አዲሱ ገረመው
ጓዘ ብዙው ምርጫችን እየተቃረበ ነው አይደል? እርሶ መራጭ ፣ተመራጭ ወይስ አስመራጭ? ዝግጅቱስ እንዴት ነው? የየሰፈራችሁ የምረጡኝ ቅስቀሳና ሽርጉድ እንዴት ነው? በዚህች ሰበብ መነሻነት ለዛሬ ስለ ምርጫና ሽኩቻ ብንነጋገርስ ብዬ አሰብኩ።
የምርጫ ቦርዳችን የፓርቲዎችን የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ካስተዋወቀን በኋላ የፓርቲዎቹ ሽርጉድ በዝቷል። ይገርማችኋል በአካል አይቶኝ የማያውቅ ሁሉ ወዳጄ ሆኗል። ያለ ማጋነን ለኔ ለተራው ሰው እንኳን ከአራት ፓርቲዎች የምረጠኝና ቅስቀሳ አድርግልኝ ግብዣ መጥቶልኛል። ዳሩ ምን ዋጋ አለው፤ መስሚያዬ ጥጥ ነው።
የምርጫ ምልክት ሲተዋወቅ እንዲህ አልመሰለኝም ነበር። ባለፈው ጊዜ ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎችን የምርጫ ምልክት ሲነግረን ትከሻዬን ከበዶኝ ነበር። በቃ ደስ አላለኝም ነበር። ባለፉት ምርጫዎች ያገለገሉ የፓርቲዎች ምልክቶች ዘንድሮም በእነዚያው ፓርቲዎችም ባይሆን ዘንድሮም የምርጫ ምልክት ሆነው የቀረቡበት ሁኔታ አለ። ምናለበት አዳዲስ ምልክቶች ይዘው በሚጡ።
አራዳዎቹን የሸገር ልጆች የሚወክሉ ምልክቶችን አላየሁም። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የሸገርን ልጅ የሚመጥኑ የምርጫ ምልክቶች አላየሁም። አሁን ለኛ ለሸገር ልጆች የሚሆን ምልክት ጠፍቶ ነው? ምናለበት ቪትስ መኪና ቢሆንልን? (የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ!)።
አለ አይደል ሳምሰንግ፣ ኣይፎን፣ ያሪስ፣ ቪኤይት፣ ቲክቶክ፣ ያልተገደብ ኢንተርኔት፤ ሳኒታይዘር፣ ጥሬ ስጋ፣ ሃሽታግ፣ ሂውማን ሄር ወዘተ ነው መሆን ያለበት። እናንተ ነገሩ ቀልድ እንዳይመስላችሁ።
አረ ተው እጅህን ከፖለቲካው ሰብስብ አትሉኝም! እንኳን እናቴ ሞታ እንዳውም አልቅስ አልቅስ ብሎኛል ነው ያለችው። ደግሞ ይችን ጣል አድርጌ ሸቤ ልስመጥ እንዴ። ግድየለም ጊዜው የዴሞክራሲ ነው፤ ላውራበት።ምን ላርግ ያለፉት ምርጫዎች ጥለውብኝ ያለፉት መጥፎ ጠባሳ ባያባንነኝ አይገርምም።
ለማናቸውም ፓርቲዎች አሸንፈው ስልጣን መያዝ ከፈለጉ አጀንዳቸውን ብቻ ሳይሆን ምልክታቸውንም ይቀይሩ! አሁን ይሄንን ስል አዛዥ አልመስለም? ለነገሩ ምልክታቸው ምንም ይሁን ምን ምርጫው ሠላማዊ እንዲሆን ነው የምንመኘው።
እንግዲህ ምርጫው ደርሷል፤ ሽርጉዱም ተጀምሯል። ሰውየው “ሚስትህ አረገዘች ወይ?” ቢሉት “ማንን ወንድ ብላ” አለ! በድሮ ማሊያ አሁንም ወደ ሜዳ የሚገቡ አሉ መሰለኝ። አይ የድሮ ቅስቀሳ እቴ፤ ሶሻሊስት ነኝ ሲል ቆይቶ ድንገት ተነስቶ “ነጭ ካፒታሊዝም” ተከታይ ነኝ በማለት ሰርፕራይዝ የሚያደርገን ነበር። አናወራም ብልን ነው እንጂ መጪው ጊዜ ከእከሌ ጋር ብሩህ ነው እንዳላልን የጨለመብን ስንቶች ነን? ይሁን ፤ያም አልፎ ደግሞ ሌላ ዘመን መጥቷል።
ከምርጫ ምልክቶቻቸው ክብደት አንጻር ሲመዘኑ ትንሽ የሆኑ ፓርቲዎች አሉ። የፖለቲካ መጫሚያቸው 44 ቁጥር ሆኖ እግራቸው ከ30 በላይ የማያስኬድ የሉም ነው የምትሉት? በነገራችን ላይ 44 ቁጥር ጫማ የሚያደርጉ ሰዎች አደረጉ ነው የሚባለው ተሳፈሩ? እህ ካለችሁኝ እኮ ብዙ አወራለሁ።
ኢትዮጵያ ተዓምረኛ አገር ናት እኮ! ባለፉት ምርጫዎች ፓርቲዎች ለማሸነፍ እንደሚታተሩት ሁሉ ሽንፈትን ለመቀበል የተዘጋጀ አንድ እንኳን ፓርቲ አልተገኘም? እኔማ አንዳች ኮሽታ ሳይሰማ ምርጫው በሰላም ሲካሄድ ማየት ነበር ምኞቴ፤ ሲያምርህ ይቀር እንዳሉት ሆነ።
እኔ የምለው ግን ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ያን ያህል ከባድ ነው እንዴ? ቁርጠኝነቱ ካለ እኮ ይቻላል። ዋናው ችግር ምን መሰላችሁ? ሁሉም ተፎካካሪ ገና የምርጫ ውድድር ሳይጀመር የአራት ኪሎን ቤተመንግሥት ብቻ እያለመ እኮ ነው ችግሩ። ስልጣን መመኘት ሐጢያት ነው የሚል ነገር አልወጣኝም።
ምርጫ ማሸነፍ ከመሸነፍ እኩል ነው። ወዳጄ የስነልቦና ዝግጅት ማድረግ እኮ ቀላል በረከት አይደለም። እንደው ሌላው ቢቀር ድንገት ራስን ከመሳት /ፌንት ከማድረግ/ ይታደጋል። የኛ ፖለቲከኞች ሲሸናነፉ አሸናፊውን “እንኳን ደስ አለህ“ ማለት አያውቁም እኮ።
ገና ከአሁኑ በቅድመ ምርጫ “ካላሸነፍኩ ሞቼ እገኛለሁ” ብለው ወደ ውድድር ሜዳው የገቡ ብዙ ናቸው። እንዴ ውጤቱን የሚወስነው እኮ እልህ ሳይሆን የድምፅ ሳጥን ነው። አረ ተረጋጉ! ወዳጄ በውጭው ዓለም እኮ (ከአፍሪካ ውጪ) አንዳንድ ፓርቲዎች ወይም እጩዎች ከምርጫው በፊት መሸነፋቸውን አምነው አሸናፊ ነው ላሉት አስቀድመው ስልክ ይደውሉና እንኳን ደስ አለህ ይላሉ አሉ። ይሄ ማለት ግን አልበሸቁም ወይም አልተንጨረጨሩም ማለት አይደለም፤ እንዴት አይበሽቁ! ግን ደግሞ እንደ አገራችን ፖለቲከኞች ዕድሜ ልካቸውን ሲበሽቁ ሲቃጠሉ አይኖሩም።
በቅድመ ምርጫው አትንጨርጨሩ አቦ! ሳትጀመሩት ጨረሳችሁት እኮ። ህዝብ ካልመረጣችሁ አልመረጣችሁም ነው። ታዲያ ደርሶ ጥጃ መሆን ለምን አስፈለገ? ራስን ከማስተዋወቅና የተሻለ ሃሳብ ከማቅረብ ይልቅ በተገኘው መድረክ ሁሉ መዘላለፍስ ምን ይጠቅማል? ለነገሩ ይሄም የዴሞክራሲ ውጤት ነው። የሌላውን የምርጫ ዝግጅት አጮልቀው እያዩ የራስን ማስተዋወቅስ ለምን ይጠቅማል።
አባቴ በፊት እኮ አንድ ወጣ ያለ ቃል ወርወር ብታደርግ “ገዥ ፓርቲው” መጫወቻ ነበር የሚያደርግህ። ሸቤ ቤት ይከትህና ብቻውን ይወዳደራል። አሁን ግን በህቡዕ ሳይሆን በግልጽ ገዥውን ፓርቲ ሳይቀር የሚዘልፉ አሉ። ዴሞክራሲያችን ቀና ቀና ማለት ጀመረች ይህ አይደል ታዲያ። ቱቱቱ…ከዓይን ያውጣሽ በሉልኝ። ግን ስንቶቹ ፓርቲዎች ናቸው አገር አቀፍ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም ቀርጸው የሚንቀሳቀሱ ብንል ምላሽ ለመስጠት የሚሸማቀቁ ብዙ ናቸው።
አንዳንድ ፓርቲዎች እንደ ፓርቲ ወጥ የሆነ ርእዮትም ሆነ ስትራቴጂ እንደሌላቸው ያወቅኩት ለመዋሃድ ሲሯሯጡ ነው። እኛንም ሊያዋዩን በመጡ ጊዜ ነው። ድብልቅልቅ ያለ በዓለም ላይ የሌለ “አይዲዮሎጅ” ያስተዋወቀኝም አለ። በተለይ የኢኮኖሚ ስርዓቱን እንዴት ሊያስኬዱት እንዳሰቡ ጭራሽ የወሰኑም አይመስልም። ግን እኮ ምርጫ ደርሷል። መነታረክ ብቻ!
አንድ ስሙን የማልጠራው ፖለቲከኛ ዓይኑን በጨው አጥቦ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከድቶ፣ አሁን ደግሞ ሌላ ደግፎ የምርጫ ክርክር ሲገጥም አስባችሁታል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጥሩ ነው አልወጣኝም፤ የሆነው ሆኖ ግን ሰውየው ጥሩ ሰው ነው። ተማሪ እያለሁ የመምረጫ ዕድሜዬ ሳይደርስ ገና በፕላዝማ ስለ ኢህአዴግ የሆነ ነገር ሰብኮን 50 ብር አበል አሰጥቶናል። ይሄ ውለታው አይረሳም።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2013