አመራርነት አገልጋይነት ነው። በአዲስ አስተሳሰብ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማገልገል ነው። መሪዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ይዘው ሕዝብን ወይም ተቋምን ሲያገለግሉ እንደ ተቋም ሆነ እንደ ሀገር ለውጥ ይመጣል።
በዛሬው የዘመን እንግዳ ገጽ በአገልግሎት አሰጣጥና በመሪነት ውስጥ ያለ አገልጋይነትን በተመለከተ ከዛሬው እንግዳችን አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ አድርጓል።
አቶ ሰለሞን ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ መስፍን ሐረር መንገድ ወይም አዲሱ ገበያ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ፤ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
በሕግ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ እና በአካውንቲንግ ዲፕሎማ፤ በንግድ ሥራና አስተዳደር ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው። በተጨማሪም በኢንፎሜሽን ሲስተም አስተዳደር እና በትምህርት አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪቸውን ሰርተዋል።
በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በአመራርነት የሰሩ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለአስራ ሶስት ዓመታት በመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው አገልግለዋል።
በአጠቃላይ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ለ41 ዓመታት በሥራ ላይ ቆይተዋል። በ2013 ዓ.ም በጡረታ ከሥራ የወጡ ቢሆንም አሁን ላይ በአንድ የግል መሥሪያ ቤት በጊዚያዊነት ተቀጥረው እያገለገሉ ይገኛል። በአጠቃለይ ከእኚህ ጉምቱ ባለሙያ ጋር የነበረን ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል።
አዲስ ዘመን፡- አመራር ስንል ምን ማለት ነው?
አቶ ሰለሞን፡- አመራር ግልጽ የሆነ ራዕይ ይዞ ተቋሙን እና ፈጻሚውን በመለወጥ አሰራርን መቀየር ነው። አመራር ክህሎት ይጠይቃል፤ ስለዚህ በአመራር አሰራሮችን እንቀይራለን።
አመራር ሥራንና ሥራን ብቻ ማዕከል ያደረገ፤ ሰውን እና ሥራን እየመራ ከለውጥ ማድረስ ነው። ከፈጻሚዎቹ ጋር አብሮ እየሰራ፣ ቁርጠኛ እንዲሆኑ እያበረታታ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻል ነው። አመራር የሚሆኑት መሪዎች ናቸው። መሪ ስንል የሃይማኖት መሪ አለ፣ የተቋም፣ የሀገር እና የተለያዩ ተቋማት መሪዎች አሉ። በመሪነታቸውም ብዙ ኃላፊነቶች የመወጣት ኃላፊነት አለባቸው።
‹‹ለውጥ የለውጥ ካፒቴን ይሻል ይላል›› ማይክ ራመር፤ ስለዚህ ለአንድ ተቋም መሪ ወሳኝ ነው። ለተቋሙ ውድቀት ሆነ መነሳት የመሪው ተግባር ነው የሚወስነው። ይህን ማድረግ የሚችል ሰው ነው እንደመሪ የሚቆጠረው።
መሪ ከራዕይ ይጀምራል። እሴቶች፣ ግቦች፣ እቅዶች እና አሰራሮች ያማከለ ነው መሆን ያለበት። የትምህርት ዝግጅት ስላለው እና ለፖለቲካ ታማኝ ስለሆነ ብቻ መሪ መሆን አይችልም። ክህሎት ይጠይቃል፤ ልምድ ይጠይቃል።
እነዚህ መስፈርቶች ባለመሟላታቸው ነው ብዙ ጊዜ አንድ ሰው ሥልጣን ላይ ከተቀመጠ በኋላ ውድቀት የሚያጋጥመው። መጀመሪያ አንድ ሰው ሲሾም የኋላ ታሪኩ መታየት አለበት። ለህብረተሰቡ፣ ለሀገር ያበረከተው አስተዋጽኦ ምን ይመስላል? እውቀቱስ ምን ይመስላል የሚለው መታየት አለበት።
ብዙ ጊዜ ትምህርት ነው የሚታየው፣ ነገር ግን ትምህርቱ ያን ሰው ይገልጸዋል ወይ? የሚለው መታየት አለበት። በሥራ ዓለም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች እንደተመለከትኩት፤ እራሳቸውን መግለጽ የሚያቅታቸው ብዙ መሪዎች አሉ። ለዚህ ነው አንድ መሪ፤ መሪ ነው ለመባል እውቀትና ታማኝነቱ ብቻ በቂ አይደለም የምለው። እውቀት እና ልምድ ያስፈልጋል ለማለት ፈልጌ ነው።
አንዳንድ ተቋማት ላይ እንደምንመለከተው መሪዎች በሰሩት ጥሩ ሥራ እና በትምህርት ደረጃቸው ወደ ኃላፊነት ይመጣሉ። በተቃራኒው ደግሞ በትውውቅ ብቻ የሚመጡ አሉ። እናም ችግሩ ያለው እሱ ጋር ነው። መሪነት ልምድና ክህሎት ይጠይቃል የምለው ለዚህ ነው።
ለምንድነው በየቦታው ስንሄድ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የምናየው? ህብረተሰቡ ለምን ይንገላታል? የሚለውን ስንፈትሽ ከአመራር ጥበብ ጋር ይያያዛል። እዚያ ቦታ ላይ መሪ እስካለ ድረስ፤ ሰው የሚጉላላው ለምንድነው? ያ ሰው መሪ ነው ለማለት ህብረተሰቡ ጋር ያለው መጉላላት ብቻ ማየት በቂ ነው።
ወደ በርካታ ተቋማት ሲኬድ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴት ተለጥፎ እናያለን። በተጨማሪ ደግሞ የሥነ ምግባር መርሆች እናያለን። እነዚህ ነገሮች አመራሩም ሆነ ፈጻሚው በአግባቡ ይረዳቸዋል ወይ የሚለው ጥያቄ ያጭርብኛል።
እንደዚህ የምለው በየቦታው ያለውን መጉላላት ስመለከት ነው። አገልግሎት ሰጪ ተቋሞቻችን ደንበኛን አክብረው ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል። አመራር ሁልጊዜ የተገልጋይ ርካታን የህልውና ጉዳይ አድርጎ መውሰድ አለበት። ችግሮች መኖራቸው አይቀርም ያሉትን ችግሮች እንዴት ነው መቅረፍ የሚቻለው የሚለውን ቁጭ ብሎ ማሰብ መቻል አለበት።
አልበርት አንስታይ በዚህ ዙሪያ የጻፋቸው በርካታ ነገሮች አሉ። አሁን ‹‹ያሉብንን ችግሮች መቅረፍ የምንችለው፤ ችግሮችን በፈጠረው አስተሳሰብ ሳይሆን፤ በአዲስ አስተሳሰብ ነው›› ይላል። አመራር ሆኖ ሲመረጥ አንድ ሰው የኋላ ታሪኩ መጠናት አለበት። የቤት ሥራዎቹን መሥራት አለበት። ምንድነው መሥራት ያለብኝ? ያለውን የአረጀና ያፈጀ አሰራር እንዴት ነው የምቀይረው? የሚሉ ነገሮችን በማሰብ ወደ ተግባር መቀየር አለበት።
ለውጥ ብዙ ጊዜ ተግዳሮቶች አሉት። ለውጥ የመጣለት ሲደሰት፤ ለውጥ የመጣበት ያለቅሳል። የሚከፋበት ምክንያት በአረጀ አሰራር ተጠቃሚ የሆነ ሰው የሚቀርበት ነገር ስላለ መከፋቱ አይቀርም። አዲስ አሰራር የመጣለት ሰው ደግሞ መደሰቱ አይቀሬ ነው።
ስለዚህ አንድ ሰው ወደ ሹመት ከመሄዱ በፊት ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለውን ነገር መቅረፍ አለበት። ለውጥ የህልውና ጉዳይ አድርጎ መውሰድ፣ በራስ መተማመን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሥራ ለማስገባት ከሌሎች መኮረጅ ያስፈልጋል። መኮረጅ በራሱ ለእኔ እውቀት ነው። በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) በጣም ነው የማመሰግናቸው፤ ወደ ተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ሲሄድ ትልቅ ለውጥ ነው የሚታየው። ይህን ነገር አምጥቶ ሥራ ላይ ማዋል በራሱ ትልቅ ነገር ነው።
በእንግሊዝኛ አጠራሩ ቤንች ማርክ የምንለው እኮ ከሌሎች ተሞክሮ መውሰድን ነው። እኔ አሁን ራስ ደስታ ላይ የግል ህክምና መስጫ ለማቋቋም፤ ኦሮሚያ ሄጄ ነው ልምድ የቀሰምኩት። ቢሾፍቱ ሆስፒታል ላይ ተቋቁሞ ስለነበር የግል ህክምና መስጫ እዛ ሄጄ ቤንች ማርክ አደረኩ። በኋላም አዲስ አበባ አምጥቼ በሁሉም ሆስፒታሎች እንዲተገበር አደረግኩ።
“መጥፎ ጎረቤት እቃ ያስገዛል” ይባላል። ይህ ማለት አንድ ጎረቤት ሁልግዜ እየመጣ እቃ ልዋስ ብሎ የሚጠይቅ ከሆነ፤ የሚያውሰው ጎረቤት በመሰላቸት የለም ይላል። ያን ጊዜ የሚዋሰው ሰውዬ በቁጭት የሚያስፈልገውን እቃ ይገዛል። ለዚህ ነው፤ ቁጭት ሁልጊዜ የለውጥ መንስኤ ነው የሚባለው።
ከወዳጆቻችን መልካም ነገሮችን ስናይ ያን ነገር ለማድረግ በቁጭት እንነሳለን። ከዛን እናደርገዋለን። ቁጭት የለውጥ መንስኤ ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ለዚህ ነው አመራር ቁርጠኛ መሆን አለበት የሚባለው።
የአዲስ ዘመን፡- የአንድ መሪ የአስተዳደግ መንገድ በመሪነት ሥራው ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላል? ምን ዓይነት ተጽዕኖ ነው የሚያሳድረው?
አቶ ሰለሞን፡- በእድገት የሚያጋጥም ነገር ይኖራል፤ ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገሮች ከእድገት ጋር ተያይዘው ሊንጸባረቁ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ነገር በትምህርት ይቀየራል። በተለያዩ መንገድ የሚያድጉ ልጆች 12ኛ ክፍል ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ይገባሉ። በከፍተኛ ትምህት ቆይታቸው እንደተማሩበት የትምህርት መስክ ዕውቀት ይገበያሉ፤ የሕይወታቸውም አካል ያደርጉታል። ለአብነት የአስተዳደር ትምህርት ከተከታተለ አስተዳደራዊ እውቀት ይዞ ነው የሚወጣው።
ያገኘው እውቀት ከክህሎት ጋር ሲታከል ያ ግለሰብ በቂ መሪ ይሆናል። ለምሳሌ አንድ ከከፍተኛ ትምህርት በአካውንቲንግ የተመረቀ ሰው መጀመሪያ የሚማረው ንድፈ ሃሳቡን ነው። አጠቃላይ ስለወጪ፣ ገቢ እና ሌሎች ነገሮች፤ ክህሎት የሚኖረው ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ክህሎት ያስፈልጋል ሲባል በኑሮ ያዳበረው ወይስ በሥራ ?
አቶ ሰለሞን፡- አመራርነት በመወለድ የምናገኘው ነገር አይደለም። ምናልባት በሩህሩህነት፣ አስተዋይነት እና የመሪነት ባህሪ በተፈጥሮ ሊኖር ይችላል። እድገት የሚሰጠው ነገር የአመራርነት ሂደቱን ሊያፋጥነው ይችላል። የሚዳብረው ግን በትምህርት ነው።
ጋዜጣዎች ላይ የሥራ ቅጥር ሲወጣ ይሄን ያህል ዓመት የሥራ ልምድ ይላል። ይህም ክህሎትና ልምድ ያለው ሰው ስለሚፈለግ ነው። ጀማሪ ሰው ተቀጥሮ አመራር ሊሆን አይችልም።
ትምህርቱን ነው እንጂ የወሰደው ሰውም ሆነ ሥራ እንዴት እንደሚመራ አያውቅም። ሥራ ላይ በቆየ ቁጥር ከጓደኞቹ እና ከአለቆቹ ያለውን አሰራር እየተማረ ይሄዳል።
ለምሳሌ ከቤተሰብ አንድ ቤተሰብ ቤቱን የሚያስተዳድርበት መንገድ፤ እንዴት ነው? አባት ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ከሚለው ስንነሳ፤ ለአንድ መሪ ተጨማሪ እውቀት ይሰጣል። የኑሮ ክህሎት ከሰብዓዊነት ጋር ነው የሚገናኘው፣ በተፈጥሮም የሚሰጥ ነው። ለምሳሌ የሃይማኖት መሪነት ከሃይማኖት ትምህርት ጋር የሚመጣ ነው። በተጨማሪም ከእድገታቸው ጋር የሚመጣ አለ። ሆኖም ትምህርት እና ልምድ ወሳኝ ነው።
አንድ መሪ መጀመሪያ ከላይ ከአስተዳደር ሆነ ከተቆጣጣሪ አካላት ልምድ እያዳበረ ሲመጣ ነው ብቁ መሪ ሊሆን የሚችለው። የቀረውን ደግሞ እያነበበ ይሞላዋል። አንድ ጊዜ ከትምህርት ቤት ተወጣ ተብሎ ንባብ መተው አይገባም። ሁልጊዜ እራስን ለማሸነፍ መማር ያስፈልጋል። በተከታታይ የትምህርት ሂደቶች አንድ ሰው ብቁ ይሆናል። እናም በብዙ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች አንዱ ክፍተታቸው እራሳቸውን እያበቁ አለመሄዳቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ በአገልግሎት አሰጣጣችን ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች ከአመራር ክፍተት ብቻ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን?
አቶ ሰለሞን፡- ሙሉ ለሙሉ ነው ማለት ባይቻልም በአብዛኛው ግን ከአመራር ክፍተት ጋር የሚያያዝ ነው። ብዙ ጊዜ ምን ሰራ?፣ ለሀገር ምን አስተዋጽኦ አደረገ?፣ የት መሥሪያ ቤት ሆኖ ምን ውጤት አስመዘገበ?፣ የአመራር ብቃቱ ምን ይመስላል ? የሚለው ሲታይ አንድ ሰው ወደ ሹመት ይመጣል።
እኔ ለ13 ዓመታት በአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል እና የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነበርኩ። በእነዚህ ዓመታት እይታዬ ብዙ ሰው ሾመናል። አንድ ሰው ይሄ ሹመት አይመጥነኝም፤ ለዚህ ሹመት ብቁ አይደለሁም የሚል ተሿሚ አይቼ አላውቅም።
ምክንያቱም የሚታያቸው በሥልጣኑ ምክንያት የሚያገኙት ጥቅም፣ ክብር ብቻ ስለሚታያቸው ነው። የሕዝብና የመንግሥት አደራ እየተሸከሙ መሆኑን አይረዱም። ለዚህ ነው አንዳንድ ተሿሚዎች በተሾሙ በስድስት ወር ውስጥ ከሥልጣን ሲወርዱ የምናያቸው። ወደ ወረዳ ወይም አንድ አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ ሲኬድ ሰው ሲጉላላ ይታያል። ለዚህ ለምን ከተባለ መሪው ትክክል ስላልሆነ ነው። ህብረተሰቡ የሚያዝነው በሾመው አካል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የምክር ቤቱ አባል እንደመሆኖ አንድ ሰው ለሹመት ሲቀርብ ግምገማ አታደርጉም?
አቶ ሰለሞን፡- የሚሾሙ አመራሮችን የሚሾመው አካል እገሌ ለዚህ ቦታ የተሻለ ነው ብሎ ያመጣቸዋል። እኛ ደግሞ ስለተሿሚው የቀረበውን ገለጻ አድምጠን ሃሳብ እንሰጣለን። ያመጣው አካል አምኖበት ስለሆነ ያመጣው በሚል ድጋፍ ይሰጣል። ለዛ ነው የተሾመው አካል ለውጥ ካላመጣ የሾመውን አካል አንገት ያስደፋል ያልኩት።
ቅድም እንዳልኩት አንድ ሰው ወደ አመራር ሲመጣ ብቃቱ ታይቶ አይደለም። በትውውቅ የሚመጡ ብዙ ናቸው። ይህ ደግሞ ሀገርን ይገድላል፤ ሕዝብን ያማርራል።
አዲስ ዘመን፡- አንድ አመራር ራሱን ለማሳደግና የህብረተሰቡን ጥያቄ ለማርካት ምን ማድረግ አለበት?
አቶ ሰለሞን፡- አመራር በማያቋርጥ ሁኔታ ራሱን እያሻሻለ መሄድ አለበት። የትላንት እውቀት ለዛሬ አይረዳም። ስለዚህም ሁልጊዜ ራሱን ለማሻሻልና ለመለወጥ መጣጣር አለበት። የሚያከናውናቸው ነገሮች ምን ያህል ህብረተሰቡን እያረኩ ነው ብሎ ዘወትር መፈተሽ አለበት።
ይህን ለማድረግ ደግሞ ማንኛውንም መጽሐፍ ማንበብ አለበት። ነገር ግን አቅሙን ለማሳደግ አመራርነት ላይ የተጻፉ መጻሕፍትን የበለጠ ቢያነብ፤ አዳዲስ እውቀቶችን ያገኛል፤ ሌሎችንም ይቀይራል። ከባዱ ነገር ሰው መምራት ነው፤ ሰው ላይ ደግሞ ሥራ አለ። ሁለቱን አቀናጅቶ መምራት ለአንድ መሪ ትልቅ ክህሎት የሚጠይቅ ነው።
አመራር እኮ ማለት ማዘዝ እና መፈረም ብቻ አይደለም። አብሮ መሥራት አለበት፤ ስለሥራው ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። ከስር ያሉ ሠራተኞች ስለሚሰሩት ሥራ ሲጠየቅ፤ ምላሽ መሰጠት ካልቻለ እሱ መሪ አይደለም። ትክክለኛውን ሰው፤ በትክክለኛ የሥራ ቦታ ማስቀመጥ መቻል አለበት የሚባለው ለዚህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንድ አመራር በተቋሙ ሲሾም፣ ሁሉንም ነባር አሰራሮች መቀየር አለበት? ይሄ ነገር የአሰራር ግንባታ ከሚለው ሃሳብ ጋር አይጣረስም?
አቶ ሰለሞን፡- ነባር አሰራሮች ሁሉም መቀየር አለባቸው አይባልም። እስከዛሬ ሲሰራ የነበረው ሥራ ሁሉም ስህተት ነው ማለትም አይቻልም። የነበሩ ጥሩ አሰራሮች ማጠናከር ይገባል። ስህተት ሆነው ነገር ግን ያልታዩ ነገሮች መታረም አለባቸው።
ለምሳሌ በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ፤ አንድ ሰው ለማስተናገድ 10 ደቂቃ የሚወስድ ከሆነ፤ አመራሩ ወደ አምስት ደቂቃ ዝቅ እንዲል ውሳኔ በማስተላለፍ ይሰራበታል። ለውጥ ማለት አንዱ ይሄ ነው። ጊዜ ውድ ነገር እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል። ስለዚህ ጊዜ በአግባቡ አለመጠቀም፤ በተዘዋዋሪ ገንዘብ እንደማባከን ይቆጠራል።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ነባሩ አሰራር ከመቀየሩ በፊት፤ አንድ አመራር ምን መሥራት አለበት?
አቶ ሰለሞን፡- መጀመሪያ ከስር ያሉ አመራሮች ሰብስቦ በዘርፉ ያሉ ሥራዎችን እየጠየቀ ካደመጠ በኋላ በሁሉም አሰራሮች ዙሪያ በቂ እውቀት መጨበጥ ይኖርበታል። ከዛ በኋላ ያሉትን ሥራዎች እየዞረ መመልከት ይኖርበታል። ተዘዋውሮ በሚመለከትበት ወቅት የሚያያቸውን ክፍተቶች በመያዝ የመፍትሔ አሰራር ይዘረጋል።
አንዴ አሰራር ተዘርግቷል ተብሎ፤ እስከ እድሜ ልክ መቆየት የለበትም። ያለውን ክፍተት ካጠና በኋላ፤ ከስር ያሉ አመራሮችን በመጥራት ያሉትን ጥሩ ነገሮችን በመግለጽ፤ ክፍተቶችን ለመቀየር ደግሞ መወያየት ያስፈልጋል። የእያንዳንዱ ሰው አስተሳሰብ የተለያየ ስለሆነ ሃሳብ መቀበል እና ያሉትን ክፍተቶች መዝጋት ተገቢ ነው።
አመራር ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን አለበት። እሱ የሚናገረውንና ሊተገብር ያሰበውን ሌሎች አምነውበት ሊቀበሉት ይገባል። ተጽዕኖ መፍጠር የማይችል አመራር አዲስ አስተሳሰብ ፈጥሮ ሌሎችን ወደ ሥራ ማስገባት አይችልም።
ለውጥ ለማምጣት ዝም ብሎ ብቻውን መሮጥ አይደለም። መጀመሪያ ለውጥ የሚመጣበትን መንገድ ማየት ያስፈልጋል። ከስር ያሉ ፈጻሚዎችን ማገዝ፤ የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት፤ ጥያቄዎችን መመለስ አለበት። በአጠቃላይ ችግር ፈቺ እና ውሳኔ ሰጪ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የአንድ መሪ የአስተዳደር መንገድ ከስር ባሉ ፈጻሚዎች ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል? ካለስ በምን መልኩ?
አቶ ሰለሞን፡- የራሱን ክህሎት እና እውቀት ከስር ያለው ሠራተኛ እንዲያውቅ ማድረግ አለበት። በሥራ ላይ እና ከሥራ ውጭ በሚሰጡ ሥልጠናዎች አማካኝነት እገዛ ሊያደርግላቸው ይገባል። መሪው የሚያውቀውን ያህል ሠራተኛው እንዲያውቅ የማድረግ ኃላፊነት አለበት።
ዲፕሎማ ያለውን ሠራተኛ ዲግሪ ማስተር፣ ዲግሪ ያለው ደግሞ ማስተርስ እንዲማር በማድረግ፤ ተቋሙ የኔ ነው የሚል ስሜት እንዲሰማው ማድረግ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የአንድ አመራር አቅም የሚፈተነው ተቋሙ ችግር ላይ ሲወድቅ፤ ለችግሩ በሰጠው ምላሽ ነው ይባላል። ይሄን ሃሳብ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ሰለሞን፡- የምቀበለው ሃሳብ ነው። የአመራር ክፍተት ካለ፤ ብቁ መሪ ካልሆነ፣ የትምህርት ዝግጅቱ እና የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን ብቻ አይተን የምናመጣው ከሆነ፤ የተበተኑ ነገሮችን ማደራጀት ያቅተዋል። ከስህተት ያለመማር ሁኔታም ይፈጠራል። ችግሮች ሲፈጠሩ በቅጣት የሚያምን ነው የሚሆነው። አመራር ብቁ ካልሆነ ተቋም ነው የሚፈርሰው። መሪነት ማለት ተዳሮቶችን አልፎ ውጤት ማስመዝገብ ነው።
አመራር ስናመጣ ሁልጊዜ ጭንቅላታችን ማሰብ ያለበት ህብረተሰቡን ነው። በምሳሌ የምጠቅሰው መንጃ ፈቃድ ለማሳደስ ስንሄድ በአስር ደቂቃ ውስጥ የምንመለስበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ ይህን አሰራር ወደ ሌሎች ማምጣት ያስፈልጋል። እንደዚህ ሲሆን ጊዜ አይባክንም፤ እነሱም ሥራቸውን ይሰራሉ እኔም ሥራዬን እሰራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ወደ አንዳንድ ተቋማት ሲኬድ አመራሩም ሆነ ሠራተኛው በቢሮ አይገኙም። በዚህ ሁኔታ በቂ አገልግሎት መስጠት ይቻላል?
አቶ ሰለሞን፡- አሁን አሁን በሥራ ቦታ ላይ አለመገኘት ለአገልግሎት አሰጣጡ ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ ነው። አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች በሱስና በተለያዩ የግል ጉዳዮች ቢሮ የማይገኙበት ሁኔታ ሰፊ ነው። ግለሰቡ የተለያየ ሱስ ያለበት ከሆነ በሥራው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። የማውቃቸው ሰዎች አሉ፤ ሥራቸውን ጠንቅቀው ይሰራሉ። ነገር ግን ጫት ለመቃም ከሥራ ገበታቸው ይጠፋሉ። አንድ ሰው አብዝቶ ከጠጣ ይታመማል። እንደዛ ሲሆን ደግሞ ከሥራ ይቀራል። ስለዚህ ሥራው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
እንደዚህ ዓይነት ሠራተኞችም ካሉ መሪው ሰብስቦ በማወያየት፤ ለሰውዬው ሕይወትም ሆነ ለተቋሙ ስለማይበጅ ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጣ ማድረግ አንዱ የአመራሩ ኃላፊነት ነው።
በራሳቸው ገቢ የሚንቀሳቀሱ ልማት ድርጅቶችም ሆኑ በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸው ተገቢ አገልግሎት መስጠታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። ብዙ ጊዜ ክፍተቶች የሚስተዋሉት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ነው። ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ብዙ ጊዜ ክፍተቶች የሚታዩት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ነው።
ለዚህ ምክንያቱ መሥሪያ ቤቱን የሚያስተዳድረው መሪ የህብረተሰቡን ርካታ እየመዘነ ስለማይመጣ ነው። በዕለት ሥራዎች በመጠመድ ጊዜውን ያሳልፋል። ሰዎች ተሰልፈው ሲንገላቱ እየተመለከተ ችግሩን ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት የለም። የሕዝብ እንግልት ግድ አይሰጠውም። እንደዚህ ዓይነት አመራር ደግሞ መንግሥትን ያሳዝናል፤ እራሱንም ያዋርዳል።
አዲስ ዘመን፡- በአመራርነት ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እና ቀጣይ ሀገርን በተገቢው መልኩ የሚያገለግል ብቁ ትውልድ ለማፍራት ምን ይሰራ?
አቶ ሰለሞን፡- ትውልዱ ብቁ አገልጋይ እንዲሆን ከስር መሰራት አለበት። የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ፤ የማንበብ ልማድ እንዲኖረው ማድረግ፤ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ የሚጀምረው ከስር ካሉት ትምህርት ቤቶች ነው።
በኋላም እነዚህ ልጆች ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚያስችላቸውን እውቀት ራሳቸውን በማስተማር ሊያዳብሩ ይገባል። አንድ ደራሲ በመጻፉ ላይ “አዕምሮህ አንተ ከምታስበው በላይ ነው” ይላል። ብዙ ሰው ትንሽ ችግር ሲገጥመው ‹‹ምን አስጨነቀኝ›› ይልና ይተወዋል። በዛን ወቅት አዕምሮውን እየዘጋ ነው። አዕምሮን ካሰራነው መሥራት የሚገባውን ያህል ይሰራል ማለት ነው። አሁን ግን ከአቅም በታች ነው እየሰራን ያለው።
በመንግሥት በኩል ደግሞ ወደ አመራር የሚመጡ ሰዎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት። ሕዝብን የማገልገል ፍላጎትና እና ተነሳሽነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ወደ አመራር እንዲመጡ ማድረግ አለበት። ይህ ሲሆን የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ይቻላል፤ ህብረተሰቡም በመንግሥት ላይ ያለው መተማመን እንዲጨምር ይረዳል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመስግናለሁ፡፡
አቶ ሰለሞን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም