አስናቀ ፀጋዬ
ኢትዮጵያ የከበሩ የተፈጥሮ ማዕድን ሀብት ባለቤት ናት። ሰፊ የማዕድን ሃብት አብዝቶ ከቸራቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ደግሞ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይጠቀሳል። በክልሉ ወርቅ፣ ኦፓል፣ አኳማሪንና መሰል የከበሩ ማዕድናት በስፋት የሚገኙ ሲሆን፣ ክልሉ ለተለያየ ጌጣጌጥ ከሚውሉ ከነዚህ ማዕድናት በተጨማሪም ለግንባታ (ኮንስትራክሽን)እና ኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ ሀብቶች መገኛም ነው። ከክልሉ ደግሞ በጋሞ ዞን ኦፓል፣ አጌት፣ አኳማሪንና የድንጋይ ከሰል እንዲሁም የኮንስትራክሽን ማዕድናት በስፋት ይገኛል።
የአካባቢውን የማዕድን ሀብት አስመልክተው የጋሞ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ እንድሪያስ ዋጌ እንደገለጹት በዞኑ በስፋት ከሚገኙ ሀብቶች በዋናነት ለግንባታ የሚውሉ ጠጠርና አሸዋ የሚጠቀስ ቢሆንም የጌጣጌጥና ከፊል የከበሩ ማዕድናትም በአንዳንድ አካባቢዎች ይገኛሉ።
ከፊል ከከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ውስጥ አጌትና አኳማሪን በገረሴ፣ ካምባና ጋርዳ መርታ ወረዳዎች መኖሩ በጥናት ተረጋግጧል። በገረሴና ካምባ ዙሪያ ወረዳዎች ላይ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በባህላዊ መንገድ በማምረትና በመጠቀም ላይ ናቸው። ወጣቶች ከባህላዊ የአመራረት ዘዴ ወጥተው በቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲያመርቱ ከባለሃብቶች ጋር በጥምረት የማምረቻ መሳሪያ(ማሽን)ለማስገባት በዞኑ ጥረት እየተደረገ ነው። በቅርቡም በጋርዳ መርታ ወረዳ በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘ የማምረት ሥራ ለመጀመር ታቅዷል።
የተጠኑት ጥናቶች በተመረጡ አካባቢዎች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ እንድሪያስ፤ በዞኑ ያሉትን የማዕድን ሀብቶች ለመለየት ሰፊ የጥናት ሥራ ማካሄድ ይጠይቃል ብለዋል። በሁሉም አካባቢዎች ጥናት ተደርጎ ያለው ሀብት ባለመታወቁም የዞኑ የማዕድን ሃብት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ እንዳልሆነ ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳሉት የጌጣጌጥ ማዕድናቶቹ ወጥተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ያለው ስራም ጅምር ተጠቃሚነትን ያጎለበተ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቁጫ እና ቁጫ አልፋ በተባሉ የዞኑ ወረዳዎች ጥናት በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ ጥናቱ በዋናነት የድንጋይ ከሰል መኖሩን ለማረጋገጥ ሲሆን፣ በወርቅና የብረት ማዕድናት ላይም በተመሳሳይ ጥናቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።
እንደ ሃላፊው ገለፃ የጌጣጌጥ ማዕድናቱን ለገበያ የሚቀርቡት ህጋዊ ፍቃድ የተሰጣቸው አዘዋዋሪዎች ሲሆኑ በሀገር ውስጥ የሚያቀነባበሩና የሚልኩትም እንዲሁ ፈቃድ ያላቸው ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ በዞኑ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች የኮንስትራክሽን ማዕድናትን እያመረቱ ለገበያ በማቅረብ ይጠቀማሉ። በአነስተኛ ደረጃ በማሽን አምርተው ለገበያ በማቅረብ ባለሀብቶችም ተጠቃሚ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ለግንባታ የሚውሉ ማዕድናት ከጌጣጌጥ ማዕድናት በተሻለ ጥቅም ላይ ውለው በዘርፉ ለተሰማሩት ገቢ እያገኙ ነው።
ሃላፊው እንደሚሉት የማምረቻ ማሽኖችን በመጠቀም የጌጣጌጥ ማዕድናቶችን ለገበያ በማቅረብ የበለጠ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻል ግንዛቤ በመያዙ ማሽን ማቅረብ ከሚችሉ ባለሀብቶች ጋር ወጣቶች በሽርክና እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣በተለይም አንዱ በሆነው የዞኑ ጋርዳ መርታ ወረዳ ላይ በጥራትን በብዛት በማምረት ቀደም ሲል በአካባቢው የነበረውን ክፍተት ለመቅረፍ ዝግጅት ተደርጓል።
በወረዳው ላይ የሚገኘውን ተሞክሮም በቀጣይ በሌሎች ወረዳዎችም በማስፋት ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ከወዲሁ እየተሰራ ነው። በዞኑ የጌጣጌጥ ማዕድናት ክምችት በመኖሩ ህጋዊ የማዕድን አዘዋዋሪዎች ገብተው እንዲሰሩ ይፈለጋል። በተለይ ደግሞ የማምረቻ መሣሪያ ወይንም ማሽን ያላቸው ይበረታታሉ።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ እስካሁን ድረስ በተለይ የጌጣጌጥ ማዕድናቱ በስፋት ጥቅም ላይ ሳይውሉ የቀሩት በቂ ጥናት ባለመካሄዱ ነው። በቀጣይ የማዕድን ሀብቱን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ጥናቶችን ማካሄድና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማስማራት ይጠይቃል።
በአሁኑ ወቅትም ማዕድናቱ በስፋት ይገኙባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ቦታዎችን ለማወቅ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጂኦሎጂካል ሰርቬዬ ከክልሉ ፍቃድ አግኝቶ የጥናት ሥራውን ጀምሯል። ከዚህ በፊትም ደራሴ ወረዳ ላይ ዩኒቨርሲቲው የአኳማሪንና አጌት ማዕድኖችን ያጠና ሲሆን፣ ካምባና ጋርዳ መርሳ ወረዳዎች ላይም ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አካሂዷል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ቁጫ አካባቢ የድንጋይ ከሰል ላይ እያጠና ነው።
የማዕድን ጥናት ሥራው በዩኒቨርሲቲዎች እየተከናወነ ቢሆንም የጋሞ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ በስፋት በማስጠናት የማዕድን ሀብቱን ማወቅ ይፈልጋል። ሆኖም ጥናቱን በስፋት ለማካሄድ በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ ስለሚያስፈልገው ከፌዴራል መንግስት ድጋፍ ይጠይቃል።
በኢትዮጵያ በማዕድን ፍለጋና ጥናት ረገድ በዘረፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረትና ለምርመራ አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎች አቅርቦት ማነስ ጋር በተያያዘ ሰፊ ክፍተት መኖሩ ይነገራል። ባለፈው ሳምንት ከወላይታ ዞን ማዕድን ሃብት ጋር በተያያዘ በሰራነው ዘገባ ተመሳሳይ ችግር መኖሩን መግለጻችን ይታወሳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም