በቆሎና ሱፍ የሚፈለፍል ማሽን የሠራው የፈጠራ ባለሙያ

አሰልጣኝ ብርሃኑ በየነ ይባላል:: በጅማ ዞን አሰንዳቦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አሰልጣኝ ነው:: በቆሎና ሱፍ በየተራ የሚፈለፍል ማሽን ሠርቷል:: ማሽኑ ለመሥራት ያነሳሳው በሚኖርበት አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለመሰብሰብ የሚያልፉበትን ውጣ ወረድ መመልከቱ ነው::

ከድሮ ጀምሮ እስካሁን ምርቶች ለመሰብሰብ የሚጠቀሙት በባኅላዊ የአመራረት ዘዴ ነው:: በባኅላዊ መንገድ ደግሞ ብዙ አሰልቺ ሂደት ማለፍ ይጠበቅባቸዋል:: በተለይ የበቆሎና የሱፍ ምርቶችን ለመሰብሰብ በእጅ መፈልፈል፤ በእግር በማሸትና፣ በዱላ ለመውቃት ይገደዳሉ:: አብዛኛውን በዚህ ሥራ ላይ የሚሰማሩት ሴቶች በመሆናቸው ከፍተኛ የሥራ ጫና ይፈጥርባቸዋል:: ባህላዊ አመራረት ዘዴ ተጠቅሞ ማምረት ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚፈጅና ወጪ የሚያስወጣ ከመሆኑም ባለፈ ምርቱን ለብክነት የሚዳርግ እንዲሁም በብዙ መልኩ ተጎጂ የሚያደርጋቸው ነው::

ይህም የአርሶ አደሩን በተለይም ሴቶችን ለከፍተኛ ድካምና ልፋት የሚዳርግ አሰልቺ ሥራ ከመሆኑም ባሻገር የጤና እክል የሚያስከትል እንደሆነ የሥራ ፈጠራ ባለሞያው ይናገራል:: በቅርበት ባሕላዊው መንገድ የሚያስከተለው ጉዳት ጭምር ማየት የቻለበት አጋጣሚ እንደነበረው የሚያስረዳው አሰልጣኙ፤ በተለይ ተማሪዎች ሲሆኑ ደግሞ ወላጆቻቸውን እየረዱ ስለሚማሩ፤ የምርት መሰብሰቢያ ሰዓት ሲደርስ ወላጆቻቸው ለማገዝ በሚያደርጉት ጥረት የምርት አሰባሰብ ዘዴው ረጅም ጊዜን ከመውሰዱ ባሻገር ይህም ጊዜያቸው በአግባብ እንዳይጠቀሙና እንዲሰለቹ ስለሚያደርጋቸው ትምህርታቸውን በአግባብ እንዳይከታተሉና ከትምህርት ገበታቸው እንዲቀሩ ምክንያት ይሆናል ይላል::

ባሕላዊ አሠራሩ ለጤና እክል ይዳርጋቸዋል የሚለው አሰልጣኝ ብርሃኑ፤ ይህን ተከትሎ የችግሩ ጥልቀት ስለገባው፤ እነዚህ ችግሮች ከግንዛቤ በማስገባት መፍትሔ በአቅራቢያ ካሉት እንደሱ አይነት ባለሙያ እንደሚጠበቅ በማመን መፍትሔ ያለውን መላ ለመዘየድ አቅዶ ሥራ እንደጀመረ ይናገራል::

አሰልጣኙ እውቀቱና ክህሎቱን ተጠቅሞ ችግሩን በመፍታት በዋናነት የሴቶች ድካም ለማቅለል ያስችላል ያለውን ማሽን ለመሥራት መነሳቱን ይናገራል:: የግብርና ምርቶች ለመሰብሰብ ከባዱን አሠራር ሊያቀልና ሊያዘመን የሚችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መኖር እንዳለበት አምኖ፤ ምን አይነት ቴክኖሎጂ ቢያመጣ ምርቶችን በቀላሉ መሰብሰብ እንደሚያስችል ሲያሰላስል ቀላል ያለውን ቴክኖሎጂ በመምረጥ ለመሥራት መሞከር ጀመረ:: በሙከራው እና ባደረገው ጥረት በተለይ በቆሎን እና ሱፍን በየተራ መፈልፈል የሚያስችል ማሽን መሥራቱን ይገልጻል::

የግብርና ምርቶች በማምረትም ሆነ በመሰብሰብ ሂደቶች ያሉ ችግሮች ምርቶች በአግባብ እንዳይሰበሰቡ፤ እንዲባክኑ ያደርጋሉ:: በወቅቱም ወደ ገበያ የመውጣትና የማምረት ሂደቱም እንዲቀንስ ምክንያት እንደሚሆን አሰልጣኝ ብርሃኑ ይናገራል::

እንደ አሠልጣኙ ገለፃ፤ በተጨማሪ በባሕላዊ መንገድ ማረስ፣ ማጨድም ሆነ መፈልፈል የከበደው አርሶ አደር ችግሩን ለመውጣት የምግብ እህሎችን በመተው ባህርዛፍ የመሳሳሉት ተክሎችን ወደ መትከል እያዘነበለ ነው:: ይህ አካሔድ የሚፈጥረውን ችግር ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፤ እንደዚሁም ይህንን እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት፤ የምርት አሰባሰብ ሂደቱን ዘመናዊ እንዲሆን በማሰብ ማሽን ሠርቷል::

እንደዚህ አይነት በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎች ለአንድ ዓላማ ብቻ ታስበው የሚሰሩ እንደሆነ የሚገልጸው አሰልጣኙ፤ በቆሎን እንዲፈለፍል ከተሠራ ማሽን በቆሎን ብቻ የሚፈለፍል መሆኑን ያስረዳል:: እሱ የሠራው ማሽን ግን ‹‹ የበቆሎ ምርት በደረሰበት ወቅት በቆሎን ፤ የሱፍ ወቅት ደግሞ ሱፍን በመፈልፈል ሁለት አይነት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተሠራ ነው›› ይላል::

አሰልጣኙ እንዳብራራው፤ ይህ የፈጠራ ሥራ የተሰራው 2017 ዓ.ም ነው:: ለመሥራት አራት ወራት ያህል የፈጀ ሲሆን፤ ማሽኑን በቀላሉ በአካባቢ ከሚገኙ ግብዓቶች የተሠራ ነው:: ከውጭ የሚመጣ ግብዓት ስለሌለ በቀላሉ መሥራትና ማባዛት የሚቻል ነው:: ማሽኑ የተሠራው ከተለያዩ ሊገጣጠሙ ከሚችሉ ቁሶች (ፕሌቶች) በመሆኑ ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ መንቀሳቀስም ሆነ ማጓጓዝ ይቻላል:: በነዳጅም ሆነ በኤሌክትሪክ ኃይል በመጠቀም ይሠራል::

ወደፊት አቅም በመጨመር በፀሃይ ሃይል (በሶላር) እንዲሠራና ለገጠሪቷ የሀገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን ዓቅዶ እየሠራ ነው:: ማሽኑን አርሶ አደሩ እንዲያውቀው በተለያዩ አውደ ርዕዮች በማቅረብ እያስተዋወቀ ይገኛል:: ከውጭ የሚመጣና ሀገር ውስጥ የሚሰራ እንዲዚህ አይነት ማሽን እንዳለ አሰልጣኙ ያመላክታሉ:: ማሽኑ ከእነዚህ ማሽኖች የሚለይበት ዋናው ምክንያት፤ በአንድ ሞተር ሁለት ነገሮች መሥራት መቻሉ ነው::

ማሽኑ ውስጣዊ ክፍሎችም ከሌሎች የተለዩ ናቸው:: ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ በቆሎውን ወደ መፈልፈያ የሚያመጣና ከተፈለፈለ በኋላ ቆሮቆንዳውን (ተረፈ ምርቱን) እና ምርቱን ለየብቻ እንዲወጣ ያስችላል:: እስካሁን ያሉ ማሽኖች ግን በቆሎን ሲፈለፍሉ ጫፉን ይሠባብራሉ:: ይህም በቆሎው በድጋሚ ቢዘራ እንዳይበቅል የሚያደርግ በመሆኑ በሌላ ማሽን የተፈለፈለ በቆሎ ለዘር አይሆንም:: አዲሱ ማሽን ግን በቆሎ እንዳይሰባበር አድርጎ ስለሚፈለፍል ለዘር ሆነ ለሌላ አገልግሎት ማዋል ያስችላል::

ማሽኑ በሰዓት 200 ኪሎ ግራም( ሁለት ኩንታል )በቆሎን መፈልፈል የሚችል ነው:: ሱፍ በባኅሪው ቀላል ስለሆነ በሰዓት 100 ኪሎ ግራም (አንድ ኩንታል) ሱፍ ይፈለፍላል:: ማሽኑ አዲስ የተሠራ እንደመሆኑ በቆሎና ሱፍ በጥራት እንደሚፈለፍል ተፈትሾ ተረጋግጧል የሚለው አሰልጣኙ፤ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ተወዳድሮ አሸንፎ በፌዴራል በክህሎት ውድድር ላይ ማቅረቡን ጠቁሟል::

ማሽንኑን የተመለከቱና ጠቀሜታውን የተረዱ በሙሉ ለአርሶ አደሩ በፍጥነት ተሰርቶ እንዲደርስ እየመከሩ ይገኛሉ የሚሉት አሰልጣኙ፤ በመሆኑም ማሽን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ድጋፍ የሚያደርግ ከተገኘ በተባለው ልክ ሰርቶ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል ይላል::

በተለይ የችግሩ ባለቤት የሆነው አርሶ አደሩ ማሽኑን ቢመለከት ገዝቶ ለመጠቀም ወደኋላ እንደማይል በመጠቆም፤ ምክንያቱም ‹‹ማሽኑ ከፖሊቴክኒክ ኮሌጁ ወደ ውድድር ሲመጣ የተመለከቱ አርሶ አደሮች ማሽኑን እንዳልወስድ ብዙ ጥረት አድርገዋል:: ይዤ የመጣሁት፤ በትግል ነው:: ማሽኑን ሰርቼ ለአካባቢው አርሶ አደር ተደራሽ እንደማደርግም እምነት አለኝ:: ›› ይላል::

በተጨማሪም በሀገር ደረጃ ለተለያዩ ክልሎች ተደራሽ ማድረግ ቢቻል የአርሶ አደሩን ችግሮች በመፍታት ጊዜ፣ ወጪንና ብክነት በመቀነስ ምርትና ምርታማነት መጨመር ያስችላል:: ይህም ግብርና ከማዘመን አንጻር ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ ያደርጋል ሲል ተናግሯል::

አሰልጣኙ እንደሚለው፤ ከውጭ የሚገባ አንዱን አይነት ሰብል ብቻ የሚፈለፍለው ማሽን በገበያ ላይ ዋጋው ከ250 እስከ 300ሺ ብር ነው:: ይህ ማሽን ግን የአርሶ አደሩን የመግዛት አቅም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ ከ125 እስከ 130 ሺህ ብር ለገበያ ይቀርባል:: ወደፊትም በብዛት የሚመረት ከሆነ አርሶ አደሩን አቅም ባገናዘበ መልኩ ከዚህም ባነሰ ዋጋ የሚቀርብበት ሁኔታ ይፈጠራል::

በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች ያለባቸው ችግር ለመፍታት በማሰብ ለመሥራት ሲነሳ በብዙ ፈተናዎች መካከል በማለፍ፤ የራሱን ጥረትና ትግል አድርጎ አሁን ያለበት ደረጃ እንደደረሰ የሚናገረው አሰልጣኙ፤ ማሽኑን ለመሸጥ የተተመነው ዋጋም ቢሆን አርሶ አደሩን ኪስ በማይጎዳ መልኩ ተብሎ እንጂ ከተሰራው ሥራና ከልፋቱ አንጻር ሲታይ የሚያዋጣ ሆኖ አይደለም ይላል::

ይህ ማሽን የሕብረተሰቡን ችግር ሲፈታና እየተለመደ ሲመጣ ፍላጎቱም እየጨመረ ውጤታማ እየሆነ ከመጣ ቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት መነሳሳትንም እንደሚፈጥር ተናግሯል::

በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ማሽኖች ከጥራትና ከጥንካሬ አንጻር ብዙ ጊዜ ችግር እንዳለባቸው ይነገራል:: ይሁን እንጂ ሀገር ውስጥ ምርቶች የጥራት ሆነ የጥንካሬ ችግር የለባቸውም:: ይልቁኑ አብዛኛው አጨራረስ ላይ ችግር እንዳለባቸው ይስተዋላል የሚለው አሰልጣኙ፤ አጨራረስ በልምድ እየዳበረ ሲመጣ የሚስተካከል ነው:: በጥራትና በጥንካሬ ከውጪ የሚመጣው ቢበልጡ እንጂ የሚያንሱ አይደሉም ሲል አስረድቷል::

‹‹ፈጠራ ሥራዎች ስሠራ መጀመሪያ የሰራሁትና አሁን የሠራሁዋቸው ያላቸው ልዩነት ሰፊ ነው:: ይህንን ማሽን መሥራት የቻልኩት ከመጀመሪያው ባገኘሁት ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ በመሠረታዊነት ያሉት ጎድለቶች በመሙላት እያሻሻልኩ መጥቼ ነው::›› ብሏል::

በአካባቢው ላሉ አርሶ አደሮች ደግሞ በተለያዩ አውደርዕዮች ላይ በማቅረብ የማስተዋወቅ ሥራ ለመሥራት አቅዷል:: በቀጣይ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም ማሽኑ አርሶ አደሩን እንዲያውቀው ማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል የሚለው አሰልጣኙ፤ ቀደም ሲል እጁ ሲያፍታታ ከቆየበት የፈጠራ ሥራዎች በኋላም የሠራቸውና በወርክሾፑ ያስቀመጣቸው ብዙ ቴክኖሎጂዎች እንዳሉ ይናገራል::

በተለይ ግብርና ዘርፍ ላይ ያሉ ችግሮች ለመፍታት የሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች መካከል አብዛኛው አርሶ አደር ሴቶች ልፋት የሚያቀል የጤፍ መንፍያ ቴክኖሎጂ በመሥራት ተሸጋግሮ ጥቅም ላይ እየዋለ አርሶ አደሩ እየተጠቀመበት መሆኑን ይገልጻል:: የጤፍ መንፍያውን እንዲሠራላቸው የሚፈልጉ አርሶ አደሮች ጥያቄ በማቅረባቸው ሌላ ተጨማሪ የጤፍ መንፍያዎችን እየሠራ መሆኑን ይገልጻል::

ከዚህ ሌላም ለከብቶች መኖ አገልግሎት የሚውል ማሽን መሥራቱን ያመላክታል:: ማሽኑ በቆሎ አገዳ፣ ሸንኮራ አገዳና ቆጮ የመሳሳሉ ለከብቶች መኖ የሚውሉት ሰብሎች እየቆራረጥ ለመኖነት በሚውል መልኩ ያዘጋጃል:: ይህም ማሽን ለከብት አርቢዎች፣ ለዶሮ አርቢዎች ተደራሽ ተደርጎ ጥቅም ላይ ውሏል ሲል አብራርቷል::

የተሰሩ የፈጠራ ሥራዎች ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ሂደት ተግዳሮቶች ከሆኑት ነገሮች ዋነኛው በቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች መካከል ቅንጅት አለመኖር ቴክኖሎጂ ተሰርቶ በታሰበበው ጊዜ የታለመለት ችግር ለመፍታት መዋል አለመቻሉ እንደሆነ ያመላክታሉ:: ምክንያቱም በአርሶአደሩን በሚመራው ተቋምና በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ መካከል የተቀናጀና የተናበበ ሥራ ስለማይሰራ ነው ይላል:: የተናበበ ሥራ መስራት ቢቻል የሚሠሩት ቴክኖሎጂ በወቅቱ አርሶ አደሩ ጋር ደርሰው ጥቅም ላይ ውለው ውጤታማ ሥራ መስራት ይቻል ነበር ይላል::

ሕብረተሰቡ ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ሆኖ የአኗኗር ዘይቤው በማሻሻል ምርታማ በመሆን ለራሱ ለሀገርም መጥቀም ያስችል እንደነበር ጠቅሶ፤ ያሉትን ክፍተቶች በሂደት በመፍታት ለፈጠራ ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ መሥራትንም ይጠይቃል ሲል አስገንዝቧል::

የፈጠራ ሥራዎች መስራት አንድ ጊዜ ተሞክሮ ተሰልችቶ የሚተው ሳይሆን፤ ውጤታማ እስኪሆን ብዙ ጥረትና ሥራዎችን ይጠይቃል የሚለው አስልጣኙ፤ የሚታየው ከብዙ ጥረትና ልፋታ በኋላ ስለሆነ ውጤታማ ሆኖ ሲታይ ከምንም በላይ ያስደስታል ይላል::

‹‹አሰልጣኝ እንደመሆኔ መጠን በፈጠራ ሥራ በኩል የበኩሌን ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት አደርጋለሁ:: አሰልጣኞችም ለተማሪዎች አርአያ በመሆን በፈጠራ ሕብረተሰቡንና ሀገራቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉ ሥራዎችን መስራት እንዲችሉ እመክራለሁ::›› ይላል::

ብዙ በቴክኖሎጂ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ብዙ ሥራዎች በመስራት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቅሶ፤ ፈጠራ ልፋት፣ ጥረትና ትግል እንደሚጠይቅ በማስታወስ፤ እነዚህን በማለፍ ወደፊት የሚወጣ ሥራ ይዘው ሊቀርብ ይገባል ሲል ይመክራል::

በወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You