ጌትነት ተስፋማርያም
በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኘው የአፋር ክልል በአብዛኛው በረሃማ የአየር ንብረት ያለው አካባቢ ነው። ክልሉ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተዳክሞ የቆየ እና እንደሌሎች ታዳጊ ክልሎች ሰፊ የመንገድ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚያስፈልገው አካባቢ መሆኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር ሲገለጽ ቆይቷል።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያመላክተው ከምስራቅ አፍሪካ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው አፋር ክልል በአምስት የአስተዳደር ዞኖች የተዋቀረ እና አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 270,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚገመት የቆዳ ስፋት ይሸፍናል፡፡
ይህን ሰፊ የመሬት አካል በመንገድ መሰረተ ልማት በማገናኘት ህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ዋነኛው የነዋሪዎች ጥያቄ ነው። በክልሉ ስላለው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እና ስለመሰረተ ልማት ክንውኖች በተመለከተ ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሃ አህመድ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን : – በአፋር ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በመንገድ እና ድልድይ ግንባታዎች ምን ያክል ሥራ ተከናውኗል፤ የመንገድ ፕጀክቶቹ ግንባታ ሂደት ይዘገያል የሚሉ አሉ፤ ይህ ለምንድነው?
አቶ ጣሃ አህመድ: – በአሁኑ ወቅት በተለይ ከለውጡ በኋላ በአፋር ክልል መንገድ ዘርፍ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልል መንግሥት የሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉ። ፕሮጀክቶቹ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በመንገዶች ባለስልጣን ስር ዘጠኝ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል። ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት የተደረገባቸው እና በፌዴራል ደረጃ የተያዙት የአስፋልት መንገድ ግንባታዎች ናቸው።
በክልል ደረጃ ደግሞ ከ260 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ የመንገድ ጥገና፤ የአዳዲስ መንገድ መስመር ከፈታ እና የደረጃ ማሻሻል ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። አሁን ላይ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በመደበኛ ጥገና ደረጃ 70 ኪሎ ሜትር ያክሉን መንገድ ለመጠገን ተችሏል።
ወቅታዊ በሚባል የጥገና አሰራር ደግሞ 50 ኪሎ ሜትር መንገድ ተጠግኗል። በሌላ በኩል የመንገድ ከፍታ ሥራዎች ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገድ ከፍታ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ የመንገዶች ደረጃ የማሻሻል ሥራ አለ።
በመንገድ ግንባታ ስምንት ድልድዮች እንዲገነቡ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን፤ ስድስቱ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃሉ። ሁለት ድልድዮች ደግሞ በ2013 ዓ.ም ቀሪ ዘመን ላይ ግንባታቸው እንዲጀመር እቅድ ተይዞ የጨረታ ሂደቱ በመከናወን ላይ ይገኛል። ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የህብረተሰቡ የትራንስፖርት ችግር በመጠኑ ለማቃለል እድል ይገኛል።
አዲስ ዘመን: – የአፋር ክልል አዳጊ ክልል እንደመሆኑ ያለው የመንገድ ሽፋን እና የመንገድ መስመር ግንባታ ምጣኔው ዝቅተኛ መሆኑ ይታወቃል፤ ዝቅተኛውን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት እንዲጠናቀቁ ያደረጋችሁት ጥረት ምን ያክል ነው?
አቶ ጣሃ አህመድ: – በአፋር ክልል ያለውን የቆዳ ስፋት እና የመንገድ ሽፋን ምጣኔ በቁጥር አስደግፎ ለመናገር ጥናቶች ያስፈልጋሉ። እውነት ለመናገር ግን በአፋር ክልል ያለው የመንገድ ሽፋን እጅግ አነስተኛ መሆኑን መናገር ይቻላል።
በርካታ የገጠር ቀበሌዎች ላይ መመልከት ቢቻል ለመስክ ተሽከርካሪዎች እንኳን አስቸጋሪ የሆኑ እና የጠረጋ ሥራቸው ያልተጠናቀቁ የመንገድ መስመሮች ናቸው የሚበዙት።
ህብረተሰቡ ቢያንስ በሁለት እና ሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የመንገድ አማራጮችን እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን ላይ ግን በአፋር ክልል አካባቢዎች ሁለት እና ሶስት ቀን ተጉዘውም እንኳን የአስፓልት መንገድ አማራጭ የማያገኙ ዜጎች አሉ። ስለዚህ በክልል ደረጃም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያስፈልገውን የመንገድ ሽፋን መጠን በማሳደግ ረገድ ብዙ ተሰርቷል ማለት አይቻልም።
በክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች ላይ አሁንም ድረስ አባጣ ጎርባጣ ያለባቸው እና አቧራማ መንገዶች ናቸው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት። ሰዎች ወደጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤቶች ለመሄድ ቢያስቡ እንኳን የትራንስፖርት አማራጭ የማያገኙባቸው ቦታዎች በርካታ ናቸው።
በአጠቃላይ በክልሉ አራቱም አቅጣጫዎች የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያቀሉ እና የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን የሚረዱ በርካታ የአስፓልት መንገድ ግንባታ መስመሮች እንደሚያስፈልጉ ጥርጥር የለውም።
በክልሉ ያለውን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ የረጅም ጊዜ እና የአጭር ጊዜ እቅድ ተይዞ ከፌዴራል መንግሥት ግንባታዎች በተጨማሪ በክልሉ በጀት አቅም ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው።
በተለይ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የመንገድ ግንባታዎች በክልሉ መነቃቃት አሳይተዋል። ይህን አጠናክሮ በየዓመቱ የፋይናንስ አቅምን እያሳደጉ እና የህብረተሰቡን ተሳትፎ እያጎለበቱ መስራት ከተቻለ የክልሉን የመንገድ ሽፋን ማሳደግ አያቅትም።
እንደ አፋር ክልል መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ብቻ ሳይሆን እንደክልል ደግሞ የክልሉ መስተዳድር አቶ አወል አርባ የመንገድ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት እንዲጠናቀቁ ልዩ ክትትል እያደረጉ ይገኛል። እኔም እራሴ የክልል መስተዳድር ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ፕሮጀክቶች መሃንዲስ ነኝ በማለት ጭምር እየተናገሩ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል።
ከአመራሩ የሚደርስ ቁጥጥር እና ክትትል ግንባታዎችን በተሻለ ፍጥነት ለማከናወን እና የክልሉን መንገድ ሽፋን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና አለው። ቅዳሜና እሁድ አሊያም ከሥራ ሰዓት ውጪም ቢሆን የክልሉ አመራሮች የመንገድ ግንባታዎችን እየጎበኙ እና ያጋጠሙ ችግሮችን እየለዩ ቀና ክትትል እያደረጉ ይገኛል።
በዚህ ረገድ ክልል የተለያዩ አመራሮቹን በማስተባበር ለመንገድ ግንባታዎች አፈጻጸም መሻሻል እያደረገ ያለው ጥረት በቀጣይ የመንገድ ሽፋኑን ለማሳደግ ተጨማሪ ጉልበት ሆኗል።
አዲስ ዘመን: – የመንገድ ፕሮጀክቶችን በብዛት እና በፍጥነት ለማከናወን ከአቅም ጋር ተያይዞ ያለባችሁን ችግር ለመፍታት ምን አይነት መፍትሄዎችን አስቀምጣችኋል?
አቶ ጣሃ አህመድ: – እንደአፋር ክልል በእራሳችን አቅም የሚከናወኑ የመንገድ ግንባታዎችን በብዛት ለማከናወን ትልቅ ችግር ከሆኑት አንዱ የማሽነሪ እና የግንባታ መሳሪያዎች እጥረት ነው።
የማሽነሪ እጥረቱን ለመቀነስ ክልሉ በየጊዜው አቅሙን ለማጠናከር እና አዳዲስ የመንገድና ትራንስፖርት መሳሪያዎች ቁጥር በመጨመር ላይ ይገኛል። ይሁንና አሁንም ድረስ በክልል ደረጃ መኖር ያለበት የማሽነሪ ብዛት የለም።
አንዳንድ ማሽኖች ጥገና ያስፈልጋቸዋል፤ አሊያም ተበላሽተው ይቆማሉ። ማሽኖቹ እስኪጠገኑ ድረስ ደግሞ የመንገድ ግንባታዎች የሚዘገዩበት ሁኔታ ይፈጠራል። እንግዲህ ችግሩ ዞሮ ዞሮ የሚሄደው ወደገንዘብ አቅም ነው።
የገንዘብ አቅምህ ሲጠናከር የምትገዛቸው መሳሪያዎች በብዛትም ሆነ በጥራት ከፍ እያሉ ይሄዳሉ። በዚህ ረገድ ካለው የበጀት ሁኔታ አንጻር ባሉት በጣት በሚቆጠሩ ማሽነሪዎች ነው የመንገድ ጠረጋ እና ከፈታ ሥራ እየተከናወነ የሚገኘው።
ከካፒታል እጥረት ጋር ተያይዞ ከዓመት ወደዓመት የመሻሻል ሁኔታ ቢያሳይም አሁንም ግን ከክልል ስፋት አንጻር በጀቱ ውስንነት አለበት። ከበጀቱ ላይ ለሥራ ማስኬጃ እና ለሰራተኞች ደመወዝ ሲቀናነስ ፕሮጀክቶችን በብዛት ለመገንባት እክል ይሆናል።
ለመንገድ ግንባታዎች የሚያስፈልገው በጀት በጣም ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። ክልሉ ካለበት የበጀት ውስንነት አንጻር በተፈለገው ደረጃ ግንባታ ይከናወናል ማለት አይቻልም።
እንደ አፋር ክልል ለመንገድና ትራንስፖርት ሥራዎች ለበጀት ዓመቱ 260 ሚሊዮን ብር ሲመደብ ምናልባትም ገንዘቡ በሌሎች የፌዴራል መንገድ ግንባታዎች ላይ ለአንድ ፕሮጀክት ብቻ ከሚመደበው አንጻር ብናወዳድረው ሊያንስ ይችላል።
በፌዴራል ደረጃ 60 እና 70 ኪሎ ሜትሮች ለሚረዝም አንድ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ሊወጣበት ይችላል። በመሆኑም በአፋር ክልል ያለው አነስተኛ የመንገድና ትራንስፖርት የበጀት ሁኔታ በዘርፉ አነስተኛ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ እንዲሸጋገሩ ችግር ሆኗል።
ይሁንና በእራስ አቅም የአዳዲስ መንገድ ጠረጋ እና ከፈታ ሥራዎችን በደመወዝ ተቀጥረው በሚሰሩ ባለሙያዎች በማሰራት የበጀት ውስንነቱን ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው።
ከዚህ ባለፈ በክልል ደረጃ ትላልቅ የመንገድ ግንባታዎች በአፋር አካባቢዎች እንዲከናወኑ ጥያቄ በማቅረብ የህብረተሰቡን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በመሰረታዊነት ግን የክልሉን በጀት በማሳደግ በርካታ ግንባታዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የክልል ምክር ቤት የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ በተያዘላቸው በጀት እንዲጠናቀቁ የሚያደርጉት ድጋፍ እና የመንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ እንዲጠናከር እያገዙ መሆናቸው ለዘርፉ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይታመናል።
አዲስ ዘመን: – በክልሉ አቅምም ሆነ በፌዴራል ደረጃ አፋር ላይ የሚሰሩ የመንገድ ግንባታዎች በተለያየ ምክንያት የሚቋረጡበት አጋጣሚ አለ፤ በዚህ ረገድ የግንባታ መቋረጦችን ለመቀነስ ምን አይነት እርምጃዎችን እየወሰዳችሁ ነው?
አቶ ጣሃ አህመድ: – በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚጀመሩ የመንገድ ግንባታዎች በተለያየ ምክንያት ሲቋረጡ ይስተዋላል። በአንድ በኩል ግንባታዎችን የሚያከናውኑ ኮንትራክተሮችም ሆኑ አንዳንድ ባለሙያዎች ከአካባቢው በረሃማ የአየር ንብረት እና ለአካባቢው ማህበረሰብ ባህል አዲስ ከመሆናቸው አንጻር ፤በተለይ ከፍተኛ ሙቀት ባለባቸው ቦታዎች ላይ የአየር ንብረቱን እስኪላመዱት ድረስ የተወሰነ ይቸገራሉ ከጊዜያት በኋላ ግን ሲላመዱን ግንባታቸውን ቀጥለው ያጠናቅቃሉ።
በሌላ በኩል ግን የማህበረሰቡን አኗኗር እና ባህል ካለማወቅ የተነሳ ግርታ ሊፈጠርባቸው ይችላል፤ ከማህበረሰቡ ጋር ተግባብተው ያለመስራት ክፍተት ይስተዋላል። የአፋር ማህበረሰብ መረጃ የሚለዋወጠው ዳጉ በተሰኘው ባህላዊ የመረጃ ስርዓት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንድ ጥፋት ሲከሰት በፍጥነት ከጫፍ እስከጫፍ ያለው ማህበረሰብ ስለጉዳዩ ሊነጋገርበት ይችላል።
ለግንባታ ወደክልል የመጡ ኮንትራክተሮች እና አንዳንድ ባለሙያዎች የነዋሪውን ባህል እና ስርዓት ባከበረ መልኩ ሥራቸውን ማከናወንም እንዲችሉ በቢሮው ደረጃም ሆነ በክልል ደረጃ ምክክር ይደረጋል። በአብዛኛው ጊዜ በህብረተሰቡ እና በሰራተኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ተፈተው የተቋረጡ ሥራዎች እንዲቀጥሉ ይደረጋል።
በተመሳሳይ ቀደም ባለው ጊዜ ከጸጥታ ችግር ጋር የሚያጋጥሙ የመንገድ ግንባታዎች ይኖራሉ። ጉዳዮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ወደመፍትሄው በመምጣት ሰራተኞች ደህንነታቸው መጠበቁ ከተረጋገጠ በኋላ ግንባታዎች እንዲካሄዱ ይደረጋል። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ከጸጥታ ጋር ተያይዞ ክልሉ የተሻለ ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ የመንገድ ግንባታዎች የሚቋረጡበት ምክንያት ቀንሷል።
በሌላ በኩል ልክ እንደማንኛውም የሀገሪቷ ክፍል ሁሉ በአፋር ክልል የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የሚያጋጥመው ችግር የወሰን ማስከበር ችግር ነው። አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ የወሰን ማስከበር የቦታ ክፍያዎችን ከፍ አድርጎ የመጠየቅ ሁኔታ አለ። አንዳንድ ወቅት ደግሞ መሬታቸውን ለግንባታዎች ያለመፍቀድ ችግር ይስተዋላል።
የመንገድ ግንባታዎች ላይ ያለው የወሰን ማስከበር እና ከዚህ ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ ዘንድ በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ያለው አነስተኛ ግንዛቤ ፕሮጀክቶችን በማጓተት ረገድ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል።
ለዚህ መፍትሄ ለማበጀት ከአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጀምሮ እስከታችኛው አመራር ድረስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳይጓተቱ በመጎብኘት እና የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን በመከታተል የተሻለ አፈጻጸም እንዲገኝ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ለወሰን ማስከበር ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ ከአፋር ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር እና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ጋር የተለያዩ ውይይቶች እና የጋራ ሥራዎች ይከናወናሉ።
በርካታ ጊዜያትም ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት በማካሄድ ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ደግሞ በህግ አግባብ እየፈታን የተቋረጡ ግንባታዎች እንዲቀጥሉ አድርገናል። በዋነኛነት በግንባታዎቹ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንደሚሆን ግንዛቤ በማስያዝ እና ስለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሄ በማበጀት ባለፉት ዓመታት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት እንዲጠናቀቁ ጥረት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን: – ከመንገድ ፕሮጀክቶች ጋር ያለው የገንዘብ አጠቃቀም ምን ይመስላል፤ በተለይ በታዳጊ ክልሎች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ይደርሳል የሚል ቅሬታ ይሰማልና፣ በዚህ ረገድ ክልሉ ምን እየሰራ ነው?
አቶ ጣሃ አህመድ: – የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የሚያሰራቸው መንገዶች ላይ ከፋይናንስ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ላይ አንገባም። ፕሮጀክቶቹን ጨረታ የሚያወጣውም ሆነ ክፍያ የሚፈጽመው የበላይ አካል ነው።
የእኛ ኃላፊነት ግንባታዎቹ እንዳይቆሙ እና በወቅቱ እንዲገነቡ ከህብረተሰቡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ መስራት ላይ ነው የምናተኩረው። በእራሳችን ገንዘብ የሚገነቡ መንገዶችም ጨረታ ወጥቶላቸው ነው በተገቢው የፋይናንስ አሰራር የሚከናወኑት።
የታዳጊ ክልሎች ቢሮ ላይ ገንዘብ ያባክናሉ፣ ያጠፋሉ፣ የሚባለው ሃሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ጊዜ ታርጋ ከተለጠፈብህ ስለማይነሳ ነው እንጂ በአፋር ከበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የከፋ ችግር የለም።
ቀደም ባሉ ጊዜያት የተባለ እና የበጀት አጠቃቀም ጉድለትን ያገናዘበ አስተያየት ተሰጥቶ ሊሆን ይችላል፤ መጀመሪያ ላይ ህብረተሰቡ ካለው ግንዛቤ አንጻር ችግር ተፈጥሮ ይሆናል።
አሁን ላይ ግን ከየትኛውም ተቋም ጋር ቢነጻጸር በተሻለ ሁኔታ ክልሉ የበጀት አጠቃቀሙን በተገቢው መንገድ እያስኬደው ይገኛል። የመንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮም በተገቢው የፋይናንስ አሰራር መሰረት መከናወን ያለባቸውን ሥራዎች እያከናወነ ነው የሚገኘው።
አዲስ ዘመን: – የመንገድ ፕሮጀክቶች የሥራ እድል ፈጠራው ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም በአፋር ክልል ግን የመንገድ ግንባታዎች የሥራ እድል ፈጠራ ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው በሚል ይተቻልና፤ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ጣሃ አህመድ: – በአፋር ክልል ደረጃ የሥራ እድል ፈጠራው ቁጥር ከፌዴራል አሊያም ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነጻፀር ሊያንስ የሚችለው በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹ የበጀት ሁኔታ ውስንነት የተነሳ ነው። በአፋር ክልል ያለው አነስተኛ የመንገድና ትራንስፖርት የበጀት ሁኔታ በዘርፉ ያለውን የሥራ እድል ቁጥር ከሚፈለገው በታች ሊያደርገው ችሏል።
ይህም ሆኖ ግን ባለው የፋይናንስ አቅም በመጠቀም በስድስት ፕሮጀክቶች ላይ ወጣቶች የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው ጥረት ተደርጓል። በዘንድሮው ዓመት የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ በስድስት ወር በመቶዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ጊዜያዊ የሥራ እድል ተፈጥሯል።
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የሚፈጠረው የሥራ እድል በአብዛኛው ጊዜያዊ የሥራ እድል ነው። የጉልበት ሥራ የሚያከናውንም ሆነ በኢንጂነሪንግ ሙያ የተሰማሩ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ እንደየ ፕሮጀክቶቹ የጊዜ ቆይታ ለወጣቶች የሥራ እድል ይፈጠራል።
በሁለተኛው አጋማሽ በጀት ዓመት ደግሞ የመንገድ ግንባታዎቹ ሂደት ሲፋጠን ደግሞ በተጨማሪነት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ እድል እንደሚፈጠር ይጠበቃል።
የአፋር ክልል እንደሚታወቀው በአብዛኛው የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ያለበት አካባቢ ነው። አርብቶ አደሩ ከከብት ማርባት ሥራው በተጨማሪ በመንገድ ፕሮጀክቶች የሥራ እድል ላይ እና በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርቶ ገቢ እንዲያገኝ ለማስቻል ከከተሞች አካባቢ ካለው ሥራ የበለጠ ጥረት ይጠይቃል።
ወጣቶችን አሳምኖ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሰማሩ እንዲሁም ክህሎቶችን እንዲቀስሙ ለማድረግ በየጊዜው የማንቂያ መርሐ ግብሮች በቢሮው አማካኝነት እየተካሄዱ ይገኛል። ከከተሞች መስፋፋት እና ከጊዜ ወደጊዜ የመንገድ ግንባታዎች መበራከት ጋር ተያይዞ በዘርፉ የሚኖረው የሥራ እድል ፈጠራ እየተሻሻለ እንደሚመጣ ይታመናል።
አዲስ ዘመን: – የመንገድ ግንባታ በዘርፉ የሰለጠኑ እና ልምድ ያላቸው ብቁ ባለሙያዎችን ይጠይቃል፤ ከዚህ አንጻር ቢሮው ያለበትን የብቁ ባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ ምን ታስቧል?
አቶ ጣሃ አህመድ: – ኢንጂነሩ፣ የሳይት መሃንዲሱ፣ የሎቤድ እና ግሬደር አሽከርካሪውም ሆነ የመንገድ ንጣፍ ሰራተኛው በአጠቃላይ በየፕሮጀክቶቹ ላይ የሚሳተፉ ሰራተኞች ክህሎት እና ልምድ ያስፈልጋቸዋል። አንድ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተመረቀ ወጣት ከሌሎች ልምድ ካላቸው ሰዎች ጋር ካልሆነ በቀር በቀጥታ ፕሮጀክቶችን እንዲመራ አይደረግም። ከዚህ አንጻር በዘርፉ በርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው ሰራተኞች ያስፈልጋሉ።
በዚህ ረገድ በአፋር ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ውስጥ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ቢኖሩም አነስተኛ ዓመት የሰሩ እና ተጨማሪ ክህሎት የሚያስፈልጋቸው በርካታ ሰራተኞች አሉ። የሰራተኞችን ክህሎት እና እውቀት ለማሳደግ በየጊዜው የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ ተግባራዊ ልምድ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል።
ከዚህ ባለፈ በአጫጭር ስልጠናዎች እና የመስክ ላይ ልምምዶች ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ጥረቶች ይከናወናሉ። እንደክልልም በዘርፉ ያለውን አነስተኛ የመንገድ ግንባታ ባለሙያዎች ቁጥር ለማሳደግ በመላ ሀገሪቷ የሚገኙ ባለሙያዎች አወዳድሮ የመቅጠር እና የክልሉን አቅም የማጠናከር ሥራ በየጊዜው ሥራዎች እየተሰሩ ነው።
በረጅም ጊዜ እቅድ ግን ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ትምህርት እና ስልጠና ላይ ትኩረት ተደርጓል። በአጫጭር ስልጠናዎች እና በተግባር ላይ ልምምዶች የክልሉን የመንገድና ትራንስፖርት አቅም ለማሳደግ ነው የታሰበው።
ከሌሎች ክልሎች እና ከፌዴራል ተቋማት በሚገኝ የልምድ ልውውጥ ባለሙያዎች ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ እየተደረገ ይገኛል። ከፌዴራል ተቋማት ጋር በመተባበር ባለሙያዎች የተሻለ ክህሎት የሚያገኙባቸው የትምህርት እድሎች ከጊዜ ወደጊዜ ማበራከት እንደሚያስፈልግ ይታመናል።
አዲስ ዘመን: – ወደ ኢትዮጵያ ወጪ እና ገቢ ምርት በዋነኛነት የሚመላለስበት የኢትዮ- ጅቡቲ የመንገድ ኮሪደር የአፋር ክልልን አቋርጦ የሚያልፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ከባድ ተሽከርካሪዎች መንገዱን ይጠቀሙበታል። መንገዱ ሲበላሽ ግን የፌዴራል መንግሥት ሥራ ነው በሚል ጥገና ያለማድረግ ችግር እንዳለ ይነሳል፤ በዚህ ረገድ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ጣሃ አህመድ: – ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ጅቡቲ የሚያቀናውን የአስፓልት መንገድ የሚያስተዳድረው የፌዴራል መንግሥት መሆኑ ይታወቃል። በአፋር ክልል ከጅቡቲ የሚመጡ እና ወደ ወደብ የሚመላለሱ በርካታ እቃ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች በአስፓልት መንገዱ ላይ ቀንና ሌሊት ሲመላለሱ ነው የሚውሉት።
የሀገሪቷ ወሳኝ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ መንገድ በመሆኑ ምክንያት በርካታ ጫና ያለበት መንገድ ነው። በርካታ ተሽከርካሪዎችን ስለሚያስተናግድ የኢትዮ ጅቡቲ የመንገድ ኮሪደር በተለይም በአፋር ክልል ያለው ዋናው የመንገድ መስመር በተደጋጋሚ ጊዜ አደጋ ይደርስበታል።
በተፈጥሮ አደጋም ይሁን በሰው ሰራሽ ምክንያት የአስፓልት መንገዱ ጉዳት ስለሚያጋጥመው የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥገና እየተደረገለት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
የመንገድ መስመሩን በዋነኛነት የሚጠግነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ነው። የአፋር መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ግን መንገዱን የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን ነው የሚጠግነው ብሎ አይተወውም።
የአስፓልት መንገዱ ለሀገሪቷ ልማት ካለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንጻር ጉዳት ሲደርስበት በአፋጣኝ ሪፖርት በማድረግ ባለስልጣኑ ጥገና እንዲያከናውንበት ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል።
ጥገናው በሚካሄድበት ጊዜም አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ለሥራው መቀላጠፍ ቢሮው ሰራተኞቹን ያሰማራል። ከዚህ ባለፈ ህብረተሰቡን እና የጥገና ባለሙያዎችን በማስተባበር የተበላሸው መንገድ ክፍል በአስቸኳይ ወደሥራ የሚገባበት ሁኔታ እንዲመቻች ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።
በዚህ ረገድ ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ የመንገድ መስመሩ በሚጠገንበት ወቅት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ተሰርቷል። በመሆኑም ስለመንገዱ ደህንነት እና የጥገና ስራ ቸል የምንልበት ሁኔታ የለም።
አዲስ ዘመን:- የአፋር ክልል ማህበረሰብን የመንገድ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮው መጠናከር ይኖርበታል። ተቋሙን ለማጠናከር ምን አይነት ሥራዎች ያስፈልጋሉ?
አቶ ጣሃ አህመድ: – የክልል መንገድ እና ትራንስፖርት ዘርፍ ወጥ የሆነ አደረጃጀት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የመንገድ እና ትራንስፖርት ዘርፍ አሰራር እና አደረጃጀት በሁሉም ክልሎች ላይ መውረድ አለበት። ወጥ አደረጃጀት እና አሰራር በመከተል ከፌዴራል መንግሥት ቢሮዎች ጋር የበለጠ ቅንጅት መፍጠር ይቻላል። በዚህ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ዳር ማድረስ የሚጠይቅ ነው።
አደረጃጀቱ ወጥ ሲሆን ቢሮው በስልጠና፣ በአቅም ግንባታ እና የማሽነሪ እንዲሁም በበጀት አቅም እያሳደጉ መቀጠል ያስፈልጋል። የአፋር ክልል በርካታ የመንገድ መስመር እንኳን ያልወጣላቸው ቦታዎች ያሉበት በመሆኑ በቀጣዮቹ ዓመታት ሰፊ የግንባታ ሥራ የሚከናወንበት መሆኑ ጥርጥር የለውም። በዚህ ረገድ የቢሮውን አቅም በማጠናከር ከፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በክልሉ አቅም የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ማበራከት ይቻላል።
በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኘው ህዝብ 90 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ አርብቶ አደር ሲሆን፤ ግመሎችን፣ የቀንድ ከብቶችን፣ ፍየልና በግ እንዲሁም አህያዎችን ያረባል፡፡ በክልሉ በቆሎ፣ ባቄላ፣ ማሽላ፣ ፓፓዬ፣ ሙዝ እና ብርቱካን በስፋት ይመረታሉ፡፡ በጥጥ ምርትም ክልሉ ይታወቃል፡፡
የንግድ እንቅስቃሴ በተለይም የጨው ማውጣት ሥራ በክልሉ በስፋት ይከናወናል፡፡ ለክልሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ማደግ የመንገድ ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ የክልሉን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በአቅም ማጠናከር ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው። ቢሮውን በገንዘብም ሆነ በሰው ሃይል በማጠናከር ግንባታዎችን ማብዛት ይቻላል። በዚህም ህብረተሰቡ ወደሚፈልገው አካባቢ መንቀሳቀስ የሚያስችለውን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ጣሃ አህመድ:- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013