አዲስአበባ፡- የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ባለፉት ስድስት ወራት ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጥምረት ባካሄደው ቁጥጥር በቦሌ ዓለምአቀፍ ኤርፖርት በመንገደኞች ሊገቡ የነበሩ ከ30 አይነት በላይ መድኃኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ህብረተሰቡ ካለሀኪም ትዕዛዝ መድኃኒቶችን ገዝቶ ከመጠቀም እንዲቆጠብና ህገወጦችንም እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በባለስልጣኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አያልሰው መለስ እና የመድኃኒት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ ትናንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊመግለጫ በግለሰቦች ሻንጣ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ከነበሩት የመድኃኒት አይነቶች መካከል‹‹ቪ ማክስ››የተባለ ለስንፈተ ወሲብ፣ለራሰ በረሃነትና ለፀጉር ማሳደጊያ ‹‹ሚኖግዚዳል››የሚባልና ለካንሰር የሚውሉ ይገኙባቸዋል፡፡
አቶ አያልሰው እንደገለጹት ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩት መድኃኒቶች በባለስልጣኑ ያልተመዘገቡ፣አምራቹ የማይታወቅ፣ በሀገር ውስጥም ወኪል የሌላቸው፣ትክክለኛውን የአከመቻቸትና የአጓጓዝ ስርአት ሳይጠብቁ ከመንገደኞች ጓዝ ጋር ሊገቡ የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣መድኃኒቶቹ ጥቅም ላይ ቢውሉ የጎንዮሽ ጉዳታቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ አያልሰው ቀደም ሲል በህገ ወጥ መንገድ በገበያ ውስጥ የተሰራጩትን መድኃኒቶች በማህበራዊ ድረገጽና በተለያዩ መንገዶች የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱ ደግሞ ችግሩን እንዳባባሰው አስታውቀዋል፡፡
ባለስልጣኑ በአምስቱ መግቢያና መውጫ በሮች ባለፉት ስድስት ወራት ጥራትና ደህንነታቸው ያልተጠበቀ 686.8ቶን የሚመዝኑ የተለያዩ የምግብ ጥሬ ዕቃዎችና መስፈርቶችን የማያሟሉ ዋጋቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የህክምና መሳሪያዎችና መዋቢያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉን አቶ አያልሰው አስረድተዋል፡፡
አቶ ገዛኸኝ እንዳለ በበኩላቸው ባለስልጣኑ ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን ህገወጦችን ለመያዝ ጥረት ቢያደርግም በእንስሳት፣በግለሰቦችና በተለያዩ መንገዶች በስውር ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገቡ ገልጸው፤ባለስልጣኑ ህገወጦችን ለፍትህ በማቅረብ ችግሩን ለመከላከል ጥረት ቢያደርግም ለውጤታማነቱ የሌሎች አካላት እገዛ እንደሚያስፈልገው አስታውቀዋል፡፡
ኃላፊዎቹ ህብረተሰቡ ካለሀኪምና ባለሙያ ትዕዛዝ መድኃኒት ከመጠቀም መቆጠብ እንዳለበትና የታሸጉ ምግቦች ላይም ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈው፤ ህገወጦችን ለፍትህ አካል በማጋለጥና ለባለስልጣኑም በ8482 ጥቆማ በመስጠት ችግሩን በጋራ እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
ለምለም መንግሥቱ