ወንድወሰን መኮንን
አርክቴክት ዳዊት በንቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕንጻ ኮሌጅ በአርክቴክቸር አግኝተዋል። ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተምረው የወሰዱት ህንድ ከሚገኘው ኢንዲያን ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ሩርኪ ዩኒቨርሲቲ ነው። ላለፉት 25 ዓመታት በአዳማ ዩኒቨርሲቲ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርክቴክቸር መምህር በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ።
በሀገራችንና በዓለም ላይ ያለውን ኪነ ሕንጻ በተለይ ዘመናዊውንና አሁናዊውን በተመለከተ የተለየ ፍላጎት አላቸው። በዚህ ላይ የምርምር ሥራዎችን ይሰራሉ። በዚሁ መስክ የፒኤችዲ ተማሪ ናቸው። በኢትዮጵያ አርክቴክቸርና በተለይም በከተማ ንድፍ ወይም አርበን ዲዛይን ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል። ይከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡- ቀድሞ ከነበረው የዘመናዊው ጊዜ አንጻር ስናየው በኢትዮጵያ ኪነህንጻ ውስጥ መሰረታዊ ለውጦች አሉ ማለት ይቻላል ?
አርክቴክት ዳዊት፡- ኪነ ህንጻን ለመስራት የኢኮኖሚ መነቃቃት ይጠይቃል። ከኢኮኖሚ መነቃቃት ተጀምሮ ብዙ ተስፋ ሰጪም ባይሆን ደረጃቸውን የጠበቁ አንዳንድ ሕንጻዎች እየተሰሩ ለመኖሪያ በቅተዋል። ይሄም ብቻ ሳይሆን ኪነ ሕንጻዊ ፋይዳ ያላቸው ሕንጻዎች ጥቂት አለፍ አለፍ ብሎ ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን እያየን ነው። የጎላ ባይሆንም ይህን እንደ መልካም ጅምር ልንወስደው እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ምን አይነት ለውጦች ናቸው ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ናቸው ያሉት?
አርክቴክት ዳዊት፡- ኪነ ሕንጻ ማለት ስታየው ከሕንጻና ከመኖሪያ በላይ መሆን አለበት። የምትበላውን ምግብ ጣፍጦህ መብላት አለብህ። ለመብላት ብቻ ከሆነ ዱቄቱን፤ እህል ውሀ የማይለውን ጥሬውንም ሳትጠብሰው መብላት ትችላለህ። እየበላህ ሕይወትህ ይቆያል። እውነተኛ ምግብ በላሁ ለማለት መቀመም አለብህ።
ማጣፈጥ አለብህ ። እንዳይሰለች መሆን አለበት። ኪነ ሕንጻም እንደዚሁ ነው። የምትለብሰውን ልብስ ከለሩን ትመርጣለህ። ማማር አለበት። ዝም ብሎ ለመልበስ ለመልበስ ብቻ አትለብስም። ጆንያ ሰፍተህ አትለብስም። ብትሰፋና ብትለብሰው ከብርድ ይከላከልልሀል። እርቃንህን ይሸፍናል። ሕንጻዎቻችንም እርቃናችንን ይሸፍናሉ። ማደሪያ ይሆኑናል እንጂ ኪነ ጥበባዊ ኪነሕንጻዊ መሆን አይችሉም። መጠበብ የረቀቀ የኪነ ሕንጻ እውቀት ስለሚፈልግ።
አዲስ ዘመን፡- ወደዚያ የሚያድገው እንዴት ነው ?
አርክቴክት ዳዊት፡– ኪነሕንጻው ወደላቀ ደረጃ የሚያድገው በባለሙያው ብቃት ችሎታና እውቀት ነው። አርቲስት ወይንም ዘፋኝ ወይንም ሙዚቀኛን ብትመለከት ለብ ለብ ለዛሬ የሚያደርስ አለ።
ስነጥበባዊ ፋይዳ ያላቸው ዘመን ተሻጋሪ ሆነው የሚሄዱ ሙዚቃዎች ደግሞ አሉ። ምርጥ የሙዚቃ ሥራዎች በየትኛውም ዘመን ብትሰማቸው እንደ አዲስ የሚኮረኩሩህ የማትሰለቻቸው የማይጠገቡ በትውስታ ጭነው የሚያመላልሱህ ናቸው። ለምሳሌ ኪነ ሕንጻን ብትወስድ አሁን ተጠቦ የሚሰራበት ሰው የለም። ለምን አይሰራውም ብለህ ብትጠይቅ መልሱ አናውቀውም ነው። የባለሙያውን ክፍያም ሊሆን ይችላል። ይሄን በተመለከተ በተለየ ሁኔታ ኢትዮጵያ ብቸኛ ሀገር ነች። እጅግ የወረደ ክፍያ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ?
አርክቴክት ዳዊት፡– የኪነ ሕንጻ ሙያ ዋጋ ከግንባታ ዋጋው ጋር የተያያዘ አይደለም። ደካማ ብቻ ሳይሆን የሞተ ነው። ይሄንን ለአንድ ኬንያዊ ብትነግረው እውነት የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች እየኖራችሁ ነወይ ሊልህ ይችላል። ስለዚህ እኛ ዲዛይን ስንሰራ ንድፍ ስናወጣ ሕንጻውን የሚያስገነባ ሳይሆን በቃ ከእጃችን መገላገያ በሆነ ዋጋ ነው የምንሰራው። ስለዚህ የደረጁ የኪነ ሕንጻ ቢሮዎች የሉንም።
ትላልቅ 30 ዓመት የሰራና 2 አመት የሰሩ አርክቴክቶች ያሉበትን ቢሮ እይ። አብዛኞቹ ባዶ ቤቶች ናቸው። ብዙ አርክቴክቶችን ቀጥሮ በሰፊው እዚህ ሥራ ላይ ያለ ቢሮ የለም። ስለዚህ ባለሙያውን ይዞ ሊቆይ የሚችል ዘመን ተሻጋሪ ሥራ የሚሰራ ቢሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። እንግዲህ ይሄ ኪነ ሕንጻውን በተመለከተ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኪነ ሕንጻው ውስጥ አንዱ የተሻለ የከተማ ንድፍ መኖር ነው ሊያሰራ የሚችለው። እስቲ ስለ ከተማ ቦታ ንድፍ ወይም አርበን ዲዛይን ቢያስረዱን ? በእናንተ ሙያ የከተማ ንድፍ እንዴት ይታያል ?
አርክቴክት ዳዊት፡- ኪነ ሕንጻው እንደሞተ ሁሉ የከተማ ቦታ ንድፍም አብሮ ወድቆብናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሞች ቢኖሩም ከተሜነት የለም። ከተሜነት በባሕርይው ኪነ ሕንጻ በተፈጠረው በቁሳዊውም በባሕርይውም የለብንም። ይሄ እንግዲህ ከተለያዩ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል። አርበን ዲዛይን ወይንም ደግሞ የከተማ ንድፍ ስትል በዋነኛነት ምን መሰለህ ለሰዎች የሚመች፤ ለአዛውንቱ፤ ለወጣቶች፤ ለሕጻናት፤ ለሴቶች፤ ለሁሉም የሚመች መሆን ነው ያለበት።
ሴቶች እንደ ልባቸው ማንም ተደብቆ ሳያጠቃቸው የሚሄዱበት የከተማ ቦታዎች አሉን ወይ ? መብራት ያለበት ለሕጻናት መሻገሪያ ያለበት ቦታ አለን ወይ ? አዲስ አበባ ውስጥ ድንጋይና ጉድጓድ ያለበት ሳትሻገር፤ የተጣመመ ጎዳና ላይ ንግድ ሳይርመሰመስ 100 ሜትር የምትሄድበት ምቹ የእግረኛ መንገድ አለወይ ? ጉድጓድ ሳትዘል ወይንም እይታቸውን ያጡ ዜጎቻችን ደረታቸውን ነፍተው የሚሄዱበት ጎዳና አለወይ ? ብለህ መጠየቅ ትችላለህ ።
ሌላው ምን መሰለህ ኢኮኖሚ ሲያድግ የሰዎችም እድሜ እየጨመረ ይመጣል። ኢትዮጵያ ትልቁ ያስመዘገበችው ነገር ምንድነው ካልክ የሰዎች የእድሜ ጣሪያ (ላይፍ ኤክስፔክታንሲ) መጨመሩ ነው። ከአረጀህ በኋላ ሰው ትፈልጋለህ። ኢኮኖሚው ስለተንቀሳቀሰ አሁን ወጣት ዘመዶች ወይ እንደ ድሮው ከገጠር መጥታ አዛውንቱን የምትደግፍ አብራ የምትኖር ዘመድ የለችም ። ሽማግሌዎች አሁን በድብርትና በጭንቀት ሊጎዱ ይችላሉ። ሲያረጁ ወጥተው ከማን ጋር ነው የሚጫወቱት ? የት ነው የሚሄዱት ?
አዲስ ዘመን፡- አርበን ዲዛይን ለዚህ የሚሆን መልስ አለው ?
አርክቴክት ዳዊት፡– መልስ አለው። በየሰፈሩ ምን ታደርጋለህ መሰለህ ክፍት ቦታዎችን ታቋቁማለህ። ብርሀን ያለበት ሽማግሌዎች፤ ልጆች፤ አካል ጉዳተኞች የሚጫወቱበት ማለት ነው። ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት እንደ ጋሪ ፈረስ እየተሮጠ ያለው በአንድ አቅጣጫ ነው። መጠለያ መስራት፤ ጥሩ ይሄ ባልከፋ። ግን እነዛ መጠለያዎች ላይ ሶሻል ክራይስስ ወይንም ማሕበራዊ ቀውስ ይፈጠራል። ለዛ ማሕበራዊ ቀውስ አርበን ዲዛይን ወይንም የከተማ ንድፍ መፍትሄ አለው።
አዲስ ዘመን፡- ምን አይነት መፍትሄ ?
አርክቴክት ዳዊት፡- መፍትሄው ምን አይነት መሰለህ በየቦታው የታጠረ ቦታ ይተዋል። እነዚህን ቦታዎች የሚተውት ለሽማግሌዎቹ ከቤታቸው ወጥተው ቀስ ባለ ዳገት የሚያወሩበት የሚያወጉበት ማለት ነው። ከሆነ ዓመት በኋላ ከስትሮክ የተነሳ ፓራላይዝድ የመሆን ነገር ሊመጣ ይችላል። ካለህበት ወጥተህ ግን ሰው ማየት አለብህ። ሰው የሚደቀው ዲፕሬስድ ሲሆን ነው። አርበን ዲዛይን ለዚህ መፍትሄ አለው።
አርበን ዲዛይን እነዚህን የመሰሉ ማህበራዊ ቦታዎች ከማዘጋጀት በላይ እግረኛን ቢስክሌተኛን ያበረታታል። እስቲ በዚህ ጉዳይ በትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ባለድርሻ አካላትን ስትመለከት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ፤ የትራፊክ ማኔጅመንት አለ። ሁልቀን የሚያሳዩህ ማስታወቂያ የዚህ የዚህ አስፋልት ተከፈተ ነው። ይሄ የሚሆነው ለመኪና ማሳለጫ ነው።
ከተማ ለመኪና አይደለም የሚሰራው። ከተሞች በዋናነት የሚሰሩት ለመኪና ሳይሆን ለሰው ልጅ የተመቹ የሚመቹ እንዲሆኑ ተደርጎ ነው። አሁን እየተባለ ያለው መርህ ወይም ፕሪንሲፕል ምን መሰለህ ከተማው ለኑሮ ይመች (ላይቨብል) እና ለእግረኛ ተደራሽ ይሁን (ወከብል) ይሁን የሚል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በእናንተ ሙያ “ላይቨብል” እና “ወከብል” ትርጉሙ ምንድነው ?
አርክቴክት ዳዊት፡- ላይቨብል ለመኖር ያመቻል ነው። ከቤትህ ወጥተህ እዛው ሱቅ አለወይ ወይንስ መርካቶ ድረስ ሄደህ ነው ልብስህን የምትገዛው ? እዛው ያለህበት አካባቢ ሰው ታገኛለህ፤ ከጓደኞችህ ጋር ትሆናለህ ? ይመችሃል ወይ ? ወይንስ ቪድዮ ጌም ነው ቤትህ ውስጥ የምትጫወተው ? ወጣቱ እኮ ሥራ ፈታ ስንል የት ሄዶ ኳስ ይጫወታል ? የተለመደው ምንድነው ባዶ ቦታ ሲገኝ ኮንዶሚኒየም አሁንም ባዶ ቦታ ሲገኝ ኮንዶሚኒየም ባዶ ቦታ ሲገኝ ሕንጻ ነው የሚሰራው።
ብዙ ጥናቶች ተጠንተዋል። ላይቨብል ሲሆን ለእግረኛ ተደራሽነትን (ወከብል) ያበረታታል ወይ ? ሰፈርህ ሁነህ ተደስተህ መዋል ትችላለህ። የግድ ፓርክ መሄድ የለብህም ። እዛው አካባቢ ቁጭ ብለህ ከእድሜ እኩዮችህ ጋር ወጣ ብለህ ተዝናንተህ 24 ሰአት መብራት ያለበት ሆነህ ማሳለፍ ትችላለህ ማለት ነው።
ሌላው አረንጓዴ ስፍራዎች መኖር አለባቸው። አረንጓዴ ስፍራዎች ማለት አረንጓዴና ሰማያዊ ገጸ ምድር በመባል ይከፈላሉ። (ግሪን እና ብሉ ላንድስኬፕ) ይባላል። አረንጓዴው በዛፍ የተሸፈነ ሲሆን ሰማያዊው ደግሞ በውሀ የተሸፈነ ቦታ ያስፈልገናል ማለት ነው። ይሄ መሆን ያለበት በየወረዳው ነው።
ይሄ ለሕጻናቶች፤ ለሽማግሌዎች፤ ለአሮጊቶች ጭምር ማለት ነው። ሕጻናት በአንድ አንድ ሀገሮች እንደ ባለድርሻ አካል ተቆጥረው የሚያስቡትን በነፃነት እንዲናገሩ አመራር ቦርድ ውስጥ ሳይቀር ይገባሉ።
አሁን እኛ ለሕጻናት እናውቅላችኋለን እንላለን። የምናውቅላቸው ይመስልሀል። ግን አናውቅላቸውም። ራሳቸውን ማሳተፍ አለባቸው። ያ ሰፈር ለሴቶች ይመቻል ወይ ? ሴቶችን አሳትፈናቸዋል ወይ ? ይሄ ማለት ነው ከጾታዊ ጥቃት መከላከያ ማበጀት ማለት ።
አዲስ ዘመን፡- በሰፈር ውስጥ ከጾታዊ ጥቃት መከላከልን እንዴት ነው ማበጀት የምንችለው ?
አርክቴክት ዳዊት፡– ጨለማውን በመግፈፍ ሰፈሩን በብርሀን ትሞላዋለህ። ወንጀል የሚፈጸመው ጨለማን ተገን በማድረግ ነው። ብርሀን ሆነ ማለት ጥቃት ቀነሰ ወንጀል ቀነሰ ማለት ነው። ከዛም በንድፍ እይታን ታበዛለህ መሰወርያን እና መደበቂያን ትቀንሳለህ። እዛ ሰፈር ይሄን ታደርጋለህ። እንግዲህ አርበን ዲዛይን ለሰው ልጅ የተመቸ ሥራን መስራት ማለት ነው።
አሁን የምናየው ለመኪና የተመቸ ነገር ነው የሚሰራው። ይሄ ደግሞ የከተማ ዲዛይን ያልገባቸው መሐንዲሶች የሚያወሩት ነው። መሐንዲሶች ትልቁ ችግራቸው ቁጥርና ስታትስቲክስ ነው የሚያስቡት።
ከተማን የሚያስቡት ለመኪና ነው። በዚህ መንገድ አይሰራም። ከታወቁ ፕሮፌሰሮች ውስጥ በዚህ ጉዳይ ትልቅ ሥራ የሰራው ያን ጌል የሚባል ዴንማርካዊ አርክቴክትና ከተማ ዲዛይነር ነው። ያን ጌል ማለት ከተማ መጀመሪያ የሚሰራው ለሰው ነው፤ የተረፈው ለመኪና ነው የሚል ነው። እኛ ግን መኪናን ማእከል ያደረገ ከተማ ነው እየሰራን ነው ያለነው።
በቅርቡ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የሞተር አልባ እንቅስቃሴ ስትራቴጂ አዘጋጅቶአል። ወረቀት ላይ ነው ያለው። አሁንም ከተማ ተመረቀ፤ መንገድ ተከፈተ የሚለውን ዜና የእግረኛው መንገድ ሶስት ዓመት ሳይሰራ አስፋልት ሲመረቅ ያሳይሀል። ለእግረኛው መንገድ መሆን ባለበት ላይ ደግሞ የሚተከለው ዛፍ ግራቪልያ የሚባል ከአውስትራሊያ የመጣ ሀገር በቀል ያልሆነና ወፍ እንኳን ጎጆ ሊሰራበት የማይፈልገው ብዝሀ ህይወት የማይደግፍ ዛፍ ነው።
ስሩ ብዙ ርቀት የሚሄድና አስፋልቱን መንገዱን ጭምር ፈነቃቅሎ ታየዋለህ። ለምሳሌ ከመስቀል አደባባይ እስከ አቃቂ ቃሊቲ ድረስ ግራና ቀኝ የተተከሉት ግራቪልያ ዛፎች እንዴት አድርገው የሀገር ሀብት አባካኝ መሆናቸውን ታያለህ። ዛፉ ሲያድግ የእግረኛውን ንጣፍ ይፈነቃቅሉታል።
ያ ሁሉ የፈሰሰ የሀገር ሀብት ይጠፋል። በዛ ላይ መራመድ መንቀሳቀስ አትችልም። ይሄ እንግዲህ የከተማ ዲዛይን ነው። መጀመሪያ ለእግረኛ የሚመች ስንት እግረኛ ያንቀሳቅሳል ነው ጥያቄው። አሁን እኮ አዲስ አበባ እንዲሁ ከሌሎች ከተሞች ልምድ ብንማር ለብስክሌቶች መንገድ ቢታሰብላት ሰው በብስክሌት እስከ 5 ኪሎ ሜትር በደስታ እስከ ሥራው ድረስ ጠዋትና ማታ መመላለስ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ያን ለማድረግ የአዲስ አበባ የመሬት አቀማመጥ ይፈቅዳል ?
አርክቴክት ዳዊት፡- አዲስ አበባ ምስራቅና ምእራቡ ለዚህ ሁኔታ ይፈቅዳል። ሰሜን ደቡብ ነው የሚያዳግተው። እኔ ደግሞ ተራራማዋ ስዊዘርላንድ አይቼዋለሁ። ዳገቱንም ቢሆን ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ?
አርክቴክት ዳዊት፡- ዳገታማ ቦታዎችን የአህያ መንገድ እንደሚባለው ምስራቅ-ምእራብ ዚግ ዛግ እያደረጉ ይሰሩታል። አሁን ቸርችል መንገድ የተሰራው በስህተት ነው። ቸርችል ጎዳና ከስሙ ጀምሮ ለእኛ እንግዳ ነው። ቸርችል መንገድን እኮ መጥቶ የፈጠረው ኤል ዲ ማሪየን የተባለ ፈረንሳዊ አርክቴክት ነው። እዛ ፈረንሳይ ሀገር ሾንዜ ሊዜ የተባለ መንገድን ኮፒ አድርጎ የሰራብን ሥራ ነው እንጂ ከሰሜን ወደ ደቡብ መፈቀድም
አልነበረበትም። ወደታች ገደል ነው። ቁልቁለት ስትወርድ ከሰሜን ደቡብ ወንዝ የሚፈስበት በሙሉ ገደል ነው። ምን እያደረክ ነው መሄድ ያለብህ መሰለህ ምስራቅ ምእራብ ፤ምስራቅ ምእራብ እያደረክ ተዳፋት እየሰጠህ ነው መውረድ ያለብህ። ልክ እንደ አላማጣና ሊማሊሞ መኪና መንገድን ካየኸው ተራራውን ስትሄድበት ዚግ ዛግ እያደረክ ነው እንጂ በቀጥታ አይደለም።
ለሱም ዘዴ አለው። ትልቁ ችግር ምንድነው የከተማ ዲዛይንን በተመለከተ ቲንክ ታንክ ቡድን የለንም። ለሥራው የሚቀመጡት ባለሙያዎች ወይ አርክቴክቶች ወይ ከተማ ዲዛይነሮች አይደሉም። መሐንዲሶች ይሆናሉ። ይሄን ያህል መኪና እናሳልጣለን ነው የሚሉት።
የከተማ መንገድ ማብዛት ነው በከተማ ውስጥ ትልቁ አደጋ። በእኛ ሀገር የመኪና ባለቤትነትን ስታይ ቁጥሩ በጣም ታች የወረደ ነው። እኛ በብዛት የመኪና ተጠቃሚዎች አይደለንም። በአደጋው ደግሞ አንደኛ ነን። ይሄ ምን ያሳየናል ካልክ ባለችን መኪና እንኳን ከተሜነትን የምንቀርጽበት መንገድ የተሳሳተ ነው ማለት ነው። የከተማ ንድፍ መሰረታዊ ችግር አለ። በሌለን መኪና ይሄ ሁሉ አደጋ ከየት መጣ ነው ጥያቄው ?
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ ?
አርክቴክት ዳዊት፡– አንደኛው ለእግረኛ የሚመች ምንም ነገር የለንም። እግረኛው ራሱ እኮ የመኪና አስፋልት ላይ ነው የሚሄደው። እንቅፋት ሳይመታው ተመችቶት የሚሄድበት መንገድ የለም። እንደገና መንገዱ ሁሉ የንግድ ቦታ ሆኖአል። የሚያስደነግጥህ ነው። መንገድ እኮ ራሱን የቻለ የምትዝናናበት ቦታ ነው። የመንገዱን ዙሪያ ለአይን የሚስብ አረንጓዴ ማድረግ አለብህ።
ለብስክሌት ተጠቃሚዎች የሚሆን ቦታ መተው አለበት። የአርበን ዲዛይን አካል ነው። መሰራትም አለበት። መንገዶች ሲታቀዱ ለሁለት ለሶስት ለአራት መኪና ይባሉና ሌላ የሚታሰበው ሙሉ በሙሉ ሕንጻ መስራት ነው። ይሄ ደግሞ የመሐንዲሶች አስተሳሰብ ነው። መሐንዲስ በቃ በቁጥር ይለካና ይሄን ያህል መኪና ያስተላልፍልኛል ነው የሚለው። የመንገድ የትራንስፖርት ፕላኑ ላይ ትልቁ ችግር አዲስ መንገድ ስትከፍት መኪና እንደ ማግኔት ነው የሚስበው።
ለጎርፍ መንገድ ስትቀድለት እንዴት ነው ? ያ ሁሉ ተቸግሮ በሌላ ቦታ ይሄድ የነበረ መኪና ወደ አዲሱ መንገድ ይገባል። ልክ ስትከፍትለት የመኪና ባለቤትነትን ነው የምታበረታታው። መኪና መጨናነቅን ለመቀነስ መንገድ ማብዛት የሚለውን ትንታኔ ቦርጭን ለመቀነስ ቀበቶ ከማላላት የተለየ አይደለም ይሉሃል ባለሙያዎቹ።
የመኪና ባለቤትነትን ሳታበረታታ ሞተራይዝድ (መኪና) የሌለበትን ትራንስፖርትን ነው መደገፍ ያለብህ። አሁን አውሮፓ ብትሄድ መንገዶች እየተዘጉ የእግረኛ እየሆኑ ነው ያሉት።
በነገራችን ላይ አንድ የቤት መኪና በተወሰነ ፍጥነት ሲሄድ የሚወስደው ቦታ በጣም ብዙ ነው። በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር የሚሄድ መኪና የሚወስደው በእያንዳንዱ ሰከንድ ትልቅ ነው። በዛ ውስጥ ብዙ ብስክሌተኞችን በአንዴ ማንቀሳቀስ ትችላለህ። በብስክሌትና በእግር መሄድ ኢኮኖሚያዊም ነው።
ስለዚህ ጉዳይ የከተማ መሪዎቻችን ፕላን አቃጆቻችን የመንገድ ባለሙያዎች ግንዛቤው የላቸውም። ግንዛቤው ቢኖራቸውም በዚህ መልኩ እየተናገርን እና እየተቸን አያዛልቅም ። እንደ መፍትሄ መቀመጥ ያለበት የአርበን ዲዛይን (የከተማ ንድፍ) ቲንክ ታንክ መቋቋም አለበት። ልክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ቲንክ ታንክ እንዳቋቋሙት ማለት ነው። እንደዛው ሁሉ የከተማ ንድፍን የሚመለከት ቲንክ ታንክ ከሌለ አዲስ አበባ ከተማን ዘላቂ አድርገን አንቀጥለውም። አንችለውም።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ?
አርክቴክት ዳዊት፡– በቃ ሽማግሌውም ወጣቱም በየሰፈሩ በየኮንዶሚኒየሙ እየታሸገ እና እያረጀ ይቀራል። ወጥቶ የሚጫወትበት የሚዝናናበት የለውም። ወጣቶቹም በዛ በኮንዶሚኒየም ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታና ጥግግት ውስጥ የታሰበላቸውን መሆን አይችሉም። የወንጀል መፈልፈያና መቀፍቀፊያ ይሆናል።
ከድብርትና ከተለያዩ ማህበራዊ ጠንቆች የተነሳ የእጽ ተጠቃሚነት ከዛም ወደ ጌቶነት (ጌቶዋይዝድ) ወይም ለኑሮ የማይመች ድባብ ያለበት አካባቢና መኖሪያ ስፍራ ይሆናል ማለት ነው። ይሄ ትልቅ አደጋ ነው። እኛ አሁን መጀመሪያ ለእነዚህ ሰዎች ማደሪያ ብቻ ነው ያሰብነው። ከማደሪያነት ውጪ ደግሞ የሰው ልጅ ማሕበራዊ ትስስር የሚፈጥርበት፤ ልጆች የሚጫወቱበት፤ ወጣቶች የሚዝናኑበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል።
ባዶ ቦታ ሲገኝ ተሸቀዳድሞ ወዲያውኑ ጥቅም ላይ ማዋል ነው ያለው ትልቁ ችግር። ባዶ ቦታ ወይም ባዶነት ራሱ ጥቅም እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ሥራ የማትሰራበት እረፍት ቀን አለህ አይደል እንዴት ነው የሚጠቅምህ ? እሁድ እንዴት ነው የሚጠቅምህ አእምሮህን አካልህን የምታሳርፍበት ነው።
እንደዛ ውሰደው የባዶ ቦታ መኖር ጠቃሚነት። ያ ባዶ ቦታ በአካባቢው ላለ ሕብረተሰብ ለእረፍት፤ ለመዝናኛ፤ ለመገናኛ፤ ጊዜን በጋራ ለማሳለፊያ በመሆን ይጠቅማል። ጥቅሙ ከፍተኛ ነው። ምን አለፋህ ከተማ ንድፍ ወይም አርባን ዲዛይን ከአእምሮ ስነእውቀት ወይም ከኒውሮ ሳይንስ ጋር ተያይዞ ብዙ ምርምሮች ተሰርተውበታል። ለደህንነታችን ስንል ተገቢ ከተማ ንድፍ መስራት ይኖርብናል።
እኛ ግን መኪናን እና ህንጻን ማእከል ያደረገ ከተማ ነው እየሰራን ያለነው። አርበን ዲዛይን በየቦታው ማረፊያ ስፍራዎች ያስፈልጉታል። በየወረዳው ቢቻል በተወሰነ አጎራባች ሁሉ ባዶ ስፍራዎች ያስፈልጉናል። እነዛ ስፍራዎች መንፈስህን ሰውነትህን ያድሱታል። በተረፈ መንገዶቻችን ላይ ቸርችል ጎዳና እየተደረገ ያለው በየመንገዱ ግሪን ኤርያ (አረንጓዴ) ስፍራ መሰራት አለበት። መታሰብ አለበት። አጥሮች መፍረስ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በየመንገዱ ዳር የሚተከሉት ዛፎች እንደገለጹልኝ አስፋልቱን እንዳይሰነጥቁት ምን ይደረግ ?
አርክቴክት ዳዊት፡- በየመንገዱ ዳር የሚተከሉት ዛፎችም ሆኑ አትክልቶች ሀገር በቀል መሆን አለባቸው። በየመንገዱ ዳር የውጭ ዛፎች እየተከሉ ለማሳመር እያሉ ሳያውቁ የሚሰሩት ሥራ አርበን ዲዛይነር ስለሌለን ነው። ይኸውልህ ላንድ ስኬፕ ዲዛይነር የሚባል አለ። አዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ውስጥ ላንድ ስኬፕ ዲዛይነር የለም። እውነቱን እንነጋገር በቃ።
ስለዚህ ጉዳይ አውርተንም እንደ ባለድርሻ አካል ተጠርተውም አያውቁም። ተወው ራሱ ዩኒቨርሲቲው ስለ መንገድ ሥራዎች ግንባታና አሰራር ሲታሰብ እስቲ ምን ሀሳብ አላችሁ ? ምን ብናደርግ ጥሩ ነው ? የሚል ለሀገር በጋራ ከማሰብ ተማክሮ ከመስራት የመነጨ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጥ ለመነጋገር እንኳን ተጠርቶ አያውቅም። ይሄ በጣም ያሳዝናል።
አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም በር ላይ ከአስፋልቱ ዳር ያለውን ዛፍ ተመልክተው። ዛፉ ግራቪልያ ይባላል። እስቲ ወፍ ተሳስቶ እዚህ ዛፍ ላይ ጎጆ ቤት ሰርቶ ከነበረ ወይ ከሰራ ንገረኝ። አየህ መጤ ዛፍ ነው። ለዚህ ነው።
ለእኛ ሀገር እግዜር አልፈጠረውም። ከየትም አምጥተን እንተክላለን። ይሄን የሚያደርጉት ለምን መሰለህ ወዲያው አረንጓዴ ስለሚሆን ነው። ከውጭ ሀገር የመጣ እንደ ባሕርዛፍ አይነት ነው። ይህ ጸረ ስነምሕዳር የሆነ ዛፍ ነው። ብዝሀ ህይወትን ወይም ባዮ ዳይቨርሲቲን አይደግፍም።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎቹ ከተሞቻችን የአርበን ዲዛይን የከተማ ንድፍ የላቸውም ማለት ነው ?
አርክቴክት ዳዊት፡- ከተማ ናቸው። ግን ደግሞ ከሰው ባሕርይ ጋር ተዳምሮ ከተሜነት የለባቸውም። ሰው ከብት ያርድና አንገቱን የመንገዱ ትቦ ውስጥ ነው የሚከተው። ሰውስ በየቤቱ በግ ማረድ አለበት ወይ ? የእኔን እይታና ግንዛቤ ልንገርህ። እኔም የራሴን ሀሳብ የመስጠት መብት አለኝ። ከተሜነት ምንድነው ገጠሬነትስ የሚለውን እንይ። በገጠር ሁሉንም ነገር አንድ ሰው በቤቱ ይሰራዋል።
ግብርናውን፤ ምግብ ማዘጋጀቱን፤ ልብስ መፍተልና መሸመኑን፤ መጠጥ ማዘጋጀቱንም ወዘተ። እርሻውንም ምኑንም ምኑንም አንድ ሰው ይሰራዋል። አሁን ግን ልዩነት መኖር አለበት። ባሕልና እምነታችንን ጠብቀን ቢያንስ የሚታረደው ውጭ መሆን አለበት። በሰለጠነ አኗኗር እርድ መከናወን ያለበት ቄራ ነው። ታዲያ ጥቅጥቅ ብለህ እየኖርክ እንስሳ ቤትህ እያረድክ ፈርሱን ቤት እየደፋህ ፣ ከተማ በየበዓሉ የሚገባው ከብት አርደህ ጭንቅላቱን አንጀቱን ሰፈርህ እየጣልክ እንዴት ይሆናል ።
እስቲ አስበው በበዓል ሰሞን እንዴት ነው ከተማዋ የምትሸተው? ከየሱቁ የሚወጣው ቆሻሻ የሚደፋው የሚጠራቀመው በየቱቦው ነው። እዛው ነው። በየመንገዱ በአሳፋሪ ሁኔታ የተከፈተው ትናንሽ ሱቅ የምግብና ሌላውንም ቆሻሻ የሚደፋው በእነዛው ለመንገድ ውሃ ማስተላለፊያ በተሰሩት ትቦዎች ውስጥ ነው።
የተሰሩት የዝናብ የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎች የከተማዋንና የየመንገዱን ቆሻሻ ለማጠራቀሚያ ሳይሆን ከአስፋልቱ ከመንገዱ የሚፈሱትን ውሃ ወደታች አድርጎ እንዲያስተናግድ በዚያ እንዲተላለፉ ለማድረግ ብቻ ነው።
እነዚህ የተሰሩት ለስቶርም ወተር ወይንም ለዝናብ ውሀ የገጸ ምድር ውሀውን ማስተናገጃ ብቻ ነው። የታረደ የከብት ጭንቅላት የምግብ እጣቢ መድፊያ አይደሉም። ይሄ የከተሜነት ባሕርይ አይደለም።
ከገጠር ይዘን የመጣነውን ባሕርይ ነው እዚህ ትልቅ ከተማ ላይ የምናሳየው። ለመንገድ ውሀ ማስወገጃና ለወራጅ ውሀ መተላለፊያ ተብለው የተሰሩ ቱቦዎችን ከፍተህ እያቸው። ይሄን የምልህ አሁንም ይሄ የከተሜነት ባህርይ መገለጫ አለመሆኑን ለማሳየት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሕገወጥ በሆነ መንገድ በየመንግሥት መስሪያ ቤቱ ግምብ ላይ፤ በየኤምባሲዎች ግምብ ላይ፤ በየመንገዱ መተላ ለፍ እስኪያቅት ድረስ በየቀኑ እየተከፈቱ ያሉት የጎዳና ንግዶችና ሱቆች ከተማዋን አቆሽሸዋታል። ለመንገደኛም መተላለፊያ ቦታ እየጠፋ ነው። ከተማዋ እቅድ ፕላንና ንድፍ ያላት አትመስልም። አዲስ አበባ ወደ ትልቅ የገጠር መንደርነት እየተለወጠች ነው። ምን ይላሉ ?
አርክቴክት ዳዊት፤-– ይሄን የማህበራዊ ኢኮኖሚክ ችግር ለመፍታት መነጋገር አለብን። አሁን ይሄ ያልከው ችግር ቦሌ መንገድ ላይ የለም። ገጽታ እንደሚያበላሽ ይታወቃል። ከላይ ያነሳሀቸው ነገሮች የከተማን ገጽታ ያበላሻሉ። አብሮ መታየት ያለበት ለወጣቱ እንዴት የኢኮኖሚ መስኩን እንዘርጋለት የሚለው ነው። ከከተማው አንጻር ብዙ የተበላሸ ነገር አለ። መነጋገር አለብን።
አዲስ ዘመን፡- መፍትሄው ምንድነው ይላሉ ?
አርክቴክት ዳዊት፡– አርበን ዲዛይን ለዚህ ችግር መፍትሄ አለው። የከተማ ገጽታ ሳናጠፋ እንዴት አይነት ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ማምጣት እንዳለብን መወያየት መነጋገር ነው። የማህበራዊ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ሁሉ አሉ። ምን ለማለት ፈልጌ መሰለህ የማሕበራዊ ምጣኔ ሀብት ንግግርና ክርክር ያስፈልገናል ።
እንዴት ለነዚህ ሰዎች ከመንገድ ውጭ ንግድ እንክፈትላቸው የሚለውን ማውራት አለብን። አለበለዚያ አዲስ አበባ ብቻ አይደለም በመላው ኢትዮጵያ ከተሞች ስትሄድ የከተሞች መገለጫ የመንገድ ላይ ሱቅ ነው። ሰፊ ያልተሰራበት ሜዳ ካለ ተፈልጎ እነዚህን ሰዎች እዛ ላይ ማስፈር አለብን ነው የምለው።
አዲስ ዘመን፡- በየመንገዱ ዳር ያለው ገበያ የከተማዋን ውበትና ጽዳት አበላሸው። ፈቃጅ ቀበሌዎች ናቸው። አሁን ጭራሽ ብሶበታል። ሰው መነገድ የሚፈልገው ሕዝብ በብዛት ያለበት ቦታ ነው። የከተማ ፕላን መፍትሄ አለው ያሉትን ቢገልጹልን ?
አርክቴክት ዳዊት፡- ይሄም እኮ አደጋ አለው። ከተማውን ብታየው እኮ አሁን አዲስ ፋሽን ተጀምሯል። ዋና አስፋልት መንገድ ላይ ዘፈን እየዘፈኑ ካርቶን እያነቃነቁ ሕግ ባለበት ሀገር አስፋልት መሀል ላይ እየተለመነ ነው።
ትራፊክ ያያቸዋል። በአንድ አስፋልት ላይ ከሲኤምሲ እስከ መገናኛ ስትሄድ ሁለት ሶስት ቦታ ላይ መንገድ ተዘግቶ መለመን ምን ማለት ነው ? ስፒድ ብሬከር ናቸው ? ቢገጩ ማነው ጥፋተኛው ? ወደ እስር ቤት ነው የሚወስዱህ። ይሄ መነገርም መታረምም አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ከተማ አስተዳደሩ በዚህ መጠን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ሲበላሹ፤ በብዙ ቦታዎች ተመልሳ ወደ ትልቅ የገጠር ከተማነት ስትለወጥ ፤ ሕግና ስርአት ሲጣስ ይሄን የማረም እርምጃ የመውሰድ ግዴታ የለበትም ?
አርክቴክት ዳዊት፡– እኛ አናውቅም። የቲንክ ታንክ ቡድን ይቋቋም የምንለው ወጣቶቻችን አስፋልት ላይ ከሚበተኑ ይልቅ መፍትሄ አስቦ የመስጠት ግዴታ ስላለብን ነው። ምን መሰለህ አንድ ነገር ልንገርህ። ይሄ የንግግሬ ዋናው ነጥብ ሊሆን ይችላል። ችግሮቻችንን ቅደም ተከተል ሰጥተን እናስቀምጣቸውም። መሬት በሊዝ ከተሸጠ በኋላ ለወጣቶች ሳይታሰብ ይደረግና ወጣቶች የት ይሂዱ ሲባል መንገድ ላይ ይወጣሉ።
እንዴት እንደዚህ ይደረጋል? ለምን ለወጣቶቹ መጀመሪያውኑ አይታሰብበትም ነበር ? መንገድ መሬት እንደሚደለደለው ሁሉ ለምን ለእነሱስ ታስቦ በቅድሚያ አይደረግም። ልጅ ከወለድክ በኋላ አንተ በልተህ ጠጥተህ ሲተርፍህ ነው ይሄ ተርፎአል ብለህ ልጅህን የምታበላው ? ድሮ ሊሆን ይችላል።
አባት እናት እንግዳ ከበላ በኋላ ለልጅ የተረፈው ይሰጣል። ይሄ በድሮ ጊዜ ነው። እኔ ለልጄ ካበላሁ በኋላ ነው የምበላው። አንድ ዳቦ ቢኖረኝ ማን በልቶ ነው የሚያድረው ? አሁንም የከተማ ቦታ ለባለሀብት ከተቸበቸበ በኋላ ጨረታ ከወጣለት በኋላ አይሆንም።
የኢትዮጵያ ሕዝብን ስትመለከት 70 ፐርሰንቱ ከ30 ዓመት እድሜ በታች ያለ ወጣት ነው። ይሄንን ከ30 ዓመት እድሜ በታች ያለውን ችግር ሳትፈታ እንዴት ነው የሚሆነው ? ለምን ሕንጻ እንዲገነባላቸው አይታሰብም ? ይሄ እንግዲህ የእኔ ሀሳብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን።
አርክቴክት ዳዊት በንቲ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013