በወርቅ ላይ የመጣውን ለውጥ ማጣጣም፣  ለዘላቂነቱም በትኩረት መሥራት!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እየጨመረ ይገኛል፤ ለውጭ ገበያ ከቀረበ የወርቅ ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም ከፍተኛ መሆን ጀምሯል። ከወርቅ አምራች ክልሎች እንዲሁም ከማዕድን ሚኒስቴር የሚወጡ መረጃዎችም እንዲሁ ወደ ባንኩ የሚገባው የወርቅ መጠን እየጨመረ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው።

ይህ ትልቅ ዜና ነው። ለውጡ ሀገሪቱ እምቅ የወርቅ ሀብት እንዳላት እንዲሁም የሀገሪቱን የወርቅ ሀብት በሚገባ በማልማት ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም እንዲሁም በኮንትሮባንድ ሳቢያ የሀገሪቱ የወርቅ ምርት የሕገወጦች ሲሳይ ሆኗል እየተባለ ሁሌም ሲገለጽባት በቆየች ሀገር ይህን ዜና መስማት ትልቅ የምስራች ነው።

አሁን እየታየ ያለው ለውጥ ለብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ማንሰራራት እያሳየ ነው ከሚለውም በላይ የሚገለጽ ነው። በሩብ አመቱ የታየው ከፍተኛ ለውጥ ነውና። በሩብ ዓመቱ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ወርቅ የተገኘው የውጭ ምንዛሬም እንዲሁ ከፍተኛ ነውና ለውጡን ከፍ አድርጎ መመልከት ይገባል።

ይህ ለውጥ እንዴት መጣ ብሎ መጠየቅ ግን ይገባል። የፌዴራል መንግሥት ሕገወጥ የወርቅ ግብይትን ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል በማቋቋም ባለፉት ዓመታት መሥራቱ ለመጣው ለውጥ አንዱ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሊባል ይችላል።

በዚህም በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችና ኢትዮጵያውያን ወርቅ የማውጣትም ሆነ የማዘዋወር ፈቃድ ሳይኖራቸው በዚህ ሕገወጥ ተግባር ውስጥ ተገኝተው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወቃል። በዚህም ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለውጥ እንዲያሳይ ማድረግ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

መንግሥት በ2017 በጀት አመት መጀመሪያ ወደ ሙሉ ትግበራ ባስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ደግሞ የወርቅ ሕገወጥ ግብይትን አከራካሪ መስበር የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ ምርት እንዲሁም ወደ ውጭ ከተላከ ወርቅ እየተገኘ ያለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬም ይህንን ይጠቁማል።

በ2016 በጀት ዓመት አራት ቶን ወርቅ ብቻ ነበር ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው፤ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ ግን ሰባት ቶን ወርቅ ወደ ባንኩ ገብቷል። በሩብ ዓመቱ ለውጭ ገበያ ከተላከ የወርቅ ምርት የተገኘው ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው። ማዕድን ሚኒስቴር በሩብ ዓመቱ የዓመታዊ እቅዱን 70 በመቶ ፈጽሟል። ይሄ የሚበረታታ ትልቅ ለውጥ ነው።

ከክልሎች የሚወጡ መረጃዎች ይህንኑ የሚያጠናክሩ ናቸው። ለአብነትም ከዋናው የወርቅ አምራች ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2016 በጀት ዓመት ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ ምርት 274 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዚህ እጥፍ 548 ኪሎግራም ወርቅ ወደ ባንኩ ገቢ ተደርጓል። ክልሉ በሩብ ዓመቱ ለባንኩ ገቢ ለማድረግ ከያዘው ዕቅድም በላይ ነው አፈጻጸም የታየው። ይህ ሁሉ በወርቅ ምርት ግብይት ላይ ተፈጥሮ የነበረው ችግር እየተፈታ መምጣቱን ያመለክታል።

በቅርቡ ደግሞ እንደ ሀገር የሚመረተውን የወርቅ መጠን መጨመር የሚያስችል የወርቅ ማምረቱን ሥራም ከባህላዊና ከኋላ ቀር አሠራር ለማውጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል አዲስ የወርቅ ፋብሪካ በጋምቤላ ክልል ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቋል። ፋብሪካው በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማምረት ወቅት ሊባክን የሚችለውን ወርቅ ከብክነት የሚታደግ መሆኑም ተገልጿል። በቀጣይም ሌሎች ዘመናዊ የወርቅ ፋብሪካዎች ልማቱን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።

እነዚህ በወርቅ ሕወገወጥ ግብይት ላይ የተወሰዱ ርምጃዎች፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራው፣ አዲስ የወርቅ ፋብሪካ ወደ ሥራ መግባቱ፣ በወርቅ አምራቾች ዘንድ የተፈጠረው መነሳሳት በወርቅ ምርት መጨመር ላይ ያመጡት እመርታ በቀጣይም ተመሳሳይ እመርታ እንዲመዘገብ ለማድረግ ያስችላል።

ሀገሪቱ ያላትን የወርቅ እምቅ አቅም በሚገባ ማልማት ከተቻለ ወርቅ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቁ ሀብት መሆን እንደሚችል ይታመናል፤ በሩብ ዓመቱ የታየው ለውጥም ይህን ያመለክታል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሕገወጦቹን መገዳደር የሚያስችል አቅም እንደፈጠረም መረዳት ቢታወቅም፣ የሀገሪቱ ሀብት ምን ያህል በሕገወጦች ሲመዘበር እንደቆየ በሚገባ ጠቁሟልና ሕገወጦችን ለመቆጣጠር የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ሀገር ከወርቅ ምርት ብዙ ትጠብቃለች። በተገኘው ለውጥም መዘናጋት አይገባም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር በጋምቤላ የተገነባው ኢትኖማይኒግ የወርቅ ፋብሪካን በመረቁበት ወቅት እንዳስታወቁትም ሀገሪቱ በዚሀ በጀት ዓመት ከወርቅ ሁ ለት ቢሊዮን ዶላር ለማምረት አቅዳለች።

በወርቅ ላይ የታየው ለውጥ ሊደነቅ የሚገባው ሆኖ፣ ካለው እምቅ አቅም፣ ከተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች፣ የወርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እየገቡ ያሉበት ሁኔታ ሀገሪቱ የያዘችው እቅድ ሲታሰብ ለለውጡ ዘላቂነት መሥራት የግድ ይሆናል!

አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You