ሰላማዊት ውቤ
የእግረኛ መንገዶችን በበቂ ጥራትና ስፋት መገንባት የእግረኞች እንቅስቃሴን የተቃና ያደርጋል። ከመንገድ ጋር የተያያዙ የፍሳሽ መውረጃ ቱቦዎችን ማሳለጥም ለእግር መንገዶች ምቹነት ያለው ፋይዳ ጉልህ ነው። ዓይን አያየው የለምና ታዲያ ከነዚህ ጋር በተያያዘ በጎዳና ላይ ስንቀሳቀስ በከተማችን አዲስ አበባ ብዙ ችግሮች እናያለን፤ እንታዘባለንም፡፡
ከምናያቸውና ከምንታዘባቸው ችግሮች አንዳንዶቹ ደግሞ እርምጃችን አስተውሎትና ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን የሚጋብዙን ናቸው። ምን የሚጋብዙን ብቻ የሚያስገድዱንም ናቸው እንጂ። በተለይ ጉዳይ ኖሮን በችኮላ ተጣድፈን በምንጓዝበት ጊዜ የአሸዋው፣ የጠጠሩ፣ የብረታ ብረቱ፣ የድንጋዩ፣ የእንጨቱና የሌላ ሌላው የግንባታ ግብዓትና ቁሳቁስ በመንገዳችን ላይ ተጋርጦ እንደ ልብ አላላውስ ማለቱ ለመዲናችን አዲስ አበባ ነዋሪ አዲስ አይደለም። በእነዚህ እየተደነቃቀፈ በመውደቅ ጥርሱን የሚለቅመው፤ እጅ እግሩ እየተሰበረ የአካል ጉዳተኛ የሚሆነው፤ ልቡን ካንጠለጠለውና ለመድረስ ካሰበበትና ከጓጓበት ጉዳይ የሚስተጓጎለውን ቤት ይቁጠረው።
‹‹ ግንባታ እያካሄድን ነው፤ እንዲሁም አረንጓዴ ልማት አካል ነው›› በሚል ሰበብ የእግረኛ መንገዱን ከይዞታቸው ጋር ደባልቀው የሚያጥሩ፤ አትክልት የሚተክሉና የአትክልት ማስቀመጫቸውን ከአጥር ግቢያቸው አውጥተው በመንገድ ዳር በመኮልኮል ቦታ በሚያጣብቡና በሚይዙ፤ ግራና ቀኝ ግድግዳቸው ላይ እንዲሁም ከአናታቸው ላይ የሰቀሉት ሳያንሳቸው የእግር መንገዱ ላይ ትልቅ እይታን የሚጋርፍ የከተማውን ውበት የሚያጠፋ የንግድ ማስታወቂያ እየደነቀሩ መንገድ የሚዘጉ እና መተላለፊያ የሚያሳጡም መንገድ ዳር ያሉ ንግድ ቤቶች ባለቤቶችም በመዲናችን የትየለሌ ናቸው።
በነዚህ ምክንያት አስፋልት ውስጥ ገብቶ ሲጓዝ ለመኪና ግጭት አደጋ እንዲሁም በዚሁ ሰበብ ለአካል ጉዳትና ለሞት የሚዳረግ መንገደኛም ብዙ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ በመንገዳች ከዚህ የባሰ እንቅፋት ሊገጥመን የሚችል መሆኑ ነው። እግራችን የተከፈተ ቱቦ ውስጥ ሁሉ ዘው ብሎ ሊገባና ሊሰበር ይችላል ።
እግራችንን ብቻ ሳይሆን መላ ሰውነታችንን ሊሰለቅጥ የሚችል የተከፈተ የውሃ መውረጃ ቱቦ መኖሩን ያጫወቱን በዚሁ ጉዳይ ከከተማ ነዋሪዎች አስተያየት ስናሰባስብ ሳሪስ ታክሲ መያዣ አካባቢ ያገኘናቸው ወይዘሮ ዓለም ካሣ ናቸው። ወይዘሮ ዓለም እንደነገሩን ጊዜው ቆየት ቢልም ሰዓቱ ጠዋት የሥራ መግቢያ ወቅት ነበር።
ታድያ ከደቂቃዎች በፊት በቅርብ እርቀት አንዲት ወጣት ከፊት ለፊታቸው እየተጣደፈች ስትመጣ ያስተውላሉ። ልጅቱ ሽንቅጥ ያለች ለግላጋ አለባበሷ ያማረ አረማመዷም ቄንጠኛ ነበር። ታድያ ይህቺ ልጅ ድንገት ከዓይናቸው ትሰወራለች። በድንጋጤ እያማተቡ ባሉበት ደርቀው ይቆማሉ።
‹‹ድንገት ከዓይኔ ስትሰወር ደነገጥኩ። ምትሀትም መሰለችኝ›› ብለውታል አጋጣሚውን ሲገልፁልን ዕውነታው በህልም እንጂ በገሀዱ ዓለም የሚያዩት አልመሰላቸውም። ድንጋጤው ባይለቃቸውም ከቆሙበት ሳይንቀሳቀሱ የሞት ሞታቸውን ዓይናቸውን ከእሳቸው ፊት ለፊት በቅርብ እርቀት ወዳለው መሬት ወርወር ያደርጋሉ።
የተወረወረ ዓይናቸው የተከፈተ ሰፊ ቱቦ ላይ ይተከላል። በዚሁ ቅጽበት ከገቡበት ቅዠት መሰል እውነታ በመባነናቸው ምትሀት የመሰለቻቸው ልጅ እዚህ ቱቦ ውስጥ እንደገባች ይገለፅላቸውና በቆሙበት እሪታቸውን ያቀልጡታል። ድርጊቱ በዕለቱ የተፈፀመ ያህል ያንዘፈዝፋቸዋል።
ቱቦው ጥልቀት ያለው ነበርና ጩኽታቸውን ሰምቶ የተሰበሰበው ሕዝብ ልጅቱን በቀላሉ ሊረዳት አልቻለም። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሌሎች አካላት እስኪ ደርሱ ሕይወቷ እንደ ዘበት አለፈች። በስተኋላ በአካባቢው ያሉና በጫማ ጠረጋና በሱቅ በደረቴ ንግድ የተሰማሩ ታዳጊዎች ሲያወሩ እንደሰሙት የተከፈተው ቱቦ ማንኛውንም መንገደኛ ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ በካርቶን የተሸፈነ ነበር። ‹‹ቱቦው ይባስ ተብሎ በካርቶን ባይሸፈንና ክፍቱን ቢሆን ስለምታየው ልጅቱ ሕይወቷ አያልፍም ነበር›› ይሄን ዓይነቱን ኃላፊነት የጎደለው ተግባር የፈፀሙት ደግሞ በመንገዱ ዳር ያሉ ንግድ ቤት ነዋሪዎች ሽታውን ለመሸሽ እንደሆነም ገልፀውልናል። እኛም እንደታዘብነው በተለይ ምሽት ጨለማ በሚሆንበት ጊዜ የዚህ ዓይነቱ ቱቦ መዘዝ በእግረኛው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ብዙ ነው።
አቶ እስማኤል ከሪም እንደሰጡን አስተያየት አንዳንዴ በጠራራ ፀሐይ ለነጣቂና ዘራፊ ወንጀለኞች ሁሉ ዋሻ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ። የዛሬ ሁለት ወር ገደማ አራት ኪሎ አደባባዩ ጋር ያለው አስፋልት ዳር ካለው የተከፈተ ቱቦ ጋር ተያይዞ ያዩትም ዕውነታውን የሚያረጋግጥ ነው።
አቶ እስማኤል እንደነገሩን ሰዓቱ ቀትር ነበር። አንዱ ወንበዴ ታዲያ በእጅ ስልኳ እያወራች ማዶ ከሚታየው ከአባድር ሱፐር ማርኬት ተሻግራ ወደ አዲስ አበባ ተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ በመታጠፍ ላይ ያለች ወጣትን ስልክ ይነጥቃል። በአካባቢው ሰው እና ፖሊስ በብዛት ይዘዋወር ስለነበር የትም እንደማያመልጥ ያሰበው ነጣቂ ታድያ ዘሎ አደባባዩ አጠገብ መታጠፊያው ላይ ወዳለው የተከፈተ ቱቦ ይገባል፤ በመሆኑም ሊያዝ አልቻለም።
ከተማችን ውስጥ እንደዚህ ዓይነቶቹ በመንገድ ዳርና ዳር አንዳች ምልክት ያልተደረገባቸው፣ ለወራት ብሎም ለዓመታት ሳይከደኑ የሚቆዩ የፍሳሽ መውረጃ ቱቦዎች ሞልተዋል። እነዚህን ቱቦዎችና ቦዮች በተለይ ከተማ ላይ በበቂ ጥራትና መጠን መገንባት የፍሳሽ ፍስትን በማሳለጥ ረገድ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም። ሆኖም አብዛኞቹ ባለመከደናቸው በእግረኛ ላይ በሚያደርሱት መሰናክልና በአካባቢው በሚፈጥሩት መጥፎ ጠረን አገልግሎታቸው የተገላቢጦሽ እየሆነ ነው።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን ችግሮቹ በመዲናችን አዲስ አበባ መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር መሆኑን ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉት መሥሪያ ቤቱ መንገድ ይጠግናል፣ ይገነባል፣ የመንገድ ሀብትን ያስተዳድራል። ሆኖም ከማስተዳደሩ ጋር ያለው ጉዳይ ሕግን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሙታል።
ፈተናዎቹ መንገድ የትራፊክና አጠቃላይ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥና ለማሳደግ እንዲውል የመገንባቱን ዓላማ የሚጥሱ ናቸው። እንደ አቶ እያሱ መንገድ የሚሰራው የትራፊክ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥ እና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴውን ለማሳደግም ነው። ሆኖም በከተማችን በአንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎችና በተለያዩ አካላት ከታለመለት ዓላማ ውጭ ለማዋል የሚደረግ እንቅስቃሴ መኖሩንም ይገልፃሉ።
በከተማችን መንገድ እስከ ማጠር ድረስ የሚሄዱ ሕገ ወጥ ተግባራት ይከናወናሉ። የግንባታ ቁሳቁሶችን የማስቀመጥና መንገድ ዘግቶ መተላለፊያ የማሳጣት ድርጊቶች ይፈፀማሉ። ባለሥልጣኑ በጎዳና ላይ ለሥራ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ብዙ ችግሮችን ያስተውላል። የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን ከድኖ ብዙ ርቀት ሳይሄድ በተለያዩ
የሕብረተሰብ አካላት የመከፈት፣ የማበላሸት ተግባር ሲከናወን ማየታቸውን ያስታውሳሉ። በተለያዩ አካላትና የሕብረተሰብ ክፍሎች የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች ቱቦዎች የሚዘጉበት አጋጣሚ ብዙ ነው። እነኝህን መስመሮች ከመፀዳጃና ከሌላ የፍሳሽ መስመር ጋር የማገናኘት ችግርም መኖሩን ይናገራሉ ።
‹‹የመንገድ ዳር የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች የተፈጥሮ የዝናብ ውሃን ተቀብለው ለማስተላለፍ የተዘረጉ መስመሮች ናቸው›› የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ እያሱ ሆኖም እነዚህ መስመሮች በተለያየ መንገድ ላልተገባ ተግባር የሚውሉባቸው ጊዜያት መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
ለምሳሌ፦ አብዛኞቹ በከተማ መንገድ ዳር የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ከፍሳሽ መስመር ጋር የመፀዳጃ መስመሮችን እንዲሁም ሌሎች መስመሮችን የሚያገናኙበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ። ይሄ ደግሞ ለሌላው የከተማዋ ነዋሪ የሕብረተሰብ ክፍል እጅግ ከፍተኛ የጤና ችግር የሚሆንበት ሁኔታ አለ።
የፍሳሽ ማስተላለፊያው ያለው የውሃ መስመር መዳረሻ ያለበት አካባቢ ከሆነ ደግሞ የሚያስከትለው የጤና ችግር እጅግ የከፋ ነው የሚሆነው። ነገር ግን ይሄ በሕብረተሰቡ ዘንድ እየታወቀ በተጨባጭም ችግር ሲያደርስ እየታየ የውሃ መስመር የሚያልፍባቸው ጉድጓዶች (ቀዳዳዎቸ) በየጊዜው ሲደፈኑ ይስተዋላሉ። አንዳንዶች የፍሳሽ መተላለፊያ መስመሮችን የሚደፍኑት ሽታ አመጣብን በሚል ምክንያት ነው። እነዚህ
በሚደፈኑበት ወቅት ደግሞ በተለይ በክረምት አስፋልት ላይ ውሃ የሚተኛበት ሁኔታ ይከሰታል። ይሄ ሁኔታ በበጋ ወቅት ሳይቀር ይስተዋላል። የመፀዳጃ ሌሎች ፍሳሾች ከፍሳሽ መስመሩ ገንፍሎ ይወጣል። ለዚህ መስመር ብልሽትም ምክንያት የሚሆኑባቸው አሉ።
አሁን ላይ እንደ ተቋም በባለሥልጣኑ የፍሳሽ ቱቦዎችን የመክደን፣ ክዳኑን የመሥራት፣ የማፅዳት፣ የመጠበቅና የመቆጣጠር ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለምሳሌ በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ ስድስት ወራት 303 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች ጽዳትና ጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል። በሥራው ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ፈስሷል።
ሆኖም የጋራ ሀብት የሆነውን በጋራ መጠበቅ ሲገባ በአንድ በኩል ሲሠራ በሌላ በኩል ይፈርሳል። ይሄ በህብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ የአስተሳሰብ ክፍተት ያለበት ነው። ደንብ አስከባሪ ፖሊስን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል። እነዚህ አካላት የየድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
መንገድ ሲበላሽ፣ ቱቦዎች ተከፍተው አደጋዎች ሲፈጥሩ ሕብረተሰቡ መጠየቅ አለበት። መሥሪያ ቤቱ ሃሳቡን ወይም ጥቆማውን ተቀብሎ ለማስተካከል ዝግጁ ነው። እኛም ህብረተሰቡ ከባለሥልጣኑ ጋር መተሳሰብ፣ መተጋገዝ፣ የጋራ ሀብትን በጋራ መጠበቅ ባህሉ ማድረግ አለበት በማለት ጽሁፋችንን ቋጨን።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2013