የአሜሪካ ድጋፍ በመቋረጡ ሚሊዮኖች በኤችአይቪ ሊያዙ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል

ጉጉ ጆሃንስበርግ መሐል ከተማ ከሚገኘው እና በዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግለት ክሊኒክ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ትወስድ ነበር። ነገር ግን ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ የምትሰጠውን ድጋፍ ማቋረጣቸውን ጥር ወር ላይ ይፋ ሲያደርጉ፣ እሷ እና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ደቡብ አፍሪካውያን በድንገት የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀ።

ጉጉ ዕድለኛ ነበረች። መድኃኒት የምትወስድበት ክሊኒክ ከመዘጋቱ በፊት አሳውቋታል። “መድኃኒቶቻቸውን በጅምላ ማግኘት ከቻሉት ሰዎች አንዱ ነበርኩ። ብዙ ጊዜ የሦስት ወር መድኃኒቴን ነበር የምወስደው። ክሊኒኩ ከመዘጋቱ በፊት ግን የዘጠኝ ወር መድኃኒት ሰጡኝ። “መስከረም ወር ላይ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶቿን ትጨርሳለች። እና ተጨማሪ የምታገኝ ከሆነ ለመጠየቅ አካባቢዋ ወደሚገኘው የሕዝብ ሆስፒታል ለመሄድ አቅዳለች።

ከዚህ በፊት በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርታ የነበረችው የ54 ዓመቷ ጉጉ፣ ኤች አይቪ በደሟ መኖሩን ያወቀችው ሥራውን ካቆመች በኋላ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት በመውሰድ ላይ ነች። በአሁኑ ጊዜ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የፕሮጀክት አስተባባሪ ሆና ትሠራለች። “ነፍሰ ጡር ሴቶች ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ይወስዳሉ፤ ይህ የሚወልዱት ልጅ በቫይረሱ እንዳይያዝ ይረዳቸዋል፤ እናቶች መድኃኒታቸውን በአግባቡ እየወሰዱ መሆኑን ለማረጋገጥ የቤት ለቤት ጉብኝት እናደርጋለን። ለወርሐዊ ምርመራ በሚሄዱበት ጊዜም ልጆቻቸውን እንንከባከብላቸዋል።” ስትል ትገልጻለች፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ በርካታ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶቻቸውን የሚያገኙት በአሜሪካ መንግሥት ከሚደገፉ የግል ክሊኒኮች ነው። ነገር ግን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ተመልሰው ከመጡ በኋላ አብዛኛውን የውጭ ርዳታን በማቋረጣቸው ብዙዎቹ ተቋማት ተዘግተዋል። ሐሙስ ዕለት ይፋ የሆነ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው ኤችአይቪ/ኤድስን በመዋጋት ላይ ኃላፊነት ያለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሜሪካን ብቻ ለይቶ ባይጠቅስም በርካታ ለጋሽ ሀገራት ከፍተኛ ቅነሳ ማድረጋቸው በዓለም ዙሪያ ድንጋጤን ፈጥሯል።

እንዲሁም በሽታውን በመዋጋት ረገድ የተገኘውን “አስደናቂ መሻሻል” የመቀልበስ አደጋ እንዳለው አሳስቧል። ዩኤንኤድስ እኤአ “ከ2010 ጀምሮ አዳዲስ የኤችአይቪ ኢንፌክሽን ቁጥር በ40 በመቶ ቀንሷል። ከ2000 ጀምሮ ደግሞ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሕጻናት በኤችአይቪ ቫይረስ እንዳይያዙ መከላከል ተችሏል። ከ26 ሚሊዮን በላይ ሕይወት ማትረፍ ተችሏል” ብሏል።

ዓለም ርምጃ ካልወሰደ ግን እኤአ በ2029 ተጨማሪ 6 ሚሊዮን አዳዲስ የኤችአይቪ ኢንፌክሽኖች እና አራት ሚሊዮን ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ሊገኝ እንደሚችል እና ከኤድስ ጋር የተገናኙ ሞቶች ሊኖሩ እንደሚችል አስጠንቅቋል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ ከሆነ አሜሪካ ለኤችአይቪ የምታደርገውን ድጋፍ የምታቋርጠው በታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ስኬታማ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ርምጃ ተብሎ በሚታወቀው ዘርፍ የተገኙ አንዳንድ ግኝቶችን ሊቀይር ይችላል።

በዩናይትድ ስቴትስ 43ኛ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋከር ቡሽ የተጀመረው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የኤድስ አጣዳፊ ድጋፍ መርሐ ግብር በምኅጻረ ቃሉ ፔፕፋር፣ በዓለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል ላይ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ አፍስሷል።

ይህም በዓለም ላይ አንድን በሽታ ለመከላከል በአንድ ሀገር ወጪ የተደረገ ትልቁ ገንዘብ ነው ተብሏል። በደቡብ አፍሪካ ወደ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር መሆኑን ዩኤንኤድስ ገልጿል። ከእነዚህ መካከል 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ያህሉ የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና ያገኙ ሲሆን፣ ይህም እኤአ ከ2010 ጀምሮ በኤድስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች በ66 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል። የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የፔፕፋር የገንዘብ ድጋፍ ለኤችአይቪ/ኤድስ መርሐ ግብሩ 17 በመቶ ያህል አስተዋፅዖ አድርጓል ብሏል።

ገንዘቡ ለታካሚዎች በቀላሉ ሕክምና ለማግኘት እንዲያስችላቸው በሚል የተንቀሳቃሽ ክሊኒኮችን ከማቋቋም ጀምሮ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ይውል ነበር። የትራምፕ አስተዳደር የሚያደርገውን ድጋፍ መቀነሱ የኢንፌክሽኑ መጠን እንደገና ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል። የጆሃንስበርግ ዊትስ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር ፕሮፌሰር ሊን ሞሪስ እንደተናገሩት “በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመርን፣ የቲቢ ሕሙማንን እና በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የተጠቁ ሰዎችን ማየት የምንጀምር ይመስለኛል” ብለዋል።

ጉጉ የኤች አይቪ ሕክምና የሕይወት እና የሞት ጉዳይ እንደሆነ ትናገራለች። በተለይ በወሲብ ንግድ ላይ ለተሰማሩ እና የበለጠ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕክምናው አጠያያቂ አይደለም። የርዳታው መቀነስ የኤችአይቪ ክትባት እና የኤድስ መድኃኒት ለማግኘት በሚደረገው ምርምር ላይም ተፅዕኖ አሳድሯል።

ሌላው በዚህ ዓመት የተሠራጨው ውጤታማ የሆነው የበሽታው መከላከያ መድኃኒት ሌናካፓቪር (Lenacapavir) ነው። ይህ መድኃኒት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚወሰድ ሲሆን፣ ከኤችአይቪ የሚከላከል ክትባት ሲሆን በደቡብ አፍሪካም ተሞክሯል። መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የላንሴት የሕክምና ጆርናል ላይ ባለፈው ወር ሳይንቲስቶች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ የኤድስ ሞትን በ65 በመቶ ወይም በ25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቀንሶታል ማለቱን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You