‹‹ኢትዮጵያ ለሠራባት የበረከት ምድር ናት››ወይዘሮ ዓለም መንግስቱ

ከአራዳ እስከ ቦሌ ታዋቂነትን አትርፈዋል። ሥራ ላይ ታታሪ ከመባልም በላይ ድካም የማይሰማቸው ብረቷ እንስት ቢሰኙ ይሻላል የተባለላቸው ናቸው። ባልንጀሮቻቸው በእርሻ፣ በማዕድን ልማት፣ በሥጋ ላኪነት ወይም በአንድ የተለየ የሥራ መስክ ያልረገጡት፣ ያልደረሱበት የኢትዮጵያ ክልል አይገኝም ይሉላቸዋል።

እርሳቸው በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የኢትዮጵያ ምድር በሙሉ ለሥራ የተመቸ የምርት እና የበረከት ቦታ ነው። ከአሜሪካ በተጨማሪ፣ በአውሮፓ እና በአፍሪካ የተለያዩ ሀገሮች ተዟዙረዋል። ሌሎችም ምቹ ሀገራት የተባሉትን የማየት ዕድል አግኝተዋል። ‹‹አሜሪካንን ‹land of opportunity/ የዕድል ምድር› ይሏታል። ይህን ስም ማግኘት ያለባት ግን ኢትዮጵያ ናት። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሠራ ሰው ብዙ እጥፍ ማምረት ብዙ እጥፍ ማትረፍ ይችላል። አሜሪካን የሠራ ሰው ቢያመርትም ማትረፍ የሚችለው ከአምስት እስከ ሰባት በመቶ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ላይ ተግቶ የሠራ ግን ብዙ ማምረት እና ብዙ ማግኘት ይችላል፡፡›› ይላሉ።

በኢትዮጵያ ምድር ተግቶ የሠራ ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥመውም ማለፍ፤ ማሸነፍ እና የፈለገበት ቦታ ላይ መድረስ ይችላል። ማንም ቢሆን ከማንም ድጋፍ መጠበቅ የለበትም፤ ሙሉ ትኩረቱ ሥራ ላይ ብቻ ከሆነ በትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይችላል የሚል ፅኑ እምነት አላቸው። የግብርና ልማት ላይ በመሰማራት አፋር በረሃ ላይ የውሃ ቦይ አዘጋጅተው በእርሻ ሥራ ላይ ተሠማርተዋል። በአንድ ዓመት ጉድ ያሰኘ ምርት መሠብሰብ ችለዋል።

ሞጆ ላይ በቀን 100 ቶን ስጋ ማዘጋጀት የሚችል ፋብሪካ ገንብተዋል። የሆቴል ኢንዱስትሪ ላይ ከሶስት በላይ አነስተኛ ሆቴሎች ላይ እየሠሩ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አልፈው፤ አሁን ደግሞ ባለአምስት ኮኮብ ሆቴል ለመገንባት ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ይገኛሉ። የማዕድን ልማት ዘርፍ ላይም ተሰማርተው ወርቅ በማምረት ላይ ይገኛሉ። በእነዚህ ሁሉ የሥራ መስኮች ላይ በመሰማራት 300 ሠራተኞችን ቀጥረው በማሰራት ስኬታማ ሆነዋል።

እኚህ ለአምራቾች ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉት ወይዘሮ ዓለም መንግሥቱ ናቸው። የአዲስ ዘመን ዘግጅት ክፍልም የአምራችነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ከወይዘሮ ዓለም መንግሥቱ ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ከአስተዳደጎት እንጀምርና የቤተሰብ ሁኔታን እንዲሁም አሁን ላሉበት ደረጃ እንዴት ደረሱ የሚለውን እንነጋገር።

ወይዘሮ ዓለም፡- ለቤተሰቦቼ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ። አስር ልጆች ነበርን። የመጀመሪያ ልጅ በመሆኔ የተያዝኩት በተለየ መንገድ፤ በትልቅ እንክብካቤ እና በጥንቃቄ ነበር። እናቴ ‹‹በሰባ ብር ልብስ ትገዛልኝ ነበር። በዛ ጊዜ በ70 ብር ቤት ይገዛ ነበር፡፡›› ትለኛለች እናቴ ካደግኩ በኋላ ስታጫውተኝ። ቤተሰቦቼ ባደረጉልኝ ልዩ እንክብካቤ ወንድም እና እህቶቼም የቤተሰቡ ዕዳ አለብሽ ይሉኛል። እንክብካቤው የተለየ ሲሆን ደግሞ ውለታው ከባድ ነበር።

ቤተሰቦቼ ነጋዴዎች ናቸው። እናቴ ሱፐር ማርኬት ስትሠራ አባቴ ብረታ ብረት ይሸጥ ነበር። አባቴ በጣም ኃይለኛ ነው። ትምህርት ቤት የምመላለሰው በመኪና ነው። ከትምህርት ቤት ስወጣ 10 ደቂቃ ከዘገየሁ አውቶብሷ ታመልጠኛለች። 10 ደቂቃ ካረፈድኩ አባቴ ይገድለኛል። ከጓደኞቼ ጋር ማውራት አልችልም። ደጁን ማየት አይፈቀድልኝም ነበር። አባቴ “ምንም ባይኖረኝ ኮቴን ሽጬ አስተምርሻለሁ” ይለኝ ነበር። ትምህርት ይወዳል።

አሁን ላለሁበት ደረጃ የደረስኩት ግን “ዓላማ ይዤ በመነሳቴ እና ፈጣሪም መዳረሻሽ ይህ ነው” ብሎ ስላስቀመጠልኝ ነው የሚል እምነት አለኝ። ሁሉም ይለፋል፤ እኔም እለፋለሁ ፈጣሪ ሲያግዝ ደግሞ ይሳካል። የጠዋት እና የማታ ትኩረቴም ሆነ ከሠዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ሥራ ላይ የተመሠረተ ነው። እንደአንዳንድ ሰዎች ተገናኝቶ ሻይ ቡና እያሉ ጊዜ ማጥፋት አልወድም። በአብዛኛው ግንኙነቴ ከወንዶች ጋር ነበር። ያውም በሥራ ላይ ያተኮረ ነው። ስለቤተሰብ ከተነሳ አይቀር ሁለት ልጆች አሉኝ፤ በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ናቸው። አንዷ ልጄ በቢዝነስ ማኔጅመንት ሶስተኛ ዲግሪ አላት። ወንዱ ልጄም አሜሪካን ሀገር ካውንስለር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሥራ የጀመሩበትን ጊዜ እናስታውስ?

ወይዘሮ ዓለም፡- መጀመሪያ ከንግድ ሥራ ኮሌጅ ከአሁኑ (ኮሜርስ) በቢዝነስ አድምንስትሬሽን ተመርቄ ነበር። ስለዚህ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅኩ በአንድ ቆዳ ላኪ ድርጅት ውስጥ ተቀጠርኩ። በዛ ጊዜ አስመጪ እና ላኪ አልነበረም። ኤክስፖርተር ወይም ላኪ የተሰኙ የኢትዮጵያን ምርት የሚልኩ ድርጅቶች ነበሩ። በዛ ተቋም ተቀጥሬ ትልቅ ልምድ አግኝቻለሁ። በተቋሙ ለሶስት ዓመት ብሠራም ትልቅ የቢዝነስ ሥራ ተሞክሮን ሸምቻለሁ።

በጊዜው ቴክኖሎጂ አልነበረም። እንደአሁኑ ዋትስ አፕ፣ ቴሌግራም እና ሌሎችም በቴክኖሎጂ የመገናኛ መንገዶች አልነበሩም። ይህ ቢሆንም በእርግጥ የሥራ ልምዴ የተሻለ ነበር። ነገር ግን ከሶስት ዓመት በኋላ በአጋጣሚ ድርጅቱን ለቀቅኩኝ። ብዙም ሳልቆይ ወዲያው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (በወቅቱ አጠራር ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን) ተቀጥሬ ፕሮዳክሽን የተባለ ክፍል ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። እዛም ሶስት ዓመት ከቆየሁ በኋላ ለቅቄ የራሴን ሥራ ለመሥራት ወሰንኩ። ሥራው የጫማ መሸጫ ሱቅ መክፈት ነበር። ፒያሳ አካባቢ ሱቅ ከከፈትኩ በኋላ ወደ ሳውዲ ዓረቢያ የምሔድበት አጋጣሚ ተፈጠረ።

አዲስ ዘመን፡- የጫማ ሱቁን ትተው ለምን ሄዱ?

ወይዘሮ ዓለም፡- ወደ እዛ የሔድኩት ለሥራ ሳይሆን ለእህቴ ሠርግ ነበር። ጊዜው የደርግ ዘመን ነበር። የተወሰነ ጊዜ በሳውዲ ከቆየሁ በኋላ ቤተሰቦቼ መቋቋሚያ ገንዘብ ሠጡኝ። ከዛው ሁለት ሚኒባሶች እና የካፌ ዕቃዎችን ይዤ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ። ያንን ዕቃ ያመጣሁት ካፍቴሪያ ለመክፈት ነበር። አራዳ ገበያ ሱቅ ሲጫረት በዛ ጊዜ 189 ሺህ ብር ቁልፍ ገዛሁኝ። ለጊዜው ያ ጨረታ በጣም የተጋነነ ነው ተብሎ ተነግሮለት ነበር። ሆኖም ካፍቴሪያውን ትቼ ወደ ቪዲዮ ሥራ ገባሁ። በጣም ታዋቂ “ሌና” የሚል ቪዲዮ ቤት ከፈትኩ።

ፒያሳ፣ ቦሌ፣ አስመራ መንገድ እና በሌሎችም የተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ሰባት የቪዲዮ ቤት ቅርንጫፎችን ከፍቼ እሠራ ነበር። ቪዲዮ ቤቶቹ ኮምፒተራይዝድ ሲስተም የነበራቸው ሲሆኑ፤ የማመጣቸው ፊልሞች ከሽፋናቸው ጀምሮ ጥራታቸውን የጠበቁ ኦርጅናሎች ነበሩ። በየአቅጣጫው በከፈትኳቸው ቅርንጫፎች በጊዜው ቪዲዮ በማከራየት ትልቅ ታዋቂነትን አትርፌ ነበር። ቴሌቪዥን፣ ካሜራ፣ ሰዓት እና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችንም እሸጥ ነበር።

የከተማው ሰው በጠቅላላ ቪዲዮ የሚከራየው ከእኔ እየወሰደ ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ሥራውን አደጋ ላይ የሚጥል ቴክኖሎጂ መጣ። ሠዎች በቤታቸው ዲሽ ማስገጠም ሲጀምሩ፤ የቪዲዮ ሥራ ይወድቃል ብዬ ወደ

 አውሮፓ በመሔድ ቪዲዮ ጌም ጭኜ መጣሁ። የቪዲዮ ጌም ቢዝነስን በሰፊው ለማካሔድ ሰፊ የገበያ ቦታ ሳፈላልግ ቦሌ አካባቢ ገነተ ልማት ላይ አዳራሽ አገኘሁ። ዋጋውን ተነጋግሬ ከጨረስኩ በኋላ፤ በሃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት የንግድ ምክር ቤት ሃላፊ የነበሩ ትልቅ ሰውን አማከርኩኝ። ከገነተ ልማት ፊት ለፊት አንድ ህንፃ ነበረ። የሕንፃው አስተዳዳሪ ‹‹መስራት ለሚፈልግ ሰው ሆቴል አለ፡፡›› ሲል ላማከሩኝ ሰው ተናገረ። እንዲያማክሩኝ የጠራኋቸው ሰው ‹‹የሚሠራ ሰው አይገኝም እንጂ የሆቴል ሙያ ያለው ሰው ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡›› አሉ። ሥራ ጥሩ ከሆነ ለምን እኔ አልሠራም? አልኩኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የመጫወቻ (የጌም) ቢዝነስ ጉዳይስ በዛው ቀረ?

ወይዘሮ ዓለም፡-አዎ! ሃሳቤን ቀየርኩ። በእርግጥ አጋጣሚ በጊዜው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተነስቶ ነበር። ከውጭ ያዘዝኳቸው ዕቃዎች አሰብ ቢደርሱም እዛው ቀሩ። ስለዚህ ፊቴን ወደ ሆቴል ሥራ አዞርኩኝ። ዕቃዬ አሰብ መቅረቱ ተስፋ አላስቆረጠኝም። ሆቴሉን በወር 45 ሺህ ብር ተከራየሁ። ኪሳራ ውስጥ ገብታ ትተወዋለች ያሉ ብዙዎች ነበሩ። እኔ ግን አንድ ነገር ከጀመርኩ ወደ ኋላ አልልም ብዬ ሥራዬን ቀጠልኩ። በአውሮፓ ዕቃዎች አሳምሬ ሥራዬን በትጋት ቀጠልኩ። የመጀመሪያው ሜሪዲያን ሆቴልን ስኬታማ ማድረግ ቻልኩ።

ከዛም በላይ ሶስት ቅርንጫፍ ከፈትኩ። ቀለበት መንገዱ ላይ ማሪዮት ሆቴል፣ ማሪዮት ገስት ሃውስ እና ኢምፓየር ሆቴልን አከታተልኩ። ሥራዬ ሃያ አራት ሰዓት ሆነ። የምሠራው ለሊት እና ቀን ቆሜ ነው። በቀን እስከ አንድ ሺህ ሰው አስተናግድ ነበር። በጣም ጠንካራ ስለነበርኩ፤ ከኢትዮጵያ፣ ከሳውዲ ዓረቢያ፣ ከኤሜሬት እና ከቱርክ አየር መንገዶች ጋር በመሥራት ትራንዚት ያላቸው ተሳፋሪዎችን የማሣፈር ሥራ እሥራ ነበር። እያበላሁ፣ እያጠጣሁ በአግባቡ እያስተናገድኩ በሚኒባስ እያሳፈርኩ የአንድ ሰው በረራ ሳላስተጓጉል ሠራሁ፡፡

በጊዜው ከእኛ የተሻለ ሆቴል አልነበረም። በኋላ ግን ሌሎች ትልልቅ ሆቴሎች መምጣት ሲጀምሩ ውድድሩ በረታ እና ተዳከምን። የሆቴሉ ሥራ ሲዳከም ወደ እርሻ ልማት ገባሁ። አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሔክታር አፋር ሄጄ አልምቻለሁ። የዛሬ 25 ዓመት ሥራውን ስጀምር ሰዎች “ምንጣሮውን እንኳን አትጨርስም” ሲሉኝ፤ እኔ ግን ከምንጣሮ አልፌ የመስኖ ቦይ ሠርቼ በሄክታር እስከ 40 ቶን ጥጥ አመረትኩኝ። እጅግ በጣም ብዙ ምርት ማግኘት ይቻል ነበር፤ ነገር ግን አካባቢው ላይ ችግር በመፈጠሩ የእርሻ ሥራውን በአፋር መቀጠል አልቻልኩም። ከአፋር ለቅቄ ወጣሁ፡፡

በመቀጠል የእርሻ ሥራ አዋጭ በመሆኑ ወደ ወልቂጤ በመሔድ ማረስ ጀመርኩ። አበሸጌ ወረዳ ላይ እያረስኩ እግረ መንገዴን ያቤሎ የከበረ ማዕድን ማውጣት ጀመርኩ። ነገር ግን የማዕድን ሥራ አስቸጋሪ ነው። ብዙ ተለፍቶ ትልቅ ትርፍ የሚያስገኝ ገቢ የማይገኝበት ሁኔታ ያጋጥማል። ትልቅ አቅም ያለው ሰውና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ ካልተሠራ ትርፍ የለውም። በወዛደር ሲሠራ ዋና ዋናውን ማዕድን ወስደው የማይረባውን ለአሠሪው ስለሚሰጡ ብዙም ስኬታማ መሆን አልቻልኩም። በተጨማሪ የውጭአገር ዜጎችን እና ማሽን ከውጪ በማስመጣት ለመሥራት አሰብኩ፡፡

ቤኒሻጉልም ቦታ ተረክቤ መሥራት ጀምሬ ነበር። ቦታው የወርቅ ማዕድን ለማልማት የሚያስችል ጥሩ ቦታ ነበር። ሃሳቤ በስፋት ደለል ወርቅ ላይ ለመሥራት ሲሆን፤ ከደቡብ አፍሪካ ማሽን አስመጥቼ የእኔን እና የአርሶ አደሮቹን ደለል አጣርቼ ወርቅ በኮሚሽን ከአርሶ አደሮቹ ጋር ለመሥራት ነበር። በዛ በጣም ስኬታማ እሆናለሁ የሚል እምነት ነበረኝ። በዚህም ካፒታል በማጠራቀም የመጀመሪያ ደረጃ ማዕድን አፈላላጊ ለመሆን አቀድኩኝ። በቶን እስከ ሁለት ግራም አገኝ ነበር። ሆኖም የተሰጠኝ ቦታ ላይ ገበሬዎች ያመርቱ ስለነበር ‹‹አንቺ ከገበሬዎቹ ጋር በተመሳሳይ መልኩ መሥራትሽ በመንግሥት ላይ ጥያቄ ያስነሳል ፤ስለዚህ ወደ መጀመሪያ ደረጃ ማዕድን ወደ ማፈላለግ መግባት አለብሽ፡፡›› ተባልኩኝ።

ሆኖም በዛ ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ የወርቅ ማዕድን አፈላላጊ ለመሆን ወደ ሰባት ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ወጪ ያስወጣል። እኔ ደግሞ በዛ ጊዜ አቅሜ አይፈቅድም ነበር። ስለዚህ አቋረጥኩት። እንዳሰብኩት ሳይሆን ቀረ፤ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ሰርቼ ለማቋረጥ ተገደድኩ። ከማዕድን ሥራው ጎን ለጎን አንድ የፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ አቋቋምኩኝ። በተጨማሪ በ1997 ዓ.ም አካባቢ የስጋ ፋብሪካ አቋቁሜያለሁ። የፕላስቲክ ሥራው ብዙ ስኬታማ አልሆነም፤ ምክንያቱም ሥራው የተያዘው በተወሰነ ቡድን በመሆኑ ሰብሬ ለመግባት ገድቦኛል፡፡

ስጋ ወደ ውጪ በመላክ በኩል ግን በተለያዩ ባንኮች አንደኛ ስጋ ላኪ ሆኜ ተሸልሜለሁኝ። አሁን የሥጋ ፋብሪካው እንኳን ለእኔ ለአገር የሚያኮራ ትልቅ ፋብሪካ ነው። ጥሩ ገበያ ሲኖር፤ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚተርፍ ይሆናል። አሁንም ባለአምስት ኮኮብ ሆቴል እየገነባሁ እገኛለሁ። ወደ ፊት ኢትዮጵያ ለሠራ ሰው የዕድል ምድር በመሆኗ ሌሎች ፋብሪካዎችንም የመገንባት ዕቅድ አለኝ። ለዚህ የሚሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራሁ ነው።

ወደ ፊትም ደረጃውን የጠበቀ አዲስ ቄራ ገንብቼ ትልቅ ሥራ ለመሥራት በመዘጋጀት ላይ ነኝ። ከዚህ አልፌ የሥጋ ኢንዱስትሪውን ለማስቀጠል ወደ አፋር እየገባሁ ነው። ቅርንጫፍ ከፍቼ፣ የእንስሳት መኖ ማምረት፣ እንስሳት ማራባት፣ ዝርያ መቀጠል እና ማሻሻልን የመሳሰሉ ትልልቅ ሥራዎች ለመሥራት እየተንቀሳቀስኩ እገኛለሁ።

አሁን የሥጋ ሥራውን በዋናነት እያከናወንኩ ያለሁት ሞጆ ላይ ነው። አንደኛው የመነሻዬ ቄራ አነስተኛ ሲሆን፤ ሁለተኛው ቄራ ግን በጣም ትልቅ እና ዘመናዊ ነው። አዲሱ ቄራ በቀን መቶ ቶን ስጋ ማምረት ይችላል። ነገር ግን አሁን ኢትዮጵያ ላይ ገበያው አስቸጋሪ ነው። እንስሳቶቹ በድንበር እየተሻገሩ ነው። በአጠቃላይ የመካከለኛው ምስራቅን የሥጋ ገበያ የተቆጣጠርነው እኛ እና ህንዶች ነበርን። አሁን ግን ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከገበያው እየወጣች ነው። እንደ ዕቅዳችን አልሔድንም። አንዳንዴ እከፋለሁ፤ አዲስ የገነባሁት ቄራ 100 ቶን መሥራት እየቻለ በመከራ በብዙ ጥረት ሶስት ቶን እየሠራ ነው።

ቄራው ትልቅ አቅም ያለው ቢሆንም እየሠራ ያለው ትንሽ ነው። ትልቅ ፋብሪካ ሲቋቋም ጀነሬተር እና ሌሎችም ትልልቅ ወጪዎች ይወጡበታል። እንዲህ ብዙ ማምረት የሚችል ፋብሪካ በትንሹ ሲገደብ ያሳዝናል። የሥራውን እንቅስቃሴ ለመቃኘት ዱባይ ሔጄ ነበር። በፊት የኬንያን ስጋ የሚገዛ አልነበረም፤ ርካሽ ነበር። አሁን ግን ኬንያዎቹ የኢትዮጵያን ገበያ ተቆጣጥረው ደንበኞችን በሙሉ ወስደዋል። የኢትዮጵያ የውጭ የሥጋ ገበያ ባልተጠበቀ መልኩ ወርዷል። ይህ ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ወርቅ፣ ቡና እና እንስሳት እንዲሁም የተለያዩ ማዕድኖች በሙሉ ወደ ጎረቤት አገር እየተሻገሩ ነው። አንድም የውጭ ምንዛሪ ችግር ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። ከእኛ በተቃራኒው ኬንያ እና ታንዛኒያ ስጋ ሥራ ላይ ተሰማርተው ብዙ የውጭ ምንዛሪ እያገኙ ነው።

በኢትዮጵያ ሀብት የጎረቤት አገሮች ብዙ ቢሊዮን ዶላር እያገኙ ነው። አንድ ፍየል የሌላቸው ሳይቀሩ ስጋ እየሸጡ ወደ ውጭ እየላኩ ነው። እነሱማሌ ላንድ እና ጅቡቲን የመሳሰሉ ሀገራት ሳይቀሩ ኢትዮጵያ ከምትልከው አራት እጥፍ የበለጠ ምርት ወደ ውጭ እየላኩ ምንዛሪ ያገኛሉ። በዚህ የተነሳ አሁን የሥጋ ሥራ ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሆኗል።

በሌላ በኩል ምንዛሪውም ላይ ችግር አለ። እኛ በዶላር ሃምሳ አራት እና ሃምሳ አምስት ብር ስንከፍል፤ የጎረቤት ሀገራት ግን ከኛ የተሻለ እየከፈሉ እነርሱ ከእኛ በላይ ያገኛሉ። ስለዚህ የእንስሳት አርቢዎቹ ለእኛ ከመሸጥ ይልቅ ወደ ጎረቤት ሀገር ይሸጣሉ። መንግሥት አንድ ነገር ፈጥሮ ይሔንን ካላስተካከለ ችግሩ ይቀጥላል። ጉዳዩም እየሠፋ ይሔዳል፡፡

ለወደፊቱ በመንግሥት በኩል ርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለን እናስባለን። በተደጋጋሚ በድንበር የቁም እንስሳት እንዳይወጡ ይደረግ እያልን እንጮሃለን። ነገር ግን ብዙም የሚሰማን አላገኘንም። ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ እየተቸገረች ነው። በትክክል የድንበር ጥበቃው ቢኖር እና የሥጋ ምርት ወደ ውጭ ቢላክ፤ ይህ ሁሉ ችግር አይኖርም ነበር።

አዲስ ዘመን፡- ነገር ግን ከከብት አድላቢ እና አቅራቢ አርሶ አደሮች ጋር ትስስር መፍጠር አይቻልም?

ወይዘሮ ዓለም፡- ሌላው ዋነኛው ችግር እርሱ ነው። ኬንያ ውስጥ ከብቶችን ሰብስቦ ወደ ግል ቄራዎች የሚያደርሰው መንግሥት ነው። እኛ ሀገር ግን አንድ በሬ እኛ ቄራ የሚመጣው አራት አምስት ደላላዎችን አልፎ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት እኔ ስጋ የምገዛው 8 ሺህ 500 ዶላር ነው። ስሸጠው ግን 6 ሺህ 600 ዶላር ነው። በአንድ ቶን ከሁለት ሺህ ዶላር በላይ ኪሣራ እየከሠርኩ እየሠራሁ ነው። ኪሳራ ቢኖርም ግን ፋብሪካ እንዲሁ አይዘጋም፤ የባንክ ጉዳይ አለ፤ የሠራተኛ ጉዳይ አለ፤ ኢንቨስት ያደረግናቸው ጉዳዮች አሉ፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ዋጋ እየከፈልን ነው። ወደ ፊት የተሻለ ይሆናል ብለን ተስፋ በማድረግ እየሠራን ነው፡፡

መንግሥት የራሱን ስትራቴጂ ነድፎ በመሃል ያሉትን ደላሎች ካልተቆጣጠረ እና የዋጋ ተመንንም ከሽያጩ አንፃር ካላረጋጋ ነገሩ እየቀጠለ ይሔዳል። የሥጋ ጥራትን በማረጋገጥ በኩል ደግሞ ለገበሬው የተሻለ ዘር እና ሥልጠና ቢሠጠው መልካም ነው።

የእንስሳት የሕክምና አገልግሎትም ቢሰጥ የተሻለ ምርት ይመረታል። ሌላው ወቅቶች አሉ። አንዳንዴ ድርቅ ያጋጥማል። ሥራው ወጥ አይሆንም። ቋሚ የግብርና ገበያ (commercial farm) የለም። ስለዚህ ከመሠረቱ የተሻለ ዘር ከማዳቀል ጀምሮ ከብት እርባታው ላይ ለመሠማራት እየሠራን ነው። ይሔ ደግሞ የስጋ ምርት መጠናችንን ከፍ ያደርግልናል ብለን ገምተናል። ምክንያቱም በግ እና ፍየሎች በኢትዮጵያ በሶስት እና በአራት ወር በደንብ ከተቀለቡ ጥሩ ኪሎ ይኖራቸዋል። ጥራታቸውም የተረጋገጠ ይሆናል። ስለዚህ ኢንቨስትመንቱ እንዳይከስም እና የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በአጠቃላይ የሥራውን ህልውና ለማረጋገጥ ሥራው ላይ የግብርና ሥራ ማለትም ከብቶችን ከማራባት ጀምሮ እስከ መቀለብ ድረስ ለመሥራት ጥረት እያደረግን ነው።

ይህ ገበያው ላይ ያለውን ክፍተት በትንሹም ቢሆን ለመደገፍ ይረዳናል። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ሥጋ ወደ ውጭ ለመላክ በራሳችን አደልበን ብቻ የሚሆን አይደለም። ምክንያቱም ገበያው እንደዛሬ ሳይሆን በቀን እስከ ሁለት ሺህ በግ እና ፍየል የምናርድበት ጊዜ ነበር። በወር በአማካኝ 30 እና 40 ሺህ እናርድ ነበር። ያንን ሁሉ እንስሳ በራስ ማደለብ ከባድ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች ደፍረው ወደ ሥጋ ኢንቨስትመንት አይገቡም። በተለይ ሴት ሆነው ወደ ሥጋ ሥራ እንዴት ገቡ?

ወይዘሮ ዓለም፡- ወደ ሥራው የተሠማራሁት አንድ ተስፋዬ የተባለ ወዳጅ ነበረኝ። የሆቴል ሥራዬን እያከናወንኩ ሁል ጊዜ ‹‹ለምን በሥጋ ኢንቨስመንት ላይ አትሰማሪም?›› ይለኝ ነበር። እኔ ብዙም ፍቃደኛ አልነበርኩም፤ ምክንያቱም ቤተሰቦቼ ስጋ ይሸጡ ነበር። በዛ ጊዜ በልጅነቴ ፍሪጅ ስላልነበር ቤተሰቦቼ ያልተሸጠላቸውን ሌሊት ተደብቀው ሲጥሉ አስታውሳለሁ። ስለዚህ እንደውም የሥጋ ሥራ ስሪ የሚለኝ ወዳጄን የፀዳ የሆቴል ሥራ እየሠራሁ ጨምላቃ ‹‹የሥጋ ሥራ ስሪ ›› ለምን ይለኛል? ብዬ ለማየትም ጠልቼው ነበር። በኋላ ከአንድ ሌላ ኢንቨስተር ጋር እራት እየበላን የሥጋ ሥራ ላይ ተሠማሪ የሚለኝ ወዳጄ ተስፋዬ መልሶ ጉዳዩን አነሳው፤ ሌላኛው ኢንቬስተር ‹‹ሥጋ ሥራ በጣም ጥሩ ነው። አንድ ካምፓኒ ጠቅሶ ካምፓኒው አላተረፈም ቢባል በወር 500 ሺህ ብር ያተርፋል አለኝ፡፡›› ስለዚህ ሥራውን ማሰብ ጀመርኩ።

አንድ ሆላንድ ያለ ወዳጄ ጋር ደውዬ የሥጋ ሥራ መሥራት እንደፈለግኩኝ ገለፅኩለት፤ በአጋጣሚ ሆላንድ ያለው ወዳጄ ወደ ቤልጂየም ሲደውል እዛ ከተማ ላይ ቄራ ሥራ ላይ ተሠርቶ የነበረ ግለሰብ በአንድ ወር ውስጥ ዕቃዎችህን አንሳ ተባለ። የሆላንዱ ወዳጄ ‹‹ቶሎነይ አለኝ፡፡›› በሳምንት ውስጥ ቤልጂየም ደረስኩ፤ ተዋውዬ ፋብሪካውን ገዝቼ መጣሁ። ወደ እዚህ መጥቼ መሬትም አግኝቼ ሥራውን ቀጠልኩ።

አዲስ ዘመን፡- የስጋ ሥራም ሆነ ሌሎች የተሠማሩባቸው የሥራ መስኮች ከበድ ያሉ ናቸው። ሴት ሆነው በእነዚህ ሥራዎች ላይ ሲሠማሩ ፈታኝ አጋጣሚዎች አልነበሩም?

ወይዘሮ ዓለም፡– እውነት ለመናገር ሴት በመሆኔ ለመሥራት ያስቸገረኝ ወይም ያገደኝ የሥራ ዘርፍ የለም። ከወንዶች እኩል እሠራለሁ፤ ከወንዶች እኩል አገኛለሁ። በእርግጥ ወንበዴዎች ያጋጥማሉ። ብንዘርፋት ምን ታመጣለች? የሚሉ አይጠፉም። በቅርቡ አንዱ መኪና ሙሉ ንብረት ይዞ ከነመኪናው ጠፋ፤ ሴት በመሆኔ ለመሳደብ እና ለማንቋሸሽ የሚመጣም ያጋጥማል። በተለይ ያልተማሩ ሰዎች ሴት ናት ብዘርፋት ምን ታመጣለች? የሚሉ አንዳንዴም ከሥራ የሚቀሩ ያጋጥማሉ። ሌላ ግን እንደው በሴትነት ያጋጠመ ችግር ተብሎ ሊነሣ የሚችል ነገር የለኝም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምን ያህል ምቹ ናት?

ወይዘሮ ዓለም፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ኢንቨስት ሊደረግባቸው የሚችሉ መስኮች አሉ። ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ የአገልግሎት ዘርፉ ሁሉም ክፍት ነው። ከአንድ ሰው የሚጠበቀው ፍላጎት፣ ጥራት እና አዋጪ ጥናት ማስጠናት ነው። ሰዎች አሜሪካንን ‹‹ land of opportunity›› ይሏታል። ነገር ግን አሜሪካን ውስጥ ሰዎች እየሠሩ በወር 100 ዶላር መቆጠብ አይችሉም። ኢትዮጵያ ግን በደንብ ለሚሠራ በአምስት ዓመት ውስጥ ሚሊየነር መሆን ይቻላል። ዋናው ጉዳይ ሥራ ላይ መጠንቀቅ እና ለሥራ ቁርጠኛ መሆን ነው። ጥረት ከተደረገ በደንብ ማግኘት ይቻላል።

በተለያየ ጊዜ አሜሪካን ሄጃለሁ፤ እዛ ያሉ ቤተሰቦቼ አንቺ እንደምትይው ትርፍ የለም ይሉኛል፡፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሠርቶ መቶ በመቶ ማትረፍ ይችላል። እዛ የሠራ የሚያገኘው ግፋ ቢል አምስት በመቶ ወይም ሰባት በመቶ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከትንሽ ተነስቶ ማደግ ይቻላል። የመንግሥት ፖሊሲም የሚያሳድግ ነው። በተለይ ለሴቶች የተመቻቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ብዙ ማደግ ይቻላል። በመደራጀት በዶሮ ርባታ፣ በከብት ርባታ፣ ሽሮ እና በርበሬ ማዘጋጀትም ሆነ በምንም ዘርፍ ላይ ከትንሽ ተነስቶ በመሥራት ትልቅ ውጤት ማምጣት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ብዙ ሰዎች በግልም ሆነ በመደራጀት ሥራ ይጀምራሉ፤ ነገር ግን ብዙ አይዘልቁም ያቋርጣሉ። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? በተጨባጭ የትኛውም ሰው ሠርቶ ስኬታማ እንዲሆን ምን ያስፈልገዋል?

ወይዘሮ ዓለም፡- ሰዎች ተሰባስበው እንሥራ ስላሉ ብቻ ስኬታማ መሆን አይችሉም። የተሰባሰበው ስብስብ ጥናት ላይ ተመርኩዞ ትክክለኛ መሪ ሊያስጉዘው ይገባል። ማንም እንደሚያስተውለው አሁን ላይ ወጣቱ ተበላሽቷል። ብዙሃኑ ወደ መጥፎ ሱስ እየገባ ነው። ያገኙትን ገንዘብ ይዞ ሥራ ከመጀመር ይልቅ ያገኙትን ገንዘብ ዓላማ ቢስ የሆነ ተግባር ላይ የሚያውሉ ሰዎች ብዙ ናቸው። ስለዚህም ወጣቱ ላይ መስራት ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ሰዎች ለሥራቸው ምን ያህል ትኩረት መስጠት አለባቸው? የእርስዎ ተሞክሮ ምን ይመስላል?

ወይዘሮ ዓለም፡- ምሳ የሚባል ነገር አላውቅም። ውሃ እንኳን የመጠጫ ጊዜ የለኝም። ሥራን የማየው እንደድካም ሳይሆን እንደመዝናኛ ነው። ሰዎች የሥራ ዕረፍት ሲወጡ ይገርመኛል። መዝናናት እና እረፍት የሚባል ነገር አላውቅም። ሥራዬ ራሱ ያዝናናኛል። መዝናናት ከተባለ አካል ወይም ስጋ ብቻ ሳይሆን አዕምሮም አብሮ መዝናናት አለበት። ጭንቅላቴ ውስጥ የባንክ ዕዳ እያስጨነቀኝ ሰውነቴ ቢዝናና መዝናናት አይደለም። ሥጋን ብቻ ማዝናናት ዋጋ የለውም። የሰው ዓላማ ሥራ ከሆነ ረሃብ፣ ጥማት እና ድካም የሚባል ነገር አይኖርም። 24 ሰዓት እሠራለሁ። ወጣቶች “ደከመኝ ፣ ራበኝ” ሲሉ በጣም ይገርመኛል። አንድም ቀን ደከመኝ የሚል ቃል ከአፌ ወጥቶ አያውቅም። ሥራ እየሠራሁ ምሳ ቀርቤ አልበላም፤ ሙዝም ባገኝ የሆነ ነገር ቀምሼ ልውል እችላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ሴት ነሽ፤ ያለሽ ይበቃሻል ከማለትና ከማዳከም ወይም በተቃራኒው በርቺ ብሎ መደገፍ እና ማገዝ ላይ ምን ያህል አስተያየት ይሠጥዎታል?

ወይዘሮ ዓለም፡– ቤተሰቦቼ የመነሻ ድጋፍ አድርገውልኛል። ከዛ ውጪ ግን ፈጣሪ እና እኔ ብቻ ነን። ብዙ ሰው ይበቃሻል እረፊ ይለኛል። አንድ ጊዜ “ማረፍ ይኖርብኝ ይሆን” ብዬ ራሴን ጠየቅኩኝ በኋላ ግን ጭንቅላቴን መታሁት፤ ይህንን እንዳትሰማ አልኩት። አዕምሯችን ያልነውን ይሰማል። ጉንፋን እንኳ ሲይዘኝ ሥራ አለብኝ ተወኝ እለዋለሁ። አመናችሁም፣ አላመናችሁ እዛ ጋር ይቆማል። ለአዕምሯችን ድክመትን ከነገርነው ደክሞሻል እረፊ ይላል።

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ማለት የሚፈልጉት ካለ ?

ወይዘሮ ዓለም፡- ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት። ስናድግ እኛ ኢትዮጵያ የዳቦ ቅርጫት መሆን እንደምትችል ተነግሮናል። አሁንም ሀገሪቱን የዳቦ ቅርጫት ማድረግ ይቻላል። ብዙ ማምረት፣ ብዙ ማትረፍ እና በሀገር ደረጃ መትረፍረፍ እንችላለን የሚል እምነት አለኝ። ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ዓለምን በምርት ማትረፍረፍ ትችላለች።

90 በመቶ ሕዝቡ ገበሬ ነው። ኢትዮጵያ መቀየር የምትችለው በግብርና ዘርፍ ትልቅ ሥራ በመሥራት ከፍተኛ ምርት በማምረት ነው። ይህ እንዲሆን የግብርና ዘርፍ በየአቅጣጫው ተስፋፍቶ፤ አግሮ ኢንዱስትሪ ላይ በየክልሉ መሠራት አለበት የሚል እምነት አለኝ።

አሁን ግን በተቃራኒው ብዙ ማምረት እየቻልን ምርት ከውጭ እያስገባን ነው። ነገር ግን እንኳን የግብርና ምርት ከውጭ ማስገባት፤ በሀገር ውስጥ የሚያስፈልገንን ምርት አምርተን መሸጥ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። በአምስት ዓመት እርሻ ላይ በሰፊው ሠርተው የለሙ አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ብንሰማራ በአጭር ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ሊለወጥ ይችላል። ምርጥ ዘር እና የእርሻ መሳሪያ ለየወረዳው ቢሰጥ ወዲያው ትልቅ ለውጥ ይመጣል።

ትራክተር እና ሌሎችንም የግብርና መካናይዜኝን መስጠት እና የተማረው ሰውም በስፋት ለግብርናው ትኩረት ቢሰጥ በአጭር ጊዜ የማይታሰብ እና ለመገመት የሚያስቸግር ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፤ ብዙ ጊዜ ይህንን እላለሁ። ወጣቶችም ሀገር ከሀገር እየተሰደዱ እንዳይንገላቱ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ እንዲቀየር ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክት ራዕይ ይዛችሁ ጠንክራችሁ ተነሱ እላለሁ። ካላስፈላጊ ሱሶች ተጠንቀቁ፤ የዓላማ ሰዎች ሁኑ እላለሁ።

ሀገራችን ብዙ ተስፋ አላት። የተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርቻለሁ። በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሬያለሁ። አፋር፣ ያቤሎ፣ ጉራጌ ዞን፣ ቤኒሻንጉል፣ ትግራይ ያልደረስኩበት የለም። ኢትዮጵያውያን አሀገራችንን ልንጠቀምባት እና ልንጠቅማት ይገባል። ኢትዮጵያ የበረከት ምድር ናት። በየትኛውም መስክ ተግቶ የሠራ ሰው ውጤታማ የሚሆንባት ሀገር ናት። በእኔ እምነት ኢትዮጵያ የዕድል ምድር ናት። ይህንን የምለው የተለያየ መስክ ላይ ተሠማርቼ፤ ዓይቼ ማግኘት በመቻሌ ነው። በእርግጥም ኢትዮጵያ ብዙ ማምረት የሚያስችል መሬት እና የተፈጥሮ ሀብት አላት፤ ይህንን ሀብት በአግባቡ እንጠቀምበት የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ እናመሰግናለን።

ወይዘሮ ዓለም፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You