በሀገራችን በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች መካከል የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የኑሮ ውድነትና ህገወጥነት ይገኙበታል።እነዚህ ችግሮች በየዘመኑ ሲያጋጥሙ የነበሩና በመንግስትና ህዝብ ርብርብ ሲፈቱ የኖሩ ናቸው።በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ይዘናቸው የቀረብናቸው ዘገባዎች ይህንኑ ያመለክታሉ።በመስከረም 1969 ከወጡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እትሞች በመኖሪያ ቤት እጥረት፣ በኑሮ ውድነት በኩል ምን ችግሮች ያጋጥሙ እንደነበርና እነዚህን ችግሮች ለመፋታት በመንግስትና በህዝብ ይከናወኑ የነበሩ ስራዎች ምን ይመስሉ አንደነበር እስቲ እንመልከት።
የሸቤ 02 ቀበሌ 23 ትርፍ ቤቶችን በዘመቻ አገኘ
ጅማ፡-(ኢ.ዜ.አ.) ስለ ከተማ ቦታና ትርፍ ቤት መንግሥት በአወጣው ዓዋጅ መሠረት በጅማ አውራጃ በሸቤ ቀበሌ 02 በትርፍነት የተያዙ ፳፫ ቤቶች በማጠናቀቂያ ዘመቻ መገኘታቸው ተገለጠ።እነዚሁ በትርፍነት የተያዙ ቤቶች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከመዋላቸውም በላይ በየወሩ የሚያስገኙት ኪራይ ተገምቶ ለመንግሥት ማስረከብ ሲገባቸው ካለ አግባብ ሲጠቀሙበት የቆዩ ግለሰቦች የአንድ ዓመት ኪራይ በጠቅላላው ፩ሺ፩፳፰ ብር ከሃምሳ ሣንቲም ለቀበሌው ገቢ እንዲያደርጉ ተወስኖባቸዋል።
ከዚህም ሌላ ቀበሌው በቤት እጦት ለተቸገሩ ግለሰቦች የቁጠባ ቤቶችን እየሠራ ለማከራየት ባቀደው መሠረት እስካሁን ፷ ሰዎች ማከራየቱን የቀበሌው ሊቀመንበር አቶ ካሣዬ መኰንን አስታውቀዋል።
በከፋ አውራጃ በቦንጋ ከተማ የቀበሌ 21-02-03 የኅብረት ሥራ ማኅበራት አባላት ደግሞ ከአንዳንድ አድኃሪያን በዝባዥ ነጋዴዎች አሻጥር በመላቀቅ ሰሞኑን ባደረጉት ስምምነት ለኅብረት ሱቅ መቋቋሚያ ፲፭ ሺህ ብር አዋጥተዋል።
ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ ሦስቱ ቀበሌዎች እያንዳንዳቸው ፬ ሺህ ያዋጡ ሲሆን ፫ ሺውን ደግሞ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ቀድሞ ለኅብረት ሱቅ ማቋቋሚያ የሰበሰበውን ለቀበሌዎቹ ገቢ ማድረጉን የአውራጃው አስተዳዳሪ አቶ ግርማይ ተስፋዬ አስታውቀዋል።
(መስከረም 9 ቀን 1969 ከወጣው አዲስ ዘመን)
የሆሣዕና ቀበሌዎች 40 የቁጠባ ቤቶች ሊሠሩ ተስማሙ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
በከምባታና ሐዲያ አውራጃ በሆሣዕና ከተማ የተቋቋሙት የከተማ ነዋሪዎች የሕብረት ሥራ ማኅበራት፤ በከተማው ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የቤት እጥረት ለማስወገድ ፵ የቁጠባ ቤቶች በአነስተኛ ወጪ ለማሠራት ተስማምተዋል።
በዚህም መሠረት የቀበሌ 03 የሕብረት ሥራ ማኅበር የኑሮ ደረጃቸው መጠነኛ ለሆኑ ቤተሰቦች አገልግሎት የሚውሉ ቤቶችን መሥራት ጀምሯል።እያንዳንዱ ቤት ሣሎን የእቃ ቤት መኝታ ቤትና ማዕድ ቤት ያለው መሆኑ ተረጋግጧል።
እያንዳንዱ ቀበሌ የቁጠባ ቤቶችን የሚሠራው ለጊዜው ባለው ገንዘብ ሲሆን፤ ለማጠናቀቂያ የሚውል ገንዘብ በብድር ከባንክ ለማግኘት አቅዷል።
በሌላም በኩል ደግሞ የቀበሌ ፪ እና 02 ሕብረት ሥራ ማኅበራት ሰሞኑን የሥራ ዘመቻ አድርገው ከ፲ ሺህ ያላነሱ ዛፎች ተክለዋል።
እንዲሁም በአንጋጫ ወረዳ በሺንጓ ሽቶ ንዑስ ቀበሌ የሚገኙት የ፲፬ የገበሬ ማኅበራት፤ በመተባበር በአስራ አምስት ሺህ ብር ለሕብረት ሱቅ የሚሆን አንድ መጋዘንና አንድ የእህል ወፍጮ ማቋቋማቸውን ረዳት አስተዳዳሪ አቶ ደምሴ ፍላቴ ገልጠዋል።
(መስከረም 5 ቀን 1969 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ተረካቢ ያጣው 29ሺህ ዓሣ በስብሶ ተጣለ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
ግምቱ ከሰባት ሺህ ብር በላይ የሆነ ሐያ ዘጠኝ ሺህ ዓሣ በመበላሸቱ እሬፒ የቆሻሻ መጣያና ማቃጠያ ስፍራ የተቀበረ መሆኑን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ትናንት አስታወቋል።
ዓሣው ሊበላሽ የቻለው፤ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ በአትክልት ተራ በማኅበር የተዘጋጁት ዓሣ ነጋዴዎች ለመረከብ ባለመፍቀዳቸው ተከማችቶ ስለቆየ መሆኑን ማዘጋጃ ቤቱ ጨምሮ ገልጧል።ዓሣው የተመረተው ከዝዋይ አካባቢ መሆኑም ታውቋል።
ሀይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም