አዲሱ ገረመው
ክፍል አንድ
ንጋት 12ሰዓት ጓዜን ሸክፌ ከመስሪያ ቤት በተላከልኝ መኪና ጉዞዬን ወደ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አቅጣጫ አመራሁ።በአምስት ደቂቃ ውስጥ አራት ኪሎ ደረስን።መንገደኛ ስለሆንኩ መንገድ ላይ አንድ ነገር ቢገጥመኝስ አልኩና በቂ ብር ስላልነበረኝ ሹፌሩ መኪናውን እንዲያቆምልኝ ነግሬው አራት ኪሎ ንግድ ባንክ በር ላይ በኤቲኤም ብር አወጣሁ።
ሌባ በተደጋጋሚ ጊዜ ያጠቃኝ ስለነበር ሁል ጊዜም ከባንክ ብር ሳወጣ አጠገቤ ማን እንዳለ በደንብ አስተውላለሁ።ጭር ሲል ነው ብሩን የማወጣው። በዚሁ ሁኔታ ብሬን አውጥቼ ኪስ ውስጥ ለመክተትም ሰከንድ አልፈጀብኝም ነበር፡፡
ቶሎ ብዬ ወደ መኪናው ገባሁና የአራት ኪሎን አደባባይ አልፈን ቤተ መንግስቱን በአይነ ቁራኛ እያየን በሸራተን መንገድ እየወረድን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው ስልክ ደወለልኝ።የት እንደደረስኩም ጠየቀኝ።ከኔ ውጭ ሌሎች ተጓዦች እንዳልተሟሉ ከንግግሩ ያስታውቃል።ቅርብ ርቀት ላይ መሆኔን ነግሬው ስልኩን ዘጋሁት።
ከአራት ኪሎ ጀምሮ ቤተመንግስትን ታኮ ፍልውሃ ድረስ ያለው የመንገድ ላይ መብራት ለአዲስ ዓመት ሰማይ ላይ ደማቅ ብርሀናማ ቀለማትን የሚፈጥሩ ርችቶችን ያስታውሳል።ትዕይንቱን ለመመልከት ዘወትር በምሽት ከቤት መውጣትን ያስናፍቃል።
እውነትም ሸገር ደምቆባት የለ’ንዴ? ከሆኑ ዓመታት በፊት ጣሪያቸው በርበሬ የተሰጣበት የመሰሉ እነዚያ የፊት በር መንደሮች ዛሬ ተለውጠው በወዳጅነት አደባባይ ተተክተው በትዝታ ብቻ ቀርተዋል።ኸረ እንኳንም ሰፈሩ አለፈለት።ቤት መንግሥት አቅራቢያ ሆኖ እንዲያ ማርጀቱ ሁሌም ያስቆጨኝ ነበር።አሁን ግን ልዩ ሆኖ ለኔ አይነቱ “ሁሉ ብርቁ” ሰው ሌላ ዓለም ሊመስለው ይችላል።
መቼም እነ ሙጋቤ ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ሲመጡ በነዚያ አሮጌ ሰፈሮች “ሙድ” ሳይዙብን አይቀሩም።አሁን ግን አይደለም ሙጋቤ ጆ ባይደን ቢመጣ ከአሜሪካ ግዛቶች እንደ አንዱ ሊቆጥር ይችላል።ኧረ እንዳላረፍድ ቶሎ ቶሎ እንሂድ … በዚህ ህብረ ቀላማት
እየተደመምኩ 12፡45 ሲሆን ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ተገኘሁ።በጋዜጠኝነት ሙያ የሀበሻ ቀጠሮ የሚባል ነገር የለም።እና እኔም ድረስ ከተባልኩበት ሰዓት 15 ደቂቃ ያህል ቀድሜ ነበር።
ለጉዞ አስተባባሪው ደውዬ መድረሴን ነገርኩት።በግቢው ውስጥ ሰው ጭኖ ያለ አንድ ነጭ ኮስትር መኪና ውስጥ እንደገባ ጋበዘኝ። ውይ ሳልነግራችሁ ጉዞአችን እኮ ወደ አፋር ነው።አፋር ከአዲስ አበባ ረጅም ርቀት ላይ ካሉ አካባቢዎች አንዱ እንደመሆኑ በመኪና የምንሄድ አልመሰለኝም ነበር።
ደግሞ በረሀውስ እንዴት ይቻላል? እና በድሪም ላይነሩ ቦይንግ ብንሄድ እኮ… እያልኩ ሳስብ ሳሰላስል ሁሉም ነገር ግን ምኞት ብቻ ሆኖ ቀረ።ረጅሙን የበረሀ ጉዞ በመኪና እንጓዝ ዘንድ ተፈረደብን።ሁሉም ተጓዥ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ ሹፌሩ የመኪናውን ሞተር ቀስቅሶ ከግቢ ወጣን።ጉዞ ወደ የበረሀዋ ገነት አፋር።
የየካቲት 12 የዓርቧ የጠዋት ጸሐይ ከምስራቅ በኩል ካለው የሰማዩ ግርጌ ልክ ማለዳ አንድ ሰዓት ገደማ ከደመናው ጋር ሙግት ገጥማ ብቅ አለች።አቦ ስታምር! ጸሐይዋን በመስኮቱ እየኮመኮምን የፍልውሃን መንገድ ይዘን በካዛንቺስ…እያልን ቀጠልን።ስንሄድ የነበረው መንገድ አቋራጭ የበዛበት በመሆኑ ያየኋቸው መንገዶች
ሁሉ ከዚህ በፊት ያላየናቸውና እንግዳ ናቸው።አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠን አዲስ አበባን በቅጡ የመናውቃት ባይተዋሮች እንደሆንን ተሰማኝ።
በጣም የሚገርመኝ ነገር ከትልቅ እስከ ትንሹ አገራችንን የማወቅ ደካማነት ጉዳይ ነው።ስንቱ ነው ስንት አድማሳትን አቋርጦ መጥቶ እነ ላሊበላን የሚጎበኘው እኛ ግን ሸገር መናፈሻን እንኳ በቅጡ አናውቅም።ስንቱ ነው ባህር አቋርጦ መጥቶ አልነጃሺን የሚጎበኘው እኛ ግን እንጦጦ ፓርክን ሳናይ እናልፋለን።ኧረ ጎበዝ አገራችንንማ እንወቃት።ይህ ጉዳይ የተሰማኝ ሸገር ላይ ሆኜ የሚገርሙ የአስፓልት መንገዶችን ካየሁ በኋላ ነው።
ለካንስ የመዲናችን የአስፓልት መንገዶች ዞር ብሎ ከጀርባ ላያቸው አይ ውበት ያስብላሉ። የትራፊክ መብራቶቹ ብዛት ለጥልቅ ተሀድሶ ከያሉበት የተሰበሰቡ እስኪመስል ድረስ እዚያም እዚህም አሉ። ቢጫና ነጭ ቀለም የተቀቡት እና በዋናው መንገድ መሃል ባለው አካፋይ ላይ በተርታ የተተከሉት የሸገር የመንገድ መብራቶች አይን ይስባሉ። ሰዓቱ ገና ስለሆነ በመንገዱ ላይ የሚታዩት መኪኖች ቁጥር አነስተኛ ነው።በመንገድ ዳር ቆመው ተሳፋሪ የሚጠብቁ መኪኖች አለፍ አለፍ ብለው ይታያሉ። በሸገር ያለውን ይሄን መሰሉን ነገር እያስተዋልኩ ጎሮን አልፈን አይሲቲ ፓርክ ጋ ደረስን፡፡
ገና ከአዲስ አበባ ሳንወጣ አይሲቲ ፓርክን አለፍ እንዳልን በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታው ኮየ ፈጬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ክስተት አስደነገጠን።እኛ ከምንሄድበት በስተቀኝ በኩል ሶስት የሲኖ ትራክ መኪኖች እርስ በእርስ ተገጫጭተው ተዛዝለው ቆመዋል።
አላፊ አግዳሚው ፎቶ ለማንሳት መንገድ አቋርጦ ወደ ተሽከርካሪዎቹ ይተማል።የተከሰተው የአደጋ ሁኔታ ሲታይ እጅግ አደገኛና አስደንጋጭ ነው። የመኪኖቹን አወዳደቅ ላየ ሰው ሹፌሮቹ ተኝተው የሚነዱ ነው የሚመስለው።ማንም ሰው እንዲህ አይነት ግጭት ይፈጠራል ብሎ አያስብም።ሶስቱም ሹፌሮች የሪሌ ውድድር ከሌለባቸው በቀር ፈጽሞ እንዲህ ሊጋጩ አይችሉም።
“ይህንን ሲኖ ትራክ የሚባል መኪና ያጥፉልን እንጂ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል የዘንድሮ ሾፌሮች የ17 ዓመት ፈላዎች ናቸው።ሳይበቁ መንጃ ፈቃድ እያወጡ ሰውን እያስጨረሱ ነው” አለ ከተጓዞቹ መሀል በመስኮት ከኔ አጠገብ የተቀመጠው።ሁሉም ከንፈሩን እየመጠጠ፤ አንዳንዱ እርግማን ቢጤም ጣል እያደረገ፣ የተቀረው ደግሞ ወደ ፖለቲካው አዙሮ የሌላ ወሬ መነሻ አድርጎት ጉዞችን ቀጠለ።ሳምንት የአዲስ አበባ-አዳማ ፈጣን መንገድ መግቢያ ጋር እንገናኝ!
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013