
የድሬዳዋ ስቴድየም እድሳትና ግንባታ በ2008 ዓ.ም ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን ከ520 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በ2016 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡ በአራት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ስቴድየም 25ሺህ መቀመጫ፣ 16 በሮች፣ የመሮጫ መም፣ አራት የመልበሻ ክፍሎች፣ አራት የዳኞች ክፍል፣ የVIP ማረፊያዎች፣ የVIP ካፍቴሪያ፣ የVIP ጨዋታ መከታተያ ክፍሎች፣ የጂምናዝም ክፍል፣ የሚዲያ ኮንፍረንስ ክፍሎች፣ 68 የንግድ ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ሲሆን፣ የደህንነት ካሜራዎች የተገጠመለት ነው። ስቴድየሙ ሁለት አሳንስሮች የተገጠሙለት ሲሆን ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ የተቀያሪ ተጫዋቾች ማረፊያ/መቀመጫ ከውጪ ሀገር መጥቶ ተገጥሞለታል።
ከሁሉም በላይ ስቴድየሙ በፊፋና ካፍን መስፈርት መሠረት አርቴፊሻል የእግር ኳስ መጫወቻ ሳር የተነጠፈለት መሆኑ ይታወቃል። ፊፋ በድሬዳዋ ስቴድየም የተነጠፈውን ሰው ሠራሽ ሳር (መጫወቻ ሜዳ) ከዓመት በፊት እውቅና መስጠቱን ተከትሎም አንድም የፊፋና የካፍን መስፈርት ያሟላ ስቴድየም ባለመኖሩ ባለፉት አራት ዓመታት በሌሎች ሀገራት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማድረግ ለተገደደው ብሔራዊ ቡድን ትልቅ ተስፋ ነበር።
በታን ኢንጂነሪንግ የተነጠፈው የድሬዳዋ ስቴድየም ሰው ሠራሽ ሳር ስድስት ወር የፈጀ ሲሆን፣ በፊፋ ተገምግሞ ነው እውቅና የተሰጠው። መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው “ስፖርት ላብ ዩኬ” የተሰኘ የስፖርት ቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምር ተቋም ስቴድየሙን መገምገሙ ይታወቃል።
በግምገማው ወቅት ሜዳው የተቀመጠበት ልኬት፣ የመሬቱ ጥብቅነት፣ ከተፈጥሮ ሳር ጋር ያለው መቀራረብ፣ ኳስን የማንጠርና እንደ ልብ የማሽከርከር አቅም፣ የሳሩ ቁመት፣ የራበሩ ምጣኔ፣ የመጫወቻ ጫማ መሬት ሲረግጥ የሚፈጠረው ሰበቃ እንዴት ነው? የሚለውን ገምጋሚ ቡድኑ ተመልክቷል።
በዚህም ሳሩ ደረጃውን ጠብቆ መነጠፉንና ማንኛውንም ዓለም አቀፍ ጨዋታ ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ መሠራቱን አረጋግጧል። በዚህም መሠረት የድሬዳዋ ስቴድየም መጫወቻ ሜዳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ከተወሰኑ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸው ሜዳዎች ጋር ተመጣጣኝና ምቹ መሆኑ በወቅቱ ተገልፆ ነበር።
የመጫወቻ ሜዳው የግምገማ ውጤት ወደ ፊፋ ከተላከ በኋላ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም የእውቅና ሰርተፍኬት ማግኘት ችሏል። ፊፋ ለእውቅናው ማረጋገጫ በላከው ደብዳቤ የሜዳው የምርመራ ውጤት ከተገመገመ በኋላ የፊፋን የሰው ሠራሽ ሜዳ ደረጃን እንዳሟላ ማረጋገጡን አሳውቋል። በዚህም መሠረት የድሬዳዋ ስቴድየም እኤአ ከ25/02/2024 ጀምሮ እስከ 24/02/2027 ድረስ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ማስተናገድ ይችላል ሲል በይፋ አረጋግጧል።
የስቴድየሙ እድሳት መጠናቀቁን ተከትሎ በድሬዳዋ ዋንጫ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻው ጋር ባደረገው ግጥሚያ ተመርቋል። ከዚያ በኋላ ግን ስቴድየሙ እንደተጠበቀው ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ አልታየም። ዋልያዎቹም ይህ በፊፋ እውቅና የተሰጠው ስቴድየም እያለ በሜዳቸው ማድረግ ያለባቸውን ጨዋታ በሌሎች ሀገራት ማድረጋቸውን መቀጠላቸው በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ለምን? የሚል ጥያቄ መፍጠሩ አልቀረም።
በዚህ ረገድ ስቴድየሙ ሁሉንም የፊፋ ደረጃዎች/መስፈርቶች አሟልቶ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለበት ሲገልፁ ቆይተዋል። ይህም በስቴድየሙ አካባቢ የሚገኙ የእምነትና የትምህርት ተቋማት እንዲነሱ ማድረግ ነው። በፊፋና ካፍ መስፈርት መሠረት አንድ ስቴድየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ከትምህርትና የእምነት ተቋማት እንዲሁም ከሆስፒታል ርቆ መገንባት ይኖርበታል።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማስፋፋትና ማልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢብሳ ዱሪ፣ “የፊፋ መስፈርቶች ዓለም አቀፍ ጨዋታ ለማስተናገድ እንቅፋት አልሆኑብንም። የመለማመጃ ሜዳ ከስቴድየሙ ጎን በሚገኘው የልዑል መኮንን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የምንጠቀመው፣ 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያስተናገደ ስቴድየም ነው፣ አሁን እንዲዘምን ሲደረግ የፊፋና የካፍን መስፈርቶች ጠብቆ ነው፣ የፊፋ ልዑክ አስተካክሉ ባለን መሠረት የዶፒንግ ቢሮዎች ለብቻ፣ የሚዲያ ቦታ 4 ስቱዲዮ በማዘጋጀት አስተካክለናል፣ ካፍም በሰጠን አስተያየት መሠረት የማስተካከያ ሥራዎች እየሠራን ነው፣ ከጎን ባለን ክፍት ቦታም የማስፋፊያ ሥራ እንሠራለን” በማለት ፊፋም ይሁን ካፍ በዚህ ረገድ ስቴድየሙ ዓለም አቀፍ ጨዋታ እንዳያስተናግድ ያነሳው ቅሬታ ወይም ይስተካከል ብሎ ያነሳው ሃሳብ/ጥያቄ እንደሌለ ያስረዳሉ።
ዩጋንዳና ጅቡቲ ስቴድየሙ ላይ ዓለም አቀፍ ጨዋታ ማድረጋቸውን የሚያስታውሱት አቶ ኢብሳ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከድሬዳዋ ስቴድየም እኩል የሆነ ሌላ አፍሪካ ሀገር ሜዳ ላይ እየተጫወተ እንደሚገኝ በቁጭት ይናገራሉ። “የጅቡቲ ሜዳ ከእኛ ጋር ለንፅፅርም አይቀርብም፣ ከአየር ንብረቱ ሞቃታማነት ጋር ወዘተ ምክንያት እየተደረገ ወደ ሌላ ሀገር ይሄዳሉ። ይህን ለተለያዩ የሥራ ሃላፊዎች እያሳወቅን ነው፣ ቢያንስ ብሔራዊ ቡድኑ መጥቶ ልምምድ እንዲሠራ” በማለትም ስቴድየሙ አሁንም ዓለም አቀፍ ጨዋታ ለማስተናገድ ምንም ችግር እንደሌለበት ተናግረዋል።
እንደ አቶ ኢብሳ ገለፃ፣ የድሬዳዋ ስቴድየም የምስራቅ አፍሪካ ውድድሮችን ማስተናገድ እንደሚችል ለማሳየት ጥረት እየተደረገ ነው። ድሬዳዋ ከባህር ወለል በታች ዝቅተኛ ቦታ ላይ እንደመገኘቷ ሞቃት ብትሆንም ከብዙዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ተቀራራቢ የአየር ንብረት ነው ያላት። ስለዚህ ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ አሳማኝም ምክንያታዊም አይደለም።
“ተገቢ ያልሆነ ምክንያትና ስም በመስጠት ውድድሮች ወደ ድሬዳዋ እንዳይመጡ የሚያደርጉ አካላት አሉ፣ ይህ ተገቢ አይደለም” ያሉት አቶ ኢብሳ፣ በተለይም ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎቹን ድሬዳዋ ላይ ቢያደርግ በውጪ ሀገራት የሚወጣውን ዶላር ማዳን ይቻላል ብለዋል። ለዚህ ተቀናጅቶ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግና ከተማ አስተዳደሩም ያለውን ምቹ ሁኔታ ከማስረዳትና ከማሳየት ወደኋላ ብሎ እንደማያውቅ ተናግረዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም