ተገኝ ብሩ
አንዳንድ ማስታወቂያ ከአእምሮ እንዳይረሳ ሆኖ ሲለሚዘጋጅ ባሰብነው ቁጥር ይታወሰናል:: አንዳንዱ ደግሞ ታስቦበት ባለመዘጋጀቱ ሳቢያ ምነው በቀረ ያሰኘናል:: ሰሞኑን በየቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎች የሚለቀቁት ማስታወቂያዎች የተዛነፉና የማህበረሰብ ባህልና ወግን የተፃረሩ ሆነውብኛል::
ማስታወቂያዎቹን ህዝብ ዘንድ ማድረስ እንጂ እዚያ ከደረሰ በኋላ ሊፈጠር የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ፈፅሞ ያገናዘቡ አይመስሉም:: ጎበዝ እነሱ እንካችሁ የሚሉንን እኛም አምጡ እያልን የምንቀበላቸውን ነገር ካልመረመርን ውሎ አድሮ እንፈተንበታለን::
አጃይብ ያሰኘኝን የሰሞኑን የማስታወቂያዎች ትዝብቴን እንዳነሳም ምክንያት የሆኑኝን በማስቀደም ልጀምር:: የስነ ተዋልዶና የቤተሰብ እቅድ ተጠቃሚ ሁኑ የሚሉን ምክር ሰጪዎች አልበረከቱም ትላላችሁ? ሰሞኑን በየቴሌቪዥን ጣቢያው እንዳሸን የፈሉት እነዚሁ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል እና ተመሳሳይ ምርቶች አስተዋዋቂዎች ምን አስበው ይሆን በዝተው መገኘታቸው? የሀገራችን ህዝብ ቁጥር መበራከት ከእኛ በላይ እነሱን እንቅልፍ ነስቷቸው ይሆን እንዴ?
በነገራችን ላይ እነዚህ ማስታወቂያዎች የሚመሩትና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት በበለፁጉት አገራትና በእነዚሁ አገራት ትልልቅ ድርጅቶች መሆኑን ስናስብ ሌላ እይታ አይፈጥርም:: ልጆቻችሁን መጥናችሁ በገቢ አቅማችሁ ውለዱ ማለታቸው ባልከፋ፤የአሁኑ አካሄዳቸው ከፋ እንጂ::
በአገራችን ባህል በህብረተሰባችን የዳበረ መልካም ልምድ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም ፆታዊ ግንኙነት አስነዋሪ ነው፤የሰሞኑ ማስታወቂያዎች ግን ይህንን ተላልፈዋል:: ከጋብቻ በፊት ጾታዊ ግንኙነትን የሚከለክል ማስታወቂያ መስራት ሲገባቸው፣ለችግር ጊዜ የሚሆነው ሁለተኛ ደረጃውን ማስታወቂያ መስራት ውስጥ መግባታቸው ምን ይሉታል::
ኧረ ጎበዝ!/እህም ነው እንዳትሉኝ!/ ይባስ ብለው በድፍረት በሰሞንኛ ማስታወቂያቸው ወላጆች ልጆቻቸውን አንድ ለአንድ እንዲወሰኑና የእርግዝና መከላከያ እንዲጠቀሙ ያድርጉ ሁላ ይሉን ጀምረዋል:: ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ፣ በቴሌቪዥንና ሬዲዮ በስፋት እየተላለፉ ካሉት ማስታወቂያዎች መሀል አንዱን የቴሌቪዥን ማስታወቂያ እንይ::
ይህ በአማርኛ “ወይ ጉድ እንደው ምን አይነት ጊዜ መጣ የሚያስበለው ማስታወቂያ የሚጀምረው ሁለት ወጣቶች እጮኛሞች ናቸው::/እንደ ማስታወቂያው) ከአውቶቡስ እየወረዱ ያሉበት ሁኔታና ካሉበት አገር ተደብቀው ወደ ሌላ አገር የእርግዝና መከላከያ እንክብል ለመግዛት የመጡ ስለመሆናቸው በቀላሉ ከንግግራቸው መገንዘብ ይቻላል::
እነዚህ ወጣቶች ከማህበረሰብ ባፈነገጠ መልኩ ከጋብቻ በፊት የጀመሩት ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት የተፈቀደ ያህል በነፃነት እንዲያወሩት ተደርገው መሳላቸው ያስተዛዝባል:: ወጣቶቹ አንድ ፋርማሲ ገብተው እንክብሉን ገዝተው ሲወጡ፣ የልጅትዋ አክስት መንገድ ላይ ድንገት ስታገኛቸው ለምን እዚያ እንደተገኙ ጠይቃ የያዙትን የወሊድ መቆጣጠሪያ ተመልክታ ከባህልና እምነቱ ባፈነገጠ መልኩ ልጆቼ ይሄ እኛም አካባቢ ነበረላችሁ፤ እዚህ ድረስ ምን አስመጣችሁ ትላቸዋለች፤ ጉድ ነው:: ከማህበረሰቡ ያፈነገጠ ተግባርን በድጋፍ መልክ ለዚያውም ከሚከበረውና ከሚታፈረው የቤተሰብ አባል በድፍረት ጎበዝ በርታበት ሲባል በእርግጥም ጉድ ያሰኛል::
ይህ ባህልና ደንብን የጣሰ የማህበረሰቡን ትውልድ ማቅኛ ማህበራዊ ስርዓትን መጠበቂያ ግድብ የተላለፈ ማስታወቂያ ከተሳታፊ ገፀ ባህሪያት ምስል እና ንግግር በኋላ በሌላ ተገቢነት በሌለው ሰበካው ይቀጥላል::
ማስታወቂያው ወላጆች ለወጣት ልጆቻቸው የወሊድ መከላከያ እንዲጠቀሙ ያበረታቱ የሚል መልዕክት በመንገርም ያበቃል:: ይህ ነገር አዬ ዘመን አያስብልም ታዲያ፤ወገን::
መገናኛ ብዙኃኑስ ይህንን ማስታወቂያ ለህዝቡ ሲያቀርቡ እንዴት ማህበረሰቡን አያስተውሉም:: ባህልና ስርዓት የሚፃረር ጤነኛ የሆነ ትውልድ እንዳይፈጠር ፣ስርዓት እንዲዛነፍ የሚያደርግ መልክት በድፍረት ለማስተላለፍስ እንዴት በቁ? አገር ለማቅናት ዋንኛ ሚና የሚጫወተው ትወልድ እንዲታነፅ ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሰራ አደጋ ነው:: ለአገር ተረካቢው ትውልድ በየሚዲያው በሚቀርቡ እያንዳንዳቸው ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ ካልተደረገ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም::
የበለፀጉት አገራት መሰል ማስታወቂያዎችና የዘርፉ ትልቅ ተዋናይነት ግን አንድ ነገር ያመላክታል:: የበለጸጉት ሀገሮች ስለኛ ትውልድ የተዛነፈ መሆን ቁብ አይሰጣቸውም:: እነሱ ከምርታቸው የሚያገኙትን ትርፍ ነው የሚያሰሉት፤ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የእኛ ልጆች ቁጥር መበርከት ያሳሰባቸው ለእነሱ ልጆች ዓለም እንዳይጠብ የሚያስቡም ይመስላል::
የኛው ሚዲያዎችም ይገርማሉ:: ባለማስታ- ወቂያዎቹ የሚያስተዋውቁበት መንገድ እኛና ማህበረሰባችንን ያላገናዘበ ወግና ልማዳችን የጣሰ በማህበረሰባችን ዘንድ የተለመደውን ሥርዓትና ወግ የሚፋለስ መሆኑን አለማስተዋላቸው ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል::
መነሻቸው አውሮፓ መዳረሻቸው ደግሞ የእኛ ቢጤ የሆኑት ታዳጊ አገራት ላይ በገፍ የሚፈሱት እነሱ ውለዱ ብለው እያበረታቱ፣ እኛን መውለድ አቁሙ ልጆቻችሁን አራርቃችሁ ወደዚህ ምድር ቀላቅሉ ብለው መወትወታቸው የበዛው በእነሱ ታስቦበት የሚካሄድ ዘመቻ ነው::
አትውለዱ ብለው የሚመክሩት እነሱ ዘንድ ጨምሮ እኛ ዘንድ እንዲያንስ ስለሚፈልጉ ነው::አዎን እኛ በዝተን የዓለምን ሀብት እንዳንሻማ ለእነሱ ትውልድ በመውለድ በዝቶ እድሉ እንዲሰፋ ይፈልጋሉ::
አሰብንላችሁ ብለው የተላመድነውንና የኖርንበትን ስርዓት እንዳይንዱት መጠበቅ ይኖርብናል:: በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የበለጸጉትን ሀገሮች አጀንዳ በመያዝ ያለገደብ እና አግባብ ንዋይን ለመሰብሰብ በሚፈጸም ድርጊት የማህበረሰብ ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፤ ይህም አገር እና ትውልድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ብሎ ጉዳዩን መመርመር ግድ ይላል:: ኃላፊነት የሚሰማው የማስታወቂያ አሰሪ ድርጅትም ይሁን ማስታወቂያው የሚተላለፍበት የመገናኛ ብዙኋን ሥራቸውን በጥንቃቄ ሊከውኑ ይገባል::
ምርትና አገልግሎት ለተጠቃሚ በተለያየ መልኩ ይተዋወቃል:: ማስታወቂያ የማህበረሰብ ስርዓት የሚያፋልስና በትውልድ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆን የለበትም::
እነዚህን ማስታወቂያዎች ለህብረተሰቡ በማቅረብ የተጠመዱበት መገናኛ ብዙኃን በአገር ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑ የማይታበይ ሀቅ ነው:: ሀገሪቱ ባስቀመጠችው ህግ ተመርተው ከሰሩ ለአገር ጥቅም በህዝብ ወገንተኝነት ከሰሩ ደግሞ አገርም እነሱም አትራፊ ይሆናሉ::
መገናኛ ብዙኃኑ ለህብረተሰቡ በሚያቀርቡት መረጃ አልያም ማስታወቂያ ተገቢነት የሌለውና ማህበረሰባዊ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል መሆን የለበትም::የማስታወቂያው ይዘት ባህልና ስርዓትን የሚቃረን ሲሆን ፣ ዞሮ ዞሮ የሚያጡት ያንኑ ማህበረሰብ ነው፤ ደንበኛቸው የሆነውን ያንኑ ትውልድ ነውና እነሱም በኃላፊነት ሊሰሩ ይገባል::
የወሊድ መከላከያን ለማስተዋወቅ ወላጆች ልጆቻችሁን መከላከያ እንዲጠቀሙ አበረታቱ ማለት ትልቅ ዝንፈት መሰለኝና ይህን አልኩ፤አበቃሁ ቸር ይግጠመን::
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013