የሀገሪቱ ገቢ አሰባሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ባለፉት ዓመታት በየአመቱ በመቶ ቢሊዮን ብሮች እያደገ የመጣው ገቢ ዘንድሮ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል። ሀገሪቱም ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ተገቢውን ግብር ለመሰብሰብ አሠራሮችን በማዘመንና አዳዲስ አሠራሮችን በመተግበር ስትሠራ ቆይታለች። ይህን ስራዋን ዘንድሮም በተጠናከረ መልኩ እንደምትቀጥልበት አስታውቃለች።
እንደሚታወቀው ገቢ ከተለያዩ ምንጮች ሊሰበሰብ ይችላል። እየተሰበሰበም ነው። ምንም እንኳ ሀገሪቱ የምትሰበስበው ገቢ እየጨመረ ቢመጣም፣ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት አኳያ ሲታይ መሰብሰብ ያለባትን ያህል ገቢ እየተሰበሰበ አይደለም። ይሄ ደግሞ ሁሌም በመንግሥት በኩል ይገለጻል።
ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ የግብር መሠረት ባለመስፋቱ ፣ ገቢ መሰወር በስፋት የሚስተዋል በመሆኑ፣ በደረሰኝ ግብይት ሊፈጸምበት የሚገባ ንግድና የመሳሰለው ተግባር ያለደረሰኝ መከናወኑ፣ የግብር አሰባሰቡ ባለመዘመኑ፣ ግብር ሰብሳቢ ባለሙያዎች ላይ በሚስተዋለው የኪራይ ሰብሳቢነትና የመሳሰሉት ችግሮች በመንሰራፋታቸው ስለመሆኑ ሁሌም ይገለጻል።
በተለይ ግብይትን ያለደረሰኝ መፈጸም ግብይት በደረሰኝ በሚፈጸምበት ወቅት መንግሥትና ሕዝቡ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም ያስቀራል። ለእዚህም እንደ ተጨማሪ እሴት ታክስ ያሉትን ታክሶችንና የመሳሰሉትን መሰብሰብ አይቻልም። ግብርን በደረሰኝ ላይ ተመስርቶ ለመወሰንም አያስችልም።
መንግሥት ይህን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ ሕጉ በሚያዘው መሰረት ሽያጩን በደረሰኝ እንዲያደርግ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፤ በዚህ ጥረት የተወሰኑ ለውጦችም ታይተዋል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ይሁንና አብዛኛዎቹ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ሊባል በሚችል መልኩ ያለደረሰኝ ግብይት የሚያደርግ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የሚጠበቅበትን ግብር እየከፈለ ስላለመሆኑ ይታወቃል።
በመሠረቱ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ገቢ ለመሰብሰብ ሲታቀድ በግብር መረብ ውስጥ ያለው ግብር ከፋይ ብዙም ሊያሳስብ አይገባም፤ ተጨማሪ ግብር እንዲከፍል ተፈልጎ ከሆነም በዚያው ላይ የሚሰላ ይሆናል። ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙት የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ግን በሚጠበቀው መልኩ ግብር ለማስከፈል አዳጋች ይሆናል።
ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በመሰብሰብ ሂደት አሳሳቢ ሊሆኑ የሚገባቸው እነዚህ ግብይታቸውን ያለደረሰኝ የሚያካሂዱ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ናቸው። በእርግጥ እነዚህ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጥቂት አይደሉም፤ ሁላችንም ግብይት ስንፈጽም የሚሆነውን እናውቃለንና እጅግ በርካታ ናቸው።
በሀገሪቱ ትንሽ ገቢ ያለው ሠራተኛ ግብር ይከፍላል፤ ብዙ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ነጋዴ ብዙ ግብር ሲከፍል የማይታይ ስለመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትም ይገልጻሉ። ይህ አይነቱ ሕገወጥ ተግባር በዚህች ሀገር በጣም ተኖሯል፤ ንግዱ አየር ባየር የሚካሄድ ስለሆነ አይደለም ይህ ሲሆን የቆየው፤ መደብር ይዘው፣ መደብ ይዘው የሚነግዱ፣ ንግዳቸው በጣም የሰፋ ነጋዴዎች ይከፍላሉ የሚባለው ግብር በራሱም ያሳፍራል።
እነዚህ አካላት ግብይቱን በደረሰኝ የማይፈጽሙበት አንዱ ምክንያት ግብር ለመሰወር እንዲያመቻቸው ነው፤ ሌላው ደግሞ ሸቀጦችን የሚሸጡበትን ዋጋ መንግሥት እንዳያውቅባቸውና ክትትል እንዳያደርግባቸው ስለሚፈልጉም ነው። በደረሰኝ ግብይት እንዲፈጸም መደረጉ ለህብረተሰቡም ለመንግሥትም ይጠቅማል። ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ዋጋን ለመከታተልም ይረዳል። በደረሰኝ ላይ የተመለከተው ዋጋ አላግባብ ዋጋ የተጠየቀበት ከሆነ ሕገወጦችን ለመጠየቅ ያስችላል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እነዚህን ነጋዴዎች ነው ግብይታቸውን በደረሰኝ እንዲያደርጉ ለማድረግ ወደ ሥራ የገባው። ከተማ አስተዳደሩ የንግዱ ሥራ በሥርዓት እንዲመራ ለማድረግ ከዚያም ተገቢው ግብር እንዲሰበሰብ ለማስቻል ነው እየሠራ ያለው። አሠራሩ የሠለጠነ አካሄድ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።
መንግሥት በዚህ በጀት ዓመት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ሊሰበሰብ የሚገባውን ገቢ ለመሰብሰብ እንዲቻል የተለያዩ ተግባሮች እንደሚከናወኑ በአመቱ መጀመሪያ ላይ አሳውቋል። ይህ የከተማ አስተዳደሩ ርምጃም ከዚህ የመንግሥት አቅጣጫ የወጣ ነው። ይህን ገቢ ለመሰብሰብ በቅድሚያ የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቱን በደረሰኝ ማድረግ ይኖርበታል። ግብይቱ በደረሰኝ ከተፈጸመ በዚያ ላይ በመመስረት ግብር መጣልና ገቢን መሰብሰብ ይቻላል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ የመርካቶ ነጋዴዎች ግብይታቸውን በደረሰኝ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ሥራ መጀመሩ የረፈደ ቢሆንም ትክክል ነው፤ ሌላ ምንም ዓላማ የለውም። ሥራው የቱንም ያህል ፈታኝ ቢሆን ከተማ አስተዳደሩ ይፈጽመዋል።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ መርካቶ ላይ እየታየ ያለው ማንገራገር ግን ተገቢ አይደለም። ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሥራው አልጋ ባልጋ እንዳይሆን የሚያደርጉ ሁኔታዎች ተከስተዋል። ይህ ግን ተገቢ አይደለም።
መንግሥት አሁን እየተገበረ ያለው አሠራር ከዓመታት በፊት መተግብር የነበረበት ነው። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም አሠራሩ ሳይተገበር ቆይቷል። አሁን ቀኑ ደርሶ ትግበራው ተጀምሯል። መንግሥት ለንግዱ ማህበረሰብ የአሠራሩን አስፈላጊነት አስመልክቶ ግንዛቤ እያስጨበጠ፣ ከዚህ ወጣ ያለ ሁኔታም ሲያጋጥም በሕግ እየጠየቀ ሊፈጽመው ይገባል።
ለራሱ ለንግዱ ማህበረሰብም ቢሆን ይጠቅመዋል፤ ነጋዴው ምንም እንኳ ያለውንና የሌለውን የሚያውቅ ቢሆንም፣ በቴክኖሎጂና በደረሰኝ ተጠቅሞ የሸጠውንና ያልሸጠውን በቀላሉ ማወቅም የሚያስችለው ይሆናል። በዚህ ሥራዎች ሁሉ በቴክኖሎጂ በሚሠሩበት ዘመን ያለደረሰኝ ግብይት መፈጸም ማንንም አይጠቅምም።
ሌላው ለእኔ ወሳኙ ጉዳይ ግብር ነው። ተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰብ ካለበትም እንዲሰበሰብ ያስችላል፤ ከዚያ ውጪ ደግሞ ግብር ክፍያ ሲመጣ በደረሰኝ ላይ ተመስርቶ ግብሩ እንዲሰላ ያስችላል። በደረሰኝ ግብይት መፈጸም በነጋዴው ላይ ሊያስከትል የሚችለው ችግር የለም። አሁን ጉዳዩን ለማወሳሰብ የሚሞክሩት ሌላ ዓላማ ያላቸው ናቸው።
ይሄ ደግሞ ተገቢ አይደለም። ከተማዋ ሀገሪቱ መሠረተ ልማቶችን እንዲያሟሉ፣ ጤና እንዲጠበቅ፣ ትምህርት እንዲስፋፋ ፣ ወዘተ የሚፈልግ ማህበረሰብ በእዚህ ልክ የመንግሥት አሠራር ላይ ማንገራገር አይደለም የሃሳብ ልዩነት መፍጠር የለበትም። ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው እየተፈጸመ ያለው። በፍጥነት መታረም ይኖርበታል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ባለፈው መስከረም ወር የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ2017 በጀት ዓመት የሥራ መጀመሪያ በሆነው የጋራ ስብሰባ ላይ የመንግሥትን የ2017 በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫ ባስታወቁበት ወቅትም የገቢ መሰብሰብ አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተው ማመልከታቸው ይታወቃል።
ፕሬዚዳንቱ የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ ወደ ግብር መረቡ ያልገቡትን እንዲገቡ እንዲሁም አዳዲስ የታክስ አይነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ፣ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን ለማዘመንና ታክስ በመሰብሰብ ሂደት የሚወጣውን ወጪ ውጤታማ ለማድረግ መንግሥት ይሠራል።
በፌዴራል ደረጃ ያሉትን የታክስ ማሻሻያ ሥራዎች ወደ ክልሎችም ማውረድ በክልል ደረጃ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥ በማዘመንና በማሻሻል፣ ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ ርብርብ ይደረጋል፤ ለኢንቨስትመንት ማበረታቻነት የሚሰጡ ከታክስ ጋር ግንኙንት ያላቸው ማበረታቻዎች እና ድጎማዎች ውጤታማ እንዲሆኑ እንዲሁም የታክስና ታክስ ያልሆኑ ገቢዎችን ለማሻሻል ይሠራል።
በዚህ ሁሉ ስራም አጠቃላይ የመንግሥትን ገቢ አንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ብር ለማድረስ እንዲሁም ገቢ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ድርሻ ወደ ስምንት ነጥብ ሶስት በመቶ እንዲያድግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል። ለእዚህ የመንግሥት እቅድ መሳካት ሁሉም ግብር ከፋዮች ፣ ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች ፣ የሕግ አካላት ፣ ወዘተ መተባበር ይኖርባቸዋል።
ዘካርያስ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም