ራስወርቅ ሙሉጌታ
ወጣት ንጉሱ ገመቹ ይባላል ተወልዶ ያደገው በሰሜን ሸዋ ፍቼ ሰላሌ ዞን ጅዳ ወረዳ ውስጥ በምትገኝ ነስሪ ኮሶ በምትባል አንዲት የገጠር ቀበሌ ነው። ንጉሱ እንደማንኛውም የአካባቢው ህጻን እየተጫወተም ከብትም እያገደ የልጅነት ግዜውን ያሳለፈ ቢሆንም ዘጠኝ ልጆች ላላቸው እናትና አባቱ የመጀመሪያ ልጅ በመሆኑ ነፍስ ካወቀ ጀምሮ የነበረውን ግዜ የሚያሳልፈው በእርሻ ስራ ቤተሰቡን በመደገፍ ነበር።
የንጉሱ አባት አቶ ገመቹ ቶላ በአካባቢው የተከበሩና የታፈሩ ታዋቂ ሰው የነበሩ ሲሆን ከግብርና ውጪም የተለያዩ የንግድ ስራዎችንም ያከናውኑ ነበር። በአስራ ዘጠኝ ዘጠና አምስት ዓ∙ም በህገወጥ መንገድ መሳሪያ ትሸጣለህ ተብለው በፖሊስ መፈለግ ይጀምራሉ። በወቅቱ አቶ ገመቹ ወደ ህግ ለመቅረብ ፈቃደኛ ስላልነበሩና ከዚህ ቀደም በተመሰሳይ ተጠርጥጠረው ታስረው ስለነበር ፖሊሶች እንደመያዣ ንጉሱን አስረው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይወስዱታል።
እዛም ካደረሱት በኋላ ከዛሬ ነገ አባቱ እሱን ለማስፈታት ሲመጡ እናገኛቸዋለን ብለው ሲጠብቁ ያቆዩታል። ፖሊሶቹ እንዳሉትም ልጃቸው ያለበት ሁኔታ አላስችል ያላቸው አባት ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ በአንዲት ያልተባረከች ቀን ልጃቸውን ለማየትና የሚመጣውን ለመቀበል በመወሰን እቤታቸው አድረው ንጋት ላይ ሲወጡ እዛው እደጃቸው ላይ እሳቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ ፖሊሶች ጋር ፊት ለፊት ይገጣጠማሉ።
ነገር ግን ፖሊሶቹም ነገሩን ቀለል አድርገው በሰላም ለመደራደር ከመሞከር ይልቅ ወደ ሀይል እርምጃ በማዘንበላቸው በፖሊሶቹና በአቶ ገመቹ መካከል ገና በጠዋቱ የተኩስ ልውውጥ ማድረግ ይጀመራል።
ይህም ሆኖ በወቅቱ የከፋ ችግር ሳይደርስ ተበታትነው ለመለያያት ቢበቁም ከሰዓታት በኋላ እንደገና ፖሊሶቹና አቶ ገመቹ በድጋሚ ፊት ለፊት ይገኛኙና በድጋሚ በታጠቋቸው መሳሪያዎች መነጋጋር ይጀምራሉ።
ይህቺኛዋ አጋጣሚ ግን ለንጉሱ አባት ለአቶ ገመቹ ቶላ ጥሩ አልሆነችም፤ እጃቸው ላይ ያለውን ጥይት ሲጨርሱ ተዘጋጅተው ታጥቀውና ተደራጅተው በመጡት ፖሊሶች ይመቱና ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ያሸልባሉ።
ገመቹ በዚህ አይነት የተለዩትን የአባቱን እረፍት የሰማው እዛው እስር ቤት እሱ እንደሚለው በማያውቀው ጉዳይ ለመያዣነት በተቀመጠበት ነበር። በወቅቱም እዛው እስር ቤት የነበሩ ጓደኞቹ አንድ አንድ ብር በማዋጠት ቆሎና ሻይ በማዘጋጀት ያስተዛዝኑታል።
ከዚህ በኋላ ፖሊሶችም ንጉሱን ፍርድ ቤት አቅርበው አባቱ ጋር ይሰራ እንደነበር በማድረግ እሱ ባያምንበትም ሰባት ዓመት እንዲፈረድበት ያደርጋሉ። ከቤተሰብ ተለይቶ የማያውቀው ንጉሱ በዚህ አይነት የስቃይና የመከራ ባህር ውስጥ እየዋኘ አምስት ዓመታትን በእስር ቤት ለማሳለፍ ይገደዳል።
እነ ንጉሱ ይኖሩበት የነበረው ሰፊ ግቢ ከአያት ቅድም አያት ሲወራረድ የመጣና ሶስት አባወራዎችን አቅፎ የያዘ ሲሆን ሶስቱም አባዎራዎች የንጉሱን አባት ጨምሮ ወንድማማቾች ነበሩ።
ያ ሶስት ወንድማማች አባ ወራዎችን የያዘ ገቢ ይኖር የነበረው ሰው በሙሉ ደግሞ እንደ አንድ ቤተሰብ በፍቅር በመተሳሰብ ይኖር የነበረ በመሆኑ እንኳን በበአል ቀን ይቅርና በአዘቦቱም ቢሆን በአንድ ወገን አዋቂዎች በሌላ በኩል ልጆች አንድ ላይ ተሰብስብው ወንበር ጠቧቸው ነበር ገበታ እንኳን የሚቀርቡት። እነዚህ ሁሉ ትዝታዎችና የአባቱ ሞት ብሎም የእሱ ካለበቂ ምክንያት መታሰር ንጉሱን የእግር እሳት ሆኖበታል።
በህይወት ካሉ የድል ቀን መድረሱ አይቀርምና ንጉሱ የተፈረደበትን ግዜ ጨርሶ ከእስር ተፈትቶ ወደ ቤተሰቡ ያቀናል። እቤት ሲደርስ ከአባቱ ቀጥሎ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ ቤቱን ሲቆጣጠር የነበረው እሱ ስለነበርና በተፈጠረው ችግር ግን ሁለቱም እቤት ባለመኖራቸው ብዙ ሀብት ከብቶችና በጎች በተቀመጡበት ሳያገኛቸው ይቀራል።
ምንም ሳይሆን ማንም ሳይነካው በሰላም የጠበቀው ነገር ቢኖር ሰፋፊው የአባቱ የእርሻ መሬት ብቻ ነበር። ለቤተሰቡ ትልቅ ፍቅርና አክብሮት የነበረው ንጉሱ በዚህ ወቅት የቤተሰቡን ኑሮ እንደ አዲስ ማቃናትና ሀዘናቸውንም ማስረሳት የሱው ሀላፊነት ሆኖ ያገኘዋል።
ለዚህ ደፋ ቀና ከማለቱ በተጓዳኝ ደግሞ የልጅነት ፍቅረኛው የነበረችውን ልጅ ለማግባት ብሎም ቤተሰብ መስርቶ ወግ ማዕረግ ለማየት ይወስንና በአንድ ወገን ቤተሰቡን አሰባስቦ ማስተዳደሩን በሌላ በኩል የራሱን አዲስ ቤተሰብ የመመስረቱን ስራ ይያያዘዋል።
ፍቅረኛውም ምንም እንኳን ከአንዴም ሁለት ሶስት ግዜ ጠለፋ ተሞክሮባት የነበረ ቢሆንም እሱን በልቧ አስቀምጣ ስለነበር ወደ ሌላ ሳትሄድ እየጠበቀችው ያገኛታል። በወቅቱ ነገሩን የተረዱት የሷም ቤተሰቦች ሲጠብቋት ከመኖር አልፈው አንዳች ስህተት እንዳይፈጠር በሚል ገበያ እንኳን አይልኳትም ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ የእሱና የእሷ ቤተሰቦች አንተም በሰላም እቤት ለመግባት በመብቃትህ ለሁላችን ደስታ ለሁላችን ድል ነው።
ያለህበትንም ሁኔታ ሁላችንም እናውቃለን፣ ስለዚህ ሀብት ለማፍራቱም ለሌላውም ሌላውም ነገር ይደርሰበታል፣ ዋናው የእናንተ የልብ መፈቃቀድ ነው፣ ይሄ ሁሉ ነገር ተፈጥሮ እንኳን ያልተለያያችሁት ፈጣሪ እህል ውሃችሁን አንድ ይሁን ስላለ ነው፤ ስለዚህ ምንም ግዜ ማጥፋት አያስፈልግም፣ ብለው በተፈታ በሁለተኛ ሳምንቱ በወግ በማዕረግ የአቅማቸውን አድርገው በሰርግ እንዲጋቡ ያደርጋሉ። ይህ አጋጣሚ ለንጉሱ ከአባቱም ሀዘን ከቤተሰቡም ችግር መጽናኛ ያገኘበት ነበር።
በዚህ ሁኔታ አዲሱን ህይወት የጀመረው ንጉሱ በተወሰነ ደረጃ የቤተሰቡ ህይወት እንዲስተካከል፣ እንዲቃና ብሎም ነገሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ካደረገ በኋላ እዛው ቦታ ላይ ለመኖር ፈቃዱ ስላልነበር ባለቤቱን ይዞ በቅርብ ወደ ነበረችው ከተማ ያቀናል። እናቱን ወይዘሮ ክቡ መንገሻን ወደ ከተማ በማውጣትና ለእሳቸውም ቤት በመስራት ሀዘናቸውን ረስተው አዲስ ህይወት እንዲጀምሩ ያደርጋል።
ንጉሱ እሱና ባለቤቱን ይዞ ከተማ አዲስ ህይወት ሲጀምርም በከተማ ግብርናው ስለማይታሰብ ለመተዳደሪያው የመረጠው የሙያ መስክ ደግሞ ሽመናን ነበር። ንጉሱ ከቤተሰቡም ሆነ በአካባቢው የሽመና ስራ የሚሰራ ባለሙያ ያልነበረ ቢሆንም በማረሚያ ቤት ባሳለፋቸው ግዜያት ጊዜውን በአልባሌ ነገር ከማሳልፍ ብሎ ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን የተለያዩ ሙያዎችን ይማር ነበር።
ከእነዛም ስልጠናዎቹ መካከል በብቃት ሊከውነው የሚችለውንና ብዙም ጥሪት የማይጠይቀውን ሽመና ስለነበር የሚያስፈልጉትን እቃዎች በራሱ ጥረት አሟልቶ እየሰራ እሱንና ባለቤቱን ማስተዳደሩን በአቅሙ ቀሪውን ቤተሰብ መደጎሙንም ይቀጥላል ።
ነገር ግን ስራው አድካሚ የመሆኑን ያህል በቂ ገቢ የማያስገኝ ለዚያውም ወቅት የሚመርጥ በመሆኑ ምን አልባት ከደከምኩ አይቀር በቂ ገቢ ማግኘት አለብኝ የሚል ሀሳብ ሰንቆ ጠቅሎ ወደ አዲስ አበባ በመግባት በሸማ ስራው ነጠላ ጋቢና እንዲሁም የተለያዩ የባህል ልብሶችን ማምረቱን ይቀጥላል።
ነገር ግን አዲስ አበባም ለስድስት ወር ያህል ሸማ ዘርግቶ ሲሰራ ከቆየ በኋላ አሁንም ቢሆን ገቢውና ልፋቱ ሊመጣጠን ባለመቻሉ ሌላ ስራ መቀየር እንዳለበት ይወስንና ከሳ ከሳ ያሉ ከብቶችን እየገዛ እራሱ እያደለቡ መሸጥ ይጀምራል።
ይህም ቢሆን ግን ረጅም ግዜ የሚወስድ ብዙ ጉልበትና ጥሪት የሚጠይቅ ሲሆን እንዲህም ተለፈቶ የአንድ ቀን ገበያ ዋጋ ከተናጋ ጥሪትን ሁሉ ይዞ ገደል የሚገባ ሆኖ ስላገኘው አንድያውን በሬ እየገዛሁ መሸጥ ብቻ ይሻለኛል ብሎ ጠቅሎ ወደ በሬ ንግዱ ይገባል። ይህም ቢሆን ግን እሱ እንደለመደው የእርሻ ስራ የሚቀላጠፍ አልነበረም፤ ስራው ብዙ ጥረት ብቻ ሳይሆን ትልቅ እድልንም የሚጠይቅ ይሆንበትና ሊያዛልቀው ሳይችል ይቀራል።
ነገር ግን ለእሱም ለባለቤቱና አዲሱን ቤተሰብ ለተቀላቀሉት ልጆቹም የሚያስፈልጋቸውን ማሟላት እንደሚጠበቅበት ስለሚያውቅ ስራ ፈትነት እንዳይጠናወተው ሌላ የስራ መስክ ማማተሩን ይቀጥላል። በዚህ ጊዜ ነበር በቅርብ ካገኘውና በአጭር ግዜም ውጤታማ ከሆነበት የግንባታ ስራ ጋር ለመተዋወቅ የበቃው።
ለስራ ደከመኝና ሰለቸኝ የማይለው ንጉሱ በአጭር ግዜ ሙያውን በመካን ግንበኛ ለመሆን ይበቃል። የግንበኝነት ስራ አድካሚና ትእግሰት የሚጠይቅ ቢሆንም አንጻራዊ በመሆኑ ከሽመናና ከበሬ ንግዱ የተሻለ ሆኖ ስላገኘው እሱን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ንጉሱ በእነዚህ ግዜያት ሁሉ ግን ንጉሱ የአባቱን ሀዘን ከሰማበት ቀን ጀምሮ ብሶቱንም፤ ሀሳቡንም፤ ስለፍቅረኛውና ሌሎች ነገሮች የነበረውንም ምኞቱን ሲያንጎራጉር ስለነበር ሳያስበው የሙዚቃ ስሜት ውስጡ ተፈጥሮ ነበር። እናም ከተፈታበት ቀን ጀምሮ እንደ ቀልድ ሲሞነጫጭራቸው የነበራቸውን ጽሁፎች አስተካክሎ በዜማ አጅቦ ለአድማጭ ጆሮ ለማድረስ መንቀሳቀስ ይጀምራል።
እናም ግራና ቀኙን ካማተረ በኋላ ለገጣፎ አካባቢ ወደሚገኝ የሙዚቃ አቀናባሪ በመሄድ ያሰበውንና ያለውን ነገር ያዋያቸዋል። ንጉሱ ይህንን ሲያደርግ በልቡ ሁለት ሀሳብ ሰንቆ ነበር በአንድ ወገን ሲያብላላው የኖረውን የመተማመን ጠቀሜታ፤ የመከዳዳትን አሳዛኝ መጨረሻ ለህዝብ ለማስተማር ሲሆን በሌላ በኩል እንደ ቀልድ ሲያንጎራጉርና ሲጽፍ ይተቹት የነበሩትን የሰፈር ጓደኞቹን የጉዞውን የልፋቱን መጨረሻ ማሳየት ነበር።
እነዚህን ሁለት ሀሳቦች ይዞ ያቀናበት የሙዚቃ አቀናባሪ ምንም እንኳን የሙዚቃ እውቀት እንደሌለውና ከዚህም በፊት በምንም ሁኔታ ከባለሙያ ጋር በሙዚቃ መሳሪያ ታጅቦ እንዳልሰራ ቢያውቅም አንዳች ነገር ውስጡ እንዳለ ስለተረዳ ፈይሰል አብዱራህማን ወደተባለ አቀናባሪ ይመራዋል።
ፈይሰልም ይቀበለውና ንጉሱ ይዞት የመጣው ነገር በወቅቱ አንድ ነጠላ ዜማ ለመስራት በቂ በመሆኑ የሚያስፈልገውን ነገር በሙሉ እንዲሟላ ካደረገ በኋላ አብርሃም ራያ በሚባል ቪዲዮ ቀራጭ አማካይነት አንድ ባለ ክሊፕ የኦሮሚኛ ነጠላ ዜማ እንዲሰራ አድርጎ ለህዝብ ጆሮ እንዲደርስለት ያደርጋል።
በዚህ የተነቃቃው ንጉሱም ውስጡ የነበሩት የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች በማንሳት አንድም ክፍያ የማያገኝበት ቢሆንም በተለያዩ ግዜያት እያዘጋጀ ሰባት ነጠላ ዜማዎችን ለህዝብ ጆሮ ለማድረስ ይበቃል።
ዛሬ ንጉሱ ከባለቤቱ ከወይዘሮ በሀሩ ቢቂላ ጋር በመሆን ልጆቹን ትእግስት ንጉሱንና ሳምራዊት ንጉሱን እንዲሁም ከልጅነቷ ጀምሮ ያሳደጋትን የእህቱን ልጅ መስከረም ገመቹን እያስተማረና እያሳደገ በመኖር ላይ ይገኛል።
ይህም ሆኖ ግን ንጉሱ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሚሰንፍ ባይሆንም ዛሬ በሁኔታዎች አለመመቻቸት በርካታ ስለሀገር አንድነት ስለ እርስ በእርስ መዋደድና የወጣቶችን ችግርና ጥያቄ የተመለከቱ ያዘጋጃቸውን ዘፈኖች ለህዝብ ለማድረስ አቅሙ አልፈቀደለትም። እናም አሁንም ድረስ ስፖንሰር በማድረግ ስራዎቹን ለህዝብ የሚያደርሱለትን እየማተረ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም የተወሰኑት ነጠላ ዘፈኖቹ በዩቲብ ሲለቀቁ ክፍያ እንደሚፈጸምለት ቃል ተገብቶለት የነበረ ቢሆንም የተመልካቹ ብዛት አንድ ሚሊየን ሞልቶ ገቢ ለማስገኘት በሚያስችል ደረጃ ላይ ባለመድረሱ እስካሁን ከቀጠሮ ምንም ያገኘው ነገር የለውም።
ይህም ሆኖ ንጉሱ አሁንም የቀደሙትንም ሆነ አሁን ያዘጋጃቸውን በርካታ ዘፈኖች በማቀናበር በአንድነት ለአድማጭ ለማድረስ እቅዱም ፍላጎቱም ብቃቱም ያለው ቢሆንም የአቅም ጉዳይ ገድቦት ስለሚገኝ አብሮት የሚሰራ ቢያገኝ ለሀገር ለህዝብ የሚጠቅሙ ስራዎችን ለአድማጭ ጆሮ ለማድረስ ዝግጅቱን አጠናቆ እየተጠባበቀ መሆኑን ይናገራል።
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013