ደብረ ማርቆስ / ኢዜአ /፡- በጎጃም ክፍለ ሀገር በቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ በቡሬ ወረዳ የገጠርን መሬት ለህዝብ ያደረገውን አዋጅ በመተላለፍ ጭቁን ገበሬ ሲያሳርሱና ሲበዘብዙ የተገኙ ሶስት የቀድሞ ጉልተኞች በወረዳው ገበሬዎች ማህበር የፍርድ ሸንጎ ይግባኝ ሰሚ በቀረበባቸው ክስ አድራጎታቸው በማስረጃ በመረጋገጡ ባለፈው ማክሰኞ በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው ሁለት ወር ታስረው ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ወስኖባቸዋል፡፡
ቅጣቱ ከተወሰነባቸው ሰዎች መካከል አየን መንገሻ የተገባለው በወደቀው መንግስት ጊዜ ጉልት ገዥ የነበረና አሁን ጊዜው ያለፈበትን የጉልተኝነት የብዝበዛ ስርአት ለመመለስ በከተማ ተቀምጦ ሲያሳርስና ሲያስገብር መገኘቱ ተረጋግጦበታል፡፡
እንዲሁም ሀጂ አሊ አስቴና አጥናፉ አንተነህ የተባሉት የታወቁ ክበርቴ ነጋዴዎች በንግድ ስራቸው ላይ በተጨማሪ በከተማ ተቀምጠው በገጠር እያሳረሱ ጭቁኑን ገበሬ ሲያራቁቱና ሲበዘብዙ መገኘታቸው ተረጋግጦባቸዋል፡፡
የወረዳው የገበሬዎች ማህበር የፍርድ ሸንጎ ይግባኝ ሰሚ የቀረበለትን ክስ በመረመረበት ጊዜ እነዚሁ አሳራሾች በጭቁኖቹ ላይ ያደረሱትን ብዝበዛ ከተመለከተ በሁዋላ እያንዳንዳቸው ሁለት ወር ታስረው ፶ ብር እንዲከፍሉ ሲወሰንባቸው ገንዘቡን ባይከፍሉ በለውጡ አንድ ወር ተጨምሮ እንዲቀጡ፣ ያስጠምዷቸው የነበሩት በሮችና መሬታቸው ለአራሹ ገበሬ በአዋጁ መሰረት አንዲሰጡ የወሰነባቸው መሆኑን የወረዳው የእርሻና የህዝብ ማስፈር ስራ አስኪያጅ አቶ መኩሪያው አደም ገልጸዋል፡፡
ለከበርቴዎቹ ሲያሳርሱ የነበሩት ገበሬዎች ግን መቀጣት አለመቀጣታቸውን ዜና ሰጪው አላብራራም፡፡
ሀምሌ 7 ቀን 1969
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም