‹‹ሐበሻ ምቀኛ ነው›› የሚባል ነገር እንደዋዛ አባባል መሆኑ ነው:: ‹‹የሐበሻ ቀጠሮ›› የሚለው ስድብ አነሰንና ምቀኝነትም ተጨመረልን! የተባለበት ምክንያት ግን ሁለቱም ስለሚገልጸን ነው:: በነገራችን ላይ ስማቸው ‹‹ሐበሻ›› በሚል የሚጠሩ ምርቶችን ለማዘዝ ‹‹እስኪ አንድ ምቀኛ ….›› የሚሉ አሉ፤ ይህ ቀልድ የተጀመረበት ምክንያት ‹‹ሐበሻ ምቀኛ ነው›› የሚለው ከመለመዱ የተነሳ ነው:: ምቀኛ የተባለው እንግዲህ ምርቱ ሳይሆን ‹‹ሐበሻ›› የሚለውን ስም ስለያዘ ነው፤ ምቀኛ የተባለው የሐበሻ ሕዝብ መሆኑ ነው:: አዎ ምቀኞች ነን!
ለምን ተባልን ብሎ መደንፋት ነገሩን ከሀቅነት አያወርደውም እንግዲህ! (ከቻሉ አለመሆን ነው) የሐበሻ ቀጠሮ የሚለው ስድብ በትክክል ይገልጸናል:: 3፡00 ላይ የተባለ አንድ ስብሰባ 4፡00 እና 5፡00 ላይ የምንገኝ አይደለን እንዴ? ታዲያ ይሄ እንዴት አይገልጸንም?
በነገራችን ላይ ‹‹አይገልጸንም›› የሚባል ነገር አይሠራም:: ስለ አንድ ነገር ሲነገር ሙሉውን ማለት አይደለም:: አብዛኛውን ለማለት ነው:: ለምሳሌ ወንዶች ወይም ሴቶች ሲባል ሁሉንም ማለት አይደለም፤ በብዛት ከሚታየው አንፃር ነው:: ብዙ ሰው ግን ነውሩን ለመሸፈን ሲል ‹‹…. አይገልጽም›› ይላል:: ለምሳሌ፤ አንድ መጥፎ ድርጊት ተፈጽሞ ‹‹የእገሌን ሕዝብ አይወክልም›› የምትባል ነገር ትገርመኛለች:: አንድ መጥፎ ድርጊት ሲከሰት ከቦ ‹‹ሰልፊ›› ፎቶ ሲነሳ የነበረ ሕዝብ እንዴት ነው የማይወከለው? ድርጊቱን አለማውገዝና አለመከላከል እኮ ከተሳታፊነት አያንስም! ስለዚህ ይሄ ነገር የእኛን ስም ጭምር ያስጠፋል በሚል ነውር ድርጊት እንዳይፈፀም መከላከል ያስፈልጋል፤ አለበለዚያ ከወቀሳው ማምለጥ አይቻልም::
እስኪ ስለምቀኝነታችን እና አልኩባይነታችን ልብ እንበል:: በአንድ ወቅት በምኖርበት ሰፈር አካባቢ ያጋጠመኝን አንድ ገጠመኝ ልንገራችሁ:: ከምኖርበት አካባቢ እንጀራ የምገዛቸው ሴትዮ አሉ:: እንዲያው እግረ መንገዴን ልናገረውና ሴትዮዋ በዕድሜ ገፋ ያሉ ናቸው:: እንዲህ በዕድሜ ገፋ ያሉ እናቶች ንጹህ እንጀራ እንደሚሸጡ ከዚህ በፊት ከአንዴም ሁለቴ አጋጥሞኝ ስለነበር ምርጫዎቼ ናቸው:: በዚያ ላይ ርህራሄያቸውና ትህትናቸው ቀልቤን ይገዛዋል፤ የእናትነት ለዛ አለው:: ዋጋ ሲጨምሩ ራሱ ተጨንቀው ተጠበው ነው የሚናገሩት:: አንዳንዶቹ እኮ በቁጣ ነው የሚናገሩት ነበር! (ወደህ ሳይሆን በግድህ ትገዛታለህ የሚል ፊት ነው ያላቸው)::
እናላችሁ አንድ ቀን ማታ እንጀራ የምገዛቸው ደንበኛዬ ጋ ስደርስ አንዲት ልጅ የያዘች ሌላ እናት (ወጣት ናት) ለሴትዮዋ የምክር ናዳ (ለእኔ ናዳ ነበር) ታወርዳለች:: ከዚያ በፊት ምን እንዳለቻቸው ባላውቅም እኔ የደረስኩባቸው ምክሮች፤ ‹‹ሌላ ቦታ ይህን ያህል ብር እና እየተሸጠ {በአካባቢው የሌለ ዋጋ ጨምራ ማለት ነው} አንቺ ግን በ…. ብር {ሴትዮዋ የሚሸጡበትን ዋጋ እየጠቀሰች} ትሸጫለሽ! በዚያ ላይ እንጀራሽ ደግሞ ጤፍ ብቻ ነው….›› ትላለች:: ወዲያውኑ የምክሩ ጥቅል ሀሳብ ገባኝ:: በቃ በአጭሩ ዋጋ ጨምሪ ወይም እንጀራውን ምናምንቴ ነገር ጨምሪበት ነው:: የሚያስቀው እኮ ዋጋ ለመጨመር የሚሯሯጡት ባለምናምንቴዎች ናቸው (ድሮስ ከአጭበርባሪ ምን ይጠበቃል!)
የውስጤን በውስጤ ይዤ የተጨመረውን ዋጋ ጨምሬ ልገዛ ሁለት እንጀራ ይስጡኝ አልኳቸው፤ ሰጡኝ:: ጨምር ካሉኝ ልጨምር ወስኜ የተለመደውን ብር አውጥቼ ስሰጣቸው ተቀበሉኝና በቀጣይ እንደሚያስቡበት ፈቃደኝነታቸውን እየገለጹ የሴትዮዋን ምክር በትኩረት ያዳምጣሉ:: በነገው ማታ ብቻቸውን ነው ያገኘኋቸው:: ትንሽ አወራን:: እንደነገሩኝ እንዲህ እየሸጥሽ አያዋጣሽም፤ ወይ ዋጋ ጨምሪ ወይም ሥራውን ተይው ብለው እንደመከሯቸው ነገሩኝ:: እንዲያውም ሌላ ቦታ ይህን ያህል ብር ሆኗል እያሉ ነገሩኝ:: ሥራውን ከሚተውትና የእንጀራውን ጥራት ከሚቀንሱት በሚያዋጣቸው ልክ ዋጋ ቢጨምሩ እንደሚሻል ነግሪያቸው ሄድኩ::
ወደ ቤት ስገባ ብዙ ነገር እያሰብኩ ነበር:: ይሄ በጣም ቀላል እና ተራ ምሳሌ ነው:: ይሄ የሐበሻ ችግር ግን እስከ ትልልቅ ጉዳዮች ድረስ ያለ ነው፤ ባሕሪያችንን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው:: ይቺን ተራ ገጠመኝ ያነሳሁት ብዙዎችን ስለምትወክል እንጂ ትልቅ ጉዳይ እንዳልሆነ ጠፍቶኝ አይደለም:: ሀገር ያወደሙ ትልልቅ ሙስናዎች የተሠሩት በእንዲህ አይነት ሰዎች ነው:: ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚለው አባባል ነገሩን ግልጽ ለማድረግ አጋዥ ይሆነናል:: አንድ ባለሥልጣን ገና ሲሾም ከጓደኛና ከዘመድ አዝማድ የሚሰጠው ምክር ‹‹በል እንግዲህ እወቅበት›› የሚል ነው:: ‹‹አትንከርፈፍ፣ ብልጥ ሁን! አትሞኝ›› ይሉታል፤ በአራድኛው ደግሞ ‹‹ፋራ እንዳትሆን›› ተብሎ ይመከራል:: እነዚህ ሁሉ ምክሮች በግልጽ ቋንቋ ሲቀመጡ ‹‹ስረቅ፣ ዝረፍ፣ ሌባ ሁን!›› ማለት ናቸው::
ልብ በሉ እንግዲህ! ይሄው ሕዝብ ደግሞ ‹‹ሌባ ባለሥልጣን ሁላ!›› እያለ ይሳደባል (ግራ የገባን እኮ ነን!) በእኛ በኩል መንገድ አልተሠራም እያለ መንገድ ይዘጋል፣ እኛ ጋ ኤሌክትሪክ የለም እያለ የኤሌክትሪክ ገመድ ይበጥሳል፤ የውሃ ቧንቧ የለንም እያለ የውሃ ቧንቧ ግን ያበላሻል! እንግዲህ ምን አይነት ባለሥልጣን ነው የሚሻለን? ባለሥልጣን ሲሾም ‹‹በል እንግዲህ ሀገርህን አገልግል! ሕዝብ የጣለብህን አደራ በታምኝነት ተወጣ›› ብለን ቢሆን ኖሮ ያ ሁሉ አያጋጥመንም ነበር::
አጉል አልኩ ባዮች ነን:: እንዲህ ብየህ ነበር፤ መክሬህ ነበር ለማለት እንዲያመቸን ብለን እንጂ ጠቃሚና ጎጂነቱን አጥንተን አይደለም:: እዚህ ላይ የሴትዮዋን ገጠመኝ ምሳሌ እናድርገው::
እንጀራ የሚሸጡት ሴትዮ ሥራውን ቢተውት ይጠቀማሉ ወይስ ይጎዳሉ? መተዳደሪያቸው ነውና ቢተውት ይጎዳሉ:: የሚገርመው ግን እንዲህ ካልሸጥሽ ተይው ተብለው ነው የተመከሩት፤ ወይም ደግሞ ሌላ ባዕድ ነገር እንዲጨምሩበት እየተመከሩ ነው:: እንዲህ አይነት ጨዋ ሰው ሲኖርም ጨዋነቱን አናደንቅም ማለት ነው:: አልኩ ለማለት ብላ ይህን ያህል ብር ነው አለቻቸው እንጂ በወቅቱ በዚያ አካባቢ በጠቀሰችው ብር እየተሸጠ አልነበረም:: ግዴለም የዋጋው ነገር ይሁን! ሴትዮዋም መጎዳት የለባቸውም፤ ግን ለምን የሌለ ነገር ይወራል? ሌሎችም እኮ የጨመሩት በእንዲህ አይነት አሻጥር ነው::
የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ መሃይምነት እና ምቀኝነት ነው:: ድህነት የእነዚህ ውጤት ነው:: ምቀኝነታችን ይሄው እርስበርስ መጠላለፍ ነው፤ ለወገናችን ተንኮል ማሰብ ነው፤ እኛ የምናስበው አንሶ ሌሎች ተንኮል እንዲያስቡ ማነሳሳት ነው::
ነገራችን ሁሉ በዛፎች ተረት ይመሰላል:: ‹‹ከእኛው የወጣ ጠማማ ነው የፈጀን›› እንዳሉት ዛፎች ማለት ነው:: ዛፎች እንዳይቆረጡ ተስማምተው ሕብረት ጀመሩ:: ዳሩ ግን ልብ ብለው ሲያዩት መጥረቢያ ላይ ያለው እጀታ ከእነርሱ የወጣ ነው:: ‹‹ከእኛው የወጣ ጠማማ ነው›› አሉ ይባላል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም