
ትውልዱ ወርቃማ ታሪክ ከጻፈባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋነኛው ነው:: መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመሰረት ድንጋይ ከጣሉበት ቀን ጀምሮ፤ መላው ኢትዮጵያውያን በቻሉት አቅም የግድቡን ግንባታ ሲደግፉ ቆይተዋል:: አንድ ብር ከውጪ ዕርዳታም ሆነ ብድር ያልተገኘበት ይኸው ግድብ፤ ብዙ ፈተናዎች አልፎ ሪቫኑን ለመቁረጥ ጫፍ መደረሱን መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አብስረዋል::
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፤ “ብዙ ፈተና አይተንበታል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል። የግንባታ ግብዓቶች ተገዝተው በማጓጓዝ ግድቡ እስካለበት ሥፍራ ማድረስ፤ ከውጭ ጫና ጋር ተደማምሮ “በጣም አስቸጋሪ” እንደነበርም አስረድተዋል።
14 ዓመታት ገደማ የወሰደ ይኸው ግድብ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተጠቆመው የግንባታ ሥራው ሲከናወን ብቻ ሳይሆን እስከማጠናቀቂያው ድረስ፤ ብዙ ውጣ ውረዶች ታልፈውበታል:: በተለይ ግብፅ እና ሱዳን ይፈጥሯቸው የነበሩ አንዳንድ ውዝግቦች እየታለፉ የተሔደባቸው መንገዶች እና የተገኘው ውጤት ሲታሰብ ለማመን የሚያስቸግር አስደናቂ ነው ብሎ ለመናገር ያስደፍራል።
የዓለም ትልልቅ አበዳሪዎች እና ዕርዳታ ሰጪዎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ)ን የመሳሰሉ ተቋማት የግድቡ ግንባታ የሚደግፉ ብድር እና ዕርዳታዎች እንዳይሠጡ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የግብፅ ሴራ ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም:: ይሁንና ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ማጣቱ እንደውም የኢትዮጵያን ሕዝብ አጠንክሮታል::
የመሠረት ድንጋይ መጣሉን ተከትሎ ከውጭ ያለውን ግፊት እና ጫና በመረዳት ኢትዮጵያውያን ላባቸውን እና ደማቸውን እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል:: በቂ ፋይናንስ ባይኖርም ኢትዮጵያውያን ለጦርነት ብቻ ሳይሆን ለልማትም መረባረብ እንደሚችሉ ያሳዩበት ስኬት ነው:: ለልማት መረባረባቸው በራሱ የአንድነት እና የሕብረት ስሜትን በመፍጠር በኩል የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተጫወተውን ሚና መግለፅ ይቻላል::
በተጨማሪ በግድቡ የግንባታ ሂደት ግብፅ በብዙ መልኩ ግድቡን ለማደናቀፍ ሞክራለች:: የግድቡ መገንባት በጅምር ላይ ሆኖ፤ ለመደብደብ እና ለማውደም ማቀዷን የኢትዮጵያ መንግሥት ደርሶበታል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ረብሻ በማስነሳት ሀገሪቱን በማመስ እና በማተራመስ ሀገር መረጋጋት አቅቷት ግንባታው እንዲቋረጥ አስበው ይሠሩ እንደነበር ማወቅ ተችሏል:: በተጨማሪ በግንባታው ላይ ያሉ ባለሞያዎችን በማማለል ለማደናቀፍ ሲሞክሩ ሴራቸው በመረጃ ተደግፎ በቀጥታ በቴሌቪዥን ተላልፏል::
ኢትዮጵያ ለግብፃውያን የሕዳሴው ግድብ የምትገነባው ግብፅን ለመጉዳት አለመሆኑን በማሳወቅ፤ ‹‹ግድቡ ጉልህ ጉዳት አያደርስባችሁም፤ ለዚህም የባለሞያ ቡድን አቋቁማችሁ ማጥናት ትችላላችሁ›› የሚል እጅግ ቀና መልዕክት አስተላለፈች:: ይሁንና ግብፅ በተቃራኒው የኢትዮጵያን እድገት እና ልማት በመልካም መልኩ ለማየት እና ለመቀበል አልወደደችም።
ለግብፃውያን በተለያየ መንገድ በተደጋጋሚ፤ ‹‹ የሚያጣላ፣ የሚያጨቃጭቅ፣ እዚያ እና እዚህ ገንዘብን የሚያስበትን ጉዳይ የለም። በትብብር በጋራ ቢሠራ፤ ሁለቱ ሕዝቦች እና ሀገሪቷ ተጠቃሚ ይሆናሉ::›› ቢባሉም ግብፆች ቀና ምላሽ ለመስጠት አልፈለጉም። ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ነበሯቸው:: የመጀመሪያው ለጥቁር ሕዝቦች ለአፍሪካውያን ካላቸው ዝቅተኛ አመለካከት የተነሳ ነው።
ሌላው የግድቡ መገንባት ኢትዮጵያን ያለማታል:: ይህ ደግሞ በአፍሪካ እና በዓለም ተቀባይነቷን ያሳድገዋል:: በቀጣይ ዓባይን የመጠቀም አቅሟ ይጨምራል:: የሌሎች የተፋሰሱ ሀገሮች ዐይን ይገለጣል። የሚል መነሻም ነበራቸው:: ሆኖም ግብፆች ለማደናቀፍ ምንም ዓይነት ምክንያት ቢኖራቸው ውሃ የሚያነሳ ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም::
ባሰቡት መንገድ አልሳካ ሲላቸው ወደ ድርድርም ገብተው ነበር:: በድርድሩ ግብጻውያኑ መነሻ አድርገው ሲከራከሩ የነበረው የቅኝ ገዢ ውሎችን በመጥቀስ ናይልን የመጠቀም ዓለም ዐቀፍ መብት የእነሱ ብቻ እንደሆነ በመግለፅ መጀመራቸው የሚዘነጋ አይደለም። እ.ኤ.አ. በ1891 የተካሄደውን ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን የዓባይ ወንዝን በተመለከተ ያካሄዱትን ስምምነት እያነሱ አሰልቺ ክርክር ሲያካሂዱ ቆይተዋል::
እ.ኤ.አ. በ1902 የእንግሊዝኛው እና የአማርኛው ፍቺዎች የተለያዩ በመሆናቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ያላጸደቀውን ስምምነት እየጠቀሱ ለመከራከር ሞክረዋል:: በተጨማሪ በተለይ ለግብፅ በናይል ወንዝ ላይ የሚሠራ ግድብ ድምፅ በድምፅ የመሻር መብት እስከማጎናጸፍ የሚደርሰውን እና ግብፅ እና ሱዳን ጠብታ ውሃ ሳያስቀሩ ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው የተከፋፈሉባቸውን የ1929 እና የ1959 ስምምነቶችን ለታሪካዊ መብት ዋነኛዎቹ መነሻዎቻቸው እንደሆኑ ደጋግመው ሲገልፁ ነበር::
ግብፃውያን ብቻ ሳይሆኑ ሱዳኖችም ከላይ ያሉትን ስምምነቶች እየገለፁ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል በተከታታይ ለቀናት በተለያዩ ጊዜያት ዓመታትን የፈጁ ውይይቶች አካሂደዋል:: ኢትዮጵያውያን ትልቅ ጭቅጭቅ የነበረበት፤ አንዳንዴም ግብፆች ረግጠው እየወጡ ተለምነው እየገቡ ንግግር የሚካሔድበትን ሁኔታ በትዕግስት እና በብልሃት ማለፋቸው ግብፆችን አበሳጫቸው::
በሶስትዮሽ የሚካሔደውን ውይይት አልፈው የተባበሩት አረብ ሊግ ሀገራትን ተጠቅመው መግለጫ በማስወጣት ለማስፈራራት ሞከሩ:: ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ለመውሰድም ያደረጉት ጥረት የተሳካ ውጤት አላመጣም:: በኢትዮጵያ መንግሥት ብዙ ጥረቶች ተደርገው ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ሕብረት ተመለሰ::
ይህ ሁሉ እየተከናወነ በ2012 ዓ.ም በሐምሌ ወር ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት መከናወኑ ይፋ ሆነ:: በግድቡ ግንባታ ቀጥታ ከተሳተፉት በተጨማሪ፤ ድርድሮችን እና ውይይቶችን ያካሔዱ ምሁራኖች፤ ለግድቡ ግንባታ በተደጋጋሚ ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በማበርከት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዲከናወን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ የነበሩ መላው ኢትዮጵያውያን የጋራ የደስታ ባሕር ውስጥ ተዘፈቁ:: የውሃው ሙሊቱ ኢትዮጵያ በምትፈልገው መልኩ የታችኞቹን የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያስከትል በየዓመቱ ተካሄደ:: በተሳካ መልኩ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ ተቻለ።
ግድቡ በሙሉ አቅም ኃይል ማመንጨት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ:: የዘርፉ ምሁራኖች እንደሚያመላክቱት፤ ይህ እጅግ ብዙ ትርጉም ያለው ነው:: ከኢኮኖሚ አንፃር በዋናነት መታየት ያለበት የሚመነጨው የኃይል መጠን ወይም ኃይሉ ተሽጦ የሚገኘው ገቢ ብቻ አይደለም:: በእርግጥ ይህ ጥቅም ኢትዮጵያ ካለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም ለውጭ ከምትልከው ውስን ምርት አንፃር የሚናቅ አይደለም:: ይሁንና ኃይል ከማመንጨት ጋር ተያይዞ የሚገኙ ሰፊ ጠቀሜታዎች መኖራቸውም መታየት አለበት::
የመጀመሪያው ምንም ዓይነት ፈተናዎች ቢበዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተባበረ ክንድ በጋራ በመነሳት ትልቅ ተዓምር መሥራት እንደሚችል ለዓለም ያሳየው ስኬት ነው:: ይህ ከፖለቲካም ሆነ ከኢኮኖሚ አኳያ የሚኖረው ትርጉም ሰፊ ነው:: ለኢትዮጵያውያን እርዳታ እና ብድር መከልከል ራስን ትዝብት ላይ ከመጣል ውጪ ትርፍ እንደማይኖረው ያመላክታል:: በሌላ በኩል መንግሥት በቀጣይነት ትልልቅ ግድቦችን ለመገንባት ለሚያስተላልፈው ውሳኔ ትልቅ ግብዓት ይሆናል::
በዝርዝር የግድቡ ስኬት ሲታይ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ከጤና፣ ከትምህርት እና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በሰፊው ይያያዛል:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያገኘው የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የኤሌክትሪክ ኃይል የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው:: የጤና ማዕከላት ላይ አገልግሎትን ለማቀላጠፍም ሆነ የተስተካከለ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል:: የምሽት እና የለሊት ሥራዎችን ለማከናውን ከመብራት ጀምሮ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር፤ በተለይ ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ በማሽን ለሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችም የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስገኘው ጠቀሜታ በቀላሉ የሚዘረዘር አይደለም::
ከትምህርት ጋር በተያያዘ መምህራኖችም ሆኑ ተማሪዎች ለዘመኑ የሚመጥን ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ዕውቀታቸውን ለማስፋትም ሆነ ለማስተላለፍ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው:: በሌላ በኩል በተለያየ መልኩ በየወረዳው እና በየዞኑ በየክልሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች የተቀላጠፉ እና ዘመናዊነትን የተከተሉ በማድረግ በኩል የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው::
ለኢንዱስትሪ መስፋፋት የኃይል መጠን በቂ መሆን የሚኖረው አስተዋፅኦም እንዲሁ ነጋሪ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም:: በብዛት ማመንጨት ከተቻለ ኃይል አጥተው የሚቸገሩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች አይኖሩም:: ይህ ኢንደስትሪውን ከማነቃቃት በተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው:: እነዚህ በሙሉ በዝርዝር ሲታዩ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት ላይ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ መኖሩ ክርክር ውስጥ የሚገባ አይደለም::
የሚመነጨው ኃይል ከኢንደስትሪ በተጨማሪ ለግብርና ዘርፍም ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ የሚካድ አይደለም:: በመስኖ ለማልማት ኤሌክትሪክ ካለ በግፊት ኃይል የሚንቀሳቀሱ ማሽኖችን መጠቀም ይቻላል:: መስኖን ማልማት ደግሞ ከምግብ ዋስትና ጋር የተያያዘ ነው:: በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዝ ሌላኛው መሳሪያ ነው ማለት ይቻላል::
ሆቴሎች እና ሌሎች የቱሪስት ማዕከሎችም ኃይል ይፈልጋሉ:: ቱሪስትን ለመሳብ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ግድቡ የራሱን ሚና ይጫወታል:: ለእነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ ጠቃሜታ ከፍተኛ ነው:: ከግድቡ ጀርባ የተኛው ውሃ ለአሳ ምርት የሚያገለግል ሲሆን፤ አካባቢው ላይ ደሴቶች መኖራቸውን ተከትሎ ለቱሪስት መስዕብ በመሆኑ በቱሪዝም ዘርፍ የሚኖረውን አበርክቶ መጥቀስ አያዳግትም::
እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ምክንያት አብዛኛው ሕዝብ ከጨለማ ሊወጣ የሚችልበት ዕድል ይፈጠራል:: ይህ ጨለማን በብርሃን የመተካት ጉዞ ድንበር አካባቢ ላሉ ጎረቤት ሀገራት ሕዝቦችም የሚያተርፍ መሆኑ ሲታሰብ፤ ኢትዮጵያ ኃይል በመሸጥ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ በተጨማሪ ቀጠናዊ ትስስር በመፍጠር ሊኖራት የሚችለው ፖለቲካዊ ትርፍ የትየለሌ ነው::
እነዚህ ከላይ የተገለፁት እና ሌሎችም ያልተገለፁ የግድቡ ጥቅሞች ሲታሰቡ፤ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ነው ለማለት ያስደፍራል:: የግድብ መጠናቀቅ በእርግጥም ኢትዮጵያን ወደ ቀደመው ገናንነቷ የሚመልስና ከስልጣኔ ማማ የሚያደርሳት ማስፈንጠሪያ ይሆናል ለማለት ያስችላል:: ይህን ያልነው ያለምክንያት አይደለም ከላይ ከተገለፁት ጥቅሞች ባሻገር የአሜሪካንን መስፈንጠሪያ ግድብ በማየት ነው::
የአሜሪካው ሁቨር ግድብ እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1930ዎቹ በአሜሪካ ተከስቶ የነበረው የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት የተገነባ ግድብ ነው። ግድቡን ለመገንባት በ10 ሺሕ የሚቆጠሩ አሜሪካዊያኖች ተሳትፈዋል:: በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰውተዋል። ግድቡ ለኔቫዳ፣ ለአሪዞና እና ካሊፎርኒያ ለመሳሰሉ የምእራብ ግዛቶች ዋነኛ የኃይል ምንጭ ነው:: በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎች መናኽሪያ በመሆን ለአሜሪካ ብልፅግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ብዙዎች በሠጡት ምስክርነት ሁቨር ግድብ ለአሜሪካ ስኬት አሰተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር:: ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብም ኢትየጵያን ወደ ሥልጣኔ ማማ በመመለስ ወርቃማ ታሪክ ያፅፋል የሚል ተስፋን መሰነቅ ይቻላል::
የዘርፉ ምሁራን እንደሚያሳስቡት፤ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ብዙ ፈተናዎች ታልፈው በጥሩ መልኩ የተጠናቀቀ ነው:: አንድነትን በማጠናከር የግድቡን ግንባታ ማሳካት እንደተቻለው ሁሉ፤ የተሻለች ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የታየውን አንድነትና ተነሳሽነት በሌሎች የልማት መስኮች መድገም ይገባል:: የዚህ ግድብ ታሪክ በወርቅ መዝገብ ሰፍሮ ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገር፤ ግድቡ ለዜጎች የሚያስገኘውን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚመለከተው አካል በሙሉ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም