እናት አለሜ ረጅም ጊዜ ከእናቱ እንደተለየ ህፃን ውስጤን ብሶት ያናውጠዋል። መከፋቴ ከመብዛቱ የተነሳ ትንሽ ነገር ሳይና ስሰማ በቅጡ ያልተሰራው የእንባ ግድቤ ይፈነዳና እንባዬ መንታ መንታ ሆኖ በጉንጮቼ ካለማቋረጥ ምንም ከልካይ ሳይኖረው ይወርዳል። እናት አለም ስቅቅ በሚያደረግ ፍቅርና ናፍቆት መካከል ሆኜ ስወድሽ ለፍቅሬ መግለጫ ቃል አጣለሁ። እማማዬ እንባ አጥቦ የማያጠራው ብሶት ልጅሽ ተሸክሜያለሁና በንፁህ እቅፍሽ ወድቄ ብሶቴ ይታበስልኝ እንደሁ ይችን ለናፍቆቴ መግለጫ ልኬልሻለሁ።
ሀገሬ ሙሉ አንቺነትሽን ከዳር ዳር ረግጬ ባልቃኝም መልካችንና ባህሪያችን እንደመለያየቱ የተሰራንበት ስሪት አንድነውና የወጣነው ካንቺው ማህፀን ነውና ብዙም የሚለያየን ነገር አለ ብዬ አላምንም። ሁሉም ስላንቺ ሲሰማ የሆነ የስስትና የፍቅር እሳት ውስጡ ይንቀለቀላል። ባንቺ ማንም ክፉ ማየት አይሻም። እንደ ነብር ቆዳ የተዥጎሮጎረው መልካችን ማራኪ ውበት እንጂ የደም መፍሰሻ ምክንያት እንዳይሆንብን ሀገሬ ልመርቅሽ አሜን ይሁን በይኝ።
ልዩነታችን ውበት እንዳይሆን የሚያደናቅፈን እንቅፋት ድብልቁ ጣእም አጥቶ የመረረበቱ ምክንያት ነው ብዬ እኔ የማስበው ከምርጡ ዘር ጋር ተቀላቅሎ እንክርዳድ ስለተዘራ ነው። ምርጡን ዘር ያጠለሸ ውበታችንን የደበቀ ድብልቅልቅ ማለታችን የሰርገኛ ውበት እንዳይሰጠን የሆነው በእንክርዳዱ ምክንያት ይመስለኛል። እንክርዳዱ ከስሩ ይነቀላል፤ ዳግም ላይመለስ እንደጉም በኖ ይጥፋል።
እናት አለሜ የልጅ ምርቃት ይደርስ እንደሆነ አላውቅም ግን ይሄው ጀባ ብዬ ጀምሪያለሁ። እሜየዋ ጤናውን ጀባ፤ ሰላሙን ጀባ፤ አንድነቱን ጀባ፤ ይበልሽ። እናቴ እንክርዳዱን ከምርጡ ዘር ለይቶ ንፁህ ማንነትሽን የሚያጎላ ፍሬውን የሚያሳይ ክንዱ ፈርጠም ያለ ጀግና ከጠላቶችሽ የሚታደግሽ እንባሽን አብሶ ፃእዳ የሚያለብስሸ የልጅ ጋሻ ይብዛልሽ።
ወገኑን በአንድ የሚሰበሰብ፤ ልዩነቱን አጥብቦ መከባበርን መርሁ ያደረገ፤ አንድነት ግቡ የሆነ፤ በኔ አይን የኔ ብሄር ሙሉ የማይል፤ ለታናሽ ለታላቁ ክብር ያለው፤ ዝቅ ካለው ጋር ዝቅ ብሎ ከፍታ ላይ የሚያቆምሽ ዳግም ደግነቱን የማይነፍግሽ ልጅ ፈጣሪ ይስጥሽ።
መሪም እንደ መሪ በቦታው ልክ የሚታየበት አንዱ ልጅ አንዱ የእንጀራ ልጅ የማይሆንበት በሰፊው ምጣድሽ የተጋገረው እንጀራ ለሁሉም ልጆችሽ እኩል የሚካፈልበት ታላቅ ለታናሹ የሚሳሳበት ታናሽ ታላቁን የሚተባበርበት ከእልህና ከትዕቢት የላቀ መከባበርና መተሳሰብ የሞላበት ፍቅር እንደ ሸማ የሚያላብስ ልጅ ይሰጥሽ ዘንድ ይሄው ጀባ፤ የልጅ አውራ ይስጥሽ፤ ያለፈው ክፉ ጊዜ ተረስቶ ለወደፊቱ ብርሃን ይንገስልሽ ፤ የደግነት ልብ ጀባ የሰላም ሀሳብ ጀባ ብያለሁ በይ አሜን።
ሁከት ይሰዳል በረከት ይሉት ነገር ሆኖብን ጓዳሽ ሳይነጥፍ ሁሉ ሞልቶ ወገን በረሀብ ከሚያልቅበት የሀብታም ድሃ ከሚያስመስልሸ የሚያወጣሽ የልጅ አውራ ይውጣልሽ። የወላድ መካን ከሚያደርግሽ ጦሮ አንቀባሮ አልብሶ አሳምሮ ወግ ማእረግ የሚያሳየሽ ከበረከቱት የበረከተ ከበለጡት የበለጠ ታላቅ የሙሴን በትር የያዘ ወገኑን የችግር ባህርን ከፍሎ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚያደርስ ልጅ ይስጥሽ።
እርፎ መረባ ልበል እናቴ። እርፎ መረባ ፤ መረባ ደግነት ይግባ መረባ፤ የወገን እንባ ያባራ መረባ፤ ደም መፍሰስ ይብቃ መረባ፤ ተስፋ ማጣት ይቁም መረባ፤ ህይወት ዳግም ትለምልም መረባ፤ ችግር ገደል ይግባ መረባ፤ እርፎ መረባ ያልኩልሽ ምርቃት ደርሶ ጨለማው ተገፎ ነግቶ መኖር ያለ ጭንቀት ንጋት ያለፍርሃት ይሁንልሽ፤ መስኮቶችሽ ሲከፈቱ የተስፋ ብርሃን ብቻ ይግባ። የሰላም ነፋስ እንጂ የሞት ሽታ አይሽተትን። አሜን።
መኖር ደጉ ክፉንም ደጉንም እያሳየ በህይወት ብስለት ውስጥ የሚያሻግር መሆኑን አይቻለሁ። እምዬ በእድሜሽ ስንትን አይተሻል ስንት ልጅ ወልደሽ ስንቱን ልጅ ቀብረሻል እናት አለሜ እስከ ዛሬ ካፈራሻቸው የላቀውን የትናንት ማንነትሽን የሚመልስ በክብር ከፍታ ላይ የሚያወጣሽ ጠንካራ ጋሻ የሆነ ልጅ ጀባ ይበለሽ።
ጎሳ ብሄር ሳይለይ ለሁሉ አንድ የሆነ ሁሉን ወንድሜ እህቴ ብሎ የሚያቅፍ የአንዱ ቁስል አንዱን የሚያመው አንዱን በመርገጥ ወደ ከፍታ የሚደረግ ሩጫ የሚቀርበት እጅ ለእጅ የተሳሰረ አንድ የሚያደርግ እድገት የሚመጣበት የአንዱ ቤት ሞልቶ የሌላው ራቁቱን የማይቀርበት ቆንጆ ዘመን ያመጣልሽ ዘንድ ይሄው ጀባ ብያለሁ።
ልቡ ያበጠበት ሰከን የሚልበት፤ ሁሉ ተናጋሪ ሆኖ ሰሚ እንዳይጠፋ መደማመጥ የሰፈነበት፤ ቅንነት በየፊናው የተዘራበት ከሰው ንግግር ጀርባ የማይመነዘርበት፤ ሰው እንደተናገረው የሚደመጥበት ይሁን ቤትሽ ይሄው ጀባ እሱ ይሙላልሽ፤ ለውለታሽ መልስ የሚሰጥ፤ በሀብትሽ ልክ የሚያሳድግሽ ስደት ቀርቶ እንደ ጥንቱ እንግዳ ተቀባይ የምትሆኝበት፤ ለምፅዋት የሰው እጅ መመልከትሽ ቀርቶ እጅሽ ለሌሎች የሚዘረጋበት ህይወት እንደገና ብለን እንደ አዲስ በፍቅር በተስፋ ስምሽን ይዘን ከፍ ወዳለው የምናደርስበት ቀን ያመጣልን ዘንድ እመርቃለሁ።
አሜን በይ ስልሽ አሜን በይ። ከአሜን ይቀራል ከአሜን ይገኛል እንዲሉ ልጆችሽ ደግ ደጉን ላንቺ ያብዛው። ይሄው ጀባ በክፉ የሚያይሽን ልብ ይስጠው፤ ይሄው ጀባ የቤትሽን ሰንኮፍ እሱ በኪነጥበቡ ይንቀለው፤ ይሄው ጀባ ድህነት ችግር ሰቆቃና እንባን ዳግም አያሳይሽ፤ ቸር ቸር ብቻ በደጅሽ ይታይ ይሰማ ብያለሁ። ያየሽው መከራ ይበቃልና እሱ በቃ ይበልሽ። ከመብቃቱ ጋር ተስፋውን ያብዛው።
የምዬ ምርቃት ይሰምር ዘንድ መደላድሉን የተመቸ እናድርገው። ምን ይዛቸሁ ይባረክላችሁ የሚል ጥያቄ እንዳይመጣብን ሁላችንም እንደየ መክሊታችን በቅንነት እንትጋ። መወለዳችን በአጋጣሚ ወይ በፈጣሪ ፍቃድ ነውና ፍቃዳችን ሳይጠየቅበት ስለተወለድንበት ምድር እንደ አውሬ አንበላላ።
በቅን መንፈስ ጎዶሎውን እየነቀስን እያወጣን በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን ልዩነት ቂም በቀል ሳይኖርብን መካከላችን ሰቆቃ ሳይገባ የምንኖርበትን ምቹ አለም ለመፍጠር ያብቃን።
ደግ ደጉን የምናይበት፤ መልካም መልካሙን የምናሸትበት፤ የፈካ ፃእዳውን የምንለብስበት፤ የጣመ የላመውን የምንመገብበት፤ በጎሪጥ የማንተያይበት፤ ሳቅና ፈገግታ ብቻ እንጂ ከፊታችን እንባ የማይታበስበት ደግ ቀን ያምጣልን። ይሄው ጀባ፤ አለሙን ጀባ፤ ሰላሙን ጀባ፤ ተስፋውን ጀባ፤ ፍቅሩን ጀባ፤ ጤናውን ጀባ፤ ሀብቱን ጀባ። ቀና ቀናውን ሰላሙን ደስታውን ጀባ። ይሁን ይሁን አሜን ብዬ አበቃሁ።
ብስለት
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2013