዚህ የጦርነቱ ውጤት ወደዓለም አቀፋዊነት ተሸጋግሯል።
ለምሣሌ በጦርነቱ እለት በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በፊት ገፅ ‹‹ኢትዮጵያውያን ጣሊያንን አሸነፉ›› የሚል ፅሁፍ አውጥቶ ነበር።ከአንድ ቀን በኋላ በዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣው ፅሁፍ የሮማው ጳጳስ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ መግባታቸውን አትቶ ነበር።ይህም በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት ማግኘቱን ያሣያል።
ከዚህ ባሻገር የጣሊኖቹ ሽንፈት በአፍሪካ፣ በኤዢያ፣ በአሜሪካና በካረቢያ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ማክተሚያው ሊሆን ይችላል በሚል ትልቅ ሥጋት በአውሮፓውያን ዘንድ ፈጥሮ ነበር።የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች የዓድዋ ድል ለመነሣሣት ምክንያት ተደርጎ ነው የሚቆጠረው።ወደ ነፃነት ትግል ለመግባት እንደአብሪ ጥይት ወይም መነሣሽያ ምክንያት ሆኗቸዋል።ስለዚህ ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ምልክት ሆና ልትወሰድ ችላለች።
ሌላው ሣልጠቅስ ማለፍ የማልፈልገው ጉዳይ የዓድዋ ድል የተጠናቀቀው በስድስት ሰዓታት ውስጥ ነው።እርግጥ ነው በዓለም ላይ እጅግ ፈጣን ተብለው የተመዘገቡ አሉ፤ አንዳንዶቹ በዓለም ቅርሥነት ተመዝግበዋል።ለምሣሌ በጣም የሚታወቀውና በእሥራኤል አሸናፊነት የተቋጨው የዐረብ -እሥራኤል ጦርነት የስድስት ቀን ጦርነት ነው።ይህ ጦርነት በአንድ አህጉር ውስጥ የተደረገ ነው።ከዚያ በላይ ዓለማ አቀፍ ተፅዕኖ የፈጠረውና በስድስት ሰዓታት ውስጥ ውጤት የታየበት በመሆኑ ከሁሉም በላቀ ደረጃ ሊመዘገብ የሚገባው ነኝ ባይ ነኝ።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ተፅዕኖውን ሥናይ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከማረጋገጡም በላይ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን አጎናፅፏታል።የበለጠ እንድትታወቅና እንድትከበር ዕድል ፈጥሮላታል።በአንፃሩ ደግሞ የቅኝ ገዢዎችን ቅስምንም ሠብሯል።
ፖሊሲያቸውንም እንደገና እንዲመረምሩ አስችሏቸዋል።ከዚህ በፊት ለምሣሌ የነበረው እሣቤ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የማሠፍሠፍ ጉዳይ ነበር።ከዓድዋ ድል በኋላ ግን ይህንን አመለካከታቸውን ሠርዘው ከኢትዮጵያ ጋር በአቻነት የተመሠረተ ግንኙነት ለመጀመር ሙከራ አድርገዋል።
በነገራችን ላይ ኤምባሲዎች የተከፈቱት ከዚያ በኋላ ነው።በአቻነት ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተጀመረው በዚህ ምክንያት ነው። ስለዚህ ለፓን አፍሪካኒዝም መነሣሣት፣ በሌሎች አካባቢዎች በቅኝ የተገዙ አገሮች የነፃነት ትግል ለመጀመር ፋና ወጊም በመሆኑ የዓድዋ ድል ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖው ከባድ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንዳነሱት የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ነፃነቱን ለተነፈገ ሕዝብ ፋና ወጊ ቢሆንም ለዚህ ድል የሚገባውን ክብርና ቦታ ሠጥተናዋል ማለት ይቻላል?
ዶክተር መንግሥቱ፡– እዚህ ላይ ገና ብዙ ችግር አለብን።ይህም ማለት የዓድዋ ድልን ለመዘከር የሚደረጉ ጥሩ ግን አነስተኛ መነሣሣቶች እናያለን።ነገር ግን ተገቢውን ቦታና ክብር አግኝቷል ብለን የምናስብበት ደረጃ ላይ አይደለንም።ምክንያቱም ዓድዋ የእኛ ነው።የአፍሪካ ነው።የነፃነት ድል ውጤት ነው።
እርግጥ ነው ተሸናፊው ሀይል እውቅና ሊሰጥልን አይችልም።ይህንን በማክበር የበለጠ በትምህርት ሰጪነት ወስደን አገራችንን በአንድነት፣ በሞራል፣ በልዩ የአገር ፍቅር ሥሜት ለመቀየር እንድንችል ነው ያነሣሣን።ስለዚህ በዓድዋ ድል አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን እኔ ተገቢውን እውቅናም አግኝተዋል ብዬ አላስብም።
የዓድዋ ድል ሲነሣ ከድሉ በስተጀርባ ያሉትን ሰዎች ወይም አመራሮችን ድንቅ ብቃት ለመገንዘብ እንችላለን።ይህን ስልሽም ለምሣሌ ከዚያ በኋላ የተካሄደው የማይጨው ጦርነት ብዙ የተሣካልን አልነበረም።ሽንፈት ገጥሞናል።ንጉሱም ወደ ውጭ ሄደዋል። ኢትዮጵያውያንም በየዱሩና በየጫካው አምሥት ዓመታት ሙሉ ሲታገሉ ነበር።ነገር ግን ልክ እንደ ዓድዋ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻል ነበር።
ለዚያ የተለየ ምክንያት አለ። በዓድዋ ጦርነት እንደሚታወቀው የተደራጀ ጥቅም የተደራጀ እሣቤም፣ ዘመኑን የዋጀ ዝግጅትም አልነበረም።አሠላለፉም ተመጣጣኝ አልነበረም።በማይጨው ጦርነት ግን ቢያንስ ቢያንስ የተሻለ ግንዛቤ የተሻለ የጦር ትጥቅ ነበር።ታዲያ ለምን ተሸነፍን የሚለው ትልቁ ነገር በዓድዋ ድል ላይ የአጼ ምኒሊክና የእቴጌ ጣይቱ ሚና እጅግ በጣም የጎላ ነው።
የእነሱ በሣል አመራር፣ ሥልታዊ አካሄድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ለድሉ መገኘት እጅግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።ስለዚህ የዓድዋን ድል ከእቴጌ ጣይቱና ከአፄ ምኒሊክ ለይቶ ማየት አስቸጋሪ ነው።
ይህን ለማንሣት የምገደድበት ነገር አፄ ምኒሊክ ለምንድን ነው ሕዝብን በማስተባበር ውጤታማ ሥራ የሠሩት? የሚለውን ነገር ማየት በጣም አስፈላጊ ነው።በተለይም ለዘመናችን መሪዎች ትልቅ ትምህርት ይሠጣል ብዬ አስባለሁ።
የአፄ ምኒሊክ ውጤት ከተክለ ስብዕናቸው እና ከባሪያቸው ይጀምራል።የግል ስብዕናቸው የመሪነት ብቃትና ጥበብ፣ የዲፕሎማሲያዊ ክህሎታቸው፣ የጦር ዕቅድ የማዘጋጀት አቅማቸው፣ በዓድዋ ድል በተገኘው ድል ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብዬ አምናለሁ።
በዚህ አጋጣሚ ስለአፄ ምኒሊክ አንዳንድ ነገሮችን ላንሣ።ምክንያቱም መቶ ሺህ በላይ ሠራዊት በአጭር ጊዜ ውስጥ አሠባስቦ ወደ ጦርነት ለመግባት እጅግ በጣም ትልቅ ብቃት የሚጠይቅ ነው።ይህ ሊሆን የቻለው ማህበረሰባዊ ሕዝባዊ ተቀባይነት ስላላቸው ነው።አፄ ምኒሊክ ሰብዓዊ ባህሪያቸው ሕዝባዊ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና በቀላሉ የማደራጀት አቅም እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል ብዬ አምናለሁ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነገሮችን ለማንሣት ምኒሊክ ከመናገር ይልቅ መሥማትን የሚያስቀድሙ ጥሩ አድማጭ ናቸው።ፈሪሃ እግዚአብሄር ያላቸው ሀይማኖተኛ ናቸው።ይህ ትልቅ የሥነ ምግባር ጉዳይ ነው።የዋህ ናቸው፤ ግን ደግሞ ብልህ ናቸው።የሴራ ፖለቲካ አያውቁም።
ከዚያ ይልቅ በሥነ ምግባር የታነፁ ድንቅ መሪ ናቸው።በዙሪያቸው የነበሩ አማካሪዎቻቸውን በአግባቡ የሚመርጡ መሪ ናቸው።ሲመርጡም ዋነኛ መሥፈርታቸው የአገር ፍቅር ያላቸው መሆናቸውን በመለየት ነው።
ለምሣሌ ፊት አውፈራሪ ሐብተጊርጊስ ዲነግዴ ወይም አባ መላ የሚባሉት እንዲሁም ራስ መኮንንና እቴጌ ጣይቱ ራሣቸው ተጠቃሽ ናቸው።እናም እንደዚህ ያሉ የአገር ፍቅር ያላቸውና አርቀው የሚያስቡ ሰዎች በዙሪያቸው ነው ያሉት።እነዚህ ሰዎች ጋር የሚያደርጉት ንግግር ጥሩ ነገር እንዲኖር ያስችላል፡፡
ከዚህም ባሻገር አጼ ምኒሊክ ከቂምና በቀል እጅግ በጣም የፀዱ፣ ለእርቅና ለሠላም ጠንካራ እምነት የነበራቸው ናቸው።ይህም በኋላ ላይ ትልቅ አቅም የፈጠረላቸው ነገር ነው።ለምሣሌ በእሣቸው ላይ ያመፁትንና ጦር የመዘዙትን ጠላቶቻቸውን ድል ካደረጓቸው በኋላ የተሸነፉት ሰዎችን ይቅር ብለው ወደ ቀደመ ክብራቸው እንዲመለሱ አድርገዋቸዋል።
ለምሣሌ የወላይታው ንጉስ ጦና እና የከፋው ንጉስ በአፄ ምኒሊክ ተሸንፈው መጨረሻ ላይ በምህረት ተለቀው ወደአካባቢያቸው እንዲመለሱ አድርገዋቸዋል።የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሀይማኖት ከአፄ ምኒሊክ ጋር ጦርነት ላይ ነበሩ።አፄ ምኒሊክ ካሸነፏቸው በኋላ ግን መልሰው የጎጃም መሪ አድርገዋቸዋል።
በመሆኑም የዓድዋ ጦርነት ሲመጣ እነዚህ ሁሉ ከምኒሊክ ጎን ተሠልፈዋል።ይህ ይቅርባይነት ባህሪያቸው ተቀባይነት እንዲያገኙ ትልቅ መሠረት ጥሎላቸዋል።በአጠቃላይ የአፄ ምኒሊክ አርቆ አሣቢነት፣ አገርን ማስቀደም መቻላቸው፣ ከቂም በቀል የፀዳ አመራር ያላቸው ሰው መሆናቸው በዓድዋ ጦርነት እንዲያሸንፉ አድርጓቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሌላው በአጼ ምኒሊክ እምነት ጀግንነት ማለት ማሸነፍ ብቻ ሣይሆን ለተሸነፈውም ሰው ምህረት ማድረግን ይጨምራል። ከዚህ በተጨማሪም ሲባዛ የማይቸኩሉና ለሚያደርጉት ነገር ሁሉ ምክንያታዊ ናቸው።በሥሜት ተገፋፍተው ወደ ርምጃ ወይም ወደበቀል የሚሄዱ አይደለም።
ይህ ባህርያቸው ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሣይሆን ለጣሊያኖችም ቢሆን የተረፈ ነበር።ለምሣሌ በእሣቸው ዘንድ የጣሊያን ምርኮኞች ከተማረኩ በኋላ በነፃ ክብራቸው ተጠብቆ ነበር የሚሸኟቸው። ስለዚህ እሣቸው ዘንድ ጠላትን መማረክ ብቻ ሣይሆን በክብር መያዝ፣ ሲሞቱ በክብር መቅበርና በጥቅሉ ለሰው ዘር በሙሉ ሰብዓዊ ክብር መስጠት የሚለው ቁልፍ ጉዳያቸው ነው።
ከዚህ ጋር በተገናኘ አካባቢውና ዓለማቀፋዊ ሁኔታዎችን በሚገባ መረዳት ትልቅ ሚና ነበረው።እናም ከዚያ አንፃር ዝግጅት አድርገዋል።በአካባቢው ምን እየተደረገ እንደሆነ ለማጣራት ጥረት አድርገዋል።ለኢትዮጵያ ያላቸውን አመለካከት ለማጥናት ጥረት አድርገዋል።ከዚህ አንፃር ቅድመ ዝግጅት ስላደረጉ የሚስተካከላቸው የለም።
ከጣሊያን ባሻገር ፈረንሣይና እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለመቀራመት አሠፍስፈው መቀመጣቸውን በሚገባ በመገንዘባቸው አስቀድመው ዘመናዊ መሣሪያዎችን በመሠብሰብና በመካከላቸው ፉክክር እንዲፈጠርም ሠርተዋል። ለምሣሌ በአጼ ምኒሊክ ምክንያት ሱዳን ውስጥ ፈረንሣይና እንግሊዝ አሹዳ በሚባል ቦታ ተጣልተዋል።
በዚህም እርስ በርስ እንዲጣሉ በማድረግ አጀንዳው እንዲቀየር ያደርጉ ነበር። ይህም አጠቃላይ ዓለማቀፋዊ ሁኔታን መረዳት መቻል የአፄ ምኒሊክ ትልቅ ብቃት ነው።
ሌላው አፄ ምኒሊክ ሊጠቀስላቸው ከሚፎካከራቸው መሣፍንት ጋር ሠላም ለመፍጠር አስቀድመው መሞከራቸው ነው።ምክንያቱም ወደ ጦርነት ከገቡ በኋላ ሌላ ችግር እንዳይፈጠርና ባንዳዎች እንቅፋት እንዳይሆኑባቸው በማሠብ ነው። ለምሣሌ ከትግራይ አስተዳዳሪ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር አስቀድመው ሥምምነት አድርገዋል።በዚህም አስቀድመው ችግራቸውን ፈተዋል።
እናም የአገር ውስጥ ችግራቸውን ከፈቱ በኋላ ነው ወደ ውጪው ጠላት ፊታቸውን ያዞሩት። አጼ ምኒሊክ እየመጣ ያለው አገራዊ ፈተና እና በወራሪዎች ሊከሰት የሚችለው አስከፊ ነገር በግልፅ ለሕዝባቸው ተናግረው የሕዝባቸውን ድጋፍ ጠይቀዋል።ትልቅነታቸው የሚታየው ደግሞ በሕዝባቸው ላይ ከፍተኛ መተማመን ማዳበራቸው ነው።
እና ግልፅ መሆን ያለውን ችግር በአግባቡ መናገር ሕዝቡ ከጎናቸው እንዲሠለፍ አድርጎላቸዋል።ጦርነቱ ስለቤተሠብ፣ ስለሃገር ተብሎ የሚደረግ መሆኑን፣ የአገር ዳር ድንበርና መሠረታዊ እሴቶቻችንን ለማጥፋት የመጣ ፀረ ኢትዮጵያ ሀይል መሆኑን እንዲረዳ አድርገዋል።
ከዚህም ባሻገር እንዲያሸንፉም ከፍተኛ መተማመን ነበራቸው።ይህም ሕዝቡን የማነሣሣት ሞራል የመስጠትና ከጎናቸው የመሠለፍ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።በዚህ ምክንያት ከ100 ሺህ በላይ የጦር አዝማች ለማደራጀት ችለዋል።ስለዚህ በዚህ አጭር ጊዜ ይህንን ያህል ሀይል ለማሠለፍ አጼ ምኒሊክን መሆን ያስፈልጋል።የአፄ ምኒሊክን መልካም ስብዕና መላበስ ይጠይቃል።
እቴጌ ጣይቱም ከዚህ ጋር ተለይተው የሚታዩ አይደሉም።እጅግ በጣም ብልህና አስተዋይ ናቸው።ገና ከመጀመሪያው የውጫሌ ውል ችግር እንዳለበት ሲያውቁ ውድቅ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።‹‹እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ይህንን ሥምምነት ከምቀበል ሞትን እመርጣለሁ›› የሚለው ንግግራቸው እጅግ ገዢ ነው።
በተጨማሪም የራሣቸውን ወደ 12 ሺህ የሚሆን ሠራዊት መርተው የተጓዙ ናቸው። የጠላት ሀይል በደንብ እንዲዳከምና አቅሙን እንዲያጣ አድርገዋል።ለዚህ ደግሞ የመቀሌ ውሃ እንዲከለል ለራስ መኮንን አቅጣጫና ምክር በመስጠት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።ሌሎችንም ሰዎች በመሠብሠብ የውስጥ አርበኝነት ሥራ እንዲሠሩ አስተዋጽኦ አላቸው።በመሆኑም ኢትዮጵያውያንን ለማክበርና የዓድዋን ድል ለመዘከር እንዲህ ዓይነት አሥተዋጽኦ አለው ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንፃር የሚነሱ ቅሬታዎችና ትርክቶችን በምን መንገድ ማሥታረቅ ይቻላል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር መንግሥቱ፡– እውነት ነው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በተለይ ለፀብ ምክንያት የምናደርገው ታሪክን ነው። ታሪክ ለኢትዮጵያ ትልቅ ሐብት ነው። ታሪክ ቅርስ ነው፣ ታሪክ ቱሪዝም ነው።ታሪክ ድል ነው። የህብረተሰብን አንድነት የሚያጎላ መሠረት ነው።ይህንን በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም።
ነገር ግን የሚያጣላን ታሪክ ሣይሆን ሐሰተኛ ትርክት ነው።መሠረት የሌለው ነገር በማንሣት ነው እርስ በርስ የምንባለው።ከዚህ አንፃር አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያውያን ከምናውቃቸው በላይ የውጭ ሰዎች ያውቋቸዋል ብዬ አምናለሁ።
ስለእሣቸው ጀግንነትና መልካም ስብዕና ብዙ ፅፈዋል።ትልቅ መሠረታዊ ችግር ብዬ የማስበው የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ትልቅ ኩራት ነው፤ ለኢጣሊያ ደግሞ ሽንፈት ነው።በዚህ ምክንያት ብዙ ነገር ደርሶባቸዋል።እንደሚባለው ከጦርነቱ ጀምሮም ሆነ ከጦርነቱ ማግሥት ጀምሮ ዓለም አቀፍ ዘገባ እስከሚዘገብባቸው ድረስ ጣሊያኖች ከፍተኛ ውርደት ተከናንበዋል።ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን በሠልፍ አውርደዋል።
ይህንን ሽንፈት ለመበቀል ብዙ ዘመናት ተዘጋጅተዋል።የተሸነፉበትን ምክንያት ለማወቅ ራሣቸውን መርምረዋል።እኛ ከእነሱ የተሻልን ሆነን ሣለን እንዴት በኋላ ቀርነትና ምንም መሣሪያ በሌላቸው ሰዎች ልንሸነፍ ቻልን ብለው ለዘመናት ራሣቸውን ጠይቀዋል።በነገራችን ላይ በዚህ ዙሪያ ብዙ መፅሃፎች ተፅፈዋል።
ለሽንፈታቸው ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያውያን አንድነት መሆኑን ጠንቅቀው በመረዳታቸው የአንድነታችን ምሰሶ ናቸው የሚባሉትን አንኳር ጉዳዮች ለይቶ ወደማበላሸት ተግባር ላይ ነው የተጠመዱት።የኢትዮጵያ አንድነት፣ ህብረብሄራዊነት፣ የጋራ እሣቤያችን ከጥንት እስከ ዛሬ አስተዋፅኦ አድርገዋል በሚባሉ ነገሮች ላይ ሥራ መሥራት ነው የተያያዙት።ለምሣሌ ሕዝቡን በልዩነት መከፋፋል፣ አንዱ ብሄር ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ፣ አንዱ ሀይማኖት የበላይ ሌላው የበታች አድርገን መሥራት
አለብን የሚል ሠፊ ዘመቻ አድርገዋል። ይህም ምንም እንኳን በወቅቱ ባይሣካም አሁን ላይ እያየን ነው።የሚገርምሽ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስለዓድዋ ድል ሣይንሣዊ ፅሁፍ የፃፉ ሰዎች አሉ።አንዳንዶቹ የዓድዋን ጦርነት እንደፈጠራ ጦርነት አድርገው ነው የወሰዱት።እንዲያውም አንድ የጣሊያን ፀሐፊ የዓድዋ ጦርነት ከባድመ ጦርነት ተለይቶ የሚታይ እንዳልሆነ ፅፏል።
አጼ ምኒልክ የሚመሩት የሸዋ አማራ በትግራይ ላይ ጫና ለመፍጠር ያደረገው ጦርነት ነው የሚል እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ መርዝ ድሮ የቀበሩትን ፈንጂ ፈልፍሎ የሚያፈነዳ ዓይነት እሣቤ አስከትሏል።ይህንን ነገር ሌሎቹ ደግሞ ተቀብለው የማሠራጨት፣ የማራገብና ወደተሣሣተ አቅጣጫ እንዲወርድ አድርገዋል።
በመሆኑም የተሸናፊዎች የሐሳብ ምርኮኛ መሆናችን ነው ትልቁ ችግር።የእነሱ ፕሮፖጋዳ አቀንቃኝ መሆናችን ነው ትልቁ ጥፋታችን።እነሱ መግለፅ የማይችሉትን የእኛ ሰዎች ገዝተው መግለጥ በመጀመራቸው አፄ ምኒሊክ ካበረከቱት አስተዋፅኦ ይልቅ ያላደረጉት ነገር እንደተደረገ ተደርጎ የሚነገረው ነገር ጎልቶ እየተሠማ ያለው።ይህም ኢትዮጵያውያ የዚህ የተሸናፊ ሃይሎች ተላላኪ ሀይሎች በመሆናቸው የተፈጠረ ነው ብዬ የማስበው።
ይህንን ጉዳይ በአግባቡ ማንሳት ይገባል ባይ ነኝ።አፄ ምኒሊክ ባልነበሩበት ጦርነት ጡት ቆርጠዋል ተብሎ ሃውልት መቆሙ ታሪኩን ለሚያውቅና አገሩን ለሚወድ ዜጋ እጅግ አሳዛኝና ልብ ሰባሪ ነው።እውነታው ግን አርሲ ላይ የዘመቱት አፄ ምኒሊክ ሳይሆኑ ራስ ጎበና ናቸው።ራስ ጎበና የኦሮሞ ሰው ናቸው።
አንዳንዶቹ እንደውም በዚህ ጦርነት ውስጥ አፄ ምኒሊክ ባዮሎጂካል መሳሪያ ተጠቅመዋል እስከማለት የሚደርስ የውሸት ትርክት ህዝብ ላይ እስከመጫን ደርሰዋል።በመሆኑም በዚህ ምክንያት የዚህ የሃሰተኛ ትርክት ሰለባና የውጭ ሃይሎች ርዕዮተ ዓለም አስተላላፊ እየሆነን በመገኘታችን ይመስለኛል እንዲህ አይነት ችግር የተፈጠረው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላው ማንሳት የምፈልገው ነገር የዓድዋ ድል የተወሰነ ብሄረሰቦች ድል አለመሆኑን ነው።ከዚህም አልፎ የመላው አፍሪካውያንና በጭቆና ቀንበር ውስጥ የነበሩ ህዝቦች ድል ነው፡፡በዋናነት ደግሞ የአፍሪካ ድል ነው።ለዚህ የሚያግዙ እንደፓን አፍሪካኒዝም የመሳሳሉት እንቅስቃሴዎች የተነሱት ከዚያ በኋላ ነው።
ስለዚህ ዓድዋ ለነፃነትና ለፍትህ የተደረገ ጦርነት ፣ ለጥቁሮች የነፃነት ትግል ያነሳሳ መንገድ የጠረገ ትልቅ ድል ነው።ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሰረት የጣለ ነው።በነገራችን ላይ በዓድዋ ድል መነሻነት ኢትዮጵያ ትልቅ ተቀባይነት በማግኝቷ ሌሎች አገራት ነፃ እንዲወጡ ተምሳሌት በመሆን አዲስ አበባ ላይ ህብረቱ እንዲመሰረት ሆኗል ።
ስለዚህ የዓድዋ ድል የአፍሪካ ድል ነው፣ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ያስመዘገቡት ድል ለአፍሪካውያን አንድነት መሰረት የጣለ ነው።በተጨማሪም የቀኝ አገዛዝ አስተሳሰብ እንዲያከትም ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል።ከዚሁ ጎን ለጎንም ለቀኝ ገዢዎችና ተስፋፊዎች ትምህርት ሰጥቷል።
ይህም ከአፍሪካ ጋር ተባብሮ መስራት እንጂ ሃብቱን መበዝበዝና ሰብአዊ ክብሩን መንካት የማይቻል መሆኑን ያስገነዘበ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው።ድሮ አፍሪካን የሚያስቡት የገቢ ምንጫቸው አድርገው ነው።ነገር ግን ከዓድዋ በኋላ ተባብሮ መስራትና በጋራ እሳቤ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ማድረግ አንደሚገባ ተገንዝበዋል።
ሌላው የዓድዋ ድል የቀኝ አገዛዝ ስርዓት መሸነፍ እንደሚችል ትልቅ ትምህርት ሰጥቷል።ከዚያ በፊት ነጭ በጥቁር ይሸነፋል ተብሎ አይታሰብም ነበር።ነገር ግን ዓድዋ ሽንፈት እንዳለ አስተምሯል።
ለወደፊቱም አንዲያስቡበት ያደረገ ነው።ከዚያ በኋላ ነው ቀኝ ገዢዎች አፍሪካን ለቀው የወጡት። በጥቅሉ የዓድዋ ድል የአፍሪካ ታሪክ መዘውር ነው ማለት እንችላለን። አዲስ ክስተት ፈጥሯል።ለዘመናዊ አፍሪካ ፖለቲካ ፣ የማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች መሰረት የጣለ የሁሉም አፍሪካውያ የታሪክ ቅርስ ነው፡፡
ሌላው እምነትን ጭምር ማስቀየር የቻለ ነው።ዓድዋ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ እንዲሆን በማድረግ የይቻላል መንፈስ የፈጠረ የ19ኛው ክፍለ ዘመን አብይ ክስተት ነው።ነጭን ማሸነፍ ይቻላል፤ ከወራሪዎች ነፃ መውጣት ይቻላል፤ የአገር ሉዓላዊነት ማስከበር ይቻላል፤ በአንድነት ተባብሮ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፤ የሚል አስተሳሰብን ፈጥሯል።ስለዚህ ከዚህ አንፃር የዓድዋ ድል በአለምአቀፍ ቅርስነት መታሰብ ያለበት ድል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ዶክተር መንግሥቱ፡-የዓድዋ ድል የላቀና ሁለንተናዊ እሴትነት ያለው በመሆኑ በዩኒስኮ ማስመዝገብ ይቻላል።በሌሎች አለማት የጦርነት ድሎች በቅርስነት ተመዝግበዋል። አይደለም የጦርነት ድል ይቅርና እንቅስቃሴዎቻቸው በራሱ በአለም ቅርስነት የተመዘገበበት ሁኔታ አለ።ለምሳሌ ኔልሰን ማንዴላ የታሰሩበት ደሴት በአለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡
ለዚያ ቅርስ መመዝገብ ትልቁ ምክንያት የነፃነት ታጋይ የሆኑት ታላቅ ሰው የታሰሩበት ቦታ እንደነፃነት ምልክት ተደርጎ በመወሰዱ ነው።ዓድዋ ግን ከዚያ በላይ ነው።አፍሪካዊ ምልክትም ስለሆነ የራሱ የሆነ ቦታና ክብር ሊሰጠው ይገባል ብዬ አስባለሁ።ካሉት የጦርነት ድሎች ሁሉ የነበረው ተፅዕኖ የዓድዋ ድል ሚዛን የሚደፋ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንጻር የተጀመሩ ስራዎች ካሉ ቢጠቅሱልን?
ዶክተር መንግሥቱ፡– ከዚህ አንፃር አንድ ክስተት በአለምአቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ በመጀመሪያ ደረጃ አገራት ዝግጅት ማድረግ አለባቸው።ቅርሱ የሚጠበቅበትና ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍበትን ሰነድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
እስካሁን ይሄነው የሚባል ጥረት ባይደረግም አሁን ላይ ግን የሚያስፈልጉትን መስፈርቶችን ማሟላትና ዝግጅት ማድረግ ይገባል።ለዚህ ደግሞ ድሉ የመላው አፍሪካውያን እንደመሆኑ የአፍሪካ ህብረትም ማገዝ አለበት።አፍሪካውያንም ድጋፍ ማድረግ አለባቸው።
በተለይም ህብረቱ ይህንን እንቅስቃሴ በሃላፊነት ወስዶ ለውጤት ማብቃት ይጠበቅበታል።በመሆኑም በመጀመሪያ በአፍሪካ ደረጃ እንዲታወቅ ማድረግ ያስፈልጋል።የአፍሪካውያን ድል ስለመሆኑ ማሠብና እውቅና መስጠት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር መሠነድ ይገባል። ዓድዋ ን የሚዘክር ሐውልትና ማስታወሻ በህብረቱ ግቢ ውስጥ ማቆምም ይገባል። በመሠረቱ ዓለም አቀፍ እውቅና ለማሠጠት ይቅርና በድሉ ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ራሣችን ገና አልተስማማንም።
የታሪክ ውለታው ከፍ ያለ ቢሆንም አስቀድሜ እንዳልኩሽ የቀኝ ግዛት አስተሳሰብ ውስጣችን በመሥረፁ በጋራ ድላችን መሥማማት አልቻልንም።አባቶቻችን የደም ዋጋ ከፍለው ለእኛ ያቆዩልንን አገር እኛ በገዛ ፍቃዳችን በአስተሳሰብ ቅኝ ተገዝተናል።ስለዚህ የራሣችንን እንቁዎች በመጣላችንና ለራሣችን የምሰጠው ቦታ አነስተኛ በመሆኑ ባለቤቱ ያላከበረውን አሞሌ ባለዕዳ አያከብረውም እንደሚባው ሁሉ ራሣችንን አዋርደናል።
ስለዚህ ከሁሉ በፊት እኛ አንድ መሆን አለብን።የጋራ እሣቤ የጋራ መግባባት ሊኖረን ይገባናል።ለዚህ ደግሞ በእኛ ደረጃ የቤት ሥራችንን መሥራት ይጠበቅብናል።በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የራሣቸውን ሀላፊነት መወጣትና ተባብረው መሥራት አለባቸው።
ከዚህ አንፃር በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ይልቅ ግለሰቦች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አደንቃለሁ።ለምሣሌ የእጅጋየሁ ሽባባው እና የቴዎድሮስ ካሣሁንን የጥበብ ሥራዎች ማየት ይቻላል።የፕሮፌሠር ሃይሌ ገሪማን ፊልም መጥቀስ ይቻላል።በእነያሬድ ሹመቴ የሚመራው የዓድዋ ተጓዦችን እንቅስቃሴ ማንሣት ተገቢ ነው።
የዓድዋ ፓርክ በመገንባት ሂደት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚያደርገው እንቅስቃ እንዳለ ሆኖ እንደአጠቃላይ እንደመንግሥት ግን በቂ ትኩረትና ቦታ አግኝቷል ብዬ አላምንም።በነገራችን ላይ ጥቅሙ ለእኛ ነው።
የዓድዋን እንቁዎች ማክበራችን የምንከበረው እኛ ነን።እነሱማ ታሪክ ሠርተው ይህችን አገር ለእኛ አስከብረው አቆይተዋል።ስለዚህ አሁን ያለነው ትውልድ የራሣችንን ታሪክ ሠርተን ማለፍ ነው የሚጠበቀው፡፡
እዚህ ጋር ሣልጠቅስ ማለፍ የማልፈልገው ነገር ዓድዋ ህብረብሄራዊነት የሚገለፅበት፣ ኢትጵያዊያን ያለልዩነት የተሣተፉበት የአብሮነት ምልክት ነው።ከዓድዋ በላይ ለእኛ የአንድነት ተምሣሌት የለም።ይህ ሆኖ ሣለ በሚያሣዝን ሁኔታ በጎሣ ፖለቲካ ደዌ አገራችን በፅኑ ታማለች።
ስለዚህ ውስጣችን ስለታመመ በውጭ ሃይሎች በቀላሉ እንድንደፈር ሆነናል።ለምሣሌ የሱዳን ሃይል የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሠብሮ የገባው ውስጣችን ችግር እንዳለ ስለገባው ነው።አሁንም የውስጥ አንድነት እስከሌለ ድረስ የውጭን ዳር ድንበር ለማሥከበር አስቸጋሪ ነው።ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክንያት በብሄርና በጎሣ መከፋፈላችን ነው።ከዚህ ደዌ እስካልተፈወስን ድረስ ዓድዋን መድገም አንችልም።
በነገራችን ላይ አባቶቻችን ከነጭ ወራሪ የታደጉትን አገር በጎሣ ፖለቲካ ማተራመስ በራሱ አሣፋሪ ነው።እኛ በእውነት የአባቶቻችን ልጆች ነን ብለን መናገር የሚከብድ ነው።ዓለም ወደአንድ መንደር በተለወጠበት ዘመን እኛ ወደሠፈር ወርደን ችግር ውስጥ በመግባታችን አገራችንን ለውርደት ዳርገናል።በመሆኑም ከዚህ መማር ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን:- ከዚህ አንፃር የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ምን ሊሆን ይገባል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር መንግሥቱ:- እኛ እንኳን በዚያ ደረጃ ልንደርስ እንደሃገርም ለመቆም እያቃተን መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው። ስለዚህ ትውልዱ ከዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን አንድነትንና ትብብር መማር ካልቻለ መቼም ቢሆን ለዚህ ሕመሙ ፈውስ አያገኝም ብዬ አምናለሁ። በተለይ በፈጠራ ትርክት ላይ ተመሥርቶ የሚሰራው እና የሚኬድበት መንገድ እጅግ በጣም አደገኛ ነው።
ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። ድሮም ለዓድዋ ድል መገኘት ትልቁን ሚና የተጫወተው መንግሥት ነው፤ ይህ ዓይነት የወረደ አስተሳሰብ እንዲወገድም ትልቁን ድርሻ መወጣት ያለበት መንግሥት ነው። በመሠረቱ አሁን ላለንበት ዝቅጠት፤ ልዩነት መከፋፈል እና ሀገርን ለአደጋ ላጋለጠው ነገር መፈጠር ተጠያቂው መንግሥት ነው።
በመሆኑም መንግሥት ያበላሸውን ደግሞ ራሱ መንግሥት ነው ማስተካከል ያለበት። ከዚህ አንፃር ወደክፍፍል የመራንን ሕገመንግሥት ማሻሻል እና ሕዝባዊ ተቀባይነት ያለው የተሻለ መግባቢያ ሠነድ እንዲኖር ለማድረግ ተነሣሽነቱን መንግሥት መውሰድ አለበት። መንግሥት በዚህ ረገድ የአፄ ምሊልክን ዓይነት አመራር መስጠት ከቻለ የዓድዋ ድልንም መድገም ይችላል ብዬ አምናለሁ።
የዓድዋን ድል ለማግኘት ማለትም ኢትዮጵያውያንን በአንድ ልብ በአንድ ሐሳብ ለመምራት አፄ ምኒሊክን መሆን ያስፈልጋል ብዬ እመክራለሁ። ኢትዮጵያውያንም ከዚህ አንፃር ራሣቸውን መቃኘት አለባቸው። ከልዩነት ማንም ተጠቃሚ አይኖርም፤ ትርፍ የለውም። ትርፍ ያለው ትብብርና አንድነት ነው።
ከምንም በላይ ሀገርን ማስቀደም ይገባል። በዓድዋ ድል ወቅት ዘጠኝ ሺህ ገደማ አባቶቻችን መስዋዕት የሆኑት ከራሳቸው በላይ ሀገራቸውን በማስቀደማቸው ነው። በአስቸጋሪ መንገድ እና ያለሥንቅ በችግር ውስጥ ራሳቸውን ሠጥተው ሀገራችንን አቆይተውልናል። አባቶቻችን ያቆዩልንን ሀገር ደግሞ ተቀብለን፣ አንድ ሆነን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የዜግነትም ግዴታ ነው። ኢትዮጵያዊነት ማለት ይህ ነው ለእኔ በአጭሩ።
አዲስ ዘመን:- ለአንድነቱ መሣሣት መንስዔ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የትምህርት ሥርዓቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል፤ በተለይ የታሪክ ትምህርትን ትውልዱ በአግባቡ እንዳያውቀው ተደርጓል፤ ከዚህ አንፃር ምን መሠራት አለበት?
ዶክተር መንግሥቱ:- እኔ ለሁሉ እሳቤያችን መሠረቱ ሕገመንግሥቱ ነው ብዬ ነው የማስበው፤ ለዚህም ነው እርሱ ላይ ትኩረት የማደርገው። ምክንያቱም ሕገመንግሥቱ ከመነሻውም በተሣሣተ ትርክት ተመሥርቶ ነው የተነሳው። በቀደመው ጊዜ ጨቋኝ ተጨቋን እንደነበር አድርጎ ነው የሚነሳው። በህብረተሰብ መካከል ልዩነት እንዳለና አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ አድርጎ ያቀርባል።
ኢትዮጵያ ደግሞ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ቅርጫት አድርጎ ያስቀመጠ በመሆኑ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን እና ብተና ላይ ትኩረት ያደረገ አቀራረብ አለው። አንድ ሀገር የምትተዳደረው በሕገመንግሥት ነው፤ ሥርዓተ ትምህርቱምቢሆን ከሕገመንግሥቱ አንጻር ነው አቀራረጹም የሚከናነው።
በየቦታው የሚተራመሰው የክልል አደረጃጀትም ሆነ የጎሣ፣ ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ሕገመንግሥቱን መሠረት ያደረገ ነው። ይሄ አሠራር በየትኛውም ዓለም ላይ የሌለ እና በኢትዮጵያ ብቻ ያለ መሆኑ ይታወቃል። 27 ዓመት ተሞክሮም ያልጠቀመ በመሆኑ በመጨረሻ ወደጦርነትና ወደግጭት እያመራን ነው። በሽታውን እያወቅን ለጨጓራ ሕመም የራስ ምታት ክኒን መውሰድ ያለብን አይመስለኝም።
ሕገመንግሥቱ ኢትዮጵያውያን የሚግባቡበት የመግባቢያ ውል መሆን አለበት የሚለውን ላሠምርበት እና ወደታሪክ ትምህርቱ ልመለስ። ለኢትዮጵያ ታሪክ እና እርሻ በጣም ወሣኝነት አላቸው። ከ80 በመቶው በላይ ሕዝብ በግብርና የሚተዳደር በመሆኑ ግብርናው ለሀገር ምጣኔ ሀብት ቁልፍ ነው። በተመሣሣይ ታሪክም ለዚህች ሀገር ቁልፍ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ለሦስት ዓመታት ዘመን ያልተቋረጠ የመንግሥት አስተዳደር ያላት ሀገር ናት። ማንም ሀገር ይህን ያህል የተጓዘ የለም፤ እና ግን አባቶቻችን በከፈሉት የደም ግብር የተነሣ ለዚህ ደርሠናል። ብዙዎቹ የአፍሪካ እና የዓለም ኃያላን ሀገራት ከዚያ በኋላ የተቋቋሙ ናቸው።
ከአሜሪካ በፊት ታላላቅ ለዓለም የሚተርፉ ፈጠራ እና ቅርሦችን አበርክታለች። እኛ ራስ ነበርን፤ አሁን ጅራት ሆነናል። ታሪኳ፣ ሕይወቷ እና ቅርሷ የሆነውን ወደልማት መቀየር እንችላለን። ይህ የሚሆነው ግን ትክክለኛውን ታሪክ በሚገባ መረዳት ስንችል ነው። ከመንግሥት አንፃር በትምህርት ሚኒስቴርም ይሁን ትምህርት ቢሮዎች የታሪክ ትምህርት ትኩረት እንደተሠጠው በተግባር ማሣየት አለበት።
መንግሥት ታሪክ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳልሆነ መግለጽ መቻል አለበት። ዛሬን የያዘ የትናንት ባለቤት ነው የሚባል አባባል አለ፤ ምክንያቱን ዛሬ ላይ ያለው የትናንቱን እንደፈለገ በራሱ መንገድ ስለሚቃኘው ነው። ይህ ግን መሆን የለበትም። መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ ቁርጠኝነት መኖር አለበት።
በቅርብ ጊዜ ሲያከራክር የነበረውን ጉዳይ መመልከት ቢቻል እንኳን የታሪክ ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስተማሪያ ሞጁል የነበረው በጣም አሣዛኝ እና የኢትዮጵያን አንድነት የማያውቁ ሰዎች ያዘጋጁት ነበር። ኢትዮጵያ ማለት በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ምኒሊክ የተመሠረተች አድርጎ የሣለ ነበር፤ ይህ በጣም የሚያሣዝን እና የሦስት ሺህ ዓመታት ታሪኳን የዘነጋ ነበር።
በሌላ በኩል የተሣሣቱ ትርክቶች ነበሩ ታሪክ ውስጥ፤ አፄ ምኒሊክ እንደጨቋኝ እና እንደወራሪ ተደርገው ተስለዋል። ይህ ሐሳብ ከፋፋይ በመሆኑ አይጠቅምም። በመሆኑም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚገኙ አካላት ስለታሪክ ትምህርቱ ይበልጥ ሊያስቡ ይገባል። ለሙያው የሚቆረቆሩ የታሪክ ተመራማሪዎችና ህብረትም ያስፈልጋል። ህብረት ፈጥረውም ትክክለኛው ታሪክ እንዲነገር እና ለትውልድ እንዲተላለፍ መጣር አለባቸው።
ትውልዱ በታሪክ ተጎጂ ሣይሆን ከታሪክ የሚጠቀምበትን ዕድል ለመፍጠር የታሪክ ምሁራን የራሣቸውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ይሠማኛል። በአጠቃላይ ግን እያጣላን ያለው ታሪክ ሣይሆን የፈጠራ ትርክት ነው፤ በመረጃ ላይ የተደገፈ የታሪክ ሂደት መኖር አለመቻሉ ነው።
የታሪክ ፍሠታችን እና የታሪክ አካሄዳችን እስካልተስተካከለ ድረስ መጣላታችን አሁንም ማቆሚያ የለውም። ስለዚህ ትክክለኛውን መንገድ ለመያዝ እና ተገቢውን ታሪክ ለማወቅም ሆነ ለማስተላለፍ የሁላችንም ትብብር አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሠግናለሁ፡፡
ዶክተር መንግሥቱ፡- እኔም በዚህ ታሪካዊ ድል ላይ ሐሳቤን እንድሰጥ ዕድሉን ስለሠጣችሁኝ አመሠግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013