ተገኝ ብሩ
አንዳንድ አባባሎች ያለ ዘመናቸው ዋጋ የላቸውም። ቦታና እውነታን ያላገናዘቡ ሆነው ይገኛሉ። ዛሬ ላይ ትናንት ሲባል የነበረው «ዝምታ ወርቅ ነው » አይሰራም። በዝምታችን የተነጠቅነው ባለማውራታችን ያጣነው በርክቷልና። መናገር ሲገባቸው ዝም ያሉ፤ ሀሳባቸውን ባለመግለፃቸው ሀገርን የጎዱ ሰዎችን ዛሬ በመርፌያችን ወጋ ወጋ እያደረግን ዝምታቸውን እንዲሰብሩ እንነግራለን።
ጎበዝ በዝምታችን እውነት እየተቀበረ ነው። በእኛ ለዘብተኝነት ዛሬ ላይ የውሸት ነጋዴዎች ጩኸት ገኗል። ስለዚህ «ዝምታ ወርቅ ነው» ተሽሯል። አዎን ይህቺ ታላቅ አገር በትንንሽ አሳቢዎች ጩኸት በእኛ መሰሎቹ ዝም ማለት ልትፈተን አይገባም። ዓለም ላይ የውሸት መላዕክተኞች የዚችን አገር ሰላም ለመንሳት ከመቼው ጊዜ በላይ አብረው እየሰሩ ነው። ሰላሟን ለማወክ፤ ሕዝቦቿን ለመነጣጠል እውነትን ለመቅበር በመታተር ላይ ይገኛሉ።
ፍቅር ፀጥ ማለትን ካዘወተረ ጥላቻ ቦታውን ወርሶ ይገናል። በዝምታ ምክንያት እውነትን የያዙ ብዙሀን ሀሰት በያዙ ጥቂቶች ይዋጣሉ። ዛሬ የበጎዎች ዝምታ አገራችንን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል። ብዙ የፍቅርና የአንድነት ድምፆች ዝም በማለታቸው፣ ለነሱ የጥላቻና የልዩነት ድምፆች መጉላት ምክንያት ሆነዋል። በጎዎች ምንም ያህል ቁጥራቸው ከፍ ቢል የጥቂት ክፉዎች ኮቴ ገዝፎ ተደምጧል።
እርግጥም ለምናየውና ለምንሰማው እኩይ ተግባር የእኛ ምላሽ ዝምታ መሆኑ ያሳስባል። እውነትን በጊዜው እውነት ካላሉት ሲያድር የውሸት ያህል አገርና ሕዝብ ይጎዳል። ትክክል መስሎ የታየንን ጉዳይ ትክክል ነው፣ ይቀጥል ማለት እንዲሁም የተሳሳተውን ደግሞ ስንመለከት አይ ይህ ለአገርም ለሕዝብም በጎ አይደለምና ሊገታ ይገባዋል ማለት እንዴት ተሳነን። እውነት ባልነውና ባመንበት ጉዳይ ዝም ብንል እውነቱ መቀበሩ ሀቁ መቀፍደዱ አይቀርም። እርግጥ ክፉ ነገርን የሚሰብኩ መልካም ያልሆነን የሚያሰርፁ ቁጥራቸው በዝቶ አይደለም። ይልቁንም የሰላም አምባሳደሮች ዝምታ ያነሱትን የጥላቻ ዘቦች የበዙ አስመሰላቸው እንጂ።
ወገን ስለ አገር መፅናት ማውራት ፍቅርና አንድነት መስበክ ለምን ተውን። ቢያንስ ጥላቻን የሚሰብኩትን፣ መለያየትን የሚነዙትን ያህል መጮህ እንዴት አቃተን። እነሱ ስለ ክፉ ተግባር ደጋግመው ሲያወሩ እየሰማን እኛ ስለፍቅር መስበክ ለምን ተሳነን? የራሳችን ጉዳይ ላይ እኛው ዝም ጭጭ ማለታችን ለምን ይሆን?
የምንሰማውና የምናየው ግራ እስኪገባን ድረስ ከጫፍ ደርሶ የኛ ለዘብተኛ መሆን አሳስቦኛል። ፍቅርን ማንገስ ሰላምን መስበክ ላይ መስነፋችን ነጋችንን በመጥፎ ገፅታው እንድናስበው እያደረገን ይገኛል። ዘመን ፍቅርን የጠላ መዋደድ የሰለቸው ይመስል መነጣጠል ላይ ዘምቷል። ለምን እኛ በዝምታችን የተጠላውን ጥላቻ እንዲቀርብ ፈቀድንለት።
ዛሬ ዝም ማለታችን ስለ ፍቅር መለዘባችን ትውልድ አገር ከመስፋት ይልቅ መቅደድ የተሻለ መስሎ ታይቶቷል። ሀገር ከማነፅ ይልቅ አገር ማፍረስን ያለ ምክንያት ተላምዶታል። መቅደድ የመስፋትን ያህል ስላልከበደ፤ መስፋትን የመቅደድን ያህል ስላልቀለለ የቀለለው ላይ ተዘምቷል። ፍሬ የሚታየው በዘሩት ልክ ነው። ፍቅር ካስተማሩት ፍቅርን ጥላቻ ከሰበኩት ክፋትን ማግኘት አይከብድም።
ዛሬ እንደ አገር ፍቅርን የሚያፀና አንድነትን የሚሰብክ መዋደድን የሚያውጅ ተወዷል፤ ሰላምን የሚሰብክ ቅዳጁን የሚሰፋ የሚያፋቅር ተናፍቋል። ሀገርን ከሚነጣጥሉ፤ አገርን ከሚያፈርሱ አንድነትን ከሚንዱት በላይ መትጋት ይገባናል። ፍቅርን እንስበክ፣ አንድነትን እናፅና፣ ጥላቻ ሲሰበክ ዝም ማለታችንን እንተው። በጎነትን ከፍ አድርገን እንንገር፤ ፍቅርን አጉልተን እንስበክ። ስለ እውነት መናገር ዝም ማለታችን ይብቃ።
ስለ እውነት ባለማውራታችን ስለ አንድነት ባለመናገራችን ከአንድነት ይልቅ መነጠል የተሻለ መስሎ ገዝፏል። በዝምታችን ምክንያት ስህተታችን ገዝፏል። እውነት ማለዘቡን እናቁም። በጥላቻ ሰክረው ያለዘቡትን አንድነታችን በእውነትና ፍቅር ለውጠን አገራችንን እናፅና።
የጋራ የሆነ ውብ እሴታችንን መሸርሸር ያበዛነው መልሰን አሳምረን ልናበጀው አስበን ይሆን እንዴ? ግን አይመስልም። የውሸታሞች ተግቶ ሀሰት የመንዛትን ያህል እኛ ዝም ብለናል።
ዝም ማለት ዋጋ ያስከፍላል፤ አያስከፈለንም ነው። የያዙት እውነት መልካምነት ከተፃረሩት ውሸት ቢገዝፍም፤ እውነቱ የሚዋጥበት አጋጣሚ ብዙ ነው። እርግጥ መልካም ነገሮች መገኛቸው ይርቃል። እውነት መናገር ዋጋ ቢያስከፍል እንኳ መልካም ውጤት አለው። በማህበረሰብም ያስነግሳል። እውነት ላይ የቆመ ሁሉም ያከብረዋል፤ ያ ነው እሴታችንና በጎው ልምዳችን።
እነዚያ ጥሩ ትሩፋቶች በወቅቱ ካልተጠቀምንባቸው ምንም ናቸው። በማይገባ መልኩ ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉ። ስለ ፍቅር ዝም ካሉት ይልቅ ስለ ጥላቻ የተነፈሱት ድምፅ ጎልቷል። ብዙዎች ዝም ካሉ ያነሱ ጩኸቶች ይገዝፋሉ። እርግጥ ዝም ያለ ውሀ ጥልቀት አለው። እሙን ነው፤ ነገር ግን ድምፁ ጎልቶ የሚሰማው የሚንፋፋ ውሀ ነው። ጥላቻን የሚሰብክ አንድነትን የሚንድ ውሸት አዋጅ በዝቷል። ይህ ልክ አይደለም፤ እውነቱ ይሄ ነው ብሎ በጎን የሚያመላክት ደግሞ ቁጥሩ አንሷል።
የተያያዝነውን ዝምታ ሰብረን፤ አንድነትን የሚያፀና ፍቅርን መስበክ እናዘውትር። ለትውልዱ ፍቅርን እናውርስ። ውዶቼ በጥላቻ አገር እንቅደድ ከሚሉት በላይ ጮኸን በፍቅር አገር እንስፋ፤ አገር እንገንባ ማህበረሰብ እናድን፤ ስለ ፍቅር ዝም ማለት እናቁም። ሰፊነት እኮ እርባናው ከፍ ይላል። የመቅደድ በጎነት ያለው ስፌትን ለመጠገን ሲያስቡ በጎደለ ለመሙላት ሲያስቡ ነው። ውዶቼ ከጉድለት ላይ መቀነስ እኮ ነው ክፉው መቅደድ።
በዝምታችን የምናጣው ፍቅር ባለመናገራችን የምንነጠቀው ሰላም ነው። ጥቂቶች ጥላቻን በአደባባይ ሲያውጁ እያየን እኛ ግን ስለ ፍቅርና አንድነት መተንፈስ ተሳነን። እንዴት ግን ጥላቻ ሰባኪው ከፍቅር አንጋሹ በጩኸት ያይላል? የጥላቻ ሰባኪውን ያህል ፍቅር አንጋሹን ብናበዛ የሚያበላሸውን ያህል አልሚው ቢበረክት ዛሬ የምናየው በጥባጭ ጎልቶ ይሰማ ነበር? በፍፁም። እንዲያውም ስለፍቅርና አንድነት በትንሹ ቢጮህ ከጥላቻ ገዝፎ ይሰማል።
ግን ደግሞ ፍቅር ለጥላቻ ቦታ ለቆ ጥላቻ የቀደደውን በመስፋት ጊዜውን ይፈጃል። ጥላቻ ሀይ ባይ አጥቶ ተሰፍቶ የቆየውን ሀገር ካልቀደድኩ ብሎ አደባባይ ላይ ዘራፍ ማለትን ተላምዷል። የፍቅር ሰባኪው ሚና ያልጎላበት ዋንኛ ምክንያት ይሄ ነው። የብዙ እውነተኞች ዝም ማለት ጥቂት ውሸታሞችን አገነነ።
እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነን በፍቅር ተሳስረን ዘመናትን ተሻግረናል። አንድነትን በመስበክ መዋደድን ማፅናት ችለንበትም ቆይተናል። ዛሬም የፍቅር ዝማሬያችንን ከፍ አድርገን ያለዘብነውን ድምፃችንን አጉልተን ሰላምን እንዘምር፤ ሰላም መሆንን እንስበክ፤ ያኔ እውነት ነግሶ ሀሰት ይከስማል።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2013