ወንድወሰን መኮንን
አቶ ጥላሁን ጣሰው ዘለልክ የተወለዱት አዲስ አበባ ካዛንችስ ነው።የታዋቂው የመንዝና የሸዋ አርበኛ የፊታውራሪ ጣሰው ዘለልክ ልጅ ናቸው።ያደጉትና የተማሩት አዲስ አበባና ደሴ ወይዘሮ ስሒን ትምህርት ቤት ነው።በትምህርቱ መስክ በሕዝብ አስተዳደርና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ባችለር ዲግሪ፤ በልማት ምርምር ማስትሬት ዲግሪ አላቸው።ሀገራቸውን በተለያዩ ሥራዎችና ኃላፊነቶች አገልግለዋል።በአሁኑ ሰአት በማማከርና ምርምር ስራ የተሰማራው ቲቲኤምሲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።ተመራማሪና በተለይም የወታደራዊ ታሪክ ጸሐፊ ናቸው።
በደም የቀለመው፣ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያገነነው፣ መላውን የጥቁር ሕዝብ ዘር በነጮች ከመጥፋት የታደገው ፤ የኢትዮጵያውያንን ታላቅ ጀግንነትና የጠለቀ አስተዋይነት በተለይም የአጼ ምኒሊክንና የእቴጌ ጣይቱን የላቀ የዲፕሎማሲና የላቀ ወታደራዊ የስትራቴጂ ችሎታ ለዓለም ያስመሰከረውን የዓድዋ ጦርነት በተመለከተ ወራሪ ጣሊያንን አባቶቻችን በምን ያህል ድንቅ ጀግንነት አሸንፈው እንዳንበረከኩት ያልተነገሩ ያልተዘከሩ የአውደ ጦርነቱን ታሪኮች በተመለከተ የተለያዩ መጽሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል።ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ያደረገቻቸውን ጦርነቶች በሚመለከት ለምርምር የሚጠቅሙ የታሪክ ሰነድ የሆኑ መጽሐፎችን በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ አሳትመዋል።ከ38 ዓመት በፊት አዳባይ የሚል በኩራዝ ማተሚያ ድርጅት የታተመ መጽሐፍ አላቸው።የአምስት አመቱን የአርበኝነት ታሪክ የሚያወሳ TRYING TIMES የሚል መጽሀፍ ሻማ ቡክስ አሳትሞላቸዋል።የዓድዋን ጦርነት በሚመለከት ቅድመና ድህረ ዓድዋ ጦርነት አፍሪካን ከቅኝ ገዢዎች የመከላከል ሰልፍ የሚልና አሁን ደግሞ በቅርቡ በእንግሊዝኛ Emperor minilik 2nd the military strategist and Diplomat who changed the course of history በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሀፍ ለንባብ በቅቷል ።በአጠቃላይ 9 የታሪክና የምርምር መጽሐፎች ሕዝብ ዘንድ እንዲደርስ አድርገዋል።ከእኒሁ አንጋፋ የታሪክ ተመራማሪና ደራሲ ጋር አዲስ ዘመን ልዩ ቆይታ አድርጋለች፤ ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፤- ለዓድዋው ጦርነት መነሻው ምንድን ነበር ?
አቶ ጥላሁን፤- እኔ የማተኩረው ወታደራዊ ታሪኩ ላይ ነው።ወታደራዊ ታሪኩን ስንጽፍ የውጫሌን ውል ብቻ መሰረት አድርገን ልንጽፍ አንችልም።የውጫሌ ውሉ የተደረገበት ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት በብራስልስና በበርሊን ስምምነት ባደረጉበት ዘመን ነው።ስለዚህም ነው የውጫሌውን ውል የአውሮፓ መንግሥታት እንዲያውቁላት ጣሊያን የምትሰደው።አጼ ምኒሊክም ንቃት ያገኙበት ነው።እኔ እንደዚህ አልተስማማሁም በሚል፡፡
ከዚያ ከዓድዋ ጦርነት አምስት አመት ቀደም ብሎ አፍሪካን የመቀራመት ውላችሁን አልቀበልም፤ ዝም ብዬ አላይም ብለው በ1883 ሚያዚያ ወር ላይ አጼ ምኒሊክ መልስ ሰጡ።አጼ ምኒሊክ የግዛታቸውን ወሰን በምዕራብ እስከ ነጭ አባይ፤ በምስራቅ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ፤ በደቡብ ደግሞ እስከ እንግሊዝ የዚያን ግዜ ይዛው እስከነበረው ሌክ ኒያሳ /የኒያሳ ባሕር/ ድረስ መሆኑን ገለጹ።
አዲስ ዘመን፤- ሌክ ኒያሳ የት ነው ??
አቶ ጥላሁን፤- አሁን ቪክቶሪያ አካባቢ ያለ ነው።መጀመሪያም ግዛቴ ሌክ ቪክቶሪያ ድረስ ነው ብለው የሚጠሩት አለ።ይሄንን ማእቀፍ ካልተረዳነው በስተቀር ወታደራዊ ማእቀፉን በደምብ ልንገነዘበው አንችልም።ለምሳሌ ወረኢሉ ላይ አጼ ምኒሊክ ሠራዊታቸውን በሙሉ እንዲሰበሰብ አደረጉ።የሸዋ ሠራዊት ወረኢሉ አሁን ጎንደርና ጎጃም የምንለው ደግሞ አሸንጌ ላይ ይሰብሰብ አሉ።ምክንያቱም ራስ መንገሻ ስዩም እያፈገፈጉ ስለመጡ ነው።በሁለቱም አቅጣጫ ሠራዊታቸው እንዲሰበሰብ ነው ያዘዙት።የሸዋን ጦር ወረኢሉ ላይ ላግኝህ ሲሉ የዛን ግዜ ሸዋ ማለት የአሁኑ ሸዋ አይደለም።የዛን ግዜ ሸዋ ማለት ወለጋ ፤ከፋ፤ ሐረር ሁሉ ሸዋ ነው።ገና ንጉሠ ነገሥት ሳይሆኑም በፊት ይሄ ሁሉ ሀገር ሸዋ ሆኖአል።የሸዋ ጦር ወረኢሉ ላግኝህ ሲሉ ወረኢሉ ላይ የምናገኛቸው እነማንን ነው የሚለውን እንይ ።ካኦጦና ከወላይታ ፤ ደጃዝማች ገብረእግዚአብሄር ከወለጋ፤ ደጃዝማች ጆቴ አሁን ቤኒሻንጉል ከምንለው እሳቸውም መጥተዋል።ራስ መኮንን የሶማሌን የሐረርን ጦር ይዘው ወረኢሉ መጥተዋል።ራስ ወልደ ጊዮርጊስ ከፋ የእናሪያ የሊሙ ገዢ የነበሩት እሳቸውን ወደወረኢሉ ኑ ብለው በኋላ ቀረት በሉ ብለዋቸዋል።ይሄን የምገልጸው ወታደራዊ ግንዛቤ እንዲኖረን ነው።ወረኢሉ ላይ አጼ ምኒሊክ ጦራቸውን በአራት አቅጣጫ ነው ያሰማሩት።ይሄንን በሚገባ ካልተረዳነው ወታደራዊ ታሪኩንና አሰላለፉን ልንረዳው አንችልም፡፡
አዲስ ዘመን፤- እስቲ ወታደራዊ አሰላለፉንና ታሪኩን ያስረዱን ?
አቶ ጥላሁን፤- አጼ ምኒሊክ 15 ሺህ በደምብ የሰለጠኑ በየመኳንንቱ ስር የሚታዘዙ የምኒሊክ ልዩ ኃይሎች አሏቸው።መድፈኛና መትረየስ ተኳሾች።ከራሳቸውም ጦር እነ ፊታውራሪ ታፈሰን ፤እነ ፊታውራሪ ገበየሁን ፤ ራስ መኮንን የያዙትን ጦር ከዛ እነመንገሻ አቲከም ራስ አሉላም የዛን ግዜ አዲስ አበባ ስለነበሩ ራስ መንገሻን እንዲገናኙ አድርገው አብረው ከራስ መኮንን ጋራ ወደላይ ሰደዷቸው።የጦር ኃይል አዛዡ አጼ ምኒሊክ አላጌ ላይ ያለውን የጠላት ጦር ምቱት ብለው ይሄን ያህል ጦር ሰደዱ።የዛን ግዜ በኢትዮጵያ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሥርዓት አልነበረም።መከላከያ ሚኒስቴር የለም ።በኃላ ነው የመሰረቱት።
አጼ ምኒሊክ እንዴት አድርገው ሠራዊታቸውን አራት ቦታ እንደሚከፍሉት ደግሞ እንይ ።ወለጋ ከመጡት ከፊሎቹን ለምሳሌ በፊታውራሪ ተክሌ በኩል ያሉትን ወደ አድዋ እንዲዘምቱ አድርገዋል።ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉትን የደጃዝማች ገብረእግዚአብሄርን፤ የደጃዝማች ጆቴን፤ የአባ ጅፋርን ጦር ተመልሳችሁ በምዕራብ በኩል ሀገር ጠብቁ አሏቸው።ምኒሊክ ለምን እንዲህ አሉ ? ስንል ምን ያህል ጥልቅ ወታደራዊ ስትራቴጂስት እንደሆኑ ያሳየናል።የአፍሪካን መቀራመት ውል ተቃውመውት ስለነበረ ጣሊያንን ካሸነፉ እንግሊዝ እንደምትነሳባቸው ያውቃሉ።ስለዚህ ምዕራቡ ሀገር መጠበቅ አለበት።ከዓድዋ ድልም በኋላ ቀጥሎ ጦርነቱ አራት አመት ተኩል ይካሄዳል።
አዲስ ዘመን፤- በምን መልኩ ?
አቶ ጥላሁን፤- እስከ ነጭ አባይ ድረስ እነ ራስ መኮንን ይዘምታሉ።እንግሊዝ ጣሊያንን አግዛ ጦርነቱ ውስጥ እንደምትገባ ስለሚያውቁ ለምን ወደዚያ አቅጣጫ ተጠባባቂ ጦር እንደሰደዱ ስንመለከት የምኒሊክን የስትራቴጂ ችሎታና እውቀታቸውን የሚያስረዳው አንዱ ትልቅ ነጥብ ይሄ ነው።ምክንያቱም በብራስልስ ስምምነት መሰረት እንግሊዞች ጣሊያንና ፈረንሳይ ስምምነት አላቸው።አንዱ አንዱን ከወጋ ሁለቱም ይነሳሉ።ስለዚህ አጼ ምኒሊክ አድዋ ላይ ድል ቢያደርጉም እንግሊዞችና ፈረንሳዮች እንደማይተኙ እንደሚነሱ ያውቃሉ።ስለዚህ ወደ ምዕራቡ ማጠናከር አለባቸው።ለዚህ ነው ከላይ የተጠቀሱት የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች ከነሠራዊታቸው ተመልሰው የምዕራብ ኢትዮጵያን ክፍል እንዲጠብቁ ያደረጉት፡፡ካኦ ጦናን እንዲመለሱ አደረጉ።በወላይታ ላይ ጦርነት ተደርጎ 15 ሺህ ምርኮኛ ስለነበረ እነዛ ምርኮኞች የምኒሊክ ሠራዊት አካል ሆነዋል።እነሱ ወደ አድዋ ዘመቱ።ሌሎቹ ወደ ወረኢሉ ጦር ይዘው የመጡትን የፈረንሳይም የመሀል ሀገርም ችግር ካለ እንዲቆጣጠሩ አድርገው አስቀመጡ።
ጣሊያኖች የዛን ግዜ አውሳ (አፋርን) ለመውጋት ያስቡ ነበረ።በመጀመሪያው ጣሊያኖች የላኩት ጦር በጣም ትንሽ ስለነበረ የአውሳው ሱልጣን ጣሊያኖቹን በሙሉ ገደሉና በግመል ጭነው ለምኒሊክ ሰደዱላቸው።ሁለተኛ ላይ ከጣሊያንና ከቱርክ መርሲነሪዎች ጋር ተቀናጅቶ የመጣው ኃይለኛ ጦር ነበረ።ስለዚህ ራስ ወልደጊዮርጊስ ከወህኒ አዛዡም ጋር ወደኃላ ቀረት እንዲሉ ተደርገው ስለነበር እነሱን በአውሳ በኩል እንዲዘምቱ አደረጓቸው።የዛን ግዜ የጣሊያኖች ቴክኒክ በአውሳ በኩል አልፈው ሐረርን በመያዝ የምኒሊክን የሰሜን ዘመቻ መጎተት( ማዘግየት) ነበር።
አዲስ ዘመን፤- በጣሊያን በኩል የነበረው ዝግጅት እንዴት ነበር ?
አቶ ጥላሁን፤- እስከ አሁን ያየነው በወታደራዊ መልኩ ዓድዋ ከመጀመሩ በፊት ያለውን ነበር።ጣሊያን አዲግራት ላይ አንድ ምሽግ ሰራ።ዓድዋ ላይ እንጓጓ ጊዮርጊስ የሚባል ቦታ ላይ ቤተክርስቲያኑን አስወጣና አንድ ምሽግ ሰራ።መቀሌ ላይ የሥላሴን ቤተክርስቲያን አውጥቶ አንድ ምሽግ ሰራ።አላጌ ላይ ደግሞ አንድ ምሽግ ሰራ ።ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረሥላሴ የትግራይ ዘመቻ የሚሉት ጣሊያን ትግራይን በሙሉ ይዞት ስለነበረ ነው።የመጀመሪያው ጦርነት አላጌ ላይ ሕዳር 28 ቀን 1888 ዓ/ም ተደረገ።ከጣሊያን ጋር የተደረገው ጦርነት ሶስት ወር የፈጀ ነው።ሕዳር 28 አላጌ ላይ ጥር አጋማሽ የመቀሌ ምሽግ መለቀቅ፤ የካቲት 23 /1888 ዓ/ም ዓድዋና አባገሪማ ላይ የጣሊያን ጦር በኢትዮጵያ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ተመታ።
እንግዲህ ጣሊያን እዚህ አራት ምሽግ አለው።ጣሊያን ሌላ አንድ የሚያውቀው ነገር አለው።አጼ ምኒሊክ የዛን ግዜ ከሱዳን መሀዲስቶች ጋር መግባባት ፈጥረው ስለነበረ
ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ሲገጥም መሀዲስቶቹ በከሰላ በኩል እንደሚወጉት ያስብ ስለነበረ ጣሊያን የከሰላ ምሽጉን በ40 ሺህ ጦር አጠናክሮት ነበር፡፡አሁን ስለዓድዋው ጦርነት አጠቃላይ ስዕሉ አለን ማለት ነው፡፡
አፍሪካ በኢትዮጵያና በመሀዲስት ጦር አማካኝነት ተወክሎ አውሮፓ ደግሞ በጣሊያን በእንግሊዝና በፈረንሳይ ተወክሎ ጦርነት ገጠምን ማለት ነው።የዓድዋው ጦርነት አፍሪካን ከቅኝ ግዛት የመከላከል ሰልፍ የሚሆነው ለዚህ ነው።ሌላ እንዳንስተው መረዳት ያለብን በዓድዋ ግዜ አፍሪካ ሙሉ በሙሉ ቅኝ ግዛት አልተያዘም።በማይጨው ጦርነት ጊዜ ግን ተይዟል።ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ብቻ ናቸው የቀሩት።ይሄንን ክበብ ወይንም ስብስብ ሳንገነዘብ ወታደራዊ ታሪኩን ለመረዳት አንችልም።የሆነው ምንድነው ካልን እንግሊዝ ከዓድዋ ጦርነት 14 አመት በፊት ቀደም ብላ ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ላይ የዙሉ ኪንግደምን ወግታ ይዛ ነበር።የዛን ግዜ የዙሉ ንጉሥ ሼሽቶዋኔ የሚባለው 2000 እንግሊዞችን ደምስሶአል።ልክ ራስ አሉላ 500 ጣሊያኖች እንደገደሉት ማለት ነው፡፡ሸሽትዋኔ ይዋጋ የነበረው በጦርና በጎራዴ ነበር።እንደገና በመትረየሳቸውና በመድፋቸው ወግተው አሸነፉት።የዓድዋ ድል ዘላለማዊ ሆኖ የኖረው ተመጣጣኝነት ስለነበረው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፤- ተመጣጣኝነቱ የምን ነበር ?
አቶ ጥላሁን፤- ለምሳሌ የመድፍና የመትረየስን አሰላለፍ ብንመለከት አጼ ምኒሊክ ያሏቸው መድፎች 4.5 ኪሎሜትር ይመታሉ።የአቶ ተክለጻዲቅ መኩሪያ መጽሐፍ ላይ አለ።የጣሊያኖች መድፍ 3.8 ኪሎሜትር ነው የሚመታው፡፡
አዲስ ዘመን፤- በዛን ዘመን ይሄንን መድፍ አጼ ምኒሊክ ከየት አመጡት ?
አቶ ጥላሁን፤- የዛን ግዜ ፈረንሳዮችና እንግሊዞች ፉክክር ላይ ነበሩ።ፈረንሳይ ከእንግሊዝ ጋር በነበራት ፉክክር ኢትዮጵያን መያዝ ትፈልግ ነበር።ሁለቱ የሚጋጩበት ቀጥለን የምናመጣው የፋሾዳ አክሲደንት አለ።ለዛ ስትል ፈረንሳይ ከአጼ ምኒሊክ ጋር ቅርበትና ወዳጅነት እንዲኖራት ትፈልግ ነበረ።በዚህ ምክንያት ፈረንሳይ ጥሩ ጥሩ መድፎች ለምኒሊክ ሸጣላቸዋለች።ራሽያም ከእንግሊዝ ጋር በሩሶ ተርኪሽ ዋር በክሬሚያ ጦርነት ግዜ እንግሊዝ ፈረንሳይ ጣሊያን የዛን ግዜ ሰርዲኒያን አግዛ ገብታ ነበር።ራሽያ ከአጼ ምኒሊክ ጋራ መልካም የወዳጅነት ግንኙነት ነበራት።ጥሩ ጥሩ መሣሪያዎች ታቀርባለች።ወታደሮችም ያሰለጥናሉ፡፡እዚህ ጃንሜዳ አዲስ አበባ ላይ የእኛ ወታደሮች በመድፍም በአሰላለፍም በፈረሰኝነቱም ትምህርት ይሰለጥኑ ነበር።
አዲስ ዘመን፤- በእኛ በኩል ስንት መድፍ ተሰለፈ?
አቶ ጥላሁን፤- ቁጥሩን በትክክል አላውቀውም።ግን ወደ 45 ያህል መድፍ የነበረን ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፤- በጣሊያን በኩልስ ?
አቶ ጥላሁን፤- የእነሱም በኋላ ላይ ተጨመረና ተለወጠ እንጂ መጀመሪያ ያሰለፉት ወደ 45-50 መድፍ ግድም ነበር።
አዲስ ዘመን፤- የ1888ዓ/ም የጦርነቱን አጀማመር ቢነግሩን ?
አቶ ጥላሁን፤- ሕዳር 28/1888 ዓ/ም የተደረገውና ጣሊያንን በማሸነፍ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት የተጠናቀቀው የአላጌ ጦርነት የዓለምን ታሪክ ለወጠ ይባላል።ምክንያቱም ሕዳር 28 አላጌ ላይ የተሰለፈው የኢትዮጵያ ሠራዊት ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ምኒሊክ የሚመሩት ጦር አይደለም።በራስ መኮንን የሚመራው ሌሎችን ራሶችን የያዘ የምኒሊክ ልዩ ኃይል ቢደባለቅበትም አንድ የንጉሠ ነገሥቱ የጦር ክፍል የነበረ ብቻ ነው የገጠመው።በአላጌው የጦር ግንባር ኢትዮጵያውያን ጣሊያኖችን ድል መቷቸው።ዝናውና ዜናው በዓለም ላይ ሲያስተጋባ አውሮፓ ተረበሸ ።ድሮ ትንሽ ፈረንጅ ጦር ይይዙና ሌላ ባንዳውን ይጨማምሩና እርስ በእርሱ እያከፋፈሉ እያዋጉት ይይዙታል።አሁን ግን አልሆነም፡፡ይሄ የጣሊያን ጦር አላጌ ላይ ተሸነፈ።አላጌ ውጊያ ላይ የነበረው የጣሊያን ጦር በአንድ ሻለቃ ነበር የሚመራው፡፡
ይኸው ሻለቃ እንዳይሸነፍ ብሎ ጀነራል አርሞንዲ ከመቀሌ 5000 ጦርና አምስት መድፍ ይዞ መጣ ።ኢትዮጵያውያኖች በጀግንነት ድል አድርገው እየተመለሱ ነበር።ጀነራል አርሞንዲ ረዳት ጦር ይዞ የተሸነፈውን ሻለቃ ጦር ለመርዳት ሲመጣ አዲ አርቃይ የምትባል ቦታ መንገድ ላይ ከጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኘ።የእሱንም 5000 ሠራዊት ከነጦር መሳሪያው ደመሰሱት።ማረኩ።ጄኔራሉ መድፉንም ምኑንም ጥሎ ፈረጠጠ።ግማሹ የጣሊያን ጦር ሸሽቶ መቀሌ ምሽግ ውስጥ ገባ ።ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረሥላሴ ስለ ጄኔራል አርሞንዲ ሲናገሩ የአምስቱ ቀን መንገድ ይላሉ የአምስቱን ቀን መንገድ በሶስት ቀን አቆራርጦት ፉት አድርጎት አዲግራት ገባ።ይሄ የኢትዮጵያውያን ጀግኖች የጦር ሜዳ ድል በአውሮፓ ውስጥ ሲሰማ እጅግ በጣም ትልቅ እንቅስቃሴ ፈጠረ ።ሮም ዩኒቨርስቲ ይማሩ የነበሩ የጣሊያን ተማሪዎች ገና ጣሊያን በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን የተፈጠረች ሀገር ነበረችና ተማሪዎቹ ብሔራዊ ስሜት ስለነበራቸው የጣሊያን ሠራዊት ድል መመታቱ በጣም ቆጭቷቸው ሮም ላይ ሰላማዊ ሠልፍ ወጡ ።ሹሙን ባለስልጣኑን ሁሉ መንገድ ላይ ሲያገኙት እያስቆሙ ምኒሊክ ለዘለዓለም ይኑር !! ቪቫ ምኒሊክ !! ይሉት ጀመረ።አውሮፓ በአጠቃላይ ወራሪዋና የሽንፈት ጽዋ የተከናነበችው ጣሊያን ደግሞ በተለይ ታመሰች ።በእዛ ሀገር ትልቅ ቀውስ ተፈጠረ።በቀደመው የዓለም ታሪክ ጥቁሮች ነጮችን የትም ቦታ በጦር ሜዳ ድል አድርገው አያውቁም።ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ በጦር ሜዳ ነጮችን ድል ያደረገች ብቸኛዋ የጥቁር ሕዝብ ሀገር ሆና በዓለም አደባባይ ስሟ ነገሰ።ደምቃ ወጣች።ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት ባሰቡበት ወቅት በሙሉም ባይያዝ እንዲህ አይነት የነጮችን ቅስም የሚሰብር ተሸናፊነታቸውን ያረጋገጠ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም ተነግሮም አይታወቅም።ክብር ለጀግኖቹ ለአንበሶቹ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ይሁን፡፡
በቁጭትና በጥቁሮች እንዴት እንሸነፋለን ስሜት የተነከኑት ጣሊያኖች ወጣቶችን መልምለው 46 ሺህ የጣሊያን ጦር አሰልጥነው አዘጋጅተው በመጀመሪያ በ11 መርከብ ቀጥሎ በ6 መርከብ ተጭኖ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ አድርገው በሚቀጥሉት ጦርነቶች እንዲሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ ተላከ።ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት ነው።የሕዳር 28/1888 ዓ/ም የአላጌው ጦርነት የዓለምን ታሪክ ለወጠ ቀየረው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፤- የአላጌው ድል የዓለምን ታሪክ የለወጠው እንዴት ነው ? መልእክቱስ ?
አቶ ጥላሁን፤- ዋናው ነገር ከአውሮፓ ጥቂት ወራሪ ፈረንጆችን በመላክ የአፍሪካን መሬት መያዝ አይቻልም የሚለውን መልዕክት ያስተላለፈ ነው።አፍሪካዊ የሆነ ለመቋቋም የሚችል ኃይል አለ የሚለውን ግንዛቤ የሰጠ ስለነበር እንደገና 46 ሺህ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር ሽንፈታቸውን ለመቀልበስ ተላከ ።
ከአላጌው ጦርነትና ድል በኋላ ቀጥሎ የምናገኘው ጥር አጋማሽ ላይ መቀሌ የተደረገውን ጦርነት ነው።የመቀሌ ምሽግ ቶሎ እንዲለቀቅ ጣሊያን አልፈለገም ።ለምን ቢባል ከጣሊያን ሀገር ተጉዘው በመርከብ የመጡት 46 ሺህ ወታደሮች አየሩን እስኪለምዱ ለበኋላው የዓድዋው ጦርነት ለምንለው አዲግራት ካለው ምሽግ ጋር እንዲለማመዱ ግዜ እንዲገዛ ጣሊያን ይፈልግ ነበር።መቀሌ ላይ እስከተቻለ ድረስ የኢትዮጵያን ጦር ገትተውት እንዲቀመጥ ይፈልጉ ነበር።
የመቀሌ ምሽግ ተጠናክሮ የተሰራ ነው።ዋናው ምሽግ አለ።ዙሪያውን ደግሞ ሶስት ትናንሽ ምሽጎች አሉ።በጥር መጀመሪያ ላይ ይመስለኛል አጼ ምኒሊክ መቀሌ ደረሱ፡፡
አዲስ ዘመን፤- ከወረኢሉ መቀሌ ድረስ ስንት ቀን ተጓዙ ?
አቶ ጥላሁን፤- አጠቃላይ ጉዞው ረዥም ግዜ የወሰደበት የምኒሊክ የሚሊተሪ ስትራቴጂና ታክቲክ በሚወስነው መሰረት ነው።አጼ ምኒሊክ አንድ ወታደር በቀን ከአምስት ኪሎሜትር በላይ እንዲጓዝ አያደርጉም።አንድ ሺህ ኪሎሜትር ተጉዞ ጦርነት ቦታው ላይ ሲደርስ ከስቶ መንምኖ ተዳክሞ ነው የሚደርሰው።ጉልበቱ ሳይደክም እንዲዋጋ ቀስ ብለው ነበር የሚወስዱት።
የዓድዋን ጦርነት ባናሸንፍ ኖሮ በቅኝ ግዛትነት እንያዛለን ማለት አልነበረም።ሰዎች እንዲህ ብለው ያስባሉ።ዓድዋን ብንሸነፍ ኖሮ ቅኝ ግዛት እንያዝ ነበር የሚባል ታሪክ የለም።ምኒሊክ የዓለምን ታሪክ ለወጡት ዓድዋ የዓለምን ታሪክ ለወጠው ስንል በአጠቃላይ የዓለምን የታሪክ አካሄድ ለወጠው ማለታችን ነው።እስከዛ ግዜ ድረስ የዓለም ታሪክ አካሄድ እንዴት ነበረ ? ይሄን ነጥብ ይያዙት።አውሮፓውያኖች አሜሪካን ደቡብና ሰሜን አሜሪካን ሲወሩ የቀይ ሕንዶችን ሬዲንዲያኖችን በሙሉ ዘራቸውን አጥፍተው ነው የራሳቸውን ዘር የተኩት።አውስትራሊያን ሲወሩ የአውስትራሊያ ነባር ነዋሪዎችን አቦርጅንስ ሙሉ በሙሉ አጥፍተው በራሳቸው ዘር ነው የተኩት።በአፍሪካም ውስጥ አጼ ምኒሊክ ከዚያም እስከ ነጭ አባይ ባዘመቱት ጦር ባይገታ ኖሮ የአውስትራሊያ ነባር ነዋሪዎችና የአሜሪካን ሬዲኢንዲያንስ እጣ ፈንታ የጥቁር ሕዝብ እድል ይሆን ነበር።ምኒሊክ የታሪክን ሂደት የቀየሩት ዓድዋ የታሪክን ሂደት ቀየረ የሚባለው በዚህ መሰረታዊ ምክንያት እንጂ ቅኝ ግዛት አልነበረም የምንያዘው።እንደ ሬዲኢንዲያንስና እንደ አቦርጅን አውስትራለያኖች ያለውን የጥቁር ዘር የመጥፋት ዕጣ አፍሪካ ያጋጥማት ነበር ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፤- የዓድዋ ድል በውጤቱ ያስገኘው ምንድነው ?
አቶ ጥላሁን፡- ዓድዋ በጦርነቱ ያስገኘው ውጤትና ሁለተኛው የአርበኝነት ተጋድሎ ያስገኛቸው ውጤቶች የተለያዩ ናቸው።ግን ተያያዥ ናቸው።ይሄ ነገር መምታታት የለበትም።ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ግዜ የታጠቀቻቸው መሣሪያዎች ከፍተኛ ነበሩ።በሁለተኛው ጦርነት ግዜ ባዶ እጃችንን ነበርን።የውጤቱ መገለጫም የተለያየ ነው።ዓድዋ የጥቁር ዘርን ከመጥፋት የታደገ ድል ነው፡፡
የሁለተኛው የኢትዮጵያ የአርበኝነት ጦርነት ያስገኘው ውጤት አንደኛ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ታጋይ መሆኗ እውቅና አገኘ።በደጃዝማች ወልደሰማያት መጽሐፍ ላይ እንደሚያዩት ጃንሆይ ሲሄዱ ገና አፍሪካ ነጻ ከመውጣቷ በፊት ስለአፍሪካ ነጻነት ከእንግሊዞቹም ከቤልጂጎቹም ጋር ይነጋገሩ ነበረ።ኢትዮጵያ ለሺ አመታት የምትመኘውን የባሕር በር አገኘች።የባሕር ኃይል አቋቋመች።የአፍሪካ ተሟጋችነቷ እውቅና አገኘ፡፡ሁለተኛው ውጤት ይሄ ነው።
አዲስ ዘመን፤- ከዓድዋ በፊት መቀሌ ላይ የተደረገው ጦርነት እንዴት ነበር?
አቶ ጥላሁን፤- መቀሌ ላይ ውብ ውብ የሆነ ጦርነት ነው የተካሄደው።አላጌ ላይ ጠዋት በ11 ሰዓት የኢትዮጵያ ወታደሮች ተንቀሳቀሱ።በአንድ ቀን ጦርነቱ አለቀ።መቀሌ ላይ አጼ ምኒሊክ ተጉዘው ደርሰዋል።አጼ ምኒሊክ ደጃዝማች አባተንና ደጃዝማች ባልቻን የጣሊያን መድፍ እንዳይነካችሁ አድርጋችሁ ምሽጉን ለመምታት ቦታ ያዙ አሏቸው።እነሱም ሶስት የጣሊያን ትንንሽ ምሽጎች ነበሩ፣ ዙሪያውን አስለቀቁና ዋናውን ምሽግ ለመደብደብ ቦታቸውን ያዙ።ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረስላሴ መጽሐፍ ላይ ነው መሰለኝ አጼ ምኒሊክ እናንተን እንዳይመታችሁ አድርጋችሁ አልሙ ብለው የሰጡትን ትእዛዝ የጻፉት። የኢትዮጵያ መድፎች የጣሊያኑን ምሽግ መደብደብ ጀመሩ።ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረሥላሴ ኃይማኖተኛ ስለሆኑ እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል።ጣሊያን ታቦቱን አውጥቶ ቤተክርስቲያኑን ምሽግ አድርጎት ስለነበረ የእኛ መድፎች ከዚህ ሲተኩሱ መስኮቱን ሰበሩት።መትረየሶችና መድፎች ሲተኩሱ ብዙ ጣሊያኖችም ሞቱ።ጣሊያኖች ደግሞ ጭሱን እያዩ ወደ እኛ የሚተኩሱት መትረየስና መድፍ በጣም ትልቅ ቢሆንም የምኒሊክ አምላክ ሸፍኖአቸው ስለነበረ ከእኛ አንድም ሰው አልሞተም ይላሉ።እንግዲህ በወታደራዊ ታሪክና አሰላለፍ ስንመዝነው የእኛ መድፎች 4800 ሜትር ይመታሉ።የጣሊያን ደግሞ 3800 ሜትር ብቻ፡፡የተማረከ የለም፡፡ገና ምሽግ ውስጥ ናቸው።የመድፍ ጦርነቱ ተጀመረ ማለት ነው።
የዚህ ግዜ ነው እቴጌ ጣይቱ ለምን የውሀ ምንጫቸውን አንይዘውም ብለው አንድ ሀሳብ ያመነጩት።ይሄን ሲያስቡ ገና ጥሬውን ያልበሰለ ሀሳብ ይዞ ንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ አይቀረብም።ስለዚህ ሊቀ መኳስ አባተን ጠየቋቸው።የውሀው ቦታ ቢያዝ ምን ይሆናል ብለው ሲጠይቋቸው እኔ የመድፍ ሽፋን እሰጣለሁ አሉ።አጼ ምኒሊክን አማከሩ።አጼ ምኒሊክም ሀሳቡ ጥሩ መሆኑ ገባቸው።ምክር ተደረገና 900 ያህል ጦር ተዘጋጀ።ከምኒሊክ ልዩ ኃይል በሚገባ የሰለጠኑትን ማለት ነው።
ምኒሊክን ልዩ ኃይሎቹን እንዲመግቡላቸው በየራሶቹ ይሰዷቸው ነበር።በእቴጌ ጣይቱ ስር ካሉትም ሆኖ 900 ተልእኮ የተሰጠው ተዋጊ ኃይል ተዘጋጀ።በሌሊት ይጓዛሉ። ከምሽጉ ወደ ስድስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ ነበሩ።እነዚህ 900 የኢትዮጵያ ወታደሮች ተጉዘው ሄደው ምንጩን ይዘው መከላከያ ምሽጋቸውን ሰሩ።በማዕከል ሁነው የእኛ መድፈኞች ሽፋን ይሰጧቸዋል።እስከዛ ግዜ ድረስ በሀገራችን የመድፍ ጦርነትም ሆነ የሌሊት ጦርነት ተካሂዶ አያውቅም ነበር።በዚያን ዘመን የነበረው ጦርነት ሁሉ ጸሐይዋ ስትጠልቅ በዛው ያልቅ ነበር፡፡
እነዚህ 900 የእኛ ወታደሮች ወደ ምሽጉ መሄድ ጀመሩ።ተመልከት እንግዲህ ።ከሌሊቱ 7.30 ሲሆን የኢትዮጵያ መድፎች የጣሊያኑን ምሽግ መደብደብ ጀመሩ።15 ደቂቃ ያህል ወቁት።ጣሊያኖቹ ምንድነው ይሄ ነገር ብለው ነቁ።ተደናገሩ።መልሰው ሸለብ ሲያደርጉ እንደገና ለትንሽ ደቂቃ የእኛ መድፎች ደበደቡ ።ይህ የመድፍ ድብደባ እየሰለሰ የጠላትን ትኩረት እየበተነ እያጨናነቃቸው የጣሊያን ወታደሮች ከምሽጋቸው ሳይወጡ በነበሩበት ሰዓት የኢትዮጵያ ተዋጊ ሠራዊት በሽፋን ቀውጢ ቦታዎችን እያለፈ ነበር።የመድፍ ድብደባዎቹ የጠላትን ትኩረት በመሳባቸውና በመበተናቸው ጠላት ከምሽጉ አልወጣም።እንደገና ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ አራት ሰአት ድረስ በተከታታይ መድፎቻችንና መትረየሶቻችን የጣሊያንን ምሽግ አደባዩት።መጨረሻ ላይ ጣሊያኖቹ ይሄ ሁሉ ነገር ምንድን ነበር ብለው ወጥተው ሲያዩ የውሀው ምንጭ በኢትዮጵያውያን ወታደሮች ተይዟል።የኢትዮጵያ ወታደሮች መዋጊያ ምሽጎቻቸውን በሙሉ ሰርተው ጨርሰዋል፡፡በዓለም ላይ ድንቅ የሆነ ጦርነት ተካሄደ።የዓድዋ ጦርነት ሲታወስ የሚዘከርበት ጉዳይ አለ።አንደኛው የዓለም ጦርነት ተነስቶ በጦር ሜዳዎች ላይ በብዛት ሠራዊት ከመግባቱ በፊት በዓለም ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሠራዊት የተንቀሳቀሰበትና የተሰለፈበት ትልቁ ጦርነት የዓድዋ ጦርነት ነው ።
አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲነሳ የአውሮፓ ጦርነት ስለነበረ ብዙ ሺህ ሠራዊት ተሰልፎአል።በዓድዋ ግዜ አንዳንዶቹ ሰዎች ሲገምቱ ሴቱ፤ ወንዱ፤ ምግብ አብሳዩ፤ ቁስለኛ አግላዩ፤ ሁሉም ሆኖ ወደ 120 ሺህ ጦር ተሳትፎአል ይላሉ፡፡
በዓድዋ ጦርነት እንደምናየው አጼ ምኒሊክ ያሰማሩት ጥቂት የሰለጠነ ጦር ብቻ ነበር።ሌላውን ለምርኮ ነው የሚሰጡት።ጆናስ የሚሉት ከእንግሊዝኛው የተረጎሙትን መጽሐፍ ካየኸው አጼ ምኒሊክ የሚልኩት ጦር ትንሽ ነው።ብዙ ሺህ ፈረሰኛው ጦር ተደራርቦ እያስገመገመ አቧራውን ወደላይ እያጎነው እየተመመ ሲሄድ ላየው ተራራ የተናደ ነው የሚመስለው።
ምኒሊክ ጦርነቱን የሚመሩት በእቅድ ነበር።አጼ ምኒሊክ በእግራቸው ሲጓዙ በጣም ፈጣን ተጓዥ ናቸው።ከዛ ውጭ በበቅሎ ነው የሚሄዱት።ሁልግዜ እቅድ ሲያቅዱ አንድ ብቻ አይደለም የሚያዘጋጁት።በሌሊት ምሽጉ ይያዛል።ፈረሰኛው ጦር በሙሉ እዚያ አካባቢ ያለውን ምንጭ ውሀ በሙሉ እንዲጠብቅ፤ ጣሊያን ምንም ውሀ እንዳያገኝ ተደርጓል።ጣሊያን በውሀ ጥም ተፈታ ፡፡ድርድር እናድርግ እያለ ትንሽ ግዜ ለመግዛት ፈልጎ ነበር።ዘዴው ያ 46 ሺህ ጦር እንዲዋሀድለት ለማድረግ ነበር።አማራጭ ስላጡ ጣሊያኖቹ እጃቸውን ሰጡ።የዛን ግዜ የኢትዮጵያ አጋር የነበረችው ራሽያ እንዲሁም እንግሊዞችና ፈረንሳዮች ሌሎቹም በሰላም በድርድር ይለቅ አሉ።በዲፕሎማሲው ዓለም የነበረና የሚጠበቅ ነው።በዚያን ጊዜ አጼ ምኒሊክ አንድ የዲፕሎማቲክ ድል መቱ።
አዲስ ዘመን፤- የዲፕሎማቲክ ድሉ ምን ነበር ?
አቶ ጥላሁን፤- አጼ ምኒሊክ የማረኳቸውን የጣሊያን ወታደሮች እስከ መሣሪያቸው ሂዱና አዲግራት ምሽጋችሁ ግቡ።በሰላም ካለቀ አለቀ።ካላለቀ ኑና እንደገና እናንተም ግጠሙኝ ብለው ሰደዷቸው።ለጠቁና እንግዲህ አሁን እኔ ይህን አድርጌአለሁ።ጣሊያን እርቅ ያድርግ አሉ።
ጣሊያን ለመታረቅ አይፈልግም፡፡እንግሊዞቹም ፈረንሳዮቹም እንዲታረቁ አይፈልጉም።ምክንያቱም ውላቸው አፍሪካን መቀራመት ነው።ለግዜውም ቢሆን አጼ ምኒሊክ ይሄንን ዲፕሎማቲክ ድል አገኙ፡፡
አዲስ ዘመን፤- የዓድዋ ጦርነት ለዓለም ምን ትምህርት ሰጠ ?
አቶ ጥላሁን፤- አንደኛ የዓለምን ጥቁር ሕዝብ ዘር ከመጥፋት አዳነ።ሁለተኛው በዓለም ላይ ተጨቁነው የነበሩ እንደ ሀገር የተቋቋሙ የነበሩ ለምሳሌ በቱርክ ስር የነበሩት እነ ቡልጋሪያን የመሳሰሉትን ሀገሮች ሁሉ የአጼ ምኒሊክ ድል በጣም አስፈነደቃቸው።ልጆቻቸውን ሁሉ ምኒሊክ እያሉ መሰየም ጀመሩ።ዓድዋ በዓለም የነጻነት ምሳሌ ሆነ፡፡
አዲስ ዘመን፤- የዓድዋው ጦርነት አሰላለፍ እንዴት ነበር ?
አቶ ጥላሁን፤- ዓድዋ ላይ ጣሊያን ከምሽግ አልወጣም አለ።ከምሽግ እንዲወጣ ንጉሥ ሚካኤል፤ ራስ መኮንን ጠየቁት።ከምሽግ ወጥታችሁ ብትዋጉ እኛ ከጣሊያን ጋር እንሰለፋለን፤ምኒሊክን እንክዳለን እያሉ የማስመሰል ደብዳቤ መጻፍ ጀመሩ።
ከዛ በፊት ጀነራል ባራቴሪ አበሾች ከንጉሣቸው ጋር እየተባበሩ የውሸት መረጃ እንደሚጽፉ አውቆአል።ራስ መንገሻም ከምኒሊክ ፤ አጼ ምኒሊክም ከአጼ ዮሀንስ ጋር እየተባበሩ የሚያደርጓቸውን ደብዳቤዎች ተረድቶአል። ሰናፌ ላይ ከራስ መንገሻ ጋር ጦርነት ገጥሞ ሳለ በአገልግል የያዙት ደብዳቤ ተማርኮ ምስጢሩን አውቆታል።ስለዚህ ምንም ቢሉትም አያምንም።
ጦርነቱን አምስቱ ጀነራሎች ስብሰባ አድርገው ነበር።ዋናው አዛዥ ጀነራል ባራቴሪ፤ ጀነራል አልቤርቶኒ የተገደለው ፤ ጀነራል አርሞንዲ አላጌ ላይ ሊያግዝ የመጣው ፤ጀነራል ዳቦር ሜዳ ጦርነቱ ላይ የተገደለው ነው።ከእነሱ ውስጥ ጀነራል አልቤርቶኒ ብንዋጋ ይሻላል አለ፡፡ጀነራል ባራቴሪ ማፈግፈግ ነው የሚሻለው ከምንዋጋ ብሎ ነበረ።ጀነራል ኤሌኒ የሚባል አዲስ የመጣ ነበረ እሱ ብናፈገፍግ ጥሩ ነው አለ።ሌሎቹ ሶስቱ መግጠም ነው ያለብን።ምኒሊክ ያለው 15 ሺህ ብቻ የሠለጠነ ጦር ነው፡፡እሱም ለሁለት ተከፍሎአል አሉ።
ለሁለት ተከፍሎአል ያሉት ወደ ምዕራብ የሄደውን የምኒሊክን ሠራዊት አላወቁም ።ጣሊያንን አውሣ ላይ ለመዋጋት የሄደውን የራስ ወልደጊርጊስን ጦር አስበው ከ15 ሺው ለሁለት ተከፍሎበታል በቀላሉ ድል እናደርገዋለን ብለው ወሰኑ።
በመጀመሪያው ቀን ጦርነቱን ለመክፈት ያሰቡት የካቲት 22/1888 ዓ/ም ቀን ላይ ነበር።ኃይለኛ ዝናብ ሆነና ቆመ።አጼ ምኒሊክም የካቲት 22 ጣሊያኖች ለጦርነት እንደሚመጡ ሰምተው ነበረ ።ስለዚህ ፈረሰኛውና የራስ መኮንን ጦር ለጦርነቱ እንዲዘጋጅ ወደ ዓድዋ እንዲሄድ አደረጉ።የዛን ግዜ ቤተክርስቲያን ለመሳም ነው ሰው የሚሄደው ተብሎ ተወራ ።ጣሊያኖችም በቃ አይወጉንም ጭራሹንም ቤተክርስቲያን እንዲስሙ እየሰደዱ ነው አለ።በ21 ማርያም ጽዮን ስለሆነች ለመሳለም ተብሎ ቄሶቹ አጼ ምኒሊክ ጋ መጥተዋል ።እቴጌ ጣይቱ ዘንድ ነው ያሉት።ይህ በሰፊው ተወራ።በዝናቡም ምክንያት ጣሊያን ያሰበው ጦርነት አልተሳካም።
የካቲት 23/1888 ዓ/ም ጣሊያኖች እውነተኛውን የጦርነት ዘመቻ ከፈቱ።አመጣጣቸው በሶስት አቅጣጫ የተከፈለ ነው፡፡ቀዳሚው የጀነራል አልቤርቶኒ ጦር ነው።የአልቤርቶኒ ጦር በኪዳነምህረት በኩል አድርጎ ሲመጣ የመጀመሪያውን የተኩስ ልውውጥ ከራስ መንገሻ ጦር ጋር አደረገ።በእለቱ ዙሪያ በሩን የመጠበቁ ተረኛነት የእሳቸው ነበር።አሁን የምር መምጣታቸው ታወቀ።
በዚያ በኩል ላለፈው የጣሊያን ጦር የእኛን መድፎች ከፍታው ቦታ ላይ አውጥተው እንዲጠመዱ አደረጉ።የአልቤርቶኒን ጦር መደብደብ ጀመሩ።የአልቤርቶኒም ጦር ተጠናክሮ ገፋ።ይሄን ግዜ ነው ፊታውራሪ ገበየሁ ትልቅ ጨዋታ የሚጫወቱት።ያንን ቀይ ለብሰው ነው የሚወጡት።ቅኝ ግዛትን ለመከላከል አብሮ የሚሰለፍ ሕዝብ ሁሉ መሪዎቹ ቀይ ልብስ ይለብሳሉ።ጃኖ ይሠጣቸዋል።ፊታውራሪ ገበየሁ ቀይ ልብሳቸውን ለብሰው እንዴት እንደተዋጋሁ ለሀገሬ ሕዝብ ንገሩ!! ለሸዋ ሰው ንገሩ !! ብለው ከወታደሮቻቸው ጋር ገስግሰው ፊት ለፊት ገቡና መትረየሶቹን መድፎቹንም ጸጥ አደረጓቸው ።እሳቸውም ተመተው በጀግንነት ወደቁ።የዚህን ግዜ ድሉ እየተረጋጋ የአልቤርቶኒ ጦር እየደከመ ሄደ።
የዚህን ግዜ አጼ ምኒሊክ ቀይ ጃንጥላ ያስይዛሉ አይደል አባ ተምሳስ የሚባሉ ሊቀ መኳሳቸው አሉ።እሳቸውን መስለው የሚቀመጡ።ልክ እሳቸው የመድፉ አረር የማይደርስበት ጋ ሲደርሱ አጼ ምኒሊክ ትተዋቸው በመደበኛ አለባበስ ጉዞ ጀመሩ ።ጣሊያኖቹም እንደሚሉት ተራራዎቹን ወጥተው ከፍታውን ቦታ ይይዙና ከዛ በኋላ በሁለቱ ጄኔራሎች መሀከል ያለውን አምስት ሺህ ሠራዊት በግራ፤ በቀኝ አምስት ሺህ ሠራዊት በግራ ይከፍሉና በአጠቃላይ አስር ሺህ ሠራዊት እንዲዋጋ ያስገባሉ።በኋላም ተራራው ጫፍ ላይ ወጥተው ሁለቱን ትልልቅ ከፍታዎች እንዲያዙ አድርገው የጀነራል ዳቦር ሜዳንና የጀነራል አርሞኒዲን ጦር ግራ ቀኝ መተው አሸነፉት።
ይሄ ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ ብዙ ሰዓታት አላለፉም።እስከ ሌሊቱ 6 ሰአት ድረስ ሠራዊቱ ሲመለስ ነበረ ። ከሰዓት በኋላ ወደ 9 ሰአት ግድም ጦርነቱን እየጨረሱ ነበር። እቴጌ ጣይቱ ወ/ሮ ዘውዲቱ ምኒሊክ ሌሎቹም ሴቶች ሁሉ ሆነው አባ ተምሳስ ጃንጥላውን ይዘው የደረሱበት ጋ ሁነው ጦርነቱ ድል ሲያደርግ በተኩሱ የቆሰሉትን ኢትዮጵያውያኖችንና ጣሊያኖቹንም ያክሙ ነበር፡፡ሌሎቹም ውሀ በእንስራ ይዘው ለሁሉም ያጠጡ ነበር።
እየመሸ ሄደና አሥራ አንድ ሰአት ሆነ፡፡እቴጌ ጣይቱ ይሄ ነገር ምንድነው ብለው ለአጼ ምኒሊክ መልዕክት ላኩ።እንዴት ነው ነገሩ ሲሉ እሳቸውም መልሰው መልስ ላኩ።ወደ ግራ በኩል ትንሽ ተኩስ እሰማለሁ።ጦርነቱ ግን አልቆአል እንመጣለን ብለው አሉ።እቴጌ ጣይቱም ወደ ዙፋናቸው ተመለሱ።አጼ ምኒሊክም ወደማታ መጡ።ራሶቹና ሌሎቹም ተከተሉ።በኋላ ፈረሰኛው ጦርነት ውስጥ እንዲገባ እንዲማርክ ተደርጓል።
እነ ጄኔራል ዳቦር ሜዳ የሞቱት ሸሽተው ሄደው ኤርትራ ውስጥ ነው።ገበሬው ይማርካል።ይገላል።ጦርነቱ በዚህ አይነት መልኩ አለቀ።
አጼ ምኒሊክ አራት ቀን ሬሳ ካስቀበሩ በኃላ መቀሌ ላይ ሁነው ወደ አሥመራ ለመሻገር መንገድ ያሰልሉ ጀመር።የዚህን ግዜ ነው ለውጡ የመጣው።እንግሊዝ ኪችነር በሚባለው የጦር አዛዥ የሚመራ ከእንግሊዝና ከግብጽ አንግሎ ኢጅብሽያን የምንለው በጣም ዘመናዊ የማክሲም መትረየስና መድፎች የታጠቀ ጦር አስገባች።
የዛን ግዜ መሀዲስቶቹ የያዙትን የከሰላን ምሽግ ጣሊያን ለእንግሊዝ አስረከበች።የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ አንድ ግዜ የዓድዋውን ሽንፈታችንን የሚቀይር ጦርነት አድርጉ ከዚያ በኃላ እኔ በእርቅ እጨርሰዋለሁ ሲል ወተወተ፡፡ወኔውን አጡ፡፡ከዚያ በኋላ ጦርነቱ ተለወጠ።ፈረንሳይ በጅቡቲ በኩል ኢትዮጵያ መሣሪያ እንዳታስገባ ዘጋች።የብራስልሱ አፍሪካን የመቀራመቱ ውል ስራ ላይ መዋል ጀመረ።እንግሊዝ ጣሊያንን በማገዝ ወደ ጦርነቱ ገባች።
በዚህን ግዜ አጼ ምኒሊክ መቀሌ ላይ እያሉ ከመሀዲስቶቹም ከራሽያም ደብዳቤ ደርሷቸው ነበር።በአሁኑ ግዜ ጣሊያኖች ደካማ ስለሆኑ ጦርነት አድርገው እንግሊዞችን ነው መምታት ያለብዎት የሚል ነው፡፡መሀዲስቶቹም እየተሸነፉ ስለነበር የኢትዮጵያ ጦር እንዲያግዛቸው ይፈልጉ ነበር፡፡ከደከመው ጣሊያን ጋር የእርቅ ስምምነት አድርገው ከብሪታኒያ ጋር ለመገዳደር ጦራቸውን ወደ ነጭ አባይና ታች ወደ ቪክቶሪያ ሀይቅ ሲያሰማሩ እናያለን።ጣሊያን ግን ተሸነፈ።
አዲስ ዘመን፤- ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን፡፡
አቶ ጥላሁን ጣሰው፤- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013 ዓ.ም