“የባሕር በር ጉዳይ የመተንፈስ አለመተንፈስ ጉዳይ ነው”- ረዳት ፕሮፌሰር ጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር)

ረዳት ፕሮፌሰር ጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር)በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር

የዛሬው የዘመን እንግዳችን ጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር) ይባላሉ። የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆኑ፣ ያጠኑት የቅየሳ እና ካርታ ሥራ ምሕንድስናን ነው። እስከ ሦስተኛ ዲግሪያቸው የሠሩትም በዚህ ዘርፍ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳሉ የጂኦግራፊ እና ታሪክ መምህር ነበሩ። በአሁኑ ወቅት የሚያስተምሩት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስኩል ኦፍ ሲቪል ኢንጂነሪግ አርክቴክቸር ጂኦማቲክስ ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ውስጥ ሲሆን፣ ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው ያገለግላሉ። በዩኒቨርስቲው ውስጥ ሪሰርች ኤንድ ፐብሊኬሽን ኦፊስ ዳይሬክተርም ሆነው አገልግለዋል።

ኖውሌጅ ኤንድ ቴክኖሎጂ ኢንተርቼንጅ ፋውንደር ዳይሬክተር ሆነውም ሠርተዋል። ስኩል ኦፍ ሲቪል ኢንጂነር ኤንድ አርክቴክቸር ዲፓርትመንት ዲን እንዲሁም የሰርቬይን ትምህርት ክፍል ዲፓርትመንት ሄድ በመሆን ሠርተዋል። በኢትዮጵያ ቻሪቲስ ኤንድ ሶሳይቲስ የፕሮፌሽናል አሶሴሽን ውስጥ አሶሴሽኖችን በመወከል በቻሪቲስ ኤንድ ሶሳይቲስ ፎረም የቦርድ አባል ሆነው ወደ ዘጠኝ ዓመት አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ሰርቬይን ፕሮፌሽናል አሶሴሽን ፋውንደር ፕሬዚዳንት ሆነው እየሠሩም ይገኛሉ። በሌሎች የሕዝብ ልማት ድርጅቶች ውስጥ ይሳተፋሉ። እኚህ ምሑር፣ “የግብፅና አጋሮቿ ጠላትነት እስከ መቼ” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትመው ለአንባቢያን አቅርበዋል። |አዲስ ዘመንም ከባሕር በር እና ከቀይ ባሕር ጋር አያይዞ በዘርፉ ሰፋ ያለ ጥናት ያካሄዱትን ጥላሁን ኤርዱኖን (ዶ/ር) የዛሬ እንግዳ አድርጎ አቅርቧል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከባሕር በር አንጻር ያላትን ታሪክ በአጭሩ ይግለጹልን?

ጥላሁን (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ትንሽ አገር አይደለችም። እንደሌሎቹ አገራት ከቅኝ ግዛት በኋላ የተፈጠረችም አይደለችም። በጣም በጣት ከሚቆጠሩ ጥንታዊ ሀገራት መካከል አንዷ ነች። ይህን እውነታ የምናውቀው እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎችም የጻፉለትና የተናገሩለት ሐቅ ነው። እንዲያውም ትክክለኛውን መናገር ካስፈለገ ኢትዮጵያ የምትወሰነው በባሕር ብቻ አይደለም፤ በውቅያኖስም ጭምር እንጂ። ምክንያቱም ውቅያኖሶችም የእኛ እንደነበሩ በግልጽ የሚያሳዩ ታሪካዊ ካርታዎች አሉና ነው።

ለምሳሌ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሚያውቁት በምሥራቁ በኩል በቀይ ባሕርና በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ ያለ ታሪክ መኖሩን ነው። ከአፍሪካ በስተምዕራብ ያለው አትላንቲክ ውቅያኖስ ራሱ የኢትዮጵያ የሆነ እና ደቡብ ውቅያኖስ የሚባል እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርቡ “የግብፅና አጋሮቹ ጠላትነት እስከ መቼ?” በሚል ርዕስ ለሕትመት ባበቃሁት መጽሐፌም በመረጃ ተደግፎ የሰፈረ ሐቅ ነው።

አትላንቲክ ውቅያኖስ ማለት በአሜሪካ እና በአፍሪካ መካከል የሚገኝ ውቅያኖስ ነው። ይህ እውነታ እኛ ኢትዮጵያውያን የጻፍነው ወይም ደግሞ የኢትዮጵያ ወዳጆች የጻፉት ታሪክ ብቻ አይደለም። የዓለም አሳሾች የሠሩት ካርታም ጭምር አለ፤ በተጨማሪም ታሪክም አለ። የታሪክ ድርሳናትም ጉዳዩን ይናገራሉ። ይህ ጉዳይ በቻይናውያን ተጽፏል። በባቢሎናውያን ተጽፏል። እንዲሁም በሮማውን ተጽፏል። ረፈድ ብሎ ደግሞ በእነጣሊያን፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ እና በመሰሎቻቸው ተጽፏል። ስለሆነም እኛ የሚመለከተን ስለባሕር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ስለውቅያኖስም ጭምር ሲሆን፣ ውቅያኖስ ራሱ የኛ ነበር ማለት ነው። አትላንቲክም ሆነ ሕንድ ውቅያኖስ ከእኛ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ስለዚህም ምንም የሚያጠራጥርም ሆነ ግርታ የሚፈጥር ነገር የለውም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቅርብ ርቀት የሚገኘውን የባሕር በር ተፈጥሯዊ ሀብቷን የተነጠቀችበት ሂደት ምን ይመስላል?

ጥላሁን (ዶ/ር)፡ በተቃራኒው ምስጋና ይገባቸዋል መባል ከተቻለ ምስጋና የሚሆነው ለቅኝ ገዥዎች ነው። ከራሳቸው ሀገር ወጥተው ሌላን በመመኘት ለመዝረፍና ለመንጠቅ እንዲሁም ባሪያ ለማድረግ የዘመቱ የአውሮፓ ኃይሎች ናቸው። እኛ የባሕር በር ቀርቶ የውቅያኖስ በር ያለን ነበርን። ተስፋፊዎች ኢትዮጵያን በቁጥጥር ስር ማዋል ሲያቅታቸው በተለያየ መንገድ እየገዘገዙና በአሳሾች እየሰለሉ፣ የሀገር ጎብኚዎች በመምሰል የሀገር ምስጢር እያወጡ ሲገዳደሩን ኖረዋል። ለምሳሌ በመጀመሪያ በአሰብ አካባቢ ጣሊያኖች የተቆጣጠሩት እና የሰፈሩት በቀላል መንገድ ነበር። በእዛ አካባቢ ሡልጣን ነበሩ፤ ታሪኩ የሚጀምረው እርሳቸው ለዓሣ አስጋሪ ጣሊያናዊ ከአሰብ አካባቢ የተወሰነችን ቦታ ሽጠው ነው።

ከዚያ በኋላ እንደ ፍልፍል እየፈለፈሉ አሁን ኤርትራ የምትባለውን አካባቢ ጣሊያኖቹ በቁጥጥር ስር አደረጉ። ይህም ማለትም ከኤርትራ ሰሜናዊ ጫፍ እስከ ጂቡቲ መጨረሻ ድረስ ያለውን ስፍራ ነው። ይህም ከአንድ ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆን የባሕር በር ነው። አራት እና አምስት ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ያላት ኤርትራ፣ አንድ ሺ ኪሎ ሜትር የባሕር በር ይዛ 120 ሚሊዮን ሕዝብ የምታስተናግድ አገር ኢትዮጵያ ደግሞ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የባሕር በር አጥታ ትኖራለች ማለት ነው።

ስለዚህ ይህ ሀብቷ የተነጠቀው በራሳችን ጥፋት ነው። በእርግጥ ጣሊያኖች የሚኮነኑት ኤርትራን በቁጥጥር ስር አውለው በማስተዳደራቸው ብቻ አይደለም፤ ከዚያ አካባቢ ላለመውጣት እንደእነእንግሊዝ፣ እንደእነጣሊያን ሌሎችም ቅኝ የገዙ ሀገሮች በሙሉ ቀብረውት የሚሄዱት መጥፎ መጥፎ ነገር ነበረም፤ አለም። ኤርትራ የጣሊያን ቅኝ ግዥ በነበረችበት ወቅት ለኤርትራውያን ይፈቀድ የነበረው ሲኒማ ቢዶቲ የሚባል ሲኒማ ቤት ብቻ ነው። እሱም በግልጽ ስድብ ባዘለ ስያሜ የሚጠራ ሲኒማ ቤት ነበር።

በወቅቱ ኤርትራውያን ከአራተኛ ክፍል በላይ እንዳይማሩ ሲደረጉ ነበር። ይህ ሁሉ ግፍ ተፈጽሞባቸው እንኳን የወቅቱ ተቃዋሚዎች “በጣሊያን ቅኝ ተገዝተን ስለነበር ከኢትዮጵያ እንነጠል፤ ከዚያም የቅኝ ግዛቱ ውል እና የድንበር ውል ይከበርልን” የሚል ሐሳብ ይዘው ተነሱ። በዚህም ሀሳብ ታገሉ። ይህን ሁሉ ትግል ሲያደርጉ የነበረው አንድ ሺ ኪሎ ሜትር የባሕር በር ለመያዝ ነው።

በእርግጥ የባሕር በር ሀብታችንን መልሰን ይዘነው ነበር። ዳግም ልንነጠቅ የቻልነው ጣሊያኖች ይዘውት ስለነበር ነው፤ እንግሊዞች ደግሞ ከጣሊያኖች ወስደው በሞግዚትነት አስር ዓመት አስተዳደሩ። ከዚያ በኋላ እንደገና በአፄ ኃይለሥላሴ ሰፊ ትግልና ተጋድሎ አምጥተነው ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያን ኃያልነትን የማይደግፉ ኃይሎች መልሰው ደግሞ ውስጥ ለውስጥ ሴራ መሸረብ ያዙ። በተለይ ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ የእነሱዳን እና ግብፅ መሰሪነት እየበረታ መጣ። ከእነርሱ ጀርባ ያሉ 22 የዓረብ ሀገራት በሙሉ ከእነርሱ ጋር በመተባበራቸውም መልሶ ከእጃችን ወጣ።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን ከባሕር በር ቀጣና የማሸሹ ፍራቻ እና ተገፍታ የመውጣቷ ምስጢር ከምን የተነሳ ነው ይላሉ?

ጥላሁን (ዶ/ር)፡- ምስጢሩ በዋነኝነት ከኢትዮጵያ የተለየ ባሕሪ ነው የሚል እምነት አለኝ። ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ ናት። በዙሪያዋ ባሉ በሁሉም አገሮች ዘንድ ማለት ይቻላል የውሃ ችግር አለ። ሌላው ቀርቶ ከኬንያ ጋር በራሱ ከውሃ ጋር የተያያዘ ችግር አለ። ኬንያ ቱርካና ሐይቅ የሚገባው የኦሞ ወንዝ እንዳይነካ ትፈልጋለች። የኦሞ ወንዝ ተብሎ የሚጠራው ከኢትዮጵያ ከተለያየ ቦታ የሚነሱት ግቤ ወንዝ እና ዋቤ ወንዝ ተቀላቅለውት ነው። እንደሚታወቀው ደግሞ የኢትዮጵያ ወንዝ ወደሁሉም አቅጣጫ የሚፈስ ነው።

ምንም እንኳ ዓረቦች የቱንም ያህል ስጋት ቢኖራቸውም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ የሰውን የማይነካ የራሱን የማይሰጥ ነው። ሌሎቹ ሀገራት በቅኝ ግዛት ሲገዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተገዛ ሕዝብ ነው። በቅኝ ገዥዎች ያለመገዛቱ ምስጢር የራሱን መስጠት ስለማይፈልግና የሌላውንም መውሰድ ስለማይፈልግ ነው። የብዙዎቹ ሀገራት ትልቁ ፍራቻቸው ኢትዮጵያ ወንዞችን ገድባ ውሃ ታሳጣናለች ከሚል የመነጨ ነው። ይህን የምታባብሰው እና ድራማውን የምትጫወተው ደግሞ ግብፅ ናት።

አዲስ ዘመን፡- የባሕር በርን በተመለከተ የኢትዮጵያ መሪዎች የዘመናት አቋምን እንዴት ይመለከቱታል?

ጥላሁን (ዶ/ር)፡ ከጥንቶቹ እንጀምር፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በአብርሃ እና አፅብሃ ዘመን ቀይ ባሕርን ተሻግረን የመንን፣ ከፊል ሳዑዲ ዓረቢያንም አስተዳድረናል። ቀይ ባሕር ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አልነበረም፤ አይደለምም፤ ከዚያ ቀጥሎ አፄ ቴዎድሮስን ብንመለከት እንዲያውም እርሳቸው ሁሌ የሚታወሱበት አንድ አባባል እንዳለ እናውቃለን። አፄ ቴዎድሮስ፣ የኢትዮጵያ ግዛት እስከኢየሩሳሌም መሆኑን ሲናገሩ የሚደመጡ ነበሩ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ግዛት እንኳን ቀይ ባሕር ቀርቶ እስከ ሜዲትራንያንም የሚዘልቅ መሆኑ የሚታመን ነው።

ወደ ዓፄ ዮሐንስ ስንመጣ፤ በግልጽ ቋንቋ የተቀመጠ ነገር አለ። እንዲያውም በቅርብ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ባሕር በር ነች፤ ድንበርም ነች። ወደ ዓፄ ምኒሊክ ዘንድ ሲመጣ ደግሞ ከጣሊያን ጋር ስንዋጋ በረሃብ የተነሳ ድርቅና እልቂት ነበር። ጣሊያንን ከኤርትራ ገፍተው ወደእኛ ሲገባ ወደምፅዋ መግፋት ግን አልቻሉም። ጣሊያን በአየር ከላይ ሲያዘንብብን የነበረው መርዝ ነው። እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆኖ የወጣችበት ጦርነት እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። ዓፄ ምኒልክ ኤርትራን ከጣሊያን እጅ ነፃ ለማውጣት የሚታሙ አይደሉም። ከኤርትራም ለማስወጣት ፍላጎት ነበራቸው፤ ይሁንና ፍላጎት ብቻ ምንም ዋጋ የለውም። ዓድዋን አስለቅቀው አሁን ያለውን በትግራይ በኩል ሰሜናዊ ድንበርን ይዘው እንዲቀመጡ ያስገደዳቸው የጣሊያን መርዝ የሚረጭ ሁኔታ እና ተፈጥሮ ነው።

ወደ ዓፄ ኃይለሥለሴ መለስ ስንል ደግሞ ኤርትራን መልሰው ከኢትዮጵያ ጋር ቀላቅለው ነበር። በዚህም የአንድ ሺ ኪሎ ሜትር የቀይ ባሕር ባለቤት፣ የእነዳህላክ ወደቦች ባለቤት አድርገውንም ነበር። መንግሥቱም መጨረሻ ላይ በማይጠበቅ መንገድ ከሀገር ቢሸሽም ለዚያ ሲሟሟት እና በእጅጉ ሲጋደል የቆየ ነው። እድሜውንም ሙሉ ሲታገል ኖሯል።

ቀደም ሲል ነበረው አገዛዝ ግን ሁልጊዜም በታሪክ ተወቃሽ ነው። የቅኝ ግዛት ድንበር እንዳለ ተግባራዊ እንዲደረግ በመወትወት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ እንድትሆን ፈረዱባት። 120 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደብ ገዝቶ ይኑር የሚል ፍርድ በኢትዮጵያ ላይ የተፈረደው በቀድሞ መንግሥት ነው።

የቅድመ አያቶቻችንና የአያቶቻችን ታሪክ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር ግን ለሀገራቸው ጥቅም መከበር የሚሞቱ መሆናቸውን ነው። እነርሱ ለሀገራቸው ጥቅም ለመቆም ቅንጣት ታህል አያመነቱም። የኢትዮጵያ የሆነውን ቅንጣት ታህል መሬትም አይሰጡም። የሌላውን ስንዝር ታህልም መሬትም አይፈልጉም።

አዲስ ዘመን፡- የባሕር በር ማጣት የሚያስከትሉ ጉዳቶችን በተመለከተ ዘርዘር አድርገው ቢያብራሩልን?

ጥላሁን (ዶ/ር)፡- የባሕር በር ማለት የመተንፈስ አለመተንፈስ ጉዳይ ነው፤ የገቢና ወጪ ምርት ጉዳይ ነው። ያመረትነውን ወደውጭ የምናስወጣበት፤ ከውጭ የሚመጣውን ደግሞ የምናስገባበት ጉዳይ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የባሕር በር የተዘጋባቸው ሀገሮች የባሕር በር እጦት አደጋ የሚሆንባቸው በጦርነት ጊዜ ነው። ለምሳሌ ከአንዱ የአፍሪካ ወይም የዓረብ ሀገር ጋር ጦርነት ብንገጥም የጦር መሣሪያ የምናስገባው በየትኛው ወደብ ነው? እንደሚታወቀው ደግሞ ሁሉን የጦር መሣሪያ እኛ አናመርትም። የማናመርት ከሆነ ደግሞ የተመረተውን መግዛት የግድ ነው፡።

ለምሳሌ የምንዋጋው ከሱዳን ጋር ነው ብንል፤ ጅቡቲ ፈልጋም እንኳ ባይሆን የዓረብ ሊግ አባል ሀገራት ጋር የአባልነት ስምምነት መሠረት የአንዱን አባል ሀገር ጥቅም የሚጎዳ ነገር በወደብ ማሳለፍ አትችልም። አደጋው እዚህ ላይ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ ወደብ ቅንጦት አይደለም። ወደብ እንደእኛ አይነት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለው ሀገር ከ60 ኪሎ ሜትር ባነሰ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ አለማግኘት ማለት ከባድ ነው።

ይሁንና ተፈጥሯዊ መብት ያለን ከመሆናችንም በላይ ቀይ ባሕር የሚለውን ስያሜ ያወጣነው እኛ ነን። ዛሬ የዓለም ሕዝብ በእንግሊዝኛ (Red sea) እያለ ሊጠራው ይችላል። ምክንያቱም እነርሱ የእኛን ተረጎሙት እንጂ እኛ የእንግሊዝኛውን ስያሜ ወደ አማርኛ አልተረጎምንም። በመሆኑም በታሪክ እኛ ጥንታዊ ነን። ለዚህ ደግሞ ማረጋገጫ ሊሆን የሚችለው ትልቁና ዋነኛ ተጠቃሽ የሚሆነው እንደእነሉሲ አይነት ታሪክም ጭምር ነው። ይህ የሰው ዘር መገኛነታችንን የሚያመላክት ነው። ከዚህ የተነሳ ወደብ አጥቶ መኖር ፈታኝ ነው። እንዲያም ሆኖ አደጋው ገና አልተሰማንም።

በየጊዜው ጅቡቲን እያሳደግን እኛ የምንቆረቁዝበት ምክንያት መኖር የለበትም። ይህን ማስተዋል የምንችለው ግን ኢንዱስትሪዎቻችን በሚፈለገው ልክ እያመረቱ ባለመሆናቸው ነው። በአሁኑ ወቅት ጉዳቱ ያን ያህል ያልቆረቆረን የምናስገባው ብቻ በብዙ ስለሚበልጥ ነው። በጥቅሉ የባሕር በር የማጣት ጉዳቱ በአንድ ነገር ብቻ የሚለካ ሳይሆን በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውም ሆነ በማኅበራዊው ጉዳይ ሁሉ ነው ማለት ይቻላል።

በሌላ በኩል የባሕር በር የማጣት ጉዳይ በባሕር ውስጥ የሚገኘውንም ሀብት ጭምር የሚያሳጣን ነው። የወደብ ጥገኝነት ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የባሰ ነው። የወደብ ጉዳይ ከብዙ ነገር ጋር የሚያያዝ ነው። ከውጭ የሚመጣን ጠላት ለመከላከል ጠላትን መያዝ የሚገባው ባሕሩን ከመሻገሩ በፊት ነው። ባሕሩ የእኛ ካልሆነ ግን የሚመጣው በምድር ስለሆነ ቀጥታ ወደእኛ መዝለቅ ይችላል። ከዚህም የተነሳ የባሕር በር የማጣት ጉዳቱ መጠነ ሰፊ ነው በሚል መግለጹ የተሻለ ነው።

በመሆኑም ወደብ ለኢትዮጵያ የግድ ነው። እንዲህ ሲባል ግን የማንንም መብት ለመቀማት አይደለም። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ወደቦች የነበሩና ዝም ብለው አገልግሎት ሳይሰጡ የተቀመጡ አሉ፤ እነዚያም አገልግሎት መስጠት ቢችሉ መልካም ነው።

ኤርትራ አሰብን እና ምፅዋን ካልተጠቀመችበት ምን ያደርግላታል? ሱዳን፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ሱማሊያ ሆነች ጅቡቲ ወደብ አላቸው። የኤርትራን ወደቦች ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችባቸው ማን ይጠቀምባቸዋል? የኤርትራ ሕዝብስ ቢሆን የኢትዮጵያን የባሕር በር በመዝጋት የሚጠቀመው ነገር ምን አለ? ችግሩ ኤርትራ ውስጥም ስለኤርትራ የሚያስብ አለመኖሩ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥም በዘር፣ በጎሳ እና በሥልጣን የተተበተበ እንጂ ለኢትዮጵያ የሚያስብ ባለመኖሩ ነው። ቢኖር ሁለቱ ሀገሮች የሚቸገሩበት ምክንያት አይኖርም ነበር ባይ ነኝ።

አዲስ ዘመን፡- የባሕር በር አጠቃቀምን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ሕጎች ምን ይላሉ? ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ጥያቄዋ ምን ያህል ተገቢ ነው ይላሉ?

ጥላሁን (ዶ/ር)፡- ከዚህ ጥያቄህ በፊት አስቀድሜ ላነሳ የምፈልገው ነገር የትኛው ዓለም አቀፍ ሕግ ነው? ማነውስ ነው ሕጉን የሚያከብረው? ሕጉንስ ቢሆን ማን ነው ያወጣው? በመሠረቱ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚባለው በአብዛኛው ከቅኝ ግዛት በኋላ ቅኝ ገዥዎች መጥተው በሀገራት መካከል የሠሩት ድንበር ነው። አንደኛውን ሕዝብ ከሌላኛው ሕዝብ ጋር እያጋጩ ለመኖር ትክክል ያልሆነ ድንበር ፈጠሩ። ልክ ያልሆነውን ሕግ ነው ዓለምአቀፍ ሕግ በማለት መርሕ ሆኖ የሚመጣው እንጂ ሀገሮች አሊያም ሕዝቦች ተስማምተው ያወጡት ሕግ የለም። ያለው የቅኝ ገዥዎች ኃያላን የሚባሉ ሀገሮች ለራሳቸው በሚመች መንገድ ያወጡት ሕግ ነው።

እንደዚያ ከሆነማ አሜሪካ ከጎረቤቷ ጀምሮ ስንት እና ስንት የሌላ የሆነውን ግድብ አፈረሰች? ለምሳሌ የሜክሲኮን አፍርሳ ስትሠራ ማን “ተይ!” አላት? አንዳንዶቹ ኃያላን ሀገራት ሥራቸውን የሚሠሩት ዝግት አድርገው ነው። ምንም አይነት ነገር ሳይሉ ነው። የቅኝ ግዛት ውልን እና ድንበርን ይከበር የሚሉት ለዚህ ነው። ለምሳሌ ኤርትራ በጣሊያን ቅኝ ተገዝታ ስለነበር ጣሊያን ባሰረችው መስመር ብቻ ተወስናችሁ ኑሩ እያሉን ነው።

ስለዚህ ስለምንድን ነው ስለዓለም አቀፍ ሕጉ እንድናስብ የምንደረገው? ማሰብም የለብንም፤ መስመር አስምረው የሚሰጡን እነርሱ ናቸው እንዴ? ያልተጋበዙ እንግዶች መጥተው አልጋችንን ሊወርሱ አይገባም፤ ከሆነም ሊተኙ የሚገባው ያነጠፍንላቸው ቦታ ነው። ስለዚህ የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት በሚፈታተንበት መንገድ የሠሩት ድንበር መፍረስ አለበት። በእነርሱ ብቻ የወጣው ዓለም አቀፍ ሕግም መፍረስ አለበት ባይ ነኝ። በተለይ ቅኝ ግዛት የሚባል ውል መፍረስ አለበት።

የግብፅን በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል። ግብፅ ሁለት አስገዳጅ ስምምነቶችን ማለትም የ1929 እና የ1959ኙን እንድናፀድቅ ትሻለች። የ1929ኙ እንግሊዝና ግብፅ የተፈራረሙት ነው። ይህ ማለት ቅኝ ገዥው እና ቅኝ ተገዥው ነው። ሁለቱ ብቻቸውን የተፈራረሙት ደግሞ ውሃ አመንጪዋ ሀገር ኢትዮጵያ በሌለችበት ነው። የ1959ኙ ደግሞ ግብፅ እና ሱዳን የውሃ ክፍፍልን አስመልክተው ተፈራረሙ። አንድ መለኪያ ውሃ የማያመነጩ ሀገራት ውሃ ሲከፋፈሉ ዝም ብለን ያየነው ጉዳዩን ማስረዳት አቅቶን ነው የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ከዚህ የተነሳ የግብፅ እና የሱዳን መንግሥታት የሚያራምዱት ሞራል የሌለው ፖለቲካ ነው። እንዲያው ተሳክቶላቸው ግብፅ እና ሱዳን ውሃውን ይከፋፈሉ እንበል፤ ታዲያ ስለምን ኢትዮጵያን አላካተቱም? ሲሆን ሲሆን ማካፈል የነበረባት ውሃ አመንጪዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። ስለዚህ ዓለም አቀፍ የሚባል ሕግ የለም። ዓለምን እየመራ ያለው ጉልበተኛ የሆነ አካል ነው። በመሆኑም አንድነታችንን አጠናክረን ከጎረቤቶቻችን ጋር ሆነን በጋራ ሊገዛን የሚችል ሕግ ማውጣት ነው ያለብን እንጂ የዓለም አቀፉ ሕግ አዋጭ መሆን አልቻለም።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በፊት በሀገር መሪ ደረጃ ሳይቀር ወደብ ሸቀጥ እንደሆነ ሲነገር ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የመኖር አለመኖር ጉዳይ እንደሆነ ታምኖበታል፤ ከዚህ አኳያ እርስዎ ምን ይላሉ?

ጥላሁን (ዶ/ር)፡- ከዚህ በፊት ወደብ ሸቀጥ ነው ሲባል ሰምተናል። በወቅቱ ሸቀጥ የተባለው የኢትዮጵያን ሕዝብ ዓይንና ጆሮ ለመድፈን ሲሆን፣ ጉዳዩንም አቅልሎ እንዲያይና ጥያቄም እንዳያነሳ በማሰብ ነው። ይሁንና በወቅቱ ኢትዮጵያ ባሏት ምሑራን ወደብ ሸቀጥ እንዳልሆነ ሞግታ ነበር። በወቅቱ ወደብ ሸቀጥ ነው ላሉ አመራር ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ደግሞ ግልጽ ነው። በዚያን ወቅት ወደብ ሸቀጥ ነው በሚል ለሌላ ተላልፎ መተው የኢትዮጵያን አንገት እንደመቁረጥ የሚቆጠር ጉዳይ ነው። ዓላማው የሕልም እንጀራ ሆኖ የቀረ ቢሆንም “ታላቋን ትግራይ” ለመፍጠር ነበር።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን አንድ ማንሳት የምፈልገው ነገር አለ። ግብፆች የአስዋንን ግድብ ከገነቡ በኋላ ግድቡን ለምረቃ አበቁ፤ በወቅቱ ግድቡ ሲመረቅ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ሲጠሩ የውሃ አመንጪዋ አገር ንጉሥ የሆኑት ዓፄ ኃይለሥላሴ ግን አልተጠሩም ነበር። በወቅቱ የነበረው የግብፁ መሪ አብዱል ናስር ሲጠየቁ ያሉት፤ “የዓባይ ጉዳይ ኢትዮጵያን አይመለከትም” ነው። ስለዚህ ግብፆች ጥፋተኛ ማድረግ ካለባቸው መሪያቸውን ነው እንጂ ኢትዮጵያውያንን አይደለም።

በአንድ ወቅት ዓፄ ኃይለሥላሴ የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥን የዓባይ በረሃ ወስደው ባስጎበኙበት ጊዜ ጢስ ዓባይን እያስጎበኟቸው እያለ ዓፄ ኃይለሥላሴ “ይህቺን ግድብ መገደብ እፈልጋለሁና ብር ያስፈልገኛል ያበድሩኝ” ሲሉ ይጠይቋቸዋል። ይሁንና ምላሻቸው የነበረው “አይ! ወዳጃችን ግብፅ ትቆጣለች” ነው። ንግሥቷ፣ እንዲያ ቢሉም አፄ ኃይለሥላሴ ያሉት ነገር ነበር። ይኸውም “ብድር ስጡን ብንል ግብፅ ትቀየመናለች ብለው አይሰጡንም። ” በአሜሪካውያን የተጠና ጥናት ነበርና “ጥናቱ በክብር ይቀመጥ፤ የእኛ ልጆች ይሠሩታል። ” ነበር ያሉት።

አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በርና የወደብ ጥያቄ ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ጥላሁን (ዶ/ር)፡- ከላይ እንደገለጽኩት የባሕር በር ጉዳይ እስትንፋስ ጉዳይ ነው። ስለዚህም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ ተገቢ ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በዚህ እንስማማለን። የራሳችን የሆነና እኛ የምናዝዝበት ወደብ ማግኘት አጠያያቂ አይደለም። እንዲህ ሲባል ግን የሆነ ሀገር ወረን የምናገኘው ጉዳይ አይደለም። የውስጥ ሠላማችንን ማስከበር እስከቻልን ድረስ በየትኛውም ጊዜ ወደብ የማግኘት መብታችንን ማስጠበቅ እንችላለን የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም የመጀመሪያው ጉዳይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደጋራ ማንነቱ ማምጣት ይቀድማል እላለሁ።

ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ነግሶ የሚታየው የብሔር እና የዘር ፖለቲካ ነው። ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ጥቂቶች ብዙኃኑን የኢትዮጵያ ሕዝብን ለማስተዳደር ሲሉ ሕዝቡን በዘርና በጎሳ መከፋፈልን እንደ መፍትሔ አድርገው ወስደው ነበር።

አሁን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀድሞ የነበረውን በጋራ አብሮ የመኖር ባሕሉን መመለስ ይኖርበታል። የመተሳሰብና የመከባበር እሴቱን ከወደቀበት ማንሳት ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ ሠላም ሊሰፍን የግድ ነው። ሠላም ካለ የሕግ የበላይነት ይሰፍናል፤ መልካም አስተዳደር ይመጣል። መልካም አስተዳደር የሚጀምረው ደግሞ ከታች ከቀበሌ ነው።

መልካም አስተዳደር ካለ የሕግ የበላይነት አለ ማለት ነው። የሕግ የበላይነትም ሠላምም ካለ የልማት ፍላጎት አለ ማለት ነው። ልማት ካለ ደግሞ ብልፅግና አለ። ብልፅግና ሲኖር ምንም ሳንጠይቅ ወደባችንን ተጠቀሙ የሚል አካል በራሱ ጊዜ ይመጣል። ነገር ግን ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ሠላም መኖር አለበት።

ሠላምን ለማስከበር መንግሥት ረጅም ርቀት መሄድ ይጠበቅበታል። መጀመሪያ የውስጥ ሠላማችን ላይ መሥራት አለብን። ሠላም ሳይመጣ የምንጀምረው የወደብ ጥያቄ መጥፊያችን ይሆናል። እጅግ አደገኛ ነው። በመጀመሪያ ሠላም የሚነሱንን ችግሮች ማምከን አለብን።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ተፅዕኖ መልሶ ለማምጣት ምን መደረግ አለበት?

ጥላሁን (ዶ/ር)፡- በቀይ ባሕር ላይ በአሁኑ ሰዓት ምንም አይነት ሚና የለንም። የነበረንን ሚና ካጣን ቆየን። አንደኛ በአሰብ አካባቢ በርካታ ሀብት ነበረን። አሰብ ላይ ያለን ወደብ ብቻ አልነበረም፤ የነዳጅ ማጣሪያም ጭምር እንጂ። ከዚህ ሌላ በጣም ጠንካራ የነበረ የባሕር ኃይልም ነበረን።

ቀደም ሲል እርግጥ በቀይ ባሕር አከባቢ ኢትዮጵያ የነበራት ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበር። ያንን ተፅዕኖ ይዛ ቆይታ ቢሆን ዛሬ ላይ የት በደረሰች ነበር? የገነባነው ጠንካራ የባሕር ኃይል ነበርና በሱማሊያ አካባቢ የሚታየው የባሕር ላይ ውንብድና ባልኖረም ነበር። ይሁንና አሁንም ቢሆን ተስፋ የሚቆረጥበት አይደለም። በቀጣይ ተፅዕኖ ይኖረናል የሚል እምነት አለኝ፡። እኔ ተስፋ አልቆርጥም። ይህ ግን የሚወሰነው የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝቡን የሚይዝበት አያያዝ ሲስተካከል ነው፡።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው በሠላም መኖር ነው። ለፖለቲከኞች ብሎ መሞት አይፈልግም። በተጣመመ ፖለቲካ ምክንያት ደግሞ ሀገራችን እንድትበተን ሕዝቡ አይፈልግም። እና ኢትዮጵያውያን ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ብዙ ጊዜ እንፈርስ የነበርን ሀገር ነን። ነገር ግን ሕዝቡ እጅግ በጣም ታጋሽ፣ ስብዕናው ላቅ ያለ እና ሀይማኖት ያለው ሕዝብ ነው። ዛሬ ሆዱን እየራበው ነገ ሌላ ቀን ይመጣል ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ሕዝብ ነው። ይህንን ሕዝብ ማስተዳደር አለመቻል ደግሞ ከባድ ነገር ነው። ይህ ሕዝብ ለማስተዳደር በጣም የሚመች ነው።

በዙሪያችን ያለው ወደብ በሙሉ ማለት ይቻላል በዓረብ ሊግ አባል ሀገራት የተያዘ ነው። ኤርትራም ተለዋጭ የዓረብ ሊግ አባል ሀገር ነች። ስለዚህ የራሳችን ወደብ የሚያስፈልገን መሆኑ የግድ ነው ማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም የምንጠቀምበት የጅቡቲ ወደብ እንደመሆኑ በጊዜ ሒደት ጅቡቲ ተፅዕኖ ውስጥ ልትገባ ትችላለች። ሱማሊያም ብትሆን የተዳከመች ሀገር ከመሆኗ በተጨማሪ አልሸባብም እያስቸገረ ነው። ሌላውም ወደብ የራሱ ተፅዕኖ ያለበት ከመሆኑ በተጨማሪ የቀድሞ ቅኝ ገዥዎች የእጅ አዙር ተፅዕኖ ያለበት ነው።

ስለዚህ እኛ ወደብ እንድናገኝ ማድረግ ያለብንን ሁሉ በእቅድ በመያዝ ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል። ውስጣዊ ሠላማችንን ስናረጋግጥና ልማትችን ስናፋጥን የጀመርነው የባሕር በርም ሆነ የወደብ ጥያቄ መልስ ያገኛል። ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ያድጋል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

ዶክተር ጥላሁን፡- እኔም ዕድሉ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You