ተገኝ ብሩ
ያኔ እንዲህ ሆነ
እንደ ኢትዮጵያውያን ዘመን ቀመር በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ይህ ሆነ። አገር በወራሪ ጠላት ተደፈረች። ነፃነት የሚያሳጣ ሉዓላዊነትን የሚጥስ ባዕድ ድንበር ተሻግሮ በነፃነት ዘመናትን የተሻገረችውን አገር ኢትዮጵያን ተዳፈረ። ይሄኔ ደመ መራሩ ኢትዮጵያዊ ከያለበት ተጠራርቶ የአገሩን ልዓላዊነት ለማስከበር ራሱን በመሰዋት አገር ለማቆየት ተመመ። በወቅቱ የነበረበትን የውስጥ ችግር ለይደር አቆይቶ አገሬን በሚል የአንድነት ስሜት ወደ ሰሜን የአገሪቱ ክፍል አመራ።
ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ካነገበውና ምስራቅ አፍሪካን በሙሉ በቅኝ ግዛቴ ስር አውላለሁ ካለው የኢጣሊያ ጦር ጋር የዚህች ታላቅ አገር ህዝብ በጀግንነት ተዋደቀ። ለነፃነትና ለአገር ባለው ጥልቅ ፍቅር ደሙን አፈሰሰ። ለሚወዳት አገሩ ምትክ የሌለው ራሱን ከፈለ። አገሩን ለመጠበቅ ክቡሩ የሰው ልጅ አጥንቱን ከሰከሰ። ሉዓላዊነቱ እንዳይነጠቅ ራሱን ያለ ስስት ለመስዋዕትነት ከፊት አሰለፈ።
የታላቁ ድል ብስራት
በዚህም ዘለዓለም የሚዘከር በትውልድ የሚነገር ታላቅ ድል ተበሰረ። የአገራቸውን ክብርና የህዝባቸውን ነፃነት ከራሳቸው ከፍ አድርገው የሚያዩት ኢትዮጵያዊያን በከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት ታላቅ ድል ተጎናፀፉ። በአንድነት ቆመው ወደር በሌለው ጀግንነት አገራቸውን አፀኑ። በዚያ ለጥቁሮች ጭለማ በነበረ ዘመን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አድዋ ላይ ዘመን ተሻግሮ የማይረሳ፤ ጊዜ ተቀይሮ የማይደበዝዝ ታላቅ ታሪክ ሰሩ። አድዋ ላይ ለኢትዮጵያ የድል ሻማ፤ ለመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ችቦ ተለኮሰ።
የድሉ መገኘት አንድነት፣ የብስራቱ መቅረብ ህብረት መሆኑ የገባቸው ኢትዮጵያውያን ከውጪ የመጣ ጠላትን በሀያል ክንዳቸው ደቁሰው አለምን ጉድ አሰኙ። ጦርነቱን በአስገራሚ ሁኔታ በድል በማጠናቀቅ የጠላትን ክንድ ሰበሩ። ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በአንድነት ለአገር ዘብ ቆመው ወርቃማ ታሪክ ፃፉ። የዚህችን ታላቅ አገር ክብር አስጠበቁ። ጦርነቱ ጠላት እንዳሰበው ሳይሆን ኢትዮጵያውያን እንደፈለጉት ሆኖ ተጠናቀቀ። ይህ የኢትዮጵያውያን ታላቅ ገድል በዓለም ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ተስተጋባ።
የአድዋ ታላቅ ድል መገኘት የመሪዎች አስተባብሮ የመምራት ታላቅ ብልሀት፣ የተደነቀ የጦርነት ስትራቴጂና ስልት፣ የህዝብ አገር ወዳድነት ከጀግንነት ጋር ተዳምሮ ያስገኘው ውጤት መሆኑ አይታበይም። በዚህ ታላቅ ተጋድሎ ስለአገራቸው ራሳቸውን የሰጡ ኢትዮጵያውያን ስለህዝባቸው ነፃነት የተዋደቁ ሀበሾች፤ ስለ ሉዓላዊነታቸው የተጋደሉ አገር ወዳዶች የከፈሉት መስዋዕትነት ሀያል ነውና ሁሌም ይዘከራሉ። በዚህ ጦርነት የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ የስለላ ዘይቤ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ስለላ በዓድዋ ጦርነት
ያኔ በአባቶች የተፈጸመው ጀብዱና በእናቶች ትጋት የተበሰረው ድል የእያንዳንዱን አርበኛ ቆራጥነት የእያንዳንዱን ዘማች ጀግንነት ይጠይቅ ነበር።በጦር ሜዳ ውሎ ድል ለመቀዳጀት የጠላት ሀይል አሰላለፍ፣ የመሳሪያ እና የሰው ሃይል ብዛት፣ ጥንካሬና ድክመት በአጠቃላይ የተቃራኒ ወገን ስነልቦናዊ ሁናቴን ማወቅ በዚያ ልክ ለመዘጋጀትና ለማጥቃት ስለሚረዳ የተሻለ ድል ያጎናፅፋል። በመሆኑም በአድዋ ጦርነት ላይ ኢትዮጵያውያን የመረጃ ሰዎች ለኢትዮጵያ ጦር ድል መቀዳጀት ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚዘነጋ አይደለም።
በአድዋ ድል ላይ ኢትዮጵያውያን ለተቀዳጁት ድል ያበቃቸው ታላቅ የስለላ ጥበብና መረጃ የማነፍነፍ ችሎታቸው ነው፤ መረጃውን ለወገን ጦር በሚበጅ መልኩ መተንተናቸውም ትልቅ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ነበረው። እጅግ አስገራሚ ውጤት ያቀዳጀው የኢትዮጵያውያንን ልዩ የስለላ ጥበብ በወቅቱ ከነበረው ሁነት ጋር ከብዙ በጥቂቱም ቢሆን መጥቀስ ይገባል። በተለይም የኢትዮጵያውያን የስለላና የመረጃ ሰዎች በወቅቱ ለአገራቸው የከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነትና ተጋድሎ በመጨረሻም የተቀዳጁት ድል አይረሴ ሆኖ ለዘላለም ይኖራል።
የጣሊያኖች የስለላ መረብ በኢትዮጵያ
በወቅቱ ጣሊያኖች የኢትዮጵያን ጦር በቀላሉ አሸንፈን ኢትዮጵያን እንቆጣጠራለን እኛ በፈለግነው መልክም አገሪቱን እናስተዳድራለን ለዚህም ብቁና በቂ የሆኑ የመረጃ ሰዎች አደራጅተናል በስለላ ጥበብም እኛን የሚያህለን የለም ቢሉም፤ ኢትዮጵያውያን ግን በእውን የታየ የመረጃና ስለላ ጥበብ ችሎታቸውን አስመስከረዋል።ጣሊያኖች ከውጫሌው ውል በኋላ ኢትዮጵያን በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን የስለላ መረብ ዘርግተውም ነበር። በዚህም የተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛት ያስተዳድሩ ለነበሩ ሹማምንት፣ የጦር አዛዦችና የአካባቢ ገዢዎች ስጦታዎችን በማበርከት፣ የተለያዩ አማላይ ቃሎችን በመግባት በማዕከላዊ መንግስት ላይ እንዲያምፁና ሀገር ሰላም እንዳትሆን እንዲሰሩ ለማድረግ ሞክረዋል።
ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀትና ለመውረር ባላቸው ጥልቅ ፍላጎት የዘረጉት የስለላ መረብ ነበር። ስለላው ወደ ኢትዮጵያ በተለያየ መንገድ በገቡ ጣሊያናዊያን የተመራ ነበር፤ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን አሳልፈው ለጠላት እንዲሰጡም ጥሪ ተደርጎላቸዋል። በዚህም ነጋዴው፣ ፊትለርና ሀኪሙ ትራቨርሲ የሀረሩን ራስ መኮንን፤ ጄኔራል ጋንዶልፊ የትግራዩን ራስ መንገሻን፣ ኢንጂነር ካፑቹ የቤተ መንግስቱን የጦር መኮንኖች፣ ሳልመንዲን ንጉስ ተክለ ሀይማኖትን የመሳሰሉ ግለሰቦችንና የተለያዩ የጦር መኮንኖችን ቀርበው ለማስከዳትና በአገር ላይ ለማሳመፅ ጥረት አድርገዋል።
ይሁንና ጣሊያኖች በገቡላቸው ቃልና የተለያዩ ስጦታዎች ተታለው አገራቸውን ለጠላት አሳልፈው የሰጡ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ የትግራዩ ገዢ ራስ መንገሻ ዮሀንስ (በኋላ ላይ በአፄ ምኒልክ ስትራቴጂያዊ ስልት አገር ክደው ተስማምተው ከነበረው ከኢጣሊያኑ ከጄኔራል ባራቴሪ ጋር ተዋግተዋል)፣ የውጫሌውን ውል ያስተረጎሙት ግራዝማች ዮሴፍ የተለያዩ መረጃዎችን ለጣሊያን አሳልፈው ሰጥተው እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያስረዳሉ።
በእርግጥ ጣልያኖች በጥቂት ኢትዮጵያውያን ላይ ዘመቻቸው ቢሳካም፣ የጣሊያንን አገርህን ሰልል የሚል ግብዣን በመፀየፍ ለአገራቸው ያላቸውን ታማኝነትና ክብር በተግባር ያረጋገጡት ቁጥራቸው በርካታ ነበር። በተለይም የሀረሩ ራስ መኮንንን የመሳሰሉት ገዢዎች ለአፄ ምኒልክ ስለ ጣሊያኖች በማሳወቅና የጣሊያኖችን ግብዣ ባለመቀበል ብሎም ጣሊያኖችን በማታለል ለአገራቸው ያላቸውን ታማኝነት አስመስክረዋል። በተለያየ አካባቢ የነበሩ የኢትዮጵያ የጦር መኮንኖች ጣሊያኖችን በማታለል መረጃዎችን ተቀብለው ለንጉሱ ያደርሱ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
የአፄ ምኒልክ የስለላ ቡድን ማቋቋም
ኢትዮጵያውያን የአድዋ ድልን እንዲቀዳጁ ያደረጋቸው አንደኛው ምክንያት የመረጃ አሰባሰብና አተናተናቸው ብሎም መረጃው በጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጋቸው ነው። የኢጣሊያ ጦር የዘረጋውን የስለላ መረብ ለመበጣጠስና ጦርነቱን በድል ለመወጣት እንዲያስችል የኢትዮጵያው መሪ አፄ ምኒልክ በኢትዮጵያ በኩል የስለላ ቡድን መስርተው መስራት ጀመሩ።በየጠረፉ በሚወጣና በሚገባው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግም ትዕዛዝ ተላለፈ። በዚህም ለብዙ ጊዜያት ከንጉሱ መረጃ እየሰበሰበ ወደ አስመራና የጣሊያን ጦር ወደሚገኝበት ሲልክ የቆየው የቤተ መንግስቱ አናፂ የነበረው ጣሊያናዊው ካፑቹ በመጨረሻ በሸንበቆ ዘንግ አድርጎ ከላከው መረጃ ጋር ተያዘ። ከዚያም ሌሎች ለጣሊያን ይሰሩ የነበሩ ሰላዮችም ቀስ በቀስ ተይዘው የጣሊያንን የስለላ መረብ መበጣጠስ ተቻለ።
የአድዋ ጦርነት ሲቃረብም አፄ ምኒልክ ከጦር መኮንኖቻቸው ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ጦር አሸናፊ መሆን የሚያስችለውን ዕቅድ ማውጣት ጀመሩ። በዚህም መልኩ ሰላዮችን መመልመልና የጣሊያንን ጦር አጠቃላይ ሁኔታ መረዳት የሚያስችል መረጃ ማግኘት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት ተሰራ። በስለላ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ለድሉ መገኘትና የወገን ጦር መስዋዕትነትን በመቀነስ ለአገራዊ ሉዓላዊነት መከበር ታላቅ አበርክቶ ነበራቸው።
ለድሉ መገኘት ታላቅ አስተዋፅኦ የነበራቸው የኢትዮጵያውያን የመረጃና የስለላ ሰዎች፤ በልዩ ጥበብ ጦርነቱ በድል እንዲጠናቀቅ ታላቅ ጀብድ ፈፅመዋል። የስለላና መረጃ ባለሙያዎቹ የጠላት ጦር አሰላለፍን ለወገን ጦር በመጠቆም፣ የጠላት የጦር መሳሪያ ብዛትና የተዋጊ ወታደሮች ቁጥርና አሰፋፈርን በመለየት ለወገን ጦር በማሳወቅ፣ ለጠላት የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የወገን ጦር ድል እንዲያገኝ በማድረግ ልዩ የሆነ የስለላ ጥበብ ተጠቅመዋል።
ድሉ ሲጠቀስ በታሪክ ሰነድ ላይ ስማቸው ተከትቦ ስራቸው ጎልቶ ከሚነገሩት መካከል ባሻ አውዓሎምና ገብረ እግዚ ተጠቃሽ ናቸው።አፄ ምኒልክም ለእነዚህ ሁለት የስለላ ሰዎች ተልዕኮ ሰጥተው የጣሊያንን የጦር እንቅስቃሴ ማወቅ ቻሉ።
ባሻ አውዓሎም ( ኢትዮጵያዊው ሰላይ)
ውልደታቸው እንቲጮ ሲሆን በአድዋ ጦርነት ላይ የተሳተፉ አገር ወዳድ አርበኛና ሰላይ ነበሩ። ባሻ አውዓሎም በልዩ የስለላ ጥበብና የጦር ሜዳ መረጃዎችን ለወገን በማቀበል በሰሩት ታላቅ ጀብዱ ይወሳሉ ።በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያን በስለላ ሙያ በማገልገል ለአገራቸው ታላቅ ገድል ፈፅመዋል። እኚህ ታላቅ የመረጃና ስለላ ሰው ከጠሊያን ጦር ጋር አብሮ የተሰለፈና ኢትዮጵያን የሚሰልል በመምሰል በተለየ ጥበብ ለኢትዮጵያ ጦር ትክክለኛ መረጃ ሲያቀብሉና ለጣሊያን ጦር ደግሞ የተሳሳተ መረጃ በመንገር ለአገራቸው ውለታን ፈጽመዋል።
ታላቁ የስለላ ሰው ባሻ አውዓሎም በጣሊያኑ የጦር መሪዎች ሰልጥነው ኢትዮጵያን እንዲሰልሉ ተልዕኮ ቢሰጣቸውም የአገራቸውን ፍቅር ገፍተው፣ የህዝቡን አደራ ዘንግተው ያን ማድረግ አልፈለጉም። ይልቁንም የጣሊያንን ጦር ይበልጥ ለመቅረብ የረዳቸውን እድል ተጠቅመው ለአገራቸው ነፃነት በስውር ታግለዋል። ለኢትዮጵያ ጦር መሪዎች የጣሊያኖች አጠቃላይ ሁናቴን የተመለከተ መረጃ በማቀበል ድሉ እንዲገኝ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል።
በራስ መንገሻ አማካኝነት ከአፄ ምኒልክ በቀጥታ የተገናኙት ጥበበኛው ባሻ አውዓሎም ጣሊያኖችን በማታለልና ለእነሱ ሰላይ ሆነው የሚሰሩ በማስመሰልና በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የጣሊያን ጦር የሚገኝበትን ሁኔታ በመንገር በልዩ ጥበብ ሰልለዋል። በተለይ እኚህ ሰላይ ለጣሊያን ጦር መሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ጦር የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ለመሸነፋቸው ምክንያት ሆነዋል።
ባሻ አውዓሎም በወቅቱ ለጣልያን ጦር ከሰጡት የተሳሳተ መረጃ መካከል የኢትዮጵያ ጦር በረሀብ ተዳክሞ እየተበታተነ መሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን በእሁድ ቀን ሰንበትን ስለሚያከብሩና ስለማይዋጉ በዚያን ቀን ጣሊያኖች ከምሽግ ወጥተው ቢዋጉ እንደሚያሸንፉ፣ የጦር መኮንኖች ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ባለመግባባት ቅራኔ ውስጥ መግባታቸውና የኢትዮጵያ ጦር መድከሙን የሚገልፅ የተሳሳተ መረጃ በማቀበል የጣልያን ወታደሮች ከምሽጋቸው ወጥተው እንዲዋጉና በተሳሳተ መረጃ እንዲሸነፉ ሰርተዋል።
ከባሻ አውዓሎም ጋር የሰሩትና ብዙ መረጃዎችን ከጣሊያን እየመነተፉ በመውሰድ ለኢትዮጵያ ያቀብሉ የነበሩት ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሰላይ ገብረ እግዚ ነበሩ። እኝህ ኢትዮጵያዊ ሰላይ ለአገራቸው በሰሩት ታላቅ ተግባር በታሪክ እንዲዘከሩ አድርጓቸዋል።
ኢትዮጵያውያን በዘመናዊ መልክ የሰለጠነውን የጣሊያን የስለላ ጥበብ በሚያስከነዳ መልኩ ልዩ ሀገርኛ የስለላ ጥበብና ወኔን ተላብሰው በሰሩት ታላቅ ተግባር አገሪቱ ድል እንድትቀዳጅ አድርገዋታል። በታላቅ ጀግንነት ከዛሬ 125 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የተገኘው ድል የዛሬው ትውልድ እያወሳ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው የከፈሉትን ጀብድ እያደነቀ ዛሬ ድረስ አገሩን ከጠላት ጠብቆ ሉዓላዊነትን አስከብሮ መዝለቁን ቀጥሏል።
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ይሁን! ይህን ፅሁፍ ሳዘጋጅ ከታሪክ መዛግብት መካከል የእውቆቹ የታሪክ ፀሀፊያን ማለትም በርክለይ፣ ራይመንድ ጆናስ፣ የፀሀፊ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ፣ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ፣ጳውሎስ ኞኞ ስለ አድዋ ጦርነት የጻፏቸውን መፅሀፍት በዋናነት ጠቅሜአለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013 ዓ.ም