ኢያሱ መሰለ
የሰው ልጆች ልምድ ባህልና ተሞክሮ ዛሬ ዓለም ለደረሰበት የእድገት ደረጃ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይታመናል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች፣ የምርምር ውጤቶች፣ ፍልስፍናዎች፤ አባባሎች፣ አዳዲስ እይታዎችና አሰራሮች፣ ከነባራዊው ዓለም ተቀድተው እየተተረጎሙ፣ እያታረሙና እየተገሩ፣ እያደጉና እየበለጸጉ መልሰው የዓለም ህዝብን ያገለግላሉ።
ዛሬ ሀገራት የሚከተሉት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በአንድ ወቅት በአንድ አካባቢ ያሉ ህዝቦች ይጠቀሙበት የነበረ መልካም ልምድና ተሞክሮ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በ ዊክ ፒዲያ ዘ ፍሪ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው፤ የምርጫ ፍልስፍና እና አስተሳሰብ ከጥንታዊቷ ግሪክ እና ሮም አካባቢዎች ተነስቶ ዛሬ ዓለምን በማዳረስ የስልጣን ወንበር ለመያዝ የሚያስችል ብቸኛው መንገድ ለመሆን በቅቷል። ታዲያ ይህ መልካም ልምድ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው በርካታ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት መሆኑም ተጠቅሷል።
ይህን ተከትሎም በ17ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓና ሰሜን አሜሪካን ሀገራት ዘመናዊ የምርጫ ስርዓትን መተግበር እንደጀመሩ ይነገራል። እንዲያውም አሜሪካን ያገኘችውን ልምድ ቀምራ ዘመናዊ የምርጫ ስርዓትን በማስፈን የመጀመሪያ ፕሬዘዳንቷን ‹‹ጆርጅ ዋሺንግተንን›› እ.ኤ.አ በ1789 ለመምረጥ መቻሏን የታሪክ ድርሳናት ያስታውሳሉ።
እድሉን አግኝተው በዓለም መድረክ ቢቀርቡ ማህበራዊ ትሩፋት የሚኖራቸው በርካታ የሀገራችን እሴቶች አሉ። ይሁን እንጂ ለዘመናት በአንድ ቦታ ተቸንክረው የቀሩ በመመሆናቸው እንኳንስ የዓለም ህዝብና ሀገሬውም በወጉ ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። ማህበራዊ እሴቶቻችን የዘመናዊ አስተሳሰብና አሰራር ሽታ እንዲኖራቸው ቢደረጉ በርካታ ችግሮችን ልንፈታባቸው የሚያስችሉን ናቸው።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት አቶ ብሩህ ዓለም የኢትዮጵያ ፍልስፍና በሚለው መጽሃፋቸው ዶክተር ዳኛቸው አሰፋን ጠቅሰው ተከታዩን አስፍረዋል። ‹‹ባህል ስንል ዝም ብሎ የተቀመጠ ነገር ሳይሆን ሁልጊዜ የምንፈትሸው የምንመረምረው፣ የምናነጋግረው፣ ትርጉም የምንፈልግለት መሆን አለበት፤ ይሄም መደረግ ያለበት ባህል ወላድ (productive) እንዲሆን ነው፤ ቆሞ ቀር እንዳይሆንና እንደኩሬ ውሃ አንድ ቦታ ረግቶ የከረፋ ሽታ እንዳያመጣ ነው። ባህል ህያው የሚሆነው ወላድ ሲሆን ነው፤ ወላድነቱም የሚገለጸው በየመስኩ ባህሉን የሚተነፍሱ ሰዎችን ሲያፈልቅ ነው። ባህል ህያው እንዲሆን ግን ኩሬውን የሚነቀንቁ ሰዎች ያስፈልጋሉ›› ይላሉ።
የነገሬ ማጠንጠኛ ሳይንስ ሳይሆን ፍልስፍና ነው፤ ይሁንና ጉዳዬን ለማስረዳት እንዲያስችለኝ ጥቂት ማሳያዎችን ከሳይንስ ልኮርጅ። ሳይንስ አሞራን መነሻ አድርጎ አውሮፕላንን ሰርቷል። “ተሳቢ እንስሳትን መነሻ አድርጎ ባቡርን፣ ሰውን መነሻ አድርጎ ሮቦትን ሰርቷል። ሳይንስ ሌሎችንም በርካታ ፍጡራን መነሻ እያደረገ ጠቃሚ ነገሮችን ለዓለም አበርክቷል።
ፍልስፍናም በነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ተመስርተን እውነትን የምንፈልግበት ጥበብ ነው። አንድ ቦታ አይቆምም፤ አንድ ድምዳሜ ላይ ብቻ አይወሰንም። ባህላችንና እሴቶቻችን የየዘመኑ የፍልስፍና ውጤቶች ናቸው።
ማህበራዊ ቅርስ መሆናቸው ባያጠያይቀንም፤ እንደ አክሱም ላሊበላና ጥያ ትክል ድንጋይ አሻራቸው እንዳይበላሽ በሚል ማሻሻያ ሳናደርግባቸው የምናስቀምጣቸው መሆን እንደሌለባቸው ምሁራን ይናገራሉ።
ሁልጊዜ በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ጥቅም ላይ የምናውላቸው እሴቶቻችንን ከህብረተሰቡ ወቅታዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር እንዲጣጣሙ እያደረግን ወደፊት ልናስቀጥላቸው ይገባል። ያን ጊዜ እሴቶቻችን ችግር ፈቺ የመሆን አቅማቸው ይጨምራል። ተቀባይነታቸውም ያድጋል።
ኢትዮጵያ በማህበራዊ እሴቶች የበለጸገች ሀገር ብትሆንም ያሏትን ሀብቶች ከዘመን ወደ ዘመን እያወራረሱ ከመጠቀም አንጻር እዚህ ግባ የሚባል ስራ አልሰራችም። አንዳንዶች እንደውም ባህላዊ እሳቤዎችንና ድርጊቶችን የኋላ ቀርነት ወይም ያለመሰልጠን መገለጫ አድርገው ሲመለከቱ ይስተዋላል።
ብሩህ ዓለም ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› በሚለው መጽሃፋቸው ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስን ጠቅሰው የሚከተለውን አስፍረዋል። ‹‹አንድ ማህበረሰብ ከራሱ ህሊና የራሱን አዲስ ዕውቀት በማፍለቅ ፈንታ የቀድሞ የእውቀት ጀግኖቹ ያፈለቁትን ስራ ብቻ እየጠቀሰ እያብራራና እየተነተነ የሚኖር ከሆነ ስልጣኔው የውድቀት ዝንባሌ መሸከሙን ያሳያል።
መንፈስ ከራሱ ምንጭነት በራቀ መጠንና ከውጭ በተመራ መጠን ጉልበቱ እየደከመ ይሄዳል። ህይወቱም በደካማ መሰረት ላይ ይቆማል›› ይላሉ። እያንዳንዱ ሰው ሀሳብን ከሰዎች ኮርጆ ከማስተጋባት ይልቅ ነገሮችን በራሱ መንገድ በመመርምር የጎደለውን የሚያሟላ መሆን ይኖርበታል።
ኢትዮጵያውያን ከአባቶቻችን የወረስናቸውን ማህበራዊ እሴቶች እያዳበርን ብንጠቀምባቸው ወደ ዘመናዊነትና ስልጣኔ የምናደርገውን ጉዞ ያፋጥኑልናል እንጂ ወደኋላ አይጎትቱንም።
እንደውም እንደየወቅቱ ማዘመን የምንችላቸውን ሀገር በቀል እሴቶች እንደዋዛ እየተውናቸው ባዕድ አስተሳሰቦችንና አሰራሮችን መከተላችን ለተለያዩ ችግሮች ዳርጎናል። በተለያዩ ጊዜያት ወደ ስልጣን የሚመጡ መሪዎቻችን የተለያዩ የፖለቲካ ፍልስፍናዎችን ከውጭ እያመጡ ለመተግበር የሚገደዱት ጠቃሚ እሴቶቻችንን በዘመናዊ አሰራር ስላልቃኘናቸውና ስላላሳደግናቸው ነው።
ለምሳሌ ለዲሞክራሲዊ የስልጣን ሽግግር ምሳሌ መሆን የሚችሉና ያልተጠቀምንባቸው እንደውም በዩኔስኮ ደረጃ እውቅና አግኝተው እኛ ግን ለችግሮቻችን መፍቻ ያላዋልናቸው እሴቶች አሉን። ከነዚህም አንዱ የገዳ ሥርዓት ነው። የገዳ ስርአት ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ የጾታ እኩልነት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ወዘተ የሚታይበት እሴታችን ነው።
ይህ ጠቃሚ እሴት በምርምርና ጥናት ዳብሮ፤ በተቋም ደረጃ ተመርቶ ‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ›› እንዲሉ ለሀገራችን ጥቅም መስጠት ቢችል ኖሮ እኛን የማይመስሉ ባእድ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ከውጭ እያመጣን ለተለያዩ ውጥንቅጦች ባልተዳረግን ነበር።
በደርግ ስርዓተ መንግስት የማርክሲስት ሌኒኒስት የፖለቲካ ፍልስፍናን ማጥናት የዚያ ዘመን የእውቀት ጥግ ተደርጎ ይታይ ነበር። ኢትዮጵያ የሶሻሊስት ስርዓት ለማስፈን ጉድ ጉድ ባለችባቸው በነዚያ ዓመታት ምን ያህል ዜጎቻችንን እንዳጣን ቤቱ ይቁጠረው።
በየጊዜው የተለያዩ ፍልስፍናዎች በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ እየተፈራረቁ ቦታ ቢይዙም ይህ ነው የሚባል ውጤት አላየንባቸውም። እንዲያውም የጭቆና መሳሪያ በመሆን ብዙዎችን ለከፋ እንግልትና መከራ ሲዳርጓቸው ተመልክተናል።
ለአብነት ያህል ከቅርብ ዓመታት በፊት ሀገሪቱ ስትመራበት የነበረውን የአብዮታዊ ዲሞክራሲዊ አስተሳሰብ ከሀገር በቀሉ የገዳ ስርዓት ጋር ብናነጻጽረው እንኳ በርካታ ጉዳዮች ሊታዩን ይችላሉ።
‹‹የገዳ ስርዓት እና አብዮታዊ ዲሞክራሲን›› ለማነጻጸር ስነሳ ሁለቱን ምን ያገናኛቸዋል በሚል ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ በተሰጣችሁ ሀሳብ በሃሳብ የመጣል መብት ተጠቅማችሁ ጉዳዬን የምታጣጥሉ አትጠፉም፤ እኔም ምስጋና ሀሳብን የማፍለቅ ነጻነት ለሰጠኝ ፍልስፍና ብዬ እቀጥላለሁ።
ለማንኛውም ዋለልኝ እምሩ ‹‹በፍልስፍና መደመም›› በሚለው መጽሐፉ ‹‹ፍልስፍና የሰው ልጅ የአካባቢውንና የራሱን ማንነት የሚረዳበት መንገድ ነው። ግምታዊ፣ ሳይንሳዊ ወይም ሃይማኖታዊ ከሆነ የግንዛቤ መንገድ ነገሮችን በተለየ መንገድ ለመረዳትና ለመግለጽ የሚጠቅም የእውቀት አይነት ነው›› ማለቱን አስታውሻችሁ ወደ ጉዳዬ እገባለሁ።
‹‹የገዳ ስርዓት›› የኦሮሞ ህዝብ ሁለንተናዊ ችግሮቹን ዲሞክራሲዊ በሆነ መንገድ የሚፈታበት የአስተዳደር ስርዓት ነው። ‹‹አባ ገዳ›› /የገዳ አባት/ የአስተዳደር ስርዓቱ ያስቀመጠውን መስፈርት አሟልቶ ህዝቡን ለመምራት ሃላፊነት የሚሰጠው ተሿሚ ነው። በገዳ ስርዓት ውስጥ የኦሮሞን ህዝብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች እየተመለከተ መፍትሄ የሚሰጥ የአስተዳደር ስርዓት ተዘርግቷል።
የልጆች፣ የእናቶች /የሴቶች/፣ የአዛውንቶች፣ የባሎች፣ የሚስቶች መብትና ግዴታ ተደንግጓል። የስራ ድርሻቸውም ተለይቷል። የበዳይና የተበዳይ ጉዳይም አደባባይ ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል። ያጠፋ እንደጥፋቱ መጠን ይቀጣል፣ የተበደለም ይካሳል። ህዝብን እና ድንበርን ከጠላት ለመጠበቅ እንዲቻል የጦር መሪ /አባ ዱላ/ ተሹሟል።
በአጠቃላይ ገዳ በአንድ ሀገር የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በሙሉ አቅፎ የያዘ የአስተዳደር መዋቅር ነው። ‹‹የገዳ ስርዓት የስልጣን ክፍፍል ብቻ ሳይሆን ገደብንም ያስቀመጠ ነው። በገዳ ስርዓት አንድ አባ ገዳ / ስልጣን የተሰጠው አካል/ በስልጣን ላይ የሚቆይበት ጊዜ ለስምንት ዓመት ብቻ ነው። ከስምንት ዓመት በኋላ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ያደርጋል።
በመሆኑም የዲሞክራሲ ስርዓትን እንከተላለን ከሚሉ ሀገራት አንጻር ሲታያይ የተሻለ እንጂ ያነሰ አይሆንም። የዲሞክራሲ ስርዓትን አስፍናለች የምትባለው አሜሪካን የዲሞክራሲ ስርዓቷ ቢፈተሽ የገዳን ያህል ላይሆን ይችላል። ዘንድሮ በጆ ቫይደን እና በዶናልድ ትራምፕ መካከል ያየነው የምርጫ ውዝግብ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
ዛሬ በዓለማችን በተለይም በአፍሪካ ለሚፈጠሩ ግጭቶች ዋናው ምክንያት አንድ ጊዜ ወንበር ከያዙ አንለቅም የሚሉ መሪዎች መብዛታቸው ነው። ወንበራቸውን ላለመልቀቅ ሲሉ ምርጫ የሚያጭበረብሩ ወይም በድንገት ተነስተው በህግ መንግስታቸው ላይ የተቀመጠውን የስልጣን ዘመን የሚያሻሽሉ በርካቶች ናቸው።
ዛሬ ዓለም ሰልጥና እያለች እንኳን በህዝቦችና በመሪዎች መካከል አለመተማመን ይታያል። በገዳ ስርዓት ግን እንዲህ አይነቱ አለመተማመን እልባት የተሰጠው ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ገንብተናል ከሚሉት ሀገራት በፊት ነው። በገዳ ስርዓት በህዝቦችና በመሪዎች መካከል መተማመን አለ፤ ህዝብ በመሪ የሚመራው፣ መሪው በህዝቡ ስለሚመረጥና ተቀባይነት ስላለው ነው። መሪው ህዝቡን ይሰማል፤ ህዝቡም መሪውን ይከተላል።
አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከመነሻው ስልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ ይገኛል የሚለውን የማኦ ፍልስፍና የሚከተል በመሆኑ ዲሞክራሲው ላይ ሳይሆን አብዮቱ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የነበረ ነው። አብዮት ለውጥ ለማምጣት መታገል ነው።
እንደ እኛ ሀገር አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሲያገለግል የነበረው ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን ግላዊ ጥቅምን ለማካበት ነው። ኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን መርሆው አድርጎ ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ የኢኮኖሚም ይሁን የፖለቲካ እኩልነት አልታየም።
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዘመን የተካሄደው ምርጫና የስልጣን ሽግግር በዘመናዊ እውቀት ካልዳበረውና እና የተጻፈ ህግ ከሌለው የገዳ ስርዓት በአፈጻጸሙ እጅግ ኋላ ቀር ነው። ኢህአዴግ እግሩ ስር ያለውን የገዳ ስርዓት አበልጽጎ ታላቅ ሀገርና ህዝብ መፍጠር ሲገባው ‹‹በእጅ ይዞ ፍለጋ›› እንዲሉ ይህን የመሰለ እሴቱን ትቶ መሰሪ ተግባሩን ለማስፈጸም የሚጠቅመውን ይቀላውጣል።
ኢህአዴግ ያካሄዳቸውን አምስት ምርጫዎች አሸንፌያለሁ ብሎ ምክር ቤቶችን የተቆጣጠረው በይስሙላህ ምርጫ ካለሆነም በጉልበት መሆኑ ሲታይ፤ በአብዮታዊ ዲሞክራሲና በገዳ ስርዓት መካከል ያለውን ርቀት መገመት አያዳግትም። የሚገርመው ግን የገዳ ስርዓት ጥንታዊ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ደግሞ ዘመናዊ ሆነው መፈረጃቸው ነው።
‹‹ሳትቸገር ተበደረች፣ ሳትከፍል ሞተች›› እንዲሉ ኢትዮጵያን የሚጠቅመውን ሀገር በቀል እሴት ትተን ሀገርን የሚቆረቁዘውንና የሚቀብረውን የፖለቲካ ፍልስፍና መከተላችን ዛሬ ለገጠመን ሀገራዊ ችግር አንድ ምክንያት ሆኗል። አባቶቻችን ያቆዩልንን ጠቀሚ እሴቶች እያዘመንን እድገታችንን ለማፋጠን እንትጋ። የሰው ወርቅ አያደምቅ ተብሏልና።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013