ወርቁ ማሩ
የ19ኛው ክፍለዘመን መባቻና የ20ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ ነጮች በተለይ አውሮፓውያን አፍሪካውያንን ቅኝ በመግዛት በሃይል ማንበርከክና ሃብታቸውን መዝረፍ እንደ ትልቅ እቅድ ይዘው የተሰማሩበት ወቅት ነበር።በዚህ የተነሳ አብዛኞቹ አውሮፓውያን በተቻላቸው መጠን ፊታቸውን ወደአፍሪካ በማዞር ጥቁሮችን ለማንበርከክና በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ በየአቅጣጫው የዘመቱበት ዘመን ነበር።በዚህም አብዛኞቹ ተሳክቶላቸው አፍሪካን በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ ችለዋል።ይሄን ተከትሎም ወቅቱ የነጮች የበላይነት ትክክል ነው የሚለው አስተሳሰብ በመላ አውሮፓውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በተገዢ የአፍሪካ አገራትም ጭምር የናኘበት ዘመንም ነበር፡፡
ከነዚህ አገራት መካከልም ጣልያን አንዷ ነበረች።በዘመኑ ጣልያን ለቅኝ ገዢነት ከመረጠቻቸው አገራት አንዷ አፍሪካዊት አገር ደግሞ ኢትዮጵያ ነበረች።እናም ዘመናዊ መሳሪያና ብዙ ሺህ ወታደር ይዛ ወደ ኢትዮጵያ ዘመተች።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን ለጠላት እጅ የመስጠት ባህል የላቸውምና ያንን በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የተደራጀ ወራሪ ሃይል አንበርክከው እንዳልነበር በማድረግ አዲስ ታሪክ ፃፉ፤ ይህ ድል ታዲያ በዘመኑ በመላ አውሮፖ ትልቅ ድንጋጤን የፈጠረ፣ በአንፃሩ በጥቁር ህዝቦች ዘንድ ደግሞ አዲስ የነፃነት ተስፋን የፈነጠቀ የነፃነት ምዕራፍ ነበር።እነሆ ይህ ድል ከተመዘገበ 125 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ዘንድሮ የዓድዋ ድል ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ሁኔታ በአፍሪካውያን ጭምር የሚከበር ሲሆን፤ በአገራችንም በደማቅ ሁኔታ ሲከበር ቆይቶ ዛሬ የማጠቃለያ መርሐግብር ይካሄዳል።
እኛም በዓድዋ ድል ዙሪያ በተለይ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የመጣችባቸውን ታሪካዊ ሁነቶችና መንገዶች አስመልክቶ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቅርስ ጥበቃ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በከሪ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ የተለያዩ የግዛት ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ አንዳንዶች የኢትዮጵያ ግዛት እስከ ሩቅ ምስራቅ ድረስ ነው፣ አንዳንዶች እስከ የመን ድረስ፣ ከፊሉ ደግሞ ምስራቅና ሰሜን አፍሪካን አካሎ ያለውን ግዛት ሁሉ ያጠቃለለ ነው ይላሉ።ለመሆኑ የታሪክ ምሁራን የኢትዮጵያ ቅድመ ታሪክ እስከ የት ያለውን ግዛት የሚያጠቃልል ነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- የኢትዮጵያ ግዛት አንዴ ሲሰፋ፤ ሌላ ጊዜ ሲጠብ የኖረው ነው።ስለኢትዮጵያ ስንናገር ኢትዮጵያ የጥንት፣ የመካከለኛና የዘመናዊ ታሪክ ያላት አገር ናት።በዚህ መሰረት አሁን የምናውቃት ኢትዮጵያ ያንን ስም የወሰደችው ከአምስተኛው መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ ነው።
በወቅቱ በሒብሩ ቋንቋ ውስጥ ኩሽ የሚል ቃል ነበር።ይህ ቃል ካሳ የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን መጽሃፍ ቅዱስ ወደግሪክ ሲተረጎም ቃሉም አብሮ መጣ።በዚህ ወቅት ታዲያ ቃሉ ኢትዮጵያ ከሚለው ቃል አቻ ሆኖ አብሮ ይነገር ነበር።ከዚያ በኋላ መፅሃፍ ቅዱስ ከግሪክ ወደግዕዝ ሲተረጎም ኢትዮጵያ የሚለው ቃል አብሮ መጣ።
ኢትዮጵያ የሚለው ከመወሰዱ በፊት የአክሱም ስርወ መንግሥት ነበር።እና ክርስትና ከመግባቱ ጋር ተያይዞ ነው ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ አሁን የያዘውን ማንነት ይዞ የመጣው ማለት ነው፡፡
ከዚያ በፊት ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረውን ስናይ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል አብዛኛው አፍሪካን የሚወክል ነበር። በወቅቱ እንግዲህ ይታወቁ የነበሩት በሰሜን በኩል ማህገረብ የሚባለውና አብዛኛውን ሰሜን አፍሪካ የሚይዘው ሊቢያ የሚለው ስያሜ ሲሆን፤ ሌላው ግብፅ ነው፤ ከዚህ ውጭ ያለው ግን ኢትዮጵያ የሚል ስያሜ ነበረው።ስለዚህ አፍሪካ በነዚህ ሦስት ስያሜዎች የተጠቃለለ ነበር፡፡
የጥንት ፀኃፊዎች አፍሪካ በሁለት የተከፈለ እንደነበር ያነሳሉ፤ ምስራቅና ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚልም ይጠራ እንደነበርና እስከ ህንድ ውቅያኖስ ያለውን እንደሚያካትትም ፅፈዋል። ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያ የሚለው በጣም በጥንት ስያሜው አፍሪካንና ከፊል ኤሽያን የሚያጠቃልል ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ በነበረው የግብፅ የስልጣኔ ዘመን የግብፅ 25ኛው ስርወመንግሥት ኢትዮጵያ በሚል ይጠራ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።ይህ 25ኛው ስርወመንግሥት ደግሞ ግብጽን፣ ሱዳንንና የታችኛው አፍሪካ አገራትን የሚያጠቃልልና ትልቁና ረጅሙ የግዛት ወሰን እንደነበርም ይጠቀሳል፡፡
ከላይ እንዳልኩት ኢትዮጵያና ኩሽ ተቀያያሪ ስያሜዎች ነበሩ።የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት የአክሱም ስርወመንግሥት ነው።ሌሎችን እየወጋ እያስገበረ የገዛ መንግሥት ማለት ነው።ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁን ካለው በተለየ ሁኔታ ሰፊ ግዛት ያካተተ እንደነበር የታሪክ ድርሳናቱ ይጠቁማሉ፡፡
በዘመናዊ ኢትዮጵያ ግን ህጋዊ በሆነ ሁኔታ መንግሥታት በተፈራረሙት ስምምነት መሰረት የተደረሰበት ድንበር ነው።ለምሳሌ አፄ ሚኒልክ በሱዳን፣ በኬንያ እና በሱማሌ በኩል ከእንግሊዞች ጋር የተፈራረሙት የድንበር ስምምነት አለ።ይህ የ19ኛው ክፍለዘመን ስምምነት ነው።
አዲስ ዘመን፡-ኢትዮጵያ በታሪኳ ከተለያዩ አገራት ጋር ጦርነት አካሂዳለች፤ ከአውሮፓ ከመጡ ወራሪዎች ጀምሮ እስከ አፍሪካዊቷ ግብፅ ድረስ በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያን ለመውረር ሞክረው እንደነበር ይነገራል፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ያደረገቻቸው ጦርነቶች ምክንያታቸው ምን ይሆን?
ተበባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- የኢትዮጵያ ታሪክ ከኋላ ጀምረህ ስታይ ወደጦርነት የገባችው ራሷ ፈልጋ ሄዳ ሳይሆን ከውጭ በመጣባት ግፊት ነው፡፡ኢትዮጵያ ሄዳ የወሰደችው አንድም ግዛት የለም።በርግጥ አፄ ሚኒልክ የኢትዮጵያ ግዛት እስከ ካርቱምና ዩጋንዳ ድረስ እንደሚዘልቅ ይገልፃሉ።በዘመኑ እነዚህ አገራት ከሚገዙት ቅኝ ገዢዎች ጋር የተለያዩ ንግግሮች አድርገዋል፤ ተወያይተዋል፤ ስምምነትም አድርዋል።ነገር ግን ወደጦርነት አልገቡም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ እነዚህን ጦርቶች በአሸናፊነት መወጣቷ ምን አንድምታ አለው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡– ነፃነታችንን ጠብቀን በነፃነት ለመኖር መቻላችን አንድ ትልቅ ነገር ሲሆን በዓለም ላይ በቅኝ ግዛት ስር ያልወደቀች አገር በመባል መታወቁም ሌላ ነገር ነው፡፡ይህ ደግሞ ለራስ ማንነታችን ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነት አገራቸውን ለመጠበቅና ጠላት ሲመጣ በአንድነት ለመመከት እንዲነሱ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኗቸዋል።በአጠቃላይ በኢትዮጵያዊነታችን እንዳናፍርና ለዚያ የሚሆን ማንነት እንዲኖረን በማድረግ ትልቅ ፀጋ አጎናፅፎናል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ስሟ ከፍ አድርገው ካሳዩ የጦርነት ታሪኮች አንዱ የዓድዋ ድል እንደሆነ ይታወቃል፤ ለመሆኑ ይህ ድል ለኢትዮጵያና ለሌሎች ጥቁር ህዝቦች ያለው እንድምታ ምንድነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- የዓድዋን ድል ትልቅነት ለመገንዘብ አፍሪካውያን ያንን ቅኝ ግዛት ለመቋቋም ያደረጉትን እንቅስቃሴ ማየት ይገባል፡፡አንደኛ ብዙ አገሮች በቅኝ ግዛት ስር ላለመውደቅ በርካታ ትግሎችን አካሂደዋል።ለምሳሌ፣ ሳሞራ ቱሬ የተባሉ የወቅቱ የማሊ መሪ በቅኝ ግዛት ስር ላለመውደቅ 17 ዓመታት ከፈረንሳይ ጋር ተዋግቶ በመጨረሻ ተሸንፏል።ያኔ ታዲያ ማሊ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ጭምር ነበራት።አልጄሪያ “ዋር ኦፍ ኢንዲፐንደንስ” በሚል ከፈረንሳይ ጋር 18 ዓመታት ተዋግታለች።ዛንዚባር ደግሞ በ30 ደቂቃ ተሸንፋለች፡፡
በተጨማሪም የዘመኑ የአውሮፓ ምሁራንና የተማሩ ዜጎች የስነልቦናና የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን፣ ወዘተ ይህን በህዝብ ውስጥ ያሰረፁበት ወቅት ነበር።እነዚህ ሁሉ ታዲያ ነጮችን ማሸነፍ አይቻልም የሚል የፍራቻ ስሜት እንዲነግስ ያደረገበት ሁኔታ ነበር የፈጠረው።ስለዚህ ለመኖር የፈለገ የነጮቹ ሁለተኛ ዜጋ መሆን የግድ ነው የሚል የተሸናፊነት የሞራል የበታችነት በተፈጠረበት ዘመን ነው ዓድዋ የመጣው፡፡
በወቅቱ ታዲያ ጣልያን ልክ እንደፈረንሳይ ቅኝ ግዛቷን የማስፋት ተልዕኮ ስለነበራትና የነጮቹ የበላይነት ስነልቦናም ስለነበር በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችው ወረራ በዚህ ጊዜ የተከሰተ ነበር።ከዚህ በመነሳት የዓድዋ ጦርነት በጣልያንና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ነው ማለት ይቻላል።አውሮፓውያን እንደ ቅኝ ገዢ ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ እንደአንድ ጥቁር ተገዢ አገር ነበር የተሰለፉት።በዚህ ጊዜ ታዲያ ጣልያን በዚህ ሁኔታ መሸነፋቸው በመላ አውሮፓና ቅኝ ገዢዎች ዘንድ ትልቅ ድንጋጤ ያመጣና ሌላ አዲስ እይታን ያሳየ ነበር።ስለዚህ ድሉ ትልቅ ትርጉም ነበረው፡፡
አዲስ ዘመን፡-ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ለድል የበቃችበት ሚስጢር ምንድነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- እንግዲህ የአሸናፊነቱ ዋና ምክንያት የኛ ማንነት ነው።እኛ እንዴት እንደምንኖር፣ ርስ በርሳችን ያለን ተግባቦት፣ ስነልቦናችን፣ ህልማችን፣ ወዘተ ሁኔታ የሚገልጽ ነው።ሃገራችን የተለያዩ ማንነቶች ያላቸው ህዝቦችን የያዘች አገር ናት፤ በብሄር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ወዘተ፣ የተለያየ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ነን።ነገር ግን እነዚህን ሁሉ የሚያቅፍ ኢትዮጵያዊ ማንነት ያለን ህዝቦች ነን።
እኔ ከዚህ ብሄር ነኝ አልሄድም፣ እኔ ከዚህ ሃይማኖት ነኝ አልሄድም አላለም።በአጠቃላይ ሁሉም ጥልቅ በሆነ ሁኔታ የተሳሰረ ህዝብ ሌላ መጥቶ ያንን ማንነት ሊያፈርስበት ባለ ጊዜ ያ ማንነት ከሚፈርስ ሞቴን እመርጣለሁ ብሎ በፈቃደኝነት ሄዶ ተዋግቶ ያን ማንነቱን አስረግጧል ማለት ነው።
በዘመኑ ከግብር ጋር በተያያዘ የተለያዩ አተካራዎች፣ ግጭቶች እና ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ።ያን ለማስገበር የማዕከላዊ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ የነበረበት ሁኔታ ነበር።ነገር ግን በሃገር ጉዳይ ላይ እንደዚያ አይነት አደጋ ሲመጣ ያንን ወደጎን በመተው ነው ሁሉም ሃገር ሲኖር ነው እኔ መኖር የምችለው ብሎ በአንድነት የተነሳው።እና ያ ድል ትልቅ የአንድነት ስሜት የፈጠረ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዓድዋ ኢትዮጵያዊ አንድነትን አጠናክሯል ማለት ይቻላል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- አዎ በደምብ ነው ያጠናከረው።የዓድዋ ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የቀደሙ ጉዳዮቻቸውንና ልዩነቶቻቸውን ሁሉ ወደጎን ትተው በአንድነት የተዋጉበትና ያሸነፉበት ስለሆነ ኢትዮጵያ በሚለው ላይ የጋራ አቋም እንዲይዙ አድርጓል።ኢትዮጵያ ከዓድዋ በኋላ የሸዋ፣ የጎንደር፣ የአርሲ፣ የጅማ፣ የትግራይ፣ የጎጃም ፣ ወዘተ ብቻ አልነበረችም።
ሁሉንም ያካተተ ነው የሆነው።ስለዚህ ትርጉሙ ሰፋ።ከዚህ አኳያ የዓድዋ ትግልና ድል የኢትዮጵያዊነትን ለተወሰኑ አካላት ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን የሁሉም እንዲሆን አደረገ።የኛ ዘመናዊነትም በጉልህ መገለጽ የሚጀምረው ከዚያ ነው፡፡ስለዚህ የተገኘው ድል ኢትዮጵያዊነትን ያገዘፈ ነው፡፡
በሌላ በኩል ጦርነቱ ሲካሄድ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ቋንቋ ቢናገሩም፣ የተለያየ ማህበራዊ መሰረት እና ሐይማኖት ቢኖረውም ያለመናበብ ችግር አልገጠማቸውም ነበር።የኢትዮጵያ ጦር ያለምንም ችግር ይግባባና ይናበብ ነበር።በአንፃሩ አንድ ቋንቋ የነበራቸው ጣልያኖች መናበብ አልቻሉም ነበር።
በወቅቱ ጣልያን በሦስት ግንባር ጦርነት የከፈተች ሲሆን እነዚህ ግንባሮች ርስ በርስ እንኳ ለመናበብ ትልቅ ክፍተት ነበረባቸው።ስለዚህ ኢትዮጵያ እነዚህን ሦስት ሃይሎች ለይታ ለመምታት ትልቅ አጋጣሚ ተፈጥሮላት ነበር።እናም ያ ረጅም ታሪካችን እዚያ ቦታ አድርሶናል ማለት ነው።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ከብዙ ዓመት በኋላ ማይጨው ላይ ለምን ዓድዋን መድገም አልቻለችም የሚለው ጥያቄ ይነሳል።ለዚህ ዋናው ምክንያት ባገኘነው ድል መሰረት ራሳችንን ወደፊት ማስኬድና መለወጥ አለመቻላችን ነው።በወቅቱ ጣልያኖች ተሸንፈው ከሄዱ ጀምሮ የቤት ስራቸውን ነው የሰሩት።
መሳሪያቸውን አስተካከሉ፣ የተሸነፉበትን ምክንያት አጠኑ።እኛ ግን በዚያ ልክ አልሄድንም፡፡ከዚያ ይልቅም አንዱ ራስ ከሌላኛው፤ አንዱ አካባቢ ከሌላኛው ጋር ሲነታረክ ባለንበት ቆመን ጠበቅናቸው።እናም የማይጨው ጦርነት ተቀምጠን የመጠበቃችን ውጤት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት ዘመን አንድነቷ ተበታትኖ፣ በየቦታው በነበሩ መሳፍንትና የጦር አበጋዞች ስትመራ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ መልሳ አንድ በመሆን የፋሽስት ኢጣልያን ጭምር ድል ማድረግ ችላለች፤ ለመሆኑ በወቅቱ ለኢትዮጵያ አንድነት መፈጠር የነበረው ዋነኛ መነሻ ምን ነበር፤ እውን አንድነት የመጣው በሃይል ነው ወይስ ቀድሞውንም የአንድነት ስሜቱ ስለነበረ ነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- የኢትዮጵያ አንድነት በሃይል ነው እየተጠናከረ የመጣው።ነገር ግን በዘመኑ ትንንሽ ሃይሎች ይኖሩና እነዚያ ሃይሎች ተራ በተራ አንዱ ሌላውን የሚያጠቃበት ሁኔታ ነበር።ይህ ደግሞ የሃብት ብክነት ጭምር የሚያስከትል ነው።ለምሳሌ በመካከለኛው ዘመን ከዘመነ መሳፍንት ዘመን በፊት ጠንካራ መሪዎች ነበሩ።እንደሚታወቀው ከዚያ በፊት አስገባሪ ስርዓቶች ስለነበሩ ማስገበር የግድ ነበር።መሪዎቹም ተንቀሳቃሽ ስለነበሩ በየሄዱበት አስገድደው ነው የሚስገብሩት።በዘመነ መሳፍንትም ቢሆን የንጉሡን ስርዓት ብዙም አልተፈታተነም፡፡
በወቅቱ የፖለቲካ አካሄዱ ብዙ ፉክክሮች የነበሩበት ነበር።ይህ ግን በቀጥታ ከሃይማኖት ጋር የተገናኘ አልነበረም።ከኢብን አህመድ ጋር ክርስቲያኖች ነበሩ፤ ከአፄ ልብነድንግል ጋርም ሙስሊሞች ነበሩ፡፡በአጠቃላይ እንዲህ አይነት ግጭቶችና አካሄዶች በሂደት ዘመናዊነት እየተላበሱና በህግ እየተመሩ ነው ዘመናዊ እየሆኑ የመጡት።እና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የመመስረት ጠቀሜታውም ይኸው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያዊነት እየደበዘዘ እና የብሄር ማንነት እየጎላ እንዲሄድ መደረጉን ብዙዎች ይናገራሉ፤ ለመሆኑ ይህ ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ይሆናል ብለው ያስባሉ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- አንዳንድ ጊዜ በጥሞና ወደኋላ ሄደን ታሪኮቻችንን መመርመር አለብን።አሁን አንዳንድ አደጋዎች ይታያሉ።ለምሳሌ፣ አንድ ሰው የፖለቲካ ድርጅት ሲፈጥር እነዚህን እነዚህን መመሪዎች ተከትዬ ነው የምሰራው ብሎ ነው።ስለዚህ ያንን የፖለቲካ ድርጅት እኔ መመሪያውን አይቼ ጥቅሜን የሚያስከብርልኝ ከሆነ ልቀላቀለው እችላለሁ።ነገር ግን ይህ የፖለቲካ ድርጅት በቋንቋ ወይም በዘር በሚሆንበት ጊዜ ለጥያቄዎቹና ፍላጎቶቹ ወሰን ይፈጠርለታል፡፡
ለምሳሌ፣ ፋሺዝምን ስንመለከት ከኛ በስተቀር ሌላው ሰው አይደለም በሚል እሳቤ ነው የተፈጠረው።ይህ ደግሞ የቡድንተኝነት ስሜትን ይፈጥራል።ስለዚህ ስትደግፍም፣ ስትጠላም በቡድን ይሆናል ማለት ነው።ግለሰብ መብቱ ሳይጠበቅ፣ ሰፋ ያለ ፍላጎት ሳይኖር፣ ወዘተ ማለት ነው።ለምሳሌ ክልል የተፈጠረው ባለፉት ሰላሳና ዓርባ ዓመታት ነው። ክልል የሚባለው ደግሞ ፌዴራል ስርዓቱ ሊቆጣጠረው ካልቻለ አደጋ እንደሆነ በተጨባጭ አይተናል።
ከዚህ አንጻር እኛ ዛሬ ላይ ከታሪካችን ትምህርት ወስደን ማስተካከል አለብን።ይህ ሳይሆን ቀርቶ የቡድን ስሜቱ ብቻ እያደገ ከሄደና ያንን ብቻ የሚያስጠብቅ ከሆነ ግጭት የመፈጠር እድሉ እየሰፋ ይሄዳል ማለት ነው።ስለዚህ የተሻለ ነገር ለማምጣት አሁን በተያዘው አካሄድ መሄድ ያስፈልጋል።ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተሻለና ለሁሉም የሚጠቅም ነገር መፍጠር አለብን፡፡
በሃገራችን አንድ ኢትዮጵያዊ በሁሉም አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ መስራትና መኖር መቻል አለበት።በእያንዳንዱ ክልል ውስጥ ህገመንግሥት እየፈጠርክ እና በዚያ ህገመንግሥት ውስጥ የምትጨምረው ነገር ሌላውን የሚያገልል ከሆነ አደጋ ነው።እዚያ ክልል ተወልደው ዘራቸው ወይም ቋንቋቸው ብቻ የተለየ በመሆኑ የምታገልላቸው ከሆነ ያ ወደግጭት ያመራል፤ አሁን በመተከል የሚታየውም ይኸው ነው፡፡ስለዚህ ይህንን በጥሞና አይተን ማስተካከል አለብን፡፡
እኔ በአሜሪካ ለብዙ ዓመት ኖሬአለሁ።በዚያ የሚከተሉት የፌዴራል ስርዓት ነው።ነገር ግን በዚያ ፌዴራል መንግስቱ የበላይ ነው።በአንዳንድ ጉዳዮችም የሚወስነው የፌዴራል መንግሥት ነው።ከዚህ ውጭ ግን ክልሎች ከአቅማቸው በላይ ከተንሰራፈፉ አደጋ ነው።ስለዚህ በግልፅነት እየተወያየንና እየተከራከርን ችግሮቻችንን እየፈታን መሄድን መለማመድ አለብን።ለምሳሌ፣ አንድ ሰው በአንድ ክልል ውስጥ ሲኖር “አናሳ ስለሆነ መምረጥ አይችልም” የሚለው ነገር መታየት አለበት።
ለአብነት ብንወስድ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉምዝ በቁጥር ከፍተኛ ነው።ከዚያ ቀጥሎ ግን ያለው አማራ ነው።አማራ ግን ድምፅ መስጠት አይችልም።ስለዚህ እንዲህ አይነት ፍትሃዊ ያልሆኑ ነገሮች እንዴት ነው በዚህ አገር አንድነትና ሰላምን ሊያመጡ የሚችሉት።ስለዚህ በዚህ ሃገር መነጋገርና መስተካከል ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ስለዚህ ዓድዋ ለዚህ ትልቅ ትምህርት ሊሆነን ይገባል።በዓድዋ ሐይማኖት፣ ቋንቋ ብሄር ወዘተ አልገደቡንም።
ስለዚህ ቋንቋ የፖለቲካ ድርጅት መፍጠሪያ መሆን የለበትም።ደቡብ አፍሪካ ዘጠኝ ቋንቋዎች የሃገሪቱ የስራ ቋንቋዎች ናቸው።ስለዚህ ቋንቋ ለሁላችንም ሊያገለግለን የሚችል መሆን አለበት።አሁን አሁን እኮ ሁለት ወጣቶች በኳስ ሜዳ ሲጣሉ ሁለት ልጆች ተጣሉ ሳይሆን ሁለት ብሄሮች እንደተጣሉ ነው የሚወሰደው።ስለዚህ እርስ በርሳችን መተማመን ፣ መግባባት ሲቻል፣ ህገመንግሥቱ ላይ መግባባት ስንችል፣ እንዲህ አይነት ችግሮች ቀስ በቀስ እየተቀረፉ ይሄዳሉ።
ስለዚህ ስርዓታችንን መገንባት ላይ ከሰራን ችግሮቹ እየተቀረፉ ይሄዳሉ።ለምሳሌ በአሜሪካ የትራምፕ ደጋፊዎች ባስነሱት ነውጥ ከፍተኛ ረብሻና ቀውስ ለመፍጠር ጥረት አድርገው አይተናል፤ ነገር ግን ስርዓቱ በመጠንከሩ ከሚመጣው ችግር ሊታደጋቸው ችሏል፡፡ከዚህ ውጭ ግን ይህ ስፍራ የኔ ነው፣ እዚህ ውስጥ መግባት የለብህም እያልን ሌላ ዘመነ መሳፍንት እየፈጠርን መሄድ የለብንም።
አዲስ ዘመን፡ – የጋራ ጀግኖቻችንን ማክበር ያቃተንስ ለምንድነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- በትክክል ይህን ማድረግ አልቻልንም፡፡የኛ ባህል ራሱ የሚሰራ፣ የሚጣጣር እና ጀግና የሆነ ሰው መካብ ላይ ችግር አለበት።ከዚህ ውስጥ መውጣት አለብን።በሁሉም ቦታ አንድ ጥሩ የሰራን ሰው አመሰግናለሁ የማለት ባህል የለንም።ከዚህ መውጣት አለብን።ይህ ደግሞ እየጎዳን ነው።እኔ ያንተን ስራ ሳበረታታ እና አንተም የኔን ስታበረታታ ነው ተያይዘን ማደግ የምንችለው።እርስ በርስ የመተሳሰቡም ነገር የበለጠ እውነተኛ ይሆናል።እዚህ ላይ ትልቅ ድክመት አለብን።
ለምሳሌ በቅርቡ የራስ መኮንንን ሃውልት ለማፍረስ የተሄደበት መንገድ ታሪኩን ካለመረዳት የሚመነጭ ነው።ራስ መኮንን በዓድዋ ጦርነት ከሐረር ጦር ይዘው የመጡና ዓድዋ ድረስ ሄደው የተዋጉ ናቸው።የዲፕሎማሲም ስራ የሰሩ ናቸው።ለዚያ ነው ሃውልት የተቀመጠላቸው።በወቅቱ ደግሞ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰብ ሰብስበው ነው የተዋጉት።እና ይህንን ሃውልት ማፍረስ ያለንን ታሪክ መካድ ነው፡፡ራስ አባተ ቧያለው የተባሉትም ተመሳሳይ ነው።አባተ ቧያለው ሚኒልክን ተመስለው በተለያዩ ግንባሮች የተሳተፉና የእሳቸውን ወካይ ነበሩ።የዚህ ሰው ታሪክ ብዙም አይነገርም፡፡
ጣይቱም በተመሳሳይ ከፍ ያለ ሚና የተጫወቱ ሴት ናቸው።ለእኚህ ሴት ሃውልት ይሰራ ተብሎ ነው የቆመው።ይህ ከምን የመነጨ ነው ካልን የመቻቻልና የሆደሰፊነት ማነስ እና ታሪክን በአግባቡ ያለመረዳት ችግር ነው።በሃገራችን በተለይ ከሃይለሥላሴ በኋላ የቀደመውን ነገር ይዞ ያለመቀጠል ችግር አለብን።ደርግ ሲመጣ ሁሉንም ነገር በዜሮ አባዛ፣ ኢህአዴግ እንዲሁ አደረገ ፤ ስለዚህ ይህ መታረም አለበት።
አዲስ ዘመን፡- በአፄ ሚኒልክም ቢሆን እኮ ወጥ አቋም ያለ አይመስልም፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡– አሁን በዚህ ላይ ካለፈው አንድ ወር ወዲህ የተሰራው ስራ ትልቅ ነው።ይህ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።ስለዚህ ቀስ እያልክ ህዝቡ አገናዛቢ እየሆነ እንዲሄድ ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች አፄ ሚኒልክ እግር ቆረጡ እጅ ቆረጡ ወዘተ የሚል ታሪክ ያነሳሉ።በርግጥ ያ በእሳቸው ጊዜ የተጀመረ አልነበረም።
ለምሳሌ አንድ ሰው ከድቶ ወደጠላት ሲገባ እና ሲያዝ እንዲህ አይነት መቀጣጫዎች ከዚያ በፊትም ነበሩ።እናም ከማይጨው ጦርነት በኋላ ሃማሴኖች ሸዋ ሲገቡ ያንን ታሪክ አስታውሰው የሸዋን እግርና እጅ ቆርጠዋል።
በዚህ አይነት ደግሞ ሃገር ሊያድግ አይችልም።ስለዚህ በአንድ ወቅት የተፈፀመን ስህተት መቀበልና ከዚያ ትርጉም ያለው እርቅ ማድረግ ያስፈልጋል።ቢያንስ ችግሩን መገንዘብና ቆም ብሎ የወደፊቱን ማየት ይገባል።በኛ አገር ደግሞ ድርጊቱንም በደንብ ሳንረዳ ነው ቶሎ ወደ እርምጃ ለመሄድ የምንቸኩለው፡፡
በአሜሪካ እኮ ማንም ነው እዚያ ሄዶ የሚኖረው።እነሱ የሚጠይቁት ሁለት ነገር ብቻ ነው።አንድ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናገር፤ ሁለተኛ ህገመንግሥቱን ተቀበል።ከዚህ ውጭ ግን በሰላም እንደአገርህ መብትህ ተከብሮ ትኖራለህ።መንገድ ዘግተህ የብራዚል የባህል ቀን ነው ብለህ ልትጨፍር ትችላለህ።ስለዚህ ዴሞክራሲ ተብሎ ሁሉም በአንድነት በሰላም ይኖራል።
እና እኛ ለዚያ አይነት ነገር ነው ጥረት ማድረግ ያለብን።የባህል ብዝሃነት መኖሩ ለሃገራችን ውበት የሚሰጥ ነው፡፡ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ የሰዎች እኩልነት ነው መከበር ያለበት።ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የትም ቦታ መኖር መቻል አለብህ።ህዝብ በባህርይው ለሱ የሚሆነውን ነገር ያውቃል።ያንን የሚገድብ ነገር ሲኖር ደግሞ ያንን ላስጠብቅ ስትል ስትነታረክ ትኖራለህ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታሪክ ትምህርት ጭምር መስማማት አቅቶን የታሪክ ትምህርት ማስተማር ሁሉ እስከመቆም ደርሷል፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው፤ እኛ ኢትዮጵያውን አንድ የሚያደርገን ታሪክ ስላጣን ነው ማለት ይቻላል?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡– የታሪክ ትምህርት ስርዓት ባለው መንገድ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተቀርፆ ትውልድም እያወቃቸው እንዲሄድ አልተደረገም።አሁን ነው ትንሽ በዚህ ላይ መስራት የተጀመረው።የሰላም ሚኒስቴር ያዘጋጀው አንድ ኮንፈረንስ በቅርቡ በቢሾፍቱ ተካሂዶ ነበር።የማንነት መሰረት ታሪክ ነው።
ታሪክን በአግባቡ ስትገነዘብ ደግሞ ሆደ ሰፊ ትሆናለህ።ግጭትም ቢኖር በመነጋገርና በሰለጠነ መንገድ የመፍታት አቅምና ፍላጎት ይኖርሃል።አሁን ግን ያ እየተቀየረ ነው።አሁን ያለነው በለውጥ ላይ ነን።ስለዚህ ለውጡ እነዚህን ነገሮች በትክክለኛ መስመር ላይ ማስቀመጥ አለበት፡፡
አሁን በየትምህርት ቤቱ የሰላም ክለብ እንዲቋቋም ሃሳብ ቀርቧል፡፡ይህ እርስ በርስ ለመተዋወቅ፣ ለመቀራረብ፣ ሃሳብ ለመለዋወጥ ወዘተ ይጠቅማል።ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደግጭት ለመሄድ ያለውን እድል ይቀንሰዋል፡፡
አሁን የአንደኛ ዓመት የታሪክ ትምህርት ይዘጋጅ ተብሎ በሱም ላይ አንድ መሆን አልተቻለም።ይህ ካልተጨመረ፣ ይህ ካልተጨመረ ሲባል ልጆቹ ታሪክ ሳይማሩ ቀሩ።እና ፖለቲካው ገባበት።በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ፖለቲካ በምንም መልኩ ጣልቃ አይገባም።ባለሙያው ራሱ የራሱን ካሪኩለም ቀርፆ ለዚያ ይሆናል የሚለውን ነው የሚያስተምረው።ከዚያ እሱን የሚገመግሙት አቻዎቹ ናቸው።በምንም መልኩ ፖለቲካው በዚህ ውስጥ አይገባም።በኛ አገር ግን ከዚህ የተለየ ነው።ፖለቲካው ነው የሚረብሸው።
የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን “ኢንትሮዳክሽኑን” ብቻ እንዲያውቁ ነው ማድረግ ያለብህ።ከዚያ ቀስ በቀስ ወደአራተኛ ዓመት ሲደርሱ ነው ታሪክን በጥልቀት እየተማሩ መሄድ ያለባቸው።በዚህ ጊዜ ለማገናዘብም፣ ለመግባባትም አይቸገሩም።በዚህ መልኩ ቢሰራ ጥሩ ነው።የታሪክ ምሁራንም ቢሆን በቅርቡ አራት ሰዓት አብረው ተቀምጠው ተወያይተዋል።ይህ ጥሩ ጅምር ነው።ስለዚህ ይህንን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን አሁን አንድ ከሚያደርጉን የጋራ ታሪኮች ይልቅ የሚያለያዩን ታሪኮች እየጎሉ የመጡት ለምንድነው?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- አንተ አስበህ ሁል ጊዜ ላንተ የሚሆን ጥቅም ብቻ የምታሳድድ ከሆነ ለዚያ የሚሆን ነገር ነው የምትፈልገው።የኛ ታሪክ በጣም ረጅም ነው።ብዙ ውስብስብ ነገሮች አሉበት።ሰዎች ሁሉንም ነገር ሊረዱ አይችሉም።የተወሰነውን ነገር ነው የሚረዱት።ነገር ግን አንዱን ነገር ቁንጽል አድርገው ከወሰዱና ያንን መነሻ በማድረግ ለግል ጥቅም የሚጠቀሙበት ከሆነ ከባድ ነው።በአገራችን ደግሞ ጠባብ ፍላጎትን የሚያሣድድ በዛ።ትልቁ ችግራችንም እሱ ነው።
እኔ ከዚህ ቀደም በንጉሡ ዘመን የማስታውሰው አንድ ነገር ነበር።ከከተማ አንዳንድ መሳፍንቶች ወደ ገጠር ይሄዱና ለፓርላማ አባልነት ይወዳደራሉ።ይህ የሚሆነው በዚያ አካባቢ ከከተማ በመሄዳቸው እንደትልቅ ስለሚታዩና የተሻለ ሆነው ለመታየት ነው።ያ የገጠር ህብረተሰብ አግዝፎ ስለሚያያቸው ከነሱ የተሻለ የለም ብሎ ይመርጣቸዋል፡፡
ልክ እንደዚሁ አሁን ዘርህን መሰረት አድርገህ ወደላይ ብትወጣ ለማንም የሚጠቅም አይደለም።ለህብረተሰቡ የሚጠቅም ነገር መስራት ካልቻልክ ወርደህ ትከሰከሳለህ።ለሌላው የምትሰጠው ምንም ነገር የለም።ስለዚህ ችግሩ ይህ ስለሆነ መፈታት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ከዓድዋ ድል ምን እንውሰድ?
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- ዓድዋ አገራችንን ጠላት እንዳይወስድብን ያደረገ ድል ነው።ዓድዋ አንድ ስንሆን ማሸነፍ እንደምንችል ያስተማረን ትልቅ ትምህርት ቤት ነው።አሁንም ትላንት የማይደፍረን ሁሉ እንዳይደፍረን ከተፈለገ የሚያዋጣን አንድነታችን ነው።ለኢትዮጵያ ከአንድነት የተሻለ መንገድ የለም።
እና አንድ ስንሆን ብዙ ነገሮችን ልናሳካ እንችላለን።ይህ ደግሞ ዝም ብሎ ስሜት ብቻ ሳይሆን ታሪክ ራሱ ያስተማረን ነው።ስለዚህ አሁን አንድነትን ለእድገት መጠቀም አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስም አመሰግናለሁ፤
ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013