በጋዜጣው ሪፓርተር
የሁለት ሰንጋዎች ስጋ በእሳት ተቃጠለ
የከብቶቹ ጤና ሳይመረመርና ከመደበኛው የስጋ ማዘጋጃ ከቄራው ውስጥ ሳይታረዱ ከጫካው ውስጥ ተገፈው ለህዝብ ሲሸጡ የተገኙ የሁለት ሰንጋዎች ስጋ በእሳት እንዲቃጠል ተፈረደ።
የሁለቱም ሰንጋዎች ስጋ ደንበኛ ምርመራ ሳይደረግበት ሲሸጥ የተያዘው ከአዲስ አበባ ከደጃዝማች አባ ኮራን ሰፈር ከአቶ ነጋሽ አርጋው የስጋ መሸጫ ልኳንዳ ቤት ውስጥ መሆኑን ከ1ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት የተገኘው ዜና አረጋገጠ።
ያልተመረመረው ስጋ በክፍሉ የጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት ተቆጣጣሪዎች አማካይነት ከነሻጩ ተይዘው 1ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ በማስረጃ ከተጣራ በሁዋላ ሀምሌ 15 ቀን በቻለው ችሎት ስጋው ሰው ከማይደርስበት ስፍራ እንዲቃጠል ተወሰነ።
ያልተመረመሩ ከብቶችን አርደው ጤናው ያልተጠበቀ ስጋ ለህዝብ ለመሸጥ ሲሞክሩ
የተደረሰባቸው አቶ ነጋሽ በፈጸሙት የጤና ጥበቃ ደንብ መተላለፍ 100 ብር መቀጫ ከፍለው ለወደፊቱ ያልተመረመሩ ከብቶች ከቄራው ውጪ አርደው ለበላተኞች እንዳያቀርቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ሲሉ የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ ተሾመ ገብረ ወልድ በሰጡት ዜና አስታወቁ።
ይህ አይነቱ አድራጎት ለህዝብ ጤና አጠባበቅና ለአካባቢም የጽዳት ጤና አጠባበቅና ለአካባቢም የጽዳት ይዞታ አደገኛ ከመሆኑም በላይ በህግ ተቋቁሞ በንጽኅና ከተያዘው ቄራ ውስጥ አዘጋጅቶ ለህዝብ በማከፋፈል ፋንታ በየስርቻው ከብት አርዶ ለተመጋቢዎች ማቅረብ ህዝብን ማሳሳትና የጤናውን ሁናቴ ማሰናከል ስለሚሆን ፍርድ ቤቱ ስጋው ተቃጥሎ ነጋዴውም እንዲቀጡ ወሰነ በማለት ዳኛው በፍርዱ ሀተታ አስታወቁ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሀምሌ 21 ቀን 1962
በ33 ሰዎች ላይ በሀሰት የመሰከረው 2 አመት ተፈረደበት
አዋሳ/ኢዜአ/ በ፴፫ ሰዎች ህይወት ላይ በሀሰት የመሰከረው ዲንጋ ፉላሳ በ2 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አዋሳ ከተማ ያስቻለው ከፍተኛ ፍ/ቤት ሰኔ ፲፱ ቀን ፈረደ።
ዲንጋ ፉላሳ መጋቢት ፳፰ ቀን ፷፪ አም ፴፫ ሰዎች አባሪ ተባባሪ በመሆን የአቶ ኬሪ ቦጮን ባለቤት እመት ፋዬ ጉራሮን በዱላ ደብድበው ከገደሉ በሁዋላ ፴ የቀንድ ከብቶች ዘርፈዋል በማለት በሀሰት የመሰከረው በገንዘብ ተገዝቶ መሆኑ የተደረሰበት ሞታለች የተባለችው ሴት በህይወት ስለተገኘች ነው። ተከሳሹ በዚሁ አፈጻጻሙ በቀጠሮ ወህኒ ቤት ቆይቶ በመጨረሻ ጥፋተኛነቱን ስላመነ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር ፬፻፵፯ መሰረት በ፪ አመት ጽኑ አስራት እንዲቀጣ ተበይኖበታል።
እንዲሁም በ፴፫ ሰዎች ላይ በሀሰት መስክሮ የነበረው ኢቦ ጎትያ የፍርድ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ወህኒ ቤት እንዳለ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን አንድ የፍ/ቱ ቃል አቀባይ ገልጸል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሀምሌ 9 ቀን 1962
በዘረፋ የተከሰሰ 40 ጅራፍና እስራት ተፈረደበት
ደብረ ማርቆስ /ኢዜአ/ በዘረፋ ወንጀል የተከሰሰው ታፈረ ዋሴ በ፵ ጅራፍና በ፰ አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ደብረ ማርቆስ ከተማ ያስቻለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት ፈረደ።
ተከሳሹ በጎጃም ጠ/ግዛት በባህር ዳር አውራጃ ይልማና ዲንሳ ወ/ግዛት ውስጥ ግንቦት ፰፪ ቀን ፷፩ አም ከሌሊቱ ስድስት ሰአት በሚሆንበት ጊዜ ካልተያዙት ግብረ አበሮቹ ጋር ሆኖ ከአቶ ብርሃኔ ደረስ ቤት ድረስ ሄደው በጦር መሳሪያና በጩቤ አስፈራርተው ፭፻ ብርና ፭ የቀንድ ከብቶች ዘረፉ።በዚህም ጊዜ የአካባቢው ህዝብ በጩኸት ሲደርስባቸው ፭ ጥይትና ቦምብ ተኩሰው ሌሎቹ ሲያመልጡ ያሁኑ ተከሳሽ ታፈሰ ዋሴ ተይዞ ሁኔታው ከተጣራና አድራጎቱ በማስረጃ ከተረጋገጠ በሁዋላ በ፵ ጅራፍና በ፰ አመት ጽኑ እስራት አንዲቀጣ ተፈርዶበታል።
እንዲሁም በዚሁ አውራጃ ግዛት ታንኳ በር ቀበሌ ጥቅምት ፱ ቀን ፷፩ አም ከቀኑ ፭ ሰአት በሚሆንበት ጊዜ ለባህር ዳር ከተማ ገበያ ውሎ የሚመለሰውን ህዝብ መንገድ ጠብቆ በጦር መሳሪያ በማስፈራራት ፩፻፲፭ ብርና ሌላም ንብረት ዘርፎ የተያዘው አዘነ እማኝ አድራጎቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠ በ፯ አመት እስራት እንዲቀጣ ይኸው ፍ/ቤት በትናንትናው ቀን በዋለው ችሎት በይኖአል።