አዲስ አበባ፡- ለስታርት አፕ ምቹ ምህዳር ለመፍጠር በፖሊሲ የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ለስታርት አፕ እድገት ተቋማዊና ሕጋዊ አሠራርን የሚዘረጋ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ውይይት ቀርቦ ትናንት ምክክር ተደርጎበታል። በምክክሩ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የስታርት አፕ እድገትን የሚያሳልጥ ምቹ ምህዳር ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ነው። ወደፊት ትልቅ ኢኮኖሚ ምንጭ እንደሚሆን በመገመት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ስታርት አፕ ለብዙዎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥርና በኢኮኖሚ ዕድገቱ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በፖሊሲ የመደገፍ ሥራ እየተሠራ ነው። ረቂቅ አዋጁ ለስታርት አፕ ተቋማዊና ሕጋዊ ድጋፍን በመስጠት በኢትዮጵያ የዘርፉን እድገትን ያጠናክራል።
ረቂቅ አዋጁ በስታርት አፕ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታትና የፋይናንስ አቅርቦትን ማመቻቸት ሌላው ዓላማው ነው። ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታከናውነውን ተግባርና የምትከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ለመደገፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ከሦስት ዓመት በፊት ያልዳበረ የባንክ ሥርዓትን ጨምሮ የስታርት አፕ ፍላጎት ለማሟላት ምቹ ሁኔታ አልነበራትም። አሁን ላይ ፖሊሲዎችን ከማሻሻል ጀምሮ ለስታርት አፕ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እውን ለማድረግ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት ስታርት አፕን በፖሊሲ መደገፍ የግድ መሆኑን አንስተዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች ኢኮኖሚውን እየተቀላቀሉ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የስታርት አፕ አዋጁ ሲጸድቅ ለሥራ ፈጣሪዎች ትልቅ እድል ይዞ ይመጣል። መንግሥት ለስታርት አፕ በሰጠው ልዩ ትኩረት በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች እየተፈጠሩ በመሆኑ አሠራር ለመዘርጋት ረቂቅ አዋጁን ማዘጋጀት አስፈልጓል ብለዋል።
አዋጁ ሲጸድቅ በዘርፉ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን በመፍታት አዳዲስ ፈጠራን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ላለፉት ሦስት ዓመታት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ረቂቅ አዋጁ ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቂ ውይይት ተደርጎበታል። ለስታርት አፕ ምቹ ያልሆኑ መሰናክሎችን በማስወገድ ፈጠራንና ደፋር ሃሳቦችን በማጎልበት ዘርፉን የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ ስታርት አፕን በፖሊሲ በመደገፍ ኋላ ቀርነትንና ረሃብን ታሪክ ማድረግ ይገባል። እንዲሁም ሥራ ፈጣሪዎችን ለማብዛትና ውጤታማነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ረቂቅ አዋጁ ለስታርት አፕ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እንደ ሀገር የተያዘውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እውን ለማድረግ ያግዛል። ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ጋር በንግድ በማስተሳሰር ዘርፉን ለማሳደግ ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም