ጽንሰሃሳብን ከተግባር ያዋደዱ አምራች እጆች

ሥራ ላይ በማተኮር ከዝቅታ ዝቅ ብሎ የጀመረ ከከፍታው ከፍ ማለቱ የማይቀር ነው። እርግጥ ነው፤ ከከፍታው ከፍ ለማለት ብዙ ጥረትና ትጋት ይጠይቃል። ከብዙ ጥረትና ትጋት አስቀድሞ ታድያ ሰዎች ስለሚሠሩት ሥራ ካላቸው ውስጣዊ ፍላጎት ባለፈ ዕውቀት፣ ክህሎትና ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ። በተለይ ቢዝነስ ‹‹ሀ›› ብለው የሚጀምሩ ሰዎች የሚሠሩትን ጉዳይ ጽንሰሃሳብን ከተግባር ልምምድ ጋር ካገናኙ፤ ክትትልና ድጋፍ ካልተለያቸው ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ ይታመናል። ለዚህም የንግድ አማካሪ ድርጅቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው።

ከተመሠረተ አስር ዓመታትን ያስቆጠረው አዲስ ዕይታ የንግድ አማካሪ ድርጅት፤ በሀገሪቱ ከሚገኙ የንግድ አማካሪ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው። ድርጅቱ ከተለመደው የማማከር ሥራ ባለፈ እሴት ጨምሮ እንደመጣ ይነገርለታል። ድርጅቱን ከመሰረቱ ሶስት በተለያየ ዘርፍ ከሰለጠኑ ባለሙያዎች መካከል አቶ ክብረት አካሳ ቀዳሚ ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ክብረት፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሕግ አግኝተዋል። ከሁለት ተመሳሳይ ራዕይ ካላቸው ጓደኞቻቸው ጋር የጀመሩት የማማከር ሥራ እያሰፋ በአሁኑ ወቅት 30 አባላት ደርሰዋል። እያንዳንዳቸው የተለያዩ የሙያ ባለቤቶች ናቸው። በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ወደ ድርጅቱ ለሚመጡ ደንበኞች የማማከር፣ የማስተማርና የተግባር ስልጠና የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። የሚሰጡት ቢዝነስ የማማከር አገልግሎትና ስልጠና ታዲያ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ውጤቱን መመልከት ችለዋል።

በአዲስ እይታ ውስጥ የማማከርና የማስተማር ኃላፊነት ያለባቸው አቶ ክብረት፤ የቢዝነስ፣ የሥነልቦናና የሕግ አማካሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ማንኛውም ቢዝነስ በዕውቀት፣ በጥናትና በባለሙያዎች ምክር መጀመር እንዳለበት ያምናሉ። ለዚህም የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። የድርጅቱ አባላት በሙሉ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው። በሀገሪቱ ከሚገኙና ከተለመዱት የንግድ አማካሪዎች ለየት ባለ አቀራረብ መምጣታቸውም በዚሁ ምክንያት ነው። ይህም ሲባል ጽንሰሃሳብን ብቻ ከማማከር ባለፈ የተግባር ልምምድን ጨምሮ ስልጠና ይሰጣሉ። በዚህም ድብልቅ የማማከር አገልግሎትን ለደንበኞቻቸው በመስጠት በርካቶችን ውጤታማ ማድረግ ችለዋል።

በሀገሪቱ በስፋት የተለመደው ንግድ ወይም ቢዝነስን የማማከር ሥራ ጽንሰሃሳቡን ብቻ ማስረዳትና ማማከር ነው። አዲስ ዕይታ ግን ጽንሰሃሳብን ከተግባር ጋር በማዋደድ ደንበኞቹ በፈለጉት የሙያ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሚታይና በሚጨበጥ ነገር ያምናል የሚሉት አቶ ክብረት፤ አዲስ እይታም የተከተለው ይህንኑ እንደሆነ አስረድተዋል።

አብዛኛው ንግድ ውስጥ የተሰማራ ሰው ንግድን እየሠራ ያለው በልምድ ማለትም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ በአሁን ወቅት አያዋጣም። ምክንያቱም ጊዜው በፍጥነት እየተቀየረ በመሆኑ አዳዲስ እይታዎች ይፈለጋል። እስካሁን የነበረው የንግድ ሥርዓት ‹‹ሬድ ኦሽን›› ስትራቴጂ ነው። ይህ ማለት ባሕላዊ በሆነ መንገድ የሚከወን የንግድ ሥርዓት ሆኖ አንድ ሲደመር አንድ ሁለት እንደማለት ነው። ይህ አይነቱ ፍልስፍና አብቅቶለታል። ስለዚህ ከወቅቱ ጋር ሊስማማ የሚችል አዲስ እይታ አስፈልጓል ይላሉ፡፡

ለዚህም አሁን ላይ ‹‹ብሉ ኦሽን›› የሚል ስትራቴጂ መጥቷል። ይህ ደግሞ አንድ ሲደመር አንድ ሶስት ማለት ሲሆን፤ ይህ ፍልስፍና አዲስ አመለካከት አዳዲስ እይታዎችን የሚፈልግ አዋጭና ተመራጭ ነው። ዋና ዓላማውም ቢዝነስ ውስጥ አዲስ አይነት ነገር ይዞ በመምጣት ውጤታማ መሆን ነው። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅና ውጤታማ የሆነ የንግድ ስትራቴጂ በመሆኑ አዲስ እይታም ይህንኑ በመከተል ለደንበኞቹ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ወደ ቢዝነስ የሚገቡ ደንበኞች ገበያ ውስጥ ተመራጭና ውጤታማ መሆን እንዲችሉ አዳዲስ አቀራረቦችን የሚከተለው አዲስ እይታ፤ የቢዝነስ ጽንሰሃሳብን ከማማከር ባለፈ የተግባር ስልጠና ይሰጣል። በአስር ዓመት የሥራ እንቅስቃሴው ውስጥም ያጋጠሙትን በርካታ እንቅፋቶች አልፎ 10 ሺህ የሚደርሱ ደንበኞችን አምራች ማድረግ ችሏል። ደንበኞች በፈለጉት የሥራ ዘርፍ የማማከርና ለሥራው አስፈላጊ የሆነውን የስልጠና አገልግሎት በመስጠት ወደ ምርት እንዲገቡ አድርጓል። ደንበኞች ካገኙት አገልግሎት መካከል ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ አስመጪና ላኪ፣ አገልግሎት አሰጣጥና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

በተለያየ ዘርፍ የማማከር አገልግሎት ያገኙ ደንበኞችም በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ደስተኛና ውጤታማ እንደሆኑ ያነሱት አቶ ክብረት፤ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በቀላሉ በቤት ውስጥ አምርተው ገቢ ማመንጨት የቻሉ ዜጎች ቀላል ቁጥር የላቸውም። እሳቸው እንዳሉት፤ አዲስ እይታ ሃሳብ ከመስጠት ጀምሮ እስከ ተግባር ድረስ ያማክራል፤ ይደግፋል፤ ይከታተላል። ድርጅቱ በተለይ በቀላሉ የሚጀመሩና አላቂ በሆኑ ቢዝነሶች ላይ ትኩረት በማድረግ ብዙዎች ጋር መድረስ ችሏል።

ለአብነትም ሻማ፣ የጽዳት ዕቃዎች፣ ቅባት፣ ኤ ፎር ወረቀት፣ ሶፍት፣ ቾክ፣ ጅብሰም፣ ቆርቆሮ፣ ሚስማርና መሰል አላቂ ዕቃዎችን በቀላሉ በትንሽ ቦታ ማምረት የሚያስችል ስልጠና እና የማማከር አገልግሎት ይሰጣል። እነዚህን ምርቶች ለማምረት የሚያስችሉ ግብዓቶች አብዛኞቹ በሀገር ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ተመራጭ ያደርገዋል። ከዚህ ቀደም ከውጭ ይገቡ የነበሩ ጥሬ እቃዎች በአሁን ወቅት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ጥሬ ዕቃው በሀገር ውስጥ ይገኛል። በመሆኑም አንድ ሰው ሶፍት አምርቶ ለመሸጥ የሚያስችለውን የማማከርና የተግባር ስልጠና ከድርጅቱ ያገኛል። መጠነኛ በሆነ መነሻ ካፒታልም ወደ ሥራ ይገባል።

ድርጅቱ በተለያዩ ቢዝነሶች መሰማራት የፈለጉ ደንበኞችን ከማማከር ጀምሮ በተግባር ልምምድ ስልጠና በመስጠት ደንበኛውን ለመረጠው ቢዝነስ ብቁና ንቁ እያደረገ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ክብረት፤ ከስልጠና በኋላ ደንበኛው ማምረቻ ማሽን ማግኘት እንዲችል ብድር እንደሚያመቻችም ተናግረዋል። ለዚህም በትብብር ከሚሰራባቸው ከአዲስ ካፒታል፣ ከልማት ባንክና ከኦሮሚያ ጉድስ ብድሩን በማመቻቸት የማምረቻ ማሽን ለደንበኞቹ ያቀርባል።

ደንበኞች ወደ ሥራ ወይም ወደ ምርት ከመግባታቸው አስቀድመው ቢዝነሱ ያዋጣል አያዋጣም የሚለውን በሚገባ ማወቅና መረዳት ይኖርባቸዋል። ያሉት አቶ ክብረት፤ ከመረዳት ባለፈ የሚመረተው ምርት ጥሬ ዕቃ በቀላሉ የማይገኝ ከሆነ ችግር ያጋጥመዋል። ስለዚህ እዚህ ላይም ጥናትና ምክር መስጠት ያስፈልጋል ይላሉ። በሀገር ደረጃ ያለውን አቅም መረዳትና ክፍተት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራትን ይጠይቃል። በመሆኑም በአሁን ወቅት በርካታ ምርቶችን በቀላሉ በሀገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ ነው፡፡

ቆርቆሮ፣ ሚስማር እና ሌሎችም በሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ መመረት የቻሉ ሲሆን፤ ከሶስት እስከ 12 ቁጥር ሚስማር እና ቆርቆሮ ማምረት ለሚፈልጉ ደንበኞች ስልጠናውን በመስጠት በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል። እሴት ጭመራ ላይም እንዲሁ ቡና ቆልቶና ፈጭቶ ለገበያ ማቅረብ የፈለጉ ደንበኞችን አሰልጥኖ ወደ ምርት እንዲገቡ አድርጓል። እነዚህንና መሰል ምርቶችን በጥራት አምርቶ ገበያ ውስጥ መግባት የቻሉ ደንበኞች በርካቶች ናቸው። ለዚህም ስልጠናና የቢዝነስ ስትራቴጂን መከተል ወሳኝ ነው ይላሉ። ድርጅቱ ትኩረት ያደረገባቸው የምርት አይነቶች በየትኛውም የሀገሪቷ አካባቢዎች በስፋት የሚፈለጉ፣ አላቂና በየጊዜው በሚፈለጉ ምርቶች ላይ እንደሆነም አስረድተዋል።

ድርጅቱ በአሁን ወቅት የዘንቢል ቢዝነስን በስፋት እያስተዋወቀ እንደሆነ ያነሱት አቶ ክብረት፤ ከዛሬ አራት ዓመት አስቀድሞ ሃሳቡ እንደነበራቸው ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ወደዚህ ቢዝነስ ለመግባት አስፈላጊውን ጥናት አድርገዋል። ጎረቤት ኬኒያ በመሄድ ተሞክሮ ቀስመዋል። ምክንያቱም ጊዜው እየዘመነ ሲሄድ ይህ ቀን እንደሚመጣ ቀድመው ተረድተዋል። ኢትዮጵያ እያደገች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤም አብሮ ያድጋል።

በዓለም ላይ ያሉ ካምፓኒዎች ለምርቶቻቸው መያዣ ደረጃቸውን የጠበቁ ካርቶኖችን ሲጠቀሙ ይስተዋላል። ይህም የስልጣኔ መገለጫ ነው የሚሉት አቶ ክብረት፤ ሰዎች የሚጠቀሙት ማንኛውም ነገር ከተፈጥሮ ጋር መስማማት እንዳለበት ያምናሉ። ኢትዮጵያም በአሁን ወቅት ፌስታል ከመጠቀም ወጥታ የተለያዩ የወረቀት፣ የካርቶንና የጨርቅ መያዣዎችን የምትጠቀምበት ጊዜ ላይ በመሆኗ አዲስ እይታ እዚህ ላይ በስፋት ለመሥራት ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ስልጠና እና ቢዝነሱን የማማከር ሥራ ጀምሯል፡፡

‹‹ሥራው ወቅታዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ ሰዎች ወደዚህ ቢዝነስ እንዲገቡ እመክራለሁ›› ያሉት አቶ ክብረት፤ አሁን ላይ ሶስት የዘንቢል አይነቶች ማምረት የሚያስችል የጽንሰሃሳብና የተግባር ስልጠና እየሰጡ እንደሆነ ገልጸዋል። አንደኛው የወረቀት ቦርሳ ሲሆን፤ ይህን ቦርሳ ለማምረት ክራፍት ወይም መደበኛ የሆነውን ካርቶን ተጠቅሞ የሚዘጋጅ ነው። ሁለተኛው ዱፕሌክስ ነው። ይህም ካርቶን ቢሆንም ከመደበኛው የካርቶን ቦርሳ የተሻለ ውበትና ጥንካሬ አለው። ሶስተኛው ነንውቨን ወይም ያልተሸመነ ክር ማለት ነው። እነዚህ ዘንቢሎች በጣም ጠንካራና ውበት ያላቸው ናቸው። በመሆኑም ክብደትና ርጥበት ያላቸውን ዕቃዎች ጭምር መያዝ ይችላል። ከእነዚህ በተጨማሪ የጨርቅ ዘንቢሎች ይገኙበታል፡፡

ፌስታል መጠቀም ያስቀጣል የሚለውን አዋጅ ተከትሎ፤ እንዲህ አይነት አማራጮችን ማምጣት በብዛት አምራች እጆች እንዲፈጠሩ ያደርጋል ያሉት አቶ ክብረት፤ የዘንቢል ቢዝነስን ለመጀመር በትንሹ 50 ሺ ብር፤ ከፍ ሲል በአራት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል መጀመር ይቻላል ብለዋል፡፡

በቀን ከ100 ሺ ዘንቢሎች በላይ ማምረት በሚችሉ ማሽኖች ቢዝነሱን መጀመር እንደሚቻልም አስረድተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ቢዝነሱን ኬኒያ ሄደው አጥንተዋል። ጥናቱ ኬንያ ሙሉ ለሙሉ የምትጠቀመው ካርቶን እና ነንውቨን የተባለውን መያዣ እንደምትጠቀም አመላክቷቸዋል።

በአሁን ወቅትም ኬኒያ ውስጥ የትኛውም ሱቅ ወይም ማምረቻ ቦታ የሚጠቀሙት ካርቶን እና ነንውቨን ነው። ይህም ከአካባቢ ብክለት ነጻ በመሆኑ ተመራጭ አድርጎታል። ይህን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ተችሏል። ያሉት አቶ ክብረት፤ ፌስታል ይወገድ በተባለበት በዚህ ወቅት ወደ ቢዝነሱ መግባት አዋጭ በመሆኑ ሰዎች በቀላሉ የሚጀምሩት አዋጭና ተመራጭ ቢዝነስ ነው። ስለዚህ ቢዝነሱን ትላልቅ ባለኃብቶች ግዙፍ ማሽኖችን አምጥተው ከሚሠሩት ይልቅ በርከት ያሉ ሰዎች በቤታቸው በቀላሉና አነስተኛ በሆኑ ማሽኖች ማምረት ቢችሉ ብዙዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ለዘንቢል ቢዝነስ እየሰጠ ያለው የጽንሰሃሳብ ምክርና ስልጠና መጠነኛ በሆነ ክፍያና ባጠረ ጊዜ መሆኑን ያስረዱት አቶ ክብረት፤ ዘንቢል ወይም የካርቶን ቦርሳ ለማምረት ቀለም፣ ክር፣ ከምሱር፣ መቀስ፣ መቀቢያ፣ ማቅጠኛና ዋናው ካርቶን ያስፈልጋል። አብዛኘው ግብዓት በሀገር ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ድርጅቱም እነዚህን ግብዓቶች አቅርቦ በሶስት ቀናት ውስጥ ስልጠናውን ይሰጣል። ሰልጣኙ የቢዝነስ ጽንሰሃሳብን ተረድቶ በተግባር ዘንቢል ለማምረት በትንሹ ሶስት ቀናት የሚፈጅበት ሲሆን፤ ለዚህም ስድስት ሺ ብር ክፍያ ይጠየቃል።

ሥራው በቤት ውስጥ በቀላሉ ሲልክ ስክሪን በሚባል አነስተኛ ማሽን የሚሠራ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ሊሳተፉበትና የገቢ ምንጭ ሊያገኙበት ይችላሉ። በቀን በሁለትና በሶስት ሰዎች በትንሹ ከ200 በላይ ዘንቢል ማምረት ይቻላል። ይህም በወር ውስጥ ትርፋማ ያደርጋቸዋል። ከዚህ ከፍ ሲል ታድያ ለአምስት ቀናት የሚሰጥ ስልጠናም አለ። ስልጠናው ተግባር ብቻ ሳይሆን ጽንሰሃሳብንም ጭምር እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሰፊውን ጊዜ የሚወስደው የተግባር ስልጠናው እንደሆነና ተግባርና ጽንሰሃሳብ መቀናጀት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ነጋዴ ለምን እንደሚነግድ ራዕዩን ግልጽ ማድረግ አለበት የሚሉት አቶ ክብረት፤ ይህንኑ ለደንበኞቻቸው እንደሚያስረዱ ተናግረዋል። ለአብነትም ሰዎች በንግድ ሲሰማሩ የገንዘብ ነጻነት፣ የአዕምሮ ነጻነትና ከራስ አልፎ ማኅበረሰብን ለመጥቀም መሆን አለበት ይላሉ። ታድያ ደንበኞች ይህንን በሚገባ ተረድተው ስልጠና አግኝተው ወደ ቢዝነስ ሲገቡ ውጤታማ እንደሚሆኑም ዕምነታቸው ነው።

አዲስ እይታ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር የተለያየ ድጋፎችን እያደረገ ሲሆን፤ ለአብነት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በማኅበር ለታቀፉ ወጣቶች ነጻ ስልጠናና የማማከር አገልግሎት ሰጥተዋል። በልደታ ክፍለ ከተማም እንዲሁ ብርሃን ለሕጻናት ለተባለ የተለያዩ የአካል ጉዳት ላለባቸው ሰዎች የአንድ ሳምንት ሙሉ የቢዝነስ ስልጠና ሰጥቷል። ስልጠናውም ሻማ፣ ሶፍት፣ ዘንቢልና ሌሎችንም ማምረት የሚያስችል ነው። በተለያዩ ወረዳዎች ላደረጉት ድጋፍም የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡

ድርጅቱ በቀጣይ ቢዝነስን ዘመናዊ የማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ክብረት፤ እንደ ሀገር በርካታ ዜጎችን ወደ ቢዝነስ በማስገባት ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ዋነኛ ዓላማቸው መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና አሁን ያሉበት የሰርቶ ማሳያ ወይም ማሰልጠኛ ማእከል ጠባብ በመሆኑ፤ እዚህ ላይ መታገዝ ይፈልጋሉ። ሰፊ ቦታ ላይ ሰፋፊ ሥራዎችን የመሥራት ዕቅድም አላቸው። ለዚህም ትልቅ አቅምና በርካታ ባለሙያዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል።

በፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You