የተወለዱት በድሮ አርሲ ክፍለሀገር አርባ ጉጉ አውራጃ ነው። ያደጉትም በዛው በመርቲ ወረዳ ቀጤ እና ከቢሮ መንደር ነው። ትምህርታቸውን ከአንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል የተከታተሉት አቡምሳ ከተማ ሲሆን፤ በከተማው የነበረው አንድ ትምህርት ቤት ብቻ ስለነበር የ8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ አሰላ ጠቅላይ ግዛት መሔድ ነበረባቸው።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ትምህርታቸውን በዛው እንዲቀጥሉ፤ ትምህርት ቤቱም ከ8ኛ ክፍል በላይ እንዲያስተምር ውሳኔ ተላለፈ። እሳቸውም ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን ትምህርት ቤቱ በቂ መምህር እና የማስተማሪያ መሣሪያ የለም በሚል አመጹ። ‹‹ወላጆችን ስንቅ በመላክ ልታስቸግሩ ነው። ትምህርት ቤቱን ዕድል ልታሳጡት ነው›› በሚል የወላጅ ኮሚቴ፣ የአውራጃው ትምህርት ጽሕፈት ቤት እና መምህራን በፈጠሩት ጫና በ1967 ዓ.ም የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን እዛው ተማሩ። በ1968 ዓ.ም እንደገና በተማሪዎች እና በአስተማሪዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ዓመቱን ሙሉ ትምህርት ቤቱ ተዘጋ።
በ1969 ዓ.ም ትምህርት ቤቱ ተመልሶ መማር ማስተማር ሥራው ሲመለስ፤ ተማሪዎቹ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ተሳታፊ በመሆን የተለያዩ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ማንሳት ጀመሩ። በዚህ ሳቢያ ትምህርታቸውን አቋርጠው ለእስር የሚዳረጉባቸው ሁኔታዎች ተከሰቱ። እሳቸውም ከታኅሣሥ እስከ ግንቦት መጨረሻ ታስረው ተፈቱ። ከአንድ ወር በኋላም ለፈተና ተቀምጠው ፈተናውን አልፈው ‹‹ወደ አስራ አንደኛ ክፍል ተዘዋውረሃል›› ተባሉ። ወደ አሰላ ሔደው እንዲማሩም ተፈቀደላቸው። እርሳቸው ግን በተወለዱበት አካባቢ/ጠቅላይ ግዛት የመማር ግዴታ ቢኖርባቸውም፤ ታስረው በመቆየታቸው እና እዛ የነበረ ታሪካቸው እንዳይከተላቸው አሰላ መማር አልፈለጉም።
በ1970 ዓ.ም በዘመድ እርዳታ ሸዋ ያለው አፄ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት ገቡ። ትምህርት የሚማሩት በፈረቃ ነበር። የትምህርት ቤቱን አስተዳዳሪዎች በመጠየቅ በቅጡ ሳይማሩ ያለፉትን የ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ጠዋት፤ የ11ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከሰዓት ተማሩ። ለ12ኛ ክፍል ፈተና በደንብ በመዘጋጀታቸው አልፈው አለምማያ እርሻ ኮሌጅ ገቡ።
ከገበሬ ቤተሰብ ቢወለዱም ገበሬ አልሆኑም። ያልተማሩት ቤተሰቦቻቸው ከተማረውም ሰው በላይ አርቀው የሚያስቡ በመሆናቸው ብዙ ዋጋ ከፍለው አስተማሯቸው። እርሳቸውም ለመማር ገና በለጋ ዕድሜያቸው አንዳንዴ በቀን አንድ ጊዜ እየበሉ 12 ኪሎ ሜትር እየተጓዙ ኮሌጅ ለመግባት በቁ። በመጀመሪያ ዲግሪ ሳይገደቡ፤ የሦስተኛ ዲግሪ ባለቤት መሆን ቻሉ።
የዛሬ እንግዳችን በአሁን ወቅት የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅቶች ልማት ማኅበር (Consortium of Christian Relief and Development Association) ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ፈቃድ የሚሰጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የቦርድ አባል፣ የግሎባል ፈንድ ምክትል ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ጥምረት ለምርጫ ቦርድ ዳይሬክተር በመሆንም እያገለገሉ የሚገኙት ዶክተር ንጉሠ ለገሰ ናቸው ። ከሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
አዲስ ዘመን፡- ዓለምማያ እርሻ ኮሌጅ እንዴት ገቡ? ፍላጎትዎ ምን ነበር ከሚለው ጀምረን እንቀጥል?
ዶ/ር ንጉሡ፡- በጊዜው ኮሌጅ የሚገባው በኮታ ነበር። ፈተና ያለፈ ተማሪ ከአንድ እስከ ስድስት ምርጫ ይሰጠው ነበር። ከእኔ ጋር እኩል ነጥብ ካመጣ ጓደኛዬ ጋር ሕክምና ለመማር ፎርም ሞላን። በቅደም ተከተል 1ኛ ሜዲካል፣ ኢንጂነሪንግ፣ አግሪካልቸር፣ ናቹራል ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፔዳጎጂ በማለት መረጥን። ሆኖም ግን ጓደኛዬ ከሔደ በኋላ ትንሽ ቆይቼ ከአዳማ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ወደ ወንጂ ልሳፈር ስሔድ ሌላ ጓደኛዬን አገኘሁ። ጓደኛዬ ‹‹ሰባት ዓመት ዶክተር ለመሆን ከምትማር ቀድመህ ሦስት ዓመት በግብርና ከተማርክ በኋላ በዛው ቀጥለህ ዶክተር ለመባል ትበቃለህ።›› ሲለኝ ከመኪና ተራ ተመልሼ፤ ወደ አፄ ገላውዲዮስ ሄጄ፤ የመጀመሪያ ምርጫዬን ግብርና አድርጌ ከተመረጡ አምስት ሰዎች ውስጥ አንዱ እኔ ሆንኩ።
አዲስ ዘመን፡- የዩኒቨርስቲ ሕይወትዎት እንዴት ነበር?
ዶ/ር ንጉሡ፡- ጊዜው በ1971 ዓ.ም ነበር። ወደ ኮሌጁ የተቀላቀለው ሁለት ቡድን ነበር። አንደኛው ቀድሞ አንድ ዓመት የኮሌጅ ትምህርት ተምሮ ተፈትኖ የመጣው ቡድን ነው። የእኛ ቡድን ደግሞ ጀማሪ የኮሌጅ ተማሪ ነበር። ዩኒቨርስቲው በሶማሌ ጦርነት ምክንያት ለሁለት ዓመት ትምህርት አቋርጦ፤ ሰው ናፍቆት ነበር። ስለዚህ አቀባበል የተደረገልን ከኮሌጁ አምስት ኪሎ ሜትር አቋርጠው በመጡ የኮሌጁ አመራሮች አማካኝነት ዓለምማያ ከተማ ላይ ነበር። አንድ ዓመት ከተማርን በኋላ በድጋሚ አራት ምርጫ ቀረበልን። አንደኛው የዕፅዋት ሳይንስ፣ የእንስሳት ሳይንስ፣ ምጣኔ ሃብት እና የግብርና ኢንጂነሪንግ ነበር። የእኔ ምርጫ የዕፅዋት ሳይንስ ነበር።
ለሦስት ዓመት የዕፅዋት ሳይንስ ተምሬ በ1974 ዓ.ም መጨረሻ ተመረቅኩ። ዓለምማያ መምህር ለመሆን ተወዳደርኩና ተመረጥኩኝ። ነገር ግን የኮሌጁ አስተዳደር እና የዲፓርትመንቱ ኃላፊ ግጭት ውስጥ ነበሩ፤ በሁለቱ አለመስማማት በጀት የለንም በሚል ሰበብ ዓለምማያ አስተማሪ መሆን አልቻልኩም። እውነት ለመናገር ለመማር እንጂ ማስተማሩን ፈልጌው አልነበረም።
በጊዜው አስተማሪነት ቢቀርም ሌላ ሥራ ለማግኘት የሚያስፈልገው ዕጣ ማውጣት ብቻ ነበር። ዕጣ ሳወጣ ወለጋ ያሉ እርሻዎች ደዴሳ አካባቢ ደረሰኝ። በዕጣዬ ደስተኛ አልነበርኩም። ምንም እንኳ አርሲ በመወለዴ ቋንቋውን ብችልም፤ አካባቢውን ስለማላውቀው እና በአካባቢው ሰላም የለም ስለሚባል ለመሔድ ከበደኝ። አንድ የጎጃም ልጅ ደግሞ ወለጋ መሔድ ይፈልግ ነበር። የደረሰው ምርጥ ዘር ነው። ማቀያየር ይቻል ነበር፤ ስለዚህ ሃሳቡን ሳይቀይር ቶሎ ከእርሱ ጋር ተለዋወጥን። በዚህ ምክንያት ምርጥ ዘር ኮርፖሬሽን ገባሁ። ምርጥ ዘር ድርጅት ከገባሁ በኋላም እንደገና የመጨረሻ ማረፊዬን ለመወሰን ዕጣ ማውጣት ነበረብኝ። አማራጮቹም አንደኛው ወለጋ፣ ሁለተኛው ባሌ ሦስተኛው ደግሞ አርሲ ነበር። ባሌ ወጣልኝና ወደ ባሌ ሔድኩኝ።
የባሌው ሥራ ሰፊ ነበር። የመንግሥት እርሻዎች ዘር ማባዣ ጣቢያው፣ ዘር ማበጠሪያው ሁሉም በእኔ ሥር ነበር። ለሦስት ዓመት ጥሩ የሥራ ልምድ አገኘሁ። በሁለተኛ ዲግሪ የዘር ቴክኖሎጂ እንድማር ዕድሉ ተሰጠኝ። በወርልድ ባንክ ገንዘብ እንግሊዝ ስኮትላንድ ኤድንብራ በተባለች ከተማ የዘር ቴክኖሎጂ ተማርኩኝ። እርሱን እንደጨረስኩ ከእዛ ሳልመለስ ሦስተኛ ዲግሪ ለመማር የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች አመለከትኩኝ። አሜሪካን ኦሪጋን ዩኒቨርስቲ አገኘሁ። ነገር ግን በረዳትነት እየሠራሁ ሰባት ዓመት እንድማር ያስገድዳል። ሰባት ዓመት እስረኛ ሆኜ ሦስተኛ ዲግሪ ማግኘት በዛብኝ ብዬ ተውኩት።
አውስትራሊያዎች ደግሞ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ። መንግሥትህ ይፍቀድልህ ተባልኩ። የተላኩት ለሁለተኛ ዲግሪ እንጂ ለሦስተኛ ዲግሪ ባለመሆኑ ማንም እንደማይፈቅድልኝ ስለማውቅ ተውኩት። እዛው እንግሊዝ ስሞክር አፍሪካ ኤዱኬሽናል ትረስት የተባለ ድርጅት ‹‹ዕድሉን እሰጥሃለሁ፤ ዩኒቨርስቲ መርጠህ አሳውቀን አለኝ።›› ሬዲንግ የተባለ ዩኒቨርስቲን መምረጥ ፈልጌያለሁ። ምክንያቱም ዘር ሲከማች እንዳይበላሽ ዕድሜው እንዲረዝም እ.አ.አ በ1960 ሴራሊዮን ላይ የተጠና ጥናት በቲዎሪ ብቻ የተቀመጠ ነበር። ጥናቱን በተግባር መሞከር ፈለግኩ። ነገር ግን እዛ ለመማር ጥያቄ ሳቀርብ ተመራማሪው እረፍት ላይ ነበር። ጥያቄ ሳቀርብ፤ ተቀባይ አጣሁ። ከአቨርጂን ዩኒቨርስቲ ያስተማረችኝ ፕሮፌሰር መምህርት ነበረች። እርሷ ጋር ጥያቄ ሳቀርብ ወዲያው ተቀበለችኝ። እዛው ስኮትላንድ ወደ ሰሜን ራቅ ባለ ቦታ፤ ለአራት ዓመት ተማርኩ።
በዚህ መሐከል ፓስፖርቴ ጊዜው አለፈ። ለንደን ኢትዮጵያ ኤምባሲ ሄድኩ፤ ፓስፖርቴ ይታደስልኝ ብልም ለአንድ ዓመት ብቻ መጥተህ መመለስ ሲገባህ፤ በመቆየትህ አናድስም አሉኝ። በዚህ ምክንያት ሀገሬ ገብቼ ማገልገል ብፈልግም አልሆነም። በዛ ምክንያት ፓስፖርትም ሆነ መታወቂያ የለኝም ነበር፤ ምንም ነገር ሳይኖረኝ ቆየሁ።
ታኅሣሥ 1990 የመመረቂያ ጽሑፌን ጨርሼ ባቀርብም፤ ፈታኜ ከኢንግላንድ የሚመጣው መጋቢት ነው ተባለ። በዛ ጊዜ ኢትዮጵያ ኢሕአዴግ ሊገባ ነበር። እኔ ደግሞ ሀገሬ ለመግባት ፈልጌ ነበር። ፈታኜ ሦስት ወር ቆይቶ መጣ፤ ተፈትኜ ውጤቴ ጥሩ ሆኖ ሦስተኛ ዲግሪዬን አገኘሁ። ሆኖም ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቴ በፊት ኢሕአዴግ ገባ። ከመምጣቴ በፊት ወሬ ሳጣራ፤ እዚህ ያለውም ሰው ‹‹የዘር ፖለቲካ ሆኖ እንዴት ትመጣለህ? ›› አሉኝ፤ እዛ በሚካሔድ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ መሳተፍ ጀመርኩ።
በመጨረሻም ወደ ሀገሬ መጣሁ። አዲስ አበባ በምርጥ ዘር ላይ ዩ ኤን ዲ ፒ አሰላ ላይ የሚያሠራው ጥናት ነበር። እዛ አመልክቼ መሥራት ጀመርኩ። ለሁለት ዓመት እነርሱ ጋር ቆየሁ። እንግሊዝ ተመልሼ ሄድኩ፤ አንድ ዓመት ኮምፒውተር ሳይንስ ተማርኩ። ትምህርቱን ጨርሼ ስመጣ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያን ተራድኦ ኮሚሽን የሚል የኮሚሽነር ማስታወቂያ አየሁ። ቤተክርስቲያን መኖሩን እንጂ የቤተክርስቲያን የልማት ድርጅት መኖሩን አላውቅም ነበር። ተወዳደርኩ፤ መስከረም 24 የወጣ ማስታወቂያ አምስት ቃለመጠይቅ አልፌ በመጨረሻ ሲኖዶሱ ጋር ቀርቤ ሰኔ 8 ቀን 1995 ዓ.ም የልማቱ ኃላፊ ሆኜ ተቀጠርኩ። ሊዘጋ የነበረውን ቤት ለስድስት ዓመት ስሠራ ቆይቼ ውጤታማ መሆን ቻልን። ጥሩ ሥራ በመሥራቴ ስሜ ወደ ዓለም ወጣ።
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ማስታወቂያ ሲያወጣ ተወዳድሬ ጄኔቫ በሚገኘው የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ኃላፊ ሆኜ ለ10 ዓመታት አገለገልኩ። ከዛ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ፍላጎት ነበረኝ። በተጨማሪ ሲሲአር ዲኤ ላይ ትንሽ ቅሬታም ነበረኝ። አንደኛ ወጥቼ አሸንፌ እንዳልገባ ተከልክያለሁ። ከአስር ዓመት በኋላ የተሻለ ቦታ ሔጄ፤ እዚህ መጥቼ ዳይሬክተር ሆኜ እየገለገልኩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ሙያዎ እንመለስ፤ የመንግሥት እርሻ ላይ ሠርተዋል። በወቅቱ የደርግ መንግሥት ወደ እርሻ መግባቱ ምን ያህል ውጤታማ አድርጎታል?
ዶ/ር ንጉሱ፡- ብዙዎቹ ትልልቅ የመንግሥት እርሻ ልማቶች በግለሰቦች የተጀመሩ ናቸው። በጣም ውጤታማ እና አትራፊ ነበሩ። መንግሥት ሲወርሰው ብዙዎቹ ከአገር ወጡ መንግሥት ራሱ ልረስ አለ። ነገር ግን ብዙም አትራፊ አልነበረም። ግለሰቡ ወጪ እና ትርፉን እየተከታተለ ሲሠራ የተሻለ ነበር። የመንግሥት ሲሆን ግን ሠራተኛው ሠራም አልሠራም፤ ደሞዙንም ስለሚያገኝ ብዙ ውጤታማ አልነበረም።
በተወሰነ መልኩ ሲታይ ለመንግሥት ብዙ ጠቅሞት ነበር። መንግሥት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰሠራዊት ነበረው። ለዛ ቀለብ ማቅረብም ቀላል አልነበረም። የእህል ዋጋን ለመተመን ረድቶታል። በኮታ እህል ስጡ ሲባልም ገበሬው ማረሱን እየተወ ነበር። የመንግሥት ትኩረት ለመንግሥት እርሻ ነበር። ሆኖም የመንግሥት እርሻ ያስወጣ ከነበረው ወጪ አንፃር ውጤታማ አልነበረም። አዋጪ ስላልነበሩም አብዛኞቹ ከስመዋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ እና የዕፅዋት ሳይንስን አገናኝተው ይግለፁልኝ። ኢትዮጵያ ካላት የዕፅዋት ሃብት ምን ያህል ተጠቃሚ ሆናለች?
ዶ/ር ንጉሡ፡- ዕፅዋት ሳይንስ ሰፊ ነው። አትክልት እና ፍራፍሬው፤ ሰብል፤ የዘር ሳይንስ እና ሌላም እያልን ለየብቻው ማየት ይቻላል። እኔ በተማርኩበት ጊዜ ተማሪው ዕፅዋት ሳይንስን ጨርሶ ሲወጣ እኔ ወደ ዘር
እንደሄድኩት ሁሉ ግማሹ ወደ ደን ፣ አንዳንዱ ወደ ገብስ፣ ስንዴ እያንዳንዱ ወደፈለገው ቀጥሏል። ነገር ግን በጥቅሉ እንይ ከተባለ በምግብ እህል ዙሪያ ብዙ ጥረት ተደርጓል፤ በእርሻ ምርምርም ብዙ ተሠርቷል። ነገር ግን የኢትዮጵያን ግብርና ሥራ ሊለውጥ በሚችል መልኩ ውጤት ተገኝቷል ማለት አይቻልም።
በግብርና ምሕንድስናውም መካናይዜሽን በመጠቀም ገበሬው ከጉልበቱ ትንሽ ቆጥቦ ሻል ያለ ሥራ ተፈጥሯል ለማለት ይከብዳል። በእርግጥ በተለያየ ጊዜ ለገበሬው እርሻ የሚውሉ ዘሮች ይወጣሉ። ነገር ግን እነርሱን የመተካት እና የማሳደግ ሁኔታ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር ብዙ አልሔድንበትም። የሕዝቡ ቁጥር ደግሞ በየጊዜው እየጨመረ ነው። ሕዝቡ የጨመረውን ያህል የምርት ጭማሪ እየታየ አይደለም።
ቀድሞ ከሦስት እስከ አምስት ሚሊዮን ሰው ይራባል ይባል ነበር። አሁን ደግሞ ከአምስት እስከ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ እየተራበ ነው። ድርቅ እና ጦርነቱ ሲጨመር ወደ 20 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚራብ ይገለፃል። ይህ ሁሉ ሲታይ ግብርናው ብዙ ሥራ ይፈልጋል። መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ግብርና ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ ነው።
ኢትዮጵያ በቅኝ እንዳለመገዛቷ እና በግብርና ቀደምት ሀገር እንደመሆኗ ብዙ ውጤት አልተገኘም። ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በቅኝ የተገዙትም በነበረው ሥርዓት ለመቀጠል ሞክረው ብዙም አልተሳካላቸውም። ለምሳሌ የዳቦ ቅርጫት የምትባል የነበረችዋ ዚምባብዌ ሙሉ ለሙሉ ችግር ውስጥ ገብታ የገንዘብ ኖታቸው ላይ እሳት እስከመለኮስ እና በዶላር እስከመገበያየት ደርሰዋል።
ደቡብ አፍሪካም በተመሳሳይ መልኩ የውጪውም ተፅዕኖ ተጨማምሮባቸው ብዙ ውጤታማ አልሆኑም። ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ በቀኝ አልተገዛንም። በጃንሆይ ጊዜ ከምዕራቡም ከምስራቁም ጋር መልካም ግንኙነት ነበረን። ብዙ ተፅዕኖ አልነበረብንም፤ ስለዚህ ሾልከን መውጣት ነበረብን። ሆኖም በቂ ሥራ ባለመሥራታችን ሕዝቡን ከረሃብ መታደግ አልቻልንም። አሁንም ገበሬዎቻችን አልተሻሻሉም። ዛሬም የምናርሰው በበሬ ነው። አሁንም ብዙ ሥራ መሠራት አለበት ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በግብርና ሥራ ውስጥ ለዘመናት እንደመቆየታችን ለምን በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ መሆን አቃተን?
ዶ/ር ንጉሡ፡- በደርግ ጊዜ ምርጥ ዘር ድርጅት ስሠራ የዘር እጥረት ነበር። ዘር ጠፍቶ ብጣሪ እንዲዘራ ተባልን። ባለሙያው እንዴት ብጣሪ ይዘራል? ሲል ጠየቀ። ከላይ ያለው ደግሞ መሬቱ ባዶውን እንዳያድር ብጣሪም ቢሆን ዝሩ አለ። ለዚህ ሁሉ ያበቃን ከእርሻ ምርምር ተነስቶ ወደ ምርጥ ዘር የሚመጣው ግብዓት በቂ ባለመሆኑ ነበር። ዘር ለማባዛት ጊዜ ይወስዳል። ለምሳሌ ስንዴን ብንወስድ በትንሹ ከእርሻ ምርምር ጀምሮ እስከሚስፋፋ አስር እና አስራ ሁለት ዓመት እንደውም አስራ አምስት ዓመት ሊወስድ ይችላል። በዚህ ልክ ዝግጅት ካልተደረገ በአጭር ጊዜ ብዙ ውጤት አይመጣም።
በተጨማሪ የመንግሥት እርሻ ሰፊ ነው፤ ያለችውንም ዘር የሚወስደው መንግሥት ነው። ገበሬው ጋር የሚደርስ ነገር አልነበረም። ገበሬውን የጠቀመው ዘር የማስቀመጥ ባሕል አለው። ያቺኑ ይጠቀም ነበር። ከእርሻ ምርምር ጀምሮ ምርጥ ዘር ላይ የነበረው ዝግጅት በቂ አልነበረም። እርሻ ምርምር ውስጥ ምርጥ ዘር የሚዘጋጀው ውስን ቦታ ላይ ነበር። ስንዴን ብንወስድ ቁሉምሳ እና አሰላ አካባቢ እንዲሁም ሆለታ የስንዴ ምርጥ ዘር ምርምር ነበር። ወረር እየሔዱ በየስድስት ወሩ የማባዛት ሥራ ይሠራ ነበር። በእርሱ ትንሽ መግፋት ቢቻልም ብዙ ውጤታማ መሆን አልተቻለም። አንዱ ወደ ኋላ ያስቀረን ከምርምሩ ጋር የተያያዘ ሥራ ነው። አሁንም የምርምር ሥራው እንደሌሎች አገሮች በሩዝ ምርት ላይ ስኬታማ እንደሆኑት እኛም ስኬታማ መሆን ችለናል ለማለት ያዳግታል። አንዳንድ ለውጦች አሉ። ነገር ግን ብዙ ይቀረናል።
አዲስ ዘመን፡- ግብርናውን ከሳይንስ ጋር በማስተሳሰር የሚሠራውን ሥራ እና የግብርና ባለሙያ መጠንንና ጥራትስ ለግብርናው አለመዘመን ምክንያት አይሆኑም ?
ዶ/ር ንጉሡ፡– ግብርናው ከሳይንስ ጋር የሚተሳሰረው በምርምር ነው። እኛ ጋር የሚመደቡት ከዓለምማያ ኮሌጅ የተመረቁ ነበሩ። በፊልድ ሥራ አስተራረሱን እና አበቃቀሉን አስተራረሙን የተመለከቱ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዘው ወጥተዋል። ነገር ግን ብዙ አይደሉም። 200 ባለሙያን አስመርቆ በሀገሪቱ መበተን ብዙ አይደለም።
በመጨረሻ የግብርና ምርምርን ከልማት ባለሙያ ጋር የማያያዝ ማለትም ከእርሻ ምርምር የሚወጣውን የምርምር ውጤት ገበሬው ጋር ለማድረስ ከኤክስቴንሽን ባለሙያ ጋር ለማስተሳሰር በመሠራቱ ውጤታማ የመሆን ምልክት ታይቶ ነበር። ከዚህ ውጪ ገበሬው ብዙ ነው፤ ነገር ግን ደግሞ የባለሙያ እጥረት ነበረበት። በሚፈለገው ደረጃ በሳይንስ ላይ ተመርኩዞ አለመሠራቱ ብዙ ጉዳት አድርሷል። በተለይ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖሩ፤ ለግብርናችን አለማደግ አስተዋፅዖ አበርክቷል።
አዲስ ዘመን፡- በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ተሳትፎ ነበረዎት። ኢትዮጵያን በመወከል ግብፅ ድረስ በመሔድ ተሳትፈዋል። ተሳትፎዎ ምን አስገኘ?
ዶ/ር ንጉሡ፡- ወደ ግብፅ በተለያዩ ጊዜያት ሔጃለሁ። በአየር ንብረትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ሃሳቦችን አንሸራሽሬያለሁ። በኮፕ 27 ግብፅ ሻርማን ሼክ ቀይ ባሕር አካባቢ ሔደን ብዙ ትምህርት አግኝተናል። ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች ተቋማትም የተገኙ ነበሩ። በአየር ንብረት ለውጡ የተጎዳን ሀገር መሆናችንን በመግለጽ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአየር ብክለት እየተጎዱ ላሉ ሀገራት ማካካሻ መክፈል እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተን ተናገርን። በዚውም በኢትዮጵያ ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተያይዞ እየተሠራ ያለውን ሥራ ገለጽን። ኬኒያዎችም ‹‹ከኢትዮጵያ ተምረን በፓርላማ ደረጃ እ.አ.አ እስከ 2030 18 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ውሳኔ ተላልፏል።›› አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመቀነስ የሚያዋጣው ሀገር ውስጥ መትከል ብቻ አይደለም። የሀገራችንን ድንበር አልፈን እነርሱም ጋር በመትከል በሌሎች አገሮችም ማስቀጠል አለብን ማለታቸው እና ድርጊቱ መፈፀሙ፤ ሌሎች አገሮች ላይም ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን አስተውያለሁ። ከዛ ከመጣን በኋላ በሲሲአርዲኤ ሥር ያሉ ወደ 470 ድርጅቶችን ሰብስበን በተለይ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሠሩ 60 የሚሆኑትን አነጋግረን ችግኝ በአግባቡ እየተከልን ነው።
ሲ አር ዲ ኤ አወዳድሮ ከስልሳ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ ገበሬዎች ጫካ እንዲጠብቁ በማድረግ 500 ሚሊዮን ብር ተገኝቶ አርሶ አደሮች እንዲከፋፈሉ አድርገናል። ሌሎችም ድርጅቶችን ጨምሮ በማወዳደር እና እስከ ባሌ፣ ጂንካ እና ሻሸመኔ በመሄድ ከአንድ እስከ አስር ለወጡት የምስክር ወረቀት ሰጥተናል። የሲ አር ዲ ኤን 50ኛ ዓመት በማስመልከት ከአንድ እስከ አምስት ለወጡት ከ150 ሺህ ብር ጀምሮ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
አዲስ ዘመን፡-መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በተመለከተ ወደ ወጡ ሕጎች እንመለስ። በቅድሚያ የ1997ቱን አዋጅ በተመለከተ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ንጉሡ፡- በደርግ ጊዜ የበጎ አድራጎት ሥራው የሚሠራው ከድርቅ ጋር በተያያዘ ነበር። ከ1977 ዓ.ም በኋላ በድርቅ የተጎዱትን መልሶ የማቋቋም ሥራ ሲሠራ ነበር። ይህ ሥራ ቀጠለ። ኢሕአዴግም ሲመጣ ብዙ ችግር አልነበረም። ‹‹በኋላ የተጎዱ ዜጎችን ማቋቋም የመንግሥት ሥራ ነው።›› ተባለ። እናንተ ወደ ልማት ግቡ ሲባል፤ ትምህርት ቤት ፣ ጤና ጣቢያ እንዲሁም የመጠጥ ውሃ ማዳረስ ላይ በትኩረት መሥራት ተጀመረ። በዚህ ጊዜ ሲሲአርዲኤ አባላትን ማሰባሰብ ጀመረ፤ እየቀጠለ ሔዶ አሁን በስሩ 470 ድርጅቶችን አቅፏል።
በምርጫ 97 ጊዜ አዲስ ነገር መጣ። ሲሲአርዲኤ ምርጫ ያስተባብር ነበር። ምርጫውን ሲያስተባብር ከፍተኛ ፈተና ገጠመው። አንደኛ ‹‹ምርጫ መታዘብ አትችልም›› ተባለ። እኔ በጊዜው የሲ አር ዲ ኤ ቦርድ ነበርኩ። ምርጫው ሦስት ወር ሲቀረው ከአውሮፓ ኅብረት እነአና ጎሜዝ እና ከአሜሪካ እነ ጂሚ ካርተር እየመጡ እንዴት በገዛ ሀገራችን እንከለከላለን በማለት ምርጫ ቦርድን ከሰስን። ዳኞቹ መታዘብ ትችላላችሁ ብለው ውሳኔ አስተላለፉ። በድጋሚ በይግባኝ ተጠየቅን። በመጨረሻ ከብዙ ክርክር በኋላ፤ ምርጫው ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ለመካሔድ ሁለት ቀን ሲቀረው ግንቦት 5 ቀን 1997 ዓ.ም እንድንታዘብ ተፈቀደልን።
እኛ ቅድመ ዝግጅት ስናደርግ ስለቆየን፤ በየቦታው ተሠማራን። አንዳንድ ቦታ ለመታዘብ አልተቻለም። አንዳንድ ቦታ ግን እስከ መጨረሻው ቆጠራው እስኪካሔድ ታዝበን ነበር። በመጨረሻ ውጤቱ እንደታየው ሆነ። በወቅቱ ሲ አር ዲ ኤ እንደጠላት ታየ። መግለጫ ተሰጠበት።
በመጨረሻም አዋጅ 621/1997 ወጣ። ይህ አዋጅ ሲወጣ መንግሥታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶችን ሽባ የሚያደርግ ነበር። 90 በመቶ ከአገር ውስጥ 10 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ብቻ ከውጭ ማምጣት ትችላላችሁ ተባለ። በተለይም ከሰብዓዊ መብት ጋር ተያይዞ በሰላም እና በዴሞክራሲ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ተዘጉ። በፊት የነበሩት አራት ሺህ ድርጅቶች ቢሆኑም፤ አሁን አዋጁ ከተለወጠ በኋላ ምዝገባ ሲካሔድ ሁለት ሺህ አልሞሉም። በሕጉ መሠረት የዘጉትም ቢሆኑ ማሳወቅ ቢኖርባቸውም ያንን አላደረጉም።
አዲሱ ሕግ ከወጣ በኋላ ብዙ መሻሻሎች አሉ። መብት ላይ ተመርኩዞ ሥራ መሥራት ተችሏል። በዚህም ሕዝቡ መብቱን እንዲጠይቅ የማበረታታት ሥራ እያከናወንን ነው። ነገር ግን የገንዘቡ ፍሰት እንደልብ አይደለም። የሀገር ውስጥ እና የውጪ ጦርነቱ እንዲሁም በውስጥ ያለው ችግርም ፈተና ነው።
ነገር ግን አሁን መሻሻሎች አሉ። ካውንስል ተቋቁሟል፤ ሴክረተሪያት አለው። የሰው ኃይል እየጨመረ ነው። ከምክክር ኮሚሽን ጋር፣ ከፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር ተፈራርመናል። ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው። ይህ ሁሉ አዲሱ አዋጅ ያስገኘው ውጤት ነው።
የ1997ቱ አዋጅ ምንም ገንዘብ እንዳናገኝ፤ ምንም ሥራ ሠርተን እንዳናገኝ የሚያደርግ ነበር። እንዳንሠራ ሲከለክል ገንዘብ የምናገኝበት ሁኔታ ሲጠፋ ድርጅቱን ለመዝጋት እንገደድ ነበር። አሁን ግን መነገድ እና መሥራት እንችላለን። አዲሱ አዋጅ የቢዝነስ ሥራን ሳንቀላቅል በመሥራት የሚገኘውን ገንዘብ ለበጎ አድራጎት እንድናውል ይፈቅዳል።በዚሁ መሠረት ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ሪፖርት በማድረግ እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የበጎ አድራጎት ሥራ ያደጉ ሀገራት በርዳታ ስም በደሃ ሀገራት እጃቸውን ለማስገባት የሚጠቀሙበት አንደኛው መሣሪያ እንደሆነ ይታወቃል። ይህስ በኢትዮጵያ ላይም እየተፈጸመ አይደለም?
ዶ/ር ንጉሡ፡– ትክክል ነው። ይህ ስጋት እኛም ጋር አለ። ስውር የሆነው ነገር አይታይም። በተጨባጭ ያልተያዘ ነገር ቢነበብም አይነገርም። ችግሩ ያሳስበናል። ለዚህ ችግር እንደመፍትሔ ያስቀመጥነው የአሠራር ሥነምግባር ደንብን ማውጣት ነው። ይህንን ደንብ አሰራጭተናል። ከብክነት ጀምሮ ሌሎችም ነገሮች ከደንብ ውጪ የሚፈፀም ከሆነ አንድ የርዳታ ድርጅት በመንግሥት ቢዘጋ የማንቆምለት መሆኑን አሳውቀናል።
በእርግጥ ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረውን ሁሉም ያውቃል። ለጦርነትም የበቃነው አንዳንድ ኃያላን አገሮች በሚፈጥሩት ተፅዕኖ ነው። ጦርነቱ በሚካሔድበት ጊዜ ለፀጥታው ምክር ቤት የቀረብነው 13 ጊዜ ነበር። እውነት ኢትዮጵያ ለምን ይህን ያህል ተፅዕኖ ተፈጠረባት? ስንል እና ስንታዘብ ነበር። አብዛኛው ተፅዕኖ የሚመጣው ከርዳታ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ነው። ስለዚህም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።
የሀገር ውስጥ የርዳታ ድርጅቶች በሁሉ ነገር ቅድሚያ ቢሰጣቸው መልካም ነው። ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ርዳታ ቢሰጡም ሥራው መሠራት ያለበት በሀገር ውስጥ የእርዳታ ድርጅቶች መሆን አለበት። ለሀገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱት ሀገር ውስጥ ተፈጥረው ያደጉ የርዳታ ድርጅቶች ናቸው።
ከመንግሥት ተቋም ጋርም ጭቅጭቃችን ይኸው ነው። የሀገር በቀል የርዳታ ድርጅቶች ማደግ አለባቸው የሚል ነው። የባሕል ተፅዕኖ አለ። ይህንን ካልሠራችሁ አንረዳም የሚሉ አሉ። ይህ ሁሉ የሚካድ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በነፃነት መሥራቱ ምን ያህል ነው?
ዶ/ር ንጉሡ፡– አሁን በመንግሥት በኩል ምንም የነፃነት ችግር የለብንም። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ያስተዳድረናል። ከእርሱ ጋር ብዙ ሥራ እንሠራለን። በብዙ መልኩ ነፃነቱ አለ። ይልቁኑ በበጎ አድራጎት የዕርዳታ ድርጅቶች በኩል ነፃነቱን ለመጠቀም የዕውቀት፣ የመረዳት እና የገንዘብ እጥረት አለ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ እናመሰግናለን።
ዶ/ር ንጉሡ፡– እኔም እጅግ አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2015