ጽጌረዳ ጫንያለው
አርበኝነት እና ሽፍትነት እንደሙያና እንደመፍትሄ ይቆጠር በነበረበት ዘመን ሁሉም ትምህርቱን እያቋረጠ ወደ ጦርነት የተጓዘበት ነው አድዋ።ምክንያቱም የአገሩን ክብር ሊቀማ ነው ፤ እያንዳንድህ ልትገዛ ነው፤ ባሪያ ሆነህ ሌሎችን ልታገለግል ሲባል መቼም አይሆንም የሚለው የአገሬው ጀግና ድምጹን ያሰማበት ነው።ወደ እውቀትም ወደ ሽፍትነትም የሚሄደው የአገርን ችግር ለመፍታት አንድ የሆነበትም ነው።ከሁሉም በላይ ደግሞ አለቃ ምንዝር ሳይባልበት መሪዎች፣ ኃላፊዎች፣ ሹማምንቱ ከሰራተኛው ጋር እኩል የዘመተበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
በአድዋ የእርስ በርስ ቅያሜና የስልጣን ጉዳይ እንዲሁም ገንዘብም ዋጋ አልነበረውም፤ ከሁሉም የሚልቀው የአገር ደህንነት ነው።በዚህም ለአገር ክብር ተሰባስበው በአንድ ላይ ሆነን እናስብ አሉ።አስበውም በአንድነት ጉልበት ለውጥ በሚያመጣ ለዋጭ አእምሮ ውስጥ ጉዟቸውን አደረጉ። ለመሆኑ በወቅቱ የነበረው አእምሯዊ ዝግጅነታቸውና ስነልቦናቸው እንዴት ተገነባ፤ አንድነት ለእነርሱ ምን መልክ ነበረው፤ የልቦና ውቅራቸውስ ምን ይመስላልና የመሳሰሉትን ለህክምና ዶክተር እና የስነ ልቦና አማካሪ ዶክተር ወዳጄነህ መሃረነ አነሳንላቸው።ምሁሩ የነገሩንን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ስነልቦና ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ስነልቦና ማለት ሳይንስ ሲሆን፤ ባህሪን የሚያጠና ነው።ባህሪ ማለት ደግሞ ማንኛውም ሰው በድርጊትና በሚሰጣቸው ምላሾች የተገለጠና የተደበቀ ማንነቱን የሚያይበት ሁነት ነው።ስለዚህም ስነልቦና የሰውን ስሜት፣ እውቀት፣ ባህሪና አኗኗር የሚያጠና ሳይንስ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።ይህ ሳይንስ በዋናነት የሚመልሰው ደግሞ ሰዎች የሚሆኑትን ለምን ሆኑ፣ ለምንስ አደርጉትና የመሳሰሉትን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከስነልቦና አንጻር ወደኋላ መለስ ብለን የአድዋ ድልን ስናነሳ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ የገጠሙት አካል በቴክኖሎጂ አቅሙ የጎለበተ፣ በመሳሪያ የተደራጀና የነጭ የበላይነት የነገሰበት ወቅት ላይ ነው። ይህ በኢትዮጵያውያን ላይ ምን አይነት ጫና አሳርፏል? ከዚህ አንጻርስ ስነልቦና እና አድዋን እንዴት ያሰናስሉታል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ይህንን ለማስረዳት ወደኋላ ተመልሶ የነበሩትን ክስተቶች ማንሳት ግድ ይለናል።እናም በአፍሪካ ላይ የነበረውን ስናነሳ ነጮች ከመቀራመታቸው በፊት ያለው ነባራዊ ሁኔታን ማለትም ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት አፍሪካ በራሷ መንገድ እያደገች የነበረች አህጉር ነች።ጋናን፤ ኢትዮጵያን፣ ማሊን፣ ዚንባብዌንና የመሳሰሉትን ብናነሳም እንዲሁም ለዓለም ሁሉ የሚያስገርም ስልጣኔ ነበራቸው።ሆኖም ከ16ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ አፍሪካውያን ክፉ ነገር ገጠማቸው።በአትላንቲክ ዳርቻ ያሉ አፍሪካውያንን በባርነት እየወሰዱ ይጠቀሙባቸው ጀመር።ይህ ደግሞ የሆነው በፖርቱጋሎች ሲሆን፤ ንግዱ እየተስፋፋ ሲሄድም ሌሎቹ መግባትና የባሪያ ንግድም በይፋ በእነርሱ ላይ እንዲታይ ሆነ።ስቃዩንም አጠነከረባቸው።
የአፍሪካ አንዳንድ ነገስታት፣ የጎሳ መሪዎች፣ አለቆች ጭምር የንግድ ስርዓቱ በትናንሽ ስጦታዎች የበለጠ እንዲጠናከር በማገዛቸው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ የተለያዩ ስቃዮችን እንዲያሳልፉ ተፈረደባቸው።በካርጎ ጭምር እየተወሰዱ የባሰ ስቃይ ውስጥ እንዲገቡም ይደረግ ነበር።በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ደግሞ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን አፍሪካውያን በባርነት ተወስደዋል።ከእነዚህ ውስጥም ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪካውያን በአያያዝ ምክንያት መንገድ ላይ ሞተዋል።ተርፈው የሄዱትም ቢሆኑ በደንብ አይያዙም።ከእርሻ ውጪ ሌላ ቦታ ላይ አያሰማሯቸውም።
እንደ ሰው ሳይሆን እንደ እቃና ንብረት ስለሚቆጥሯቸው የፈለጋቸውን ያሰሯቸዋል።በዚህም የሚደርስባቸው ሰቆቃ ቀላል አልነበረም።ይህ ታሪክ ደግሞ አፍሪካውያንን የሰበረ፤ ቀና ብለው እንዳይሄድ ያደረገና አንገታቸውን ያስደፋቸው ነበር።ስብዕናቸውንም ቢሆን የሰበረና ጠባሳ የጣለ ነው።ባሪያ መያዝ ከተከለከለ ወዲህም ቢሆን ብዙ ጫና አሳርፎባቸዋል።ለአብነት ጥቁር አሜሪካውያን ጭምር ከአራተኛ ክፍል በኋላ እንዳይማሩ፣ ነጮች የሚታከሙበት ቦታ እንዳይታከሙ ተደርገዋል።ይህ ደግሞ በጣም የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል። በአጠቃላይ ይህ ሁኔታ የአፍሪካውያንን ስብዕና ሰብሮ በራስ መተማመናቸውን አሳጥቷቸዋል።እችላለሁ እንዳይሉና ሰርተው እንዳይለወጡ አድርጓቸዋል።አቅሙ ቢኖራቸውም እንዳያወጡትም ገድቧቸዋል።ፍርሀት እንዲነግስባቸውም ሆነዋል።
አፍሪካውያን በርሊን ኮንፍረንስ ጭምር 13 አገራት ተመራርጠው በመቀራመት ብዙ ስቃይ ያበዙባቸው ናቸው። አሁን የምንጠቀምበትን ካርታ ጭምር በመስራት የፈለጉትን አድርገዋል። ነገር ግን አይበገሬዋ ኢትዮጵያ ለጣሊያን ብትሰጥም በአድዋ ድል ከአፍሪካውያን ልዩ ሆና እንድትወጣ ሆናለች።ለሌላው ጭምር የነጻነት አርማ በመሆን ቀስቅሳለች። ስለዚህም አድዋን ስናስብ ጫና ሳይሆን እምነት፣ ፍቅርና አንድነት ኃይል መሆናቸውን በስነልቦና ያየንበት ነው።
ስልጣኔ ከእነርሱ ውጪ እንደሌለ ያሳዩበት፤ መታጠቅ በመሳሪያ ሳይሆን በእምነትና በአንድነት መሆኑን በተግባር ያሳዩበት ነው።ምክንያቱም እነርሱ የበላይም ሆነ የበታች የሚለውን ስሜት አላዩትም።ማንም አልገዛቸውም።ገና ጅማሮው ላይ ነው አይበገሬነታቸውን በስነልቦናም በተግባርም ያሳዩት።ስለሆነም የአድዋ ድል ከስነልቦና አንጻር ሲታይ በበርሊን ኮንፍረንስ አፍሪካውያን ሰዎች አይደሉም የተባለውን አመለካከት ውሸት ያደረገ፤ ነጮች ገዢዎች ብቻ አለመሆናቸውን ያሳየ፣ ጥቁሮችም ማስተዳደርና ክብራቸውን እንደሚጠብቁ ያረጋገጠ፤ አፍሪካውያን ታሪክ የላቸውም ወደፊትም ታሪክ አይሰሩምን የቀየረና ስነልቦናውን ያስተካከለ ነው።
በአጠቃላይ የአድዋ ጉዳይ የክብር ጉዳይ እንጂ የስልጣንና ለማህበረሰቡ የመስጠት ጉዳይ አይደለም።በዚህም ምንም ብታደርጉልን እናንተ እኛን መግዛት አትችሉም ሲሉ ነው የዘመቱት።የማንነት ጉዳይ በገንዘብ የሚሸጥ አይደለም፤ በብርቅርቅ ጉዳይም እንዲሁ።ስለሆነም ማንነታችንና ክብራችንን ለእኛ ተውልን አሉ።ነገር ግን የሰማቸው ስላልነበረ ጦር ሰበቁ።ሊሞቱ እንደሚችሉ እያወቁም ነው ከዘመናዊው ታጣቂ ጋር የገጠሙት።ብዙዎችም ለአገር ብለው መስዋዕትነትን ተቀብለዋል።ግን ታሪክ እንደሚዘክራቸው ያውቃሉና ቤተሰብ ጭምር አይከፋም።በዚህ ስነልቦናም ነው ድሉን ለዛሬ ታሪክ ያበቁት።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያውያን ስነልቦና ከዚህ አንጻር እንዴት ይታያል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ኢትዮጵያውያን በብዙ ነገሮች የተለዩ ናቸው። የመጀመሪያው የባሪያ ንግድን አያውቁትም።እነርሱ ዘንድም አልደረሰም።በባርነት ተሸጠውም ስቃዩን አላዩትም።ስለዚህም የተሰበረው የአፍሪካ ስነልቦና ከእነርሱ ውስጥ የለም።ጣሊያኖች ሲመጡባቸውም እንግዳ የሆነባቸው ለዚያ ነው።የነጭ የበላይነት ቀርቶ ጥቁርና ነጭ የሚባለውን ልዩነት አይረዱም።ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ግን ከዚህ ቀደም ባሪያ አድርገው እንደወሰዷቸውና እንደገዟቸው ስለሚያውቁ ሊይዟቸው ሲመጡ ምንም አላሏቸውም።ኢትዮጵያ ግን ያልተሰበረ ስብዕና ላይ ስላሉ ማን ነው ደፋሩ አሉ።ሞክረኝ ሲሉ ጦራቸውን ሰበቁ።
ኢትዮጵያውያን የተለየ ስብዕና ያላቸው ናቸው የሚባለው ያለምክንያት አይደለም።ሁለት መሰረታዊ ነገሮች ነበሩ ።እነዚህም ከፍተኛ የራስ መተማመን፣ ብቁ መሆናቸውን ማመናቸውና የፍትህ ስነልቦና ናቸው።እናም ሰውን ለመበደል ሳይሆን የመጣባቸውን ጠላት ሊከላከሉ አድዋ ላይ ዘምተዋል።አእምሯቸው በነገራቸው መሰረትም የመጠቃት ስሜት ስለተሰማቸው መከላከል ይገባናል ሲሉ በአንድነት ጦርነቱን ተቀላቅለዋል።ሌላው ኢትዮጵያን የበላይና የበታች የሚሉት ነገር የላቸውም።ከዚያ ይልቅ ሰው ሁሉ እኩል ነው ብሎ ማመኑ ያደጉበት ስነልቦና ስለነበር አይደፈሬነታቸውን እንዲያሳዩ ሆነዋል።
በአምላካቸው ላይ የመተማመን ስነልቦና ያላቸውም ናቸው።ሁሉን የፈጠረው አምላክ ከእኛ ጋር አለ ብለው የሚያምኑ በመሆናቸው ሁሉንም በእርሱ እናሸንፋለን የሚል ወኔ እንዲላበሱ ሆነዋል።የማሸነፋቸው ምስጢርም ይኸው ነው። በተለይም ከፍተኛ በደል ደርሶባቸውና ስቃይ ውስጥ ያሉ ቢሆኑም ‹‹እኔ ለአገሬ እንድሞት ይፈቀድልኝ›› ብለው የሚጠይቁ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- የጥቁር ህዝብን ለነጻነት የሚደረግ ትግል የአድዋ ድል ምን ያህል ሞራል የሰጠ ነበር? የሞራል ስንቅ ከመሆን አንጻርስ እንዴት ይታያል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- የአድዋ ድል ሲሰማ በመጀመሪያ አውሮፓ በሙሉ ተደናግጧል።ምክንያቱም ተግባሩ በነጮች ላይ ተደርጎ አያውቅም።ሁልጊዜ ነጩ ቆሞ ጥቁሩ ተንበርክኮ ነው በሰው አዕምሮ ውስጥ የሚሳለው።ድሉ ሲመጣ ግን ሙሉ ለሙሉ ተቀየረ ።ይህ ብቻ ሳይሆን ጥቁሩ ህዝብ በሙሉ እንዲህም ይቻላል ማለት ጀመረ።ጥቁር ሲባል አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ ጥቁር አሜሪካውያንንም ስለሚጨምር ሁሉም ነጻነቱን ለማግኘት ወደመታገሉ ገባ።ከሁሉም በላይ ደግሞ የአድዋ ድል ለአፍሪካ ነጻነት ብቻ ሳይሆን ለሰብአዊ መብት መከበርም መሰረት የሆነ ነው።
በአሜሪካ እነ ማርቲሉተር የሰብዓዊ መብት መከበር ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት ድሉን ካዩ በኋላ ነው።ስለዚህ መብት የሰጠ የድል በዓል ነው።ከዚያ ባሻገር በነጭ አዕምሮ ውስጥ ተቀምጦ ያለውን አስተሳሰብም በማጥፋት ትልቅ ምሳሌ የሆነ ነው። ለአብነት አፍሪካውያን ሰዎች አይደሉም የሚለውን ሰው ብቻ ሳይሆኑ ተዋግተው አሸንፈው ነጻነታቸውን ያስከበሩ፤ የተቸገረን መግበው፣ ሊወጋቸው የመጣውን ደግሞ ሳይጎዱት ተንከባክበው ወደአገሩ የመለሱ ከሰውም ሰው ናቸው የሚል አመለካከትን ያጎላም ነበር።
አድዋ አፍሪካውያን ታሪክ የላቸውም ፤ ታሪክም አይሰሩም የሚለውን ፉርሽ ያደረገ፣ ነጭ ከጥቁር ይበልጣልን ያስቀረ፣ ሁልጊዜ ጥቁሮች የበታች መሆን አለባቸው የሚለውንም አመለካከት የቀየረ ነው።ስለዚህም እንደበዓል ሸፍነነው የምናከብረው ስለሆነ ነው እንጂ ታሪኩ የበዛና የኢትዮጵያውያንና የጥቁርን ህዝብ ምንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።ለዚህም በፊት ላይ እኔ የነበረኝ አመለካከት ጥሩ ማሳያ ነው።ስለ አድዋ ትኩረት ከማይሰጡት መካከል እመደብ ነበር።ግን አንድ አጋጣሚ ታሪክ ተቀየረ።ይህን ያደረገው ጥቁር አሜሪካዊ ነው።
ለሥራ ወደ ውጭ በሄድኩበት ወቅት ሻንጣ ስጠብቅ ‹‹ ከኢትዮጵያ ነህ አይደል›› አለኝ።እኔም ‹‹አዎ ›› አልኩት።ቀጠለና ‹‹ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ አገር ነች›› አለኝ።አሁንም በትዝብት እያየሁት ‹‹ አዎ›› የሚል መልስ ሰጠሁት።ቆየት አለና የተናገረው ግን ከምንም በላይ አስደመመኝ።ይኸውም ‹‹ ጣሊያኖች ወረውን ነበር አይደል የሚል ነበር።አዎ መልሴ ነው።አሸነፍናቸው አይደል! ሲልም ራሴን ማመን አቃተኝ።ምክንያቱም እነርሱ እንዲህ ያከበሩት እኛ ለምን የሚለው አዕምሮዬን እየጠለዘኝ ለጠየቀኝ ምላሽ ሰጠሁ።ምክንቱም እርሱ አሜሪካዊ ሆኖ ሳለ ራሱን ኢትዮጵያዊ አድርጎ ሲናገር ምን ያህል ደስታ ውስጡ እንደተሞላ ማመንም ያቅታል።
ድሉ የእርሱም ጭምር እንደሆነ ሲናገረውም እንዲሁ በደስታ ነበር።ታዲያ እኛስ ስንል ሲፈልገን ለአንድ ብሔር እንሰጠዋለን፤ ካሻን ደግሞ ለዚህ ድል ያበቁንን አባቶች የበዛውን መልካሙን ነገራቸውን ትተን እናጥላላቸዋለን።በጣም ብዙ መጥፎ ትርክቶችንም ስለእነርሱ እንናገራለን።በዚህም ታሪካችንን፣ ማንነታችንን ሳንረዳ ኮናኝ ብቻ ሆነን እንንቀሳቀሳለን።ከዚያች ቀን በኋላ እኔም ይህንን ነበር የተረዳሁት።እናም የአድዋ ድል የእኛ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ጥቁር ህዝብ ድል እንደሆነ አምነን ብዙ መመርመርና የተሻለ ማድረግ ላይ መስራት አለብን።
አዲስ ዘመን፡- በጦርነት ውስጥ የአድዋ ጀግኖች የነበራቸው የሞራል ፤ በየዘመኑ የነበረው አገራዊ አንድነት ምን ያህል ስነልቦናዊ ጥንካሬ የሰጠ ነበር ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- አላማ ጽናት ነው።ያልተሰበረ ማንነት መኖርም እንዲሁ ብርታትን ማግኘት ነው።ባርነትን ያለመደ ስብዕና መኖሩና አይደፈሬነትን መላበስም ድልን ያቀዳጃል።ለዚህም ነው ሁሉን አስተባብረው በመያዛቸው ድሉ ለእነርሱ ቀላል የሆነው።በተለይ የአላማ ጽናት መኖሩ ለአንድነታቸው መሰረት ሆኖ ወደፊት እንዲገሰግሱ አድርጓቸዋል።የአሁኑንና የአድዋ ድልን ስናነሳ ልዩነቱ የሚታየውም እዚህ ላይ ነው። አገር የሚለው ስያሜ ለነእርሱ ከራስ በላይ ነው።ከጥቅምና ከስልጣንም በላይ ነው።ለዚህም ማሳያው አድዋ የተካሄደበት ቦታ ትግራይ ውስጥ ቢሆንም ኦሮሞው፣ አማራው፣ አፋሩ፣ ጋምቤላው፣ ሀረሬው፣ ደቡቡ፣ ጉራጌው …ወዘተ ተነካሁ ብሎ ዘምቷል።
የዓይናችንን የማየት 180 ዲግሪ የተጠቀሙበት እነርሱ ናቸውም።ምክንያቱም ሩቁን ጭምር
አይተው በተግባር አስበውታል፤ በድላቸው ነጻነትን አድለውታል።ለዚህ ደግሞ ቤተሰቦቻቸውና ማህበረሰቡ የአገርን ፍቅር በልባቸው አትሞላቸዋል።ኖረውትም አሳይተዋቸዋል።እነርሱም እንዲኖሩትና ሌሎችን እንዲያኖሩበትም አስተምረዋቸዋል።የሚማርባቸው ጠፋ እንጂ።ይህ ስነልቦናቸው ደግሞ አገር የሚለው ነገር በምንም የሚደራደሩበት አድርጎላቸዋል።ቂምና ቁርሾ እንኳን በአገር የመጣ ካለ ከድሉ በኋላ የሚሉ ስብዕና ያላቸው ናቸው።
የዛሬው ትውልድ ግን በፖለቲከኞቻችንና በአክቲቪስቶቻችን ሥራ እንደ ጋሪ ፈረስ ጎማና ላስቲክ ከጎንና ከጎን ተደርጎበት ከሰፈሩ ውጪ እንዳያይ ሆኗል።እይታውም ጠቧል።ስለዚህ ጎማና ላስቲኩን የማንሳቱ ጊዜ አሁን ነው።በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም ጭምር አድዋን ማሰብም ከዛሬ ውጪ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።ድፍን አፍሪካ የሚጠብቀው ኢትዮጵያን በመሆኑ ይህንን በተግባር ማሳየትም የአሁኑ ትውልድ ድርሻ መሆን ይጠበቅበታል። ምክንያቱም የአፍሪካ አንድነትን አምጪ መሪም ኢትዮጵያውያን ናቸው።ለዚህ ምክንያቱ ቢቢሲ ባጠናው ጥናት አፍሪካውያን ነን የሚሉት ኢትዮጵያን ብቻ መሆናቸው ነው።ለአብነት ግብጻውያን እኛ አረቦች ነን ይላሉ። ሌሎችም እንዲሁ።እናም ለጥቅም ሳይሆን ለማንነት አፍሪካዊ ነኝ የምትል ኢትዮጵያ ብቻ በመሆኗ ይህንን ማስጠበቅ ላይም መስራት ያስፈልጋል።እርሷን ለሚፈልግ ሁሉ መድረስም ይገባል።ድፍን አፍሪካ አቢሲንያ ሲባል እንደነበረ በማስታወስ ኢትዮጵያውያን አፍሪካዊነታቸውን ሊያጎሉ አፍሪካውያን ደግሞ አንድነታቸውን ከፍ ሊያደርጉ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- አገራዊ አንድነት በአድዋ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ይህ እይታ ከአመራር ጥበብ ጋር ይያያዛል።አገር መሪዋን ትመስላለች የሚባለውን የሚያሳይ ነው።እናም በጊዜው የነበሩ መሪዎች ምን ያህል ተሰሚነት ነበራቸው ሲባልም በአንድ አዋጅ ያ ሁሉ ክተት ሰራዊት ሲደረግ ማየት የተቻለበት ነበር።ከመሪ ስነልቦና አንጻር ደግሞ በትህትናም፣ በፍቅርም በእምነትም የጠነከሩ እንደሆኑም በግልጽ የሚታይበት ነው።ለዚህም ማሳያው ጥሪ ሲያደርጉ እንኳን ‹‹ አልበደልኩህም፣ ማርያምን አልምርህም ›› ብለው መጥራታቸው ነው።
ቁርሾው ለነገ ያሉትም የእምነታቸው ጥንካሬና የአገር ወዳድነታቸው ያመጣው እንደሆነ ይሰማኛል።ምክንያቱም በእነሱ ጊዜ ኢትዮጵያ የአስራት አገር ነችና እግዚአብሔር ይጠብቃታል።በዚህም ታቦታቱን ይዘን ዘመተን እናሸንፋለን፤ የእርሱን አገር ካስደፈርን ደግሞ ችግር ውስጥ እንገባለን ብለው በማመንም ወደ ጦርነቱ ገብተዋል።የሚፋለሙትም ለህዝብ ብቻ ሳይሆን አስራት ተሰታለች ብለው ለሚያምኗት ማርያምም ነው።ይህ እምነታቸው ደግሞ ድል አድርጎላቸዋል።ነገሩ ከዚህም የላቀ እንደሆነ አምናለሁ።በመሆኑም በስነልቦና ምን ነበሩና ኢትዮጵያዊያን እንዴት አሸነፉ የሚለውን በደንብ ማጥናትና መመርመር ያስፈልጋል።እነርሱ ከበፊት የተሰራባቸው ነገር ስላለ አገሬ እንዳሉ ሁሉ እኛም አገሬ የሚል ትውልድ መፍጠር ላይ ዛሬ መስራት አለብን።
አገር የሚለው ነገር አዕምሯቸው ውስጥ የተቀመጠላቸውና መጠበቅ እንዳለባት የሚረዱም ናቸው።አሁን እየፈረሰብን ያለው እርሱ ነው።ለዚህ ደግሞ በተደጋጋሚ ስድብ እንጂ ይህንን ሰርታለች የሚሉ ኢትዮጵያን በትውልዱ ልብ ውስጥ አልፈጠርንም።በተለይም ለዚህኛው ብሔር አልሆነችም፣ አትሆንም እየተባለ ሲነገር መቆየቱ አገራዊ ፍቅር እንዳይኖርና አገራዊ አመለካከታችን እንዲዛባ አድርጓል።ይህ ደግሞ ነገ ሱማሌ ተነካ ሲባል ምን አገባኝን ያመጣል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንጻር ዛሬ ላይ ስለ አገራዊ አንድነት ያለን ስነልቦና እንዴት ይታያል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ዛሬ ላይ ሁለት ትግሎች አሉ።ኢትዮጵያዊነት ስሜት ከአዕምሯችን ውስጥ በቀደመው ልክ ማስረጹ፣ አገርን የመጠበቅ፣ የመወደድና ቅድሚያ ለአገር መስጠት የሚለው ነገርን ከልብ ማኖር የሚሉትን የያዘና በተቃራኒው ያንን ለማፍረስ የሚሰሩ ፖለቲከኛና አገር ጠል ሰዎች አሉ።ይህ ደግሞ ተደጋግሞ ሲሰራ ወደ ማመኑ የሚገባበት ሁኔታ ይመጣል።ዛሬ እየታየ ያለውም ይኽው ነው።ምክንያቱም እነዚህ ተግባራት ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።በዚህም ኢትዮጵያ የሚለው አስተሳሰብ የጥቂት ተጠቃሚዎች አስተሳሰብ እንደሆነ ሆኖ ይታሰባል።ይሄ አገራዊ እሳቤውንም ይስታል።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እሳቤ ሲነሳ ደግሞ አሃዳዊ ናቸው ሚል ስያሜ ይነሳል።ክልሎች ፈርሰው አንድ አገር ለመመስረት የተነሱ ናቸው ወዘተ ይባላል።የክልሉን ተጠቃሚነት ሊነጥቁ ነው በሚልም ለማስነሳት ይሞክራሉ።ስለዚህ ይህንን ድል ሊያደርግ የሚችል ስራ መስራትም ያስፈልጋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ድህነታችን ጭምር ኢትዮጵያዊነትን ቀንሶብናል የሚል ምልከታ አለኝ።አውሮፓውያን ልጆቻቸው እስኪያድጉ ድረስ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸው ያውቃሉ፤ መንግሥትም ቢሆን በነጻ መሰረታዊ ፍላጎትን ማሟላት ግዴታው ነው።ስለሆነም የምግብ ጉዳይ፣ የመጠለያና የጤና ጉዳይ የእርሱ አይሆንም።ይህንን ሳያስብ ያደገ ደግሞ አገሩ ብዙ ነገር እንደዋለችለት ያስባል።ለዚህ ደግሞ ዋጋ መክፈል እንዳለበት በማመን ወደ ሥራ ይገባል።እኛ ጋር ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው።ሳይበላ ስለሚያድር ጉዳዩ ምግብ ነው፤ ሥራ ስለሌለው የሥራ ጉዳይ ያሳስበዋል።ስለዚህም መሰረታዊ ፍላጎትን እንኳን ለማግኘት ብዙ መልፋት ግድ ነው።ይህም ሆኖ የስራ እድል አያገኝም።ይህ ደግሞ ሌላ አገር ናፋቂ ያደርገዋል።
አገሬ ለፍቼላት እንኳን አልጠቀመችኝም ይላታል።በመሆኑም ድህነት ሲያስመርረው ሁሉን ትቶ ለመሄድም ይቋምጣል።መንግሥት 200 ዜጎችን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገባ በግድ አሽከራችሁ ካላደረጋችሁኝ እያለ 500 በመርከብ ይጓዛል።ያውም ከሞት ተርፎ መስራት ከቻለ ነው።እናም ይህ አስተሳሰባችን ካልተቀየረ አገር ወዳድነትም ሆነ ስለ አገር ማሰብ በፍጹም ሊመጣ አይችልም።ወጣቱን በስራ ወጥሮ አዕምሮው ባተሌ እንዲሆን ካልተደረገም የሚሰራ አዕምሮ ሊኖር አይችልም።ስለሆንም ይህንን ነገር ለማሳካት የሚያስችል ተግባር መከወን አለበት።በተለይም መንግሥት አጉልቶ ማገዝም ያስፈልጋል።ህዝቡም ቢሆን እንደመንግሥት የሚሰራውን ኢትዮጵያዊነት መደገፍ ያስፈልጋል።ይህ ደግሞ ፖለቲከኛ መሆን አይደለም፤ መማርንም አይጠይቅም።ዋናው አገር መውደድ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አገራዊ ነጻነት ባለው እና ነጻነት በሌላው ህዝብ መካከል የሚኖረው የስነልቦና ውቅር ልዩነት እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- የመጀመሪያው ቅኝ ግዛት አሁን በአካል ቀርቷል።ነገር ግን የአዕምሮ መገዛቱና አለመገዛቱ ዛሬም አብሮን እየኖረ ይገኛል።ለአብነት ወጣቱ የአዕምሮው ቅኝ መገዛት በተለያዩ ፊልሞች መያዝ፣ ወደሌላ አገር የመሄድ ጉጉት፣ የትኛውም አገር ከኢትዮጵያ ይበልጣል ብሎ ማሰብ፣ ከኢትዮጵያ መውጣት ብር የሚታፈስበት እና ልዩ ጥቅም እንዳለው አድርጎ መታመን አምጥቷል።
የሰው ስብዕና የሚባለው ከሶስት ነገር የተገነባ ነው።የመጀመሪያው ስሜታችንን የምናንጸባርቅበት ድርጊት በሙሉ ስብዕናን የምናይበት ነው።ሁለተኛው የእውቀት ልኬታችንና ምልከታችን ሲሆን፤ ሶስተኛው ባህሪያችን ነው።እናም ስብዕና የሚጎዳው በልጅነት በሚሰሩ ሥራዎች ነው።በራስ የመተማመን አለመኖር፣ ፍራቻና አንተ አትረባም እየተባሉ ማደግ በማንነት ላይ ጠባሳ ስለሚጥል ሲያድጉ የስነልቦና ቀውስ እንዲያጋጥማቸው ያደርጋል።የመምህራን ቁጣም እንዲሁ።ስለዚህ ስውሩና ንቁው አዕምሮ በተለያየ ነገር መጎዳት ሲያጋጥመው የሚመጣ ነው።የአዕምሮ ስብራት።
ስውር አዕምሯችን ውስጥ የሚጠራቀመው ነገር አስገራሚ ነው።ማንም በቀላሉ ሊረዳውም የሚችል አይደለም።ነገር ግን በህጻንነት የተነገረንን በማውጣት ዛሬ ለቆምንበት መሰረት ነው።በዚህም የስነልቦና ስብራት በብዙ መልኩ ሊመጡ ይችላሉ።እነዚህ ደግሞ የተለያዩ ሲሆን፤ ጭንቀት፣ ድብርት፣ ደስተኛ አለመሆን የመሳሰሉትን ማንሳት ይቻላል።እነዚህ ደግሞ የሰውን ልጅ ከመኖር አለመኖር ይሻላልን እስከማስመረጥ የሚደርሱ፤ የሚያሳብዱም ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በህክምና ደረጃ ስነልቦና ቀውስን ለመመለስ ምን ምን ነገሮች ተግባራዊ ይሆናሉ? ምን ያህልስ ውጤታማ ናቸው ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ሥራው የሚሰራው በስነልቦና ህክምና እና በአዕምሮ ህክምና ባለሙያዎች ነው።በዚህም እነዚህ ባለሙያዎች በተለያየ መንገድ ህክምናውን ይሰጣሉ።ከእነዚህ መካከል ሳይኮ ቴራፒ የሚባለው ነው።ይህም መጀመሪያ ምክር አገልግሎት ሲሰጣቸው ችግራቸውን ለማግኘት የሚሉትን ማዳመጥ ነው።ከዚያ ሁኔታው ችግራቸውን በመተንፈስ የማይፈታ ከሆነ ቀጣዩን ደረጃ እንዲከተሉ ይደረጋል።ነገር ግን ብዙዎቹ ችግሮች የውስጣቸውን ጭንቀት ባለሙያው ሳይሰለች ሲያዳምጣቸውና እነርሱም ደስተኛ ሆነው ሲናገሩ ይጠፋሉ።
ሌላው የህክምና አይነት እነርሱ የማያውቁት ችግር ሲያጋጥማቸው የሚመጣ ሲሆን፤ ይህም ከመጠን በላይ መጨነቅ ነው።እናም ችግሩ ራስምታት፣ የጨጓራ ህመምና ሌሎች ነገሮችን ስለሚያመጣ በምርመራ የሚገኝ ላይሆን ይችላል።የዚህን ጊዜ የቀደመ ታሪካቸውንና የአኗኗራቸውን እንዲሁም የቤተሰብ ሁኔታቸውን በጥበብ ጠይቆ እንዲያወሩ ይደረግና ችግሩ ምን ላይ እንደሆነ ለመረዳት ይሞከራል።የተባሉትን ማድረግ ካቆሙ በሽታውም ይተዋቸዋል።ስለዚህ የስነልቦናው ችግር ደረጃን ማየት አንዱ የመፍትሄ አቅጣጫና የህክምና ዘዴ ነው።ብንዘረዝራቸውም በርካታ ናቸው።እነዚህ ደግሞ በተግባር ከዋሉና ማህበረሰቡ በአግባቡ ከተጠቀመባቸው ውጤታማ መፍትሄ ይሰጣሉ።ሆኖም ምክር ፈልገው ወደ ባለሙያው የሚሄዱ ሰዎች በጣም ጥቂት ብቻ ሳይሆኑ የሉም በሚባል ደረጃ ላይ የተቀመጡ ናቸው።
ብዙዎች በዚህ ህመም ቢሰቃዩም የአመለካከት ለውጥ ባለመምጣቱ መታከምን አይፈልጉም።ይህ ህክምና ያስፈልጋችኋል ሲባሉም እብድ መሰልኩህ ብለው እስከመሳደብ ይደርሳሉ።እናም ህክምናው በተገቢው ሁኔታ ለሚፈለገው ሰው እየተሰጠ ነው ለማለት ያስቸግራል።በርካታ በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ የተማሩ ባለሙያዎችም ቢሆኑ ሥራ አጥ በመሆናቸው ሙያውን እንዲቀይሩ ይገደዳሉ።ይህ ደግሞ የባለሙያ እጥረት ጭምር እንዲያጋጥምም ያደርጋል።በአጠቃላይ ዘርፉ ውጤታማ ሰውን የማዳን ሥራ ቢሰራም የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊና ጠባብ በመሆኑ ግን ተፈላጊውን ውጤት አላመጣም የሚል እይታ አለኝ።የምክር አገልግሎት ችግርን ማየት ነው።ለችግር መፍትሄ ማግኘትም ነው።ስለዚህም ይህንን ማሰብ ለሁሉም ያስፈልጋልና ብንጠቀምበት እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ዛሬ ያለው ትውልድ ብዙ ታሪክ ተቀምጦለት ከዚያ ሲማር አይታይም።ለምንድነው ይላሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ሁሉም አገሮች አሳዛኝ ታሪኮች አሏቸው።ነጮቹ ከአውሮፓ ሄደው አሜሪካን ሲመሰርቱ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አይደለም።ኢንዲያን የሚባሉ ነባር ዝርያዎች ነበሩ።እነርሱን ብዙ ነገር በማድረግ ነው የዛሬዋን ገናና አገር የመሰረቱት።ይህንን ግን በፍጹም አያነሱትም።ከዚያ ይልቅ ገናና የነበሩ ታሪኮች ይተረካሉ።ጨለማ የነበረው አልፏል ማን ብርሃን ሰጠኝ የሚለውንም ነው የሚያጎሉት።ለምሳሌ እንደ ጆርጅ ዋሽንግተን፣ እነአብርሃም ሊንከን አይነት ሰዎችን ነው ጀግናችን እያሉ የሚያወሩት።ስለእነርሱ ሲናገሩም የአገራችን መስራቾች በሚል ነው።እነዚያ አባቶች ግን በርካታ ጥፋቶች አጥፍተው ነበር።ሆኖም ስለጥፋታቸው ሳይሆን ስለሰሩት ጀግንነት፤ ስለመልካም ታሪካቸው ብቻም ነው የሚተርኩላቸው።እኛ ጋር ግን በተቃራኒው ነው የሚወራው።መልካም ነገራቸውም አይነሳም።
አባቶቻችን ከጥፋታቸው ይልቅ መልካምነታቸው የበዛ ነው።ሆኖም በጣም ጥቂት ስህተታቸው ከታሪክ እየተመዘዘ ያባላናል። ለመበጣበጫም መሰረት ይሆናል።አንዳንዱ ደግሞ ያላደረጉት ጭምር ተፈጥሮ ለጸብ ማማሟቂያ ይጨመራል።በጦርነት ብዙ ነገሮች ሊደረጉ ይችላሉ።ነገር ግን ቂም የሚያዝበት አይሆንም።እነርሱ ትተውት ያለፉትን ጭምር እኛ አንስተን እንባላበታለን።ይህ ደግሞ ስለነገስታት ለማውራት ጭምር አስፈሪ እንዲሆን አድርጓል።መልካም ታሪካቸውን ለመናገርም አንተ የእንትና ወገን ነህ አለበትና እንዲዳፈንም እንፈቅዳለን።
በአገር ደረጃ ታሪክን ማወቅ ሳይሆን የጋራ ጀግና እንዳይኖረን መስራት የነበረበት በመሆኑ ማጠልሸት እንጂ መገንባት ትኩረት አልተሰጠውም።አንዳንድ ጊዜ እንደውም ስለ ነገስታቶቻችን ታሪክ ሲነሳ ሌላ የማይታወቅ ጭምር ይመስላል።ራስን መጠራጠር ውስጥም ይከታል።ያላነበብንና ያልሰማንም እንደሆንን እንዲሰማን ያደርጋል።ስለዚህም ይህ ነገራችን እስካልተለወጠ ድረስ ትውልዱ ከታሪኩ ተምሮ የነገ ታሪኩን ሊያስተካክል አይችልም።በመሆኑም ታሪክ ለትውልዱ የምንነግርበትን ሁኔታ ማስተካከል ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- መፍትሄውስ ምን ይሆን?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ወጣቱን ከአዕምሮ ቅኝ ግዛት ማውጣት፤ ታሪክን እንዲያውቅ፣ እንዲማረውና እንዲኖረው ማድረግ፣ አገር ወዳድነትን ከልብ ማስተማር፣ ሥራ ሰጥቶ ድህነትን እንዲያሸንፍ እንዲሁ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያመጣ ማበርታት ያስፈልጋል።የጋራ ጀግኖች እንዳሉን ማሳየትና ከስህተቱ እንዲማር መስራትም ይገባል።ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ ሰዎችን ማብዛት፣ መደገፍና ከስኬት ማማ ላይ የሚደርሱበትን መንገድ መጥረግም ጠቃሚ ነው።የአመለካከት ለውጥ ላይ ሁሉም ሰው መስራት መቻልም መፍትሄ ያመጣል።
አዲስ ዘመን፡- ቀረ የሚሉት እና የሚያስተላልፉት መልዕክት
ዶክተር ወዳጄነህ፡- አድዋ ዘንድሮ የተለየ ትርጉም ተሰጥቶት ወሩን ሙሉ መከበሩ ይበል የሚያሰኝ ነው።በቀጣይ ደግሞ በሽታውን አጥፍቶልን ፤ሰላምና መረጋጋቱን ሰጥቶን ከአፍሪካ ወንድሞቻችን እንዲሁም ከዓለም ማህበረሰብ ጋር እንድናከብረው አምላክ ይፍቀድልን።ምክንያቱም ይህ በዓል የዓለምም ጭምር ድል ነውና እነርሱም ስለሚያጓጓቸው አህጉራዊ እንዲሁም አለምአቀፋዊ ማድረግ ላይ መስራት ይኖርብናል እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ በጣም እናመሰግናለን።
ዶክተር ወዳጄነህ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013 ዓ.ም