ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ሁሌም የምትፈስ ጅረት ነች

እገሌ ጽኑ ነው፣ ብርቱ ነው፣ ሰላም ወዳድ ነው… እንላለን። ምክንያት ስንባልም በዋናነት የምናነሳው በችግር ውስጥ እንዴት እንዳለፈና ድሎችን ወደራሱ ማምጣት እንዴት እንደቻለ ስንመለከት ነው። አዎ ድል ዝም ብሎ የሚታፈስ አይደለም። ትግልን፣ ተፈትኖ ማሸነፍን፣ አለመውደቅን ይፈልጋል። ባለን ነገር ደስታን ለራስ መፍጠርንም ይሻል። ከሌሎች ጋር መወዳደር ሳይሆን ከራስ ጋር ተወዳድሮ የተሻለው ላይ መድረስንም ይጠይቃል።

ምክንያቱም ሰው እንደ እራሱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም። ሰው ራሱን ካየና በሚችለው ልክ በሥራ ከተጋ ብሩህ አዕምሮ ከፈጣሪው የተሰጠው በመሆኑ ማንንም ሳይከተል በራሱ ሀሳብ የተሻለውን ያገኛል። ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ሰላምን የሥራ አማራጭንና መልካም እድሎችንም ይፈጥራል።

አሁን ሰው ራሱን ሳይሆን ሌሎችን ማየትና በእነርሱ መቅናትን ብቻ ስለተያያዘው ነው ከፈተናዎች መውጣት ያቃተው። ሀገሩንም ወደተሻለ ጎዳና ለማሻገር ሰማይ የሆነበት። ይህንን ሳስብ አንድ ነገር አዕምሮዬ ላይ ብቅ አለ። ያለፉት የኮሮና ጊዜያት።

ያ ወቅት ሀገራት በከፍተኛ ችግር የወደቁበት፣ እርስ በርስ መነካካት የማይቻልበት፣ ብዙኃኑ ሀገራትም ዜጎቻቸውን በሞት የተነጠቁበት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ደግሞ ወደ አምላካቸው እጃቸውን ዘርግተው እየጸለዩ ጎን ለጎንም መተጋገዛቸውን ያሰፉበት እንደነበር እንረሳውም። ያ ጊዜ ሁሉም ፍራቻ ውስጥ ነበር።

ግን አድርግ የተባለውን እያደረገ ቤተ መቅደስ ባይገባም በቤቱ ሆኖ ከአምላኩ ጋር እየተገናኘ ለችግረኞች ከመድረስ ያልተቆጠበበት ነበር። ይህ ጉዳይ እንደ ሀገር ሲሰፋ ደግሞ ብዙዎች ኢኮኖሚያቸው ሲደቅና ዜጎቻቸውን ሲያጡ የእኛ ሀገር ግን ከሌሎች በተሻለ መልኩ የተንቀሳቀሰችባቸው በርካታ መንገዶች ነበሩ።

አንዱ የሀገሪቱ ዓርማ ሆኖ የነበረው አየር መንገዳችን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የእኛ አየር መንገድ አንድ ዓመት፣ ስድስት ወር ከሥራ ውጪ ሆኖ ቢቆይ እንደሌሎች ሀብታም መንግሥታት ከፍተኛ ገንዘብ ድጎማ ይወድቃል:: ቀጣይነቱና ችግሩን ተቋቁሞ ለመሄድም ይቸገራል::

የለም ወንበር እንፍታና ካርጎ እናድርገው ብለን ዓለም ያገናኘ አየር መንገድ እንዲሆን አስችለናል። ከስድስት በመቶ በላይ ትርፋማ የሚሆንበትን እድልም ፈጥረናል:: በኮሮና ውስጥ በትልቁም በትንሹም ሀገር አየር መንገዶችን መንግሥታት ድጋፍ ሳያደርጉላቸው ችግሩን መቋቋም የቻሉ የሉም:: ብዙዎችም ወድቀዋል::

ግን መቋቋም የቻሉትም በመንግሥት ድጋፍ ነው:: የእኛ አየር መንገድ ግን አንድ ብር አልተሰጠውም:: ያንን ፈተና ወደሚመቸን መንገድ ቀይረን ተጠቀምንበት::

ፈተናዎች ኮሮናም ይሁን አንበጣ ጦርነትም ይሁን ሌላ መልክ ያለው ፈተና የራሱ የሆነ መልካም እድሎች ይዞ ይመጣል:: ያንን ለማየት የሰከነ ማንነት፤ የሚያስተውል ማንነት፤ ችግርን በችግርነቱ ብቻ ሳይሆን ከችግር ውስጥ የሚገኝ እድልን ፈልቅቆ የማውጣት ብቃት ይፈልጋል። ይህ እስከተፈጠረ ድረስ ደግሞ በየአንዳንዱ ፈተና ውስጥ ጠቀሜታዎች አሉ።

ለምሳሌ አሁን ዓለም ላይ ያለው የታሪፍ ሁኔታ አስጊ ነው፤ አስጨናቂ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራትም ቢሆን ከባድ ነገር ነው:: ግን ክብደቱን በመልካም ጎን ለማየት፣ ወደ እድል ለመለወጥ ተቀምጠን ተወያየን:: እንጠቀምበት እድል አለው ችግሮች ብቻ አይደለም አልንም።

እውነቱን ለመናገርም ከፍተኛ ጥቅም እያገኘንበት ነው:: እናም ከማንኛውም ፈተና፤ ከማንኛውም ችግር በማስተዋል ተፈልቅቆ የሚወጣ መልካም እድሎችን ማየት እስከቻልን ድረስ ምንም ጥርጥር የለውም ፈተና የሚያመጣቸው ድሎች አሉ:: እነርሱን መጠቀም የሚያስችል ብቃት መፍጠር ደግሞ ያስፈልጋል::

በዚህ አግባብ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሰባት ዓመታት በጣም በርካታ ፈተናዎች ገጥመውን ለማመን የሚያስቸግሩ ድሎችን፤ ለማመን የሚያስደንቁ ተዓምር ሊባሉ የሚችሉ ስኬቶችን ማስመዝገብ የቻልነውም ይላሉ::

ያክሉናም እነዚህ ድሎች ሲመጡ ማዕበል የለም ማለት አይደለም:: ማዕበሎችም፤ ፈተናዎችም አሉ:: ግን እነርሱ ወደምንፈልገው ግብ የሚያደርሱን ጉልበት እንዲሆኑ አድርገን ተጠቅመንባቸዋል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እኛ መዳረሻችን ብልፅግና ነው፣ መዳረሻችን የፀናች ኢትዮጵያን ማየት ነው። መዳረሻችን ልመና ያቆመች ኢትዮጵያን ማየት ነው።

እሱን ስናስብ ደግሞ መሀል ላይ ውዳሴም እርግማንም ቢመጣም፣ ብዙ ሚዛን የሚያስት ጉዳይ አይደለም ሚዛናችንን የምንጠብቀው መልህቃችን መርህ ስለሆነ ማለት ነው ሲሉም ፈተና ኢትዮጵያን እንደማይጥላት አበክረው ይገልጻሉ።

አዎ እርሳቸው እንዳሉት፣ ችግሮች በተቃውሞና እጅን አጣጥፎ በመቀመጥ አለያም በማማረር የሚፈቱ አይደሉም። ይልቁንም መፍትሄያቸውን የምናገኘው ከመደጋገፍና በትናንት ሥራ ላይ በመመርኮዝ ዛሬን እያስዋቡ ነገን መሥራት ስንችል ነው።

በዛሬ ለውጥና ትናንትን የመቀበል ልክ፣ ስህተትን ላለመድገም በሚደረጉ ጥረቶች መጠን ፈተናዎቻችን ወደ ድል እንደሚቀየሩ ማንም ይረዳዋል። ለዚህ ደግሞ የትውልድ ግንባታ ከምንም በላይ ያስፈልጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የጀመርነው ትውልድ ካልቀጠለ፣ የምናስበውን ትውልድ ካልቀጠለ በስተቀር በአንድ ትውልድ፣ በአንድ ቤተሰብ፣ በአንድ ቡድን ሀገር ተሰርቶ አያልቅም:: ምክንያቱም ሀገር የቅብብሎሽ ውጤት ናት:: ስለሆነም ያን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ መሥራት የሚቻለው ትውልድን እያሰብን ልንሠራ ይገባል::

ነገን እያሰብን ልንታትር የግድ ነው:: ነገን የምናስብ ሰዎች ግን ዞር ብለን ትናንትናን መመልከት የማንችል ከሆነ፣ ትናንትናችንን የዘነጋን ከሆነ፣ ከትናንትናችን መማር የማንፈቅድ ከሆነ ነገ አይሠራም:: ለዚህ ነው እኛ ትናንትን ከዛሬ ዛሬን ከነገ አስተሳስረን፣ ሚዛን ጠብቀን ሀገር እንገነባለን ብለን የተነሳነው::

ሁልጊዜም ሰዎች ትናንትን ሲመለከቱ ዛሬ ባሉበት የእውቀት ልክ፣ ዛሬ ባሉበት አለማዊ ሁኔታ፣ ዛሬ ባሉበት የሀብት ልክ ካዩት ሚዛን ይስታሉ:: የከፋም የለማም ነገር እንደሆነ ትናንትን ማየት ያለብን በዛን ጊዜ በነበረ አውድ ነው:: ትናንትን ማየት የሚያስፈልገው ለፍርድ አይደለም:: ትናንትን ማየት የሚያስፈልገው ለመማር ነው::

ትናንትና ውስጥ ልንማራቸው የሚገቡ በጣም በርካታ ጉዳዮች አሉ:: እነሱን ካልተማርን ስህተት እንደግማለን:: እነሱን ካልተማርን ጥፋት እንደግማለን:: ጥፋት ከደገምን ደግሞ ለትውልድ ይሻገራል:: ስለሆነም ትውልድን ለመሥራት ትናንት መልካም ነገሮች እንዳሉ በመንገርና ዛሬ የተሻለ እንዲሆን በዛሬ አውድ እንዲሠራ በማስተማር ነውም ሲሉ ዘመናት በምን መልኩ ተሳስረው ለትውልዱ መድረስ እንዳለባቸው ያነሳሉ። በተለይ ደግሞ የዛሬው ትውልድ እንዴት ችግሮችን ወደ ድሎች መቀየር እንደሚችልም ያመላክታሉ።

ማንኛውም ሀገር በየዘመናቱ ፈተና ይገጥመዋል። የእድገት መሰረቱን የሚጥለው ፈተናውን እንደሚጋፈጥበት ልክ ነው። ለፈተናው የሚሰጠው ምላሽ በአለት ላይ ወይም በአሸዋ ላይ ሀገሩን ይገነባል። በመከራ ውስጥ ሆኖ ችግሩን እድል ማድረግ ከቻለ መቼም ውድቀቱን ሊያፋጥን አይችልም። ለምሳሌ እንደ ሀገር የሥራ አጥ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው።

ግን ደግሞ የሥራ አማራጮችም በብዙ መልኩ ሰፍተዋል። ሰዎች የመሥራት ፍላጎት ካላቸው የፈጠራ እድሎቻቸውን ተጠቅመው የሚለወጡባቸው በርካታ መንገዶች ተመቻችተውላቸዋል። ችግሩ መንግሥት ብቻ እንዲቀጥር መጠበቁ ላይ ነው።

ዛሬ ላይ ሊሞላ የሚገባው ክፍተት ሀገር ምን ትፈልጋለች የሚለው ብቻ ይመስለኛል። ያንን አይቶ ፈጣሪ መሆን ከተቻለ ገበያው ሳይወድ በግድ በመብራት ፈልጎ ይወስደናል። ነገር ግን ትናንት ላይ ከቆምንና በዚያ ውስጥ መቆየትን ከፈለግን መቼም ቢሆን ከተቀመጥንበት መነሳት አንችልም። ችግሩንም ወደ እድል ለመቀየር እንቸገራለን። ስለሆነም ነገን ቁልጭ አድርገን ለራሳችን ለማሳየት ከፈለግን ዘመኑን የዋጀ ሰው መሆን የግድ ይለናል።

ትናንትናን በወጉ ተገንዝበንና ተረድተን እሱን ጠግነን ለልጆቻችን መሻጋር እንዲችል ለማድረግ ዛሬን በዘመኑ ልክ መዋጀት ይጠበቅብናል። በትናንትና ውስጥ የጎደሉትን ዛሬ ስንሞላቸው ነጋቸው ብሩህ የሆኑ ልጆችን እንዳንፈጥር የሚገድበን አይኖርምም:: ይህ ግን ከግለሰብ ላይ የሚቆም ሳይሆን አካባቢን አልፎ ተርፎ ደግሞ ሀገርን የሚመለከት ጉዳይ ይሆናል።

ምክንያቱም ልጆች የነገ ሀገር ተረካቢና ገንቢ ናቸው። ችግሮች ሲገጥማቸው እንዴት እንደሚያልፉት ካለፉት ተግባራት የሚቀስሙ ንቦች ናቸው። ለዚህም ነው ትናንትን አይተን፣ ዛሬን ሰርተን ነገን ውብ አድርገን የተሻለችውን ሀገር ለተረካቢው ዜጋ እንስጠው የሚባለው። የኢትዮያዊነት መልክም ይህ ብቻ እንደሆነ ሁሉም ከውስጡ ሊያስገባው ይገባል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱትን ሀሳብ ልጥቀስ። ‹‹ኢትዮጵያዊነት የምንሰዋለት ዓላማ፣ ነገ የምሰበስበው ብቻ ሳይሆን አንዳንዱ በልጆቻችን የሚታይ ሊሆን ይችላል:: ለዚያም ቢሆን ዋጋ የሚከፈልለት ጉዳይ ነው::

ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ታይቷል:: ሰዎች ዓድዋ፣ ማይጨውና ባድመ ላይ የሞቱት ትውልድና ሀገር እንዲቀጥል እንጂ ከሞቱ በኋላ ሌላ የሚያገኙት ወረት፤ ክፍያ ስላለ አይደለም:: ሰዎች ሕይወታቸውን ከፍለው ሀገር የሚያፀኑት ኢትዮጵያዊነት እንደዛ ባለ ደርዝ የሚለካና የሚታይ ስለሆነ ነው::››

እርሳቸው እንዳሉት፣ ኢትዮጵያዊነት ከትናንት እስከ ነገ ነው:: ኢትዮጵያዊነት ከሀ እስከ ፐ ነው እንጂ ሲመቸን፣ ሲደላን፣ ጥቅም ስናገኝበት የምናዜመው፣ የምናወድሰው፣ ሲከፋን፣ ሳይመቸን ሲቀር፣ ሕልሞቻችን ሲጨነጋገፉ የምንተወው የወረት ጉዳይ አይደለም::

የሁልግዜ ነው:: በከፍታም በዝቅታም፤ ሲመችም ሳይመችም የምንኖረው ጉዳይ እንጂ ኢትዮጵያዊነት ሲደላንና ለእኛ ሲመች ለምሳሌ ሥልጣን ስንይዝ ኢትዮጵያዊ ብለን ኖረን ሥልጣኑ ሲቀር ደግሞ የለም ኢትዮጵያዊነት አያስፈልግም የምንለው አይደለም።

ኢትዮያዊነት ኩልል ብሎ የሚፈስ ጅረት ነው:: ክረምት ከበጋ የማይቋረጥ በድምፀቱ፣ ለተጠሙ በመድረሱ፣ ለእርሻ በመሆኑ ፈጥኖ በመጠበቁ እጅግ እርካታን የሚሰጥ በሰፈር ውስጥ የሚያልፍ ኩልል ያለ ጅረት ካለ ኢትዮጵያዊነት እንደሱ ነው:: አንዳንዴ ዘምቦ ሊደፈርስ ይችላል::

ኢትዮጵያዊነት የማይቆም በቀጣይነት የሚፈስ፣ በሙላት የሚመለስ፤ በልጆች የሚገለጥ የኖረ፣ ያለና የሚኖር ነው:: እናም ይህንን ዥረት ዘላለም እንዲፈስና ምድሪቱን እንዲያረሰርስ ብሎም ለምለሙን ነገር በሕይወት እንዲገለጥ እናድርገው በማለት ለዛሬ የያዝኩትን ሀሳብ ቋጨሁ። ሰላም!!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You