ሰላማዊት ውቤ
ከተሞች ዕድገታቸው ወደላይ እንጂ ወደ ጎን ባለመሆኑ በአነስተኛ የቆዳ ስፋት ላይ ነው የሚመሰረቱት። በውስጣቸው የሚኖረው ህዝብም በገጠር የሚኖረውን ህዝብ ያህል ሰፊ ቁጥር ያለው ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።
በከተሞች የሚኖረው ህዝብ በቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚያበረክተው ሚና የጎላ እንደሆነ እንዲሁም ከተሞች የሰው ልጅ ለውጥ ማዕከሎች መሆናቸውን የማህበራዊ ዘርፍ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ እንደሚጠ ቁመው ከተሞች የቆዳ ስፋታቸው 0 ነጥብ 6 በመቶ ሲሆን፣ በውስጣቸው የሚኖረውም ህዝብ 22 በመቶ ያህል ነው።
የከተሜነት ዕድገት ምጣኔያቸውም 5 ነጥብ 4 በመቶ ሲሆን፣ የተለያየ ምርት በማምረት 58 በመቶ ድርሻ አላቸው። በአጠቃላይ ከተሞች ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት አስፈላጊ ናቸው።
የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ብክለት ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የአየር ብክለት ቁጥጥርና ክትትል ባለሙያ አቶ መሰረት አብዲሳ፤ ከተሞች ላይ አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ ጉዳታቸውም ከሚያስገኙት ጥቅም በላይ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት ከዕድገት ጋር ተያይዞ የሚያደርጓቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በጥንቃቄ መከናወን ይኖርባቸዋል። በተለይም ከተሞች ከፍተኛ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ የሚያመነጩ በመሆናቸው አካባቢን በመጥፎ ጠረን ይበክላሉ። ለውስጣዊና ውጫዊ የጤና ጉዳት ይዳርጋሉ። ለመኖሪያ ተስማሚና ምቹ የማይሆኑባቸው በርካታ መጥፎ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
በከተሞች አዳዲስ ግንባታዎች በስፋት ይከናወናሉ። ዕድሜ ጠገብ የሆኑ አካባቢዎችም ፈርሰው በአዲስ ይቀየራሉ። እንዲህ ያሉ ሰፊ ሥራዎች ደግሞ የአካባቢ ብክለትን በማስከተል ጉልህ ሚና አላቸው።
በንፋስ ሀይል አየር ውስጥ ገብተው ተመልሰው የሰውን ልጅ ጤና ይጎዳሉ። እንደ ካንሰር ያሉ ተላላፊ ላልሆኑ የጤና ችግሮች በማጋለጥ የሰውን ልጅ ይጎዳሉ። በአሁኑ ጊዜ ከሚያስከትሉ የጤና ችግሮች አንዱ የአካባቢ ብክለት እንደሆነ አቶ መሠረት ያስረዳሉ።
እንደ አቶ መሠረት ገለጻ ከተሞች ኮቪድ- 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታን ጨምሮ ሳምባና ሌሎች በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ በመተንፈሻ አካል ላይ የጤና ጉዳት የሚያስከትሉ በሽታዎች በፍጥነት የሚስፋፉትና የጤና ጠንቅ የሚሆኑት በከተሞች ውስጥ ነው። በከተማ የሚኖር ህዝብ አብዛኛው እጅግ በተጨናነቀና ምቹ ባልሆነ መንደር ውስጥ የሚኖር በመሆኑ ለከፋ የጤና ችግር ተጋላጭነቱ ከፍተኛ ነው።
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችንም ሆነ በዓለም ላይ እጅግ ስጋት የሆነው ኮቪድ- 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ በከተማ ለሚኖረው ህዝብ እጅግ ፈታኝ ሆኗል። ፈታኝ የሆነው የከተማ ነዋሪ ከከፍተኛ እስከ ታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ኑሮን ለማሸነፍ እጅግ ፈጣን እንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሲሆን፣ የበሽታው ስርጭትም የዚያኑ ያህል አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል።
ወረርሽኙ ስመጥር የሆኑና ለሀገር ብዙ ሥራ ያበረከቱ የህክምና፣ የጥበብ ሰዎችንና ሌሎችንም ባለሙያዎች እንደሀገር እያሳጣ ይገኛል። ተጋላጭነቱ በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ቢሆንም በህዝቡ ላይ የሚስተዋለው ከፍተኛ መዘናጋት በተለይም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በአግባቡ አለመጠቀም ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን በየቀኑ በጤና ሚኒስቴር የሚሰጠው መረጃ ማሳያ ነው።
ሚኒስቴሩ ሀገሪቱ ባላት የመመርመር አቅም በኮቪድ የሚሞተውን፣ በጽኑ ህመም ውስጥ የሚገኘውንና ከበሽታው ያገገመውን በአሀዝ እያስደገፈ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ መረጃ ለህዝብ ማድረሱን አላቋረጠም።
በተለይም የኢትዮጵያ ዋና መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ኮቪድን በመከላከል በኩል የሚታየው መዘናጋት ከየመኖሪያ ቤቱና ድርጅቶች የሚመነጩት ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች የአካባቢ ብክለትን በማስከተል ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የጎላ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሌላው ያነጋገርናቸው ከፍተኛ የጤና መኮንን የሆኑት አቶ አንተነህ መሐመድ ‹‹በጤና ተቋሟት ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች ጥቅም ላይ ሲውሉ ለጌጥ ወይንም ተቋሙ የጤና ተቋም ስለሆነ አይደለም›› በማለት በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎችንም ለመከላከል እንደሆነ ይገልጻሉ። የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም በተለይ በአራቱም መዓዘን ወጪ ገቢው በሚበዛባት አዲስ አበባ ከተማ አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው ብለው ይወስዳሉ።
እንደ አቶ አንተነህ ማብራሪያ ኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ከተከሰተ ወዲህ ህዝቡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀሙ በትንፋሽ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እንዳስቻለ ሲሆን እንደጉፋን ያለ በሽታ ሊቀንስ ችሏል።
ከዚህ ቀደም እንደሚስተዋለው በየመንገዱ አብዝቶ የሚያስልና የሚያስነጥሰው ሰው እየታየ አይደለም። የአፍና የአፍንጫ መከላከያ ጭብሉ ቢያንስ የጉንፋን ወረርሽኝን መከላከል ችሏል።
ፒያሳ ያለው ታክሲ ተራ አካባቢ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሮማን ልሳነወርቅ የአፍና አፍንጫ ጭንብል እንደማይለያቸውና ተጠቃሚነታቸውን ለማጉላትም ፈገግ ብለው ጥንድ የአፍና አፍንጫ ጭንብል ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ ቦርሳቸውን ከፍተው አሳይተውናል። ‹‹አሁን ያለሁበት አካባቢ ታክሲ ተራ ነው።
እኔም የአዲሱ ገበያ አካባቢ ነዋሪ በመሆኔ ሥራ ቆይቼ ወደ ቤቴ ለመመለስ ታክሲ እየጠበቅኩ ነው›› ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የጀመሩልን ወይዘሮዋ። የእርሳቸውን ጥንቃቄ አድንቄ ሌላውን ለመታዘብ ፊቴን ወደ አካባቢው አዞርኩ። በአካባቢው የታክሲ ተራ ጠባቂ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰው ይተላለፋል።
ተሳፋሪ የሚጠሩ ረዳቶች፣ ልብስና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመሸጥ ዋጋውንና የዕቃውን ስም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚጠሩና የሚሸጡ ነጋዴዎችም ይገኛሉ። አንዳንዶቹ የአፍና አፍንጫ ጭንብላቸውን አገጫቸው ላይ አውርደው ነበር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ገዥውን ሲያግባቡ የነበረው። ጥቂት የማይባሉትም ጭንብል አላደረጉም፤ ከዚህ አንጻር ወረርሽኙ ሞትና የከፋ ጉዳት ቢያስከትል ምን ይገርማል።
ከትዝብቴ መለስ ብዬ ወደ ወይዘሮ ሮማን ዞርኩ። እርሳቸውም ‹‹በፊት በፊት በዚሁ አካባቢ ስመላላለስ አዝወትሮ ጉንፋን ይይዘኝ ነበር። ብርድ ብርድ በማለት ጀምሮ ኃይለኛ እራስ ምታት በማስከተል አስተኝቶኝም ያውቃል›› በማለት ለኮቪድ መከላከያ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም መጀመራቸው እንደጠቀማቸውና ሌላውም እንደርሳቸው ጠንቃቃ ሆኖ ከተጠቀመ ጤናውን ሊከላከል እንደሚችል መክረዋል።
በተለይ በታክሲ ተራ አካባቢ የሚስተዋለውን መዘናጋት አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ግራና ቀኙን ባሉ ግንባታዎች መካከል የፓርኪንግ አገልግሎት የሚሰራው ወጣት አሸናፊ ፍቅሬም ይጋራል። እርሱም እንዳጫወተኝ በአፍና አፍንጫ ጭንብል ብዙ በአየር ውስጥ ተቀላቅለው ለሚከሰቱና ለጤና፣ ጠንቅ የሆኑ ችግሮችን መከላከል ችሏል።
የሚሰራበት አካባቢ ግራና ቀኙን ግንባታ የሚካሄድበት እንደመሆኑ በአፍና አፍንጫው በመግባት በከፍተኛ ደረጃ ጤናውን እያወከ ሲያስቸግረው የነበረውን አቧራ እንዲሁም በሽንትና በተለያየ ነገር ከሚከሰት መጥፎ ጠረን ተከላክሎለታል።
እንደ ወጣቱ አስተያየት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ህብረተሰቡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ባያደርግ ኖሮ ኮቪድ የሚያስከትለው ጉዳትም ሆነ ሌሎች ወረርሽኝ በሽታ የከፋ ይሆን ነበር። መዘናጋቱ እንዲበቃም መክሯል።
በኢትዮጵያ ከአምና መጋቢት ወር ጀምሮ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ታማሚ የሆኑ ሰዎች ቁጥር እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ 2013 ከ121 ሺህ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሲገልጽ በመገናኛ ብዙሃን መስማታቸውን በማስታወስ ሀሳባቸውን ያጋሩን አቶ ሙዲሰር ከማል በመዲናዋ ስርጭቱ የበዛው ነዋሪው በጤና ሚኒስቴርና በተለያዩ አካላት የሚሰጠውን መረጃና ምክር ተግባራዊ
ባለማድረጉ እንደሆነ ያምናሉ። በተለይም በበዓላት ወቅት ህብረተሰቡ ጋር የሚታየው መዘናጋት ከፍተኛ እንደሆነ መታዘባቸውንም ተናግረዋል። ካነጋገርናቸው የመዲናዋ ነዋሪዎችና ከባለሙያዎች ሀሳብ መገንዘብ እንደቻልነው። ምንም እንኳን ኮቪድ እጅግ ከፍተኛ ስጋት ቢሆንም መልካም ጎኖችን አስገኝቷል።
መልካም ጎኑ ቀደም ሲል በአየር ብክለትና በተለያየ ምክንያት ይስተዋል የነበረው የመተንፈሻ አካል የጤና ችግር በመጠኑም ቢሆን እንዲሻሻል እድል ሰጥቷል። የአፍና የአፍንጫ መከላከያ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ሁሉም ተገንዝቦ ሳይዘናጋ እንዲጠቀም እኛም መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
ጭንብሉ ጉንፋንና በትንፋሽ አማካኝነት ሊተላለፉ የሚችሉ እንደሳምባ ያሉ በሽታዎች የስርጭት መጠን በምን ያህል ደረጃ መቀነስ እንደቻለ ወይም የመቀነስ አቅም እንዳለው በጥናት መለየት እንዳለበት መዘንጋት የለበትም።
ከዚህ ባሻገርም የአፍና አፍንጫ ጭንብል ለሁሉም በትንፋሽ አማካኝነት ለሚተላለፉ በሽታዎች መከላከያ ፍቱን መድኃኒት መሆኑን እናውቃለን። ነገር ግን አንዳንዴ ጭንብሉን ዘንግተን ከቤታችን የምንወጣበት ጊዜ አለ የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም ገጥመውን ነበር። አንዱ ወጣት ፈይሰን አበጋዝ ነው።
ፈይሰን እንደገለጠልን ከዚህ በፊት የአፍና አፍንጫ ጭንብል በተደጋጋሚ ዘንግቶ ከቤቱ ይወጣ ነበር። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዚህ መፍትሄ አግኝቷል፤ አንዱ የስልኩን መጥሪያ የኮቪድ መከላከያ መልዕክቶች እንዲሆኑ ማድረግ ነው።
ወጣት ፈይሰን በተጨማሪ እንደሚለው የአፍና አፍንጫ ጭንብልን ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች በአግባቡ ተረድቶ አብዝቶና አዝወትሮ ለመጠቀም የተለያዩ ጉዳዮችን ማስታወስም ይበጃል። ለምሳሌ፦ በተደጋጋሚ መልዕክቶችን ማድመጥ አንዱ ሊሆን ይችላል።
‹‹ጤና ይስጥልኝ። የኮቪድ ፅኑ ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ነው። መዘናጋት ብዙዎችን አሳጥቶናል። ጥንቃቄ ዛሬን ያሻግራል። እባክዎትን ማስክዎን ያደርጉ፣ ሕይወትን ያትርፉ!›› የሚለውን መልዕክት መስማት በራሱ በቀላሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን እንድንጠቀም የሚያነቃን ደወል ነው።
ይህ ስልካችንን ለወዳጅ ዘመዳችን ስንመታ ወደ ጆሯችን የሚንቆረቆረው የኢትዮ ቴሌኮም የጥሪ ድምፅ ያለ ምክንያት አይደለም የሚለቀቀው። ይልቁንም ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ሳያንስ እኛ በመዘናጋታችን ሕይወታችንን እንዳናጣ አሊያም እንዳንታመምና እንዳንሰቃይ ለማስገንዘብ ነው። እርግጥ ነው፤ እኛም እንደምንመክረው እንዲህ ዓይነት መልዕክቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን የአፍና አፍንጫ ጭንብል እንድንጠቀም የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
ከነዚህ በተጨማሪ በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ጥንቃቄና ከኮቪድ ራሱን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረትም የአፍና አፍንጫ ጭንብሉን ለመጠቀም ያነሳሳል። ለአብነት ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ተከሰተ በተባለበት መጋቢት 2012 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት እንዳሁኑ ግንዛቤው የተሻለ ባይሆንም፣ ፍርሃት በወለደው ጥንቃቄ ብዙዎች የኮቪድ-19 መከላከያዎችን ሲተገብሩ ማየቱ የአፍና አፍንጫ ጭንብልን ለመጠቀም ያለውን ወይም የነበረውን አበርክቶ ማውሳት ይቻላል።
ያን ጊዜ የአፍና አፍንጫ ተጠቃሚዎችም እየተበራከቱ የመጡበት ሁኔታ ነበር። በተለይ በአዲስ አበባ ተቋማትን በከፊል ከመዝጋት፣ የትራንስፖርት የመጫን አቅምን በግማሽ ከመቀነስ አንስቶ የተሠሩ ሥራዎች መልካም የጥንቃቄ ትግበራዎች እንዲደረጉ ማስቻላቸውም የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው።
አሁን ላይ ይህ ቢዘነጋም በወቅቱ በየመገናኛ ብዙኃን በስፋት ይተላለፉ የነበሩ መልዕክቶች ቢደበዝዙም ኮቪድ- 19 ከሀገራችን ብሎም ከዓለማችን አለመጥፋቱን ማስታወስና የአፍና አፍንጫ ጭንብላችንን ዘወትር መጠቀም ይበጀናል። የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች እንደ ቀድመው ጊዚያት ወይም ወራት እንዲተገበሩ እኛም የአፍና አፍንጫ ጭንብላችንን በመጠቀም ከራሳችን አልፈን ተርፈን ሌላውን የማዳን ድርሻችንን መወጣት አለብን በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013