“በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ የሥራ ባሕል ለውጥ መጥቷል ” – ኢንጂነር ታምራት ሙሉ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

ዓለም ሕንጻ ከላይ ወደታች እንደሚገነባ ሳያውቅ ላሊበላን ከአንድ አለት ተፈልፍሎ መሰረቱ ከላይ ጫፉ ወደውስጥ የተገነባባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ:: ዓለምን ያስደመሙ የአክሱም ሐውልትን ያነጹ፣ የፋሲለደስ ቤተመንግሥት ያቆሙ፤የሀረር ግንብን ያነጹ እጆች ከኢትዮጵያ ምድር ፈልቀዋል::

ዓለምን ያስደመሙ እነዚህ ሥራዎች በዛሬው ትውልድም በልዩ ገጽታ እየተከናወኑ ነው::የዓድዋ ሙዚየም፤ ልዩ ልዩ የቱሪስት መስህቦችና በከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪዶር ሥራዎች ለዚህ አባባል ዋቢ የሚሆኑ ናቸው:: እነዚህ ሥራዎች ጥራትን እና ፍጥነትም በማዋሀድ መተግበራቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ያለውን የኮንስትራክሽን እድገት አመላካች ነው::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍጥነት ሠርቶ ማጠናቀቅ አዲሱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ መለያ እየሆነ ነው:: የኮንስትራክሽን ዘርፉ አሁናዊ ገጽታ ምን ይመስላል? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘርፉ የሚታዩት ለውጦች መነሻ ምንድነው? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ይዘን የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ታምራት ሙሉ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገናል:: ያደረግነውን ቆይታ ታነቡት ዘንድ ጋበዝን!

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለበት ደረጃ እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር ታምራት፡- የኮንስትራክሽን ዘርፉ በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል ማለት ይቻላል:: ከዚህ ቀደም ግንባታዎች ሲጀመሩ መጨረሻቸው አይታወቅም ነበር:: ከአጭር ጊዜ አንስቶ እስከ አስር ዓመት ግንባታዎች የሚጓተቱበት ሁኔታ ነበር:: ይህም ውል ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን የተለያዩ ክፍተቶች ስለነበሩ ነው:: ይህም ፕሮጀክቶች የሚመሩበት ሁኔታ ውስንነት፣ የአቅም ክፍተት፣ ቴክኖሎጂው በሚፈለገው ደረጃ አለመድረስ፣ የጨረታ ሂደት መንዛዛት፣ በዲዛይን ዝግጅት ያሉ ክፍተቶች፣ ለሥራዎች ትክክለኛ ሥራ ተቋራጭ ያለመመደብ እና ሌሎችም ምክንያቶች ተደምረው ፕሮጀክቶች በተባለላቸው ዋጋና ጊዜ ለመጠናቀቅ ይሳናቸው ነበር::

በዚህም ምክንያት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በግዜ ማጠናቀቅ አይቻልም ተብሎ ይወሰድ ነበር:: አሁን ግን ፕሮጀክት ተጀምሮ በአጠረ ጊዜ ማለቅ እንደሚችል እያየን ነው:: በተለይ በአዲስ አበባ አሁን የሚታዩት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቪ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ሲታዩ፤ እነዚህን ፕሮጀክቶች ከዚህ ቀደም ይሠሩ በነበሩ ባለሙያዎች ሥራዎቹ ቢሠሩም በአፈጻጸማቸው ልዩነት አለ::

በአሁኑ ወቅት የእኛ ሀገር ሥራ ተቋራጮችም ሆነ ባለሙያዎች ፕሮጀክትን እጅግ በአጠረ ጊዜ ማጠናቀቅ ችለዋል:: ያውም ጥራትም ሆነ ውበት ተጠብቆ በአጠረ ጊዜ ውስጥ እየተጠናቀቀ ይገኛል:: ይሄ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ የሥራ ባሕል ለውጥ አምጥቷል:: በዘርፉ ማታ መሥራት ባሕል የሆነበት፤ ማታ ተቆፍሮ የታየው ጉድጓድ ጠዋት ተጠናቆ ማየት ተጀምሯል:: ይሄ በዘርፉ በሕንጻ ግንባታም ሆነ በመንገድ ሥራ ተመሳሳይ ለውጥ መጥቷል:: በዘርፉ ከእይታ ጀምሮ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ ፕሮጀክት የሚመራበት አግባብና ቁርጠኝነት ፕሮጀክት ተጀምሮ በአጠረ ጊዜ ማጠናቀቅ ባሕል እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ስትፈተንባቸው ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ የፕሮጀክቶች መጓተት ነው:: በዚህ ረገድ በፕሮጀክቶች መጓተት የተከፈለው ዋጋ እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር ታምራት፡- በግንባታ መጓተት የደረሰውን ጉዳት ለመለካት በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል:: ሁሉም ጥናቶች ያሳዩት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ዋጋና ጊዜ እንደማይጠናቀቁ ነው:: በሕንጻ፣ በመንገድና በውሃ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ወደ 52 በሚሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንስቲትዩቱ ከወርልድ ባንክ ጋር በመሆን ጥናት አስጠንቶ ነበር:: ጥናቱ ያሳየው በዘርፉ 124 በመቶ የጊዜ ጭማሬ መኖሩንና 76 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ነው:: ይህም የሚያሳየው ፕሮጀክቶችን አውቀን እየመራን አለመሆኑን ነው:: ከዛ በኋላም በሌሎች ተቋማት ተመሳሳይ ጥናት የተጠና ቢሆንም የኋለኞቹ ከበፊቱም የከፋ ውጤት አሳይተዋል::

እነዚህ አላስፈላጊ የዋጋና የጊዜ ጭማሪዎች ትልቅ ጉዳት ያደርሳሉ:: ለምሳሌ የሚሠራው መንገድ ቢሆንና መጠናቀቅ ካለበት አምስት ዓመት ዘግይቶ ቢጠናቀቅ ከፍተኛ የሆነ የማኅበራዊ ጉዳት ያስከትላል:: ምክንያቱም ወደትምህርት ቤት መሄድ የሚገባቸው ልጆች በተባለው ጊዜ እንዳይሄዱ ያደርጋል:: ወደጤና ተቋማት መሄድ የሚገባቸው ሰዎች በአጠረ ጊዜ እንዳይደርሱ ያደርጋል::

ወደ ንግዱ፣ ወደ ሥራው እንዲሁም ወደ ቤቱ መሄድ የሚፈልግ በተገቢው መልኩ ሰዓቱን መጠቀም እንዳይችል ይሆናል:: የትራንስፖርት ዋጋም የሚጨምር ሲሆን በተመሳሳይ በሕንጻም ላይ ሆነ በሌሎች ግንባታዎች ላይ የኢኮኖሚም ሆነ የማኅበራዊ ተጽእኖ አለው:: ከዚህ ባለፈ በተለይ የመንግሥት ፕሮጀክት በሚሆንበት ጊዜ ሕብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፤ መንግሥት የማስፈጸም አቅም ውስንነት አለበት ብሎ እንዲደመድም ወይም “መንግሥት ለእኛ ትኩረት ስላልሰጠን እንጂ ትኩረት ቢሰጠን ኖሮ ፕሮጀክቱን በውሉ መሰረት ያስፈጽም ነበር” የሚል አተያይ እንዲኖራቸው ያደርጋል:: በመሆኑም የመንግሥትን ተቀባይነትም ከማሳጣት ባሻገር የመንግሥትንም ሆነ የሀገርን ገጽታ ያበላሻል::

አዲስ ዘመን፡- የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከመጓተት እንዴት በጊዜ ወደማጠናቀቅ ሊለወጥ ቻለ?

ኢንጂነር ታምራት፡- በዋናነት ለውጡ ፕሮጀክት የሚመራበት መንገድ ላይ ነው:: ድሮ የነበረው አሠራር አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ለሥራ ተቋራጭ ሥራን ከሰጠ በኋላ ክትትሉ የላላ ነበረ:: ምናልባትም በተቋሙ ያለ አንድ የሥራ ክፍል ይሆናል ፕሮጀክቱን የሚከታተለው:: ስለዚህም የሥራ ተቋራጩ ጥያቄ ሲኖረው በጊዜ አይመለስለትም፤ ክፍያ በጊዜ አይከፈለውም፤ ለሚጠይቃቸው ማብራሪያ የሚፈልጉ ጉዳዮች ቶሎ ምላሽ አያገኝም ነበር:: ሥራዎችን በማዘግየቱ የሚመጣበት ጠንካራ የተጠያቂነት ሁኔታ አልነበረም:: ስለዚህ ሥራውን በተመቸው ጊዜ ይሠራል:: ሳይፈልግም አይሠራም::

አሁን ያለው አሠራር ግን መንግሥት በጥብቅ ሁኔታ ይከታተላል:: ሥራዎች በክብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተው፣ በከተማ ከንቲባ፣ በየደረጃው ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ሥራውን ማታም ጭምር ይጎበኙታል:: ዛሬ ያዩታል፣ ነገ ማታ ሲሄዱ ሥራው ላይ ለውጥ ይፈልጋሉ:: ስለዚህ በሥራው ላይ ያሉ የሥራ ተቋራጭ ባለሙያዎችም ተጠያቂ እንደሚሆኑ፣ ገጽታቸው እንደሚጠፋ ያውቁታል:: ሥራውን በተገቢው መልኩ ካልሠሩ ወዲያው ርምጃ ስለሚወሰድ በጥንቃቄ ይሠራሉ::

አንዳንዶቹ ደግሞ የፕሮጀክቱን ትርጉም በመረዳት ጭምር ቀንና ማታ ይሠራሉ:: ይሄ የዘርፉን የሥራ ባሕል ቀይሯል:: የሚጠይቁት ጥያቄ ካለ እዚያው ወዲያው ይመለስላቸዋል:: የቢሮክራሲ ጣጣ የለም:: የአመራሩ ቁርጠኝነት ለውጥ አምጥቷል ብዬ አስባለሁ::

በዘርፉ ጥቅም ላይ የዋሉት ቴክኖሎጂዎች እራሱ አስተዋጽኦ አላቸው:: ለአብነት የኮንክሪት ሙሌት አሁን በባሬላ ሲሠራ አይታይም:: አሁን የምንጠቀመው ሬዲ ሚክስ ኮንክሪት ነው:: ሳይት ላይ የግድ ሲሚንቶና አሸዋ መቀላቀል፣ ማቡካት ሳይጠበቅብን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ደረጃውን የጠበቀ ኮንክሪት ከአምራች መጥቶ በሚፈለገው ሰዓት የሚፈለገው ቦታ ላይ በአጠረ ሰዓት ሥራ እንዲሠራ አስችሏል:: ቴክኖሎጂ መጠቀማችን ከፕሮጀክት አስተዳደራችን ቀጥሎ ወሳኝ ነገር ነው::

ወደ ሕንጻው ዘርፍ ስንመጣ የምንጠቀማቸው እንደቢም ያሉ ቴክኖሎጂዎች የዲዛይንም ሆነ የኮንስትራክሽን የመፈጸም አቅማችንን ለማሳደግና ግንባታችን ተገማች እንዲሆን አግዘውናል::አንድ ፕሮጀክት በ50 ሚሊየን ያልቃል ተብሎ በ50 ቢሊየን ካለቀ አንዱ የተሳተው ነገር ፕሮጀክቱ በደንብ አልተጠናም ማለት ነው:: ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም አንዱ ግን ከጥናት ጀምሮ እጥረት እንዳለ ነው የሚያሳየው::

ሌላው ከዚህ በፊት በነበረው ለፕሮጀክቶች መጓተት ትልቅ እንቅፋት የሚሆነው የቦታ ባለቤትነት ጉዳይ ሳይፈታና ካሳና መሰል ጉዳዮች ባልተፈቱበት ሁኔታ ውል ይፈረም ነበር:: ወደ ሥራ ሊገባ ሲል በፍርድ ቤትና በተለያየ

መልኩ ፕሮጀክት የሚቆምበት አጋጣሚ ብዙ ነው:: አሁን ግን እንደዚህ አይነት ነገር የለም:: እንደሚታይው ካሳ ለሚገባቸው ወዲያው ችግራቸው ይፈታል፤ ፕሮጀክቱ ግን አንድ ቀንም አይዘገይም:: ይሄን ያመጣው የአመራሩ ቁርጠኝነት ነው:: ስለዚህ ቴክኖሎጂ የአመራር ቁርጠኝነት፣ ሀገራዊ እይታ እያደገ መምጣትና በዚሁ ልክ የሥራ ተቋራጮች የመፈጸም አቅም እያደገ መምጣት የምናያቸውን ውጤት ማምጣት አስችሏል::

አዲስ ዘመን፡-ቀደም ሲል በግንባታዎች ላይ የጥራት ጉድለት በስፋት ይነሳ ነበር:: በአሁኑ ወቅት ግንባታዎችን በጥራት በመገንባት ረገድ የመጣ ለውጥ አለ?

ኢንጂነር ታምራት፡- ጥራት ብዙ ትርጉም ነው ያለው:: አሁን የተቀመጥንበት ቦታ ወለሉ ላይ ያለው ፖርስሊ ይባላል:: ይሄ ፖርስሊ ሲታይ ያምራል፤ ለምሳሌ ይሄ በሸክላ ቢሠራ እንደዚህ አያምርም:: ውሉ ላይ ግን መሬቱ በሸክላ ነው መሠራት ያለበት የሚል ከሆነ ከሸክላ አንጻር ቆንጆ ነው:: ስለዚህ አንዱ ጥራትን የሚብራራበት ሁኔታ የሚመጥን ስፔስፊኬሸን ማዘጋጀት ነው:: ይህ የሚሆነው ሲጀመር ገና ነው:: መሬቱ ሸክላ ይሁን ተብሎ ውል ተፈጽሞ ለምን አላማረም ሊባል አይገባም:: የሚመዘነው ከሸክላ አንጻር ነው:: እንዲያምር ከተፈለገ ማርብል፣ ወይ ግራናይት ቢሆን ውድ ነው፤ ግን ይበልጥ ያምራል:: ይሄን የማነሳው ጥራትና ውበት ስለሚጣጣሙ ነው::

ስለዚህ ከመጀመሪያው ጥራትን ለማስጠበቅ እንዲሠራ ለሚፈለገው ሥራ የሚመጥን ስፔስፊኬሽን ማዘጋጀት ይገባል:: በስፔስፊኬሽኑ ጥቅም ላይ የሚውሉት እቃዎች የጥራት ሁኔታ፣ የአሠራር ሁኔታና ጥቅም ላይ የሚውለው ቴክኖሎጂ በተገቢው መልኩ ከመጀመሪያው መቀመጥ አለበት:: ይህ የሚመጣው በዲዛይን ዝግጅት ላይ ነው:: ዲዛይን ዝግጅት ላይ ማንነው ያለው ሲባል አማካሪ መሃንዲስ ነው:: ስለዚህ አማካሪ መሃንዲሱ ጥራቱን የጠበቀ ዲዛይን እንዲያዘጋጅ ማድረግ ነው:: ይህንን ለማድረግ ሁለት ነገር ያስፈልጋል:: አንደኛ የሚመረጠው መሃንዲስ ብቃት ያለው መሆን አለበት:: ብቃት ከገንዘብ አቅም፣ ከልምድ፣ ከትምህርት ዝግጅት፣ ካለው የሰው ኃይልና ከዚህ በፊት ካለው የሥራ ልምድ አንጻር የሚያያዝ ነው::

ሁለተኛው አማካሪው የሚቀጠርበት የግዢ አግባብ ይወስነዋል:: የማወዳደሪያ መስፈርቱ ዋጋ ብቻ ከሆነ ብቃት ያላቸው አማካሪዎች ሥራውን አያገኙም:: ሥራው ላይ በቂ ልምድ የሌላቸውና በትንሽ ዋጋ ሥራውን የሆነ ነገር አድርገው ማስረከብ የሚፈልጉ ሰዎች ይመጣሉ::ነገር ግን ሥራው ጥራትን ያማከለ እንዲሆን ቢደረግ መነሻ ካፒታሉ ትልቅ ሊሆን ይችላል ግን የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው አማካሪዎች ወደ ጨረታው ለመምጣት ይጋበዛሉ:: የሆነ ሳንቲም ለማትረፍ በማሰብ ተገቢ ያልሆነ ሰው ሲመጣ የዚህ ሰው ጣጣ እስከመጨረሻ ይሄዳል:: ጥራትን ስናስብ የምንመርጠው አማካሪ መሃንዲስ ብቃት፣እና ልምድ የጎላ ድርሻ አለው::

አስፈጻሚው አካል ባለሙያዎች አሉት ወይ የሚለው ሦስተኛ ነው:: የመጣውን ዲዛይን በደንብ አይተው ወደግንባታ ከመገባቱ በፊት “አይ ይሄ አይመጥንም፤ ይሄ ጥራትን አያመጣም፤ ይሄ ደህንነትን አያረጋግጥም” ብለው ከመጀመሪያው ተከራክረው እንዲስተካከል ማድረግ የሚችሉ ባለሙያዎች አሉ ወይ? የሚለው ይወስነዋል:: ከዚህ በኋላ ወደግንባታ ሲገባም ለግንባታው የሚመጥን የሥራ ተቋራጭ ሥራውን ይዟል ወይ የሚለው ወሳኝ ነው:: ይሄም ልክ እንደ አማካሪው ከግዢ ሂደት ጀምሮ ጥሩ አፈጻጸም ሊያመጣ የሚችል ኮንትራክተርን መምረጥ መቻል ዋና ጉዳይ ነው::

ዋጋ ብቻ ታይቶ የሚመረጥ ከሆነ ቀብድ ተቀብሎ ሥራ ጀምሮ የሚጠፋ ኮንትራክተር ይመጣል:: በዚህ ሂደት መጀመሪያ ላይ የተወሰነ ሳንቲም ማትረፍ ይቻል ይሆናል:: ግን መጨረሻ ላይ ጣጣ አለው:: ብቃት ያለው ኮንትራክተርን መምረጥ የሚያስችል መስፈርት ከተቀመጠ ይህም በሥራ ልምዱ፣ ሌሎች ሥራዎችን ሲሠራ ከተሰጠው አስተያየት፣ ካለው ማሽንና የሰው ኃይልና ሌሎችም መስፈርቶችን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የተሻለ የሥራ ተቋራጭ ከተመረጠ ድርጅቱ ለስሙ ሲል፣ ካለው ልምድም ተነስቶ ጥሩ ሥራ ይሠራል::

እነዚህ ሁሉ ጥሩ ሆነው ግንባታውን ደግሞ የሚከታተል አማካሪም ሆነ የተቀጠረ ባለሙያ ከሌለ ጥራት ሊጓደል ይችላል:: ስለዚህ ከቅድመ ዲዛይን ጀምሮ ስለዲዛይኑ ትክክለኛነትና ለታሰበው ሁኔታ ተገቢ መሆኑን ከማረጋገጥ አንስቶ ወደግንባታ ሲገባ ግንባታውን የሚከታተል ጥሩ የአማካሪ ቡድን ካለና ክትትል ከተደረገ ጥራትን ማረጋገጥ ይቻላል:: እነዚህ ከጎደሉ ግን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ጥራት መጓደሉ አይቀርም::

ጥራት ያለው ነገር ሲሠራ መነሻ ኢንቨስትመንቱ ከፍተኛ ይሆናል:: ስለ ሁሉም ሳይሆን በአጭር መክበር የሚፈልጉ የሥራ ተቋራጮች ጥራትን በመቀነስና ለበስ ለበስ በማድረግ ከተወሰነ በኋላ ችግር የሚፈጠርበት ሥራ ይሠራሉ:: ጠንካራ የሆነ የጥራት መቆጣጠሪያ ካለ ግን ይህንን ማስቀረት ይቻላል::

ጥሩው ነገር በዘርፉ ግንባታዎችን የሚቆጣጠር ተቆጣጣሪ አካል አለ:: የተቆጣጣሪ አካላት አንዱ ሥራ ኮንትራት የተሰጠው ሥራ እንዴት እየተሠራ ነው የሚለውን ማየት ነው:: እዚያ ውስጥ አንዱ መመዘኛ የሚሠሩ ሥራዎች ጥራታቸውን ጠብቀዋል ወይ የሚለውን ማየት ነው:: ለዚህም ጥራት የሚታይባቸው የተለያዩ መስፈርቶች አሉ:: አንዳንዱ ቦታው ላይ በመገኘት በዐይን የሚታይ አለ:: አንዳንዱ በዐይን የማይለይና ናሙና ተወስዶ የላብራቶሪ ምርመራ የሚያስፈልገው አለ:: ይህም ሁሉም ደረጃ ላይ የምህንድስና ጽንሰሀሳብን በጠበቀና በተገቢው መልኩ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን ማረጋገጥ ነው:: ይህ በተገቢው መልኩ ሲረጋገጥ የምንፈልገውን ጥራት እናረጋግጣለን::

ሆኖም የግንባታ ግብአቶቹ ጥሩ ሆነው፣ ዲዛይኑም የተሻለ ሆኖ ነገር ግን ሳይት ላይ ያለው ባለሙያ በቂ እውቀት የሌለው ከሆነ ከአገጣጠምና ከመሰል ሁኔታዎች የጥራት ጉድለት ሊያጋጥም ይችላል:: ስለዚህ ጥራት በፕሮጀክቱ የሚሳተፉ አካላት ድምር ውጤት ነው:: ስለዚህ ዲዛይኑ ትክክል መሆን፣ የሚመረጠው ሥራ ተቋራጭ ተገቢ መሆን፣ ሥራውን የሚሠሩት ባለሙያዎች ብቃት ያላቸው መሆን፣ የክትትል ሥርዓቱና የፕሮጀክት አመራሩ በሚፈለገው ልክ ከሆነ ጥራት ይመጣል:: ከእነዚህ ውስጥ የጎደለ ካለ ይዞት የሚመጣው የጥራት ጉድለት ይኖራል::

አዲስ ዘመን፡- ተቋራጮችን የመምረጫ መስፈርቱ ወሳኝ መሆኑን አይተናል:: ነገር ግን አብዛኛው የመንግሥት ተቋማት የጨረታ ሂደቱ የዋጋ ቅናሽ ላይ የሚያተኩር ስለሆነ ጥራትን ማረጋገጥ እንቸገራለን ሲሉ ይሰማል:: በተቃራኒው ኮንትራክተሮች የማይሆን መስፈርት እየተቀመጠ መሥራት የምንችላቸውን ሥራዎች እኛ እንዳንሠራና ሀገር በቀል እውቀት እንዳይፈጠር አብዛኛው ሥራ ለውጪ ተቋማት ይሰጣል የሚል ቅሬታ ያነሳሉና እንዴት ነው ማጣጣም የሚቻለው?

ኢንጂነር ታምራት፡- ሁሉም ተቋማት በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ላይ እምነት የላቸውም ብለን መደምደም አንችልም:: ሁሉም የውጭ ተቋራጮች ጥሩ ናቸው፤ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች በሙሉ ደካማ ናቸው ብሎ መደምደምም ልክ አይደለም:: ሁለቱም ጽንፎች ልክ አይደሉም:: በዚህ ሂደት ግን ከእኛ ባለሙያዎች የውጪዎቹ ይሻላሉ የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሱ የሉም ማለት ግን አልችልም:: እኔ እዚህ ጋር ልል የምችለው እንደኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩሽን ተልእኮአችን የዘርፉን ተዋናዮች አቅም መገንባት ስለሆነ እያየን ባለው ክፍተት አቅም እየሞላን ማተኮር ያለብን የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጭ፣ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችና የሀገር ውስጥ የግንባታ ግብአት ላይ መሆን አለበት::

በዚህ ሂደት የሚገጥሙንን ጉድለቶች እያረምን ማለት ነው:: የውጭዎቹ ሥራ ተቋራጮችም ላይ እያየናቸው ያለነው ጉድለቶች አሉ:: ድሮ አንገታቸውን ለማስገባት ሲሉ ዝቅ ያለ ዋጋ ማቅረብ ጀምረው ነበር፤ አሁን ግን ዋጋቸውም የሚቀመስ አይደለም:: ስለዚህ ወደሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች፣ ወደሀገር ውስጥ አማካሪዎች መምጣት አለብን:: የሚገርመው ከደገፍናቸው የሀገር ውስጦቹ ቶሎ የውጭዎቹ ጋር የሚደርሱ ናቸው:: አሁን እኮ የሀገር ውስጦቹ ትላልቅ ሕንጻዎችን እየሠሩ ነው:: በሀገር ውስጥ የምንገረምባቸውን ግንባታዎች እየሠሩ ያሉት እንደድሮው በውጪ ባለሙያዎች አይደለም፤ የሀገር ውስጥ ናቸው:: ስለዚህ የእኛ አያያዝ፣ አደጋገፍና ክትትል ነው የሚወስነው እንጂ የሀገር ውስጦቹ የመሥራት ችግር የለባቸውም::

የሀገር ውስጥ የዘርፉ ተዋናዮችን ዝቅ ከሚያደርግ እሳቤ መውጣት አለብን:: ነገ የሚጠቅሙን እነሱ ናቸው:: የውጭዎቹ ሀብቱንም አሰባስበው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አይገኙም፤ ተጠያቂም ለማድረግ አስቸጋሪ ነው:: የሀገር ውስጦቹ ግን የእኛው ናቸውና የትም አይሄዱም:: እየደገፉና እያበቁ መሄድ ይሻላል:: ለዚህ አብነት የፕሮጀክቱን ስም ሳልጠቅስ የተሳተፍኩበትን አንድ ፕሮጀክት ላንሳልሽ:: ፕሮጀክቱ ሲጀመር ውሉ የተፈረመው በሦስት መቶ ሚልየን ብር አካባቢ ነው:: ሥራውን የወሰደው የሀገር ውስጥ ተቋራጭ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ነበር መጨረሻ ላይ አቅም አጣ::

በወቅቱ የኮንስትራክሽን ግብዓት በከፍተኛ ዋጋ የጨመረበት ወቅት ነው:: ከውጪ የሚመጡ የግንባታ እቃዎች ነበሩና እነዚያን እቃዎች በዚያ ኮንትራት ማምጣት አልቻልኩም ከሰርኩ የሚል ቅሬታ አቀረበ:: መቶ ሚሊየን ብር ብትሰጡኝ ግን ሙሉ ፕሮጀክቱን አጠናቅቀዋለሁ የሚል ሀሳብ አቀረበ:: ነገር ግን ይህንን ሀሳብ የምናስተናግድበት የሕግ አግባብ የለንም በሚል ውሉ ተቋረጠ:: ነገር ግን ከዚያ በኋላ ቀሪ ሥራውን ለማጠናቀቅ ከሁለት ቢሊየን ያላነሰ ብር አስፈልጓል:: ነገር ግን በወቅቱ የተጠየቀው መቶ ሚሊየን ነበርና ነገሩን በሆደ ሰፊነት ማየት የሚቻልበት ሁኔታ ቢኖር በአራት መቶ ሚሊየን ብር ፕሮጀክቱን መጨረስ እየተቻለ ሌላ ሁለት ቢሊየን ብር ለማውጣት አንገደድም ነበር:: ስለዚህ አንዳንዴ ሕጎቻችንም የመንግሥትን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር የተወሰነ ሆደሰፊነት መፍጠር የሚቻልባቸው ሁኔታዎችን ማጥናት አለብን::

የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ከደገፍናቸው ይችላሉ:: በትክክል ለውጥም እያየን ነው:: አሁን ባለው ሁኔታ ከውጪዎቹ ይልቅ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች የተሻለ አፈጻጸም እያሳዩ ነው:: ስለዚህ በሚገባ ልክ ስላልደገፍናቸው፣ ምቹ ሁኔታን ስላልፈጠርንላቸው፣ ለሚጠይቁት ጥያቄ ተገቢውን መልስ እየሰጠን ስላላበቃናቸው እንጂ የመፈጸም ችግር ስላለባቸው አይደለም:: የውጪ ተቋራጭ አንድ ጥያቄ ይጠይቅና ካልተመለሰለት ቀን ቆጥሮ የደረሰበትን ኪሳራ ይጠይቃል:: የሚጠይቀው የጊዜ ብቻ ሳይሆን የዋጋ ማካካሻ ብሎ ከፍተኛ ዋጋ ይጠይቃል::

የእኛዎቹ እንደዚህ አይነት ባሕል የላቸውም:: ከአቅማቸው በላይ ካልሆነ ለዘገየበት ምናምን እያሉ ለእያንዳንዱ ክፈለኝ ብለው መንግሥትን የሚያስጨንቁ አይደሉም:: የውጪዎቹ ግን አንዳንዴ የሚጠይቁት ከፕሮጀክቱ የመፈጸሚያ ዋጋ በላይ ይሆናል:: ምንም አይጨንቃቸውም፤ እምቢ ቢባል፤ ዓለም አቀፍ ቦታ ሄደው አንዳንድ አንቀጽ ጠቅሰው እንደሚያገኙት ያውቃሉ:: የእኛዎቹ በዚያ ልክ አይደሉም:: ስለዚህ አንዳንድ አሰሪዎች የውጪዎቹ ሲሆኑ በፍጥነት ምላሽ ይሰጣሉ:: የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ሲሆኑ ግን በዚያ ልክ ተባባሪ አንሆንም:: በርግጥ ይሄ ሁሉም ቦታ አይደለም:: የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሀገር ውስጦቹን አቅም እየጎዳ የሚሄድበት ሁኔታ አለ::

ድሮ አንዱ ችግር የነበረው፤ የውጪ የሥራ ተቋራጭ ዶላር ሲጠይቅ ወዲያው ይፈቀድለታል፤ እቃውን ያስገባል:: የሀገር ውስጦቹ እቃውን ለመግዛት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ባንክ ወረፋ ይጠብቃሉ:: እኩል እድል አልነበራቸውም:: አሁን በፋይናንስ ሴክተሩ በተሠራው ሪፎርም የውጭ ምንዛሬ ከባንክ ማግኘት ስለሚቻል ብዙ ችግር የለም:: ስለዚህ ከደገፍናቸው ውጤታማ ይሆናሉ፤ ሆነውም አይተናል::

አዲስ ዘመን- የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የዘርፉን ተዋናዮች አቅም በመገንባት ፕሮጀክቶች በጊዜና በጥራት እንዲገነቡ ለማስቻል የተቋቋመ ተቋም ነውና በዘርፉ የእናንተ አበርክቶ ምን ይመስላል?

ኢንጂነር ታምራት፡- እኛ የዘርፉን ተዋናዮች እንደግፋለን:: ለዚህም ከኮንትራክተር አሶሲዬሽን ጋር በጋራ እንሠራለን:: የሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የሚችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እያመቻቸን እየሰጠን ነው:: በዋናነት ከጥራትና ደህንነት ጋር የሚያያዙ፣ ከፕሮጀክት አስተዳደር ጋር የሚያያዙ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ፕሮጀክትን ለመምራት ክህሎትና ብቃትን የሚያስጨብጥ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ፕሮፌሽናልስ ትሬኒንግ የሚባል ስልጠና አለ:: ይሄ አሜሪካ የሚገኝ ፕሮጀክት ኢንስቲትዩት የሚባል ተቋም ማረጋገጫ የሚሰጠው ስልጠና ነው:: ስልጠናው ለኮንስትራክሽን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ፕሮጀክቶች አመራር አቅም የሚፈጥር ነው:: ይሄንን ስልጠና ለሥራ ተቋራጮች፣ ለአማካሪዎችና ለኢንዱስትሪው ተዋናዮች እየሰጠን የዘርፉን አቅም እየገነባን ነው::

አማካሪዎችም የተለመደ የዲዛይን ሥራቸውን በቢውልዲንግ ኢንፎርሜሽን ሞደሊንግ በሚባለው በቢም ቴክኖሎጂ ቢሰሩ በጣም ውጤታማ ናቸው:: ኢንስቲትዩቱ መሰል ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ አማካሪው፣ ኮንትራክተሩም ሆነ አሰሪው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሠራን ነው:: በሌሎችም የሥልጠና አይነቶች የዘርፉን ተዋናዮች አቅም ለመገንባትና በዘርፉ ጥራት የሚያስጠብቅ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል:: በዘርፉ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች የበቁ እንዲሆኑ ተቋማቱ ለተማሪዎቻቸው የቢም ቴክኖሎጂን የትምህርታቸው አካል እንዲያደርጉ ሥምምነት በመፈራረም የአሰልጣኖች ሥልጠና እንሰጣለን:: ይህም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ተማሪዎቻቸውንና በአቅራቢያቸው የሚገኙ ባለሙያዎችን እንዲያበቁ ማድረግ አስችሏል:: በዘርፉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ፈጠራዎችን ለዘርፉ ተዋናዮች በማስተዋወቅ ሚናችንን እየተወጣን እንገኛለን::

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ሥም አመሰግናለሁ!

ኢንጂነር ታምራት፡- እኔም አመሰግናለሁ!

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You