ኢትዮጵያ ዛሬ በውስጥና በውጭ ሆነው ሊያተራምሷት በሚሰሩ ኃይሎች ሴራ አጣብቂኝ ውስጥ ብትገባም፤ ፈተና የማለፍ ብቃት ያለው ሕዝብና መንግሥት አላትና ሁሉጊዜም ጠላቶቿን እያሳፈረች አንድነቷን አስከብራ ትጓዛለች፡፡ ኢትዮጵያ ብትወድቅም፤ ብትደማም፤ ብትቆስልም ‹‹ኢትዮጵያውያን እያሉ ኢትዮጵያ አትፈርስም›› እያሉ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የነገሩንን እኛ ኢትዮጵያውያን በልባችን ይዘን በገጠሙን አጣብቂኞች ሁሉ ተጣብቀን፣ ተጨንቀንና ቆዝመን ግን ደግሞ ተስፋ ሳንቆርጥ የሰጡንን ቃል በልባችን ሰንቀን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ እንዳሉንም ቃል በተግባር ሲውል ማየት ጀምረናል፡፡
በትናንትናው ዕለትም ጠላቶቻችንን አሳፍረናል ወዳጆቻችንን አኩርተናል፡፡ በምርጫው ተሳትፈን ለአገራችን ያለን ቀናኢነት አሳይተናል፤ ከብርድና ከቁሩ ጋር ተናንቀን ለአገራችን ያለንን ክብር
ገልጸናል፡፡ በአንድነት ወጥተን ታሪክ ሰርተናል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት መከራና ችግር ቢፈራረቁብንም ይህም ያልፋል ብለን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ በመንታ መንገዶች ውስጥ አልፈን የትናንትናው ታሪካዊ ቀን ላይ ደርሰናል፡፡
ኢትዮጵያ ምርጫ ካደረገች ጠናካራ አገር እንደምትሆን የሚያውቁ ጠላቶች ምርጫው እንዳይካሄድ ብዙ ጉድጓድ ምሰዋል፡፡ በየቦታው እልቂትና ሁከት በመፍጠር አገሪቱ ሰላሟ እንዲናጋና ከተቻለም እንድትበታተን ብዙ ደክመዋል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻችን ለሚምሱት ጉድጓድ ሳይበገሩ በርካታ ዓይነ ግቡ ፕሮጀክቶችን ይፋ በማድረግ በችግር ውስጥም ሆነው ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ለጠላቶቻቸው ጭምር ትምህርት የሚሆኑ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ መሰል ፕሮጀክቶች ፍጻሜ እንዳያገኙ ካላቸው ጥልቅ ፍላጎት በመነሳት አድብተው ሴራ ጎንጉነዋል፡፡ በዚህ የተነሳም በጠራራ ፀሐይ የንጹሃን ሕይወት ተቀጥፏል፤ ንብረት ወድሟል፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ገጥሟት የማያውቅ ከፍተኛ የዜጎች መፈናቀልም ገጥሟታል፡፡ ይሁ ሁሉ ታዲያ ዛሬ በአገሪቷ እየታዩ ያሉትንና ነገም በጉጉት የምንጠብቃቸውን ለውጦች ለመቀልበስ ታቅዶ የተተወነ ትወና ስለመሆኑ ከማናችንም የተሰወረ አይደለም፡፡
አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች እንዲሉ እኛ እንዳሻችን የማናደርጋትና የማንፈልጣት የማንቆርጣት ኢትዮጵያ አትኖርም ከማለት ባለፈ ‹‹ከመስከረም 30 በኋላ አገር አታስቡ፣ ኢትዮጵያ ፈርሳለች ቁርጣችሁን ስሙ» እያሉ የአገር መፍረስ መርዶን ገና ከጅምሩ ሲያረዱን የሰነበቱት የአሸባሪው ህወሓት አመራሮች
ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም ሆነና ነገሩ እምቢኝ አሻፈረኝ ከማለታቸው ባለፈ የማይደፈረውን ደፍረው ካለኛ ማን አለ በማለት ጦርነት የገበጣ ጨዋታቸው መሆኑን በነገሩን ማግስት ማንነታቸውን አይተናል፡፡ ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትራችን በገቡልን ቃል መሠረት ኢትዮጵያውያን እያሉ ኢትዮጵያ አትፈርስምና የደፈሯትና ሊያፈርሷት ያሰቡ ከሃዲዎች በክህደታቸው ማግስት ተዋርደዋል፡፡
ታዲያ ዛሬ ላይመለሱ አፈር ልሰው አፈር ሆነው ከቀሩትም ሆነ አሁንም አልሞት ባይ ተጋዳይ እንዲሉ በአይጥ ጎሬ ሆነው እኛ እንዳሻን የማናደርጋት ኢትዮጵያ ልትኖር አይገባም፡፡ እያሉ የሚዝቱና የሚፎክሩ የጁንታ ስብስቦች ተሟጠው ባይጠፉም ኢትዮጵያ የገጠሟትን እንቅፋቶች ሁሉ ተቋቁማ ዛሬ ላይ ደርሳ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አድርጋለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉንም ‹‹ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚከናወንና የተሸነፈው ፓርቲ ላሸነፈው አካል እጁን ስሞ ሥልጣን ያስረክባል፡፡ ያኔ እውነትም የኢትዮጵያ የትንሳኤ ብርሃን ይበራል፡፡ ብርሃኑንም ከወዲሁ ማየት ጀምረናል፡፡
ኢትዮጵያ በገጠሟት ጊዜያዊ ግን ደግሞ እጅግ አስጨናቂና ተስፋ አስቆራጭ ችግሮች ብትደናገጥም ከችግሮቿ ሁሉ እየተሻገረች ዛሬ ታሪካዊውን ምርጫ ለማካሄድ በቅታለች፡፡ እጅግ አስጨናቂና ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ችግሮች ውስጥ አልፎ ሊታመን ቀርቶ ሊታሰቡ የማይችሉ ፕሮጀክቶችን ዕውን አድርጋም በገጸበረከትነት ለሕዝቦቿ እንካችሁ ብላለች፡፡
ትናንት መዲናችን አዲስ አበባ ከነበረችበት ክርፋት ቆሻሻዋን አራግፋ ቀና ብላ ስናይ ብዙዎቻችን ‹‹ይህቺ ደግሞ ማናት ከየት መጣች›› በሚል አግራሞት ተመልክተናታል፡፡ ማንነቷ እስኪጠፋን ተገርመንባታል፡፡ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም እንዲሉ ‹‹ለካስ እንዲህም መስራት ይቻላል›› በሚል የቁጭት ስሜት ትናንትን ከትናንት መሪዎቹ ጭምር ረግመናል፡፡
ትናንት ያካሄድነው ምርጫ የተጀመሩ መልካም ነገሮችን የምናጠናክርበት ያለፍንባቸውን ክፉ ገጽታዎቻችንን ደግሞ የምንለውጥበት ሊሆን
ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን የእኛና የእነሱ የሚል የመገፋፋት ስሜት ማዳበር ከጀመርን
ሰነባብተናል፡፡ ስለዚህም በትናንትናው ዕለት በአንድነት ወጥተን በአንድነት ለአገራችን አንድነትና ሉዓላዊነት እንደቆምን ሁሉ ከዚህ በኋላም እኔነትን ትተን እኛነትን በጋራ ማዳበር አለብን፡፡ ይሁንና በትንሳኤው ብርሃንም ኢትዮጵያ አሻጋሪዎቿን እማኝ በማድረግ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰረት ጥላለች፡፡ ጠቅላያችንም ‹‹ወደ ሥልጣን መምጣት የሚቻለው በምርጫና በምርጫ ብቻ›› ስለመሆኑ ደግመው ደጋግመው በገቡት ቃል መሠረት የእርሳቸው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ይበጃል ያሻግራታል ያሉትን ሀሳብ ፍትሃዊና ነጻ ሆኖ በተመቻቸላቸው መድረክ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አቋማቸውን አንጸባርቀው፤ ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን በማስተዋወቅ ፍጻሜ ያገኘው የምረጡኝ ቅስቀሳ አብቅቶ ሕዝቡ ድምጽ ሰጥቷል፤ ከዚህ በኋላ የሚቀረው የሕዝብ ድምጽ ማክበር ብቻ ነው፡፡
በዕለቱም ሕዝቡ ያለ አንዳች መንገራገጭ ድምጹን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መስጠት ችሏል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ መስመር እንዲይዝ ደፋ ቀና
ብሏል፡፡ ስለዚህም የዚህን ሕዝብ ልፋትና ድካም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ የወደደውንና የፈቀደውን መርጧልና የሕዝቡን ድምጽ ማክበር ጨዋነት ነው፡፡ ስለዚህም ሕዝቡ ያሰናዳውን ድግስ ያለምንም ማጉረምረም መቋደስ እንዲቻል፤ የሕዝብን ድምጽ ማክበር እራስንም ማክበር መሆኑን ተረድቶ ኢትዮጵያን ወደ ገናናነትና እድገት ማሻገር ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2013